በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቆምከው ለሰይጣን ዓለም ነው ወይስ ለአዲሱ የአምላክ የጽድቅ ሥርዓት?

የቆምከው ለሰይጣን ዓለም ነው ወይስ ለአዲሱ የአምላክ የጽድቅ ሥርዓት?

ምዕራፍ 25

የቆምከው ለሰይጣን ዓለም ነው ወይስ ለአዲሱ የአምላክ የጽድቅ ሥርዓት?

1. ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት መቆምህን በእርግጥ የሚያሳየው ምንድን ነው?

የአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ደጋፊ ነህን? እንዲመጣስ ትፈልጋለህን? የሰይጣን ተቃዋሚ ነህን? የሰይጣን ዓለምስ ወደ መጨረሻው እንዲመጣ ትፈልጋለህን? ለሁሉም ጥያቄዎች አዎ የሚል መልስ ትሰጥ ይሆናል። ነገር ግን ይህ በቂ ነውን? ከቃላት ይልቅ የተግባር ድምጽ የጐላ ነው የሚል የድሮ አነጋገር አለ። በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት መምጣት የምታምን ከሆነ ይህንን የሚያረጋግጠው የአኗኗርህ ሁኔታ ነው። — ማቴዎስ 7:21-23፤ 15:7, 8

2. (ሀ) ልናገለግላቸው የምንችል ሁለት ጌቶች እነማን ናቸው? (ለ) የማንኛቸው ባሪያ ወይም አገልጋይ መሆናችንን የሚያሳየው ምንድን ነው?

2 እንደ እውነቱ ከሆነ የምትከተለው የአኗኗር መንገድ ከሁለት ጌቶች ውስጥ አንደኛውን ብቻ ያስደስታል። የምታገለግለው ይሖዋ አምላክን አለዚያም ሰይጣን ዲያብሎስን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ይህንን ለመገንዘብ ይረዳናል። እርሱም “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደሆናችሁ አታውቁምን?” ይላል። (ሮሜ 6:16) የምትታዘዘው ማንን ነው? የማንን ፈቃድ ታደርጋለህ? ምንም ዓይነት መልስ ብትሰጥ የዓለምን የኃጢአት መንገዶች የምትከተል ከሆነ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እያገለግልኩት ነው ለማለት አትችልም።

የሰይጣን ዓለም ምንድን ነው?

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም ገዥ ማን መሆኑን እንዴት ያሳያል? (ለ) ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ በዚህ ዓለምና በደቀ መዛሙርቱ መካከል ልዩነት መኖሩን ያሳየው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል። ሐዋርያው ዮሐንስም “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደተያዘ እናውቃለን” ብሏል። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ደቀመዛሙርቱ የሰይጣን ዓለም ክፍል እንደሆኑ አድርጎ እንዳልተናገረ አስተውል። እንዲህ አለ “እኔ ስለ እነዚህ [ስለ ደቀመዛሙርቱ] እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም . . . እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:9, 16፤ 15:18, 19) እውነተኛ ክርስቲያኖች ከዓለም ተለይተው መኖር እንዳለባቸው ይህ ግልጽ ያደርግልናል።

4. (ሀ) በዮሐንስ 3:16 ላይ “ዓለም” የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል? (ለ) ክርስቲያኖች መለየት የሚያስፈልጋቸው ከየትኛው “ዓለም” ነው?

4 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ዓለም” ባለ ጊዜ ምንን ማመልከቱ ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለም” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ የሰውን ዘር በጠቅላላ ያመለክታል። አምላክ ልጁን የላከው ለዚህኛው የሰው ዘሮች ዓለም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ ነው። (ዮሐንስ 3:16) ሆኖም ሰይጣን አብዛኛውን የሰው ዘር አደራጅቶ የአምላክ ተቃዋሚ አድርጎታል። ስለዚህ የሰይጣን ዓለም ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ውጭ ያለውና ከዚያ ተነጥሎ የሚኖረው ይኸኛው የተደራጀ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ነው። ክርስቲያኖች መለየት ያለባቸው ከዚህኛው ዓለም ነው። — ያዕቆብ 1:27

5. የሰይጣን ዓለም አንዱ ዐቢይ ክፍል ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስስ እንዴት ሆኖ ተገልጿል?

5 የሰይጣን ዓለም ይኸውም የተደራጀው ሰብዓዊ ኅብረተሰቡ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ልዩ ልዩ ክፍሎች አሉት። አንዱ ዐቢይ ክፍል የሐሰት ሃይማኖት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሐሰት ሃይማኖት በአንዲት “ታላቅ ጋለሞታ” ወይንም “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ በምትጠራ አመንዝራ ተመስሏል። ታላቂቱ ባቢሎን ዓለም አቀፍ ግዛት ናት። “በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ” መባሏ ይህንን ያሳያል። (ራእይ 17:1, 5, 18) ይሁን እንጂ ታላቂቱ ባቢሎን ዓለም አቀፍ የሆነች ሃይማኖታዊት ግዛት መሆኗን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?

6, 7. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖታዊት ግዛት መሆኗን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? (ለ) የሐሰት ሃማይኖት ከፖለቲካዊ መንግሥታት ጋር ምን ዝምድና ይዞ ቆይቷል?

6 “የምድር ነገሥታት” ከእርሷ ጋር ሴሰኑ ስለተባለ ታላቂቱ ባቢሎን የዓለም የፖለቲካ ግዛት ልትሆን አትችልም። በተጨማሪም እርሷ በምትጠፋበት ጊዜ የምድር ነጋዴዎች ከሩቅ ቆመው እንደሚያለቅሱላት ስለተገለጸ እርሷ ዓለም አቀፍ የንግድ ግዛትን ልታመልክት አትችልም። (ራእይ 17:2፤ 18:15) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋል” ብሎ መናገሩ በእርግጥም ሃይማኖታዊት ግዛት መሆኗን ያሳያል። — ራእይ 18:23

7 ከዚህም በተጨማሪ ታላቂቱ ባቢሎን ከአንድ “አውሬ” ጋር ያላት ግንኙነት ሃይማኖታዊት ግዛት መሆኗን ያረጋግጣል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደነዚህ ያሉ አውሬዎች ምድራዊ መንግሥታትን ያመለክታሉ። (ዳንኤል 8:20, 21) ታላቂቱ ባቢሎን “ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች” ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ እንደተቀመጠች ተደርጋ ተገልጻለች። ስለዚህ ይህንን “አውሬ” ወይም የዓለም መንግሥት ወደፈለገችው አቅጣጫ ለማዞር ስትሞክር ቆይታለች። (ራእይ 17:3) እንደ እውነቱ ከሆነ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሃይማኖት ከፖለቲካ ጋር ተጣምሮ ሲሠራ ቆይቷል። ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ መንግሥታት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይነግራቸዋል። በእርግጥም ታላቂቱ ባቢሎን “በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ” ናት። — ራእይ 17:18

8. ሌላው የሰይጣን ዓለም ትልቅ ክፍል ምንድን ነው? እርሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምን ተመስሏል?

8 እነዚህ ፖለቲካዊ መንግሥታት የሰይጣን ዓለም ሌላው ዐቢይ ክፍል ናቸው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ አውሬዎች ተደርገው ተገልጸዋል። (ዳንኤል 7:1-8, 17, 23) እነዚህ አውሬ መሰል መንግሥታት ሥልጣናቸውን ያገኙት ከሰይጣን እንደሆነ ሐዋርያው ዮሐንስ የጻፈው ራእይ ያሳየናል:- “አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት . . . ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።” (ራእይ 13:1, 2፤ 12:9) ሰይጣን ኢየሱስን እነዚህን መንግሥታት እሰጥሃለሁ ብሎ መፈተኑ እነዚህ መንግሥታት የሰይጣን ዓለም ክፍል ለመሆናቸው ሌላው ማስረጃ ነው። ሰይጣን የእነርሱ ገዥ ባይሆን ኖሮ እንደዚያ ለማለት ባልቻለም ነበር። — ማቴዎስ 4:8, 9

9. (ሀ) በራእይ 18:11 ላይ ሌላው የሰይጣን ዓለም ትልቅ ክፍል የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) እርሱስ ሰይጣን ከበስተኋላው እንዳለ የሚያረጋግጥ ምን የሚያደርገውና የሚያበረታታው ነገር አለ?

9 ሌላው ትልቁ የሰይጣን ዓለም ክፍል ስግብግብና ጨቋኝ የሆነው የንግድ ሥርዓት ነው። እርሱም በራእይ 18:11 ላይ “የምድር ነጋዴዎች” ተብሎ ተገልጿል። ይህ የንግድ ሥርዓት የሚያወጣቸው አንዳንድ ምርቶች ለሕዝብ የማያስፈልጉ ቢሆኑም ወይም ያለነዚህ ዕቃዎች በተሻለ ሁኔታ መኖር ቢቻልም ሰዎች እነዚህን ነገሮች እንዲጐመጁ ያደርጋቸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን የንግዱ ሥርዓት በትልልቅ ጎተራ እህል እያከማቸ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መግዣ ገንዘብ ስለሌላቸው በረሀብ ሲያልቁ ዝም ብሎ ይመለከታል። በሌላው በኩል ግን መላውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ለማጥፋት የሚችሉ ወታደራዊ መሣሪያዎች ይመረታሉ፣ ለትርፍ ሲባልም ይሸጣሉ። ስለዚህ ከሐሰት ሃይማኖት እና ከፖለቲካዊ መንግሥታት ጋር በመሆን የሰይጣኑ የንግድ ሥርዓት ራስ ወዳድነትን፣ ወንጀልንና አሠቃቂ ጦርነቶችን ያስፋፋል።

10, 11. (ሀ) የሰይጣን ዓለም ሌላው ገጽታ ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ነገር እንዳንጠመድ የሚያሳስቡ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያዎች አሉ?

10 በሰይጣን ዲያብሎስ ስር ያለው የተደራጀው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ክፉና ምግባረ ብልሹ ነው። የአምላክን የጽድቅ ሕጎች ይቃወማል። ሁሉም ዓይነት የብልግና ድርጊቶች የሞሉበት ነው። ስለዚህ የሰይጣን ዓለም ሌላው ገጽታ መረን የለቀቀ አኗኗሩ ይኸውም የብልግና መንገዶቹ ናቸው ለማለት ይቻላል። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ ክርስቲያኖች አሕዛብ ከሚፈጽሟቸው መጥፎ ድርጊቶች እንዲርቁ አስጠንቅቀዋል። — ኤፌሶን 2:1-3፤ 4:17-19፤ 1 ጴጥሮስ 4:3, 4

11 ሐዋርያው ዮሐንስም እንደዚሁ ክርስቲያኖች ስሕተት ከሆኑት የዓለም ምኞቶችና የብልግና መንገዶች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው አጥብቆ ገልጿል። እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” (1 ዮሐንስ 2:15, 16) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል” ብሎ ተናግሯል። — ያዕቆብ 4:4

የዓለም ክፍል ከመሆን መራቅ የሚቻልበት መንገድ

12, 13. (ሀ) ክርስቲያኖች በዓለም ውስጥ መኖር እንዳለባቸው ኢየሱስ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዓለም ውስጥ እየኖሩ የዓለም ክፍል ከመሆን መቆጠብ የሚቻለው እንዴት ነው?

12 የሰይጣን ዓለም እስካለ ድረስ ክርስቲያኖች የግድ በውስጡ መኖር አለባቸው። ኢየሱስ “ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” ብሎ ወደ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ይህንን አሳይቷል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “የዓለም ክፍል አይደሉም” የሚል ቃል ጨምሯል። (ዮሐንስ 17:15, 16 አዓት) በሰይጣን ዓለም ውስጥ እየኖሩ የዚያ ዓለም ክፍል ላለመሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

13 አንተ የምትኖረው የተደራጀው የሰይጣን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ አባላት በሆኑት ሰዎች መሀከል ነው። ከእነዚህ ሰዎች መሀከል አመንዝሮች፣ ስግብግቦችና ክፉ ነገሮችን የሚፈጽሙ ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል። ከእነርሱ ጋር ትሠራ ይሆናል፣ አብረሃቸው ወደ ትምህርት ቤት ትሄድ ይሆናል፣ አብረሃቸው ምግብ ትበላና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ትሳተፍ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 5:9, 10) በተጨማሪም አምላክ እነርሱን እንደሚወዳቸው አድርገህ መውደድ ያስፈልግሃል። (ዮሐንስ 3:16) ይሁን እንጂ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሰዎች የሚያደርጓቸውን ክፉ ነገሮች አይወድም። ዝንባሌያቸውን፣ አድራጎታቸውንና በሕይወት ውስጥ ያሏቸውን ግቦች አይከተልም። ብልሹ በሆነው ሃይማኖታቸውና በፖለቲካቸው ውስጥ እጁን አያስገባም። መተዳደሪያ ለማግኘት ብሎ በንግዱ ዓለም ውስጥ ለመሥራት ቢገደድም ቅጥፈት ያለበት ሥራ አይሠራም። ወይም ደግሞ ሥጋዊ ሀብት ማግኘትን ዋነኛ የሕይወቱ ግብ አያደርግም። እርሱ የቆመው ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ስለሆነ ለሰይጣን ዓለም ከቆሙት ሰዎች ጋር መጥፎ ጓደኝነትን አያበጅም። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ መዝሙር 1:1፤ 26:3-6, 9, 10) ስለዚህም በሰይጣን ዓለም ውስጥ እየኖረ የዚያ ዓለም ክፍል አይሆንም

14. የቆምከው ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ከሆነ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ትከተላለህ?

14 አንተስ እንዴት ነህ? የሰይጣን ዓለም ክፍል ለመሆን ትፈልጋለህን? ወይስ የቆምከው ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ነው? የምትኖረው ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ከሆነ ከዓለም፣ ከሐሰት ሃይማኖቱ ጭምር፣ ተለይተህ ትኖራለህ። “ሕዝቤ ሆይ ከእርስዋ [ከታላቋ ባቢሎን] ውጡ” የሚለውን ትእዛዝ ትከተላለህ። (ራእይ 18:4) ይሁን እንጂ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቋ ባቢሎን መውጣቱ ከሐሰተኛ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጋር የነበረንን ግንኙነት ማቋረጥ ማለት ብቻ አይደለም። በሃይማኖታዊ በዓሎች አለመሳተፍ ማለት ጭምር ነው። — 2 ቆሮንቶስ 6:14-18

15. (ሀ) ክርስቲያኖች የኢየሱስን ልደት ሳይሆን ምንን እንዲያከብሩ ታዘዋል? (ለ) ኢየሱስ በቀዝቃዛው የክረምት ወራት ሊወለድ እንደማይችል የሚያሳየው ምንድን ነው? (ሐ) ታህሣሥ 25 የኢየሱስን ልደት ለማክበር የተመረጠው ለምንድን ነው?

15 በዛሬው ጊዜ የገና በዓል ከዋና ዋናዎቹ ሃይማኖታዊ በዓሎች አንዱ ነው። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ያላከበሩት በዓል መሆኑን ታሪክ ያሳያል። ኢየሱስ የተወለደበትን ሳይሆን የሞተበትን መታሰቢያ በዓል እንዲያከብሩ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:24-26) እንደ እውነቱ ከሆነ ኢየሱስ ታህሣሥ 29 [ወይም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታህሣሥ 25] አልተወለደም። ይህ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ እረኞች በሌሊት ሜዳ ላይ እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። በአውሮፓ ውስጥ ይህ ወር ቀዝቃዛው የክረምት ወቅት ስለሆነ እረኞቹ በዚያ ሊገኙ አይችሉም ነበር። (ሉቃስ 2:8-12) ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚገልጸው የኢየሱስን ልደት ለማክበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታህሣሥ 25 የተመረጠው:- “ቀደም ሲል የሮም ሕዝብ የፀሐይን ልደት ለማክበር የሳተርን የፈንጠዝያ በዓል አድርጎ ያከብረው ስለነበር ነው።”

16. (ሀ) አመጣጣቸው ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ዋና ዋናዎቹ ሌሎች ሃይማኖታዊ በዓሎች ምንድን ናቸው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ገናንና ፋሲካን ላለማክበር ምን ጥሩ ምክንያቶች አሏቸው?

16 ፋሲካ ሌላው ትልቁ ሃይማኖታዊ በዓል ነው። በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚከበረው ቅዱስ ሳምንትም ተመሳሳይ ነው። ሆኖም የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ፋሲካንም ቢሆን አያከብሩም ነበር። ይህም በዓል ቢሆን ክርስቲያናዊ ካልሆኑ ባሕሎች የመነጨ ነው። ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የፋሲካ በዓል እንደተከበረ የሚያመለክት ምንም ነገር የለም።” ነገር ግን ገናም ሆነ ፋሲካ ክርስቲያናዊ በዓሎች ከመሆን ይልቅ የሐሰት አማልክትን ከሚያመልኩ ሰዎች የመጡ መሆናቸው ለውጥ ያመጣልን? ሐዋርያው ጳውሎስ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል” በማለት እውነተኛውን ከሐሰተኛው ጋር እንዳናደባልቅ አስጠንቅቆናል። (ገላትያ 5:9) በሙሴ ሕግ ይከበሩ የነበሩ አምላክ ግን ለክርስቲያኖች የሰረዘላቸውን አንዳንድ ቀኖች ማክበሩ ስሕተት መሆኑን ለአንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ነግሯቸዋል። (ገላትያ 4:10, 11) ታዲያ በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ እንዲከበሩ ፈጽሞ ያላዘዛቸውንና ከሐሰት ሃይማኖት የመጡትን በዓሎች ከማክበር መራቃቸው ከዚያ ይበልጥ አስፈላጊ አይደለምን?

17. (ሀ) ለዝነኛ ሰዎች ወይም ለብሔራት ክብር የሚሰጡ በዓሎች ስሕተታቸው ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባውን መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት አድርጎ ያሳያል?

17 ሌሎቹ የዓለም በዓሎች ዝነኛ ለሆኑ ሰዎች ክብር የቆሙ ናቸው። አሁንም ሌሎቹ በዓሎች ብሔራትን ወይም ዓለማዊ ድርጅቶችን ያከብራሉ፤ ያወድሳሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች የአምልኮን ያህል የሆነ ክብር ከመስጠትና አምላክ ብቻ ማድረግ የሚችለውን እንዲያደርጉልን በሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ ከመመካት እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። (ሥራ 10:25, 26፤ 12:21-23፤ ራእይ 19:10፤ ኤርምያስ 17:5-7) ስለዚህ ሰውን ወይም ሰብዓዊ ድርጅትን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ በዓሎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ አይደሉም። እውነተኛ ክርስቲያኖችም በዚያ በዓል አይሳተፉም። — ሮሜ 12:2

18. (ሀ) ሰዎች ክብር የሚሰጣቸው ወይም የሚሰገድላቸው ምን ነገሮችን ሠርተዋል? (ለ) ለአንድ ዕቃ የአምልኮትን ያህል ክብር ስለ መስጠቱ የአምላክ ሕግ ምን ይላል?

18 ሰዎች እንዲያከብሯቸው ወይም እንዲሰግዱላቸው ተብሎ ብዙ ነገሮች ተሠርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከብረት ወይም ከእንጨት የተሠሩ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ከጨርቅ የተሠሩ ሆነው በሰማይ ወይም በምድር ያለ የአንድ ነገር ምስል ይለጠፍባቸዋል ወይም ይሳልባቸዋል። አንድ አገር እያንዳንዱ ሰው ለእንዲህ ዓይነቱ ነገር የአምልኮትን ያህል የሚቆጠር ክብር እንዲሰጥ ሕግ ያወጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ አገልጋዮቹ እንደዚህ ማድረግ የለባቸውም ይላል። (ዘፀአት 20:4, 5፤ ማቴዎስ 4:10) የአምላክ ሕዝቦች እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን አድርገዋል።

19. (ሀ) የባቢሎን ንጉሥ እያንዳንዱ ሰው ምን ማድረግ አለበት ብሎ አዘዘ? (ለ) ክርስቲያኖች የማንን ምሳሌ ቢከተሉ ጥሩ ነው?

19 የጥንቱ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አንድ ትልቅ የወርቅ ምስል አሠራና ሁሉም ሰው እንዲሰግድለት አዘዘ። ይህንን ያልፈጸመ ማንኛውም ሰው በእሳት ወደሚቃጠለው እቶን ይጣላል ብሎም ተናገረ። መጽሐፍ ቅዱስ ሲድራቅ ሚሳቅና አብድናጎ የተባሉ ሦስት ወጣት ዕብራውያን የንጉሡን ትእዛዝ ለመከተል እምቢ እንዳሉ ይናገራል። ለምን እምቢ አሉ? ምክንያቱም ነገሩ አምልኮትን የሚነካ ነበር። አምልኮታቸው ደግሞ ለይሖዋ ብቻ የሚሰጥ ነበር። ያደረጉትን ነገር አምላክ ተቀበለው፤ ከንጉሡም ቁጣ አዳናቸው። እንዲያውም ናቡከደነፆር እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ለአገሩ አደገኛ እንዳልሆኑ ለመረዳት ቻለ። ስለዚህ ነፃነታቸውን ለማስከበር ሕግ አወጣ። (ዳንኤል 3:1-30) የእነዚህን ወጣት ሰዎች ታማኝነት አታደንቅምን? የአምላክን ሕጎች በሙሉ በመታዘዝ ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት በእርግጥ የቆምክ መሆንህን ታሳያለህን? — ሥራ 5:29

20. አምላክ ስለ ጾታ ስነ ምግባር ያወጣቸውን ሕጎች እንድናፈርስ ሰይጣን በምን ልዩ ልዩ ዘዴዎች ይጠቀማል?

20 ሆኖም ሰይጣን ይሖዋን እንድናገለግል አይፈልግም። የሚፈልገው እርሱን እንድናገለግል ነው። ለምንታዘዝለት ለማንኛውም ነገር ባሪያ ወይም አገልጋይ እንደምንሆን ስለሚያውቅ ፍላጎቱን እንድንፈጽም ለመገፋፋት ይጥራል። (ሮሜ 6:16) ሰይጣን በልዩ ልዩ ዘዴዎች እየተጠቀመ፤ ለምሳሌ በቴሌቪዥን፣ በሲኒማ፣ በአንዳንድ የጭፈራ ዓይነቶችና የብልግና ጽሑፎች አማካይነት ባልተጋቡ ሰዎች መሀከል የጾታ ግንኙነት እንዲደረግ ያገቡትም ምንዝር እንዲፈጽሙ ያበረታታል። እንደዚህ ዓይነቱ አድራጎት ተቀባይነት እንዳለው እንዲያውም ተገቢ እንደሆነ መስሎ እንዲታይ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ይህ የአምላክን ሕግ የሚጻረር ነው። (ዕብራውያን 13:4፤ ኤፌሶን 5:3-5) እንደዚህ ባለ አድራጎት የተጠመደ ሰው ለሰይጣን ዓለም የቆመ መሆኑን ያሳያል።

21. አንድ ሰው ቢፈጽማቸው ለሰይጣን ዓለም የቆመ መሆኑን የሚመሰክሩበት ሌሎቹ ድርጊቶች ምንድን ናቸው?

21 ከአምላክ ሕጎች ጋር የሚጋጩ ነገር ግን የሰይጣን ዓለም በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ያደረጋቸው ሌሎች ድርጊቶችም አሉ። ከእነዚህ አንዱ በአልኮል መጠጦች አማካኝነት መስከር ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ሌላው ደግሞ ለደስታ ስሜት ተብሎ እንደ ማሪዋና እና ሔሮይን የተባሉ ዕፆችን መውሰድ እንዲሁም ትንባሆ ማጨስ ነው። እነዚህ ነገሮች ሰውነትን የሚጎዱና የረከሱ ናቸው። በእነዚህ ነገሮች የሚጠቀም ሰው “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” የሚለውን የአምላክ መመሪያ ይጥሳል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ሲጋራ ማጨሱ በአቅራቢያው ያሉ ሰዎች ጭሱን ወደ ሰውነታቸው እንዲስቡ ስለሚያስገድዳቸው ጤንነታቸውን ይጎዳል። ስለዚህ ሲጋራ የሚያጨሰው ሰው አንድ ክርስቲያን ጎረቤቱን መውደድ አለበት የሚለውን የአምላክ ሕግ ያፈርሳል። — ማቴዎስ 22:39

22. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም ምን ይላል? (ለ) በደም ስር በኩል ደም መውሰድ ደምን ከመብላት የተለየ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) ‘ከደም መራቅ’ ደምን ወደ ሰውነት ጨርሶ አለማስገባት ማለት መሆኑንን የሚያሳየው ምንድን ነው?

22 በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ያለው ሌላው ልማድ ደምን መብላት ነው። እንስሶች ደማቸው በደንብ ሳይፈስ ሥጋቸው ይበላል ወይም ደማቸውን በዕቃ ይቀበሉና ጠብሰው ለመብልነት ያቀርቡታል። የአምላክ ሕግ ግን ደም መብላትን ይከለክላል። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:10) ታዲያ በደም ስር በኩል ደም ስለመውሰድስ ምን ሊባል ይቻላል? አንዳንድ ሰዎች ደም መውሰዱ መብላት ማለት አይደለም የሚል ሰበብ ያቀርቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ሕመምተኛ በአፉ ምግብ መብላት በማይችልበት ጊዜ ሐኪሙ ደም በሚሰጥበት መንገድ ምግብ እንዲሰጠው ያዝ የለምን? መጽሐፍ ቅዱስ “ከደም ራቁ ” ይላል። (ሥራ 15:20, 29) ይህ ምን ማለት ነው? አንድ ሐኪም አልኮል አትውሰድ ቢልህ በአፍህ አልኮል መውሰድ አትችልም ነገር ግን ወደ ደም ስሮችህ በቀጥታ ልታስገባው ትችላለህ ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ ‘ከደም መራቅ’ ማለት ወደ ሰውነት ውስጥ በጭራሽ አለማስገባት ማለት ነው።

23. (ሀ) ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብሃል? (ለ) ምን ዓይነት ውሳኔ እንዳደረግህ የሚያሳየው ምንድን ነው?

23 ለአምላክ አዲስ ሥርዓት እንደቆምክና የዚህ ዓለም ክፍል እንዳልሆንክ ለይሖዋ ማሳየት ያስፈልግሃል። ይህም አንድ ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል። እርሱም ይሖዋን ለማገልገል፣ ፈቃዱን ለማድረግ የሚደረግ ውሳኔ ነው። በጥንት ጊዜ እስራኤላውያን እንዳደረጉት ሳትወስን እያመነታህ ልትቆይ አትችልም። (1 ነገሥት 18:21) ምክንያቱም ይሖዋን እያገለገልክ ካልሆነ ሰይጣንን እያገለገልክ መሆንህን አስታውስ። እኔ የቆምኩት ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ነው ብለህ አንተ ትናገር ይሆናል። ነገር ግን አኗኗርህ ምን ብሎ እየተናገረ ነው? ለአዲሱ የአምላክ ሥርዓት መቆም አምላክ የሚያወግዛቸውንና በጻድቁ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ቦታ የማይኖራቸውን ድርጊቶች ሁሉ ማስወገድ ማለት ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 209 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሊጸልይለት ያልፈለገውና ደቀ መዛሙርቱ የዚያ ክፍል ያልሆኑበት ዓለም የትኛው ነው?

[በገጽ 211 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሐሰት ሃይማኖት በሰከረች ጋለሞታ ሲመሰል እርሷ የምትጋልበው የዓለም መንግሥት ደግሞ በአውሬ ተመስሏል

መረን የለቀቀ አኗኗር የሰይጣን ዓለም አንዱ ገጽታ ነው። ስግብግብነት ያለበት የንግድ ሥርዓትም አንዱ ትልቁ ክፍል ነው

[በገጽ 213 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሲወለድ እረኞች ሌሊት መንጋቸውን ይዘው በሜዳ ላይ ይገኙ ስለነበረ እርሱ ታህሣሥ 25 ወይም 29 ሊወለድ አይችልም

[በገጽ 214 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ አገልጋዮች አንድ ንጉሥ ላቆመው ምስል ለመስገድ እምቢ ብለዋል። አንተስ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርግ ነበር?