በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ አለብህ?

ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ አለብህ?

ምዕራፍ 30

ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ አለብህ?

1. (ሀ) ምን ሁለት መንገዶች ተከፍተውልሃል? (ለ) ትክክለኛውን መንገድ እንዴት ለመምረጥ ትችላለህ?

ይሖዋ አምላክ አንድ አስደናቂ ነገር አቅርቦልሃል። ጽድቅ በሚሰፍንበት በአዲሱ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወትን እንድታገኝ ጥሪ አቅርቦልሃል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ በሕይወት መኖርህ አሁን የአምላክን ፈቃድ በማድረግህ ላይ የተመካ ነው። አሁን ያለው ክፉ ዓለም፣ እንዲሁም ዓለምን ሙጥኝ ብለው የሚይዙት ሁሉ በቅርቡ ይጠፋሉ። “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:17) ስለዚህ ከሁለት መንገዶች አንዱን መምረጥ አለብህ። አንደኛው መንገድ ወደ ሞት ሌላው ደግሞ ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል። (ዘዳግም 30:19, 20) የትኛውን መንገድ ትከተላለህ?

2. (ሀ) እውነተኛ እምነት ካለህ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ትሆናለህ? (ለ) ልጅ በአንድ አፍቃሪ አባት እንደሚመካ አድርገህ በይሖዋ መተማመንህ እርሱን ለማገልገል የሚረዳህ እንዴት ነው?

2 ምርጫህ ሕይወት መሆኑን የምታሳየው እንዴት ነው? ከሁሉ በፊት በይሖዋና እርሱ በሰጠን ተስፋዎች ላይ እምነት ማድረግ አለብህ። “አምላክ እንዳለና ከልብ ለሚፈልጉት ዋጋቸውን እንደሚከፍል” የፀና እምነት አለህን? (ዕብራውያን 11:6 አዓት) አንድ ልጅ አፍቃሪና መሐሪ በሆነ አባት ላይ ትምክህቱን እንደሚጥል አንተም በአምላክ ላይ እምነትህን መጣል አለብህ። (መዝሙር 103:13, 14፤ ምሳሌ 3:11, 12) እንዲህ ዓይነቱ እምነት ካለህ ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ባታስተውላቸውም የአምላክ ምክር ጥበብ ያለበት ስለመሆኑ፣ መንገዶቹም ትክክል ስለመሆናቸው ምንም ጥርጥር አያድርብህም።

3. (ሀ) ከእምነት በተጨማሪ ምን ያስፈልጋል? (ለ) ሕይወትን እንደመረጥህ የሚያሳዩ ምን ሥራዎች አስፈላጊ ናቸው?

3 ይሁን እንጂ ከእምነት በተጨማሪ የሚያስፈልግ ሌላም ነገር አለ። ስለ ይሖዋ ያሉህን እውነተኛ ስሜቶች በተግባር ለመግለጽ የሚያስችሉ ሥራዎችም አስፈላጊ ናቸው። (ያዕቆብ 2:20, 26) ባለፉት ጊዜያት ትክክል የሆነውን ሳታደርግ በመቅረትህ አሁን እንደምታዝን ለማሳየት ያደረግሃቸው ነገሮች አሉን? ንስሐ ለመግባት ወይም ለውጦችን ለማድረግና ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ሕይወትህን ለማስማማት ተገፋፍተሃልን? ከአካሄድህ ተመልሰሃልን? ማለትም ስትከተለው የነበረው ማንኛውንም የተሳሳተ መንገድ ትተሃልን? አምላክ የሚፈልግብህንስ ነገሮች ማድረግ ጀምረሃልን? (ሥራ 3:19፤ 17:30) እንደነዚህ ያሉ ሥራዎች ሕይወትን እንደመረጥህ ያሳያሉ።

ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ

4. (ሀ) የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሊገፋፋህ የሚገባው ምንድን ነው? (ለ) አምላክን ለማገልገል ስትወስን ምን ማድረግ ተገቢ ነው?

4 የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ሕይወትን ለመምረጥ ሊያነሳሳህ የሚገባው ምንድን ነው? አድናቆት ነው። እስቲ አስበው፣ ይሖዋ ከማንኛውም ሕመም፣ ከስቃይና ከሞትም እንኳን መላቀቅ የምትችልበትን ዝግጅት አድርጎልሃል! ውድ ስጦታ የሆነውን ልጁን በመስጠት ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ማለቂያ የሌለው ሕይወት የምታገኝበትን መንገድ ከፍቶልሃል። (1 ቆሮንቶስ 6:19, 20፤ 7:23፤ ዮሐንስ 3:16) የይሖዋ ፍቅር አንተም በአጸፌታው እንድትወደው ከገፋፋህ ምን ማድረግ አለብህ? (1 ዮሐንስ 4:9, 10፤ 5:2, 3) በኢየሱስ ስም ወደ አምላክ ቀርበህ አገልጋዩና ንብረቱ ለመሆን እንደምትፈልግ በጸሎት መንገር ይኖርብሃል። በዚህ መንገድ ራስህን ለአምላክ ትወስናለህ። ይህ ራስህ የምታደርገው የግል ጉዳይ ነው፤ ሌላ ማንም ሰው በአንተ ፋንታ ሊያደርገልህ አይችልም።

5. (ሀ) ሕይወትህን ለአምላክ ከወሰንክ በኋላ ምን እንድታደርግ ይጠብቅብሃል? (ለ) በውሳኔህ ለመጽናት ምን እርዳታ ተዘጋጅቶልሃል?

5 ራስህን ለአምላክ ከወሰንክ በኋላ የገባኸውን ቃል እንድትፈጽም ይጠብቅብሃል። ስለዚህ በሕይወት እስካለህ ድረስ ይህንን ውሳኔ ወይም ውስንነት ሙጥኝ ብለህ በመያዝ ቃልህን የምትጠብቅ ሰው መሆንህን አስመስክር። (መዝሙር 50:14) ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ጋር ዘወትር ተጠግተህ የምትኖር ከሆነ እንደ አንተው ያሉ ክርስቲያኖች ፍቅራዊ ማበረታቻና ድጋፍ በደስታ በመስጠት ይረዱሃል። — 1 ተሰሎንቄ 5:11

6. (ሀ) ሕይወትህን ለአምላክ ከወሰንክ በኋላ ምን እርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ ነው? (ለ) የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው?

6 ይሁን እንጂ ለይሖዋ የእርሱ ንብረት መሆን እንደምትፈልግ በግል መንገርህ ብቻ አይበቃም። ከዚያም አልፈህ መሄድ አለብህ። አምላክን ለማገልገል ራስህን ለእርሱ እንደወሰንክ በሌሎች ፊት ማሳየት ይኖርብሃል። እንደዚያ የምታደርገው እንዴት ነው? በውሃ በመጠመቅ ነው። ይህ ዓይነቱ የውሃ ጥምቀት አንድ ሰው ሕይወቱን ለይሖዋ መወሰኑንና አሁን ፈቃዱን ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን በይፋ የሚያሳይበት መንገድ ነው።

7. (ሀ) ኢየሱስ ለክርስቲያኖች ምን ምሳሌ ትቶላቸዋል? (ለ) ኢየሱስ ያዘዘው ጥምቀት የሕፃናት ጥምቀት ያልሆነው ለምንድን ነው?

7 ጥምቀት ከእኛ የሚፈለግ ትልቅ ጉዳይ ለመሆኑ ኢየሱስ የተወልን ምሳሌ ማስረጃ ነው። ኢየሱስ የሰማይ አባቱን ፈቃድ ለማድረግ እንደመጣ እንዲሁ በቃሉ ብቻ ተናግሮ ዝም አላለም። (ዕብራውያን 10:7) የአምላክ መንግሥት ሰባኪ በመሆን አገልግሎት ለመጀመር ሲል ራሱን ለይሖዋ አቀረበና በውሃ ተጠመቀ። (ማቴዎስ 3:13-17) እንግዲህ ኢየሱስ ምሳሌ ስለተወልን በዛሬው ጊዜ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕይወታቸውን ለይሖዋ የሚወስኑ ሁሉ መጠመቅ አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 2:21፤ 3:21) እንዲያውም ኢየሱስ ተከታዮቹ ከአሕዛብ ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና ከዚያ በኋላ እነዚህን አዳዲስ ደቀ መዛሙርት እንዲያጠምቁ አዟቸዋል። ይህ የሕፃናት ጥምቀት አይደለም። ይሖዋን ለማገልገል የወሰኑ አማኞች የሚጠመቁበት ጥምቀት ነው። — ማቴዎስ 28:19፤ ሥራ 8:12

8. ለመጠመቅ ከፈለግህ በጉባኤ ውስጥ ይህንን ማሳወቅ ያለብህ ለማን ነው? ለምንስ?

8 ይሖዋን ለማገልገል ብትወስንና ለመጠመቅ ብትፈልግ ምን ማድረግ አለብህ? አንተ በምትሰበሰብበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ላለው መሪ የበላይ ተመልካች ምኞትህን ማሳወቅ አለብህ። እርሱም ከሌሎች የጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ሆኖ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል ልታውቃቸው የሚያስፈልጉህን ነጥቦች በጥያቄ ይከልሱልሃል። ከዚያ በኋላ እንድትጠመቅ ዝግጅት ሊደረግልህ ይችላል።

ዛሬ አምላክ ለአንተ ያለው ፈቃድ

9. ኖኅ ከጥፋት ውሃ በፊት ያደረገው አሁን ደግሞ አንተ እንድታደርገው አምላክ ፈቃዱ የሆነው ሥራ ምንድን ነው?

9 ከጥፋት ውሃ በፊት “የጽድቅ ሰባኪው” ኖኅ ስለመጪው ጥፋት እንዲያስጠነቅቅና ብቸኛ የመዳን ሥፍራ ወደሆነው መርከብ ሰዎችን እንዲያመለክት ይሖዋ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 24:37-39፤ 2 ጴጥሮስ 2:5፤ ዕብራውያን 11:7) በአሁኑም ጊዜ ተመሳሳይ የስብከት ሥራ እንድትሠራ የአምላክ ፈቃድ ነው። ኢየሱስ ስለ ጊዜያችን የሚከተለውን አስቀድሞ ተናግሯል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ሌሎች ሰዎች ከአሁኑ ሥርዓት ጥፋት ተርፈው ለዘላለም እንዲኖሩ ከተፈለገ አንተ ስለ አምላክ ዓላማዎች የተማርካቸውን ነገሮች ማወቅ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) ይህንን ሕይወት ሰጭ የሆነ እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ልብህ አይገፋፋምን?

10. (ሀ) ለሰዎች ያለን ፍቅር የትኛውን የኢየሱስ ምሳሌ እንድንከተል ሊያደርገን ይገባል? (ለ) አብዛኛው የስብከቱ ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው?

10 የክርስቶስን ምሳሌ ተከተል። ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት ሊያዳምጡ የሚችሉ ሰዎችን ለመፈለግ ወደ እነርሱ ሄደ እንጂ ወደ እርሱ እንዲመጡ ቁጭ ብሎ አልጠበቃቸውም። በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ እንደዚሁ እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:19፤ ሥራ 4:13፤ ሮሜ 10:10-15) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የክርስቶስን መመሪያና ምሳሌ በመከተል ወደ ቤታቸው ሄደው ሰዎችን አነጋግረዋል። የመንግሥቱን መልእክት ይዘው ‘ከቤት ወደ ቤት’ ሄደዋል። (ሉቃስ 10:1-6፤ ሥራ 20:20) በዛሬውም ዘመን እውነተኛ ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑበት ዋነኛው መንገድ ይህ ነው።

11. (ሀ) ስለ አምላክ መንግሥት መስበኩ ድፍረትን የሚጠይቀው ለምንድን ነው? ሆኖም ለምን መፍራት አይገባንም? (ለ) እኛ የምንሠራውን ሥራ ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?

11 ይህንን ሥራ ለማከናወን ድፍረት ያስፈልጋል። ሰይጣንና የእርሱ ዓለም የመጀመሪያዎቹን የክርስቶስ ተከታዮች ስብከት ለማቆም እንደሞከሩ ሁሉ አንተም እንዳትሰብክ ለማቆም እንደሚሞክሩ የተረጋገጠ ነው። (ሥራ 4:17-21፤ 5:27-29, 40-42) ሆኖም መፍራት አያስፈልግህም። ይሖዋ እነዚያን የመጀመሪያ ክርስቲያኖች እንደደገፋቸውና እንዳበረታቸው ሁሉ ለአንተም ልክ እንደዚያው ያደርግልሃል። (2 ጢሞቴዎስ 4:17) ስለዚህ አይዞህ በርታ! ሕይወት አድን በሆነው የስብከትና የማስተማር ሥራ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ይሖዋንና እንደ አንተው ያሉትን ሰዎች እንደምትወድ አረጋግጥ። (1 ቆሮንቶስ 9:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16) ይሖዋ ዋጋህን አብዝቶ ይከፍልሃል እንጂ ሥራህን አይረሳውም። — ዕብራውያን 6:10-12፤ ቲቶ 1:2

12. ከሎጥ ሚስት ምን ለመማር እንችላለን?

12 ይህ አሮጌ ሥርዓት ሊሰጥህ የሚችል እውነተኛ ዋጋ ያለው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ጀርባህን ስለሰጠኸው የቀረብኝ ነገር ይኖራል ብለህ ፈጽሞ አታስብ። “የሎጥን ሚስት አስቧት” ሲል ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 17:32) እርሷና ቤተሰቧ ከሰዶም ካመለጡ በኋላ ትተዋቸው ለወጡት ነገሮች በመጓጓት ወደኋላ ዘወር ብላ ተመለከተች። ልቧ የት ላይ እንዳረፈ አምላክ ተመለከተ፤ ስለዚህም የጨው ዐምድ ሆነች። (ዘፍጥረት 19:26) እንደ ሎጥ ሚስት አትሁን! ወደፊት ቀጥ ብለህ በመመልከት በአዲሱ የአምላክ የጽድቅ ሥርዓት ውስጥ በሚገኘው “እውነተኛ ሕይወት” ላይ ዓይኖችህን ትከል። — 1 ጢሞቴዎስ 6:19

ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ምረጥ

13. ሁላችንም ማድረግ የሚገባንን ምርጫ ኢየሱስ ከፊታችን ያስቀመጠልን እንዴት ነው?

13 እንደ እውነቱ ከሆነ ያሉት ምርጫዎች ሁለት ብቻ ናቸው። ክርስቶስ ሁኔታውን ከሁለት መንገዶች መካከል አንዱን ከመምረጥ ጋር አመሳስሎታል። አንደኛው መንገድ “ሰፊና ትልቅ” ነው በማለት ኢየሱስ ተናገረ። በዚያ ላይ የሚጓዙት መንገደኞች ራሳቸውን እንዲያስደስቱ ነፃነት አላቸው። ሌላው መንገድ ግን “ጠባብ” ነው። አዎ፤ በጠባቡ መንገድ የሚጓዙት ሰዎች የአምላክን መመሪያዎችና ሕጎች እንዲያከብሩ ይፈለግባቸዋል። ኢየሱስ እንደተናገረው አብዛኞቹ ሰዎች በሰፊው መንገድ ሲጓዙ ጥቂቶች ብቻ ጠባቡን መንገድ መርጠዋል። አንተስ የትኛውን መንገድ ትመርጣለህ? ምርጫ በምታደርግበት ጊዜ አንድ ቁምነገር አስታውስ:- ሰፊው መንገድ ገደል ወደሆነው ማለቂያው በድንገት ይደርሳል፤ ጥፋት ዱብ ይላል! በሌላ በኩል ግን ጠባቡ መንገድ ወደ አዲሱ የአምላክ ሥርዓት በቀጥታ ያስገባሃል። ወደዚያ ከገባህ በኋላ ምድርን ለዘላለም በደስታ መኖር የሚቻልባት ታላቅ ገነት ለማድረግ በሚካሄደው ሥራ ተካፋይ ለመሆን ትችላለህ። — ማቴዎስ 7:13, 14

14. ከጥፋት ተርፈህ ወደ አዲሱ የአምላክ ሥርዓት ለመግባት የምን ክፍል መሆን ያስፈልግሃል?

14 በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት ማግኘት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ ብለህ አትደምድም። ያለው መንገድ አንድ ብቻ ነው። ከጥፋት ውሃ የተረፈው አንድ መርከብ ብቻ ነበር እንጂ የተለያዩ ጀልባዎች አልነበሩም። በፍጥነት እየመጣ ያለውን “ታላቅ መከራ” የሚያልፈውም አንድ ድርጅት ብቻ ይኸውም የሚታየው የአምላክ ድርጅት ብቻ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ ግብ ያደርሳሉ የሚለው አባባል ትክክል አይደለም። (ማቴዎስ 7:21-23፤ 24:21) የአምላክን የዘላለም ሕይወት በረከት ለማግኘት የእርሱን ፈቃድ እያደረግህ የይሖዋ ድርጅት ክፍል መሆን አለብህ። — መዝሙር 133:1-3

15. (ሀ) በየቀኑ ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) ሕልም ያልሆነው ተስፋ ምንድን ነው?

15 እንግዲያው አምላክ ቃል የገባልን የአዲሱ የነገሮች ሥርዓት ሥዕል በአእምሮህና በልብህ ውስጥ ሁልጊዜ ደማቅ ይሁን። ይሖዋ አምላክ ስላዘጋጀልህ ታላቅ ሽልማት ይኸውም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚገኘው ሕይወት በየቀኑ አስብ። ይህ ሕልም አይደለም፤ እውነተኛ ነገር ነው! “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ . . . ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። — መዝሙር 37:29, 34

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 251 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን ለይሖዋ መወሰን . . . ከዚያም መጠመቅ

[በገጽ 253 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የሎጥን ሚስት አስቧት”

[በገጽ 254 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አዲሱ የአምላክ ሥርዓት በአእምሮህና በልብህ ውስጥ ሁልጊዜ ደማቅ ሆኖ ይታይህ