በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 15

‘ጉባኤዎችን ማበረታታት’

‘ጉባኤዎችን ማበረታታት’

ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ጉባኤዎች በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ ይረዳሉ

በሐዋርያት ሥራ 15:36 እስከ 16:5 ላይ የተመሠረተ

1-3. (ሀ) አዲሱ የጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ ማን ነው? እሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

 ተጓዦቹ አባጣ ጎርባጣ የሆነውን መንገድ ይዘው ከአንድ መንደር ወደ ሌላው እያቀኑ ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አብሮት ስለሚጓዘው ወጣት እያሰበ አየት ያደርገዋል። ወጣቱ ጢሞቴዎስ ይባላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቢሆን ነው። በትኩስ የወጣትነት ጉልበትና በጉጉት ራመድ ራመድ እያለ ነው። ጉዞው በቀጠለ መጠን ልስጥራና ኢቆንዮን ከዓይናቸው እየተሰወሩ መጡ፤ ወጣቱም ከአገር ከመንደሩ እየራቀ እየራቀ ሄደ። ከፊታቸው ምን ይጠብቃቸው ይሆን? ጳውሎስ የዚህን ጥያቄ መልስ ያውቀዋል፤ ይህ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ነው። በርካታ አደገኛና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ያውቃል። ይሁንና አብሮት እየተጓዘ ያለው ወጣትስ ይችለው ይሆን?

2 ጳውሎስ በጢሞቴዎስ ይተማመናል፤ ምናልባትም ይህ ትሑት ወጣት ስለ ራሱ ከሚያስበው በላይ! ጳውሎስ አብሮት የሚጓዝ ጥሩ ጓደኛ እንደሚያስፈልገው ያውቃል፤ በተለይ በቅርብ ያጋጠሙት ሁኔታዎች ይህን ይበልጥ እንዲገነዘብ አድርገውታል። የጉዞው ዓላማ ጉባኤዎችን መጎብኘትና ማጠናከር ነው፤ ይህ ዓላማ እንዲሳካ ተጓዦቹ የአቋም ጽናትና የሐሳብ አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጳውሎስ ያውቃል። እንዲህ የተሰማው ለምን ሊሆን ይችላል? አንዱ ምክንያት፣ ቀደም ሲል እሱና በርናባስ እንዲለያዩ ያደረገው አለመግባባት ሊሆን ይችላል።

3 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ አለመግባባቶችን በተሻለ መንገድ መፍታት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን የመረጠው ለምን እንደሆነም እናያለን፤ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች ስለሚጫወቱት ቁልፍ ሚና ግንዛቤ እናገኛለን።

‘ወንድሞችን ተመልሰን እንጠይቃቸው’ (የሐዋርያት ሥራ 15:36)

4. ጳውሎስ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ምን ለማድረግ አስቦ ነበር?

4 ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው የበላይ አካሉ የላካቸው አራት ወንድሞች ይኸውም ጳውሎስ፣ በርናባስ፣ ይሁዳና ሲላስ በአንጾኪያ የነበረውን ጉባኤ አጠናክረዋል፤ እነዚህ ወንድሞች የበላይ አካሉ ግርዘትን አስመልክቶ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለጉባኤው አድርሰዋል። ከዚያ በኋላስ ጳውሎስ ምን አደረገ? አዲስ የጉዞ ዕቅድ አወጣ፤ በርናባስን “የይሖዋን ቃል ባወጅንባቸው ከተሞች ሁሉ ያሉት ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተመልሰን እንጠይቃቸው” አለው። (ሥራ 15:36) ጳውሎስ ይህን ሲል እንዲሁ ማኅበራዊ ጥየቃ ስለ ማድረግ መናገሩ አልነበረም። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ያደረገበትን ዓላማ በሚገባ ይገልጽልናል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የበላይ አካሉ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለጉባኤዎቹ ለማሳወቅ ነው። (ሥራ 16:4) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን ጉባኤዎቹን በማበረታታት በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ ለመርዳት ነው። (ሮም 1:11, 12) ዛሬ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅትስ ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ የሚከተለው እንዴት ነው?

5. በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካል ለጉባኤዎች መመሪያና ማበረታቻ የሚሰጠው እንዴት ነው?

5 በዛሬው ጊዜ ክርስቶስ ጉባኤውን ለመምራት የይሖዋ ምሥክሮችን የበላይ አካል ይጠቀማል። የበላይ አካል አባላት የሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ታማኝ ወንድሞች፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ጉባኤዎች መመሪያና ማበረታቻ ይሰጣሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት በደብዳቤዎች፣ ድረ ገጽ ላይ በሚወጡና በታተሙ ጽሑፎች፣ በስብሰባዎች እንዲሁም በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ነው። የበላይ አካሉ ከእያንዳንዱ ጉባኤ ጋር የቅርብ ግንኙነት የሚያደርግበት ሌላም መንገድ አለው። ይህም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን መላክ ነው። የበላይ አካሉ በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎችን የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲያገለግሉ ሾሟል።

6, 7. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ካሉባቸው ኃላፊነቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

6 ዛሬ ያሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ጉባኤዎችን ሲጎበኙ ለሁሉም ወንድሞችና እህቶች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ለመስጠት ይጥራሉ፤ መንፈሳዊ ማበረታቻም ይሰጧቸዋል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? እንደ ጳውሎስ ያሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ በመከተል ነው። ጳውሎስ አብሮት የሚያገለግለውን ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል መክሮታል፦ “ቃሉን ስበክ፤ አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ በጥድፊያ ስሜት አገልግል፤ በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ውቀስ፣ ገሥጽ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር። . . . የወንጌላዊነትን ሥራ አከናውን።”—2 ጢሞ. 4:2, 5

7 ይህን ምክር በመከተል የወረዳ የበላይ ተመልካቹ (ያገባ ከሆነም ከነሚስቱ) ከጉባኤው አስፋፊዎች ጋር በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ይካፈላል። እነዚህ ተጓዥ ሰባኪዎች በአገልግሎት ቀናተኞች ሲሆኑ ጥሩ የማስተማር ችሎታም አላቸው፤ ይህም በመንጋው ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ሮም 12:11፤ 2 ጢሞ. 2:15) በወረዳ ሥራ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች፣ ለራሳቸው ሳይሳሱ በሚያሳዩት ፍቅር ይታወቃሉ። ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ሌሎችን ያገለግላሉ፤ አመቺ ባልሆነ የአየር ሁኔታ፣ ሌላው ቀርቶ አደገኛ በሆኑ አካባቢዎች እንኳ ለመጓዝ ፈቃደኞች ናቸው። (ፊልጵ. 2:3, 4) በተጨማሪም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን በመስጠት እያንዳንዱን ጉባኤ ያበረታታሉ፣ ያስተምራሉ እንዲሁም ይመክራሉ። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ የእነዚህን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መልካም ምግባር ማጤናቸውና እነሱን በእምነታቸው መምሰላቸው በእጅጉ ይጠቅማቸዋል።—ዕብ. 13:7

“ኃይለኛ ጭቅጭቅ” (የሐዋርያት ሥራ 15:37-41)

8. በርናባስ፣ ጳውሎስ ላቀረበው ሐሳብ ምን ምላሽ ሰጠ?

8 በርናባስ፣ ጳውሎስ ‘ወንድሞችን ተመልሰው እንዲጠይቁ’ ባቀረበው ሐሳብ ተስማማ። (ሥራ 15:36) ጳውሎስና በርናባስ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አብረው ሲያገለግሉ ነበር፤ የሚሄዱባቸውን አካባቢዎችም ሆነ የሚጎበኟቸውን ወንድሞችም ሁለቱም ያውቋቸዋል። (ሥራ 13:2 እስከ 14:28) በመሆኑም በዚህ ተልእኮ አብረው መሆናቸው ምክንያታዊና ተገቢ ነው። ይሁንና አንድ ችግር ተፈጠረ። የሐዋርያት ሥራ 15:37 “በርናባስ፣ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራው ዮሐንስ አብሯቸው እንዲሄድ ወስኖ ነበር” ይላል። በርናባስ እንዲሁ ሐሳብ እያቀረበ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዘመዱ የሆነው ማርቆስ በዚህ ሚስዮናዊ ጉዞ አብሯቸው እንዲሄድ “ወስኖ ነበር።”

9. ጳውሎስ በበርናባስ ሐሳብ ያልተስማማው ለምንድን ነው?

9 ጳውሎስ ግን በዚህ አልተስማማም። ለምን? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ ግን ማርቆስ በጵንፍልያ ተለይቷቸው ስለነበረና ያከናውኑት ወደነበረው ሥራ ከእነሱ ጋር ስላልሄደ አሁን አብሯቸው እንዲሄድ አልፈለገም።” (ሥራ 15:38) ጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዟቸውን ሲያደርጉ ማርቆስ አብሯቸው ነበር፤ ሆኖም እስከ ጉዞው መጨረሻ ከእነሱ ጋር አልቀጠለም። (ሥራ 12:25፤ 13:13) ማርቆስ የተለያቸው በጉዟቸው ብዙም ሳይገፉ ነው፤ ገና ጵንፍልያ እንደደረሱ፣ ተልእኮውን ዳር ሳያደርስ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። መጽሐፍ ቅዱስ ማርቆስ የተመለሰበትን ምክንያት አይገልጽም፤ ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ የማርቆስ ድርጊት ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ ሳይሰማው አልቀረም። በማርቆስ ላይ እምነት መጣል ከብዶት ሊሆን ይችላል።

10. በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ምን መራቸው? በመጨረሻስ ምን አደረጉ?

10 ይሁንና በርናባስ ማርቆስን ይዞ ለመሄድ ቆርጦ ነበር። ጳውሎስም አቋሙን ለመቀየር ፈቃደኛ አልነበረም። የሐዋርያት ሥራ 15:39 “በዚህ ምክንያት በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ” ይላል። በርናባስ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ አገሩ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ሄደ። ጳውሎስም በዕቅዱ መሠረት ጉዞውን ቀጠለ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ . . . ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለይሖዋ ጸጋ በአደራ ከሰጡት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ሄደ።” (ሥራ 15:40) ጳውሎስና ሲላስ ‘ጉባኤዎችን እያበረታቱ በሶርያና በኪልቅያ በኩል አለፉ።’—ሥራ 15:41

11. አንድ ሰው ቢያስቀይመን በመካከላችን ዘላቂ የሆነ ቅራኔ እንዳይፈጠር የትኞቹን ባሕርያት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው?

11 ይህ ዘገባ ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን መሆናችንን ያስታውሰናል። ጳውሎስና በርናባስ የበላይ አካሉ ልዩ ተወካዮች ሆነው ተሹመው ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ራሱ የዚህ የበላይ አካል አባል የመሆን መብት ሳያገኝ አይቀርም። በዚህ ወቅት ግን ጳውሎስም ሆነ በርናባስ ሰብዓዊ አለፍጽምና ለሚያሳድረው ተጽዕኖ እጅ ሰጥተዋል። ታዲያ ይህ ሁኔታ በመካከላቸው ዘላቂ የሆነ ቅራኔ እንዲፈጠር አድርጎ ይሆን? ጳውሎስና በርናባስ ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ትሑት ሰዎች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ በክርስቲያናዊ ወንድማማችነትና በይቅር ባይነት መንፈስ ችግራቸውን እንደፈቱ ጥርጥር የለውም። (ኤፌ. 4:1-3) በኋላ ላይ ጳውሎስና ማርቆስ በሌሎች ቲኦክራሲያዊ ምድቦች ላይ አብረው ሠርተዋል። aቆላ. 4:10

12. ዛሬ ያሉት የበላይ ተመልካቾች እንደ ጳውሎስና እንደ በርናባስ ምን ዓይነት ባሕርይ ሊኖራቸው ይገባል?

12 ይህ የአንድ ጊዜ ጭቅጭቅ የጳውሎስንና የበርናባስን ማንነት የሚገልጽ አይደለም። በርናባስ አፍቃሪና ለጋስ በመሆኑ ይታወቅ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ሐዋርያቱ ዮሴፍ በሚለው ስሙ ከመጥራት ይልቅ “የመጽናናት ልጅ” የሚል ትርጉም ያለው በርናባስ የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለት ነበር። (ሥራ 4:36) ጳውሎስም ቢሆን የሚታወቀው ገርና አፍቃሪ በመሆኑ ነው። (1 ተሰ. 2:7, 8) የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን ጨምሮ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስንና የበርናባስን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባል፤ ትሕትናን ለማንጸባረቅና አብረዋቸው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎችንም ሆነ መንጋውን በገርነት ለመያዝ ምንጊዜም ጥረት ማድረግ አለባቸው።—1 ጴጥ. 5:2, 3

“በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” (የሐዋርያት ሥራ 16:1-3)

13, 14. (ሀ) ጢሞቴዎስ ማን ነበር? ጳውሎስ ከእሱ ጋር የተገናኘው እንዴት ሊሆን ይችላል? (ለ) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ለየት ያለ ትኩረት የሰጠው ለምንድን ነው? (ሐ) ጢሞቴዎስ ምን ኃላፊነት ተሰጠው?

13 ጳውሎስ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው በሮም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ገላትያ ሄደ፤ በዚያ ጥቂት ጉባኤዎች ተቋቁመው ነበር። ከዚያም “ወደ ደርቤና ወደ ልስጥራ ሄደ።” ዘገባው “በዚያም አማኝ የሆነች አይሁዳዊት እናትና ግሪካዊ አባት ያለው ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር” ይላል።—ሥራ 16:1 b

14 ጳውሎስ ከጢሞቴዎስ ቤተሰብ ጋር የተገናኘው በ47 ዓ.ም. ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚያ አካባቢ በሄደበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደዚያ አካባቢ ሲመጣ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ለየት ያለ ትኩረት ሰጥቶት ነበር። ለምን? ምክንያቱም ጢሞቴዎስ በወንድሞች ዘንድ “በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት ነበር።” ጢሞቴዎስ ተወዳጅነት ያተረፈው ባደገበት ከተማ ባሉ ወንድሞች ዘንድ ብቻ አልነበረም፤ በአቅራቢያው ባሉ ሌሎች ጉባኤዎች ዘንድም መልካም ስም ነበረው። በልስጥራ፣ ከዚያም አልፎ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኘው በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች ስለ እሱ መልካም ነገሮችን ይናገሩ እንደነበር ዘገባው ይገልጻል። (ሥራ 16:2) ሽማግሌዎቹ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ከባድ ኃላፊነት ሰጡት፤ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር እየተጓዘ እንዲያገለግል ጠየቁት።—ሥራ 16:3

15, 16. ጢሞቴዎስ ጥሩ ስም ሊያተርፍ የቻለው ለምንድን ነው?

15 ጢሞቴዎስ ገና በወጣትነቱ እንዲህ ዓይነት ጥሩ ስም ያተረፈው ለምንድን ነው? ብሩህ አእምሮ፣ ጥሩ ቁመና ወይም በተፈጥሮ ያገኛቸው ግሩም ተሰጥኦዎች ስላሉት ነው? ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንዲህ ባሉት ነገሮች ይማረካሉ። ነቢዩ ሳሙኤል እንኳ በአንድ ወቅት በውጫዊ ገጽታ ተታልሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶታል፦ “አምላክ የሚያየው ሰው በሚያይበት መንገድ አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው።” (1 ሳሙ. 16:7) ጢሞቴዎስም በክርስቲያን ባልንጀሮቹ ዘንድ መልካም ስም ሊያተርፍ የቻለው በውስጣዊ ማንነቱ እንጂ በተፈጥሮ ባገኛቸው ነገሮች አልነበረም።

16 ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ፣ የጢሞቴዎስን አንዳንድ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ጠቅሷል። ጢሞቴዎስ በጎ አመለካከት እንዳለው፣ ለራሱ ቅንጣት ሳይሳሳ ለሌሎች ፍቅር እንደሚያሳይ እንዲሁም የተሰጠውን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት በትጋት እንደሚወጣ ገልጿል። (ፊልጵ. 2:20-22) በተጨማሪም ጢሞቴዎስ “ግብዝነት የሌለበት እምነት” በማሳየት ይታወቅ ነበር።—2 ጢሞ. 1:5

17. ዛሬ ያሉ ወጣቶች የጢሞቴዎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ዛሬ ያሉ ብዙ ወጣቶች አምላካዊ ባሕርያትን በማዳበር የጢሞቴዎስን ምሳሌ ይከተላሉ። በዚህም የተነሳ ገና በለጋ ዕድሜያቸው በይሖዋም ሆነ በሕዝቦቹ ዘንድ መልካም ስም ያተርፋሉ። (ምሳሌ 22:1፤ 1 ጢሞ. 4:15) ሁለት ዓይነት ሕይወት ባለመምራት ግብዝነት የሌለበት እምነት ያሳያሉ። (መዝ. 26:4) በመሆኑም እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ ብዙ ወጣቶች በጉባኤ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። የምሥራቹ አስፋፊዎች ሲሆኑ፣ ውሎ አድሮም ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ሲጠመቁ ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ ትልቅ የብርታት ምንጭ ይሆናሉ!

“በእምነት እየጠነከሩ” ሄዱ (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5)

18. (ሀ) ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ለበላይ አካሉ ምን እገዛ አበርክተዋል? (ለ) ጉባኤዎቹስ የተጠቀሙት እንዴት ነው?

18 ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ለዓመታት አብረው አገልግለዋል። የበላይ አካሉን በመወከል ከቦታ ቦታ እየተጓዙ የተለያዩ ተልእኮዎችን ፈጽመዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በየከተሞቹ ሲያልፉም በዚያ ለሚያገኟቸው ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ጉዳዩን ያሳውቋቸው ነበር።” (ሥራ 16:4) ጉባኤዎቹ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የሰጧቸውን መመሪያ እንደታዘዙ ግልጽ ነው። በውጤቱም ጉባኤዎቹ “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።”—ሥራ 16:5

19, 20. ክርስቲያኖች ‘አመራር የሚሰጧቸውን’ ወንድሞች መታዘዝ ያለባቸው ለምንድን ነው?

19 በተመሳሳይም ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ‘በመካከላቸው ሆነው አመራር የሚሰጧቸውን’ ወንድሞች መታዘዛቸው በረከት አስገኝቶላቸዋል። (ዕብ. 13:17) የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው፤ በመሆኑም ክርስቲያኖች “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረው መመገባቸው ወሳኝ ነው። (ማቴ. 24:45፤ 1 ቆሮ. 7:29-31) ይህም ከመንፈሳዊ አደጋና ከዓለም እድፍ ይጠብቃቸዋል።—ያዕ. 1:27

20 ጳውሎስ፣ በርናባስ፣ ማርቆስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሌሎች ቅቡዓን ሽማግሌዎች ፍጹማን አልነበሩም፤ ዛሬ ያሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም እንደዛው፤ ይህ የበላይ አካል አባላትንም ይጨምራል። (ሮም 5:12፤ ያዕ. 3:2) ይሁንና የበላይ አካሉ የአምላክን ቃልና ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ በጥንቃቄ ይከተላል፤ በመሆኑም እምነት የሚጣልበት ነው። (2 ጢሞ. 1:13, 14) ጉባኤዎችም ይህን በማድረጋቸው እየተጠናከሩና በእምነት እየጎለበቱ ሄደዋል።

a ማርቆስ ብዙ መብቶች አግኝቷል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።