በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 11

አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

1. (ሀ) ዛሬ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ ምን ዓይነት ነው? (ለ) አንዳንድ ሰዎች ምን ቅሬታ ያሰማሉ?

በዓለም ውስጥ በየትም ቦታ ብትመለከት ወንጀል፣ ጥላቻና ረብሻ አለ። ብዙውን ጊዜ ዐመፁ የሚፈጸምባቸው ከክፉ አድራጎቱ ንጹሕ የሆኑት ሰዎች ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ለዚህ ሁሉ አምላክን ይወቅሳሉ። ‘አምላክ ካለ እነዚህ ሁሉ አስጨናቂ ነገሮች እንዲኖሩ ለምን ይፈቅዳል?’ ይሉ ይሆናል።

2. (ሀ) ክፉ ነገሮችን እየሠሩ ያሉት እነማን ናቸው? (ለ) በምድር ላይ ያለው አብዛኛው መከራ እንዴት ሊቀር ይችል ነበር?

2 ይሁንና በሌሎች ላይ እነዚህን ክፉ ነገሮች የሚፈጽሙት እነማን ናቸው? ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደለም። አምላክ ክፉ ድርጊቶችን ያወግዛል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሰዎች የአምላክን ሕጎች ቢታዘዙ ኖሮ በምድር ላይ ያለው አብዛኛው ሥቃይ ባልኖረም ነበር። እርሱ እንድንዋደድ አዞናል፤ መግደልን፣ መስረቅን፣ ማመንዘርን፣ ስግብግብነትን፣ ስካርንና በሰዎች ላይ መከራ የሚያመጡ ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን ከልክሏል። (ሮሜ 13:9፤ ኤፌሶን 5:3, 18) አምላክ አዳምንና ሔዋንን አስደናቂ የሆነ አእምሮና አካል ሰጥቶ ፈጥሯቸዋል፤ ሕይወታቸውንም ሙሉ በሙሉ እንዲደሰቱበት ችሎታ ሰጥቷቸዋል። እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው እንዲሠቃዩ ወይም ችግር እንዲደርስባቸው በፍጹም አልፈለገም ነበር።

3. (ሀ) ዛሬ ላለው ክፋት ተጠያቂዎች እነማን ናቸው? (ለ) አዳምና ሔዋን የሰይጣንን ፈተናዎች ሊቋቋሙ ይችሉ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?

3 በምድር ላይ ክፋትን የጀመረው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋንም ቢሆኑ ለዚህ ተወቃሾች ናቸው። ዲያብሎስ ሲፈትናቸው ያንን ለመቋቋም የማይችሉ ደካሞች አልነበሩም። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ከዚያ ቆየት ብሎ እንዳደረገው ሰይጣንን “ሂድ” ሊሉት ይችሉ ነበር። (ማቴዎስ 4:10) ይሁን እንጂ እንደዚያ አላደረጉም። ከዚህም የተነሳ ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ። ልጆቻቸው ሁሉ፣ እኛም ጭምር፣ በሽታን ኀዘንንና ሞትን የሚያስከትለውን አለፍጽምናን ወርሰናል። (ሮሜ 5:12) ይሁን እንጂ አምላክ ለምን መከራ እንዲቀጥል ፈቀደ?

4. አፍቃሪ የሆነው አምላክ ለጊዜው ክፋትን ሊፈቅድ እንደሚችል ለመገንዘብ ምን ይረዳናል?

4 አንድ ሰው አምላክ ለብዙ ክፍለ ዘመናት በሰው ላይ የደረሰውን ሥቃይ ለመፍቀድ ይህን ያህል ትልቅ ምክንያት ሊኖረው አይችልም ብሎ በመጀመሪያ ያስብ ይሆናል። ሆኖም እንደዚያ ብሎ መደምደሙ ትክክል ነውን? አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው አካል ላይ የደረሰውን ችግር ለማስተካከል ሥቃይ ያለበት ቀዶ ጥገና እንዲደረግባቸው ይፈቅዱ የለምን? አዎን፣ ጊዜያዊ ሥቃይ እንዲደርስባቸው መፍቀዱ አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ በቀሪው ሕይወታቸው የተሻለ ጤንነት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ታዲያ አምላክ ክፋት እንዲኖር በመፍቀዱ ምን ጥሩ ነገር ተገኝቷል?

መልስ ማግኘት የሚያስፈልገው አንድ ትልቅ ጥያቄ

5. (ሀ) ሰይጣን አምላክን የተጻረረው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን ለሔዋን ምን ተስፋ ሰጣት?

5 በኤደን የአትክልት ቦታ በአምላክ ላይ የተነሳው ዐመጽ ከፍተኛ የሆነ አከራካሪ ጉዳይ ወይም ጥያቄ አስነስቷል። አምላክ ክፋት እንዲቀጥል ለምን እንደፈቀደ ለመረዳት ይህንን ጥያቄ ልንመረምረው ያስፈልገናል። ይሖዋ ለአዳም በገነት ውስጥ ካለችው ካንዲት ዛፍ እንዳይበላ ነግሮት ነበር። አዳም ቢበላ ምን ይደርስበታል? አምላክ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” አለው። (ዘፍጥረት 2:17) ይሁን እንጂ ሰይጣን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ተናገረ። ለአዳም ሚስት ለሔዋን ከተከለከለው ዛፍ እንድትወስድና እንድትበላ ነገራት። ሰይጣን ‘ፈጽሞ አትሞቱም ’ አለ። እንዲያውም ሐሳቡን በመቀጠል “ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” በማለት ለሔዋን ነገራት።— ዘፍጥረት 3:1-5

6. (ሀ) ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ለምን አፈረሰች? (ለ) ከተከለከለው ዛፍ መብላት ማለት ምን ማለት ነበር?

6 ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ አፈረሰችና በላች። ለምን? ሰይጣንን ስላመነችው ነው። ‘የአምላክን ትእዛዝ ባፈርስ እጠቀማለሁ’ የሚል የራስ ወዳድነት ሐሳብ መጣባት። ከዚህ በኋላ እሷም ሆነች አዳም የአምላክ የበታች እንደማይሆኑ አድርጋ አሰበች። ከእንግዲህ ወዲህ ለሕጎቹ መገዛት እንደሚቀርላቸው አድርጋ አሰበች። ለራሳቸው “መልካም” ወይም “ክፉ” ምን እንደሆነ ራሳቸው መወሰን ሊችሉ ነው። አዳምም ሚስቱን ተከተለና በላ። ሰው በአምላክ ላይ ስለሠራው ኃጢአት ማብራሪያ ሲሰጥ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል በሚባለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ይላል:- “ለራሱ ጥሩና መጥፎ የሆነውን የመወሰንና በዚህ መሠረት የፈለገውን ነገር የማድረግ ሥልጣን መውሰዱ ነበር። ይህም በስነምግባር በኩል ሙሉ ነፃነት ይገባኛል ባይነት ነበር። . . . የመጀመሪያው ኃጢአት በአምላክ የበላይ ገዥነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነበር።” ይህም አምላክ የሰው ፍጹም ገዥ ወይም የበላይ ለመሆን ባለው መብት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነበር።

7. (ሀ) የሰው አለመታዘዝ ምን ጥያቄ አስነሣ? (ለ) ከዚህ አከራካሪ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መንገድ መልስ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ምን ጥያቄዎች ናቸው?

7 ስለዚህ አዳምና ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ በመብላት ራሳቸውን ከአምላክ የበላይ አገዛዝ ሥር አስወጡ። በራሳቸው ውሳኔ መሠረት “መልካም” ወይም “ክፉ” የሆነውን በማድረግ በራሳቸው መንገድ መሄድ ጀመሩ። ስለዚህ አሁን የተነሣው ከፍተኛ የሆነ አከራካሪ ጉዳይ ወይም ጥያቄ:- አምላክ የሰው ዘር ፍጹም ገዥ ለመሆን መብት አለውን? የሚል ነበር። በሌላ አባባል ለሰዎች መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር መወሰን ያለበት ይሖዋ ነውን? የትኛው ትክክለኛ ምግባር እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለመናገር የሚችለው እርሱ ነው ወይስ ሰው ራሱን ቢመራ የተሻለ ነገር ይመጣለታል? ከሁሉ የተሻለው አገዛዝ የማን ነው? ሰዎች ይሖዋ ሳይመራቸው በሰይጣን በስውር እየተመሩ ቢገዙ ይሳካላቸዋልን? ወይስ ለምድር ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችል የጽድቅ መንግሥት ለማቋቋም የአምላክ አመራር ያስፈልጋል? በአምላክ የበላይ ገዥነት ላይ ማለትም በሰው ዘሮች ላይ ብቸኛና ፍፁም ገዥ ለመሆን ባለው መብቱ ላይ የተደረገው ጥቃት እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች አስነስቷል።

8. ይሖዋ ዐመፀኞቹን ወዲያውኑ ለምን አላጠፋቸውም?

8 እርግጥ ነው፤ ዐመፁ እንደተፈጸመ ይሖዋ ሦስቱን አመጸኞች ወዲያው ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። እርሱ ከሰይጣን ወይም ከአዳምና ከሔዋን የበለጠ ኃይል እንዳለው ምንም አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ እነርሱን ማጥፋቱ ለጥያቄዎቹ የተሻለ መልስ አይሆንም። ለምሳሌ ያህል ሰዎች ያለ አምላክ ርዳታ ራሳቸውን በተሳካ ሁኔታ መግዛት ስለመቻላቸው የተነሳውን ጥያቄ አይመልሰውም። ስለዚህ ለተነሳው ከፍተኛ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሖዋ ጊዜ ፈቀደ።

ለጥያቄው መልስ ማስገኘት

9, 10. ሰዎች ያለ አምላክ መመሪያ ራሳቸውን ለመግዛት ያደረጉት ሙከራ ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው?

9 ከዚያ በኋላ ረጅም ጊዜ አልፎአል። ታዲያ ውጤቱ ምንድን ነው? አንተ ራስህ ምን ትላለህ? ያለፈው የ6, 000 ዓመታት ታሪክ ሰዎች አምላክ ሳይመራቸው ራሳቸውን በመግዛት በኩል እንደተሳካላቸው ያሳያልን? ሰዎች ለሁሉም በረከትንና ደስታን የሚያመጣ ጥሩ መንግሥት አስገኝተዋልን? ወይስ የታሪክ መዝገብ “ለሚራመደው ሰው አካሄዱን ለማቅናት አልተሰጠውም” የሚሉት የነቢዩ ኤርምያስ ቃላት ትክክል መሆናቸውን ያሳያል?— ኤርምያስ 10:23 አዓት

10 በታሪክ ውስጥ ሁሉም ዓይነት መንግሥታት ተሞክረዋል፤ ሆኖም የትኞቹም ቢሆኑ በሥራቸው ለሚተዳደሩት ደህንነትንና እውነተኛ ደስታን አላመጡም። አንዳንድ ሰዎች የሚታዩትን የዕድገት ምልክቶች ይጠቅሱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ደጋንና ቀስት በአቶሚክ ቦምብ ከተተኩና በአሁኑ ጊዜ ሌላ የዓለም ጦርነት ይነሳል የሚል ታላቅ ፍርሃት ካለ እውነተኛ ዕድገት አለ ብሎ መናገር ይቻላልን? ሰዎች በጨረቃ ላይ ለመራመድ ችለው በምድር ላይ ግን በሰላም አብረው መኖር ካልቻሉ ይህ ምን ዓይነት ዕድገት ነው? በውስጣቸው የሚኖሩት ቤተሰቦች እርስ በርስ ተበጣብጠው የሚለያዩ ከሆነ በሁሉም ዓይነት ዘመናዊ የቤት ዕቃዎች የተሞሉ ቤቶችን መሥራቱ ምን ጥቅም አለው? በመንገዶች ላይ የሚታዩት ረብሻዎች፣ የንብረትና የሕይወት ጥፋት እንዲሁም እየተስፋፋ ያለው ዐመጽ የሚኮራባቸው ነገሮች ናቸውን? ፈጽሞ አይደሉም! ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ሰዎች ከአምላክ ተገንጥለው ራሳቸውን ለመግዛት መሞከራቸው ያስከተላቸው ውጤቶች ናቸው።— ምሳሌ 19:3

11. እንግዲያው ሁኔታው እንደሚያሳየው ሰዎች ምን ያስፈልጋቸዋል?

11 ማስረጃው ለሁሉም ግልጽ መሆን ይኖርበታል። ሰው ከአምላክ ነፃ ሆኖ ራሱን ለመግዛት ያደረጋቸው ጥረቶች ክፉ ውድቀት አስከትለዋል። በሰው ላይ ታላቅ መከራ አምጥተዋል። “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (መክብብ 8:9 አዓት) ሰዎች ጉዳዮቻቸውን ለመምራት የአምላክ መመሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። አምላክ ሰውን ምግብ መብላትና ውሃ መጠጣት እንዲያስፈልገው አድርጎ እንደፈጠረው ሁሉ ሰው የአምላክን ሕጎች መታዘዝ እንደሚያስፈልገው ተደርጎ ተፈጥሮአል። ሰው ለአካሉ አስፈላጊ የሆኑትን ምግብና ውሃ ችላ ብሎ ቢተው ሥቃይ እንደሚመጣበት የተረጋገጠ እንደ ሆነ ሁሉ የአምላክን ሕጎች ችላ ብሎ ቢጥስ ችግር ላይ ይወድቃል።— ምሳሌ 3:5, 6

ጊዜው ለምን ረዘመ?

12. አምላክ ጥያቄው መልስ እንዲያገኝ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ የፈቀደው ለምንድን ነው?

12 ሆኖም አንድ ሰው ‘አምላክ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማስገኘት 6, 000 ዓመታትን የሚያክል ረጅም ጊዜ ለምን ፈቀደ?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ጥያቄው ከረጅም ጊዜ በፊት አጥጋቢ መልስ ማግኘት አይችልም ነበርን?’ በእርግጥ አይችልም ነበር። አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት ጣልቃ ገብቶ ቢሆን ኖሮ ሰዎች አገዛዛቸውን እንዲሞክሩ በቂ ጊዜ አልተሰጣቸውም የሚል ስሞታ ይቀርብ ነበር። ሆኖም ሰዎች የዜጎቻቸውን ሁሉ ፍላጎት ለማርካት የሚችል መንግሥት ለማቋቋምና ሁሉም ሰው እንዲበለጽግ የሚረዱ ሳይንሳዊ እድገቶች ለማድረግ በቂ ጊዜ አግኝተዋል። ባለፉት ክፍለ ዘመናት ሰዎች ሁሉንም ዓይነት አገዛዝ ሞክረዋል። በሳይንስ መስክ ያደረጉትም ዕድገት አስደናቂ ነው። አቶምን በቁጥጥራቸው ስር አድርገዋል፤ ወደ ጨረቃም ተጉዘዋል። ነገር ግን ውጤቱ ምን ሆኖ ተገኘ? ለሰው ዘር በረከት የሆነ ታላቅና አዲስ ሥርዓት መጥቷልን?

13. (ሀ) ሰው ይህን ሁሉ ሳይንሳዊ እድገት ቢያደርግም እንኳ ዛሬ ያለው ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) ይህስ በግልጽ የሚያረጋግጠው ምንን ነው?

13 እውነተኛው ሁኔታ ከዚያ በጣም የራቀ ነው! በዚህ ፋንታ በምድር ላይ ከምን ጊዜውም የበለጠ ሐዘንና ችግር ያለው አሁን ነው። እንዲያውም ወንጀል፣ የአካባቢ መበከል፣ ጦርነት፣ የቤተሰብ መፈራረስና፣ ሌሎች ችግሮች በጣም አደገኛ ወደሆነ ደረጃ በመድረሳቸው ሳይንቲስቶች የሰው ሕልውና አደጋ ላይ ወድቋል ብለው ያምናሉ። አዎን ሰው ራሱን በራሱ ለመግዛት ለ6, 000 ዓመታት ሙከራ ካደረገና በሳይንሳዊ “እድገት” ጫፍ ላይ ከደረሰ በኋላ የሰው ዘር ራሱን በራሱ የመደምሰስ አደጋ ከፊቱ ተደቅኖበታል! ሰዎች ከአምላክ ተለይተው ራሳቸውን በተሳካ ሁኔታ ለመግዛት አለመቻላቸው እንዴት ግልጽ ነው! ከዚህም በተጨማሪ ካሁን በኋላ ማንም ሰው አምላክ ለዚህ ጥያቄ በቂ ጊዜ አልፈቀደም ብሎ ቅሬታ ሊያሰማ አይችልም።

14. ሰይጣን ያስነሣውን ሌላውን ከፍተኛ ጥያቄ ለመመርመር መበረታታት ያለብን ለምንድን ነው?

14 ሰዎች በሰይጣን አገዛዝ ስር ለዚህን ያህል ረጅም ዘመን ክፋት እንዲያደርጉ ለመፍቀድ አምላክ በእርግጥ ምክንያት ነበረው። ሰይጣን በጀመረው ዐመፅ መልስ ለማግኘት ጊዜ የሚያስፈልገው ሌላ ጥያቄም አስነስቷል። ይህንን ጥያቄ መመርመራችን አምላክ ክፋት እንዲቀጥል ለምን እንደፈቀደ ለማስተዋል በበለጠ ይረዳናል። በተለይ ይህ ጉዳይ አንተን በግል የሚመለከትህ በመሆኑ ስለዚሁ ለማወቅ ፍላጎትህ ሊነሳሳ ይገባዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 100 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕመሙ የሚያሰቃይ ቢሆንም እንኳ አንድ ወላጅ ልጁ ቀዶ ጥገና እንዲደረግለት ለመፍቀድ ጥሩ ምክንያት አለው። አምላክም ሰዎች ለጊዜው መከራ እንዲደርስባቸው ለመፍቀድ ጥሩ ምክንያቶች አሉት።

[በገጽ 101 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳምና ሔዋን የተከለከለችውን ፍሬ በመብላት ከአምላክ አገዛዝ ኰበለሉ። ጥሩና መጥፎ የሆኑትን ነገሮች በሚመለከት የራሳቸውን ውሳኔዎች ማድረግ ጀመሩ።

[በገጽ 103 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰው ሲፈጠር የሚበላ ምግብና የሚጠጣ ውኃ እንዲያስፈልገው ተደርጎ እንደተሠራ ሁሉ የአምላክ መመሪያም እንደሚያስፈልገው ተደርጎ ተፈጥሯል።