በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአርማጌዶን በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች

ከአርማጌዶን በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች

ምዕራፍ 19

ከአርማጌዶን በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች

1. (ሀ) ስለ አርማጌዶን ያለው የተለመደ አስተሳሰብ ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስስ ስለ እርሱ ምን ይላል?

“አርማጌዶን” ብዙዎችን የሚያስፈራ ቃል ነው። ብዙውን ጊዜ የዓለም መሪዎች ሊነሣ የሚችለውን ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ለማመልከት ይጠቀሙበታል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶንን በአምላክ የሚደረግ የጽድቅ ጦርነት የሚካሄድበት ቦታ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። (ራእይ 16:14, 16) ይህ የአምላክ ጦርነት ለአዲስ የጽድቅ ሥርዓት መንገድ ይከፍታል።

2. (ሀ) በአርማጌዶን የሚጠፉት እነማን ናቸው? (ለ) ስለዚህ አዋቂ በመሆን ከምን ዓይነት ድርጊቶች መራቅ ይኖርብናል?

2 አርማጌዶን ጥሩና መጥፎ ሰዎችን ሳይለዩ ከሚደመስሱት የሰዎች ጦርነቶች የተለየ ነው። የሚያጠፋው ክፉዎችን ብቻ ነው። (መዝሙር 92:7) ፈራጁ ይሖዋ አምላክ ሲሆን የጽድቅ ሕጎቹን ሆነ ብለው ለመታዘዝ እምቢ የሚሉትን ያጠፋቸዋል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እንደ ዝሙት፣ ስካር፣ ውሸት ወይም ማታለል ያሉትን ነገሮች ምንም ስህተት እንደሌለባቸው አድርገው ይመለከታሉ። ይሁን እንጂ በአምላክ አስተያየት እነዚህ ነገሮች ስህተት ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ድርጊቶች መፈጸማቸውን የሚቀጥሉትን ሰዎች በአርማጌዶን ከጥፋቱ አያድናቸውም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8) እንደነዚህ ያሉ መጥፎ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ስለነዚህ ነገሮች አምላክ ያወጣቸውን ሕጎች አውቀው አካሄዳቸውን መለወጣቸው በጣም አስፈላጊ ነው።

3. (ሀ) ኢየሱስ የአሁኑን ዓለም ፍጻሜ ከምን ጋር አወዳድሮታል? (ለ) ሰይጣንና አጋንንቱ ምን ይሆናሉ? (ሐ) በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ባሉት ጥቅሶች መሠረት በገነቲቱ ምድር ምን አስደሳች ሁኔታዎች ይኖራሉ?

3 ከአርማጌዶን በኋላ የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል የሆነ ምንም ነገር አይቀርም። አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ብቻ ሕያው ሆነው ይቀጥላሉ። (1 ዮሐንስ 2:17) ኢየሱስ ክርስቶስ ሁኔታውን ከኖኅ ዘመን ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 24:37-39፤ 2 ጴጥሮስ 3:5-7, 13፤ 2:5) ከአርማጌዶን በኋላ በመላው ምድር ላይ የምትገዛው የአምላክ መንግሥት ብቻ ትሆናለች። ሰይጣንና አጋንንቱ ይወገዳሉ። (ራእይ 20:1-3) በሚቀጥሉት ገጾች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጻቸውን ታዛዥ ሰዎች የሚያገኟቸውንና የሚደሰቱባቸውን አንዳንድ በረከቶች ተመልከት።

ሁሉም የሰው ዘሮች በሰላም ይኖራሉ

“ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም . . . የሰላም [መስፍን] ተብሎ ይጠራል። . . . በመንግሥቱም ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7

“በዘመኑም [ጽድቅ] ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል።”—መዝሙር 72:7, 8

ጦርነት አይኖርም

“የይሖዋን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል።”—መዝሙር 46:8, 9

ሁሉም ሰው ጥሩ ቤትና አስደሳች ሥራ ይኖረዋል

“ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ . . . ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ . . . እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። እነርሱ ከነልጆቻቸው የይሖዋ ብሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።”—ኢሳይያስ 65:21-23

ወንጀል፣ ዓመፅና ክፋት የሉም

“ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ . . . ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።”—መዝሙር 37:9, 10

“ኃጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”—ምሳሌ 2:22

መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች

ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።”—ሉቃስ 23:43

“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

ሁሉም ሰዎች ለመብል የሚሆኑ የተትረፈረፉ መልካም ነገሮች ያገኛሉ

“የሠራዊት ጌታ [ይሖዋ] ለሕዝቡ ሁሉ . . . ታላቅ የሰባ ግብዣ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።”—ኢሳይያስ 25:6

“በምድር ላይ ብዙ እህል ይኖራል፤ በተራሮችም ጫፍ ላይ ይትረፈረፋል።” “ምድር ፍሬዋን [ትሰጣለች] እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።”—መዝሙር 72:16 አዓት፤ 67:6

4, 5. (ሀ) ከዚያ በኋላ በገነቲቱ ምድር ላይ ምን ሁኔታዎች አይኖሩም? (ለ) ሰዎች በዛሬው ጊዜ በብዙ ቦታዎች ማድረግ ያልቻሏቸውን ምን ነገሮች ወደፊት ሊያደርጉ ይችላሉ?

4 የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረባትን በምትመስል ገነት ምድር ላይ ለመኖር እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 2:8፤ ሉቃስ 23:43) እስቲ አስበው፤ ከዚያ በኋላ ጦርነት፣ ወንጀል ወይም ዓመፅ አይኖርም። በቀንም ሆነ በሌሊት በየትኛውም ሰዓት ላይ ጉዳት ይደርስብኛል ብለህ ሳትፈራ ወደምትፈልገው ቦታ ለመሄድ ትችላለህ። በአጭሩ ክፉዎች አይኖሩም።—መዝሙር 37:35-38

5 ይህም ሲባል ሕዝብን የሚጨቁኑ ውሸተኛ የፖለቲካ ሰዎችና ስግብግብ የንግድ መሪዎች አይኖሩም ማለት ነው። ሰዎችም ለወታደራዊ መሣሪያዎች መግዣ ከፍተኛ ቀረጥ አይጫንባቸውም። ከእንግዲህ ወዲህ የገንዘብ አቅሙ ሳይፈቅድለት በመቅረቱ ምክንያት ጥሩ ምግብና ምቹ መኖሪያ ቤት የማያገኝ ማንም ሰው አይኖርም። ሥራ አጥነት፣ የገንዘብ ዋጋ መቀነስና የኑሮ ውድነት አይኖሩም። በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቦችን የሚያሠቃዩ ችግሮች ያቆማሉ። ሁሉም ሰዎች አስደሳች ሥራ ይኖራቸዋል፤ የሥራቸውንም ውጤት ለማየትና በዚያ ለመደሰት ይችላሉ።

6. (ሀ) ከአርማጌዶን የሚተርፉት ምን የሚሠሩት ሥራ ይኖራቸዋል? (ለ) የሰዎቹን ሥራ አምላክ የሚባርከው እንዴት ነው?

6 ከአርማጌዶን የሚተርፉት ሰዎች በመጀመሪያ ምድርን የማጽዳትና የዚህን አሮጌ ሥርዓት ፍርስራሽ የመጥረግ ሥራ ይኖራቸዋል። ከዚያ በኋላም የመንግሥቱ አገዛዝ በሚሰጠው አመራር ምድርን ለማልማትና ውብ የመኖሪያ ቦታ ለማድረግ ልዩ የሆነ መብት ያገኛሉ። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ሥራ ይሆናል! አምላክም የተሠራውን ሥራ ሁሉ ይባርካል። እህል ለማብቀልና ከብት ለማርባት ተስማሚ የሆነ የአየር ሁኔታ እንዲኖር ያደርጋል። እነዚህ እህሎችና ከብቶችም ከበሽታና ከጉዳት እንዲጠበቁ ያደርጋል።

7. (ሀ) አምላክ የሰጠው የትኛው ተስፋ ይፈጸማል? (ለ) በአምላክ የተስፋ ቃል መሠረት ክርስቲያኖች ምን ይጠብቃሉ?

7 አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪ የሰጠውና በመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ የተገለጸው:- “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” የሚለው ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል። (መዝሙር 145:16) አዎ፤ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች የሚኖሯቸውን ተገቢ ፍላጎቶች ሁሉ በማግኘት ሙሉ በሙሉ ይረካሉ። ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ሕይወት ምን ያህል አስደናቂ እንደሚሆን ለመገመት እንኳ ያዳግተናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ ሕዝቡን ለመባረክ ስላለው ዝግጅት ሲገልጽ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ብሎ ጽፏል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22

8. (ሀ) ግዑዝ የሆኑ አዲስ የሰማይ ፍጥረታት የማያስፈልጉን ለምንድን ነው? (ለ) ‘አዲሶቹ ሰማያት’ ምንድን ናቸው?

8 እነዚህ “አዲስ ሰማያት” ምንድን ናቸው? አዲስ የሆኑ ግዑዛን የሰማይ ፍጥረታት ይኖራሉ ማለት አይደለም። አምላክ የሚታዩትን የሰማያት ፍጥረታት ፍጹም አድርጎ ሠርቶአቸዋል፤ ለእርሱም ክብር ያመጣሉ። (መዝሙር 8:3፤ 19:1, 2) “አዲስ ሰማያት” የሚለው አነጋገር ምድርን የሚገዛውን አዲስ አገዛዝ ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሰማያት ሰው ሠራሽ መንግሥታት ናቸው። በአርማጌዶን ላይ እነዚህ ያልፋሉ። (2 ጴጥሮስ 3:7) እነርሱን የሚተኩት “አዲስ ሰማያት” የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ነው። ንጉሡም ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆናል። ይሁን እንጂ 144, 000 ታማኝ ተከታዮቹም ‘የአዲስ ሰማያት’ ክፍል በመሆን ከእርሱ ጋር ይገዛሉ።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3

9. (ሀ) “አዲስ ምድር” ምንድን ነው? (ለ) የሚጠፋው ምድር ምንድን ነው?

9 “አዲስ ምድር” የተባለውስ ምንድን ነው? አዲስ ፕላኔት አይደለም። አምላክ ፕላኔቷ ምድራችን ለሰው መኖሪያ በደንብ እንደምትስማማ አድርጎ ሠርቷታል፤ ለዘላለም እንድትኖርም ፈቃዱ ነው። (መዝሙር 104:5) ‘አዲሲቱ ምድር’ አዲስ የሰዎችን ቡድን ወይም ኅብረተሰብ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ በዚሁ መንገድ ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ያህል “ምድርም [ማለትም ሰዎች] ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች” ይላል። (ዘፍጥረት 11:1) የምትጠፋዋ “ምድር” ራሳቸውን የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ክፍል ያደረጉት ሰዎች ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:7) እነርሱን የሚተካው “አዲስ ምድር” ደግሞ ከዚህ የክፉ ሰዎች ዓለም ራሳቸውን የለዩት እውነተኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ይሆናሉ።—ዮሐንስ 17:14፤ 1 ዮሐንስ 2:17

10. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ እነማን እየተሰበሰቡ ናቸው? ወደ ምንስ? (ለ) በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ባሉት ጥቅሶች መሠረት ሰብዓዊ መንግሥታት ያልቻሉት ምን ነገር ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ይደረጋል?

10 አሁንም እንኳ ከተለያዩ ዘሮችና ብሔሮች የመጡና ‘የአዲስ ምድር’ ክፍል የሚሆኑ ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እየተሰበሰቡ ናቸው። በመካከላቸው ያለው አንድነትና ሰላም ከአርማጌዶን በኋላ በገነቷ ምድር ላይ መኖር አስደሳች እንደሚሆን የሚያሳይ ትንሽ ቅምሻ ብቻ ነው። በእውነቱ የአምላክ መንግሥት የትኛውም ሰብዓዊ አገዛዝ ለመሞከርም እንኳን የማያስበውን ነገር ያከናውናል። እስቲ በሚቀጥሉት ገጾች ላይ እንደነዚህ ካሉት በረከቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ተመልከት:-

በሰው ዘሮች መካከል ፍቅራዊ ወንድማማችነት ይኖራል

“እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያዳላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ [ነው]።”—ሥራ 10:34, 35

“እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ . . . ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም።”—ራእይ 7:9, 16

በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም ይሆናል

“ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።”—ኢሳይያስ 11:6፤ 65:25

በሽታ፣ እርጅና ወይም ሞት አይኖርም

“በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮዎችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደሚዳቋ ይዘላል የድዳም ምላስ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6

“እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4

ሙታን እንደገና በሕይወት ይኖራሉ

“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት [እና የሚወጡበት] ሰዓት ይመጣል።”—ዮሐንስ 5:28, 29

“ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ።”—ራእይ 20:13

11. በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚሠሩአቸውን ገነት መሰል ቦታዎች ብዙ ጊዜ የሚያበላሹባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

11 በአምላክ መንግሥት ስር የምትኖረዋ ገነት ይህ አሮጌ ሥርዓት ሊያመጣ ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ምን ያህል በጣም የተሻለች ትሆናለች! እርግጥ ነው፣ በአሁኑም ጊዜ አንዳንድ ሰዎች የሚኖሩበትን ቦታ ገነት አስመስለውታል። ይሁን እንጂ በእነዚህ ቦታዎች የሚኖሩት ሰዎች ክፉና ራስ ወዳድ እንዲሁም እርስ በርሳቸው የሚጠላሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ደግሞም ውሎ አድሮ ይታመማሉ፣ ያረጃሉ፣ ይሞታሉ። ከአርማጌዶን በኋላ በምድር ላይ የምትኖረዋ ገነት ግን የሚያምሩ ቤቶች፣ የአትክልት ቦታዎችና መናፈሻዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ነገሮችንም ታስገኛለች።

12, 13. (ሀ) ከአርማጌዶን በኋላ ምን ዓይነት የሰላም ሁኔታዎች ይኖራሉ? (ለ) እነዚህን ሁኔታዎች ለማምጣት ምን ያስፈልጋል?

12 እስቲ አስበው። ከሁሉም ዘሮችና ብሔሮች የመጡ ሰዎች በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንዳሉ ወንድማማቾችና እኅትማማቾች በመሆን አብረው መኖርን ይማራሉ። እርስ በርሳቸው በእውነት ይዋደዳሉ። ማንም ሰው ራስ ወዳድ ወይም ክፉ አይሆንም። የሌላውን ዘር፣ ቀለም ወይም የመጣበትን ስፍራ ተመልክቶ የሚጠላው ማንም ሰው አይኖርም። ሰውን በጭፍኑ መጥላት ይቀራል። በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ለሌላው እውነተኛ ወዳጅና ጎረቤት ይሆናል። አካባቢው በመንፈሳዊ መንገድ እውነተኛ ገነት ይሆናል። በ“አዲስ ሰማያት” በሚገዛው በዚህ ገነት ውስጥ ለመኖር ትፈልጋለህን?

13 በዛሬው ጊዜ ሰዎች በሰላም አብሮ ስለመኖር ብዙ ያወራሉ። “የተባበሩት መንግሥታት” ድርጅትንም አቋቁመዋል። ይሁን እንጂ ሕዝቦችም ሆኑ መንግሥታት ከምን ጊዜውም የበለጠ ተከፋፍለዋል። ታዲያ የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? የሰዎች ልብ መለወጥ ይኖርበታል። ነገር ግን ይህን ተአምር መፈጸሙ ለዚህ ዓለም መንግሥታት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። ሆኖም ስለ አምላክ ፍቅር የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ይህንን ውጤት እያስገኘ ነው

14. እነዚህ ገነታዊ ሁኔታዎች ሊመጡ እንደሚችሉ የሚያረጋግጠው በአሁኑ ጊዜ ያለ ምን ሁኔታ ነው?

14 ብዙ ሰዎች ጽድቅ ስለሚሰፍንበት አዲስ ሥርዓት ሲማሩ ልባቸው አምላክን ለመውደድ ተገፋፍቷል። ስለዚህ እነርሱም ራሳቸው አምላክ እንደሚያደርገው ለሌሎች ፍቅር ማሳየት ጀምረዋል። (1 ዮሐንስ 4:9-11, 20) ይህም በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተደረገ ማለት ነው። እንደ አውሬ ክፋትና ጥላቻ የነበረባቸው ብዙ ሰዎች በዚህ መንገድ ገሮችና ሰላማውያን ሆነዋል። እንደ ታዛዥ በጎች በመሆን ወደ ክርስቲያናዊው መንጋ ተሰብስበዋል።

15. (ሀ) ምን ሁለት የክርስቲያን ቡድኖች አሉ? (ለ) የመጀመሪያዎቹ የ“አዲስ ምድር” አባሎች እነማን ይሆናሉ?

15 ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትንና “ታናሽ መንጋ” የተባሉትን 144, 000 ክርስቲያኖች ለመሰብሰብ የሚደረገው ሥራ ከ1, 900 ለሚበልጡ ዓመታት ተካሂዷል። ከእነዚህ ውስጥ አሁን በምድር ላይ የቀሩት ጥቂት ብቻ ናቸው። አብዛኞቹ ቀደም ብለው ከክርስቶስ ጋር በሰማይ መግዛት ጀምረዋል። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 20:6) ነገር ግን ኢየሱስ ስለሌሎቹ ክርስቲያኖች ሲናገር “ከዚህም በረት [ከታናሹ መንጋ በረት] ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 10:16) የእነዚህ “ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” አሁን በመሰብሰብ ላይ ናቸው። የ“አዲስ ምድር” የመጀመሪያዎቹ አባላት እነርሱ ይሆናሉ። ይሖዋም በዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ ከሚሆነው “ታላቅ መከራ” አድኖ በምድራዊ ገነት ላይ ያኖራቸዋል።— ራእይ 7:9, 10, 13-15

16. ከእንስሳት ጋር መኖርን አስደሳች የሚያደርገው የትኛው ተአምር ነው?

16 ከአርማጌዶን በኋላ በገነታዊ ሁኔታዎቹ ላይ ሌላ ተአምር ይጨመራል። እንደ አንበሳ፣ ነብር፣ አነርና ድብ የመሳሰሉት አሁን አደገኛ የሆኑ እንስሳት ሰላማዊ ይሆናሉ። እንግዲያው ለሽርሽር ወደ ጫካ መሄድና አንበሳ መጥቶ ለትንሽ ጊዜ ከጎናችን ቁጭ ሲል፣ በኋላም አንድ ትልቅ ድብ መጥቶ እንደዚያ ሲያደርግ እንዴት ደስ ይል ይሆን! ከዚያ በኋላ ማንም ሰው የትኛውንም ሕያው ፍጥረት መፍራት አያስፈልገውም።

17, 18. (ሀ) በገነቲቱ ምድር ውስጥ ለኀዘን ምክንያት የሚሆን ምን ነገር አይኖርም? (ለ) ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት እንደሚያገኝ እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

17 ይሁን እንጂ ቤቶችና የአትክልት ቦታዎች የቱንም ያህል የተዋቡ ቢሆኑ፣ ሰዎችም ምንም ያህል ደግና አፍቃሪ ቢሆኑ፣ እንስሶችም ከሰዎች ጋር የቱንም ያህል ወዳጅነት ቢኖራቸው፣ የምንታመም የምናረጅና የምንሞት ከሆነ አሁንም ኀዘን ይኖራል። ታዲያ ለሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት ማን ሊያመጣ ይችላል? ሰብዓዊ መንግሥታት ካንሰርን፣ የልብ ሕመምንና ሌሎች በሽታዎችን ጨርሶ ለማጥፋት ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህንንም እንኳ ለማድረግ ችሎታ ቢኖራቸው ኖሮ ይህ ሰዎችን ከማርጀት ሊያስቀራቸው እንደማይችል ሐኪሞች ያምናሉ። ማርጀት ይቀጥል ነበር። ውሎ አድሮ ዓይናችን መፍዘዙ፣ ጡንቻዎቻችንም መላላታቸው፣ ቆዳችን መጨማደዱ በውስጣችን ያሉት የአካል ክፍሎች መፈራረሳቸው አይቀርም ነበር። ከዚያ በኋላ ሞት ይከተላል። እንዴት የሚያሳዝን ነው!

18 ከአርማጌዶን በኋላ በገነት ምድር ውስጥ በአምላክ የሚፈጸም አንድ ታላቅ ተአምር ይህንን ሁሉ ይለውጠዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 33:24) ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከአዳም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት የሚመጣውን ሁሉንም ዓይነት ሕመምና በሽታ ለመፈወስ ኃይል እንዳለው አረጋግጧል። (ማርቆስ 2:1-12፤ ማቴዎስ 15:30, 31) እርጅናም ቢሆን በንጉሣዊ አገዛዙ ስር ይወገዳል። ያረጁትም እንኳ እንደገና ወጣት ይሆናሉ። አዎን፣ ‘የአንድ ሰው ሥጋ ከወጣትነቱ የበለጠ ለጋ ይሆናል።’ (ኢዮብ 33:25) በዚያን ጊዜ ጠዋት ጠዋት ስትነሣ ጤንነትህ ካለፈው ቀን የተሻለ ሆኖ ስታገኘው እንዴት በደስታ ትፈነድቅ ይሆን!

19. የትኛው የመጨረሻ ጠላት ይሻራል? እንዴትስ?

19 በወጣትነት ዕድሜው ላይ ሆኖ፣ በገነቲቱ ምድር ውስጥ ፍጹም ጤንነት አግኝቶ የሚኖር ማንኛውም ሰው መሞት እንደማይፈልግ የተረጋገጠ ነው። ማንም ሰው ቢሆን የግድ መሞት አያስፈልገውም! የቤዛውን መሥዋዕት ጥቅሞች መቀበላቸው በመጨረሻው “በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት” ያስገኝላቸዋል። (ሮሜ 6:23) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አምላክ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች [እስኪያደርግለት] ድረስ [ክርስቶስ] ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:25, 26፤ ኢሳይያስ 25:8

20. አሁን በሕይወት ከሚገኙት ሰዎች በተጨማሪ በገነት ምድር ውስጥ በመኖር የሚደሰቱት እነማን ናቸው? ይህስ የሚቻለው እንዴት ነው?

20 አሁን ሞተው ያሉት ሰዎችም እንኳ ቢሆኑ በገነቲቱ ምድር ውስጥ ገብተው ይደሰታሉ። ወደ ሕይወት ይመለሳሉ! ስለዚህ በዚያን ጊዜ ስለሞቱት ሰዎች መርዶ በመስማት ፋንታ ከሞት ስለተነሡት ሰዎች አስደሳች ዜናዎች ይነገራሉ። የሞቱ አባቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ሌሎች ዘመዶችን ከመቃብር መቀበሉ ምንኛ አስደናቂ ይሆናል! የገነቲቱን ምድር ውበት የሚያበላሹ የመቃብር ቦታዎች ወይም ሐውልቶች አይኖሩም።

21. (ሀ) ‘ከአዲሶቹ ሰማያት’ የሚመጡት ሕጎችና መመሪያዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን በመቆጣጠር የሚረዱት እነማን ይሆናሉ? (ለ) ‘አዲስ ሰማያትን’ እና ‘አዲስ ምድርን’ በእርግጥ እንደምንፈልግ እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

21 በገነቲቱ ምድር ላይ የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠረው ወይም የሚመራው ማን ይሆናል? ሁሉም ሕጎችና መመሪያዎች ከላይ ማለትም ‘ከአዲሶቹ ሰማያት’ ይመጣሉ። ይሁን እንጂ በምድርም ላይ ቢሆን እነዚህ ሕጎችና መመሪያዎች መፈጸማቸውን የሚከታተሉ ታማኝ ሰዎች ይሾማሉ። እነዚህ ሰዎች ልዩ በሆነ መንገድ ሰማያዊውን መንግሥት ስለሚወክሉ መጽሐፍ ቅዱስ “መሳፍንት” ብሎ ይጠራቸዋል። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ መዝሙር 45:16 አዓት) በአሁኑም ጊዜ ቢሆን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የጉባኤውን ሥራዎች ለማከናወንና ለመምራት ወንዶች በቅዱሱ የአምላክ መንፈስ ይሾማሉ። (ሥራ 20:28) ከአርማጌዶን በኋላ ክርስቶስ ለንጉሣዊ አገዛዙ ወኪል የሚሆኑትን ትክክለኛ ሰዎች ይመርጣል ብለን ለመተማመን እንችላለን ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በምድር ጉዳዮች ላይ እጁን በቀጥታ ያስገባል። ታዲያ አንተ የአምላክን “አዲስ ሰማያት” እና “አዲስ ምድር” በጉጉት እየተጠባበቅህ መሆንህን እንዴት ልታሳይ ትችላለህ? በአዲሱ የጽድቅ ሥርዓት ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ግዴታዎች ለማሟላት የምትችለውን ሁሉ በማድረግ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:14