በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 13

“የጦፈ ክርክር” ተነሳ

“የጦፈ ክርክር” ተነሳ

ግርዘትን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ ለበላይ አካሉ ቀረበ

በሐዋርያት ሥራ 15:1-12 ላይ የተመሠረተ

1-3. (ሀ) በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ላይ የመከፋፈል አደጋ እንዲያጠላ የሚያደርግ ምን ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር? (ለ) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ይህን ዘገባ መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

 ጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዟቸውን ጨርሰው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ መመለሳቸው ነው። ይሖዋ “ለአሕዛብ የእምነትን በር [ስለከፈተላቸው]” እጅግ ተደስተዋል። (ሥራ 14:26, 27) ምሥራቹ በአንጾኪያም በሚገባ እየተሰበከ ነው፤ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው” አሕዛብም ጉባኤውን እየተቀላቀሉ ነው።—ሥራ 11:20-26

2 ይህ አስደናቂ ጭማሪ መገኘቱን የሚገልጸው ዜና ብዙም ሳይቆይ ይሁዳ ደረሰ። በዜናው የተደሰቱት ግን ሁሉም አልነበሩም፤ እንዲያውም ይህን ሪፖርት ተከትሎ ቀድሞም ሲያወዛግብ የነበረው የግርዘት ጉዳይ ይበልጥ ተጧጧፈ። አይሁዳውያን በሆኑና አይሁዳውያን ባልሆኑ ክርስቲያኖች መካከል ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖር ይገባል? አይሁዳውያን ያልሆኑ ክርስቲያኖችስ የሙሴን ሕግ እንዴት ሊመለከቱት ይገባል? ይህ ጉዳይ የጦፈ ክርክር አስነሳ፤ የክርስቲያን ጉባኤን ሊከፋፍል የሚችል አደጋ እያጠላ ነበር። ታዲያ ጉዳዩ እልባት የሚያገኘው እንዴት ይሆን?

3 በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ይህን ዘገባ ስንመረምር ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች እናገኛለን። በዛሬው ጊዜ የጉባኤውን አንድነት ስጋት ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥም ልንወስደው የሚገባውን የጥበብ እርምጃ ያስገነዝበናል።

“ካልተገረዛችሁ በቀር” (የሐዋርያት ሥራ 15:1)

4. አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን የተሳሳተ አመለካከት ያራምዱ ነበር? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

4 ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው ‘በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ በቀር ልትድኑ አትችሉም’ እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ጀመር።” (ሥራ 15:1) ‘ከይሁዳ የመጡት’ እነዚህ ሰዎች ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ፈሪሳውያን ነበሩ? የምናውቀው ነገር የለም። አንድ የምንረዳው ነገር ግን አለ፤ ይኸውም ሕጉን ሙጭጭ አድርጎ የሚይዘው የፈሪሳውያን ኑፋቄ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ በኢየሩሳሌም ያሉትን ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወክለው እንደሚናገሩ አድርገው ሳይቀርቡ አልቀሩም። (ሥራ 15:23, 24) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከአምላክ ባገኘው መመሪያ መሠረት ያልተገረዙ አሕዛብ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እንዲቀላቀሉ ካደረገ 13 ዓመታት ገደማ አልፈዋል፤ ታዲያ እነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሁንም ስለ ግርዘት ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱት ለምንድን ነው? aሥራ 10:24-29, 44-48

5, 6. (ሀ) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ግርዘትን የሙጥኝ ያሉት ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የግርዘት ቃል ኪዳን የአብርሃም ቃል ኪዳን ክፍል ነበር? አብራራ። (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

5 ይህ ሊሆን የቻለባቸው ብዙ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። አንዱ ምክንያት ይህ ነው፦ የግርዘትን ሥርዓት ያቋቋመው ይሖዋ ራሱ ነው፤ ግርዘት፣ አንድ ሰው ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና እንዳለው የሚያሳይ ምልክት ሆኖም ያገለግል ነበር። የግርዘት ሥርዓት የተጀመረው በአብርሃምና በቤተሰቡ ነበር፤ ከሕጉ ቃል ኪዳን በፊት የተቋቋመ ቢሆንም በኋላ ላይ የሕጉ ቃል ኪዳን ክፍል ሆነ። b (ዘሌ. 12:2, 3) በሙሴ ሕግ ሥር፣ የባዕድ አገር ሰዎችም እንኳ አንዳንድ መብቶች ለማግኘት መገረዝ ነበረባቸው፤ ለምሳሌ፣ ከፋሲካው ምግብ መብላት የሚችሉት ከተገረዙ ብቻ ነው። (ዘፀ. 12:43, 44, 48, 49) አዎ፣ ያልተገረዘ ሰው ለአንድ አይሁዳዊ ርኩስ ነበር፤ አምላክን ለማገልገል የሚያስችል አቋም እንዳለው አድርጎ አይቆጥረውም።—ኢሳ. 52:1

6 በመሆኑም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ የተደረገውን አዲስ ማስተካከያ መቀበል እምነትና ትሕትና ጠይቆባቸዋል። ምክንያቱም አሁን የሕጉ ቃል ኪዳን በአዲሱ ቃል ኪዳን ተተክቷል፤ ስለሆነም አንድ ሰው ከአይሁድ ወገን መወለዱ ብቻ በቀጥታ የአምላክ ሕዝብ ክፍል አያደርገውም። ለብዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ ስለ ክርስቶስ መመሥከርና ያልተገረዙ አሕዛብን የእምነት ባልንጀሮች አድርጎ መቀበል ድፍረት የሚጠይቅ ነገርም ነበር፤ ምክንያቱም በይሁዳ ያሉትን ጨምሮ ብዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሚኖሩት በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው።—ኤር. 31:31-33፤ ሉቃስ 22:20

7. ‘ከይሁዳ የመጡት ሰዎች’ ያልተረዱት እውነት የትኛው ነው?

7 እርግጥ ነው፣ የአምላክ መሥፈርት አልተለወጠም። አዲሱ ቃል ኪዳን የሙሴን ሕግ መንፈስ የሚያንጸባርቅ መሆኑ በራሱ ይህን ያረጋግጣል። (ማቴ. 22:36-40) ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ በኋላ ላይ ግርዘትን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በውስጡ አይሁዳዊ የሆነ እሱ አይሁዳዊ ነው፤ ግርዘቱም በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በመንፈስ የሆነ የልብ ግርዘት ነው።” (ሮም 2:29፤ ዘዳ. 10:16) ‘ከይሁዳ የመጡት አንዳንድ ሰዎች’ ይህን እውነት አልተረዱትም፤ አምላክ የግርዘትን ሕግ ፈጽሞ አልሻረውም ብለው ይከራከሩ ነበር። ታዲያ የሚቀርብላቸውን ማስረጃ ይቀበሉ ይሆን?

“ክርክርና ጭቅጭቅ” (የሐዋርያት ሥራ 15:2)

8. ግርዘትን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ ኢየሩሳሌም ለሚገኘው የበላይ አካል እንዲቀርብ የተደረገው ለምንድን ነው?

8 ሉቃስ እንዲህ በማለት ዘገባውን ይቀጥላል፦ “ጳውሎስና በርናባስ ከሰዎቹ [‘ከይሁዳ ከመጡት’ ሰዎች] ጋር የጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ጉዳዩን በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።” c (ሥራ 15:2) “ክርክርና ጭቅጭቅ” የሚለው አገላለጽ እንደሚጠቁመው በሁለቱም ወገን ያሉት ክርስቲያኖች ሐሳባቸውን ለመቀየር ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የአንጾኪያ ጉባኤም ጉዳዩን ሊፈታው አልቻለም። ጉባኤው ለሰላምና ለአንድነት ሲባል፣ ጥያቄው ኢየሩሳሌም ለሚገኙት “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች” ማለትም ለበላይ አካሉ እንዲቀርብ ወሰነ። ታዲያ በአንጾኪያ ከሚገኙት ሽማግሌዎች ምን እንማራለን?

“[አሕዛብ] የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ አስፈላጊ ነው” በማለት አንዳንዶች ተከራከሩ

9, 10. በአንጾኪያ የነበሩት ወንድሞችም ሆኑ ጳውሎስና በርናባስ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑን በምን መንገድ ነው?

9 ከዚህ የምናገኘው አንዱ ጠቃሚ ትምህርት በአምላክ ድርጅት ላይ እምነት መጣል እንዳለብን ነው። እስቲ አስበው፦ የአንጾኪያ ወንድሞች፣ የበላይ አካሉ አይሁዳዊ ከሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ የተውጣጣ መሆኑን ያውቃሉ። ያም ሆኖ ግርዘትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር በሚስማማ መንገድ እልባት እንደሚያበጅለት እርግጠኞች ነበሩ። ለምን? ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱና የክርስቲያን ጉባኤ ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነገሮችን እንደሚከታተል እምነት ነበራቸው። (ማቴ. 28:18, 20፤ ኤፌ. 1:22, 23) ዛሬም አንዳንድ ከበድ ያሉ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜ የአንጾኪያ ክርስቲያኖች የተዉትን ግሩም ምሳሌ እንከተል፤ በአምላክ ድርጅትና ቅቡዓን ወንድሞችን ባቀፈው የበላይ አካል ላይ እምነት ይኑረን።

10 በተጨማሪም ትሑትና ትዕግሥተኛ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንማራለን። ጳውሎስና በርናባስ ወደ አሕዛብ እንዲሄዱ በቀጥታ በመንፈስ ቅዱስ ተሹመዋል፤ ሆኖም ይህን ሥልጣናቸውን በመጠቀም ግርዘትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ እዚያው አንጾኪያ ውስጥ ለመፍታት አልሞከሩም። (ሥራ 13:2, 3) እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ “ወደ ኢየሩሳሌም . . . የሄድኩት በተገለጠልኝ ራእይ መሠረት ነበር” ብሎ ጽፏል፤ ይህም በጉዳዩ ላይ የአምላክ አመራር እንደነበረበት ይጠቁማል። (ገላ. 2:2) ዛሬ ያሉ ሽማግሌዎችም ጉባኤውን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ጥያቄዎች በሚነሱበት ጊዜ ጉዳዩን በትሕትናና በትዕግሥት ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ። እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለው ድርቅ ከማለት ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን ይመረምራሉ፤ እንዲሁም ታማኙ ባሪያ ያወጣቸውን መመሪያዎች በመመልከት የይሖዋን አመራር ይከተላሉ።—ፊልጵ. 2:2, 3

11, 12. ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 አንዳንድ ጊዜ፣ ይሖዋ አንድን ጉዳይ በተመለከተ የእውቀት ብርሃን እስኪፈነጥቅ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። ይሖዋ ‘ከአሕዛብ ወገን የመጡት ክርስቲያኖች መገረዝ አለባቸው ወይስ የለባቸውም?’ ለሚለው ጉዳይ እልባት የሰጠው ከጊዜ በኋላ ይኸውም በ49 ዓ.ም. እንደሆነ አስታውስ፤ ወንድሞች፣ ቆርኔሌዎስ በመንፈስ ከተቀባበት ከ36 ዓ.ም. አንስቶ እስከ 49 ዓ.ም. ድረስ ለ13 ዓመታት ገደማ በትዕግሥት መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። ለመሆኑ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደው ለምንድን ነው? ይህ ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች ትልቅ ለውጥ እንደሆነ አስታውስ፤ በመሆኑም አምላክ አመለካከታቸውን የሚያስተካክሉበት በቂ ጊዜ ሊሰጣቸው ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ከሚወዱት ቅድመ አያታቸው ከአብርሃም ጋር የተገባው የግርዘት ቃል ኪዳን 1,900 ዓመታት ያስቆጠረ ነው፤ አሁን እንዲፈርስ መደረጉ በቀላሉ የሚቀበሉት ጉዳይ አልነበረም!—ዮሐ. 16:12

12 ትዕግሥተኛና ደግ በሆነው በሰማዩ አባታችን መመራትና መቀረጽ መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እሱ እንዲመራንና እንዲቀርጸን የምንፈቅድ ከሆነ ውጤቱ ምንጊዜም መልካምና ለእኛ የሚበጅ ይሆናል። (ኢሳ. 48:17, 18፤ 64:8) እንግዲያው የእኛ አመለካከት ብቻ ትክክል እንደሆነ በማሰብ ድርቅ ማለት አይኖርብንም፤ ደግሞም ድርጅታዊ ለውጦች ሲኖሩም ሆነ በአንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያዎች ላይ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ተቺዎች መሆን የለብንም። (መክ. 7:8) እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ በትንሹም እንኳ በውስጥህ እንዳለ ከተሰማህ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ ባሉት ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ አሰላስል፤ ትምህርቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲረዳህም ይሖዋን ለምነው። d

13. በአገልግሎታችን ላይ የይሖዋን ትዕግሥት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜም ትዕግሥተኛ መሆን ሊያስፈልገን ይችላል፤ ጥናቶቻችን ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን የሐሰት ትምህርት ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ልማድ መተው ይከብዳቸው ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን የአምላክ መንፈስ በተማሪው ልብ ውስጥ እንዲሠራ በቂ ጊዜ መስጠት ያስፈልገን ይሆናል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) በተጨማሪም ስለ ጉዳዩ ጠቅሰን መጸለያችን ጥሩ ነው። እነሱን ለመርዳት መውሰድ ያለብንን የጥበብ እርምጃ አምላክ በትክክለኛው ጊዜ ያሳውቀናል።—1 ዮሐ. 5:14

የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን “በዝርዝር” ተናገሩ (የሐዋርያት ሥራ 15:3-5)

14, 15. በአንጾኪያ ያለው ጉባኤ ለጳውሎስ፣ ለበርናባስና ለሌሎቹ ተጓዦች ያለውን አክብሮት የገለጸው እንዴት ነበር? እነዚህ ወንድሞች በጉዟቸው ወቅት ለእምነት ባልንጀሮቻቸው በረከት የሆኑት እንዴት ነው?

14 ሉቃስ ትረካውን በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “ጉባኤው የተወሰነ መንገድ ከሸኛቸው በኋላ በፊንቄና በሰማርያ በኩል በማለፍ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ተለውጠው አምላክን ማምለክ እንደጀመሩ በዝርዝር ተናገሩ፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኟቸው።” (ሥራ 15:3) ጉባኤው ጳውሎስንና በርናባስን እንዲሁም ሌሎቹን ተጓዦች የተወሰነ መንገድ ድረስ መሸኘቱ ለእነሱ ያለውን ክርስቲያናዊ ፍቅርና አክብሮት ያሳያል፤ እነዚህ ሰዎች በሚሄዱበት ሁሉ የአምላክ በረከት እንዳይለያቸው ያለውን ምኞት የሚገልጽ ነው። በዚህ ረገድም በአንጾኪያ የነበሩት ወንድሞች ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል! አንተስ ለመንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ “በተለይ ደግሞ በመናገርና በማስተማር ተግተው [ለሚሠሩት] ሽማግሌዎች” አክብሮት ታሳያለህ?—1 ጢሞ. 5:17

15 ወንድሞች በጉዟቸው ላይ በፊንቄና በሰማርያ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን አበረታተዋል፤ ለአሕዛብ በመመሥከሩ ሥራ እየተገኘ ስላለው ውጤት “በዝርዝር” ነግረዋቸዋል። ይህን ከሰሙት መካከል አንዳንዶቹ፣ እስጢፋኖስ መገደሉን ተከትሎ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሸሹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እየባረከው እንዳለ የሚገልጹ ሪፖርቶችን መስማት ያበረታታናል፤ በተለይም የተለያየ ፈተና እየደረሰባቸው ላሉ ወንድሞቻችን ይህ የብርታት ምንጭ ይሆንላቸዋል። ታዲያ ከእነዚህ ሪፖርቶች ሙሉ ጥቅም እያገኘህ ነው? በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም በወረቀት በታተሙት ጽሑፎቻችንም ሆነ በ​jw.org ላይ የሚወጡትን ተሞክሮዎችና የሕይወት ታሪኮች በማንበብ እንዲህ ካሉት ሪፖርቶች ሙሉ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ።

16. ግርዘት አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

16 በመጨረሻም ከአንጾኪያ የተነሱት ልዑካን በስተ ደቡብ 550 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወዳሰቡት ቦታ ደረሱ። ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኢየሩሳሌም ሲደርሱም በዚያ የሚገኘው ጉባኤ እንዲሁም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው፤ የተላኩትም ወንድሞች አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች ተረኩላቸው።” (ሥራ 15:4) ሆኖም በዚህ ጊዜ “ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን መካከል አማኞች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው ‘እነዚህን ሰዎች መግረዝና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ አስፈላጊ ነው’ ሲሉ ተናገሩ።” (ሥራ 15:5) አይሁዳውያን ያልሆኑ ክርስቲያኖችን በተመለከተ የተነሳው የግርዘት ጥያቄ ትልቅ ውዝግብ የሚፈጥር ጉዳይ እንደነበር ግልጽ ነው፤ ለዘለቄታው እልባት ማግኘት ነበረበት።

“ሐዋርያትና ሽማግሌዎች . . . ተሰበሰቡ” (የሐዋርያት ሥራ 15:6-12)

17. በኢየሩሳሌም የነበረው የበላይ አካል እነማንን ያቀፈ ነበር? “ሽማግሌዎች” ከሐዋርያት ጋር አብረው እንዲያገለግሉ የተደረገው ለምን ሊሆን ይችላል?

17 ምሳሌ 13:10 “ምክር በሚሹ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። ከዚህ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በመስማማት “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች [ግርዘትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ] ለመመርመር ተሰበሰቡ።” (ሥራ 15:6) ዛሬ እንዳለው የበላይ አካል ሁሉ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች” መላውን የክርስቲያን ጉባኤ የሚመለከት ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት ነበራቸው። “ሽማግሌዎች” ከሐዋርያት ጋር አብረው እንዲያገለግሉ የተደረገው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ያዕቆብ እንደተገደለ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ታስሮ እንደነበረ አስታውስ። ሌሎቹ ሐዋርያት ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውስ? የአመራር ሥራውን ያለምንም መስተጓጎል ማስቀጠል እንዲቻል ብቃት ያላቸው ሌሎች በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞች መኖራቸው አስፈላጊ ነበር።

18, 19. ጴጥሮስ ምን አሳማኝ ሐሳብ ተናገረ? አድማጮቹስ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰው መሆን አለበት?

18 ሉቃስ በመቀጠል እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ወንድሞች፣ አሕዛብ የምሥራቹን ቃል ከእኔ አፍ ሰምተው እንዲያምኑ አምላክ ገና ከመጀመሪያው ከእናንተ መካከል እኔን እንደመረጠኝ በሚገባ ታውቃላችሁ። ልብን የሚያውቀው አምላክ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሠከረላቸው። ደግሞም በእኛና በእነሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ።’” (ሥራ 15:7-9) አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚለው በቁጥር 7 ላይ የሚገኘው “ክርክር” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ምርመራ ማድረግ፣ ጥያቄ ማንሳት” የሚል ፍቺም አለው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ወንድሞች የአመለካከት ልዩነት ነበራቸው፤ ሐሳባቸውንም በነፃነት ይገልጹ ነበር።

19 ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ አሳማኝ ነበር፤ ካልተገረዙ አሕዛብ ወገን የሆኑት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ይኸውም ቆርኔሌዎስና ቤተሰቦቹ በ36 ዓ.ም. በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ እሱ ራሱ በቦታው እንደነበር አስታወሳቸው። ይሖዋ በአይሁዳውያንና አይሁዳውያን ባልሆኑ ሰዎች መካከል ልዩነት እንዲኖር ማድረጉን ከተወ ታዲያ ሰዎች እንዲህ ለማድረግ ምን ሥልጣን አላቸው? ደግሞም የአንድን ክርስቲያን ልብ የሚያነጻው በክርስቶስ ማመኑ እንጂ የሙሴን ሕግ መጠበቁ አይደለም።—ገላ. 2:16

20. የግርዘት ደጋፊዎች ‘አምላክን እየተፈታተኑት’ የነበሩት በምን መንገድ ነው?

20 የአምላክ ቃልም ሆነ መንፈስ ቅዱስ የሰጡትን የማያሻማ ምሥክርነት መሠረት በማድረግ ጴጥሮስ የሚከተለውን የመደምደሚያ ሐሳብ ተናገረ፦ “ታዲያ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርቱ ጫንቃ ላይ በመጫን አሁን አምላክን ለምን ትፈታተናላችሁ? በአንጻሩ ግን እኛ የምንድነው በጌታ ኢየሱስ ጸጋ አማካኝነት እንደሆነ እናምናለን፤ እነሱም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ።” (ሥራ 15:10, 11) የግርዘት ደጋፊዎች በእርግጥም ‘አምላክን እየተፈታተኑት’ ወይም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳስቀመጠው ‘ትዕግሥቱን እያስጨረሱት’ ነው። አይሁዳውያኑ ራሳቸው ሙሉ በሙሉ ሊፈጽሙት ያልቻሉትንና ለሞት ኩነኔ የዳረጋቸውን ሕግ በአሕዛብ ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው። (ገላ. 3:10) እነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ በኢየሱስ በኩል ለተገለጸው የአምላክ ጸጋ አመስጋኞች መሆን ነበረባቸው።

21. በርናባስና ጳውሎስ ለውይይቱ የሚጠቅም ምን ሐሳብ ተናገሩ?

21 የጴጥሮስ ንግግር የአድማጮቹን ልብ በጥልቅ ሳይነካ አልቀረም፤ ምክንያቱም ዘገባው “የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ጸጥ አለ” ይላል። ከዚያ በኋላ በርናባስና ጳውሎስ “አምላክ በእነሱ አማካኝነት በአሕዛብ መካከል ያከናወናቸውን በርካታ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች” ተረኩ። (ሥራ 15:12) ስለዚህ አሁን ሐዋርያቱና ሽማግሌዎቹ ማስረጃዎቹን ሁሉ ማመዛዘን የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው፤ ግርዘትን በተመለከተ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ በግልጽ ማስተዋልና ከዚህ ጋር የሚስማማ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ይችላሉ።

22-24. (ሀ) ዛሬ ያለው የበላይ አካል ጥንት የነበረውን የበላይ አካል ምሳሌ የሚከተለው እንዴት ነው? (ለ) ሁሉም ሽማግሌዎች ለቲኦክራሲያዊ ሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

22 በዛሬው ጊዜም የበላይ አካል አባላት ስብሰባ በሚያደርጉበት ወቅት መመሪያ ለማግኘት የአምላክን ቃል ይመረምራሉ፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አጥብቀው ይጸልያሉ። (መዝ. 119:105፤ ማቴ. 7:7-11) እያንዳንዱ የበላይ አካል አባል አጀንዳው ቀደም ብሎ ይሰጠዋል፤ በመሆኑም ስለ ጉዳዩ በጸሎት ለማሰብና የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል አጋጣሚ ያገኛል። (ምሳሌ 15:28) እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞች በስብሰባው ላይ ሐሳባቸውን በነፃነትና በአክብሮት ይገልጻሉ። በውይይታቸው ወቅት በተደጋጋሚ መጽሐፍ ቅዱስን አውጥተው ይመለከታሉ።

23 የጉባኤ ሽማግሌዎች የእነሱን ምሳሌ መከተል ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች በስብሰባቸው ወቅት መፍትሔ ሊያገኙለት ያልቻሉት ከበድ ያለ ጉዳይ ሊኖር ይችላል፤ በዚህ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል በዚያ አገር ያለውን ቅርንጫፍ ቢሮ ወይም ቅርንጫፍ ቢሮው የሾማቸውን ተወካዮች፣ ለምሳሌ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን ማማከር ይችላል። ቅርንጫፍ ቢሮው ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለበላይ አካሉ መጻፍ ይችላል።

24 አዎ፣ ይሖዋ ለቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች አክብሮት ያላቸውን እንዲሁም ትሑት፣ ታማኝና ታጋሽ የሆኑ ሰዎችን ይባርካል። አምላክ እንዲህ ለሚያደርጉ ሰዎች እውነተኛ ሰላም፣ መንፈሳዊ ብልጽግናና ክርስቲያናዊ አንድነት በመስጠት ወሮታ ይከፍላቸዋል፤ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህን እንመለከታለን።

a ‘ሐሰተኛ ወንድሞች’ የሚያስተምሩት ትምህርት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b የግርዘት ቃል ኪዳን ዛሬም ድረስ እየሠራ ያለው የአብርሃም ቃል ኪዳን ክፍል አልነበረም። የአብርሃም ቃል ኪዳን ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ1943 ዓ.ዓ. ነው፤ ይህም አብርሃም (በወቅቱ አብራም ይባል ነበር) ወደ ከነአን ሲጓዝ የኤፍራጥስን ወንዝ የተሻገረበት ዓመት ነው። በወቅቱ አብርሃም የ75 ዓመት ሰው ነበር። የግርዘት ቃል ኪዳን የተቋቋመው ደግሞ በ1919 ዓ.ዓ. ነው፤ በዚህ ወቅት አብርሃም የ99 ዓመት ሰው ነበር።—ዘፍ. 12:1-8፤ 17:1, 9-14፤ ገላ. 3:17

c ከተላኩት ወንድሞች አንዱ ቲቶ ሳይሆን አይቀርም። ቲቶ ግሪካዊ ክርስቲያን ነው፤ በኋላ ላይ የጳውሎስ ታማኝ የጉዞ ጓደኛና ተወካይ ሆኗል። (ገላ. 2:1፤ ቲቶ 1:4) ይህ ሰው፣ አንድ ያልተገረዘ አሕዛብ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው።—ገላ. 2:3