በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የሚባለው ማን ነው?

አምላክ የሚባለው ማን ነው?

ምዕራፍ 4

አምላክ የሚባለው ማን ነው?

1. (ሀ) ሕዝቦች የትኞቹን አማልክት አምልከዋል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በ“አማልክት“ እና በ“እውነተኛው አምላክ“ መካከል ምን ልዩነት ያደርጋል?

በዓለም ዙሪያ ሰው የሚያመልካቸው ብዙ አማልክት አሉ። በሺንቶ፣ በቡድሂስት፣ በሂንዱና በብዙዎቹ ልዩ ልዩ ጐሳዎች ሃይማኖቶች ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ አማልክት አሉ። በኢየሱስ ሐዋርያት ዘመን እንደ ዘዩስና ሄርሜስ የተባሉ አማልክት ይመለኩ ነበር። (ሥራ 14:11, 12) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ አማልክት አሉ“ በሚለው አባባል ይስማማል፤ ሆኖም “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን“ ይላል። (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ’ይህ አምላክ ማን ነው?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን ትላለህ?

2. ሰዎች ስለ አምላክ ምን የተለያየ አመለካከት አላቸው?

2 ’ጌታ ነዋ!’ በማለት ብዙዎች ይመልሳሉ። ወይም ’በሰማይ የሚገኝ አንድ መንፈሳዊ አካል ነው’ ይሉ ይሆናል። አንድ መዝገበ ቃላት አምላክን “ከሁሉም በላይ የሆነው አካል“ ብሎ ጠርቶታል። አንዳንድ ሰዎች ’የአምላክ ስም ማን ነው?’ ተብለው ሲጠየቁ ’ኢየሱስ ነዋ!’ ብለው ይመልሳሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ አንድ ሕያው አካል እንደሆነ አድርገው ሳይሆን በየትም ስፍራ የሚገኝ ብርቱ ኃይል እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። አንዳንዶች ግን አምላክ መኖሩንም ይጠራጠራሉ። ታዲያ እኛ ስለመኖሩ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለንን?

አምላክ በእርግጥ አለ

3. ቤት እንዴት ይገኛል?

3 አንድ ግሩም የሆነ ሕንፃ ስትመለከት ’የሠራው ማን ይሆን?’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህን? አንድ ሰው ’ሕንፃውን ማንም አልሠራውም፤ እንዲሁ ራሱ የመጣ ነው’ ቢልህ ታምነው ነበርን? በፍጹም አታምነውም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንደተናገረው “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአል።” ሁሉም ሰው ይህንን ያውቃል። ታዲያ ያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ቀጥሎ “ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው“ ሲል ያቀረበውን ምክንያታዊ መደምደሚያ ለመቀበል አንችልምን?—ዕብራውያን 3:4

4. በብዙ ቢልዮን የሚቆጠሩት ከዋክብት እንዴት ነው?

4 እልፍ አእላፋት ከዋክብትን የያዘውን አጽናፈ ዓለም እንውሰድ። እነዚህ ሁሉ ከዋክብት ቢኖሩም ፍጹም ትክክለኛ የሆነ ቦታቸውን እንዲጠብቁ በሚያደርጉት ሕጎች መሠረት በሰማያት ውስጥ ይጓዛሉ። ከረጅም ዘመን በፊት “እነዚህን የፈጠረ ማን ነው?“ ተብሎ ተጠይቆ ነበር። “ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል“ ተብሎ የተሰጠው መልስ ሊታመን የሚችል ነው። (ኢሳይያስ 40:26) በቢልዮን የሚቆጠሩት ከዋክብት የተሠሩት በራሳቸው ነው፤ ደግሞም ታላላቆቹ ሥርዓተ ከዋክብት ማንም ሳይመራቸው የሚያስደንቅ ሥርዓት ጠብቀው ይጓዛሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።—መዝሙር 14:1

5. (ሀ) የተለያዩት ክፍሎቹ በራሳቸው ተገጣጥመው ሥጋ መፍጫ ለመሆን ያላቸው ዕድል ምን ያህል ነው? (ለ) ይህ ስለ አጽናፈ ዓለማችን ምን ያሳያል?

5 በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀው ይህ አጽናፈ ዓለም በራሱ በድንገት ሊመጣ አይችልም። ታላቅ ኃይልና የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ ያስፈልገዋል። (መዝሙር 19:1, 2) የንግድ ሥራ የሚያካሂዱ አንድ ሰው ለምን በአምላክ እንደሚያምኑ በተጠየቁ ጊዜ በፋብሪካው ውስጥ አንዲት ልጃገረድ የአንድ የሥጋ መፍጫ መሣሪያ 17 ክፍሎች እንዴት እንደሚገጣጠሙ ለመማር ሁለት ቀን እንደሚፈጅባት ተናግረዋል። ሰውየው እንዲህ አሉ “እኔ የሥጋ መፍጫ መሣሪያ የሚያመርት የአንድ ተራ ፋብሪካ ባለቤት ነኝ፤ ሆኖም የሥጋ መፍጫውን 17 ክፍሎች በማጠቢያ ገንዳ ላይ ለሚቀጥሉት 17 ቢልዮን ዓመታት ስታገለባብጧቸው ብትኖሩ የሥጋ መፍጫ መሣሪያ እንደማታገኙ አውቃለሁ።“ በምድር ላይ ያሉትን የተለያዩ ዓይነት ሕያዋን ፍጥረታት ጭምር የያዘው ይህ አጽናፈ ዓለም ከሥጋ መፍጫ መሣሪያ እጅግ በጣም ይበልጥ የተወሳሰበ ነው። እንደዚህ ያለው መሣሪያ በጣም አዋቂ የሆነ ባለሙያ ካስፈለገው ሁሉንም ነገሮች ለመፍጠር ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እንደሚያስፈልግ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። እንግዲያው ስላደረጋቸው ነገሮች ሁሉ መመስገን ያለበት እርሱ መሆን አይገባውምን?—ራዕይ 4:11፤ ሥራ 14:15-17፤ 17:24-26

አምላክ የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል ነውን?

6. አምላክ የተወሰነ ቅርጽ ያለው አካል ስለመሆኑ እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

6 አብዛኞቹ ሰዎች በአምላክ እንደሚያምኑ ቢናገሩም የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል እንደሆነ አድርገው አያስቡም። ታዲያ እርሱ እንደዚያ ነውን? እንደሚታወቀው ሁሉ የማሰብ ችሎታ ካለ የሚያስብ አእምሮ ይኖራል። ለምሳሌ ያህል ’አእምሮዬ በአንድ ሀሳብ ላይ እንዲረጋ ማድረግ አልቻልኩም’ ብለን ለመናገር እንችላለን። አእምሮ ካለ ደግሞ የተወሰነ ቅርጽ ባለው ሰውነት ውስጥ የተቀመጠ አንጎል እንዳለ እናውቃለን። እንግዲያው ሁሉንም ነገር የፈጠረው ታላቅ አእምሮ በታላቁ ሕያው አካል ማለትም ሁሉንም በሚችለው አምላክ ውስጥ ያለው አእምሮ ነው። እርሱም ሥጋዊ አካል አይኑረው እንጂ መንፈሳዊ አካል አለው። ሕያው የሆነ መንፈሳዊ ነገር አካል አለው እንዴ? አዎን አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ”ይላል።—1 ቆሮንቶስ 15:44፤ ዮሐንስ 4:24

7. (ሀ)አምላክ የሚኖርበት ስፍራ እንዳለው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) አካል እንዳለው የሚያሳየውስ ምንድን ነው?

7 አምላክ የተወሰነ ቅርጽ ያለው መንፈሳዊ አካል ስለሆነ የሚኖርበት ቦታ አለ ማለት ነው። ሰማያት የአምላክ “ማደሪያ“ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (1 ነገሥት 8:43) “ክርስቶስ . . . በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ዕብራውያን 9:24) አንዳንድ ሰዎች የሕይወት ሽልማት አግኝተው በሰማይ ከአምላክ ጋር ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ መንፈሳዊ አካል ይሰጣቸዋል። በዚያን ጊዜ አምላክን እንደሚያዩትና እንደ እርሱ እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:2) ይህም አምላክ ሕያው የሆነና የተወሰነ አካል እንዳለው ያሳያል።

8, 9. (ሀ) አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ሩቅ ቦታ ድረስ መዝለቅ ለሚችለው የአምላክ ኃይል ምሳሌ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምንድን ነው? እርሱስ ምን ማድረግ ይችላል?

8 ይሁንና አንድ ሰው ’አምላክ በሰማይ ውስጥ በተወሰነ ቦታ የሚኖር አንድ እውን አካል ከሆነ በየትም ሥፍራ የሚፈጸመውን እያንዳንዱን ነገር እንዴት ለማየት ይችላል? የእርሱስ ኃይል በማንኛውም የአጽናፈ ዓለም ክፍል ላይ እንዴት ሊሠራ ይችላል?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። (2 ዜና 16:9) አምላክ የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል መሆኑ ኃይሉን ወይም ታላቅነቱን በምንም መንገድ አይወስንበትም። በተጨማሪም ይህ ለእርሱ የሚኖረንን አክብሮት አይቀንሰውም። (1 ዜና 29:11-13) ይህንን ለመረዳት ሩቅ ቦታዎች ድረስ ኃይል ማስተላለፍ የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን እንደምሳሌ አድርገን እንውሰድ።

9 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በከተማ ውስጥ ወይም በአቅራቢያው አንድ የተወሰነ ቦታ አለው። ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይሉ በዚያ አካባቢ ሁሉ ይሰራጭና ብርሃንና ኃይል ይሰጣል። የአምላክም ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። እርሱ የሚኖረው በሰማያት ነው። (ኢሳይያስ 57:15፤ መዝሙር 123:1) ይሁን እንጂ ምን ጊዜም በእንቅስቃሴ ላይ ያለው ኃይሉ ይኸውም በዓይን የማይታየው ቅዱስ መንፈሱ በመላው አጽናፈ ዓለም ይሠራል። አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካይነት ሰማያትን፣ ምድርንና ሕያዋን ነገሮችን በሙሉ ፈጠረ። (መዝሙር 33:6፤ ዘፍጥረት 1:2፤ መዝሙር 104:30) እነዚህን ነገሮች ለመፍጠር አምላክ አካሉን አንቀሳቅሶ በቦታው መገኘት አላስፈለገውም። ሩቅ ቦታ ላይ ቢሆንም እርሱ የፈለገውን ነገር ለማከናወን መንፈሱን ይኸውም ምን ጊዜም በእንቅስቃሴ ላይ ያለውን ኃይሉን ለመላክ ይችላል። እንዴት ያለ አስገራሚ አምላክ ነው!—ኤርምያስ 10:12፤ ዳንኤል 4:35

አምላክ ምን ዓይነት ባሕርይ ያለው ነው?

10. አምላክን ለማወቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

10 አምላክ በደንብ እያወቅነው ብንሄድ ለእርሱ ያለን ፍቅር እያደገ ሊሄድ የሚችል ዓይነት ነውን? ’ምናልባት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን አምላክን እስካላየነው ድረስ ስለእርሱ እንዴት ለማወቅ እንችላለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። (ዮሐንስ 1:18) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት እርሱን ለማወቅ የምንችልበትን አንዱን መንገድ ያሳየናል። “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።“ (ሮም 1:20) እንግዲያውስ አምላክ የፈጠራቸው ነገሮች በእውነት ከመረመርናቸውና ካሰብንባቸው እርሱ ምን ዓይነት እንደሆነ ለማስተዋል ሊረዱን ይችላሉ።

11. ከሠራቸው ነገሮች ስለ አምላክ ምን ለመማር እንችላለን?

11 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በከዋክብት የተሞሉትን ሰማያትን ማየታችን አምላክ ታላቅ እንደሆነና እጅግ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ያረጋግጥልናል። (መዝሙር 8:3, 4፤ ኢሳይያስ 40:26) ከዚያም ምድርን እንውሰድ። አምላክ ከሰማያት ውስጥ ከፀሐይ ትክክለኛ የሙቀትና የብርሃን መጠን ማግኘት በምትችልበት ቦታ ላይ አንጠልጥሏታል። የውኃንም ዑደት እንውሰድ፤ መሬቱን ለማጠጣት ዝናብ ይዘንባል። ውኃው ወደ ወንዞች ይገባል፤ ወንዞቹም ወደ ባሕር ይፈስሳሉ። በባሕር ላይ ያለውን ውኃ ፀሐዩ ወደ ተን እየለወጠ ወደ ላይ ያነሳዋል፤ ከዚያም መሬትን እንደገና ለማጠጣት በዝናብ መልክ ይወርዳል። (መክብብ 1:7) አምላክ ምግብና መጠለያ እንዲሁም ለሰውና ለእንስሳት የሚያስፈልግ ነገር ሁሉ እንዲያስገኙ ብሎ ያዘጋጃቸው በጣም ብዙ አስደናቂ ዑደቶች አሉ! ታዲያ እነዚህ ሁሉ አስደናቂ ነገሮች አምላክ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ይነግሩናል? አምላክ ታላቅ ጥበብ እንዳለውና በጣም ለጋስ መሆኑን እንዲሁም ለፍጡሮቹ እንደሚያስብ ይነግሩናል።—ምሳሌ 3:19, 20፤ መዝሙር 104:13-15, 24, 25

12. የራስህ ሰውነት ስለ አምላክ ምን ያስተምርሃል?

12 ስለ ራስህም ሰውነት እስቲ አስብ። ሰውነትህ እንዲሁ በሕይወት እንዲኖር ብቻ እንዳልተፈጠረ ግልጽ ነው። በሕይወት እንዲደሰት ተደርጎ በአስደናቂ ንድፍ የተሠራ ነው። (መዝሙር 139:14) ዓይናችን ጥቁርና ነጭ ቀለማትን ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማትን ለማየት ይችላል። ዓለማችንም በብዙ ዓይነት አስደሳች ኅብረ ቀለማት የተሞላ ነው። ለማሽተትም ለመቅመስም እንችላለን። ስለዚህ ምግብ መመገብ ለመኖር አስፈላጊ የሆነ ሥራ ብቻ አይደለም፤ አስደሳችም ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉ የተፈጥሮ ስሜቶች በሕይወት ለመኖር የግድ የሚያስፈልጉ አይደሉም። ነገር ግን አፍቃሪ፣ ለጋስና አሳቢ ከሆነ አምላክ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው።—ዘፍጥረት 2:9፤ 1 ዮሐንስ 4:8

13. አምላክ ከሰዎች ጋር ካደረጋቸው ግንኙነቶች ስለ እርሱ ምን ትማራለህ?

13 አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች መመርመርም ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ያስረዳናል። እርሱ ጠንካራ የሆነ የፍትሕ ስሜት አለው። ለተለዩ ዘሮች አድልዎ አያደርግም። (ሥራ 10:34, 35) በተጨማሪም መሐሪና ደግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከግብጽ ባርነት ላዳነው ለእስራኤል ሕዝብ ምን እንዳደረገ ሲገልጽ “እርሱ ግን መሓሪ ነው፣ . . . ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ“ ይላል። ሆኖም እስራኤላውያን ብዙ ጊዜ ሳይታዘዙ ይቀሩ ነበር፤ ይህም አምላክን አሳዘነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አስቈጡት፣ . . . የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።“ (መዝሙር 78:38-41፤ 103:8, 13, 14) በሌላው በኩል ግን አገልጋዮቹ ሕጎቹን ሲታዘዙ አምላክ ደስ ይለዋል። (ምሳሌ 27:11) በተጨማሪም “የሚነካችሁ የዓይኔን ብሌን የሚነካ ነው“ በማለት አምላክ አገልጋዮቹ ጠላቶቻቸው ሲያሰቃዩአቸው እንዴት እንደሚሰማው ገልጾአል። (ዘካርያስ 2:8) በሁሉም ዘሮችና ብሔሮች ለሚገኙ ከቁጥር ለማይገቡና ዝቅተኛ ፍጡሮች ለሆኑ ሰዎች እንደዚህ ያለ ፍቅር የሚያሳይን አምላክ ለመውደድ አትገፋፋምን?—ኢሳይያስ 40:22፤ ዮሐንስ 3:16

አምላክ ኢየሱስ ወይም ሥላሴ ነውን?

14. የሥላሴ ትምህርት ምንድን ነው?

14 ይህ አስደናቂ አምላክ ማን ነው? አንዳንድ ሰዎች ስሙ ኢየሱስ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ምንም እንኳን “ሥላሴ“ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም እርሱ ሥላሴ ነው ይላሉ። በሥላሴ ትምህርት መሠረት በአንድ አምላክ ሦስት አካሎች አሉ። በሌላም አነጋገር “አባት፣ ልጅና መንፈስ ቅዱስ የሆነ አንድ አምላክ አለ“ ይባላል። ብዙዎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ነገሩ “ምሥጢር“ ነው ብለው ቢናገሩም ይህንን አሳብ ያስተምራሉ። ሰዎች ስለ አምላክ ያሉአቸው እንደነዚህ ያሉ አመለካከቶች ትክክል ናቸውን?

15. አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ እኩል ያልሆኑ ሁለት የተለያዩ አካሎች መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ያሳያል?

15 ለመሆኑ ኢየሱስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ ያውቃልን? በፍጹም አላለም። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የእግዚአብሔር ልጅ“ ተብሎ ተጠርቷል። እርሱም “ከእኔ አብ ይበልጣል“ ብሎአል። (ዮሐንስ 10:34-36፤ 14:28) ከዚህም ሌላ አምላክ ብቻ የሚያውቃቸው እርሱና መላእክት ግን የማያውቋቸው አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማርቆስ 13:32) አንድ ጊዜም ኢየሱስ “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ“ እያለ ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ሉቃስ 22:42) ኢየሱስ ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ ቢሆን ኖሮ ወደራሱ አይጸልይም ነበር፤ ይጸልይ ነበር እንዴ? እንዲያውም ቅዱስ ጽሑፉ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ የሆነውን ሲገልጽ “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው“ ይላል። (ሥራ 2:32) እንግዲያው ሁሉን የሚችለው አምላክና ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ አካሎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ሞቶ ከተነሣና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም ቢሆን ከአባቱ ጋር እኩል አልነበረም።—1 ቆሮንቶስ 11:3፤ 15:28

16. ኢየሱስ “አምላክ“ እየተባለ ቢጠቀስም እንኳን እርሱ ሁሉን የሚችለው አምላክ እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

16 ’ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ አምላክ ተብሎ ተጠርቶ የለምን?’ በማለት አንዳንዶች ይጠይቁ ይሆናል። ይህ እውነት ነው። ሆኖም ሰይጣንም አምላክ ተብሎ ተጠርቷል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ኢየሱስ “ቃል“ ተብሎ በተጠቀሰበት በዮሐንስ 1:1 ላይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዲህ ይላሉ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።“ ይሁን እንጂ ቁጥር ሁለት ላይ ቃል “በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ“ ወይም እግዚአብሔር ጋር ነበረ ብሎ መናገሩን አስተውል። ኢየሱስን ሰዎች አይተውታል። ቁጥር 18 ግን “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድስ ስንኳ የለም“ ይላል። ስለዚህ አንዳንድ ትርጉሞች “ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፣ ቃልም መለኰታዊ ነበር“ ወይም “አምላክ ነበር“ በማለት ጽሑፉ በመጀመሪያ የተጻፈበት ቋንቋ የሚያስተላልፈውን ትክክለኛ ሀሳብ ይሰጣሉ። ይህም ማለት ቃል ኃይለኛ የሆነ አምላክ መሰል ነበር ማለት ነው። በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ኢየሱስ ሁሉን የሚችለው አምላክ አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ አባቱን “አምላኬ“ እንዲሁም “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንህ“ ብሎ ጠርቶታል።—ዮሐንስ 20:17፤ 17:3 የ1980 እትም

17. መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ መፍሰሱ የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል ያለመሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

17 ሦስተኛው የሥላሴ አካል ነው የሚባልለት “መንፈስ ቅዱስ” ግን ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል እንጂ ራሱን የቻለ ሕያው አካል አይደለም። መጥምቁ ዮሐንስ እርሱ በውኃ ያጠምቅ እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ ተናግሯል። ስለዚህ ውኃ የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል እንዳልሆነ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል አይደለም። (ማቴዎስ 3:11) ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው በነበሩት ተከታዮቹ ላይ መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰ ጊዜ ዮሐንስ አስቀድሞ የተናገረው ተፈጽሞአል። መጽሐፍ ቅዱስ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው“ ይላል። (ሥራ 2:4) የተሞሉት ሕያው በሆነ አካል ነበርን? አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የተሞሉት በተንቀሳቃሹ የአምላክ ኃይል ነበር። እንግዲያው ሥላሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዳልሆነ ማስረጃዎቹ ግልጽ ያደርጉታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት እንደ ጥንቷ ግብጽና ባቢሎን በመሳሰሉት ስፍራዎች አማልክት በሦስት በሦስት እየተደረጉ ወይም በሥላሴዎች መልክ ይመለኩ ነበር።

የአምላክ ስም

18. (ሀ) ሁሉን የሚችለው አምላክ ስሙ “አምላክ“ ነውን? (ለ) የግል ስሙ ማን ነው?

18 የምታውቀው ሰው ሁሉ ስም እንዳለው አያጠራጥርም። አምላክም ከሌሎች ተለይቶ የሚታወቅበት የግል ስም አለው። ’ስሙ “አምላክ“ አይደለም እንዴ?’ በማለት አንድ ሰው ይጠይቅ ይሆናል። አይደለም፤ ምክንያቱም “ፕሬዚዳንት“ እና “ንጉሥ“ የሚሉት ቃላት የማዕረግ ስሞች እንደሆኑ ሁሉ “አምላክ“ የሚለውም ቃል እንዲሁ የማዕረግ ስም ብቻ ነው። የአምላክ ስም ማን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል። ለምሳሌ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን በተባለው የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ መዝሙር 83:18 እንደሚከተለው ይነበባል፦ “አንተ ብቻ ስምህ ይሖዋ የሆንከው በመላዋ ምድር ላይ የመጨረሻው የበላይ መሆንህን ሰዎች ይወቁ።“ በተጨማሪም የአምላክ ስም “ሃሌ ሉያ“ የሚለው ሐረግ ክፍል በመሆን በአብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ በራዕይ 19:1-6 ላይ ይገኛል። ሃሌ ሉያ “ያህን አመስግኑት“ ማለት ሲሆን “ያህ“ የይሖዋ አጭር አጠራር ነው። በ1954 በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዘፍጥረት 22:14​ና በዘፀአት 17:15 ላይ “ያህዌህ“ ይላል። በተጨማሪም የ1980ው የአማርኛ ትርጉም ወደ መጨረሻው አካባቢ በገጽ 301 ላይ “እግዚአብሔር“ የሚለው ቃል ምንን ለማመልከት እንደገባ ሲገልጽ “በዕብራይስጥ “ያህዌህ“ ወይም በአንዳንድ ትርጉም “ይሆዋ“ የሚለውን ስም ያመለክታል“ ብሏል።

19. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክን ስም ሲያዩ ለምን ይደነቃሉ? (ለ) በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ የት ላይ ይገኛል?

19 አንዳንድ ሰዎች የአምላክን ስም በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲያዩት ይደነቃሉ። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚሆንበት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሳቸው በአምላክ ስም እየደጋገመ ስለማይጠቀም ነው። ለምሳሌ ያህል በ1879 የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ“ የሚለውን ስም ለብቻው ነጥሎ በዘፀአት 6:3 ላይ ብቻ ተጠቅሞበታል። የእንግሊዝኛው ኪንግ ጄምስ ቨርሽን ደግሞ በዘፀአት 6:3፣ በመዝሙር 83:18፣ በኢሳይያስ 12:2፣ 26:4 ላይ ለብቻው ነጥሎ ተጠቅሞበታል። ቢሆንም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ስም “ጌታ“ ወይም “አምላክ“ ብሎ ሲተረጉም እነዚህን የማዕረግ ስሞች በእንግሊዝኛ “LORD“ እና “GOD“ በማለት በትልልቅ ፊደላት (Capital letters) በመጻፍ የወል ስሞች ከሆኑት “Lord“ እና “God“ ከሚሉት ቃላት እንዲለዩ አድርጐአል። ይህንን አጻጻፍ በዚያው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 110:1 ላይ ተመልከት።

20. (ሀ) የአምላክ ስም ብዙ ጊዜ ያልተሠራበት ለምንድን ነው? (ለ) እንደዚያስ መሆን ነበረበትን?

20 ይሁን እንጂ “አሁን ባሉት መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ስሙ በበኩረ ጽሑፉ በሚገኝባቸው ስፍራዎች ሁሉ ለምን አልገባም? በቦታው ጌታና አምላክ የሚሉት ቃላት ለምን ተተኩ?“ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ በመቅድሙ ላይ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለምን እንደተጠቀመበትና ከዚያ በፊት ለረጅም ዘመናት ተርጓሚዎች ስሙን ያልተጠቀሙበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ያስረዳል “የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጂዎች ጉዳዩን በጥንቃቄ ከመረመሩ በኋላ ስሙ በጣም ቅዱስ በመሆኑ በቃል ሊነገር አይገባውም የሚለው የአይሁዶች አጉል እምነት በእንግሊዝኛም ይሁን በሌላ ቋንቋ በሚተረጐመው ላይ ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ተጽዕኖ ሊያደርግ አይገባውም በማለት በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል . . . ከብዙ ቅዱሳን ነገሮች ጋር የተያያዘው ይህ የግል ስም በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሶአል። ይህንንም ቦታ ለመያዝ የማያጠያይቅ መብት አለው።“ አዎን፤ የዚህ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲወጣ ተደርጐ የነበረበት ምክንያት ትክክል እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትክክለኛ ቦታዎቹ ላይ መልሰው አስቀምጠውታል።

21. ዱዌይ ቨርሽን የተባለው የካቶሊኮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይሖዋ ስለሚለው ስም ምን ይላል?

21 ሆኖም “ይሖዋ“ የሚለው ቃል ትክክለኛው የአምላክ ስም ስላልሆነ ልንጠቀምበት አይገባም ብለው የሚከራከሩ አሉ። ለምሳሌ በዋናው ምንባቡ ላይ በአምላክ ስም የማይጠቀመው ዱዌይ ቨርሽን የተባለው የካቶሊኮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ስለ ዘፀአት 6:3 በሰጠው የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ ብሎአል፦ “አንዳንድ ዘመናውያን ይሖዋ የሚለውን ስም ፈጥረዋል . . . ስሙ በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ቢገኝም ለረጅም ጊዜ ሳይሠራበት ስለቆየ እውነተኛ አጠራሩ አሁን አይታወቅም።“

22. (ሀ) በዕብራይስጥ ቋንቋ የአምላክ ስም እንዴት ይጻፋል? (ለ) በመጀመሪያው ላይ የአምላክ ስም እንዴት ይጠራ እንደነበረ ለማወቅ የሚያስቸግረው ለምንድን ነው?

22 አዎን፤ የካቶሊኮቹ መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ እንደተናገረው የአምላክ ስም በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ይገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት የተጻፉበት ቋንቋ ዕብራይስጥ ነው። እዚያ ውስጥ የአምላክ ስም የ-ሐ-ወ-ሐ ከሚሉት የአማርኛ ፊደላት ጋር ተመሳሳይ ድምፅ በሚሰጡ አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኝ ነበር። በድሮ ዘመን የዕብራይስጥ ቋንቋ የፊደላትን ትክክለኛ ንባብ ለማወቅ የሚያስችሉ አናባቢ ምልክቶች ወይም ፊደሎች አልነበሩትም። ስለዚህ ዛሬ ያለው ችግር ዕብራውያኑ የ-ሐ-ወ-ሐ የሚሉትን መሠረታዊ ፊደላት ሲያነቡ በየትኞቹ አናባቢ ምልክቶች ይጠቀሙ እንደነበረ ለማወቅ የምንችልበት መንገድ አለመኖሩ ነው።

23. “ሕንፃ“ የሚለው ቃል “ሐነፀ“ ተብሎ ቢጻፍ የአምላክን ስም በትክክል ስለመጥራት የሚፈጠረውን ችግር ለማስተዋል የሚረዳን እንዴት ነው?

23 ችግሩን ለመረዳት ያህል “ሕንፃ“ የሚለውን ቃል እንውሰድ። ቅጥያዎቹ ቀርተው ቃሉ ሁልጊዜ “ሐነፀ“ ተብሎ መጻፍ ተጀመረና ከጊዜ በኋላ ሰዎች በቃሉ መጠቀም አቆሙ እንበል። ታዲያ ከ1,000 ዓመት በኋላ “ሐነፀ“ የሚለውን ቃል በጽሑፍ የተመለከተ ሰው የመጀመሪያ ንባቡን እንዴት ለማወቅ ይችላል? ከዚያ በፊት ቃሉን ስላልሰማውና የቃሉን አናባቢ ምልክቶች ስለማያውቅ ስለ አነባቡ እርግጠኛ ለመሆን አይችልም። የአምላክ ስም ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። አንዳንድ ምሑራን “ያህዌህ“ የሚለው አጠራር ትክክለኛ ነው ቢሉም ቃሉ እንዴት ይነበብ እንደነበረ በትክክል አይታወቅም። ቢሆንም ይሖዋ ወይም በእንግሊዝኛ “ጅሆቫ“ የሚለው አጠራር ለብዙ ዓመታት ሲሠራበት የቆየና በስፋት የሚታወቅ ነው።

24. (ሀ) በአንድ ቃል የምንረጋ እንድንሆን በአምላክ ስም መጠቀማችን ለምን ተገቢ ነው? (ለ) በሥራ 15:14 መሠረት በአምላክ ስም መጠቀሙ ለምን በጣም አስፈላጊ ነው?

24 ታዲያ የአምላክ ስም ልክ እንደ መጀመሪያው አጠራሩ አድርገን ላንጠራው ብንችልም ልንጠቀምበት ይገባልን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ የሌሎች ሰዎች ስሞች ልክ እንደ መጀመሪያው አድርገን ባንጠራቸውም እንጠቀምባቸዋለን። ለምሳሌ የኢየሱስ ስም በዕብራይስጥ “የሽዋ“ ተብሎ ይነበባል። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጠውን የአምላክ ስም “ያህዌህ“ ወይም “ይሖዋ“ ወይም በቋንቋችን በተለመደ በሌላ መንገድ እየጠራን ልንጠቀምበት ይገባናል። ስህተት የሚሆነው በስሙ አለመጠቀሙ ነው። ለምን? ምክንያቱም ስሙን የማይጠቀሙበት አምላክ “ለስሙ የተጠሩ ሕዝቦች“ አድርጐ ከሚወስዳቸው መሐከል አይሆኑም። (ሥራ 15:14) የአምላክን ስም ማወቁ ብቻ አይበቃም። ኢየሱስ በምድር ሳለ ያደርግ እንደነበረው በሌሎች ፊት ስሙን ማወደስ አለብን።—ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6, 26

ዓላማ ያለው አምላክ

25. (ሀ) ስለ አምላክ ምን ነገሮችን መረዳት ሊያዳግተን ይችላል? (ለ) ይሖዋ መፍጠር እንዲጀምር ያንቀሳቀሰው ምንድን ነው?

25 አእምሮአችን ሊረዳው የሚከብደው ቢሆንም ይሖዋ መጀመሪያ አልነበረውም፤ ፍጻሜም አይኖረውም። እርሱ “የዘላለም ንጉሥ“ ነው። (መዝሙር 90:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17 አዓት) መፍጠር ከመጀመሩ በፊት ይሖዋ በኅዋው ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ በራሱ የተሟላ ስለሆነና ምንም ነገር ስለማይጎድለው የብቸኝነት ስሜት አልነበረውም። ሌሎችን እንዲፈጥር፣ የሚደሰቱበትን ሕይወት እንዲሰጣቸው የገፋፋው ፍቅር ነው። የመጀመሪያዎቹ የአምላክ ፍጥረታት ልክ እንደ እርሱ ሕያው መንፈሳዊ አካል ያላቸው ነበሩ። ምድር ለሰዎች ከመዘጋጀቷ በፊትም ቢሆን ታላቅ የመንፈሳዊ ልጆች ድርጅት ነበረው። እነርሱም ከሕይወትና ይሖዋ እንዲፈጽሙት ከሚሰጣቸው አገልግሎት ታላቅ ደስታ እንዲያገኙ ዓላማው ነበር።—ኢዮብ 38:4, 7

26. አምላክ ለምድር ያወጣው ዓላማ እንደሚፈጸም ለምን እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን?

26 ምድር ከተሰናዳች በኋላ ይሖዋ አዳምና ሔዋን የተባሉ ባልና ሚስት ቀደም ሲል ገነት ተደርጐ በነበረው የምድር ክፍል ላይ አስቀመጣቸው። እርሱን የሚታዘዙትና የሚያመልኩት፤ እንዲሁም ያችን ገነት በመላዋ ምድር ላይ የሚያስፋፉ ልጆች እንዲወልዱ ዓላማው ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተማርነው ያ ታላቅ ዓላማ የሚያስተጓጉል እክል አጋጠመው። አዳምና ሔዋን አምላክን ላለመታዘዝ መረጡ፤ ስለዚህ ዓላማው እስከ ዛሬ ድረስ አልተፈጸመም። ይሁን እንጂ ወደፊት የግድ ይፈጸማል፤ ይሖዋ ዓላማዎቹን አለመፈጸሙ ሽንፈትን መቀበል ማለት ይሆንበታል። ይህንን ደግሞ ፈጽሞ ሊያደርገው አይችልም! “ፈቃዴን ሁሉ እፈጽማለሁ። ተናግሬአለሁ፤ እፈጽምማለሁ“ በማለት በግልጽ አስታውቋል።—ኢሳይያስ 46:10, 11

27. (ሀ) በአምላክ ፊት ለምን ተጠያቂዎች ነን? (ለ) ስለዚህ የትኛውን ጥያቄ በጥሞና እንድናስብበት ያስፈልጋል?

27 ከአምላክ ዓላማ ጋር እንዴት መስማማት እንደምትችል አሁን ይታይሃልን? የአምላክ ፈቃድ ምን መሆኑን ሳትመረምር የፈለግኸውን በማድረግ አይደለም። ሰይጣንም ሆነ አዳምና ሔዋን ያደረጉት ይህንን ነው። የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቁ ነበር፤ ግን አላደረጉትም። አምላክም ለፈጸሙት ነገር ተጠያቂ አደረጋቸው። እኛስ በአምላክ ፊት ተጠያቂ ነንን? አዎን፤ ምክንያቱም የሕይወታችን ምንጭ አምላክ ነው። ሕይወታችን በእርሱ ላይ የተመካ ነው። (መዝሙር 36:9፤ ማቴዎስ 5:45) እንግዲያው አኗኗራችንን አምላክ ለእኛ ካለው ዓላማ ጋር የቱን ያህል አስማምተነዋል? የዘላለም ሕይወት ዕድላችን በዚህ ላይ የተመካ ስለሆነ ስለዚሁ ጉዳይ አጥብቀን ማሰብ ይኖርብናል።

ይሖዋን እንዴት ማምለክ ይገባል?

28. አንዳንድ ሰዎች አምላክን በምን ነገሮች እየተረዱ አምልከዋል?

28 ይሖዋን የምናመልክበት መንገድ ሊታሰብበት የሚገባው በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። እኛ ከተማርንበት መንገድ የተለየ ሊሆን ቢችልም እርሱ በሚለው መንገድ ማምለክ አለብን። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች በአምልኮታቸው ውስጥ በምስሎች መጠቀማቸው የተለመደ ነው። ምስሉን እንደማያመልኩትና እርሱን ማየታቸውና መንካታቸው አምላክን ለማምለክ እንደሚረዳቸው ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ በምስሎች እየተረዳን እንድናመልከው ይፈልጋልን?

29. ለአምልኮ በምስሎች መጠቀሙ ስህተት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ያሳያል?

29 አምላክ እንደዚያ አይፈልግም። በዚሁ ምክንያት አምላክ ለዓይን በሚታይ በአንዳችም ዓይነት ቅርጽ እንዳልተገለጠላቸው ሙሴ ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 4:15-19) እንዲያውም ከአሥሩ ትዕዛዛት አንዱ “የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም“ ይላል። (ዘፀአት 20:4, 5) መመለክ ያለበት ይሖዋ ብቻ ነው። ምስል መሥራት ወይም በፊቱ ተደፍቶ መስገድ፣ ከይሖዋ በቀር ማንኛውንም ሌላ ሰው ወይም ነገር ማምለክ ስህተት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ እየደጋገመ ይናገራል።—ኢሳይያስ 44:14-20፤ 46:6, 7፤ መዝሙር 115:4-8

30. (ሀ) ኢየሱስና ሐዋርያቱ በምስሎች መጠቀሙ ስህተት መሆኑን የሚያሳይ ምን ነገር ተናግረዋል? (ለ) በዘዳግም 7:25 መሠረት ምስሎች ምን መደረግ አለባቸው?

30 እንግዲያው ኢየሱስ ለአምልኮ በምስሎች በፍጹም አልተጠቀመም። ይህም ልንጠብቀው የምንችል ነገር ነው። “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል“ ሲል ኢየሱስ ገልጾአል። (ዮሐንስ 4:24) የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ይህንን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ምስሎች ለአምልኮ ይረዳሉ በማለት አልተጠቀሙባቸውም። እንዲያውም የእርሱ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም“ ብሎአል። (2 ቆሮንቶስ 5:7) የእርሱ ሐዋርያ የነበረው ዮሐንስም “ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ“ ሲል አስጠንቅቋል። (1 ዮሐንስ 5:21) ቤትህ ውስጥ ዙሪያውን ተመልክተህ ይህን ምክር እየሠራህበት ስለመሆንህ ለምን ራስህን አትጠይቅም?—ዘዳግም 7:25

31. (ሀ) አንድ ዓይነት የአምላክ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ባይገባንም እንድንታዘዘው የሚገፋፋን ምንድን ነው? (ለ) ምን ለማድረግ መሞከር ይኖርብናል? የትኛውንስ ጥሪ መቀበል አለብን?

31 ፈጣሪያችን በሚመራን መንገድ እርሱን ማምለካችን እውነተኛ ደስታ እንደሚያመጣልን የተረጋገጠ ነው። (ኤርምያስ 14:22) ይሖዋ እንድናደርጋቸው የሚጠይቀን ነገሮች ለጥቅማችን እንደሆኑ፣ ለዘላለማዊ ደህንነታችን እንደሚበጁ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እውነት ነው፣ ዕውቀታችንና የኑሮ ልምዳችን ውስን በመሆኑ አምላክ የሰጠው አንድ ሕግ ያን ያህል ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ወይም እንዴት ሊጠቅመን እንደሚችል አንዳንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ላይገባን ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ከእኛ እጅግ በጣም የበለጠ እንደሚያውቅ ያለን ጽኑ እምነት በፈቃደኛ ልብ እንድንታዘዘው ሊገፋፋን ይገባል። (መዝሙር 19:7-11) እንግዲያው “ኑ፣ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር (“በይሖዋ“-አዓት) ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፣ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና“ የሚለውን ጥሪ ተቀብለን የምንችለውን ሁሉ ስለ ይሖዋ ብዙ ለመማር ማንኛውንም ጥረት እናድርግ።—መዝሙር 95:6, 7

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 42 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም የሚገኝባቸው ሦስት ቦታዎች

ዘፀአት 6:3 (የ1879 ትርጉም)

እግዚአብሔር ለሙሴ ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ለአብርሐምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ (ኤልሸደይ) ተገለጥሁ፤ በስሜም እግዚኣ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም ከርሳቸውም ጋር ኪዳን አቆምሁ፤ የከነዓንን የእንግድነታቸውን ምድር እሰጣቸው

ዘፍጥረት 22:14

፲፬ አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል። ፲፭ የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፤ እንዲህም አለው፦ ፲፮ እግዚአብሔር በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና አንድን ልጅህንም አልከለከልህምና ፲፯ በእውነት በረከትን እባር

ዘፀአት 17:15

፲፬ እግዚአብሔርም ሙሴን የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፣ በኢያሱም ጆሮ ተናገረው አለው። ፲፭ ሙሴም መሰዊያ ሠራ፤ ስሙንም ያህዌህ ንሲ ብሎ ጠራው፤ እርሱም እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለ ጫነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ለልጅ ልጅ ይሁን አለ።

[በገጽ 34 እና 35 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ቤት ሠሪ ካለው . . . ከዚያ የበለጠ ውስብስብ የሆነው አጽናፈ ዓለም ሠሪ እንደሚኖረው የተረጋገጠ ነው

[በገጽ 39 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ወደ አምላክ ከጸለየና የራሱ ሳይሆን የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም ከጠየቀ ሁለቱም አንድ አካል ሊሆኑ አይችሉም

[በገጽ 40 እና 41 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈስ ቅዱስ 120 ደቀመዛሙርትን በአንድ ጊዜ ከሞላባቸው እንዴት የተወሰነ ቅርጽ ያለው ሕያው አካል ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 45 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምልኮ በምስሎች መጠቀሙ ትክክል ነውን?