በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 17

“ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ”

“ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ”

የውጤታማ አስተማሪነት ሚስጥር፤ የቤርያ ሰዎች የተዉት ግሩም ምሳሌ

በሐዋርያት ሥራ 17:1-15 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ከፊልጵስዩስ ወደ ተሰሎንቄ እየተጓዙ ያሉት እነማን ናቸው? ተጓዦቹ ስለ ምን ነገር እያሰቡ ሊሆን ይችላል?

 ጥሩ ችሎታ ባላቸው ሮማውያን መሐንዲሶች የተሠራው መንገድ አስቸጋሪ የሆነውን ተራራማ አካባቢ አቋርጦ ያልፋል። መንገደኛው ከወዲያም ከወዲህም የሚመጡ ብዙ ድምፆችን መስማቱ አይቀርም፤ አህዮች ያናፋሉ፤ ድንጋይ በተነጠፈበት መንገድ ላይ ሠረገሎች እየተንኳኩ ያልፋሉ፤ የወታደሮች፣ የነጋዴዎች የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና የሌሎች መንገደኞች ጫጫታም አለ። ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ ከፊልጵስዩስ መንገድ ጀምረዋል፤ ሦስቱ የጉዞ ጓደኛሞች ከ130 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ወደ ተሰሎንቄ ሊሄዱ ነው። ጉዞው አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ለጳውሎስና ለሲላስ። በፊልጵስዩስ የተደበደበው ሰውነታቸው ገና አልጠገገም።—ሥራ 16:22, 23

2 የመንገዱን ርዝመት አስበው እንዳይታክታቸው ምን ያደርጉ ይሆን? እየተጨዋወቱ መሄዳቸው እንደሚረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። መቼም በፊልጵስዩስ ያገኙት አስደሳች ተሞክሮ ከአእምሯቸው አይጠፋም፤ የእስር ቤቱ ጠባቂና ቤተሰቦቹ ክርስትናን የተቀበሉበት አስደናቂ መንገድ እንዴት ይረሳል? ይህ ተሞክሮ፣ እነዚህ መንገደኞች የአምላክን ቃል ማወጃቸውን ለመቀጠል ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ይበልጥ እንደሚያጠናክርላቸው የታወቀ ነው። ይሁንና በባሕር ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ተሰሎንቄ ሲቃረቡ ‘በዚያች ከተማ የሚኖሩ አይሁዳውያን ምን ምላሽ ይሰጡ ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። በፊልጵስዩስ የደረሰባቸው ዓይነት ጥቃት አልፎ ተርፎም ድብደባ ያጋጥማቸው ይሆን?

3. ለመስበክ የሚያስችለን ድፍረት ለማግኘት የጳውሎስ ምሳሌ የሚረዳን እንዴት ነው?

3 ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ በተሰሎንቄ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በወቅቱ ምን ተሰምቶት እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እንደምታውቁት በመጀመሪያ በፊልጵስዩስ መከራና እንግልት ደርሶብን ነበር፤ ይሁንና ከባድ ተቃውሞ እያለም የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ለመንገር በአምላካችን እርዳታ እንደ ምንም ብለን ድፍረት አገኘን።” (1 ተሰ. 2:2) አዎ፣ ጳውሎስ በተለይ በፊልጵስዩስ ያ ችግር ካጋጠማቸው በኋላ ወደ ተሰሎንቄ ከተማ ለመግባት ስጋት አድሮበት የነበረ ይመስላል። አንተስ እንደ ጳውሎስ ተሰምቶህ ያውቃል? ምሥራቹን መስበክ አስቸጋሪ የሚሆንብህ ጊዜ አለ? ጳውሎስ፣ የሚያስፈልገውን ድፍረትና ጥንካሬ ለማግኘት በይሖዋ ተማምኗል። አንተም የጳውሎስን ምሳሌ መመርመርህ ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል።—1 ቆሮ. 4:16

“ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ . . . ተወያየ” (የሐዋርያት ሥራ 17:1-3)

4. ጳውሎስ በተሰሎንቄ ከሦስት ሳምንት በላይ ቆይቶ ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

4 ዘገባው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ሳለ ለሦስት ሰንበት በምኩራብ እንደሰበከ ይገልጻል። ታዲያ ይህ ሲባል ጳውሎስ በከተማዋ ውስጥ የቆየው ለሦስት ሳምንት ብቻ ነበር ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ጳውሎስ ወደ ምኩራቡ የሄደው ተሰሎንቄ ከደረሰ ከምን ያህል ጊዜ በኋላ እንደሆነ አናውቅም። በተጨማሪም እሱና የጉዞ ጓደኞቹ በተሰሎንቄ በነበሩበት ወቅት ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ለማግኘት ይሠሩ እንደነበር ጳውሎስ የጻፈው ደብዳቤ ይጠቁማል። (1 ተሰ. 2:9፤ 2 ተሰ. 3:7, 8) እንዲሁም ጳውሎስ እዚያ በቆየበት ጊዜ በፊልጵስዩስ የሚገኙ ወንድሞች ሁለት ጊዜ ቁሳዊ ድጋፍ ልከውለታል። (ፊልጵ. 4:16) ስለዚህ ጳውሎስ በተሰሎንቄ ከሦስት ሳምንት በላይ ቆይቶ መሆን አለበት።

5. ጳውሎስ አድማጮቹን ለማሳመን ጥረት ያደረገው እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ እንደ ምንም ብሎ ለመስበክ ድፍረት ካገኘ በኋላ በምኩራብ ውስጥ የተሰበሰቡትን ሰዎች አነጋገራቸው። እንደ ልማዱ “ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤ ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት ‘ይህ እኔ የማውጅላችሁ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው’ አላቸው።” (ሥራ 17:2, 3) ጳውሎስ አድማጮቹ በስሜታዊነት እንዲቀበሉት ለማድረግ አልሞከረም፤ ጉዳዩን በሚገባ እንዲያስቡበት በሚያደርግ መንገድ ይናገር ነበር። ምኩራቡ ውስጥ የተሰበሰቡት ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚያውቁ ብሎም ለእነዚህ መጻሕፍት አክብሮት እንዳላቸው ያውቃል። ይሁንና የተሟላ ግንዛቤ አልነበራቸውም። ስለሆነም ጳውሎስ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን ከቅዱሳን መጻሕፍት ማስረጃ እየጠቀሰ ያብራራላቸውና ያስረዳቸው ነበር።

6. ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳ የነበረው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

6 ጳውሎስ በዚህ ረገድ የኢየሱስን አርዓያ ተከትሏል፤ ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለትምህርቱ መሠረት አድርጎ ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናውን በነበረበት ወቅት የሰው ልጅ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተጻፈው መሠረት መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚገደልና ከሞት እንደሚነሳ ለተከታዮቹ ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 16:21) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። ይህ ብቻ እንኳ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን ያሳያል። ሆኖም ኢየሱስ ተጨማሪ ማስረጃ ሰጥቷቸዋል። ዘገባው፣ ኢየሱስ ከተወሰኑ ደቀ መዛሙርቱ ጋር የተነጋገረውን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እሱ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን በሚገባ አብራራላቸው።” ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ደቀ መዛሙርቱ “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ሲገልጥልን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ሲሉ በአድናቆት ተናግረዋል።—ሉቃስ 24:13, 27, 32

7. የምናስተምረው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት ኃይል አለው። (ዕብ. 4:12) በመሆኑም እንደ ኢየሱስ፣ ጳውሎስና ሌሎች ሐዋርያት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ትምህርታቸው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። ለምናነጋግረው ሰው ነጥቡን ለማስረዳት፣ ጥቅሶችን ለማብራራት እንዲሁም ማስረጃ የሚሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ገልጠን ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። በመሠረቱ የምንሰብከው መልእክት ምንጭ እኛ አይደለንም። በምናገለግልበት ጊዜ በተደጋጋሚ መጽሐፍ ቅዱስን የምንጠቀም ከሆነ የራሳችንን መልእክት ሳይሆን ከአምላክ ያገኘነውን ትምህርት እንደምናውጅ ሰዎች ያስተውላሉ። እኛ ራሳችንም ብንሆን የምንሰብከው መልእክት ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆኑን ማስታወሳችን ጥሩ ነው። መልእክታችን እምነት የሚጣልበት ነው። ይህን ማወቅህ ልክ እንደ ጳውሎስ መልእክቱን በድፍረት እንድታውጅ አያበረታታህም?

‘አንዳንዶች አማኞች ሆኑ’ (የሐዋርያት ሥራ 17:4-9)

8-10. (ሀ) በተሰሎንቄ የነበሩት ሰዎች ለምሥራቹ ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) አንዳንድ አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ ቅናት ያደረባቸው ለምንድን ነው? (ሐ) አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች ምን እርምጃ ወሰዱ?

8 ጳውሎስ፣ ኢየሱስ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ እውነት መሆኑን ከራሱ ተሞክሮ መመልከት ችሏል፦ “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም . . . እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነ ደግሞ የእናንተንም ቃል ይጠብቃሉ።” (ዮሐ. 15:20) ጳውሎስም የገጠመው ይኸው ነው፤ በተሰሎንቄ ሲሰብክ ሰዎቹ የሰጡት ምላሽ የተደበላለቀ ነበር፤ አንዳንዶቹ ቃሉን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጉጉት አሳዩ፤ ሌሎቹ ግን ተቃወሙ። ሉቃስ በጎ ምላሽ ስለሰጡት ሰዎች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእነሱ [ከአይሁዳውያን] መካከል አንዳንዶቹ አማኞች [ክርስቲያኖች] በመሆን ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ከግሪካውያንም መካከል አምላክን የሚያመልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የታወቁ ሴቶች እንዲሁ አደረጉ።” (ሥራ 17:4) እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ቅዱሳን መጻሕፍትን በትክክል መረዳት በመቻላቸው እጅግ እንደተደሰቱ ጥርጥር የለውም።

9 አዎ፣ አንዳንዶች ጳውሎስ ያስተማራቸውን ነገር በደስታ ተቀብለዋል፤ ሆኖም በንዴት ጥርሳቸውን ያፋጩበት ሌሎች ነበሩ። በተሰሎንቄ ያሉ አንዳንድ አይሁዳውያን፣ ‘ከግሪካውያን መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች’ ጳውሎስን በመስማታቸው ቅናት አደረባቸው። እነዚህ አይሁዳውያን አሕዛብ ለሆኑት ግሪካውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማስተማር ወደ ይሁዲነት እንዲለወጡ የማድረግ ዓላማ ነበራቸው፤ ግሪካውያኑ የእነሱ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ ያስቡ ነበር። አሁን ግን ጳውሎስ እነዚህን ግሪካውያን እየዘረፋቸው እንዳለ ተሰማቸው፤ ያውም እዚያው ምኩራባቸው ውስጥ! ስለሆነም አይሁዳውያኑ እጅግ ተቆጡ።

“ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ” ፈልገው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 17:5

10 ሉቃስ ቀጥሎ የሆነውን ነገር እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል፦ “አይሁዳውያን ቅናት ስላደረባቸው በገበያ ስፍራ የሚያውደለድሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አሰባስበው አሳደሙ፤ ከተማዋንም በሁከት አመሷት። ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ የያሶንን ቤት ሰብረው ገቡ። ባጧቸው ጊዜም ያሶንንና አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት በማቅረብ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦ ‘ዓለምን ሁሉ ያናወጡት እነዚያ ሰዎች እዚህም መጥተዋል፤ ያሶንም በእንግድነት ተቀብሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።’” (ሥራ 17:5-7) ታዲያ ይህ የሕዝብ ዓመፅ በጳውሎስና በጉዞ ጓደኞቹ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ?

11. በጳውሎስና አብረውት ባሉት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ላይ ምን ክስ ተመሠረተባቸው? ከሳሾቻቸው ይህን ክስ ሲሰነዝሩ የትኛውን ሕግ በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

11 የሕዝብ ዓመፅ በጣም አደገኛ ነው። ድንገት ግልብጥ ብሎ እንደሚመጣ ጎርፍ ለመግታትና ለመቆጣጠር ያስቸግራል። አይሁዳውያን፣ ጳውሎስንና ሲላስን ለማስወገድ የተጠቀሙበት መሣሪያ ይህ ነበር። በመጀመሪያ አይሁዳውያኑ ‘ከተማዋን በሁከት አመሷት።’ ከዚያም ከባድ ወንጀል እንደተፈጸመ ገዢዎቹን ለማሳመን ሞከሩ። የመጀመሪያው ክስ፣ ጳውሎስና አብረውት ያሉት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ‘ዓለምን ሁሉ አናውጠዋል’ የሚል ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በተሰሎንቄ ሁከት እንዲቀሰቀስ ያደረጉት ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ አይደሉም! ሁለተኛው ክስ ደግሞ ከዚህም ከበድ ያለ ነው። ‘ኢየሱስ ስለተባለ ሌላ ንጉሥ በማወጅ የንጉሠ ነገሥቱን ሕግ ጥሰዋል’ በማለት ሚስዮናውያኑን ወነጀሏቸው። a

12. በተሰሎንቄ በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ የተሰነዘረው ክስ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችል እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

12 የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ ላይም ተመሳሳይ ክስ ሰንዝረው እንደነበር አስታውስ። ጲላጦስን “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያሳምፅ፣ . . . ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አግኝተነዋል” ብለውት ነበር። (ሉቃስ 23:2) ጲላጦስም፣ ንጉሠ ነገሥቱ ‘አገር የመክዳት ወንጀል ሲፈጸም እያየህ ዝም ትላለህ’ እንዳይለው በመስጋት ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስን እንዲገደል አሳልፎ ሰጠው። በተሰሎንቄ በሚገኙት ክርስቲያኖች ላይ የቀረበው ክስም ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችል ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “‘አንድ ሰው በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ክህደት ፈጽሟል ተብሎ ስለተወራበት ብቻ እንኳ ሊገደል ይችል ነበር’፤ በመሆኑም በክርስቲያኖች ላይ የቀረበው ይህ ክስ መዘዙ እጅግ የከፋ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።” ታዲያ አይሁዳውያን በጥላቻ ተነሳስተው የሰነዘሩት ይህ ጥቃት ያሰቡትን ውጤት አስገኝቶላቸው ይሆን?

13, 14. (ሀ) የሕዝቡ ዓመፅ የስብከቱን ሥራ ሊያስቆም ያልቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ፣ ክርስቶስ በሰጠው ምክር መሠረት ጠንቃቃ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 የሕዝቡ ዓመፅ በተሰሎንቄ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ሊያስቆመው አልቻለም። ለምን? አንደኛ ነገር፣ ሕዝቡ ጳውሎስንና ሲላስን ሊያገኛቸው አልቻለም። ሁለተኛ ደግሞ የከተማዋ ገዢዎች የቀረበውን ክስ አሳማኝ ሆኖ ያገኙት አይመስልም። ተይዘው ፊታቸው የቀረቡትን ያሶንንና ሌሎቹን ወንድሞች “የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዙ ካደረጓቸው በኋላ ለቀቋቸው።” (ሥራ 17:8, 9) ጳውሎስ “እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተከትሏል፤ በሌላ ቦታ መስበኩን ለመቀጠል ሲል አደገኛ ከሆነ አካባቢ ርቋል። (ማቴ. 10:16) አዎ፣ ጳውሎስ ደፋር ቢሆንም ጠንቃቃ አልነበረም ማለት አይደለም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የእሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

14 በዘመናችን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በተደጋጋሚ የሕዝብ ዓመፅ አነሳስተዋል። ‘የይሖዋ ምሥክሮች አገርን በመክዳትና በመንግሥት ላይ ዓመፅ በመቀስቀስ ወንጀል ይፈጽማሉ’ የሚል ክስ በመሰንዘር ገዢዎች በእነሱ ላይ እንዲነሱ አድርገዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት አሳዳጆች ሁሉ ዛሬ ያሉት ተቃዋሚዎችም ስደት የሚያደርሱት በቅናት ተነሳስተው ነው። ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን ያደርጋሉ? ራሳቸውን ለአደጋ ላለማጋለጥ ይጠነቀቃሉ። ሥራችንን በሰላም ማከናወን ስለምንፈልግ እንዲህ ያሉ በቁጣ የገነፈሉና የማያመዛዝኑ ሰዎችን ፊት ለፊት ላለመጋፈጥ እንጥራለን፤ ምናልባትም ሁኔታዎች ሲረጋጉ ተመልሰን ልንሄድ እንችላለን።

“በተሰሎንቄ ከነበሩት ይልቅ ቀና አስተሳሰብ” ነበራቸው (የሐዋርያት ሥራ 17:10-15)

15. የቤርያ ሰዎች ለምሥራቹ ምን ምላሽ ሰጡ?

15 ጳውሎስና ሲላስ ለደህንነታቸው ሲባል 65 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቤርያ ተላኩ። እዚያ እንደደረሱም ጳውሎስ ወደ ምኩራብ ገብቶ በዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር አቀረበ። ጳውሎስ እዚህ ያሉት አድማጮቹ ሰሚ ጆሮ እንዳላቸው ሲያይ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በቤርያ የነበሩት አይሁዳውያን በተሰሎንቄ ከነበሩት ይልቅ ቀና አስተሳሰብ ስለነበራቸው የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀበሉ።” (ሥራ 17:10, 11) ታዲያ በተሰሎንቄ እውነትን የተቀበሉት ሰዎችስ ትክክለኛ አመለካከት አልነበራቸውም ማለት ነው? በፍጹም! ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክን ያለማቋረጥ የምናመሰግነው ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም የአምላክን ቃል ከእኛ በሰማችሁ ጊዜ እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው፤ አማኞች በሆናችሁት በእናንተም ላይ በእርግጥ እየሠራ ነው።” (1 ተሰ. 2:13) ይሁንና በቤርያ የነበሩት አይሁዳውያን ይበልጥ ቀና አስተሳሰብ እንዳላቸው የተገለጸው ለምንድን ነው?

16. የቤርያ ሰዎች “ቀና አስተሳሰብ” እንዳላቸው መገለጹ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

16 የቤርያ ሰዎች የሰሙት ነገር አዲስ ቢሆንም እንኳ ተጠራጣሪ ወይም ነቃፊ አልነበሩም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሰሙትን ነገር እንዲሁ አምነው አልተቀበሉም። በመጀመሪያ ጳውሎስ የተናገረውን ነገር በጥንቃቄ አዳመጡ። ከዚያም ጳውሎስ የሰጣቸው ማብራሪያ ትክክል መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን አመሣከሩ። በተጨማሪም የአምላክን ቃል በሰንበት ቀን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በትጋት ይመረምሩ ነበር። ይህንንም ያደረጉት “በታላቅ ጉጉት” ነው፤ አዲስ ካገኙት ትምህርት አንጻር ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ተጨማሪ ነገሮች እንደሚገልጡላቸው ለማወቅ ጊዜ ወስደው ምርምር አድርገዋል። ትሑት ስለሆኑም ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል፤ ዘገባው “ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ . . . አማኞች ሆኑ” ይላል። (ሥራ 17:12) በእርግጥም ሉቃስ “ቀና አስተሳሰብ” እንዳላቸው መናገሩ ምንም አያስገርምም!

17. የቤርያ ሰዎች ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል? አማኞች ከሆንን በኋላም እነሱ የተዉትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

17 እነዚህ የቤርያ ሰዎች፣ ለምሥራቹ የሰጡት ምላሽ በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚቆይ የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ የቀና አስተሳሰብ ምሳሌ ተደርገው እስከ ዘመናችን ድረስ ሲነሱ እንደሚኖሩም ሊጠብቁ አይችሉም። ጳውሎስ ቢያደርጉት ብሎ የሚመኘውን፣ ይሖዋም ከእነሱ የሚጠብቀውን ነገር በማድረጋቸው ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። እኛም ዛሬ ሰዎችን የምናበረታታው ይህንኑ እንዲያደርጉ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በመመርመር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እምነት እንዲያዳብሩ እንፈልጋለን። ይሁንና ቀና አስተሳሰብ የሚያስፈልገን አማኝ እስክንሆን ድረስ ብቻ ነው? አይደለም፤ እንዲያውም ከይሖዋ ለመማር መጓጓትና የተማርነውን በሥራ ላይ ለማዋል ፈጣን መሆን ይበልጥ የሚያስፈልገን አማኝ ከሆንን በኋላ ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እንዲቀርጸንና እንዲያሠለጥነን እንፈቅዳለን። (ኢሳ. 64:8) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የሰማዩ አባታችን በሚገባ የሚጠቀምብን ከመሆኑም ሌላ ልቡን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት እንችላለን።

18, 19. (ሀ) ጳውሎስ ቤርያን ለቆ የሄደው ለምንድን ነው? ሆኖም በጽናት ረገድ ልንከተለው የሚገባ ምን ምሳሌ ትቶልናል? (ለ) ጳውሎስ ቀጥሎ የሰበከው ለእነማን ነው?

18 ጳውሎስ ቤርያ ውስጥ ረጅም ጊዜ አልቆየም። ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ጳውሎስ የአምላክን ቃል በቤርያም እንዳወጀ ባወቁ ጊዜ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ለማወክ ወደዚያ መጡ። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ወዲያውኑ ጳውሎስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ላኩት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴንስ አደረሱት፤ ከዚያም ጳውሎስ ‘ሲላስና ጢሞቴዎስ በተቻለ ፍጥነት ወደ እኔ እንዲመጡ ንገሯቸው’ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ ሰዎቹም ተመልሰው ሄዱ።” (ሥራ 17:13-15) እነዚያ የምሥራቹ ጠላቶች በቀላሉ የሚበገሩ አልነበሩም! ጳውሎስን ከተሰሎንቄ ማባረራቸው አልበቃቸው ብሎ ወደ ቤርያም በመጓዝ ተመሳሳይ ሁከት ለማስነሳት ሞከሩ፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም። ጳውሎስ የአገልግሎት ክልሉ ሰፊ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ሌላ ቦታ ለመስበክ አካባቢውን ለቆ ሄደ። እኛም ዛሬ የስብከቱን ሥራ ለማስቆም የሚፈልጉ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያቆሙ በአቋማችን መጽናት ይኖርብናል!

19 ጳውሎስ በተሰሎንቄና በቤርያ ለነበሩ አይሁዳውያን በሚገባ መሥክሯል፤ በድፍረት መስበክና ቅዱሳን መጻሕፍትን እየጠቀሱ ማስረዳት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ካጋጠመው ሁኔታ ተገንዝቦ መሆን አለበት። እኛም ይህን መገንዘብ ችለናል። አሁን ጳውሎስ በአቴንስ ለሚኖሩ አሕዛብ ሊሰብክ ነው፤ እነሱ ደግሞ እስካሁን ከሰበከላቸው ሰዎች ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። ታዲያ በዚህች ከተማ ውስጥ ምን ያጋጥመው ይሆን? የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ያብራራል።

a አንድ ምሁር እንደገለጹት በዘመኑ በነበረው የቄሳር ሕግ መሠረት “አዲስ ንጉሥ ወይም መንግሥት እንደሚመጣ በተለይም በወቅቱ ያለውን ንጉሠ ነገሥት እንደሚተካ ወይም በእሱ ላይ እንደሚፈርድ” መተንበይ የተከለከለ ነው። ተቃዋሚዎች የጳውሎስን መልእክት በማጣመም ሳይሆን አይቀርም ይህን ሕግ የሚጥስ ነገር እንዳደረገ በመግለጽ ወንጅለውታል። “ ቄሳሮችና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።