በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጸሎት እርዳታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

በጸሎት እርዳታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 27

በጸሎት እርዳታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

1. ከአምላክ ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልገናል? እንዴትስ እናገኘዋለን?

ክርስቲያኖች ክፉው የዓለም ግፊት እንዳይለውጣቸው በተለይ በጸሎት በኩል የሚገኘው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ‘በሰማይ ያለው አባት ለሚጠይቁት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣል’ ብሏል። (ሉቃስ 11:13) የአምላክን ቃል ማጥናትና ከድርጅቱ ጋር መተባበር እንደሚያስፈልገን ሁሉ ቅዱስ መንፈሱም ወይም ሁልጊዜ በሥራ ላይ ያለው ኃይሉ ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ ያንን ለማግኘት መንፈስ ቅዱስን ስጠን ብለን መጸለይ ያስፈልገናል።

2. (ሀ) ጸሎት ምንድን ነው? (ለ) የተለያዩ የጸሎት ዓይነቶች ምንድን ናቸው? (ሐ) ጸሎት ለምን በጣም አስፈላጊ ነው?

2 ጸሎት አክብሮት ባለው መንገድ ለአምላክ የሚቀርብ ንግግር ነው። አንዱ የጸሎት ዓይነት ልመና ነው። ለምሳሌ አምላክ አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርገልን ልንጠይቀው እንችላለን። ይሁን እንጂ ጸሎት ለአምላክ ምስጋናንና ውዳሴን የምንገልጽበት ጭምር ነው። (1 ዜና 29:10-13) ከሰማዩ አባታችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ከፈለግን ዘወትር በጸሎት እርሱን ማነጋገር ያስፈልገናል። (ሮሜ 12:12፤ ኤፌሶን 6:18) ሰይጣን ወይም እርሱ የሚመራው ዓለም ምንም ዓይነት መከራዎች ወይም ፈተናዎች ቢያመጡብን አምላክን በመጠየቅ የምናገኘው መንፈሱ ወይም ሁልጊዜ በሥራ ላይ ያለው ኃይሉ ያንን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሊሰጠን ይችላል። — 1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ኤፌሶን 3:20

3. (ሀ) ከአምላክ ምን ዓይነት ብርታት ለማግኘት እንችላለን? (ለ) ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን ለመኖር የምንችለው እንዴት ብቻ ነው?

3 አምላክን የማያስደስት አንድ ዓይነት ልማድ ወይም ድርጊት ለማስወገድ ኃይለኛ ትግል ገጥሞህ ይሆናል። ይህ ከሆነ ይሖዋ እንዲረዳህ ጠይቀው። በጸሎት ወደ እርሱ ዘወር በል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደዚያ አድርጎ ነበር። በኋላም:- “ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ለሁሉም ነገር ብርታት አለኝ” ብሎ ጻፈ። (ፊልጵስዩስ 4:13 አዓትመዝሙር 55:22፤ 121:1, 2) ከብልግና ኑሮ የተላቀቀች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ከእንዲህ ዓይነቱ አኗኗር ለመላቀቅ እርዳታ ለመስጠት ኃይል ያለው እርሱ ብቻ ነው። አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህንን የግል ዝምድና መጠበቅ የሚቻልበት መንገድ ደግሞ ጸሎት ብቻ ነው።”

4. አንድ ሰው ከሲጋራ ልማድ ለመላቀቅ ኃይል ያገኘው እንዴት ነው?

4 ሆኖም አንድ ሰው ‘አምላክ እንዲረዳኝ ብዙ ጊዜ ጸልያለሁ፤ ነገር ግን መጥፎ ነገር ከማድረግ ልቆጠብ አልቻልኩም’ ብሎ ይናገር ይሆናል። ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች እንደዚያ ብለው ተናግረዋል። እንደዚህ ያለ አንድ ሰው “የጸለይከው መቼ ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ “ማታ ወደ መኝታዬ ከመሄዴ በፊት፣ ጠዋት ስነሣ እንዲሁም ተሸንፌ ሲጋራ ሳጨስ ይሖዋ ባደረግሁት ነገር አዝናለሁ ብዬ እናገራለሁ” ሲል መልሷል። ጓደኛውም “የአምላክ እርዳታ የሚያስፈልግህ በተለይ ሲጋራውን ለመጨበጥ ስትቃጣ ነው፤ አይደለም እንዴ? ይሖዋ እንዲያጠነክርህ መጸለይ ያለብህ ያኔ ነው” ብሎ ነገረው። ሰውየው እንደዚያ ካደረገ በኋላ ሲጋራውን ለማቆም ከአምላክ እርዳታ አገኘ።

5. (ሀ) አምላክን በተገቢ መንገድ ለማገልገል ምን ያስፈልጋል? (ለ) ከአንድ የኃጢአት ድርጊት መላቀቁ ብዙውን ጊዜ ሥቃይን እንደሚያስከትል የሚያመለክተው ምንድን ነው?

5 እንደዚህም ሲባል ወደ አምላክ መጸለይ፣ ቃሉን ማጥናትና ከሚታየው ድርጅቱ ጋር መተባበር ትክክል የሆነውን ለመሥራት ቀላል ያደርግልሃል ማለት አይደለም። ነገሩ አሁንም ቢሆን ጥረትን ይጠይቃል። አዎን፣ ከባድ ትግል ማድረግ ያስፈልገዋል። ይህም አንዳንድ ጊዜ ሥቃይን ይጨምር ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) መጥፎ ልማዶች መጥፎ ለሆነው ነገር አስጨናቂ ምኞት ሊያሳድሩብን ይችላሉ። ስለዚህ ከኃጢአት አድራጎት መራቁ ብዙ ጊዜ ሥቃይን ያስከትላል። ታዲያ ትክክል የሆነውን ለመሥራት ስትል ሥቃዩን ለመቀበል ፈቃደኛ ነህን? — 1 ጴጥሮስ 2:20, 21

አምላክ የሚሰማቸው ጸሎቶች

6. (ሀ) ብዙዎች መጸለይ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? (ለ) ጸሎቶቻችን ተሰሚነት እንዲያገኙ ምን ያስፈልገናል?

6 ብዙ ሰዎች ለመጸለይ ይቸገራሉ። “በዓይኔ ላላየሁት ነገር መጸለዩ ይከብደኛል” ስትል አንዲት ወጣት ሴት ተናግራለች። ማንም ሰው አምላክን ስላላየው ወደ እርሱ ለመጸለይና እርሱ እንዲሰማን እምነት ያስፈልገናል። ይሖዋ በእርግጥ እንዳለና የጠየቅነውን ለመፈጸም እንደሚችል ማመን ይኖርብናል። (ዕብራውያን 11:6) የዚህ ዓይነት እምነት ካለንና አምላክን በቅን ልብ ካነጋገርነው እንደሚረዳን እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። (ማርቆስ 9:23) ይህም በመሆኑ ቆርኔሌዎስ የተባለ የሮማ ጦር ሠራዊት መኰንን አምላክ እንዲመራው በቅንነት በጸለየ ጊዜ የአምላክ ድርጅት አባል ያልነበረ ቢሆንም አምላክ ጸሎቱን ሰምቶለታል። — ሥራ 10:30-33

7. (ሀ) ምን ዓይነት ጸሎቶች አምላክን ያስደስታሉ? (ለ) አምላክ ምን ዓይነት ጸሎቶችን አይሰማም?

7 አንዳንድ ሰዎች ሐሳባቸውን በቃላት መግለጹ ያስቸግራቸዋል። ሆኖም ይህ ችግር በጸሎት አምላክን እንዳያነጋግሩ ሊያግዳቸው አይገባም። አምላክ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያውቅልንና ለመናገር የፈለግነውን እንደሚረዳልን እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። (ማቴዎስ 6:8) እስቲ ራስህ አስበው። ከአንድ ሕፃን ምን ዓይነት ቃላት ስትሰማ ነው ከሁሉ ይበልጥ ደስ የሚልህ? የምትወደው በቀላል አነጋገርና በቅንነት የገለጸውን ምስጋና ነው ወይስ ሌላ ሰው የነገረውን ምርጥ ቃላት? የሰማዩ አባታችንም እንደዚሁ ደስ የሚለው በቀላል አነጋገርና በቅንነት ሐሳባችንን ስንገልጽለት ነው። (ያዕቆብ 4:6፤ ሉቃስ 18:9-14) ልዩ የሆኑ ቃላት ወይም ሃይማኖታዊ የአነጋገር ዘይቤዎች አያስፈልጉም። እንዲያውም በሌሎች ለመደነቅ ብለው እንግዳ በሆነና ልዩ ስሜት በሚቀሰቅስ አነጋገር ተጠቅመው የሚጸልዩትን ወይም ደግሞ ቅንነት በሌለው መንገድ ሐሳብ የሚደጋግሙትን ሰዎች አምላክ አይሰማቸውም። — ማቴዎስ 6:5, 7

8. (ሀ) ድምፅ ሳናሰማ የምናቀርባቸውን ጸሎቶች አምላክ ሊሰማ እንደሚችል የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ለጸሎት የተወሰነ የአካል አቋቋም ወይም ቦታ ያስፈልጋል በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራልን?

8 ሌላው ቀርቶ ድምፅ ሳታሰማ ብትጸልይም አምላክ ሊሰማህ ይችላል። ነህምያ እንደዚያ ባደረገ ጊዜ በቅንነት ያቀረበውን ጥያቄ አምላክ ፈጽሞለታል። የሐናም ሁኔታ እንደዚሁ ነበር። (ነህምያ 2:4-8፤ 1 ሳሙኤል 1:11-13, 19, 20) በተጨማሪም አንድ ሰው በሚጸልይበት ጊዜ ትልቁ ነገር የአካሉ አቋቋም አይደለም። በማንኛውም ዓይነት አቋቋም፣ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ መጸለይ ትችላለህ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ትሕትናን የሚገልጽ ሁኔታ ለምሳሌ ራስን ዝቅ ማድረግ ወይም መንበርከክ ትክክል መሆናቸውን ያሳያል። (1 ነገሥት 8:54፤ ነህምያ 8:6፤ ዳንኤል 6:10፤ ማርቆስ 11:25፤ ዮሐንስ 11:41) ከዚህም ሌላ የግል ጸሎት በምናቀርብበት ጊዜ ለብቻችን መሆን የምንችልበትን ቦታ መርጠን ሰዎች ሳያዩን ብንጸልይ ጥሩ መሆኑን ኢየሱስ አመልክቷል። — ማቴዎስ 6:6

9. (ሀ) ጸሎቶቻችን ሁሉ መቅረብ ያለባቸው ለማን ነው? ለምንስ? (ለ) ጸሎቶቻችን በአምላክ ፊት ተቀባይነትን እንዲያገኙ በማን ስም መቅረብ ይኖርባቸዋል?

9 ጸሎት የአምልኮታችን ክፍል ነው። በዚህ ምክንያት ጸሎታችን ለፈጣሪያችን ለይሖዋ አምላክ እንጂ ለሌላ ለማንም ፍጡር መቅረብ የለበትም። (ማቴዎስ 4:10) ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ወደ አምላክ መቅረብ ያለባቸው ኃጢአቶቻችንን ለማስወገድ ሕይወቱን በሰጠው በኢየሱስ በኩል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ማለት ጸሎታችን በኢየሱስ ስም መቅረብ ይኖርበታል ማለት ነው። — ዮሐንስ 14:6, 14፤ 16:23፤ ኤፌሶን 5:20፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

10. (ሀ) የእነማን ጸሎቶች አምላክን አያስደስቱም? (ለ) አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ከተፈለገ የትኛውን መሠረታዊ ነገር ማሟላት አለብን?

10 ይሁን እንጂ ጸሎት ሁሉ አምላክን ያስደስታልን? መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት” ይላል። (ምሳሌ 28:9፤ 15:29፤ ኢሳይያስ 1:15) እንግዲያውስ አምላክ ጸሎቶቻችንን እንዲሰማልን ከፈለግን ከእኛ የሚፈለግ መሠረታዊ ነገር ፈቃዱን ማድረግ፣ ሕጎቹን መታዘዝ ነው። አለዚያ ግን ንጹሕ የሆነ ሰው አስነዋሪ ነው ብሎ የሚያስበውን የሬድዮ ፕሮግራም እንደማያዳምጥ ሁሉ አምላክም እኛን አያዳምጠንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ እናገኛለን” ይላል። — 1 ዮሐንስ 3:22

11. ለምንጸልይለት ነገር ጥረት ማድረግ አለብን ሲባል ምን ማለት ነው?

11 ይህም የጸለይንለትን ነገር ለማግኘት መጣር አለብን ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሲጋራ ወይም ማሪዋና ለማቆም እንዲረዳው አምላክን ቢጠይቅና ከቤቱ ወጣ ብሎ እነዚህን ነገሮች ቢገዛ ስሕተት ነው። እንዲሁም ይሖዋ ከጾታ ብልግና ለመራቅ እንዲረዳው ጠይቆ ብልግናን የሚያንጸባርቅ ጽሑፍ፣ ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለመመልከት አይችልም። ወይም ደግሞ የአንድ ሰው ድካም ቁማር ከሆነ አምላክ ያንን ለማቆም እንዲረዳው ጸልዮ የቁማር ጨዋታ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ለመገኘት አይችልም። ጸሎቶቻችንን አምላክ እንዲሰማልን ከፈለግን የጸለይነው ከልብ መሆኑን በምናደርጋቸው ነገሮች ማሳየት አለብን።

12. (ሀ) በጸሎታችን ውስጥ ማስገባት የምንችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ጸሎታችን አምላክን የሚያስደስት እንዲሆን ከተፈለገ ምን መማር አለብን?

12 ታዲያ ወደ ይሖዋ በምናቀርባቸው ጸሎቶች ውስጥ ሊጨመሩ የሚችሉ የግል ጉዳዮች ምንድን ናቸው? እንደ እውነቱ ከሆነ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካ ማንኛውም ነገር ለምሳሌ ጤንነታችንና ልጆቻችንን የማሳደጉ ጉዳይ በጸሎታችን ውስጥ ቢጠቀሱ ትክክል ነው። (2 ነገሥት 20:1-3፤ መሳፍንት 13:8) ሐዋርያው ዮሐንስ:- “እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል ” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:14) ስለዚህ ትልቁ ነገር የምንጠይቃቸው ነገሮች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ መሆናቸው ነው። ይህም የእርሱ ፈቃድ ምን መሆኑን በመጀመሪያ መማር ያስፈልገናል ማለት ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) ከዚያ በኋላ በምንጸልይበት ጊዜ ስለ ግል ጉዳዮቻችን ብቻ በመጨነቅ ፋንታ የአምላክን ፈቃድና ዓላማ በጉዳዩ ውስጥ ካስገባነው የምናቀርባቸው ጸሎቶች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያገኛሉ። ይሖዋ ስለሚሰጠን ጥሩ ነገሮች በየቀኑ ማመስገኑ ተገቢ ነው። — ዮሐንስ 6:11, 23፤ ሥራ 14:16, 17

13. (ሀ) በጸሎታችን ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ሊያሳስቡን የሚገባቸውን ነገሮች ኢየሱስ ያመለከተው እንዴት ነው? (ለ) በሁለተኛ ደረጃ ልንጸልይላቸው የሚያስፈልጉን ሌሎች ነገሮች ምንድን ናቸው?

13 አምላክ ምን ዓይነት ጸሎቶችን እንደሚቀበል ለተከታዮቹ መመሪያ እንዲሆናቸው ብሎ ኢየሱስ እንደ ናሙና ሆኖ የሚያገለግል ጸሎት ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:9-13) ይህ ጸሎት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የአምላክ ስም፣ መንግሥቱና በምድር ላይ ፈቃዱ መፈጸሙ መሆናቸውን ያሳያል። ከዚያ በኋላ በግል ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ለምሳሌ ስለ ዕለታዊ ምግባችን፣ ኃጢአቶቻችንን ይቅር እንዲለንና ከፈተናና ከክፉው ከሰይጣን ዲያብሎስ እንዲያድነን ለመጠየቅ እንችላለን።

ሌሎችን ለመርዳት የሚቀርቡ ጸሎቶች

14. ስለ ሌሎች መጸለዩ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 ስለ ሌሎች የመጸለይን አስፈላጊነት ኢየሱስ ባሳየው ምሳሌ አስተምሯል። (ሉቃስ 22:32፤ 23:34፤ ዮሐንስ 17:20) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደዚህ ያሉ ጸሎቶች የቱን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ያውቅ ነበር፤ ሌሎች እንዲጸልዩለትም ደጋግሞ ጠይቋል። (1 ተሰሎንቄ 5:25፤ 2 ተሰሎንቄ 3:1፤ ሮሜ 15:30) በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ:- “በጸሎታችሁ ነፃ እንደምለቀቅ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልሞና 22 አዓት፤ ኤፌሶን 6:18-20) ጳውሎስ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከእስር መፈታቱ ስለ እርሱ የቀረቡት ጸሎቶች እንደጠቀሙት ያመለክታል።

15. ስለምናፈቅራቸው ሰዎች ምን ዓይነት ጥያቄዎችን ለማቅረብ እንችላለን?

15 ጳውሎስ በጸሎቶቹ ላይ ሌሎችን የሚረዱ ነገሮችም ጠቅሷል። “አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቆጥራችሁ ዘንድ . . . ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን” ሲል ጽፏል። (2 ተሰሎንቄ 1:11) ለሌላም ጉባኤ እንዲህ ሲል ገልጿል:- ‘ልካሙን ነገር እንጂ ክፉውን ከቶ እንዳታደርጉ ወደ አምላክ እንጸልያለን።’ (2 ቆሮንቶስ 13:7) የጳውሎስን ምሳሌ ብንከተልና ስለምናፈቅራቸው ሰዎች አንዳንድ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ብናቀርብ ጥሩ ነው። “የጻድቅ ሰው [ምልጃ (አዓት)] በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።” — ያዕቆብ 5:13-16

16. (ሀ) የሚያስፈልገንን እርዳታ ለማግኘት መቼ መጸለይ አለብን? (ለ) ጸሎት ይህን ያህል ታላቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

16 አንድ የአምላክ አገልጋይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመራ የሚያስጠናቸውን ሰዎች “በሣምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ጊዜ ከምናደርገው በተጨማሪ በሌላም ጊዜ ትጸልያለህን?” ብሎ የመጠየቅ ልማድ አለው። የሚያስፈልገንን እርዳታ ለማግኘት ብዙ ጊዜ አምላክን በጸሎት ማነጋገር አለብን። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ሉቃስ 18:1-8) ልክ የምታፈቅረውንና የምትወደውን ወዳጅህ እንደምታነጋግረው አድርገህ በትሕትና ይሖዋን ማነጋገርን ተማር። ጸሎትን ወደሚሰማውና የአጽናፈ ዓለም ታላቅ ገዥ ወደሆነው አምላክ ጸሎታችንን ለማቅረብ መቻላችንና እርሱ እንደሚሰማን ማወቃችን በእውነቱ እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! — መዝሙር 65:2

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 227 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው ሲጋራ እንዲያጨስ በሚፈተንበት ጊዜ ምን ማድረግ አለበት? እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ወይስ መሸነፍ?

[በገጽ 229 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ እንዲረዳህ ከጸለይክ በኋላ ስሕተት ወደ ሆነ ድርጊት ሊመራህ በሚችል እንቅስቃሴ ውስጥ ትካፈላለህን?

[በገጽ 230 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትጸልየው ከሌሎች ጋር ስትሆን ብቻ ነው ወይስ ለብቻህም ስትሆን ትጸልያለህ?