በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ

የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ

ምዕራፍ 29

የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ

1. (ሀ) ቤተሰብ እንዴት ተጀመረ? (ለ) አምላክ ስለ ቤተሰብ ምን ዓላማ ነበረው?

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያውን ወንድና የመጀመሪያዋን ሴት በፈጠረ ጊዜ ልጆችን አፍርተው ቤተሰብ እንዲመሠርቱ በጋብቻ አጣመራቸው። (ዘፍጥረት 2:21-24፤ ማቴዎስ 19:4-6) እነዚህ ባልና ሚስት ልጆችን በማፍራት በቁጥር እየጨመሩ እንዲሄዱ የአምላክ ዓላማ ነበር። ልጆቹም ካደጉ በኋላ አግብተው የራሳቸውን ቤተሰብ መመሥረት ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ በመላው የምድር ገጽ ላይ ደስተኛ ቤተሰቦች እንዲኖሩ የአምላክ ዓላማ ነበር። እነርሱ መላዋን ምድር ውብ ገነት እንዲያደርጓት ታስቦ ነበር። — ዘፍጥረት 1:28 አዓት

2, 3. (ሀ) ቤተሰቦች የተሳካ ውጤት ባያገኙ አምላክ ለምን ሊወቀስ አይችልም? (ለ) የተሳካ የቤተሰብ ኑሮ አግኝቶ ለመደሰት ምን ነገር ያስፈልጋል?

2 ዛሬ ግን ቤተሰቦች እየፈራረሱ ናቸው። አብረው የሚኖሩትም ቢሆን ደስተኞች አይደሉም። ስለዚህ አንድ ሰው ‘ቤተሰብን ያቋቋመ አምላክ ከሆነ የቤተሰብ ሁኔታ ከዚህ የተሻለ መሆን አልነበረበትምን?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ሆኖም በቤተሰቦች ላይ ለሚታየው ውድቀት አምላክ ሊወቀስ አይችልም። አንድ የፋብሪካ ባለቤት አንድ ዕቃ ሠርቶ ስለ አጠቃቀሙ መመሪያዎችን ይሰጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዕቃውን የገዛው ሰው መመሪያዎቹን ሳይከተል ቢቀርና ዕቃው ቢሰበር የባለፋብሪካው ጥፋት ነውን? በፍጹም አይደለም። ዕቃው ፍጹም ጥራት ያለው ሆኖ ቢሠራም በአግባቡ ካልተጠቀሙበት መበላሸቱ አይቀርም። የቤተሰብም ሁኔታ ልክ እንደዚሁ ነው።

3 ይሖዋ አምላክ ስለ ቤተሰብ አኗኗር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መመሪያዎች ሰጥቷል። ይሁን እንጂ እነዚህ መመሪያዎች ሰሚ ካላገኙ ውጤቱ ምን ይሆናል? የቤተሰብ ተቋም ራሱ ፍጹም ቢሆንም የእነዚህ ሰዎች ቤተሰብ ሊፈርስ ይችላል። ከዚያም የቤተሰቡ አባሎች ደስተኞች አይሆኑም። በሌላው በኩል ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች ከተከተሏቸው ቤተሰባቸው የተሳካና ደስተኛ ይሆናል። እንግዲያው አምላክ የቤተሰብን የተለያዩ አባሎች እንዴት አድርጎ እንደሠራና በእርሱ ዓላማ መሠረት እያንዳንዳቸው ምን የሥራ ድርሻ እንደተመደበላቸው መረዳታችን በጣም አስፈላጊ ነው።

አምላክ ወንዱንና ሴቷን የፈጠረው እንዴት ነበር?

4. (ሀ) በወንዶችና በሴቶች መካከል ምን ልዩነቶች አሉ? (ለ) አምላክ እንደነዚህ ያሉትን ልዩነቶች ለምን ፈጠረ?

4 ይሖዋ ወንዶችንና ሴቶችን አንድ ዓይነት አድርጎ እንዳልፈጠራቸው ማንኛውም ሰው ለማየት ይችላል። በብዙ መንገዶች ተመሳሳይ መሆናቸው እውነት ነው። ይሁን እንጂ በአካላዊ ሁኔታቸውና በጾታ አሠራራቸው ግልጽ ልዩነቶች አሉ። በተጨማሪም ስሜታዊ ጠባዮቻቸው ይለያያሉ። እነዚህ ልዩነቶች ለምን ኖሩ? አምላክ በዚያ መንገድ የፈጠራቸው የተሰጣቸውን የተለያየ ሥራ ማከናወን እንዲችሉ ነው። አምላክ ወንዱን ከፈጠረ በኋላ እንዲህ አለ:- “ወንድ ብቻውን ይቀጥል ዘንድ ጥሩ አይደለም። ለእርሱ ማሟያ የምትሆን ረዳት እሠራለታለሁ።” — ዘፍጥረት 2:18 አዓት

5. (ሀ) ሴት የወንድ “ማሟያ” ሆና የተሠራችው እንዴት ነው? (ለ) የመጀመሪያው ጋብቻ የተፈጸመው የት ነው? (ሐ) ጋብቻ እውነተኛ ደስታ ያለበት ዝግጅት ለመሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

5 ማሟያ ከሌላ ነገር ጋር ተገጣጣሚ ወይም ተስማሚ ሆኖ ያንን ነገር የተሟላ የሚያደርገው ነው። አዳም ምድርን በሕዝብ እንዲሞላና እንዲንከባከብ ከአምላክ የተቀበላቸውን መመሪያዎች ለመፈጸም እንድትረዳው አምላክ ሴትን የምታረካ ተጓዳኝ አድርጎ ሠራለት። ስለዚህ አምላክ ከሰውየው አካል አንድ ክፍል ወስዶ ሴቷን ከሠራ በኋላ እርሷን ወደ ወንዱ በማምጣት በኤደን ገነት ውስጥ የመጀሪያውን ጋብቻ አከናወነ። (ዘፍጥረት 2:22፤ 1 ቆሮንቶስ 11:8, 9) ወንድየውና ሴቲቱ አንዱ የጎደለውን ሌላው ለማሟላት እንደሚችል ሆነው ስለተፈጠሩ ጋብቻ አስደሳች ዝግጅት ሊሆንላቸው ይችላል። የተለያዩ ችሎታዎች ያሏቸው መሆኑ እርስ በርስ ለመደጋገፍ ይረዳቸዋል። አንድ ባልና አንዲት ሚስት አንዳቸው የሌላውን ሁኔታ ከተረዳለትና ካደነቀ እንዲሁም በተሰጣቸው የሥራ ድርሻ ከተጋገዙ እያንዳንዳቸው ደስታ ለሰፈነበት ቤት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

የባልየው የሥራ ድርሻ

6. (ሀ) የቤተሰቡ ራስ የተደረገው ማን ነው? (ለ) ይህስ ተገቢ የሆነውና ተግባራዊ ጥቅም ያለው እንዴት ነው?

6 ትዳር ወይም ቤተሰብ መሪ ያስፈልገዋል። እንደዚህ ላለው የመሪነት ቦታ ተስማሚ የሆነ ጠባይና ጥንካሬ በበለጠ ይዞ የተፈጠረው ወንዱ ነው። በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ ደግሞ የቤተክርስቲያን ራስ እንደሆነ . . . ባል የሚስት ራስ ነው” ይላል። (ኤፌሶን 5:23) የዚህ ተግባራዊነት በግልጽ የሚታይ ነው ምክንያቱም መሪ ከሌለ ችግርና ግራ መጋባት ይኖራል። ቤተሰብ ያለመሪ ይሁን ማለት መኪናን ያለመሪ ለመንዳት እንደመሞከር ነው። ወይም ደግሞ ሚስትየዋ ይህ ዓይነቱን የራስነት ሥልጣን ለመያዝ ብትፎካከር በአንድ መኪና ውስጥ ሁለት ሾፌሮች ገብተው እያንዳንዳቸው መሪ እንደሚይዙና በያቅጣጫቸው ያሉትን የፊት ጎማዎች ለመቆጣጠር እንደሚሞክሩ ያህል ነው።

7. (ሀ) አንዳንድ ሴቶች ወንድ ራስ ነው የሚለውን ሐሳብ ለምን ይጠሉታል? (ለ) ሁሉም ፍጡር ራስ አለውን? አምላክ ያወጣው የራስነት ሥርዓት ለምን ጥበብ ነው?

7 ይሁን እንጂ ብዙ ሴቶች ባል የቤተሰቡ ራስ መሆኑን አይወዱትም። ለዚህ አንዱ ትልቅ ምክንያት ብዙ ባሎች የራስነትን ሥልጣን በአገባቡ ስለመጠቀም አምላክ የሰጣቸውን መመሪያዎች አለመከተላቸው ነው። ይሁን እንጂ ማንኛውም ድርጅት በትክክል እንዲካሄድ ከተፈለገ መመሪያ የሚሰጥና የመጨረሻ ውሳኔዎችን የሚያደርግ ሰው እንደሚያስፈልግ ማንም የሚያውቀው ነገር ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር” ነው የሚል ጥበብ ያለበት ሐሳብ ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ራስ የሌለው አምላክ ብቻ ነው። ሌሎቹ ሁሉ ግን፣ ኢየሱስ ክርስቶስና ባሎች እንዲሁም ሚስቶች ጭምር፣ የሌላውን መመሪያዎችና ውሳኔዎች መቀበል ይኖርባቸዋል።

8. (ሀ) ባሎች የራስነት ቦታቸውን ሲሠሩበት የማንን ምሳሌ እንዲከተሉ ይጠበቅባቸዋል? (ለ) ባሎች ከዚህ ምሳሌ ምን ምን ሊማሩ ይችላሉ?

8 ይህ ማለት ባሎች የተመደበላቸውን ሥራ ለመፈጸም የክርስቶስን ራስነት መቀበል አለባቸው ማለት ነው። በተጨማሪም ክርስቶስ በተከታዮቹ ጉባኤ ላይ ያለውን የራስነት ሥልጣን እንደሚሠራበት ሁሉ እነርሱም ምሳሌውን በመከተል በሚስቶቻቸው ላይ ያላቸውን የራስነት ቦታ እንዲሠሩበት ያስፈልጋል። ክርስቶስ ምድራዊ ተከታዮቹን እንዴት አድርጎ ይይዝ ነበር? ምን ጊዜም በደግነትና በአሳቢነት መንፈስ ይይዛቸው ነበር። የእርሱን መመሪያ ለመቀበል ዝግተኛ በሚሆኑበትም ጊዜ እንኳ ኃይለ ቃል የሚናገር ወይም ቶሎ የሚቆጣ አልነበረም። (ማርቆስ 9:33-37፤ 10:35-45፤ ሉቃስ 22:24-27፤ ዮሐንስ 13:4-15) እንዲያውም ሕይወቱን በውዴታው ለእነርሱ አሳልፎ ሰጥቷል። (1 ዮሐንስ 3:16) አንድ ክርስቲያን ባል የክርስቶስን ምሳሌ በጥንቃቄ ማጥናትና ከቤተሰቡ ጋር ባለው ግንኙነት በሚቻለው ሁሉ ያንን ምሳሌ መከተል ይኖርበታል። ይህን ካደረገ ቤተሰቡን የሚጫን፣ ራስ ወዳድ ወይም ለሌሎች የማያስብ የቤተሰብ ራስ አይሆንም።

9. (ሀ) ብዙ ሚስቶች ምን ቅሬታ ያሰማሉ? (ለ) ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን ሲሠሩበት ምን ቢያስታውሱ ጥበብ ነው?

9 በሌላው በኩል ግን ባሎች ስለሚከተሉት ነገሮች ማሰብ ይኖርባቸዋል:- ሚስትህ እንደ ቤተሰቡ ራስ ሆነህ አትሠራም የሚል ቅሬታ አላትን? ለቤተሰቡ የሥራ እንቅስቃሴዎች እቅድ በማውጣትና የመጨረሻ ውሳኔ በማድረግ ኃላፊነትህን በመወጣት ቤቱን አትመራውም ብላ ትናገራለችን? ታዲያ ባል እንደመሆንህ ይህንን እንድታደርግ አምላክ ይጠይቅብህ የለምን? እርግጥ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባሎች የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦችና ምርጫዎች ለመቀበል አአምሮህን ክፍት ብታደርግና የራስነት ቦታህን ስትሠራበት እነዚህን ሐሳቦች ግምት ውስጥ ብታስገባ ጥበብ ነው። ባል እንደመሆንህ በቤተሰብ ውስጥ ይበልጥ አስቸጋሪ የሆነው የሥራ ድርሻ ባንተ ላይ እንደወደቀ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ከልብህ ጥረት ካደረግህ ሚስትህ አንተን ለመርዳትና ለመደገፍ እንደምትነሳሳ አያጠራጥርም። — ምሳሌ 13:10፤ 15:22

ሚስት የሥራ ድርሻዋን ስታከናውን

10. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቶች ምን አካሄድ እንዲመርጡ ያበረታታቸዋል? (ለ) ሚስቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሳይሰሙ ከቀሩ ምን ይሆናል?

10 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሴት የባሏ ረዳት ናት። (ዘፍጥረት 2:18) ከዚህ የሥራ ድርሻ ጋር በመስማማት መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ” በማለት ያሳስባቸዋል። (ኤፌሶን 5:22) በዛሬው ጊዜ የሴቶች ኃይለኝነትና ከወንድ ጋር መፎካከራቸው የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። ይሁን እንጂ ሚስቶች ባሎቻቸውን በመጋፋት የራስነት ቦታቸውን ለመንጠቅ ቢሞክሩ አብዛኛውን ጊዜ ችግር እንደሚፈጠር የተረጋገጠ ነው። ብዙ ባሎች ‘ፍላጎቷ ቤቱን ራሷ ለመምራት ከሆነ እንደፈለገችው ትሁን’ ብለው እንደሚናገሩ ያህል ነው።

11. (ሀ) አንዲት ሚስት ባሏ የአመራር ቦታውን እንዲይዝና እንዲሠራበት እንዴት ልትረዳው ትችላለች? (ለ) አንዲት ሚስት አምላክ የመደበላትን የሥራ ድርሻ ካከናወነች ይህ በባሏ ላይ ምን ውጤት ማስከተሉ አይቀርም?

11 ይሁን እንጂ ባልሽ ተግባሩን ስላላከናወነ ቤቱን ለመምራት እንደተገደድሽ ይሰማሽ ይሆናል። ሆኖም የቤተሰቡ ራስ በመሆኑ የተጣሉበትን ኃላፊነቶች እንዲወጣ እርሱን ለመርዳት ማድረግ የምትችይው የበለጠ ነገር ይኖራልን? በነገሮች ላይ አመራር እንዲሰጥ ወደ እርሱ እንደምትመለከቺ ታሳያለሽን? ሐሳብና መመሪያ እንዲሰጥሽ ትጠይቂዋለሽን? እርሱ የሚያደርገውን በምንም መንገድ ላለማንቋሸሽ ትጠነቀቂያለሽን? አንቺ በቤተሰቡ ውስጥ አምላክ የሰጠሽን የሥራ ድርሻ በእርግጥ ከፈጸምሽ ባልሽም የራሱን ኃላፊነት ለማከናወን መነሳሳቱ አይቀርም። — ቆላስይስ 3:18, 19

12. ሚስቶች ያላቸው አስተሳሰብ ከባላቸው አስተሳሰብ የሚለይ ቢሆን የሚሰማቸውን መግለጻቸው ተገቢ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳየው ምንድን ነው?

12 እንዲህም ሲባል ሚስት ከባሏ የተለየ ስሜት ካላት ሐሳቧን መግለጽ የለባትም ማለት አይደለም። ትክክለኛ አስተሳሰብ ይኖራት ይሆናል፤ ባሏም እርሷን ቢያዳምጥ ቤተሰቡ ይጠቀማል። የአብርሃም ሚስት ሣራ ለባሏ በመገዛቷ ምክንያት ለክርስቲያን ሚስቶች እንደ ምሳሌ ሆና ትጠቀሳለች። (1 ጴጥሮስ 3:1, 5, 6) ይሁን እንጂ ለቤተሰቡ ችግር መፍትሔ ይሆናል ብላ ያሰበችውን አንድ ሐሳብ አቀረበች። አብርሃም በሐሳቧ ሳይስማማ በቀረ ጊዜ አምላክ “ሣራ የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ” አለው። (ዘፍጥረት 21:9-12) እርግጥ ባልየው በአንድ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ካደረገ በኋላ ያ ውሳኔ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ካልሆነ ሚስቲቱ መደገፍ ይኖርባታል። — ሥራ 5:29

13. ጥሩ ሚስት ምን ታደርጋለች? ይህስ በቤተሰቧ ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?

13 አንዲት ሚስት የሥራ ድርሻዋን ተገቢ በሆነ መንገድ ስታከናውን ቤተሰቡን በደንብ ለመያዝ ማድረግ የምትችለው ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ ለሰውነት ገንቢ የሆነ ምግብ ልታዘጋጅ፣ ቤቱን በሥርዓትና በንጽሕና ልትይዝ እንዲሁም ልጆችን በማስተማሩ ሥራ ልትካፈል ትችላለች። ያገቡ ሴቶች “ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ንጹሆች፣ በቤት የሚሠሩ፣ በጎዎች፣ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ” መጽሐፍ ቅዱስ ያሳስባቸዋል። (ቲቶ 2:4, 5) እነዚህን ተግባሮች የምታከናውን ሚስትና እናት ከቤተሰብዋ ዘላቂ ፍቅርና አክብሮት ታተርፋለች። — ምሳሌ 31:10, 11, 26-28

ልጆች በቤተሰብ ውስጥ ያላቸው ቦታ

14. (ሀ) ልጆች በቤተሰብ ውስጥ ያላቸው ተገቢ ቦታ ምንድን ነው? (ለ) ልጆች ከኢየሱስ ምሳሌ ምን ለመማር ይችላሉ?

14 ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት “ብዙ ተባዙ” የሚል መመሪያ ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 1:28) አዎን ልጅ እንዲወልዱ አምላክ ነገራቸው። የሚወለዱት ልጆች ለቤተሰቡ በረከት ይሆናሉ። (መዝሙር 127:3-5) ልጆች በወላጆቻቸው ሕግና ትዕዛዝ ሥር ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የአንድን ልጅ ቦታ ከባሪያ ቦታ ጋር ያመሳስለዋል። (ምሳሌ 1:8፤ 6:20-23፤ ገላትያ 4:1) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስም እንኳ ልጅ በነበረበት ጊዜ ለወላጆቹ ይገዛ ነበር። (ሉቃስ 2:51) ይህም ይታዘዝላቸውና መመሪያቸውን ይከተል ነበር ማለት ነው። ሁሉም ልጆች ልክ እንደዚሁ ቢያደርጉ ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

15. ልጆች ብዙውን ጊዜ ወላጆቻቸውን የሚያበሳጩት ለምንድን ነው?

15 በዛሬው ጊዜ ግን ልጆች ለቤተሰቡ በረከት መሆናቸው ቀርቶ የወላጆችን ልብ የሚያሳዝኑ ሆነዋል። ለምን? ልጆቹም ሆኑ ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስ ስለቤተሰብ አኗኗር ያወጣቸውን መመሪያዎች በሕይወታቸው ውስጥ ሳይሰሩባቸው ስለሚቀሩ ነው። ከነዚህ የአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ቀጥሎ ባሉት ገጾች ላይ ጥቂቶቹን እንመርምር። በምንመረምርበትም ጊዜ እነዚህን ነገሮች በሥራ ላይ በማዋል ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽዖ ማድረግ ይቻላል ቢባል በዚህ መስማማት የማይቻል እንደሆነ እስቲ ተመልከተው።

ሚስትህን ውደድ፣ አክብራትም

16. ባሎች ምን እንዲያደርጉ ታዘዋል? እነዚህንስ ትእዛዞች ተገቢ በሆነ መንገድ የሚፈጽሙት እንዴት ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስ “እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ስጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዷቸው ይገባቸዋል” በማለት መለኮታዊ ጥበብ የሞላበት መመሪያ ይሰጣል። (ኤፌሶን 5:28-30) ሚስቶች ደስተኞች እንዲሆኑ ከተፈለገ ሌላው እንደሚወዳቸው ሆኖ ሊሰማቸው እንደሚያስፈልግ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ታይቷል። ይህም ማለት አንድ ባል ለሚስቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጣት፣ ሊያዝንላት፣ ሁኔታዋን ሊረዳላትና እምነት ሊያሳድርባት ይገባል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘ክብር ሊሰጣት’ ይገባል። ይህንንም የሚያደርገው በሚሠራው ነገር ሁሉ እሷን በማሰብ ነው። በዚህ መንገድ የእሷን አክብሮት ያገኛል። — 1 ጴጥሮስ 3:7

ባልሽን አክብሪ

17. ሚስቶች ምን እንዲያደርጉ ታዘዋል? ይህንንስ የሚፈጽሙት እንዴት ነው?

17 ሚስቶችስ ምን ማድረግ አለባቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስትም ባሏን ትፍራ” ወይም እንደ አዓት “ለባሏ የጠለቀ አክብሮት ይኑራት” ሲል ይናገራል። (ኤፌሶን 5:33) አንዳንድ ባሎች በሚስቶቻቸው ቅር ከሚሰኙባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ይህንን ምክር አለመከተላቸው ነው። አንዲት ሚስት ባሏን የምታከብረው ውሳኔዎቹን በመደገፍና የቤተሰቡን ግቦች ለማከናወን በሙሉ ነፍሷ ከእርሱ ጋር በመተባበር ነው። ‘ረዳትና ማሟያ’ እንድትሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሰጣትን የሥራ ድርሻ ብትፈጽም ባሏ እሷን ለመውደድ ቀላል ይሆንለታል። — ዘፍጥረት 2:18

እርስ በርሳችሁ ታማኝ ሁኑ

18. ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ታማኝ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

18 “ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ታማኝ መሆን አለባቸው” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ለባልየው እንዲህ ይለዋል:- “በሚስትህ ደስ ይበልህ፤ ያገባሃትም ልጃገረድ ደስ ታሰኝህ . . . ፍቅርህን ለሌላ ሴት ለምን ትሰጣለህ? የሌላውን ወንድ ሚስት ማራኪነትስ ለምን ትመርጣለህ?” (ዕብራውያን 13:4፤ ምሳሌ 5:18-20 የዛሬው የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) አዎን ምንዝር ከአምላክ ሕግ ጋር ይጋጫል፤ በትዳርም ውስጥ ችግር ያስነሳል። አንዲት የትዳር ሁኔታ ተመራማሪ “ብዙ ሰዎች ምንዝር ለትዳር ቅመም ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ” ብለው ከተናገሩ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ አድራጎት ግን ሁልጊዜ ሁከት እንደሚያመጣ ገልጸዋል። — ምሳሌ 6:27-29, 32

የትዳር ጓደኛችሁን ለማስደሰት መንገድ ፈልጉ

19. ባልና ሚስት ግብረ ሥጋን የበለጠ ደስታ ሊያገኙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

19 ደስታ የሚመጣው አንድ ሰው በሩካቤ ሥጋ ራሱን ብቻ ለማስደሰት በመፈለግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ደስታ የሚመጣው የትዳር ጓደኛን ጭምር ለማስደሰት በመፈለግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባሏ” ሲል ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:3) ጠበቅ ተደርጎ የተገለጸው መስጠቱለሌላው ማድረጉ ነው። ሰጪውም በመስጠቱ እውነተኛ ደስታን ያገኛል። ሁኔታው ኢየሱስ ክርስቶስ:- “ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የበለጠ ደስታ ይገኛል” ብሎ እንደተናገረው ነው። — ሥራ 20:35 አዓት

ለልጆቻችሁ ጊዜያችሁን ስጡ

20. ከልጆች ጋር ሆኖ አንዳንድ ነገሮችን መሥራቱ ለምን በጣም አስፈላጊ ነው?

20 አንድ የስምንት ዓመት ልጅ እንዲህ አለ:- “አባቴ ቀኑን በሙሉ ሲሠራ ይውላል። እቤት ውስጥ ፈጽሞ አይቀመጥም። ገንዘብና ብዙ መጫወቻ ይሰጠኛል፤ ነገር ግን ፈጽሞ አላየውም። በጣም እወደዋለሁ፤ ስለዚህ የበለጠ እሱን ማየት እንድችል ጨርሶ ባይሠራ ደስ ይለኝ ነበር።” መጽሐፍ ቅዱስ ‘በቤታችሁ ስትቀመጡ በመንገድ ስትሄዱ፣ ስትተኙም፣ ስትነሱም ልጆቻችሁን አስተምሯቸው’ ሲል የሚሰጠውን መመሪያ ወላጆች ሲከተሉ የቤተሰብ ኑሮ እንዴት የበለጠ አስደሳች ይሆናል! ለልጆቻችሁ ምርጥ ጊዜ መስጠታችሁ ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ነው። — ዘዳግም 11:19፤ ምሳሌ 22:6

የሚያስፈልገውን ተግሳጽ ስጡ

21. ለልጆች ተግሳጽን ስለመስጠት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

21 የሰማዩ አባታችን ለሕዝቡ እርማትን ወይም ተግሳጽን በመስጠት ለወላጆች ተገቢውን ምሳሌ አሳይቷቸዋል። ልጆች ተግሳጽ ያስፈልጋቸዋል። (ዕብራውያን 12:6፤ ምሳሌ 29:15) ይህንን በመገንዘብ መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተም አባቶች ሆይ ልጆቻችሁን [በይሖዋ (አዓት)] ምክርና በተግሳጽ አሳድጓቸው” በማለት ያሳስባል። መቀመጫ ላይ መምታትን ወይም አንዳንድ መብት መንፈግን ሊጨምር የሚችለውን ተግሳጽ መስጠቱ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመውደዳቸው ማስረጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጁን የሚወድ ተግቶ ይገስጸዋል” ይላል። — ኤፌሶን 6:4፤ ምሳሌ 13:24፤ 23:13, 14

ወጣቶች — የዓለማዊ መንገዶችን ግፊት ተቋቋሙት

22. ወጣቶች ምን ግዴታ አለባቸው? ይህስ ምን ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

22 ዓለም ወጣቶችን የአምላክን ሕጎች ለማስጣስ ጥረት ያደርጋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ስንፍና (ሞኝነት) በሕፃን ልብ ታስሯል።” (ምሳሌ 22:15) ስለዚህ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጉ ትግልን ይጠይቃል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆች ሆይ ወላጆቻችሁን መታዘዙ ክርስቲያናዊ ግዴታችሁ ነው፤ ምክንያቱም መደረግ ያለበት ትክክለኛ ነገር ይህ ነው” ይላል። ይህን ማድረጋችሁ ብዙ በረከቶች ያመጣላችኋል። እንግዲያው እናንተ ልጆች ጥበበኞች ሁኑ። “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር ተከተሉ። አደንዛዥ ዕፅ እንድትወስዱ፣ እንድትሰክሩ፣ ዝሙት እንድትፈጽሙና ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጩ ሌሎች ነገሮችን እንድታደርጉ የሚመጣባችሁን ግፊት ሁሉ ተቋቋሙት። — ኤፌሶን 6:1-4፤ መክብብ 12:1፤ ምሳሌ 1:10-19የእንግሊዝኛው የዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስን አብራችሁ አጥኑ

23. ቤተሰቦች አብረው በማጥናት ምን ጥቅሞች ሊያገኙ ይችላሉ?

23 አንዱ የቤተሰቡ አባል የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ቢያጠናና በሥራ ላይ ቢያውላቸው ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ነገር ግን ሁሉም ማለትም ባል፣ ሚስትና ልጆች እንደዚያ ቢያደርጉ ቤተሰቡ እንዴት የተባረከ ይሆናል! እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል ሌላው ይሖዋ አምላክን እንዲያገለግል ለመርዳት ስለሚሞክር በመሀከላቸው ሞቅ ያለ የመዋደድ ስሜትና የጠበቀ ዝምድና ይኖራል፤ ሐሳባቸውንም በግልጽ ይለዋወጣሉ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን አብሮ ማጥናቱን የቤተሰቡ ልማድ አድርጉት። — ዘዳግም 6:4-9፤ ዮሐንስ 17:3

የቤተሰብን ችግሮች በጥሩ ሁኔታ መፍታት

24. የትዳር ጓደኞች አንዱ የሚሠራቸውን ስህተቶች ሌላው ችላ ብሎ ማለፍ ያለበት ለምንድን ነው?

24 ብዙውን ጊዜ ደስተኛ የሆኑ ቤተሰቦችም እንኳ አልፎ አልፎ ችግር ይኖራቸዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁላችን ፍጽምና ስለሌለንና ስሕተት ስለምንሠራ ነው። “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ያዕቆብ 3:2) ስለዚህ የትዳር ጓደኞች አንዱ ከሌላው ፍጽምናን መጠበቅ የለበትም። ከዚህ ይልቅ ስሕተት የሚሠሩ መሆናቸውን መቀበል ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ማንኛቸውም ቢሆኑ ፍጹም ደስተኛ የሆነ ትዳርን መጠበቅ የለባቸውም። ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ይህ የማይቻል ነውና።

25. በጋብቻ ውስጥ የሚነሱ ችግሮች በፍቅር መፈታት ያለባቸው እንዴት ነው?

25 እርግጥ ባልም ሆነ ሚስት አንዱ ሌላውን የሚያበሳጭ ነገር ከማድረግ ለመራቅ ይፈልጋሉ። ሆኖም የቱንም ያህል ቢጥሩ አልፎ አልፎ ሌላውን የሚያበሳጭ ነገር ማድረጋቸው አይቀርም። ታዲያ ችግሮች መፈታት ያለባቸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” የሚል ነው። (1 ጴጥሮስ 4:8) ይህ ማለት ፍቅር የሚያሳዩ ባልና ሚስት አንዳቸው የሚሠራቸውን ስሕተቶች ሌላው ሁልጊዜ አይጠቅስም ማለት ነው። ፍቅር ልክ እንደሚከተለው ብሎ እንደሚናገር ያህል ነው:- ‘አዎን ስሕተት ሠርተሻል እኔም አልፎ አልፎ እሳሳታለሁ፤ ስለዚህ ያንቺን ስሕተቶች ቸል ብዬ አልፋቸዋለሁ፤ አንቺም እንደዚያ ብታደርጊልኝ ደስ ይለኛል።’ — ምሳሌ 10:12፤ 19:11

26. አንድ ችግር ከተነሳ ችግሩን ለመፍታት ምን ሊረዳ ይችላል?

26 ባልና ሚስት ስሕተታቸውን ለመቀበል ፈቃደኞች ሲሆኑና እነዚያን ለማረም ሲሞከሩ ከብዙ ክርክርና ንዴት መዳን ይቻላል። ግብ ማድረግ ያለባቸው ተከራክሮ ለመርታት ሳይሆን ችግሮቹን ለመፍታት መሆን ይኖርበታል። የተሳሳተው የትዳር ጓደኛችሁ ቢሆንም ደግ በመሆን ችግሩን ለመፍታት ቀላል አድርጉለት። ጥፋቱ የእናንተው ከሆነ በትሕትና ይቅርታ ጠይቁ። ለሌላ ጊዜ አታሳልፉት። ችግሩን ሳይውል ሳያድር ፍቱት። “በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።” — ኤፌሶን 4:26

27. የትዳር ጓደኞች የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ቢከተሉ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይረዳቸዋል?

27 በተለይ ያገባህ ሰው ከሆንክ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” የሚለውን ደንብ መከተል ያስፈልግሃል። (ፊልጵስዩስ 2:4) የሚከተለውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ማክበር አለብህ:- “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋኅነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፤ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱ።” — ቆላስይስ 3:12-14

28. (ሀ) የጋብቻ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳው መንገድ ፍቺ ነውን? (ለ) አንድ ሰው ፈትቶ ሌላ ለማግባት ነፃ የሚያደርገው መጽሐፍ ቅዱስ የሚፈቅደው ምክንያት ምን ብቻ ነው?

28 ዛሬ ብዙ ባልና ሚስት ከአምላክ ቃል የሚገኘው ምክር ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲረዳቸው አይፈቅዱለትም። ከዚህ ይልቅ ይፋታሉ። አምላክ መፋታትን ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ መንገድ አድርጎ ይቀበለዋልን? በፍጹም አይቀበለውም። (ሚልክያስ 2:15, 16) የአምላክ ሐሳብ ጋብቻ የሕይወት ዘመን ማሠሪያ ሆኖ እንዲቀጥል ነበር። (ሮሜ 7:2) አንድ ሰው እንዲፈታና ሌላ እንዲያገባ ነፃ ለመሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚፈቅድለት ምክንያት አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ዝሙት (በግሪክኛ ፖርኒያ ማለትም ከባድ የጾታ ብልግና) ብቻ ነው። ዝሙት ከተፈጸመ ተበዳዩ ለመፍታት ወይም ላለመፍታት ሊወስን ይችላል። — ማቴዎስ 5:32

29. (ሀ) የትዳር ጓደኛሽ በክርስቲያናዊ አምልኮትሽ ባይተባበርሽ ምን ማድረግ አለብሽ? (ለ) ምናልባት ምን ውጤት ሊገኝ ይችል ይሆናል?

29 የትዳር ጓደኛሽ የአምላክን ቃል ካንቺ ጋር ለማጥናት እምቢ ቢል ወይም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴሽን ቢቃወምስ? አሁንም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ጓደኛሽ ጋር እንድትኖሪ ያበረታታል እንጂ ከችግሮችሽ ለመላቀቅ ቀላሉ መንገድ ተለያይቶ መኖር ነው አይልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለራስሽ ጠባይ የሚናገራቸውን ነገሮች በሥራ በማዋል በቤትሽ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል በግልሽ የምትችይውን ሁሉ አድርጊ። ከጊዜ በኋላ በክርስቲያናዊ ጠባይሽ ምክንያት የትዳር ጓደኛሽን ከጐንሽ እንዲቆም ልታደርጊው ትችይ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:10-16፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ለረጅም ጊዜ ያደረግሽው ፍቅራዊ ትዕግሥት በዚህ መንገድ ዋጋ ሲያስገኝልሽ እንዴት ያለ በረከት ይሆናል!

30. ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

30 በዛሬው ጊዜ ብዙ የቤተሰብ ችግሮች ልጆችን የሚመለከቱ ናቸው። በቤተሰባችሁ ውስጥ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ካለ ምን ሊደረግ ይችላል? ከሁሉ በፊት ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ራሳችሁ ጥሩ ምሳሌ ማሳየት ያስፈልጋችኋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ልጆች ከምትናገሩት ቃል ይልቅ የምታደርጉትን ለመከተል ቶሎ ስለሚያዘነብሉ ነው። የምታደርጉት ነገር ከምትናገሩት የተለየ ከሆነ ልጆች ያንን ቶሎ ይመለከቱታል። እንግዲያው ልጆቻችሁ ጥሩ የሆነ ክርስቲያናዊ ኑሮ እንዲኖሩ ከፈለጋችሁ ራሳችሁ ምሳሌ መሆን ይኖርባችኋል። — ሮሜ 2:21, 22

31. (ሀ) ልጆች የወላጆቻቸውን ምክር ለመታዘዝ ምን ከዚህ የበለጠ ምክንያት ያስፈልጋቸዋል? (ለ) ልጅህ ዝሙትን የሚከለክለውን የአምላክ ሕግ መታዘዙ ጥበብ እንደሆነ ልታሳየው የምትችለው እንዴት ነው?

31 በተጨማሪም ለልጆቻችሁ ምክንያት እያቀረባችሁ ማወያየት ያስፈልጋችኋል። ‘ስሕተት ስለሆነ ዝሙት እንድትፈጽም አልፈልግም’ ብለህ ለልጆችህ መናገሩ በቂ አይደለም። እንደ ዝሙት ያሉት ነገሮች ስሕተት ናቸው ያለው ፈጣሪያቸው ይሖዋ አምላክ መሆኑን እንድታሳዩአቸው ያስፈልጋል። (ኤፌሶን 5:3-5፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-7) ነገር ግን ይህም ቢሆን በቂ አይደለም። ልጆች የአምላክን ሕጎች ለምን መታዘዝ እንዳለባቸውና እንደዚያ ማድረጋቸው እንዴት እንደሚጠቅማቸው እንዲታያቸው ልንረዳቸው ያስፈልጋል። ለምሳሌ ወጣት ልጅህ የወንዱ ዘርና የሴቲቱ ዕንቁላል ተዋሕደው በሚያስደንቅ መንገድ እንዴት ሰብአዊ ሕፃን እንደሚሆኑ እንዲያስተውል ካደረግህ በኋላ ‘ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን አባለዘርእ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ከሁሉ የበለጠ የሚያውቀው ይህንን የወሊድ ተአምር ያስጀመረው አምላክ አይመስልህምን?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። (መዝሙር 139:13-17) ወይም ‘ታላቁ ፈጣሪያችን በሕይወት ውስጥ ደስታ የሚከለክለንን ሕግ የሚሰጠን ይመስልሃልን? ከዚህ ይልቅ የበለጠ ደስተኞች የምንሆነው ሕጎቹን በመታዘዝ አይደለምን?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ።

32. (ሀ) የልጅህ አመለካከት ከአምላክ አመለካከት ጋር የማይስማማ ሆኖ ብታገኘው ዝንባሌህ ምን መሆን አለበት? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን መከተሉ ጥበብ መሆኑን ልጅህ እንዲያስተውል እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?

32 እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች ልጅህ የአባለዘርእን አጠቃቀም ስለሚቆጣጠረው የአምላክ ሕግ ምክንያቶቹን ማሰላሰል እንዲጀምር ሊያደርጉት ይችላሉ። የሚሰጣቸውን ሐሳቦች ተቀበል። ሐሳቦቹ ደስ ባይሉህ አትናደድ ወይም አትቆጣ። የልጅህ ትውልድ ከመጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ ትምህርቶች በጣም ርቆ የሄደ መሆኑን ለመረዳት ሞክር። ከዚያም የልጁ ትውልድ የሚፈጽማቸው የብልግና ድርጊቶች ለምን ጥበብ የጎደላቸው እንደሆኑ ለልጅህ ለማሳየት ሞክር። የጾታ ብልግና ዲቃላ መውለድን፣ የአባለዘርእ በሽታን ወይም ሌሎች ችግሮችን ያስከተለባቸውን ሰዎች ምናልባት እንደ ምሳሌ አድርገህ መጥቀስ ትችል ይሆናል። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረው ምክንያታዊና ትክክል እንደሆነ እንዲገባው ልትረዳው ትችላለህ።

33. ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ያለን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ የቤተሰባችንን ኑሮ የተሳካ ለማድረግ ሊረዳን የሚገባው ለምንድን ነው?

33 የቤተሰባችንን ኑሮ የተሳካ ለማድረግ ሊረዳን የሚገባው በተለይ ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ለዘላለም እንድንኖር የተሰጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋ ነው። ለምን እንዲህ እንላለን? ምክንያቱም በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ በእርግጥ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ በዚያን ጊዜ ለማሳየት ተስፋ የምናደርገውን ዓይነት ጠባይ አሁን ለማሳየት ብርቱ ጥረት እናደርጋለን። ይህም ይሖዋ አምላክ የሚሰጠንን መመሪያዎች አጥብቀን እንከተላለን ማለት ነው። ከዚህ የተነሣ አምላክ የዘላለም ሕይወትንና ከፊታችን በተዘረጋው ዘላለማዊ ጊዜ ውስጥ ብዙ ደስታን በመስጠት አሁን ያለንን ደስታ ጥሩ ድምድማት ያደርግለታል። — ምሳሌ 3:11-18

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]