በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአንድ ትልቅ ክርክር ውስጥ አንተም ገብተሃል

በአንድ ትልቅ ክርክር ውስጥ አንተም ገብተሃል

ምዕራፍ 12

በአንድ ትልቅ ክርክር ውስጥ አንተም ገብተሃል

1, 2. (ሀ) አኗኗርህ ለአንተ ልዩነት የሚያመጣው ለምንድን ነው? (ለ) ሌላስ ማንን ይነካል? ለምንስ?

የምትከተለው የሕይወት መንገድ በውጤቱ ላይ በእርግጥ ልዩነት ያመጣል። ወደፊት ደስታን ወይም ጉስቁልናን ያስከትልብሃል። በመጨረሻም ከዚህ ዓለም ጋር መጥፋትህን ወይም ከጥፋቱ ተርፈህ ለዘላለም መኖር ወደምትችልበት ወደ አዲሱ የአምላክ የጽድቅ ሥርዓት መግባትህን ይወስናል።—1 ዮሐንስ 2:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

2 ይሁን እንጂ አኗኗርህ ከአንተ አልፎ ሌላውንም ይነካል። ሌሎችም በዚህ ውስጥ ይገባሉ። አንተ የምታደርገው ነገር እነርሱንም ጭምር ይነካል። ለምሳሌ ያህል ወላጆችህ በሕይወት ካሉ አንተ የምታደርገው ነገር ሊያስከብራቸው ወይም ውርደት ሊያመጣባቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ:- “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፣ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው” ይላል። (ምሳሌ 10:1) ከሁሉም በላይ ግን አኗኗርህ ይሖዋ አምላክን ይነካል። ደስ ሊያሰኘው ወይም ሊያሳዝነው ይችላል። ለምን? አንተንም ጭምር በሚመለከት በአንድ ትልቅ ጥያቄ ምክንያት ነው።

ሰዎች ለአምላክ ታማኝ ይሆናሉን?

3. ሰይጣን ይሖዋን ምን ብሎ ተገዳደረው?

3 ይህ ጥያቄ የተነሣው በሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ጥያቄውን ያስነሣው አዳምንና ሔዋንን የአምላክን ሕግ እንዲያፈርሱና እርሱ በአምላክ ላይ ባደረገው ዓመፅ እንዲተባበሩት ሊያደርጋቸው በቻለበት ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይህም ሰይጣን ለይሖዋ የሚከተለውን የግድድር ጥያቄ ለማቅረብ መሠረት እንዳለው እንዲሰማው አድርጎታል:- ‘ሰዎች አንተን የሚያገለግሉህ ከአንተ ለሚያገኙት ጥቅም ሲሉ ብቻ ነው። ዕድሉን ብቻ ስጠኝ እንጂ ሁሉንም ሰው ከአንተ ለማራቅ እችላለሁ።’ ምንም እንኳ እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኙም ሰይጣን ይህንን የመሰለ ቃል ለአምላክ እንደተናገረ ግልጽ ነው። የኢዮብ መጽሐፍ ይህንን ያሳያል።

4, 5. (ሀ) ኢዮብ ማን ነበር? (ለ) በኢዮብ ዘመን በሰማይ ምን ተደርጎ ነበር?

4 ኢዮብ በኤደን ገነት ውስጥ ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ብዙ ክፍለ ዘመናት ቆይቶ የኖረ ሰው ነው። እርሱም ጻድቅና ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ነበር። ይሁን እንጂ ኢዮብ ታማኝ መሆኑ ለአምላክ ወይም ለሰይጣን ልዩነት የሚያመጣ ነበርን? መጽሐፍ ቅዱስ ልዩነት ማምጣቱን ያሳያል። በሰማይ ውስጥ ሰይጣን በይሖዋ አምላክ ችሎት ላይ ስለ መታየቱ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የተነጋገሩበትን ጉዳይ ልብ ብለህ አስተውል:-

5 “ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች [በይሖዋ (አዓት)] ፊት ለመቆም መጡ፣ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። [ይሖዋም (አዓት)] ሰይጣንን:- ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፣ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ [ለይሖዋ (አዓት)] መለሰ። [ይሖዋም (አዓት)] ሰይጣንን:- በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው።”—ኢዮብ 1:6-8

6. መጽሐፍ ቅዱስ በኢዮብ ዘመን ምን ክርክር እንደነበረ ይገልጻል?

6 ይሖዋ ኢዮብ ቅን ሰው እንደነበረ ለሰይጣን የጠቀሰለት ለምን ነበር? በግልጽ እንደሚታየው ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ስለመቀጠሉ ጥያቄ ተነሥቶ ነበር ማለት ነው። አምላክ “ከወዴት መጣህ?” በማለት ስላቀረበው ጥያቄና ሰይጣን “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፣ በእርስዋም ተመላለስሁ” በማለት ስለመለሰው መልስ እስቲ አስብ። ይህ ጥያቄና ሰይጣን የሰጠው መልስ ሰይጣን ማንኛውንም ሰው ከአምላክ ለማራቅ እችላለሁ ብሎ የተናገረውን ግድድር በተግባር ለማሳየት ይሖዋ ነፃ ዕድል እንደፈቀደለት ያሳያል። ይሖዋ ስለ ኢዮብ ታማኝነት ላቀረበው ጥያቄ የሰይጣን መልስ ምን ነበር?

7, 8. (ሀ) ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በምን ምክንያት ነው ብሎ ሰይጣን ሰበብ አቀረበ? (ለ) ይሖዋ ለአከራካሪው ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ምን አደረገ?

7 “ሰይጣንም [ለይሖዋ (አዓት)] እንዲህ ብሎ መለሰለት:- በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፣ ከብቱም በምድር ላይ በዝቷል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።”—ኢዮብ 1:9-11

8 ሰይጣን እንደዚያ ብሎ ሲመልስ ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ የሆነው ሁሉ ነገር ስለተሟላለት ነው የሚል ሰበብ ማቅረቡ ነበር። ‘ኢዮብ አንተን የሚያመልክህ ስለሚወድህ ሳይሆን በሰጠኸው ነገሮች ምክንያት ነው’ ብሎ ሰይጣን ተከራከረ። በተጨማሪም ሰይጣን ይሖዋ ከፍተኛ ኃይሉን አግባብ ባልሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል ብሎ ስሞታ አቅርቧል። ‘ከክፉ ነገር ሁልጊዜ ትከላከልለታለህ’ አለ። ስለዚህ አከራካሪው ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ይሖዋ “እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፣ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው።”—ኢዮብ 1:12

9. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ምን ችግር አመጣ? ከምንስ ውጤት ጋር?

9 ወዲያውኑ ሰይጣን በኢዮብ ላይ ችግር መፍጠር ጀመረ። የኢዮብ ከብቶች እንዲገደሉ ወይም እንዲዘረፉ አደረገ። ከዚያም የኢዮብ አሥር ልጆች እንዲገደሉ አደረገ። ኢዮብ ያለውን ነገር ሁሉ አጣ፤ ሆኖም ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቀጠለ። አምላክን አልሰደበም። (ኢዮብ 1:2, 13-22) ይሁን እንጂ ነገሩ በዚህ አላበቃም።

10. ሰይጣን ተስፋ እንዳልቆረጠ የሚያሳየው ምንድን ነው?

10 ሰይጣን አሁንም ከሌሎች መላእክት ጋር እንደገና በይሖዋ ፊት ቀረበ። ይሖዋም የኢዮብን ታማኝነት ተመልክቶ እንደሆነ በድጋሚ ጠየቀውና ‘እስከ አሁን ፍጹም አቋሙን ይዟል’ አለው። በዚህን ጊዜ ሰይጣን “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል” ብሎ መለሰለት።—ኢዮብ 2:1-5

11. (ሀ) ሰይጣን በኢዮብ ላይ ምን ተጨማሪ መከራዎች አመጣ? (ለ) ውጤቱስ ምን ነበር?

11 ይሖዋም መልሶ በኢዮብ ላይ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግበት ፈቃድ ሰጠው፤ ቢሆንም ‘እንዳትገድለው’ አለው። (ኢዮብ 2:6) ስለዚህም ሰይጣን ኢዮብን አሰቃቂ በሆነ ቁስል መታው። ኢዮብ ሥቃዩ በጣም ከባድ በመሆኑ እንዲሞት ጸለየ። (ኢዮብ 2:7፤ 14:13, 14) የገዛ ሚስቱም ተነሣችበትና “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። (ኢዮብ 2:9) ይሁን እንጂ ኢዮብ ይህንን ለማድረግ እምቢ አለ። “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን (ፍጹም አቋሜን) ከእኔ አላርቅም!” አለ። (ኢዮብ 27:5) ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ በመሆን ጸና። በዚህም መንገድ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በፍቅር ሳይሆን ሥጋዊ ጥቅም ለማግኘት ነው በማለት ሰይጣን ያቀረበው ግድድር ውሸት እንደሆነ ተረጋገጠ። ከዚህም ሌላ ሰይጣን ሁሉንም ሰው አምላክን ከማገልገል ለማራቅ እንደማይችል ታየ።

12. (ሀ) ሰይጣን ላነሣው ግድድር ኢዮብ ለአምላክ ምን መልስ አስገኘለት? (ለ) ኢየሱስ ለአምላክ ታማኝነቱን መጠበቁ ምን አረጋገጠ?

12 ኢዮብ የተከተለው የታማኝነት መንገድ ይሖዋን እንዴት እንዲሰማው ያደረገው ይመስልሃል? በጣም እንዲደሰት አድርጎታል! የአምላክ ቃል “ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” ሲል ያሳስበናል። (ምሳሌ 27:11) ይሖዋን የሚሳደበው ሰይጣን ነው። ኢዮብ በተከተለው የታማኝነት መንገድ የአምላክን ልብ ደስ አሰኝቶታል። ይህም ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው አያገለግሉህም በማለት ሰይጣን ላስነሣው የጉራ ስድብ ወይም ግድድር አምላክ ጥሩ መልስ እንዲሰጠው አስችሎታል። ሌሎች ብዙ ሰዎችም አምላክ እንደዚህ ያለ መልስ እንዲሰጥ አስችለውታል። ከሁሉ በላይ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ነው። ሰይጣን በእርሱ ላይ ያን ሁሉ ፈተናና መከራ ቢያመጣበትም እንኳ ከታማኝነቱ ዝንፍ አላለም። ይህ ምሳሌ ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ቢፈልግ ኖሮ ልክ እንደዚያ ማድረግ ይችል እንደነበረና አምላክ ከሰው ፍጹም ታዛዥነትን መጠበቁ ዐመፀኛ እንደማያደርገው አረጋግጧል።

አቋምህ ምንድን ነው?

13. (ሀ) አኗኗርህ ከአከራካሪው ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት አለው? (ለ) አምላክን ልናስደስት ወይም ልናሳዝን የምንችለው እንዴት ነው?

13 የአንተስ ሕይወት እንዴት ነው? ምናልባት አኗኗርህ በእርግጥ ልዩነት እንደሚያመጣ አድርገህ አታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልዩነት ያመጣል። ብታውቀውም ባታውቀውም በክርክሩ ውስጥ የአምላክ ወይም የሰይጣን ደጋፊ ያደርግሃል። ይሖዋ ለአንተ ያስባል፤ እርሱን አገልግለህ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ስትኖር ለማየት ይፈልጋል። (ዮሐንስ 3:16) እስራኤላውያን በአምላክ ላይ ባመጹ ጊዜ አዝኖና ተሰምቶት ነበር። (መዝሙር 78:40, 41) አንተ የምትከተለውስ መንገድ አምላክን የሚያስደስት ነው ወይስ የሚያሳዝን? እርግጥ፤ አምላክን ደስ ለማሰኘት ከፈለግህ ሕጎቹን ማወቅና ማክበር ያስፈልግሃል።

14. (ሀ) የጾታ ግንኙነትን በሚመለከት አምላክን ለማስደሰት የትኞቹን ሕጎች መታዘዝ ይኖርብናል? (ለ) እንደነዚህ ያሉትን ሕጎች ማፍረሱ ወንጀል የሆነው ለምንድን ነው?

14 ሰይጣን ዒላማ ከሚያደርጋቸው ዋነኛ ነገሮች አንዱ አምላክ ሰዎች አባለዘራቸውን እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የደነገጋቸውን ሕጎች እንዲጥሱ ማድረግና የአምላክ ዝግጅት የሆነውን ጋብቻንና ቤተሰብን ማፍረስ ነው። ደስታችንን እንዳናጣ የሚጠብቁን የአምላክ ሕጎች ያልተጋቡ ሰዎች ጾታዊ ግንኙነትን እንዳያደርጉ፣ የተጋቡትም ከትዳር ጓደኛቸው ውጭ ከማንም ጋር የጾታ ግንኙነት እንዳይፈጽሙ ይከለክላሉ። (1 ተሰሎንቄ 4:3-8፤ ዕብራውያን 13:4) የአምላክ ሕግ ሲፈርስ ብዙውን ጊዜ አፍቃሪና ሰብሳቢ ወላጆች የሌሏቸው ልጆች ይወለዳሉ። ምናልባትም እናቶች ልጆቹን ከመወለዳቸው በፊት በማስወረድ ይገድሏቸው ይሆናል። በተጨማሪም ዝሙት የሚፈጽሙ ብዙ ሰዎች የሚወልዷቸውን ልጆች ሊጎዱ በሚችሉ በጣም መጥፎ በሆኑ የአባለዘር በሽታዎች ይያዛሉ። ከትዳር ጓደኛ ውጭ የጾታ ግንኙነት መፈጸሙ ታማኝ አለመሆን ነው፤ አድራጎቱ በአምላክ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው። ኢዮብ እንዲህ አለ “ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጎምጅቶ እንደ ሆነ፣ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ . . . ይህ ክፉ አበሳ ፣ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነው።”—ኢዮብ 31:1, 9, 11

15. (ሀ) ዝሙት ብንፈጽም የምናስደስተው ማንን ነው? (ለ) የአምላክን ሕጎች መታዘዙ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ይህ በዲያብሎስ የሚገዛ ዓለም ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት ተገቢና ትክክል መስሎ እንዲታይ ማድረጉ ሊያስደንቀን አይገባም። ይሁን እንጂ ይህንን ብታደርግ የምታስደስተው ማንን ነው? ይሖዋን ሳይሆን ሰይጣንን ነው። አምላክን ለማስደሰት ከፈለግህ ‘ከዝሙት መሸሽ’ ይኖርብሃል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) እውነት ነው፣ ለአምላክ ታማኝ መሆን ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ይህ ለኢዮብም ቢሆን ቀላል አልነበረም። ቢሆንም የአምላክን ሕጎች መታዘዝ ጥበብ እንደሆነ አስታውስ። ይህንን ብታደርግ በአሁኑ ጊዜ ደስታህ ይጨምራል። ከዚህም በላይ ግን በአከራካሪው ጉዳይ በአምላክ ጎን ትቆማለህ፤ እርሱንም ደስ ታሰኘዋለህ። እርሱም በምድር ላይ ደስታ ያለበት የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርክሃል።

16. (ሀ) ኢዮብ ላሳየው ታማኝነት የተባረከው እንዴት ነው? (ለ) የኢዮብን 10 ልጆች እንደ መግደል ስለመሳሰሉት ሰይጣን ስለሚያደርሳቸው ጉዳቶች ምን ሊባል ይቻላል?

16 እውነት ነው ሰይጣን ኢዮብን ሊያደኸየውና 10 ልጆቹ እንዲገደሉበት ለማድረግ ችሏል። ይህን ሁሉ ማጣት ለኢዮብ ከባድ ጉዳት እንደነበረ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ኢዮብ ታማኝ መሆኑ ሲረጋገጥ ሰይጣን እርሱን እንዲፈትነው ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ከነበረው ይልቅ ሁለት እጥፍ በመስጠት አምላክ ባርኮታል። ኢዮብ ሌሎች 10 ልጆች ወለደ። (ኢዮብ 42:10-17) ከዚህም በተጨማሪ በሰይጣን የተገደሉት የኢዮብ 10 ልጆች በሙታን ትንሣኤ ጊዜ እንደገና ሕያው እንደሚሆኑ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። ሰይጣን የፈለገውን ነገር እንዲያመጣብን ቢፈቀድለትም አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ሊስተካከል የማይችል ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ችግር ሊያደርስብን አይችልም።

17. አኗኗራችን በእርግጥ ልዩነት የሚያመጣው ለምንድን ነው?

17 እንግዲያው አኗኗርህ በውጤቱ ልዩነት እንደሚያመጣ ምንጊዜም ማስታወስ ያስፈልግሃል። ይህ በተለይ ለይሖዋ አምላክና ለሰይጣን ዲያብሎስ ልዩነት ያመጣል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሰዎች ለአምላክ ታማኝ ስለመሆናቸው በተነሣው ክርክር ውስጥ አንተም ስለገባህ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 106 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈተና ቢደርስበት ማንም ሰው ለአምላክ ታማኝ ሆኖ አይቆምም የሚለውን የሰይጣን ግድድር ኢዮብ ውድቅ አድርጎታል

[በገጽ 110 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው ከትዳር ጓደኛው ውጭ የጾታ ግንኙነት ቢፈጽም በአምላክ ላይ ወንጀል መሥራቱ ነው

[በገጽ 111 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ ላሳየው ታማኝነት ይሖዋ በፊት ከነበረው አስበልጦ በመስጠት ባርኮታል