በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ ነው?

ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ ነው?

ምዕራፍ 9

ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ ነው?

1. ሃይማኖቶች ስለ ሲኦል ምን ብለው ያስተምራሉ?

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲኦል ሰዎች የሚሰቃዩበት ቦታ ነው ብሎ ሃይማኖታቸው አስተምሯቸዋል። በኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ላይ በተገለጸው መሠረት “የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኦል . . . ዘላለማዊ ነው፤ ስቃዩም ፍጻሜ የለውም ብላ ታስተምራለች።” ኢንሳይክሎፔድያው በመቀጠል ይህ የካቶሊክ ትምህርት “ወግ አጥባቂ በሆኑት በብዙ ፕሮቴስታንት ቡድኖች አሁንም ይታመንበታል” ብሏል። ሂንዱስቶች፣ ቡድሂስቶችና መሐመዳውያን ሲኦል የመሰቃያ ቦታ እንደሆነ አድርገው ያስተምራሉ። ይህ ዓይነት ትምህርት የተሰጣቸው ሰዎች ሲኦል እንደዚህ ያለ መጥፎ ቦታ ከሆነ ስለ እርሱ ማውራት አንፈልግም ብለው ብዙ ጊዜ መናገራቸው የሚያስገርም አይደለም።

2. ልጆችን በእሳት ስለ ማቃጠል አምላክ ምን ተሰምቶት ነበር?

2 ይህ ነገር “ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ እንደዚህ የመሰለ የስቃይ ቦታ ፈጥሯልን?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ለመልሱ ፍንጭ እንዲሆን እስራኤላውያን በዙሪያቸው የነበሩትን ሕዝቦች ምሳሌ ተከትለው ልጆቻቸውን በእሳት ማቃጠል ሲጀምሩ አምላክ የነበረው አስተያየት ምን ነበር? ብለን እንጠይቃለን። እርሱ በቃሉ እንዲህ ሲል ይገልጽልናል:- “እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መስገጃዎች ሠርተዋል።”— ኤርምያስ 7:31

3. አምላክ ሰዎችን ያሠቃያል ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ የማይሆነውና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የማይኖረው ለምንድን ነው?

3 እስቲ አስበው። ሰዎችን በእሳት ላይ የመጥበሱ ሐሳብ በአምላክ ልብ ውስጥ ፈጽሞ የሌለ ከሆነ እርሱን ለማያገለግሉት እንደዚህ ያለ እሳታማ ሲኦል ፈጥሯል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃልን? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) አፍቃሪ የሆነው አምላክ በእርግጥ ሰዎችን ለዘላለም ያሰቃያልን? አንተ ብትሆን ኖሮ ይህን ታደርግ ነበርን? ስለ አምላክ ፍቅር ማወቃችን ሲኦል ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ወደ ቃሉ ዘወር እንድንል ሊገፋፋን ይገባል። ወደዚያ የሚሄዱት እነማን ናቸው? ለምን ያህል ጊዜስ?

ሺኦልና ሐዴስ

4. (ሀ) “ሲኦል” ወይም ሄል ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ምንድን ናቸው? (ለ) በኪንግ ጄምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ ሺኦል እንዴት ተብሎ ተተርጉሟል?

4 የዌብስተር መዝገበ ቃላት “ሄል” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በዕብራይስጥ ሺኦል ለሚለውና በግሪክኛ ሐዴስ ለሚለው ቃል እኩያ መሆኑን ይናገራል። በጀርመንኛ በተተረጐሙ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ “ሄል” በሚለው ቃል ፋንታ “ሆኤል” የሚለው ቃል ገብቷል። በፖርቹጊዝ ቋንቋ ኢንፌርኖ፣ በስፓኝ ኢንፊየርኖ፣ በፈረንሳይኛ ደግሞ አንፈር የሚሉት ቃላት ተሠርቶባቸዋል። የኦቶራይዝድ ቨርሽን ወይም የኪንግ ጄምስ ቨርሽን የእንግሊዝኛ ተርጓሚዎች ሺኦልን 31 ጊዜ “ሄል” (ሲኦል)፣ 31 ጊዜ መቃብር፣ 3 ጊዜ ደግሞ “ጉድጓድ” ብለው ተርጉመውታል። የካቶሊኩ ዱዌይ ቨርሽን ሺኦልን 64 ጊዜ “ሄል” (ሲኦል) ብሎ ተርጉሞታል። በተለምዶ “አዲስ ኪዳን” እየተባሉ በሚጠሩት የክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ ሐዴስ የሚለው ቃል በሚገኝባቸው 10 ቦታዎች ሁሉ ላይ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን “ሄል” ብሎ ተርጉሞታል።— ማቴዎስ 11:23፤ 16:18፤ ሉቃስ 10:15፤ 16:23፤ ሥራ 2:27, 31፤ ራእይ 1:18፤ 6:8፤ 20:13, 14

5. ሺኦልንና ሐዴስን በሚመለከት ምን ጥያቄ ይነሣል?

5 አሁን የሚነሣው ጥያቄ:- “ሺኦል ወይም ሐዴስ ምን ዓይነት ቦታ ነው?” የሚል ነው። በኪንግ ጄምስ ቨርሽን ላይ ሺኦል የሚለው አንድ የዕብራይስጥ ቃል በሦስት የተለያዩ መንገዶች መተርጐሙ ሄል (ሲኦል)መቃብርና ጉድጓድ የሚሉት ቃላት አንድን ዓይነት ነገር የሚያመለክቱ መሆናቸውን ያሳያል። ሲኦል የሰውን ዘር ተራ መቃብር የሚያመለክት ከሆነ ማሠቃያ እሳት የሚል ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ታዲያ ሺኦልና ሐዴስ መቃብር ማለት ናቸው ወይስ መሠቃያ ቦታ?

6. (ሀ) ሺኦልና ሐዴስ አንድ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በሐዴስ ውስጥ የነበረ መሆኑ ምን ያሳያል?

6 ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ሺኦል የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና ሐዴስ የሚለው የግሪክኛ ቃል አንድ መሆናቸውን ግልጽ እናድርግ። በእንግሊዝኛው የአሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን ላይ በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን መዝሙር 16:10⁠ንና በክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ሥራ 2:31⁠ን ማስተያየት ይህንን ግልጽ ያደርገዋል። እነዚህንም ጥቅሶች በሚቀጥለው ገጽ ላይ ልትመለከታቸው ትችላለህ። ሺኦል ከሚገኝበት ከመዝሙር 16:10 ላይ በመጥቀስ ሥራ 2:31 ሐዴስ በሚለው ቃል ይጠቀማል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዴስ ወይም በሲኦል እንደነበረ አስተውል። አምላክ ኢየሱስን በእሳታማ ሲኦል ውስጥ አሰቃይቶታል ብለን ልናምን ነውን? በፍጹም ሊሆን አይችልም! በቀላል አነጋገር ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ ነበር ማለት ነው።

7, 8. ስለ ያዕቆብና ስለ ልጁ ስለ ዮሴፍ እንዲሁም ስለ ኢዮብ የተገለጸው ነገር ሺኦል የመሠቃያ ቦታ አንዳልሆነ እንዴት ያረጋግጣል?

7 ያዕቆብ ሞቷል ብሎ ላሰበው ለሚወደው ልጁ ለዮሴፍ ሲያለቅስ:- “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ (ሲኦል) አዝኜ እወርዳለሁ” አለ። (ዘፍጥረት 37:35 የ1879 እትም) ይሁን እንጂ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን እዚህ ላይ የሚገኘውን ሺኦል የሚለውን ቃል “መቃብር” ብሎ ሲተረጉመው ዱዌይ ቨርሽን ደግሞ “ሄል” ብሎ ተርጉሞታል። እስቲ አሁን ቆም በልና ትንሽ አስብበት። ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍ ለዘላለም እየተሠቃየ ለመኖር ወደ ሥቃይ ቦታ ሄደ ብሎ አምኖ ነበርን? ከእርሱስ ጋር ለመገናኘት ወደዚህ ቦታ ለመሄድ ፈልጎ ነበርን? ወይስ ከዚያ ይልቅ ያዕቆብ የሚወደው ልጁ እንደ ሞተና በመቃብር ውስጥ እንዳለ በማሰብ ራሱም መሞት ፈልጎ ነበር?

8 አዎ፤ ጥሩ ሰዎች ወደ መጽሐፍ ቅዱሱ ሲኦል ይሄዳሉ። ለምሳሌ ያህል ጥሩ ሰው የነበረውና ብዙ ስቃይ የደረሰበት ኢዮብ “በሲኦል (“በመቃብር” ኪንግ ጄምስ ቨርሽን፣ “ሄል” ዱዌይ ቨርሽን፤ “የሙታን ዓለም” የ1980 ትርጉም) ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ!” በማለት ወደ አምላክ ጸሎት አቅርቦ ነበር። (ኢዮብ 14:13) እስቲ አስበው፤ ሺኦል የእሳትና የመሰቃያ ቦታ ቢሆን ኖሮ ኢዮብ አምላክ እስከሚያስበው ድረስ ወደዚህ ቦታ ሄዶ ለመቆየት ይመኝ ነበርን? በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢዮብ ስቃዩ እንዲቆምለት ሞቶ ወደ መቃብር ለመሄድ ፈልጎ ነበር።

9. (ሀ) በሺኦል ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) ስለዚህ ሺኦልና ሐዴስ ምንድን ናቸው?

9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሺኦል በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ከእሳት፣ ከእንቅስቃሴ ወይም ከመሰቃየት ጋር በተያያዘ ሁኔታ በፍጹም ተገልጾ አያውቅም። ከዚያ ይልቅ ብዙውን ጊዜ የሚያያዘው ከሞትና ከበድንነት ጋር ነው። ለምሳሌ ያህል ስለ መክብብ 9:10 አስብ። እንዲህ ይነበባል:- “አንተ በምትሄድበት በሲኦል (“በመቃብር” ኪንግ ጄምስ ቨርሽን፣ “በሄል” ዱዌይ ቨርሽን፤ “የሙታን ዓለም” የ1980 ትርጉም) ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።” ስለዚህ መልሱ በጣም ግልጽ ሆኗል። ሺኦልና ሐዴስ የመሰቃያ ቦታን ሳይሆን የሁሉንም የሰው ዘር ተራ መቃብር ያመለክታሉ። (መዝሙር 139:8) ጥሩ ሰዎችም ሆኑ መጥፎ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ወደሚናገርለት ሲኦል ይሄዳሉ።

ከሲኦል መውጣት

10, 11. ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በሲኦል ውስጥ እንደነበረ አድርጎ የተናገረው ለምንድን ነው?

10 ሰዎች ከሲኦል መውጣት ይችላሉን? እስቲ የዮናስን ሁኔታ ተመልከት። አምላክ ዮናስ በውኃ ውስጥ ሰጥሞ እንዳይሞት ሲል ትልቅ ዓሣ እንዲውጠው ባደረገ ጊዜ ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ “በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦል (“በሄል” ኪንግ ጄምስና ዱዌይ ቨርሽን) ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ ቃሌንም አዳመጥህ” ብሎ ጸለየ።— ዮናስ 2:2

11 ዮናስ “በሲኦል ሆድ ውስጥ ሆኜ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? የዓሣው ሆድ እሳታማ የመሠቃያ ቦታ እንዳልነበረ የተረጋጋጠ ነው። ሆኖም ለዮናስ እንደ መቃብር ሊሆንለት ይችላል። እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።”— ማቴዎስ 12:40

12. (ሀ) በሲኦል ውስጥ ያሉት ሁሉ ሊወጡ እንደሚችሉ ምን ማረጋገጫ አለ? (ለ) “ሲኦል” ማለት “መቃብር” ስለመሆኑ ምን ተጨማሪ ማስረጃ አለ?

12 ኢየሱስ ለሦስት ቀናት ሞቶ በመቃብሩ ውስጥ ነበረ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ነፍሱ በሲኦል አልቀረችም . . . ይህን ኢየሱስን አምላክ አስነሣው” ይላል። (ሥራ 2:31, 32) በተመሳሳይም በአምላክ መሪነት ዮናስ ከሲኦል ማለትም ለእርሱ እንደ መቃብር ከነበረው ቦታ ተነሥቷል። ይህም የሆነው ዓሣው በደረቅ መሬት ላይ በተፋው ጊዜ ነበር። አዎን ሰዎች ከሲኦል መውጣት ይችላሉ! እንዲያውም ሲኦል (ሐዴስ) ሙታኑን ሁሉ በመስጠት ባዶ እንደሚሆን ልብን በደስታ የሚያሞቅ ተስፋ ተሰጥቷል። ይህንንም ራእይ 20:13⁠ን በማንበብ ለማየት እንችላለን። እርሱም እንዲህ ይላል:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም (ሐዴስም) በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ።”

ገሃነምና የእሳት ባሕር

13. በኪንግ ጄምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ “ሄል” ተብሎ የተተረጎመው የትኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ12 ቦታዎች ላይ የሚገኝ የግሪክኛ ቃል ነው?

13 ሆኖም አንድ ሰው ‘መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሳታማ ሲኦልና ስለ እሳት ባሕር ይናገራል፤ ታዲያ ይህ ሲኦል የመሰቃያ ቦታ ስለመሆኑ ማረጋገጫ አይሆንምን?’ በማለት ይቃወም ይሆናል። እውነት ነው፣ እንደ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን ያሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ስለ “እሳታማ ሲኦል” እና ‘እሳቱ ወደማይጠፋበት ወደ ሄል (ሲኦል)’ ስለመጣል ይናገራሉ። (ማቴዎስ 5:22፤ ማርቆስ 9:45) በክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ የኪንግ ጄምስ ቨርሽን ጌሄና የሚለውን ግሪክኛ ቃል ለመተርጎም “ሄል” (ሲኦል) የሚለውን ቃል የተጠቀመባቸው በጠቅላላው 12 ጥቅሶች አሉ። ሐዴስ “ሄል” ተብሎ ሲተረጎም በቀላል አነጋገር መቃብር ማለት ሆኖ ገሃነም ግን የእሳት ማሰቃያ ቦታ ነውን?

14. ገሃነም ምንድን ነው? በዚያስ ምን ይደረግ ነበር?

14 በግልጽ እንደተመልከትነው ሺኦል የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና ሐዴስ የሚለው የግሪክኛ ቃል መቃብር የሚል ትርጉም አላቸው። ታዲያ ገሀነም ማለት ምን ማለት ነው? በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ ገሀነም “የሄኖም ሸለቆ” ነው። ሄኖም እስራኤላውያን ልጆቻቸውን በእሳት መሥዋዕት ያደረጉበት ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ ያለው ሸለቆ ስም እንደሆነ አስታውስ። ጥሩ ንጉሥ የነበረው ኢዮስያስ ከጊዜ በኋላ ይህንን ሸለቆ እንደዚህ ያለው አሰቃቂ ድርጊት እንዳይፈጸምበት አድርጎት ነበር። (2 ነገሥት 23:10) ከዚያ በኋላ ቦታው ትልቅ የቆሻሻ መጣያ ሆነ።

15. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን ገሃነም ለምን ዓላማ ያገለግል ነበር? (ለ) ወደዚያስ ምን ነገሮች በፍጹም አይጣሉም ነበር?

15 ስለዚህ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ገሃነም የኢየሩሳሌም የቆሻሻ መጣያ ነበር። በዚያም ውስጥ ቆሻሻውን ለማቃጠል ድኝ በመጨመር እሳቱ ለሁልጊዜ እንዲነድ ይደረግ ነበር። የስሚዝ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ጥራዝ 1 እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ይህ ቦታ የወንጀለኞች በድንና የእንስሳት ጥምብ እንዲሁም ሁሉም ዓይነት ቆሻሻ የሚጣልበት የከተማዋ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ነበር።” ነገር ግን በዚያ ውስጥ ምንም ዓይነት ፍጥረት ከነሕይወቱ አይጣልም ነበር።

16. ገሃነም ለዘላለማዊ ጥፋት ምሳሌ ሆኖ እንዳገለገለ ምን ማስረጃ አለ?

16 የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ስለ ከተማቸው የቆሻሻ መጣያ ቦታ ያውቁ ስለነበረ ኢየሱስ ክፉ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ እባቦች የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቷቸዋል። (ማቴዎስ 23:33) ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ ይሰቃያሉ ማለቱ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ከነሕይወታቸው በዚያ ሸለቆ ውስጥ ያቃጥሉ በነበሩበት ጊዜ አምላክ ይህ አሰቃቂ አድራጎት በልቡ ያልታሰበ ነገር እንደሆነ ተናግሯል! ስለዚህ ኢየሱስ ገሃነምን ፍጹምና ዘላለማዊ ለሆነ ጥፋት ምሳሌ አድርጎ እንደ ተጠቀመበት ግልጽ ነው። እነዚያ ክፉ ሃይማኖታዊ መሪዎች ትንሣኤ የማይገባቸው መሆናቸውን ማሳየቱ ነበር። ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎችም ልክ ወደዚያ ይጣል እንደነበረው ብዙ ቆሻሻ ወደ ገሃነም የሚሄዱ ሰዎችም ለዘላለም የሚጠፉ መሆናቸውን ለመረዳት ይችሉ ነበር።

17. “የእሳት ባሕር” ምንድን ነው? ለዚህስ ምን ማስረጃ አለ?

17 ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው “የእሳት ባሕር” ምንድን ነው? ከገሃነም ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም አለው። እርሱም የሚያመለክተው እየሰሙ መሰቃየትን ሳይሆን የዘላለም ሞትን ወይም ጥፋትን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በራእይ 20:14 ላይ እንዴት እንደዚያ ብሎ እንደሚናገር ልብ በል:- “ሞትና ሲኦልም (ሄል በኪንግ ጄምስና በዱዌይ ቨርሽን) በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” አዎን፣ የእሳት ባሕር “ሁለተኛው ሞት” ማለትም ትንሣኤ የሌለው ሞት ማለት ነው። ይህ “ባሕር” ምሳሌያዊ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ሞትና ሲኦል (ሐዴስ) ወደ እርሱ ውስጥ ተጥለዋል። ሞትና ሲኦል ቃል በቃል ሊቃጠሉ አይችሉም። ሊወገዱ ወይም ሊጠፉ ግን ይችላሉ። ደግሞም ይጠፋሉ።

18. ዲያብሎስ ‘በእሳት ባሕር’ ውስጥ ለዘላለም ይሠቃያል ሲባል ምን ማለት ነው?

18 ምናልባት አንድ ሰው ዲያብሎስ በእሳት ባሕር ውስጥ ለዘላለም እንደሚሰቃይ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ይል ይሆናል። (ራእይ 20:10) ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ የወህኒ ጠባቂዎች አንዳንድ ጊዜ “የሚያሠቃዩ” ተብለው ይጠሩ ነበር። ኢየሱስ በአንዱ ምሳሌው ውስጥ ስለ ተጠቀሰ ስለ አንድ ሰው ሲናገር “ጌታውም ተቆጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው” ብሏል። (ማቴዎስ 18:34) ወደ “እሳት ባሕር” ውስጥ የሚጣሉት ትንሣኤ ወደማይገኝበት ወደ “ሁለተኛው ሞት” ውስጥ ስለሚገቡ በሞት ለዘላለም ታስረዋል ሊባል ይቻላል። እነርሱም በአሳሪዎቹ ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ ያህል ለሁልጊዜ ሞተው ይቀራሉ። አስቀድመን እንደተመለከትነው አንድ ሰው ሲሞት ሙሉ በሙሉ ከኅልውና ውጭ ስለሚሆን ክፉዎች ቃል በቃል አይሰቃዩም። ምንም ነገር አይታወቃቸውም።

ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር

19. ኢየሱስ ስለ ሀብታሙ ሰውና ስለ አልዓዛር የተናገረው ነገር ምሳሌ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

19 ታዲያ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ውስጥ በአንዱ ላይ “ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋውም ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም (በሐዴስ) በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ፤ አልዓዛርንም በእቅፉ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ምን ማለቱ ነበር? (ሉቃስ 16:19–31) ቀደም ብለን ሐዴስ የመሠቃያ ቦታን ሳይሆን የሰውን ልጆች መቃብር እንደሚያመለክት ስለተረዳን እዚህ ላይ ኢየሱስ ምሳሌ እየተናገረ እንዳለ ግልጽ ነው። ይህ እውነተኛ ታሪክ ሳይሆን ምሳሌ ስለመሆኑ የሚከተሉትን ተጨማሪ ማስረጃዎች ተመልከት:- ሲኦልና ሰማይ እንደዚህ ያለ የንግግር ልውውጥ ለማድረግ ይህን ያህል ቅርብ ለቅርብ ናቸውን? ከዚህም በላይ ሀብታሙ ሰው ቃል በቃል በሚነድ ባሕር ውስጥ ከነበረ አብርሃም አልዓዛርን በመላክ በጣቱ ጫፍ በሚወስደው የውኃ ጠብታ ምላሱን እንዴት ሊያበርድለት ይችላል? ታዲያ ኢየሱስ በምሳሌ እየገለጸ የነበረው ነገር ምንድን ነው?

20. በምሳሌው ውስጥ (ሀ) የሀብታሙ ሰው (ለ) የአልዓዛር (ሐ) የሁለቱ ሞት (መ) የሀብታሙ ሰው ሥቃይ ትርጉም ምንድን ነው?

20 በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው ሀብታሙ ሰው ኢየሱስን አንቀበልም ያሉትን በኋላም የገደሉትን ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ የሃይማኖት መሪዎች ለማመልከት የቆመ ነው። አልዓዛር የአምላክን ልጅ የተቀበሉትን ተራ ሰዎች ያመለክታል። የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ሞት በሁኔታቸው ላይ ለውጥ መደረጉን ያመለክታል። ይህ ለውጥ የተደረገው የተናቁትን አልዓዛርን የሚመስሉ ሰዎች ኢየሱስ በመንፈሳዊ በመገባቸው ጊዜ ነበር። በዚህ መንገድ የታላቁን አብርሃም የይሖዋ አምላክን ሞገስ አገኙ። በዚሁ ጊዜም ሐሰተኞቹ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክን ሞገስ በማግኘት በኩል “ሞቱ።” ከአምላክ ሞገስ ውጭ በመጣላቸውም የክርስቶስ ተከታዮች ክፉ ሥራቸውን ሲያጋልጡባቸው ሥቃይ ደረሰባቸው። (ሥራ 7:51-57) እንግዲያው ይህ ምሳሌ አንዳንድ ሙታን ቃል በቃል በእሳታማ ሲኦል እንደሚቃጠሉ አያስተምርም።

ከዲያብሎስ የመነጩ ትምህርቶች

21. (ሀ) ዲያብሎስ ምን ውሸቶችን አስፋፍቷል? (ለ) የመንጽሔ ትምህርት ሐሰት ስለመሆኑ እርግጠኛ ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

21 ለሔዋን “ሞትን አትሞቱም” ብሎ የነገራት ዲያብሎስ ነው። (ዘፍጥረት 3:4፤ ራእይ 12:9) እርስዋ ግን ሞተች፤ ከአካሏ ውስጥ የትኛውም ክፍል ቢሆን ሕያው ሆኖ አልቀጠለም። ከሞት በኋላ ነፍስ መኖሯን ትቀጥላለች የሚለው ውሸት የመነጨው ከዲያብሎስ ነው። የክፉ ሰዎች ነፍሳት በሲኦል ወይም በመንጽሔ ይሰቃያሉ የሚለውም ቢሆን ዲያብሎስ ያስፋፋው ውሸት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ሙታን ምንም እንደማይሰሙ ስለሚያሳይ እነዚህ ትምህርቶች እውነት ሊሆኑ አይችሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ “መንጽሔ” የሚለው ቃልም ሆነ ሐሳቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም።

22. (ሀ) ከዚህ ምዕራፍ ምን ተምረናል? (ለ) ይህ እውቀት አንተን የነካህ እንዴት ነው?

22 ሲኦል (ሺኦል ወይም ሐዴስ) ሙታን በተስፋ የሚያርፉበት ቦታ መሆኑን ቀደም ብለን ተመልክተናል። ጥሩም ሆኑ መጥፎ ሰዎች ትንሣኤን ለመጠበቅ ወደዚያው ይሄዳሉ። በተጨማሪም ገሃነም የመሠቃያ ቦታ ማለት እንዳልሆነ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የዘላለማዊ ጥፋት ምሳሌ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ተምረናል። በተመሳሳይም “የእሳት ባሕር” ቃል በቃል እሳታማ የሆነን ቦታ ሳይሆን ምንም ትንሣኤ የማይገኝበትን ‘ሁለተኛውን ሞት’ ያመለክታል። ሲኦል የመሠቃያ ቦታ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እንደዚህ ያለው ሐሳብ በአምላክ አእምሮና ልብ ውስጥ ፈጽሞ ያልነበረ ነገር ነው። በተጨማሪም አንድ ሰው ለጥቂት ዓመታት በምድር ላይ በሠራው ኃጢአት ምክንያት ለዘላለም እንዲሠቃይ ማድረጉ ከፍትሕ ጋር የሚቃረን ነገር ነው። ስለ ሙታን እውነቱን ማወቁ እንዴት ጥሩ ነው! ይህ እውቀት አንድን ሰው ከፍርሃትና ከአጉል እምነት ነፃ ሊያደርገው ይችላል።— ዮሐንስ 8:32

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 83 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ሺኦል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና “ሐዴስ” የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉማቸው አንድ ነው።

መዝሙር 16:10

ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤ ፲ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ደስታን አጠገብኸኝ፤ በቀኝህም የዘለላለም

በዕብራይስጡ ላይ “ሺኦል” ይላል

ሥራ 2:31

፴፩ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፤ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው

በግሪክኛው ላይ “ሔድስ” ይላል

[በገጽ 84, 85 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮናስ ዓሣው ከዋጠው በኋላ “በሲኦል ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ” ያለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 86 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገሃነም ከኢየሩሳሌም ውጭ የሚገኝ ሸለቆ ነበር። ለዘላለማዊ ሞት ምሳሌ ሆኖ ተሠርቶበታል።