ምዕራፍ 18
“አምላክን እንዲፈልጉትና . . . እንዲያገኙት”
ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር የሚያግባባውን ርዕሰ ጉዳይ መርጧል፤ የሚሰብክበትን መንገድ እንደ ሁኔታው አስተካክሏል
በሐዋርያት ሥራ 17:16-34 ላይ የተመሠረተ
1-3. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ሳለ በጣም የተረበሸው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
ጳውሎስ በጣም ተረብሿል። የትምህርት ማዕከል በሆነችው አቴንስ፣ ግሪክ እየተዘዋወረ ነው፤ በአንድ ወቅት ሶቅራጥስ፣ ፕላቶና አርስቶትል በዚህች ከተማ አስተምረዋል። የአቴንስ ነዋሪዎች ሃይማኖተኛ ናቸው። ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር፤ ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ፣ በየቤተ መቅደሱ፣ በየአደባባዩም ሆነ በየጎዳናው ጣዖት የሌለበት የለም። ጳውሎስ፣ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ስለ ጣዖት አምልኮ ምን አመለካከት እንዳለው ያውቃል። (ዘፀ. 20:4, 5) ይህ ታማኝ ሐዋርያ ልክ እንደ ይሖዋ ጣዖታትን ይጸየፋል!
2 ጳውሎስ በተለይ ወደ ገበያ ስፍራው ሲገባ ያየው ነገር በጣም የሚያስደነግጥ ነው። በስተ ሰሜን ምዕራብ በሚገኘው ማዕዘን ላይ በዋናው በር አጠገብ፣ ሄርሜስ የተባለው አምላክ አስጸያፊ ሐውልቶች ተደርድረዋል። የገበያ ስፍራው በአምልኮ ቦታዎች የተሞላ ነው። ይህ ቀናተኛ ሐዋርያ የጣዖት አምልኮ በተስፋፋበት በዚህ ቦታ መስበክ የሚችለው እንዴት ነው? ስሜቱን ተቆጣጥሮ፣ ከአድማጮቹ ጋር በሚያግባባው ርዕስ ላይ መወያየት ይችል ይሆን? አድማጮቹ እውነተኛውን አምላክ እንዲፈልጉና እንዲያገኙት ለመርዳት የሚያደርገው ጥረትስ ይሳካለት ይሆን?
3 ጳውሎስ በአቴንስ ለሚኖሩ የተማሩ ሰዎች የሰጠው ግሩም ንግግር በሐዋርያት ሥራ 17:22-31 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ግሩም የንግግር ጥበብ፣ ብልሃትና ማስተዋል የተንጸባረቀበት በመሆኑ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ በመመርመር፣ ከሌሎች ጋር የሚያግባባንን ርዕሰ ጉዳይ መምረጥና ነጥቡን እንዲያገናዝቡ መርዳት ስለምንችልበት መንገድ ብዙ እንማራለን።
“በገበያ ስፍራ” ማስተማር (የሐዋርያት ሥራ 17:16-21)
4, 5. ጳውሎስ አቴንስ ውስጥ በየትኞቹ ቦታዎች ሰበከ? በዚያስ ምን ዓይነት ሰዎች አጋጠሙት?
4 ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን እያደረገ ነው፤ በ50 ዓ.ም. ገደማ ወደ አቴንስ ሄደ። a ሲላስና ጢሞቴዎስ ከቤርያ እስኪመጡ እየጠበቀ ሳለ እንደ ልማዱ “በምኩራብ ከአይሁዳውያን . . . ጋር ይወያይ ጀመር።” በተጨማሪም አይሁዳውያን ያልሆኑ የአቴንስ ነዋሪዎችን ለማግኘት ወደ “ገበያ ስፍራ” ሄደ። (ሥራ 17:17) ከአክሮፖሊስ በስተ ሰሜን ምዕራብ የሚገኘው የአቴንስ የገበያ ስፍራ 5 ሄክታር ገደማ ይሸፍናል። ይህ የገበያ ቦታ የንግድ አካባቢ ብቻ አልነበረም፤ ሰዎች የሚሰባሰቡበት የከተማዋ አደባባይ ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ ይህ ቦታ “የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ማዕከል” እንደነበር ገልጿል። የአቴንስ ነዋሪዎች እዚያ ተሰባስበው ጥልቅ እውቀት በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ መወያየት ያስደስታቸው ነበር።
5 ጳውሎስ በዚህ የገበያ ቦታ ያገኛቸው ሰዎች በቀላሉ ሊያሳምናቸው የሚችል አልነበሩም። ከአድማጮቹ መካከል ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦይኮች ይገኙበታል፤ ሁለቱ ቡድኖች በጣም የተለያዩ ፍልስፍናዎችን ያራምዳሉ። b ኤፊቆሮሳውያን ‘ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ነው’ የሚል አመለካከት ነበራቸው። ስለ ሕይወት ያላቸውን አመለካከት በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል፦ “አምላክን ለመፍራት ምክንያት የለም፤ የሞተ ምንም አይሰማውም፤ ጥሩን ማግኘት ይቻላል፤ ክፋትንም ችሎ ማሳለፍ ይቻላል።” ኢስጦይኮች በምክንያትና በአመክንዮ (ሎጂክ) ማመንን በጣም ያበረታታሉ፤ አምላክ የራሱ ሕልውና ያለው አካል እንደሆነ አያምኑም። ኤፊቆሮሳውያንም ሆኑ ኢስጦይኮች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚያስተምሩትን የትንሣኤ ትምህርት አይቀበሉም። እነዚህ ሁለት ቡድኖች የሚያራምዱት ፍልስፍና፣ ጳውሎስ ከሚያስተምራቸው የላቁ የክርስትና እውነቶች ጋር ፈጽሞ እንደማይጣጣም ግልጽ ነው።
6, 7. በግሪክ የነበሩ አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ለጳውሎስ ትምህርት ምን ምላሽ ሰጡ? በዛሬው ጊዜስ ምን ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል?
6 ታዲያ እነዚህ የግሪክ ምሁራን ለጳውሎስ ትምህርት ምን ምላሽ ሰጡ? አንዳንዶቹ “ለፍላፊ” ብለውታል፤ ግሪክኛው ቃል ”ጥሬ ለቃሚ” የሚል ትርጉምም አለው። (የሥራ 17:18ን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፣ nwtsty-E) ይህን ግሪክኛ ቃል በተመለከተ አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “መጀመሪያ ላይ ቃሉ፣ ወዲያ ወዲህ እያለች ጥሬ የምትለቅምን ትንሽ ወፍ ለማመልከት ይሠራበት ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ በገበያ ስፍራ የምግብ ፍርፋሪና የወዳደቁ ነገሮች የሚለቃቅሙ ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ቆየት ብሎ ደግሞ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ቃል ሆነ፤ ምንም ተዛማጅነት የሌላቸውን ወሬዎች ከዚያም ከዚህም የሚለቃቅም በተለይ ደግሞ የሰማውን ነገር ምንም ሳይረዳ ለሌሎች የሚቀባጥርን ሰው ያመለክት ጀመር።” እነዚህ ምሁራን፣ ጳውሎስ የሰማውን ሳያመዛዝን የሚደግም ቀባጣሪ እንደሆነ እየተናገሩ ነበር። ይሁንና ቀጥሎ እንደምንመለከተው ጳውሎስ፣ በዚህ የንቀት ቃል አልተሸማቀቀም።
7 ዛሬ ያለው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው እምነታችን የተነሳ ብዙውን ጊዜ መጥፎ ስም ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ምሁራን ዝግመተ ለውጥ ተጨባጭ ማስረጃ ያለው እውነታ እንደሆነ ያስተምራሉ፤ አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው ሊቀበለው እንደሚገባም ይናገራሉ። ይህን ሲሉ፣ ‘በዝግመተ ለውጥ የማያምኑ ሰዎች መሃይም ናቸው’ ማለታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር ማስተማራችንና በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን ንድፍ ማስረጃ አድርገን ማቅረባችን ተማርን ለሚሉት ለእነዚህ ሰዎች ሞኝነት ነው፤ ‘ጥሬ ለቃሚዎች’ የማለት ያህል በሰዎች ፊት ሊያብጠለጥሉን ይሞክራሉ። እኛ ግን በዚህ አንሸማቀቅም። ከዚህ ይልቅ በልበ ሙሉነት መናገራችንን እንቀጥላለን፤ በምድር ላይ ያለው ሕይወት የላቀ ንድፍ አውጪ እንዳለው፣ እሱም ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ከመናገር ወደኋላ አንልም።—ራእይ 4:11
8. (ሀ) ጳውሎስ ሲሰብክ የሰሙ አንዳንድ ሰዎች ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) ጳውሎስ ወደ አርዮስፋጎስ ተወሰደ ሲባል ምን ማለት ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
8 ጳውሎስ በገበያ ስፍራ ሲሰብክ አንዳንዶች ደግሞ ምላሻቸው ከዚህ የተለየ ነበር። “ስለ ባዕዳን አማልክት የሚያውጅ ይመስላል” አሉ። (ሥራ 17:18) በእርግጥ ጳውሎስ ለአቴንስ ነዋሪዎች አዳዲስ አማልክትን እያስተዋወቀ ነበር? ይህ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ክስ ነው፤ ከተወሰኑ መቶ ዘመናት በፊት ሶቅራጥስ ከተከሰሰባቸውና ለሞት ፍርድ ካበቁት ክሶች አንዱ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ጳውሎስ ወደ አርዮስፋጎስ ተወስዶ ለአቴንስ ነዋሪዎች እንግዳ የሆኑባቸውን ትምህርቶች እንዲያብራራ መጠየቁ ምንም አያስገርምም። c ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማያውቁ ሰዎች መልእክቱን እንዴት ያስረዳ ይሆን?
“የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ . . . አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ” (የሐዋርያት ሥራ 17:22, 23)
9-11. (ሀ) ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር ሊያግባባው የሚችል ርዕስ በማንሳት ውይይቱን የጀመረው እንዴት ነው? (ለ) በአገልግሎታችን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ በዚያ ስፍራ የጣዖት አምልኮ ተስፋፍቶ በማየቱ በጣም ተረብሾ እንደነበር አስታውስ። ይሁንና የጣዖት አምልኮን በቀጥታ አላወገዘም፤ ከዚህ ይልቅ ስሜቱን ተቆጣጥሮ ከአድማጮቹ ጋር ሊያግባባው የሚችል ርዕስ በዘዴ በማንሳት ልባቸውን ለመንካት ጥረት አድርጓል። ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው “የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ” በማለት ነው። (ሥራ 17:22) በሌላ አነጋገር ‘ሃይማኖተኛ ሰዎች እንደሆናችሁ አስተውያለሁ’ ማለቱ ነበር። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች በሃይማኖታዊ ዝንባሌያቸው ማመስገኑ ጥበብ ነው። በሐሰት እምነት ከታወሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ መልእክቱን ሊቀበሉ እንደሚችሉ ተገንዝቦ ነበር። እሱ ራሱም ቢሆን በአንድ ወቅት “ባለማወቅና ባለማመን” ይመላለስ እንደነበር ያውቃል።—1 ጢሞ. 1:13
10 ጳውሎስ የአቴንስ ሰዎች ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንዳላቸው የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ይኸውም “ለማይታወቅ አምላክ” ተብሎ የተሠራ መሠዊያ እንዳየ ጠቀሰ። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው “ግሪካውያንም ሆኑ ሌሎች ሕዝቦች ‘ለማይታወቁ አማልክት’ መሠዊያ የመሥራት ልማድ ነበራቸው፤ ምናልባት የተረሳ አምላክ ካለ ሊቀየመን ይችላል ብለው ይፈሩ ነበር።” የአቴንስ ሰዎች እንዲህ ያለ መሠዊያ መሥራታቸው፣ እነሱ የማያውቁት አምላክ መኖሩን አምነው መቀበላቸውን ያሳያል። ጳውሎስ ይህን መሠዊያ እንደ መሸጋገሪያ አድርጎ በመጠቀም የሚሰብከውን ምሥራች አስተዋወቀ። “ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ አሳውቃችኋለሁ” አላቸው። (ሥራ 17:23) ጳውሎስ መልእክቱን ያቀረበው በዘዴ ሆኖም አሳማኝ በሆነ መንገድ ነበር። አንዳንዶች እንደወነጀሉት ስለ አንድ አዲስ ወይም እንግዳ የሆነ አምላክ እየሰበከ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እነሱ ‘የማይታወቅ አምላክ’ ብለው ስለሰየሙት አምላክ ይኸውም ስለ እውነተኛው አምላክ እያብራራላቸው ነበር።
11 በአገልግሎታችን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? አስተዋዮች ከሆን የምናነጋግረው ሰው ሃይማኖተኛ መሆኑን የሚጠቁም ማስረጃ ልናይ እንችላለን፤ ምናልባትም የለበሰው ወይም ያደረገው አሊያም ቤቱ ወይም ግቢው ውስጥ የሚታየው ነገር ይህን ሊጠቁመን ይችላል። ከዚያም እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ ‘ሃይማኖተኛ ሰው እንደሆንክ አስተውያለሁ። እንደ አንተ ካሉ ሰዎች ጋር መወያየት ደስ ይለኛል።’ የሰውየውን ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንደምናከብር በመጥቀስ ከግለሰቡ ጋር የሚያግባባንን መሠረት መጣል እንችላለን። በሃይማኖታዊ እምነታቸው የተነሳ በሰዎች ላይ መፍረድ እንደሌለብን አስታውስ። ከእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ብዙዎች በአንድ ወቅት የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን አጥብቀው ይከተሉ ነበር።
አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” (የሐዋርያት ሥራ 17:24-28)
12. ጳውሎስ መልእክቱን ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ያቀረበው እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር የሚያግባባውን ርዕሰ ጉዳይ በመጠቀም ውይይቱን ጀምሯል፤ ሆኖም ይህንኑ መሠረት ሳይለቅ ውይይቱን መቀጠል ይችል ይሆን? አድማጮቹ የተማሩት የግሪክን ፍልስፍና እንደሆነ ያውቃል፤ ቅዱሳን መጻሕፍትን አያውቁም፤ በመሆኑም መልእክቱን ከእነሱ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ለማቅረብ የተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅሟል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ ሳይጠቅስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን አስተምሯቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ራሱን ከእነሱ የተለየ አድርጎ እንደማይመለከት ሊጠቁማቸው ሞክሯል፤ አልፎ አልፎ “እኛ” እያለ ራሱንም አካትቶ መናገሩ ይህን ያሳያል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የሚያስተምራቸው አንዳንድ ትምህርቶች በራሳቸው ጽሑፎች ላይም እንደሚገኙ ለማሳየት ከግሪክ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ጠቅሷል። ጳውሎስ የሰጠውን ግሩም ንግግር እስቲ እንመርምር። የአቴንስ ሰዎች የማያውቁትን አምላክ በተመለከተ የትኞቹን አስፈላጊ እውነቶች አስተምሯል?
13. ጳውሎስ ጽንፈ ዓለም የተገኘበትን መንገድ በተመለከተ ምን ብሏል? ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክትስ ምንድን ነው?
13 አምላክ ጽንፈ ዓለምን ፈጥሯል። ጳውሎስ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ እሱ የሰማይና የምድር ጌታ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም” ሲል ተናግሯል። d (ሥራ 17:24) ጽንፈ ዓለም የተገኘው እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም። ሁሉንም ነገር የፈጠረው እውነተኛው አምላክ ነው። (መዝ. 146:6) አቴናም ሆነች ሌሎች ጣዖታት ክብራቸው የተመካው ሰዎች በሚሠሩላቸው ቤተ መቅደሶችና መሠዊያዎች ላይ ነው፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ሉዓላዊ ጌታ ግን በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሊኖር አይችልም። (1 ነገ. 8:27) ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ግልጽ ነው፦ እውነተኛው አምላክ፣ ሰዎች በሠሯቸው ቤተ መቅደሶች ውስጥ ከሚገኙት ሰው ሠራሽ ጣዖታት እጅግ የላቀ ነው።—ኢሳ. 40:18-26
14. ጳውሎስ፣ አምላክ የሰዎች ጥገኛ እንዳልሆነ የገለጸው እንዴት ነው?
14 አምላክ የሰዎች ጥገኛ አይደለም። ጣዖት አምላኪዎች፣ ለአምልኮ የሚጠቀሙባቸውን ምስሎች የተንቆጠቆጡ ልብሶችን ያለብሷቸው፣ በርካታ ውድ ስጦታዎችን ይሰጧቸው ወይም ምግብና መጠጥ ያቀርቡላቸው ነበር! አማልክቱ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው የሚያስቡ ይመስላል። ጳውሎስን የሚያዳምጡት አንዳንድ የግሪክ ፈላስፎች ግን አምላክ ከሰዎች የሚፈልገው ነገር አለ ብለው የሚያምኑ አይመስልም። ይህ ከሆነ ደግሞ “[አምላክ] የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም” በሚለው የጳውሎስ ሐሳብ እንደሚስማሙ ግልጽ ነው። አዎ፣ ፈጣሪ የሚያስፈልገውና ሰዎች ሊሰጡት የሚችሉት ቁሳዊ ነገር የለም! እንዲያውም ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያገኙት ከእሱ ነው፤ “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር” ለምሳሌ ፀሐይን፣ ዝናብንና ለም አፈርን ለሰው ልጆች የሚሰጠው እሱ ነው። (ሥራ 17:25፤ ዘፍ. 2:7) ስለዚህ ሰጪ የሆነው አምላክ ተቀባይ የሆኑት የሰው ልጆች ጥገኛ አይደለም።
15. ጳውሎስ፣ ግሪካውያን ካልሆኑ ሰዎች እንደሚበልጡ የሚያስቡትን የአቴንስ ሰዎች አመለካከት ያረመው እንዴት ነው? እኛስ እሱ ከተወው ምሳሌ ምን ትልቅ ቁም ነገር እንማራለን?
15 ሰውን የፈጠረው አምላክ ነው። የአቴንስ ሰዎች፣ ግሪካውያን ካልሆኑ ሰዎች እንደሚበልጡ ያስቡ ነበር። ሆኖም በብሔርም ሆነ በዘር መኩራት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ይቃረናል። (ዘዳ. 10:17) ጳውሎስ ጥንቃቄ የሚያሻውን ይህን ጉዳይ ያብራራው በዘዴና በጥበብ ነው። “[አምላክ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” አላቸው፤ ይህ ሐሳብ አድማጮቹ ቆም ብለው እንዲያስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም። (ሥራ 17:26) እዚህ ላይ ጳውሎስ የሰው ዘር አባት ስለሆነው ስለ አዳም የሚገልጸውን የዘፍጥረት ዘገባ መጥቀሱ ነበር። (ዘፍ. 1:26-28) ሁሉም የሰው ዘር ከአንድ አባት የተገኘ በመሆኑ የትኛውም ዘር ወይም ብሔር ከሌላው አይበልጥም። ከጳውሎስ አድማጮች መካከል ይህን ነጥብ መረዳት የሚሳነው ሊኖር አይችልም። እኛም እሱ ከተወው ምሳሌ አንድ ትልቅ ቁም ነገር እንማራለን። በምሥክርነቱ ሥራችን ዘዴኛና ምክንያታዊ መሆን ቢኖርብንም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲቀበሉ ስንል አለዝበን ማቅረብ አይኖርብንም።
16. ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
16 የአምላክ ዓላማ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ነው። በጳውሎስ አድማጮች መካከል የነበሩት ፈላስፎች፣ ሰው ወደ ሕልውና የመጣበትን ዓላማ በተመለከተ ለብዙ ዓመታት ሲከራከሩ ኖረዋል፤ ያም ሆኖ አጥጋቢ ማብራሪያ ሊሰጡ አልቻሉም። ጳውሎስ ግን ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ቁልጭ አድርጎ አስቀመጠ፤ ዓላማው “ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት” መሆኑን ተናገረ፤ አክሎም “እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም” አላቸው። (ሥራ 17:27) የአቴንስ ሰዎች ያላወቁት አምላክ፣ ጨርሶ ሊታወቅ የማይችል አምላክ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እሱን ለማግኘትና ስለ እሱ ለመማር ልባዊ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች የራቀ አይደለም። (መዝ. 145:18) ጳውሎስ “ከእያንዳንዳችን” ብሎ እንደተናገረ ልብ በል፤ ይህን ሲል አምላክን ‘መፈለግና አጥብቀው መሻት’ ከሚጠበቅባቸው ሰዎች መካከል ራሱንም ማካተቱ ነው።
17, 18. ሰዎች ወደ አምላክ ለመቅረብ ሊነሳሱ የሚገባው ለምንድን ነው? ጳውሎስ የአድማጮቹን ትኩረት ለመሳብ ካደረገው ጥረት ምን መማር እንችላለን?
17 ሰዎች ወደ አምላክ የመቅረብ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ጳውሎስ “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው” ሲል ተናግሯል። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ይህን ሲል፣ በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ኤፒሜንዲዝ የተናገረውን ሐሳብ መጥቀሱ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይህ ቀርጤሳዊ ገጣሚ “በአቴናውያን ሃይማኖታዊ ወግና ልማድ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው” ሰው ነበር። ጳውሎስ ሰዎች ወደ አምላክ ለመቅረብ እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸውን ሌላም ምክንያት ገልጿል፤ “ከእናንተ ባለቅኔዎች አንዳንዶቹ ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው [ተናግረዋል]” ብሏል። (ሥራ 17:28) ሰዎች ከአምላክ ጋር ቤተሰባዊ ዝምድና እንዳላቸው ሊሰማቸው ይገባል፤ ምክንያቱም የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነውን የመጀመሪያውን ሰው የፈጠረው አምላክ ነው። ጳውሎስ የአድማጮቹን ትኩረት ለመሳብ ሲል ትልቅ ቦታ ከሚሰጧቸው የግሪክ ጽሑፎች ላይ በቀጥታ ጠቅሷል። e እኛም የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ከዓለም የታሪክ መጻሕፍት፣ ከኢንሳይክሎፒዲያዎች ወይም ተቀባይነት ካላቸው ሌሎች የማመሣከሪያ ጽሑፎች አልፎ አልፎ መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክር ላልሆነ ሰው የሐሰት ሃይማኖት ልማዶችን ወይም በዓላትን አመጣጥ ለማስረዳት ተቀባይነት ካላቸው ጽሑፎች ላይ መጥቀስ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
18 ጳውሎስ እስከዚህ ነጥብ ድረስ ንግግሩን ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር እያስማማ በማቅረብ ስለ አምላክ መሠረታዊ እውነቶችን ተናግሯል። ሐዋርያው ይህን ጠቃሚ ሐሳብ ለአድማጮቹ የተናገረው ምን እንዲያደርጉ ፈልጎ ነው? እዚያው ንግግሩን በመቀጠል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነገራቸው።
‘በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ መግባት አለባቸው’ (የሐዋርያት ሥራ 17:29-31)
19, 20. (ሀ) ጳውሎስ ሰው ሠራሽ ጣዖታትን ማምለክ ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ በዘዴ ያጋለጠው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች ምን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸው ነበር?
19 አሁን ጳውሎስ አድማጮቹ እርምጃ እንዲወስዱ ለማበረታታት ተዘጋጅቷል። ከግሪካውያን መጣጥፎች ላይ የጠቀሰውን ሐሳብ መልሶ በማንሳት እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ እኛ የአምላክ ልጆች ከሆንን አምላክ በሰው ጥበብና ንድፍ ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም።” (ሥራ 17:29) በእርግጥም ሰዎች የአምላክ የእጅ ሥራ ከሆኑ አምላክ እንዴት የሰው እጅ ሥራ የሆኑትን ጣዖታት ሊመስል ይችላል? ጳውሎስ በዘዴ ያቀረበው አሳማኝ ማስረጃ፣ ሰው ሠራሽ ጣዖታትን ማምለክ ሞኝነት መሆኑን አጋልጧል። (መዝ. 115:4-8፤ ኢሳ. 44:9-20) ጳውሎስ “እኛ” በማለት ራሱን ጨምሮ መናገሩ ምክሩን ትንሽ ለማለዘብ ረድቶታል።
20 ሐዋርያው እርምጃ መውሰድ የግድ እንደሆነ ግልጽ አደረገ፤ እንዲህ አለ፦ “አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ [ጣዖታትን በሚያመልኩ ሰዎች ደስ ይሰኛል ብለው በማሰብ የኖሩበትን ዘመን] ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ እያሳሰበ ነው።” (ሥራ 17:30) ከጳውሎስ አድማጮች አንዳንዶቹ፣ ይህን የንስሐ ጥሪ ሲሰሙ ደንግጠው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ያቀረበው አሳማኝ ንግግር፣ ሕይወት ያገኙት ከአምላክ በመሆኑ የእሱ ባለዕዳዎች እንደሆኑ አስገንዝቧቸዋል፤ በመሆኑም በእሱ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። አምላክን መፈለግ፣ ስለ እሱ እውነቱን መማርና ሕይወታቸውን ከዚህ እውነት ጋር ሙሉ በሙሉ ማስማማት ያስፈልጋቸው ነበር። የአቴንስ ሰዎች ይህን ለማድረግ፣ ጣዖት አምልኮ ኃጢአት መሆኑን መገንዘብና ከዚህ ልማድ መራቅ ነበረባቸው።
21, 22. ጳውሎስ ንግግሩን የደመደመው የትኛውን ጠንከር ያለ መልእክት በመናገር ነው? ጳውሎስ የተናገረው ነገር ዛሬ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
21 ጳውሎስ ንግግሩን የደመደመው የሚከተለውን ጠንከር ያለ መልእክት በመናገር ነበር፦ “[አምላክ] በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል፤ እሱንም ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።” (ሥራ 17:31) አዎ፣ የፍርድ ቀን ይመጣል! ይህን ማወቅ እውነተኛውን አምላክ ለመሻትና ለማግኘት የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት ነው! ጳውሎስ፣ የተሾመውን ፈራጅ በስም አልጠቀሰም። ከዚህ ይልቅ ይህን ፈራጅ በተመለከተ አስገራሚ የሆነ ነገር ጠቅሷል፤ ሰው ሆኖ እንደኖረና እንደሞተ እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው ገለጸ።
22 ይህ ስሜት ቀስቃሽ መደምደሚያ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። አምላክ የሾመው ፈራጅ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናውቃለን። (ዮሐ. 5:22) በተጨማሪም የፍርድ ቀን የአንድ ሺህ ዓመት ርዝማኔ እንዳለውና በጣም እየቀረበ እንዳለ እናውቃለን። (ራእይ 20:4, 6) ይህን የፍርድ ቀን የምንፈራበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም ታማኞች እንደሆኑ ለተፈረደላቸው ሰዎች እጅግ አስደናቂ በረከት እንደሚያመጣላቸው እናውቃለን። ከፊታችን የምንጠብቀው አስደሳች ተስፋ እንደሚፈጸም ዋስትና የሚሆነን ወደር የሌለው ታላቅ ተአምር ተፈጽሟል፤ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው።
“አንዳንድ ሰዎች . . . አማኞች ሆኑ” (የሐዋርያት ሥራ 17:32-34)
23. የጳውሎስ አድማጮች ምን የተለያየ ምላሽ ሰጥተዋል?
23 የጳውሎስ አድማጮች የሰጡት ምላሽ የተለያየ ነው። “ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር።” ሌሎቹ ደግሞ አክብሮት ቢኖራቸውም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አልነበሩም፤ “ስለዚሁ ጉዳይ በድጋሚ መስማት እንፈልጋለን” አሉት። (ሥራ 17:32) ይሁንና ጥቂቶች መልእክቱን ተቀበሉት፤ ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ሰዎች ግን ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ። ከእነሱም መካከል የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነው ዲዮናስዮስና ደማሪስ የተባለች ሴት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል።” (ሥራ 17:34) እኛም በአገልግሎታችን ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥመናል። አንዳንዶች ሊያሾፉብን ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ለእኛ አክብሮት ቢኖራቸውም ለመልእክቱ ግድየለሽ ይሆናሉ። ሆኖም አንዳንዶች የመንግሥቱን መልእክት ተቀብለው አማኞች ሲሆኑ እጅግ እንደሰታለን።
24. ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ቆሞ ከሰጠው ንግግር ምን ትምህርት እናገኛለን?
24 ጳውሎስ በሰጠው ንግግር ላይ ስናሰላስል፣ ምክንያታዊና አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንዲሁም እንደ አድማጮቻችን ሁኔታ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ብዙ እንማራለን። በተጨማሪም በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች የታወሩ ሰዎችን በትዕግሥትና በዘዴ መያዝ አስፈላጊ እንደሆነ እንማራለን። ሌላም የምናገኘው ትልቅ ቁም ነገር አለ፤ ይኸውም አድማጮቻችንን ለማስደሰት ብለን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አለዝበን ማቅረብ እንደሌለብን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ በመከተል በመስክ አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ አስተማሪዎች መሆን እንችላለን። የበላይ ተመልካቾች ደግሞ ጉባኤ ውስጥ የተሻለ ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች መሆን ይችላሉ። በውጤቱም “ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና . . . እንዲያገኙት” ለመርዳት የተሻለ ብቃት ይኖረናል።—ሥራ 17:27
a “ አቴንስ—የጥንቱ ዓለም የባሕል ማዕከል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b “ ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦይኮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
c አርዮስፋጎስ ከአክሮፖሊስ በስተ ሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ቦታ ነው፤ የአቴንስ አስተዳዳሪዎች ሸንጎ የሚሰበሰበው እዚያ ነበር። “አርዮስፋጎስ” የሚለው ቃል ሸንጎውን አሊያም ራሱን ኮረብታውን ሊያመለክት ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ የተወሰደው ወደዚህ ኮረብታ ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ ስፍራ ነው? ወይስ ይህ አገላለጽ በሌላ ቦታ ምናልባትም በገበያ ስፍራው በተሰየመ ሸንጎ ፊት እንደቀረበ የሚጠቁም ነው? ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምሁራን የተለያየ አመለካከት አላቸው።
d “ዓለም” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ኮስሞስ ሲሆን ግሪካውያን ይህን ቃል ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ለማመልከት ይጠቀሙበት ነበር። ጳውሎስም ከግሪካውያን አድማጮቹ ጋር ሊያግባባው በሚችል መንገድ ለመናገር ጥረት እያደረገ ስለነበር ይህን ቃል የተጠቀመበት ከዚህ አገባቡ አንጻር ሊሆን ይችላል።
e ጳውሎስ የጠቀሰው፣ የኢስጦይክ ገጣሚ ኧራተስ ካዘጋጀው ፊኖሚና የተባለ የሥነ ፈለክ ግጥም ላይ ነው። በሌሎች ግሪካውያን መጣጥፎች ውስጥም ተመሳሳይ አገላለጾች ይገኛሉ፤ የኢስጦይክ ደራሲ የሆነው ክሊያንቲዝ ያዘጋጀውን ሂም ቱ ዙስ የተባለውን ጽሑፍ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።