ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ የተላከ ነበርን?
ምዕራፍ 6
ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ የተላከ ነበርን?
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎች የሐሳብ ፈጠራ ሳይሆን በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ስለ ኢየሱስ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
ከጥቂቶች በስተቀር ዛሬ ያለ እያንዳንዱ ሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰምቷል። ኢየሱስ በታሪክ ላይ ከማንም ሰው የበለጠ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሚሠራበት የቀን መቁጠሪያ ኢየሱስ ተወልዶበታል ተብሎ በታሰበው ዓመት ላይ የተመሠረተ ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዳለው “ከዚያች ዓመት በፊት የነበሩት ዘመናት ከክርስቶስ ልደት በፊት [BC] ተብለው ሲጠሩ ከዚያ በኋላ ያሉት ደግሞ አኖ ዶሚኒ [AD] (ማለትም በጌታችን ዓመት) ተብለው ይጠራሉ።”
2 ስለዚህ የኢየሱስ ታሪክ የሰዎች የሐሳብ ፈጠራ አልነበረም ማለት ነው። በምድር ላይ ሰው ሆኖ በእርግጥ ኖሯል። “በድሮ ዘመናት የክርስትና ተቃዋሚዎችም እንኳን ቢሆኑ ክርስቶስ የሚባል ስለመኖሩ ፈጽሞ አልተጠራጠሩም” ሲል ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ተናግሯል። እንግዲያው ኢየሱስ ማን ነበር? በእርግጥ ከአምላክ ተልኮ የመጣ ነበርን? ይህን ያህል በጣም የታወቀውስ ለምንድን ነው?
በፊት በሕይወት የነበረ ነው
3. (ሀ) መልአኩ በተናገራቸው ቃላት መሠረት ማርያም የምትወልደው የማንን ልጅ ነበር? (ለ) ድንግልዋ ማርያም ኢየሱስን ለመጸነስ የቻለችው እንዴት ነው?
3 የኢየሱስ አወላለድ ከማንኛውም ሌላ ሰው አወላለድ የተለየ ነበር። የተወለደው ከድንግል ሲሆን ስሟ ማርያም ነበር። አንድ መልአክ ስለ ልጅዋ ሲናገር “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል” አለ። (ሉቃስ 1:28–33፤ ማቴዎስ 1:20–25) ይሁን እንጂ ከወንድ ጋር ሩካቤ ሥጋ ፈጽማ የማታውቅ ሴት እንዴት ልጅ ለመውለድ ቻለች? በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካይነት ነው። ይሖዋ የኃያሉን መንፈሳዊ ልጁን ሕይወት ከሰማይ አውርዶ ወደ ድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ አዛወረው። ነገሩ ተአምር ነበር! ለመጀመሪያዋ ሴት ልጅን የመውለድ አስደናቂ ችሎታ የሰጠ ፈጣሪ አንዲት ሴት ያለ ሰብዓዊ አባት ልጅ እንድትወልድ ማድረግ እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ሲል ይገልጽልናል።—ገላትያ 4:4
4. (ሀ) ኢየሱስ ሕፃን ሆኖ ከመወለዱ በፊት ምን ዓይነት አስደሳች ሕይወት ነበረው? (ለ) ኢየሱስ ቀደም ሲል በሰማይ ይኖር እንደነበረ ለማሳየት ምን ብሎ ተናገረ?
4 ስለዚህ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ከመወለዱ በፊት በሰማይ ውስጥ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር ነበር። እርሱም ልክ እንደ አምላክ ለሰው ዓይን ሊታይ የማይችል መንፈሣዊ አካል ነበረው። (ዮሐንስ 4:24) በሰማይ ስለነበረው ከፍተኛ ቦታ ኢየሱስ ራሱ በተደጋጋሚ ተናግሯል። አንድ ጊዜ “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” ሲል ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:5) በተጨማሪም ለአድማጮቹ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “እናንተ ከታች ናችሁ እኔ ከላይ ነኝ።” “እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?” “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ።”—ዮሐንስ 8:23፤ 6:62፤ 8:58፤ 3:13፤ 6:51
5. (ሀ) ኢየሱስ “ቃል” “የበኩር ልጅ” “አንድያ ልጅ” ተብሎ ለምን ተጠራ? (ለ) ኢየሱስ ከአምላክ ጋር በምን ሥራ ተካፋይ ሆኖ ነበር?
5 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የአምላክ ቃል ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህ የማዕረግ ስም እርሱ በሰማያት ውስጥ ስለ አምላክ ሆኖ ይናገር እንደነበር ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ “የአምላክ የበኩር ልጅ” እንዲሁም “አንድያ ልጁ” ተብሎ ይጠራል። (ዮሐንስ 1:14፤ 3:16፤ ዕብራውያን 1:6) ይህም ከሌሎቹ የአምላክ መንፈሳውያን ልጆች ሁሉ በፊት የነበረውና በአምላክ በቀጥታ የተፈጠረው እርሱ ብቻ ነው ማለት ነው። ሌሎቹ ነገሮች በሙሉ ሲፈጠሩ ይህ “የበኩር ልጅ” ከይሖዋ ጋር ሆኖ በሥራው ይካፈል እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። (ቆላስይስ 1:15, 16) ስለዚህ አምላክ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ባለ ጊዜ ያነጋገረው ይህንን ልጅ ነበር። አዎን በኋላ ወደ ምድር የመጣውና ከሴት የተወለደው መንፈሣዊ ፍጡር ሌሎች ነገሮችን በሙሉ በመፍጠሩ ሥራ ተካፍሎአል። ከዚያ በፊት ላልታወቁ ብዙ ዓመታት በሰማይ ከአባቱ ጋር ይኖር ነበር።—ዘፍጥረት 1:26፤ ምሳሌ 8:22, 30፤ ዮሐንስ 1:3
ምድራዊ ሕይወቱ
6. (ሀ) ከኢየሱስ መወለድ በፊትና በኋላ በነበሩት አጭር ጊዜያት ውስጥ ምን ሁኔታዎች ተፈጸሙ? (ለ) ኢየሱስ የት ተወለደ የትስ አደገ?
6 ማርያም የዮሴፍ እጮኛ ነበረች። ነገር ግን ማርገዟን ሲያይ ከሌላ ወንድ ጋር ሩካቤ ሥጋ ፈጽማለች በሚል እምነት እርስዋን ላለማግባት አሰበ። ይሖዋ ግን ሕፃኑ የተጸነሰው በራሱ ቅዱስ መንፈስ አማካይነት እንደሆነ በነገረው ጊዜ ዮሴፍ ማርያምን እንደ ሚስቱ አድርጐ ወሰዳት። (ማቴዎስ 1:18–20, 24, 25) በኋላም ቤተልሔም ወደ ተባለችው ከተማ ሄዱና ኢየሱስ እዚያው ተወለደ። (ሉቃስ 2:1–7፤ ሚክያስ 5:2) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ገና ሕፃን ሳለ ንጉሥ ሔሮድስ ሊገድለው ሞከረ። ነገር ግን ዮሴፍ ይሖዋ ስላስጠነቀቀው ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብጽ ሸሸ። ንጉሥ ሔሮድስ ከሞተ በኋላ ዮሴፍና ማርያም በገሊላ አውራጃ ወደምትገኘው የናዝሬት ከተማ ኢየሱስን ይዘው ተመለሱ። ኢየሱስ በዚህ ከተማ አደገ።—ማቴዎስ 2:13–15, 19–23
7. (ሀ) ኢየሱስ አሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላው ምን ነገር ተፈጸመ? (ለ) ኢየሱስ በማደግ ላይ እያለ ምን ሥራ ተማረ?
7 ኢየሱስ አሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላው የማለፍ በዓል ወይም ፋሲካ በተባለው ልዩ በዓል ላይ ለመገኘት ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። እዚያም ሳለ አስተማሪዎችን እያዳመጠና ጥያቄዎችን እየጠየቃቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሦስት ቀን ቆየ። የሰሙት ሰዎች ሁሉ ምን ያህል እንደሚያውቅ በማየት ተደነቁ። (ሉቃስ 2:41–52) ኢየሱስ በናዝሬት ሲያድግ የአናፂነትን ሥራ ተማረ። ራሱ አናፂ የነበረው አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ ይህንን ሥራ እንዳሰለጠነው አያጠራጥርም።—ማርቆስ 6:3፤ ማቴዎስ 13:55
8. ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሞላው ምን ነገር ተፈጸመ?
8 ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ አንድ ትልቅ ለውጥ መጣ። ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄደና እንዲያጠምቀው ይኸውም በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲያጠልቀው ጠየቀው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- ማቴዎስ 3:16, 17) ኢየሱስ በአምላክ የተላከ ለመሆኑ በዮሐንስ አእምሮ ውስጥ ምንም ጥርጥር ሊኖር አይችልም ነበር።
“ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ እርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።” (9. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው መቼ ነበር? ለምንስ በዚያን ጊዜ ነው እንላለን? (ለ) ኢየሱስ ሲጠመቅ ምን ለማድረግ ራሱን ማቅረቡ ነበር?
9 ይሖዋ በኢየሱስ ላይ የራሱ ቅዱስ መንፈስ እንዲፈስስ ሲያደርግ ወደፊት የምትመጣዋ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን እርሱን መቀባቱ ወይም መሾሙ ነበር። ኢየሱስ በዚህ መንገድ በመንፈስ በመቀባት “መሲሕ” ወይም “ክርስቶስ” ሆነ። እነዚህ ቃላት በዕብራይስጥና በግሪክኛ ቋንቋዎች “የተቀባ” ማለት ናቸው። ስለዚህ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም የተቀባው ኢየሱስ ሆነ ማለት ነው። ይህም በመሆኑ የእርሱ ሐዋርያ የነበረው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው” ሲል ተናገረ። (ሥራ 10:38) ከዚህም በተጨማሪ በውኃ የተጠመቀው አምላክ እርሱን ወደ ምድር የላከበትን ሥራ ለመሥራት ራሱን ለማቅረብ ነው። ያ ትልቅ ሥራስ ምን ነበር?
ወደ ምድር የመጣበት ምክንያት
10. ኢየሱስ የትኞቹን እውነቶች ለመናገር ወደ ምድር መጣ?
10 ኢየሱስ ወደ ምድር ለምን እንደመጣ ለሮማዊው አገረ ገዥ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ ሲገልጽለት “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጄአለሁ ስለዚህም ወደዚህ ዓለም መጥቼአለሁ” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:37) ነገር ግን ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው በተለይ የትኞቹን እውነቶች እንዲያሳውቅ ነበር? በመጀመሪያ ስለ ሰማያዊ አባቱ የሚናገሩትን እውነቶች ማሳወቅ ነበረበት። ተከታዮቹ የአባቱ ስም “ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተማራቸው። (ማቴዎስ 6:9) ደግሞም “ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ” ሲል ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:6) ከዚህም ሌላ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎች ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” ብሎአል።—ሉቃስ 4:43
11. (ሀ) ኢየሱስ ሥራውን በጣም ከፍ አድርጐ የተመለከተው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ከማድረግ ፈጽሞ ወደ ኋላ አላለም? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?
11 የአባቱን ስምና መንግሥት እንዲያሳውቅ የተሰጠው ይህ ሥራ ለኢየሱስ የቱን ያህል አስፈላጊ ነበር? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሎአቸው ነበር። (ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ አምላክ የሰጠው ሥራ የምግብን ያህል በጣም አስፈላጊ ነው ብሎ ያሰበው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ ስለ ሰው ልጆች ያሉትን አስደናቂ ዓላማዎች የሚፈጽመው በመንግሥቱ አማካይነት ስለሆነ ነው። ክፋትን ሁሉ የምትደመስሰውና የይሖዋ ስም ከደረሰበት ስድብ ሁሉ ነፃ የምታደርገው ይህች መንግሥት ናት። (ዳንኤል 2:44፤ ራዕይ 21:3, 4) ስለዚህ ኢየሱስ የአምላክን ስምና መንግሥት ከማሳወቅ ፈጽሞ ወደ ኋላ አላለም። (ማቴዎስ 4:17፤ ሉቃስ 8:1፤ ዮሐንስ 17:26፤ ዕብራውያን 2:12) በሰዎች ቢወደድም ባይወደድም ሁልጊዜ እውነትን ይናገር ነበር። እንደዚህ በማድረጉ እኛም አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ ተወልን።—1 ጴጥሮስ 2:21
12. ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ሌላው ትልቅ ምክንያት ምን ነበር?
12 ነገር ግን በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንድንችል ኢየሱስ ደመ ሕይወቱን በማፍሰስ መሞት ነበረበት። የኢየሱስ ሁለት ሐዋርያት እንደተናገሩት ‘በደሙ አማካይነት እንደ ጻድቃን ተቆጠርን።’ “የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” (ሮሜ 5:9፤ 1 ዮሐንስ 1:7) እንግዲያው ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ትልቅ ምክንያት ስለኛ ለመሞት ነው። ራሱ እንዲህ አለ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (ማቴዎስ 20:28) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሕይወቱን “ቤዛ” አድርጎ ሰጠ ሲባል ምን ማለት ነው። እኛ እንድንድን እርሱ ሞቶ ደመ ሕይወቱ መፍሰስ የነበረበት ለምንድን ነው?
ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጠ
13. (ሀ) ቤዛ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለማስለቀቅ የከፈለልን የቤዛ ዋጋ ምንድን ነው?
13 መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች አንድን ሰው አፍነው ሲወስዱት ብዙ ጊዜ “ቤዛ” ወይም “ካሳ” የሚለው ቃል ይሰማል። አፍኖ የወሰደው ሰው ሰውየውን ከያዘ በኋላ የተወሰነ ገንዘብ እንደ ቤዛ ወይም ካሳ ሆኖ ቢከፈለው እንደሚለቅቀው ይናገር ይሆናል። ስለዚህ ቤዛ አንድን የተያዘ ሰው ለማስለቀቅ የሚከፈል ነገር ነው ማለት ነው። ሰውየው ሕይወቱን እንዳያጣ የሚከፈል ነገር ነው። ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ለማስለቀቅ የተከፈለው የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ነው። (1 ጴጥሮስ 1:18, 19፤ ኤፌሶን 1:7) ይህ ዓይነቱ የማስለቀቅ እርምጃ ለምን አስፈለገ?
14. በኢየሱስ የተገኘው ቤዛ ለምን አስፈላጊ ነበር?
14 ይህ የሆነበት ምክንያት የሁላችንም አባት የነበረው አዳም በአምላክ ላይ ዓምጾ ስለነበረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአትም ዓመጻ ነው” ብሎ ስለሚናገር 1 ዮሐንስ 3:4፤ 5:17) በዚህ ምክንያት የአምላክን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለመቀበል ብቁ አልነበረም። (ሮሜ 6:23) ስለዚህ አዳም ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የማግኘት ዕድል አጣ። ይህንን አስደናቂ ዕድል ወደፊት ለሚያፈራቸው ልጆቹ ሁሉ አሳጣ። ‘ኃጢአት የሠራው አዳም ሆኖ ሳለ ልጆቹ በሙሉ ለምን ይሞታሉ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
የዓመጻ እርምጃው ኃጢአተኛ አደረገው። (15. ኃጢአት የሠራው አዳም ሆኖ ሳለ ልጆቹ የሚሰቃዩትና የሚሞቱት ለምንድን ነው?
15 ይህ የሆነበት ምክንያት አዳም ኃጢአተኛ ከሆነ በኋላ ለልጆቹ፣ አሁን ለምንኖረው ሰዎች ሁሉ ጭምር፣ ኃጢአትንና ሞትን ስላስተላለፈ ነው። (ኢዮብ 14:4፤ ሮሜ 5:12) “ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮሜ 3:23፤ 1 ነገሥት 8:46) አምላክን ወዳድ የነበረው ዳዊትም እንኳን “እነሆ በዓመፃ ተጸነስሁ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” ብሎአል። (መዝሙር 51:5) ስለዚህ ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ የሚሞቱት ከአዳም በተወረሰው ኃጢአት ምክንያት ነው። ታዲያ የኢየሱስ ሕይወት መሥዋዕት መሆኑ ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
16. (ሀ) አምላክ ቤዛውን ሲያዘጋጅልን ‘ሕይወት ስለ ሕይወት መሰጠት አለበት’ ለሚለው ሕጉ አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ቤዛውን ለመክፈል የሚችለው ሰው ኢየሱስ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?
16 አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ በሰጠው ሕግ ላይ የሚገኝ ሕግ ነክ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት በነገሩ ውስጥ ይገባል። እርሱም ‘ሕይወት ስለ ሕይወት መሰጠት ይኖርበታል’ ይላል። (ዘፀአት 21:23፤ ዘዳግም 19:21) ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ሳይታዘዝ በመቅረቱ ለራሱም ሆነ ለልጆቹ በሙሉ በምድራዊት ገነት ላይ ፍጹም ሕይወት የማግኘትን ዕድል አጠፋ። አዳም ያጠፋውን መልሶ ለመግዛት ኢየሱስ ክርስቶስ የራሱን ፍጹም ሕይወት ሰጠ። አዎን ኢየሱስ “ራሱን ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጐ ሰጠ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 አዓት) ኢየሱስ ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው ስለ ነበረ “ኋለኛው አዳም” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንም ሰው ቤዛውን ለመስጠት አይችልም ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት በምድር ላይ ከኖሩት ውስጥ ፍጹም የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ በመሆን ከአዳም ጋር እኩል የነበረው እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው።—መዝሙር 49:7፤ ሉቃስ 1:32፤ 3:38
17. ቤዛው ለአምላክ የተከፈለው መቼ ነው?
17 ኢየሱስ በ33 ዓመት ተኩል ዕድሜው ላይ ሞተ። ይሁን እንጂ በሞተ በሦስተኛው ቀን ላይ ወደ ሕይወት ተነሣ። ከዚያ 40 ቀናት ቆይቶ ወደ ሰማይ ተመለሰ። (ሥራ 1:3, 9–11) እዚያም እንደገና መንፈሳዊ አካል በመሆን የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ ይዞ በአምላክ ፊት ስለ እኛ ቀረበ። (ዕብራውያን 9:12, 24) በዚያን ጊዜ ቤዛው በሰማይ ለአምላክ ተከፈለ። ከዚያ በኋላ ሰዎች የሚድኑበት መንገድ ተከፈተላቸው። ይሁን እንጂ የዚህ ጥቅሞች የሚመጡት መቼ ይሆን?
18. (ሀ) ከቤዛው አሁንም ቢሆን እንዴት ለመጠቀም እንችላለን? (ለ) ቤዛው ወደፊት ምን ነገሮች እንዲቻሉ ያደርጋል?
18 የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አሁንም እንኳን ሊጠቅመን ይችላል። እንዴት? በእርሱ ላይ እምነት በማድረግ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ኖሮን ልንደሰትና ፍቅርና ደግነት በተሞላው እንክብካቤው ሥር ለመሆን እንችላለን። (ራዕይ 7:9, 10, 13–15) ብዙዎቻችን ስለ አምላክ ከመማራችን በፊት በጣም መጥፎ ኃጢአቶች ፈጽመን ሊሆን ይችላል። አሁንም ቢሆን ስሕተቶችን እንሠራለን፤ አንዳንዶቹም በጣም ከባድ ናቸው። ይሁን እንጂ ይሰማናል የሚል እምነት ኖሮን አምላክ በቤዛው መሠረት ይቅር እንዲለን ያለ ፍርሐት ልንጠይቀው እንችላለን። (1 ዮሐንስ 2:1, 2፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11) በተጨማሪም ከፊታችን ባሉት ቀናት ውስጥ ቤዛው በአምላክ የጽድቅ አዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ስጦታውን ለመቀበል የምንችልበትን መንገድ ይከፍትልናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያን ጊዜ በቤዛው የሚያምኑ ሁሉ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ሙሉ በሙሉ ይላቀቃሉ። ፍጹማን ሆነው ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙበት ጊዜ ከፊታቸው ይዘረጋላቸዋል!
19. (ሀ) የቤዛው ስጦታ አንተን እንዴት ይነካሃል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቤዛው አመስጋኝነታችንን እንዴት ማሳየት አለብን አለ?
19 ቤዛውን በሚመለከት ስላገኘኸው ትምህርት እንዴት ይሰማሃል? ይሖዋ አምላክ ለአንተ በጣም ከማሰቡ የተነሣ ውድ ልጁን ስለ አንተ እንደሰጠ ማወቅህ ልብህ ለእርሱ ሞቅ ያለ ፍቅር እንዲሰማው አያደርግምን? (ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10) ይሁን እንጂ ስለ ክርስቶስም ፍቅር ጭምር አስብ። እርሱ ስለእኛ ለመሞት ሲል በውዴታው ወደ ምድር መጣ። ታዲያ አመስጋኝ መሆን አይገባንምን? አመስጋኝነታችንን እንዴት ማሳየት እንደሚገባን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ገልጾአል “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሳው እንጂ ወደፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ሕይወትህን አምላክንና ሰማያዊ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል እየተጠቀምክበት አመስጋኝነትህን በዚህ ታሳያለህን?
ኢየሱስ ለምን ተአምራትን አደረገ?
20. ኢየሱስ ለምጻሙን በመፈወስ ከፈጸመው ድርጊት ስለ እርሱ ምን እንማራለን?
20 ኢየሱስ ባደረጋቸው ብዙ ተአምራት በጣም የታወቀ ነው። በችግር ላይ ለወደቁት ሕዝብ የጠለቀ ኃዘኔታ ይሰማው ነበር። አምላክ የሰጠውንም ኃይል እነርሱን ለመርዳት ሊጠቀምበት ይጓጓ ነበር። ለምሳሌ ቁምጥና ወይም ለምጽ በተባለ መጥፎ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ እርሱ መጣና “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። “ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና እወዳለሁ ንጻ አለው።” ሕመምተኛውም ተፈወሰ። —ማርቆስ 1:40–42
21. ኢየሱስ ብዙ ሕዝብን እንዴት ይረዳ ነበር?
21 አሁንም አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕይንት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከትና ለተጠቀሱት ሰዎች ኢየሱስ የተሰማውን የጠለቀ ርኅራኄ አስብ። “ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፣ ዕውሮችንም፣ ዲዳዎችንም፣ ጉንድሾችንም፣ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፣ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ጉንድሾችም ሲድኑ፣ አንካሶችም ሲሄዱ፣ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።” —ማቴዎስ 15:30, 31
22. ኢየሱስ እርዳታ ላደረገላቸው ሰዎች በእርግጥ ያስብ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?
22 ኢየሱስ በስቃይ ላይ ለነበሩት ለእነዚህ ሰዎች በእርግጥ እንዳሰበና ከልቡ ሊረዳቸው እንደፈለገ ቀጥሎ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረው ቃል ለመረዳት ይቻላል። ማቴዎስ 15:32–38
እንዲህ አለ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም።” ስለዚህ ኢየሱስ በሰባት ቂጣዎችና በጥቂት ዓሦች ብቻ “ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች” በተአምር መገበ።—23. ኢየሱስ የሞተውን የአንዲት መበለት ልጅ ለማስነሣት የገፋፋው ምንድን ነው?
23 በሌላም ጊዜ ኢየሱስ ናይን በምትባል ከተማ ሰዎች አስከሬን ተሸክመው ለቀብር ሲጓዙ አገኛቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል “እነሆ የሞተ ሰው ተሸክመው አወጡ፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ልጅ ነበረ፣ እርስዋም መበለት ነበረች፣ . . . ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና አታልቅሽ አላት።” ለሴትየዋ በጥልቅ አዘነላት። ስለዚህ ኢየሱስ ለአስከሬኑ በመናገር “አንተ ጐበዝ እልሃለሁ ተነሣ” ሲል አዘዘው። የድንቅ ድንቅ የሆነ ነገር ተፈጸመ! “የሞተው ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፣ ለእናቱም ሰጣት።” ያቺ እናት እንዴት ተሰምቷት እንደሚሆን ገምት! አንተ ራስህ ብትሆን እንዴት ይሰማህ ነበር? የተፈጸመው አስደናቂ ነገር ሩቅ እስካሉት ሥፍራዎች ድረስ በሰፊው ተወራ። ስለዚህ ኢየሱስ በጣም የታወቀ መሆኑ ምንም አያስደንቅም።—ሉቃስ 7:11–17
24. የኢየሱስ ተአምራት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ያሳያሉ?
24 ይሁን እንጂ ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ሰዎችን የጠቀሙት ለጊዜው ብቻ ነበር። እርሱ የፈወሳቸው ሰዎች እንደገና የአካል ችግሮች መጥተውባቸዋል። ከሞት ያስነሳቸውም እንደገና ሞተዋል። ቢሆንም የኢየሱስ ተአምራት እርሱ በአምላክ የተላከና በእርግጥ የአምላክ ልጅ እንደነበረ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም በአምላክ ኃይል አማካይነት ሁሉም የሰው ችግሮች መፍትሄ ማግኘት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። አዎን፤ በአምላክ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ወደፊት የሚፈጸመውን በትንሹ አሳይተዋል። በዚያን ጊዜ የተራቡት ይመገባሉ፣ የታመሙት ይፈወሳሉ የሞቱትም ይነሣሉ! ከዚያ በኋላ በሸታ፣ ሞት ወይም ሌላ ዓይነት ችግር ደስታችንን አያጠፋብንም። ያ እንዴት ያለ በረከት ይሆንልናል!—ራዕይ 21:3, 4፤ ማቴዎስ 11:4, 5
የአምላክ መንግሥት መሪ
25. የኢየሱስ ሕይወት በምን ሦስት መንገዶች ሊከፈል ይችላል?
25 የአምላክ ልጅ ሕይወት በሦስት ይከፈላል። አንደኛ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአባቱ ጋር በሰማይ ያሳለፋቸው በውል የማይታወቁ ዘመናት አሉ። ቀጥሎም ከተወለደ በኋላ በምድር ላይ ያሳለፋቸው 33 ተኩል ዓመታት አሉ። አሁን ደግሞ በሰማይ ውስጥ መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሕይወት ይኖራል። ከትንሣኤው ጀምሮ በሰማይ ምን ቦታ ይዞ ቆይቷል?
26. ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳየው ታማኝነቱ ምን ለመሆን ያለውን ብቃት አስመሰከረ?
ሉቃስ 1:33) በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሁልጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት ይናገር ነበር። ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። በተጨማሪም “እንግዲህ መንግሥቱን መፈለጋችሁን አታቋርጡ” በማለት አጠንክሮ መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:10, 33 አዓት) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳየው ታማኝነት የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ለመሆን ብቁ መሆኑን አስመስክሯል። ታዲያ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ ወዲያው ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረን?
26 ኢየሱስ ንጉሥ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። መልአኩ እንኳን ለማርያም “ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” የሚል ማስታወቂያ ነግሯታል። (27. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ምን ነበር?
27 አልጀመረም። ሐዋርያው ጳውሎስ መዝሙር ምዕራፍ 110:1ን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ገለጸ፣ “እርሱ ግን [ኢየሱስ] ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፣ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደፊት ይጠብቃል።” (ዕብራውያን 10:12, 13) ኢየሱስ “በጠላቶችህ መካካል ግዛ” የሚለውን የይሖዋ ትእዛዝ ለመስማት እየተጠባበቀ ነበር። (መዝሙር 110:2) ያ ጊዜ ሲደርስ ሰይጣንንና መላእክቱን ጠራርጐ በማስወጣት ሰማያትን ማጽዳት ጀመረ። በሰማይ የተደረገው የዚያ ውጊያ ውጤት በሚከተሉት ቃላት ተገልጾአል:- “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።” (ራዕይ 12:10) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ብለን በአንድ ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ይህ ሰማያዊ ጦርነት ተደርጓል፤ ኢየሱስ ክርስቶስም በአሁኑ ወቅት በጠላቶቹ መካከል በመግዛት ላይ ነው።
28. (ሀ) ክርስቶስ በቅርቡ ምን ያደርጋል? (ለ) እኛስ የእርሱን ጥበቃ ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?
28 በቅርቡ ክርስቶስና ሰማያዊ መላእክቱ የአሁኖቹን ዓለማዊ መንግሥታት በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርገው ለማስወገድ እርምጃ ይወስዳሉ። (ዳንኤል 2:44፤ ራዕይ 17:14) ኢየሱስ “አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራዕይ 19:11–16) በመጪው ጥፋት ጊዜ ጥበቃ እንዲደረግልን ብቁ መሆናችንን ለማስመስከር በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አለብን። (ዮሐንስ 3:36) ደቀ መዛሙርቱ መሆንና እርሱን እንደ ሰማያዊ ንጉሣችን አድርገን እንድንገዛለት ያስፈልጋል። ይህንን ታደርጋለህን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 58 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለመጠመቅና በይሖዋ የተቀባ ለመሆን የአናጺነት ሥራውን ተወ
[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ፍጹም ሰው ከነበረው ከአዳም ጋር እኩል ነበር
[በገጽ 64 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ በኃዘኔታ ተገፋፍቶ የታመሙትንና የተራቡትን ረድቷል
[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ሙታንን በማስነሣት የአምላክ መንግሥት በምትገዛበት ጊዜ ከዚያ በጣም በላቀ ሰፊ መንገድ ምን እንደሚያደርግ አሳይቷል