በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአሥሩ ትእዛዛት ሥር ነንን?

በአሥሩ ትእዛዛት ሥር ነንን?

ምዕራፍ 24

በአሥሩ ትእዛዛት ሥር ነንን?

1. ሙሴ ምን ሕግ ተቀብሎ ለሕዝቡ አስተላለፈ?

ይሖዋ አምላክ የትኞቹን ሕጎች እንድንታዘዝ ይፈልጋል? መጽሐፍ ቅዱስ “የሙሴ ሕግ” ወይም አንዳንድ ጊዜ “ሕጉ” ብሎ የሚጠራውን መጠበቅ አለብንን? (1 ነገሥት 2:3፤ ቲቶ 3:9) ይህንን ሕግ የሰጠው ይሖዋ ስለሆነ “የይሖዋ ሕግ” ተብሎም ይጠራል። (1 ዜና 16:40) ሙሴ ያደረገው ከይሖዋ የተቀበለውን ሕግ ለሕዝቡ ማስተላለፍ ብቻ ነበር።

2. ይህ ሕግ ምን ይዟል?

2 የሙሴ ሕግ አሥሩን ዋና ዋና ሕጎች ጨምሮ በጠቅላላው 600 ሕጎችን ወይም ትእዛዞችን ይዟል። ሙሴ እንደተናገረው :- “ታደርጉትም ዘንድ [ይሖዋ (አዓት)] ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ፤ በሁለቱም ድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው።” (ዘዳግም 4:13፤ ዘፀአት 31:18) ይሁን እንጂ ይሖዋ አሥሩን ትእዛዛት ጨምሮ ጠቅላላውን ሕግ የሰጠው ለማን ነበር? ሕጉ የተሰጠው ለጠቅላላው የሰው ዘር ነበርን? የሕጉስ ዓላማ ምን ነበር?

ለአንድ ልዩ ዓላማ ለእስራኤል ተሰጠ

3. ሕጉ የተሰጠው ለእስራኤል ብቻ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

3 ሕጉ የተሰጠው ለሁሉም የሰው ዘሮች አልነበረም። ይሖዋ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ተብለው ከተጠሩት የያዕቆብ ዘሮች ጋር ቃል ኪዳን ወይም ውል አደረገ። ይሖዋ ሕጎቹን የሰጠው ለዚህ ሕዝብ ብቻ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በዘዳግም 5:1-3 እና በመዝሙር 147:19, 20 ላይ ይህንን ግልጽ ያደርገዋል።

4. ሕጉ ለእስራኤል ሕዝብ ለምን ተሰጠ?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ “ታዲያ ሕግ ለምን ተሰጠ” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። አዎ፤ ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤል የሰጠው ለምን ዓላማ ነበር? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመልስልናል:- “የተስፋ ቃል የተሰጠበት ዘር እስኪመጣ ድረስ መተላለፍን በግልጽ ለማሳየት ነው፤ ስለዚህም ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚመራን ሞግዚታችን [ወይም አስተማሪያችን] ሆኖአል።” (ገላትያ 3:19-24 አዓት) የሕጉ ልዩ ዓላማ የእሥራኤልን ሕዝብ ንጹሕ አድርጎ ለመጠበቅና ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ሕዝቡ እርሱን ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ እየመራ እንዲያቆያቸው ነበር። ሕጉ የሚያዛቸው ብዙ መስዋዕቶች እስራኤላውያን ኃጢአተኞች እንደሆኑና አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያስታውሷቸው ነበሩ። — ዕብራውያን 10:1-4

“ክርስቶስ የሕግ ፍፃሜ ነው”

5. ክርስቶስ መጥቶ ስለ እኛ ከሞተ በኋላ ሕጉ ምን ሆነ?

5 ኢየሱስ በሚወለድበት ጊዜ መልአኩ እንዳስታወቀው ያ ተስፋ የተሰጠበት አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። (ሉቃስ 2:8-14) ስለዚህ ክርስቶስ መጥቶ ፍጹም ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ በሰጠ ጊዜ ሕጉ ምን ሆነ? ተወገደ። “ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም” ሲል ጳውሎስ ገልጿል። (ገላትያ 3:25) የሕጉ መወገድ ለእስራኤላውያን ዕረፍት ነበር። ሁሉም ቢሆኑ ያንን ሕግ አሟልተው መጠበቅ ስላልቻሉ ኃጢአተኞች መሆናቸውን አሳይቷቸዋል። “ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን” ሲል ጳውሎስ ተናግሯል። (ገላትያ 3:10-14) ይህም በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነው” ይላል። — ሮሜ 10:4፤ 6:14

6. (ሀ) ሕጉ ወደ ፍጻሜው ከደረሰ በኋላ እስራኤላውያን በሆኑትና ባልሆኑት ላይ ምን ውጤት አመጣ? ለምንስ? (ለ) ይሖዋ በሕጉ ላይ ምን እርምጃ ወሰደ?

6 ሕጉ በእስራኤላውያንና በሕግ ሥር ባልነበሩት ሌሎች አሕዛብ መካከል እንደ አጥር ወይም እንደ “ግድግዳ” ሆኖ አገልግሏል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ “በአዋጅ የተነገሩትን የትእዛዛት ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው [አፍርሷል]፤ ይህም ከሁለታቸው [ከእስራኤላውያንና እስራኤላውያን ካልሆኑት] አንድን አዲስ ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ . . . ነው።” (ኤፌሶን 2:11-18) ይሖዋ አምላክ ራሱ በሙሴ ሕግ ላይ ስለወሰደው እርምጃ እንደሚከተለው እናነባለን:- “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም [እስራኤላውያንን ኃጢአተኞች ናችሁ ብሎ ስለኰነናቸው] በትእዛዛት [በአሥሩ ትእዛዛት ጭምር] የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም [በመሰቀያው እንጨት ላይ] ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።” (ቆላስይስ 2:13, 14) ስለዚህ ክርስቶስ ራሱን ፍጹም መስዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ሕጉ ወደ ፍጻሜው መጥቷል።

7, 8. ሕጉ በሁለት እንዳልተከፈለ ምን ማረጋገጫ አለ?

7 ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ሕጉ በሁለት ይከፈላል ይላሉ። አንደኛው ክፍል አሥሩ ትዕዛዛት ሲሆኑ ሌላው ክፍል የቀሩት ሕጎቹ ናቸው ይላሉ። ሌሎቹ ሕጎች ሲደመሰሱ አሥሩ ትዕዛዛት ግን ቀርተዋል ይላሉ። ሆኖም ይህ እውነት አይደለም። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ከአሥሩ ትዕዛዛትና ከሌሎቹ የሕጉ ክፍሎች ይጠቅስ ነበር፤ በሁለቱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። የሙሴ ሕግ በሁለት እንደማይከፈል ኢየሱስ በዚህ መንገድ አሳይቷል። — ማቴዎስ 5:21-42

8 በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ከሕግ ተፈትተናል” ሲል የጻፈውን አስተውለው። አይሁዳውያን የተፈቱት ከአሥሩ ትዕዛዛት ውጭ ካሉት ሕጎች ብቻ ነበርን? አልነበረም፤ ምክንያቱም ጳውሎስ ሐሳቡን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁ ነበር፤ ሕጉ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁ ነበርና።” (ሮሜ 7:6, 7፤ ዘጸአት 20:17) “አትመኝ” የሚለው ሕግ የአስሩ ትዕዛዛት የመጨረሻው ክፍል ስለነበረ እስራኤላውያን ከአሥሩ ትዕዛዛት ጭምር ተፈትተዋል ማለት ነው።

9. ሣምንታዊ ሰንበት ማክበርን የሚጨምረው ሕግ ጭምር እንደተወገደ የሚያሳየው ምንድን ነው?

9 ታዲያ እንደዚህ ሲባል ከአሥሩ ትዕዛዛት አራተኛ የሆነው ስለ ሣምንታዊ ሰንበት የሚናገረው ሕግ ጭምር ተደምስሷል ማለት ነውን? አዎን ተደምስሷል። መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 4:8-11 እና በቆላስይስ 2:16, 17 ላይ የተናገረው ነጥብ ክርስቲያኖች ሣምንታዊ የሰንበትን ቀንና በዓመት ውስጥ ሌሎች ልዩ ቀኖችን ማክበርን ከሚጨምረው አምላክ ለእስራኤላውያን ከሰጠው ሕግ በታች ያለመሆናቸውን ያሳያል። ሣምንታዊ የሰንበት ቀን ማክበሩ ክርስቲያኖች የሚፈለግባቸው ነገር አለመሆኑን ከሮሜ 14:5 ጭምር መረዳት ይቻላል።

በክርስቲያኖች ላይ የሚሠሩ ሕጎች

10. (ሀ) ክርስቲያኖች በምን ሕጎች ሥር ናቸው? (ለ) ብዙዎቹ ሕጎችስ ከየት የተወሰዱ ናቸው? ከዚያ መወሰዳቸው ምክንያታዊ የሚሆነውስ ለምንድን ነው?

10 ታዲያ እንደዚህ ሲባል ክርስቲያኖች ከአሥሩ ትዕዛዛት በታች ስላልሆኑ ምንም ዓይነት ሕግ እንዲያከብሩ አይጠየቁም ማለት ነውን? በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም። ኢየሱስ የተሻለ መስዋዕት በሆነው በፍጹሙ የሰብዓዊ ሕይወቱ መስዋዕት ላይ የተመሠረተ “አዲስ ኪዳን” አስጀምሯል። ክርስቲያኖች ከዚህ አዲስ ኪዳን በታች ናቸው ለክርስቲያናዊ ሕጎችም ይገዛሉ። (ዕብራውያን 8:7-13፤ ሉቃስ 22:20) ከእነዚህ ሕጎች ውስጥ ብዙዎቹ ከሙሴ ሕግ የተወሰዱ ናቸው። ይህም የማይጠበቅ ወይም እንግዳ የሆነ አሠራር አይደለም። በአንድ አገር ላይ አዲስ መንግሥት በሚቋቋምበት ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ይደረጋል። የፊተኛው መንግሥት ያወጣው ሕገ መንግሥት ተሽሮ በምትኩ ሌላ ይወጣ ይሆናል፤ ሆኖም አዲሱ ሕገ መንግሥት በፊተኛው ላይ የነበሩ ብዙ ሕጎችን ሊይዝ ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ የሕጉ ቃል ኪዳን ወደ ፍጻሜው መጥቷል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ መሠረታዊ ሕጎቹና መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ወደ ክርስትና ተላልፈዋል።

11. ከአሥሩ ትዕዛዛት ጋር በጣም የሚመሳሰሉ ለክርስቲያኖች የተሰጡ ሕጎች ወይም ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

11 በገጽ 203 ላይ ያሉትን አሥሩን ትዕዛዛት አንብበህ ቀጥሎ ካሉት ክርስቲያናዊ ሕጎችና ትምህርቶች ጋር በማወዳደር ሁኔታው እንደዚህ መሆኑን አስተውለው:- “አምላክህን [ይሖዋን] አምልክ።” (ማቴዎስ 4:10፤ 1 ቆሮንቶስ 10:20-22) “ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።” (1 ዮሐንስ 5:21፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ [ከንቱ በሆነ መንገድ አይያዝ]” (ማቴዎስ 6:9) “ልጆች ሆይ፣ ለወላጀቻችሁ ታዘዙ።” (ኤፌሶን 6:1, 2) በተጨማሪም ሰውን መግደል፣ ማመንዘር፣ መስረቅ፣ መዋሸትና መመኘት ለክርስቲያኖች የተሰጠውን ሕግ እንደሚፃረሩ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደርጋል። — ራእይ 21:8፤ 1 ዮሐንስ 3:15፤ ዕብራውያን 13:4፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-7፤ ኤፌሶን 4:25, 28፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ሉቃስ 12:15፤ ቆላስይስ 3:5

12. የሰንበት ሕግ የያዘው መሠረታዊ ሥርዓት ወደ ክርስቲያን ዝግጅት የተሻገረው እንዴት ነው?

12 ምንም እንኳ ክርስቲያኖች ሣምንታዊ የሰንበት ቀን እንዲያከብሩ ባይታዘዙም ከዚያ ዝግጅት የምንማረው ነገር አለ። እስራኤላውያን ቃል በቃል ከሥራ ያርፉ ነበር። ክርስቲያኖች ግን የሚያርፉት በመንፈሳዊ መንገድ ነው። እንዴት? እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነትና ታዛዥነት ስላላቸው የራስ ወዳድነት ሥራዎችን ይተዋሉ። እነዚህ የራስ ወዳድነት ሥራዎች የገዛ ራስን ጽድቅ ለማስመስከር ጥረት ማድረግን ይጨምራሉ። (ዕብራውያን 4:10) ይህ መንፈሳዊ ዕረፍት የሚደረገው በሳምንት አንድ ቀን ሳይሆን ሰባቱንም ቀኖች በሙሉ ነው። እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች አንድ ቀን እንዲመድቡ ሲባል የተሰጣቸው የሰንበት ሕግ ጊዜያቸውን በሙሉ በራስ ወዳድነት ለስጋዊ ጥቅሞች ብቻ እንዳያውሉት ይጠብቃቸው ነበር። ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት በመንፈሳዊ መንገድ በየቀኑ ተግባራዊ ማድረጉ እኛን ከፍቅረ ነዋይ ለመጠበቅ ከዚያ የበለጠ ኃይል አለው።

13. (ሀ) ክርስቲያኖች የትኛውን ሕግ እንዲፈጽሙ ታዘዋል? የሚፈጽሙትስ እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የትኛውን ሕግ አጥብቆታል? (ሐ) ለጠቅላላው የሙሴ ሕግ መሠረት የነበረው የትኛው ሕግ ነበር?

13 ስለዚህ ክርስቲያኖች አሥሩን ትዕዛዛት እንዲጠብቁ ሳይሆን “የክርስቶስን ሕግ እንዲፈጽሙ” ታዘዋል። (ገላትያ 6:2) ኢየሱስ ብዙ ትዕዛዞችንና መመሪያዎችን ሰጥቶናል። እኛም እነርሱን በመታዘዝ የእርሱን ሕግ እንጠብቃለን ወይም እንፈጽማለን። ኢየሱስ በተለይ የፍቅርን አስፈላጊነት አጥብቆ ገልጿል። (ማቴዎስ 22:36-40፤ ዮሐንስ 13:34, 35) አዎ፤ ሌሎችን ማፍቀሩ ክርስቲያናዊ ሕግን መፈጸም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የጠቅላላው የሙሴ ሕግ መሠረት እርሱ ነበር። “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።” — ገላትያ 5:13, 14፤ ሮሜ 13:8-10

14. (ሀ) የሙሴ ሕግ የያዛቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በማጥናትና በሥራ ላይ በማዋል ምን ጥሩ ውጤት ለማግኘት እንችላለን? (ለ) ፍቅር ምን ለማድረግ ይገፋፋናል?

14 አሥሩን ትዕዛዛት የሚጨምረው በሙሴ በኩል የተሰጠው ሕግ ከአምላክ የመጡ ጻድቅ ሕጎችን የያዘ ነበር። ምንም እንኳን ዛሬ ከዚያ ሕግ በታች ባንሆንም ከሕጉ በስተጀርባ የነበሩት መለኮታዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ትልቅ ጥቅም ይሰጡናል። እነርሱን በማጥናትና በሥራ ላይ በማዋል ለታላቁ ሕግ ሰጪ ለይሖዋ አምላክ ያለን አድናቆት ያድጋል። ከዚያ ይበልጥ ግን ክርስቲያናዊ ሕጎችንና ትምህርቶችን ማጥናትና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እርሱ እንድናደርገው የሚጠይቀንን ነገር ሁሉ እንደንታዘዝ ይገፋፋናል። — 1 ዮሐንስ 5:3

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 203 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አሥሩ ትእዛዛት

1. “እኔ . . . [ይሖዋ (አዓት)] አምላክህ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ

2. “በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውሃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም።

3. “[የይሖዋን (አዓት)] የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ . . .

4. “የሰንበትን ቀን ትቀድስ ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለይሖዋ ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም . . .

5. “አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይሖዋ አምላክህ በሚሰጥህ ምድር እድሜህ እንዲረዝም።

6. “አትግደል።

7. “አታመንዝር።

8. “አትስረቅ።

9. “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስከር።

10. “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።” — ዘጸአት 20:2-17

[በገጽ 204, 205 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሕጉ በእስራኤላውያንና በሌሎች ሕዝቦች መካከል እንደ አጥር ሆኖ አገልግሏል።