የዘላለም ሕይወት ጠላት
ምዕራፍ 2
የዘላለም ሕይወት ጠላት
1. ደስታና ሰላም ብዙ ጊዜ ስለማይገኙ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
አብዛኛው ሰው በምድር ላይ ደስታን ለማየት ይፈልጋል። ታዲያ በጣም ብዙ ሰዎች ደስተኛ ያልሆኑት ለምንድን ነው? ችግሩ ምን ይሆን? አብዛኞቹ ሰዎች የሚፈልጉት ሰላም ሆኖ ሳለ አንዳንድ ብሔራት ከሌሎች ጋር የሚዋጉትና ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚጠላሉት ለምንድን ነው? ከበስተኋላ ሆኖ እነዚህን መጥፎ ነገሮች እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ኃይል ይኖር ይሆን? ብሔራትን በጋራ የሚቆጣጠር አንድ በዓይን የማይታይ ኃይል ይኖር ይሆን?
2. ሰዎችን እየተቆጣጠረ ያለ በዓይን የማይታይ አንድ ክፉ ኃይል ይኖር ይሆንን ብለው ብዙዎች እንዲጠይቁ የሚያደርጋቸው በታሪክ ውስጥ ምን የተፈጸመ ግፍ አለ?
2 ብዙ ሰዎች በሰው ዘር ላይ የሚፈፀመውን አሰቃቂ ጭካኔ ይኸውም ሰዎች ትንፋሽ አጥተውና ተቃጥለው እንዲሞቱ ተብሎ በጦርነት ጊዜ የሚጣሉትን አስፈሪ ጋዞች እንዲሁም የናፓልምና የአቶሚክ ቦምቦች ሲያስቡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚል ጥያቄ መጥቶባቸዋል። ከዚህም በላይ የእሳት ነበልባል የሚተፉ መሣሪያዎችን፣ ማጎሪያ ካምፖችንና በቅርብ ዓመታት በካምቦዲያ እንደተፈጸመው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በግፍ መጨፍጨፍ አስብ። ይህ ሁሉ ግፍ እንዲሁ እንደ አጋጣሚ የተፈጸመ ይመስልሃልን? ምንም እንኳን ሰው ራሱ አስከፊ ድርጊቶችን ለመፈጸም ችሎታ ቢኖረውም የሚያንገፈግፉ የክፋት አድራጎቶችን ስትመለከት ሰው በዓይን በማይታይ በአንድ ክፉ ኃይል እየተነዳ ያለ አይመስልምን?
3. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም አገዛዝ ምን ይላል?
3 መልሱን መገመት ምንም አያስፈልግም። የማሰብ ችሎታ ያለውና በዓይን የማይታይ አንድ ፍጡር ሰዎችንና ብሔራትን እየተቆጣጠረ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ኃይለኛ ፍጡር “የዚህ ዓለም ገዥ“ ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ታዲያ እርሱ ማን ነው?
4. ዲያብሎስ ለኢየሱስ ምን አሳየው? ምንስ ልስጥህ አለው?
4 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲጀምር ያጋጠመውን አንድ ነገር ማስታወስህ እርሱ ማን መሆኑን ለማወቅ ይረዳሃል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ምድረበዳ ማቴዎስ 4:8, 9
እንደሄደና ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ በሚጠራ በዓይን የማይታይ ፍጡር እንደተፈተነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከፈተናዎቹ አንዱ በሚከተለው መንገድ ተገልጿል፦ “ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፣ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ:- ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።”—5. (ሀ) የዓለም መንግሥታት በሙሉ የዲያብሎስ ንብረት መሆናቸውን ምን ያሳያል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት “የዚህ ዓለም አምላክ“ ማን ነው?
5 ዲያብሎስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰጠው ያቀረበለትን ነገር አስብ! “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ“ ልስጥህ ብሎታል። እነዚህ ሁሉ ዓለማውያን መንግሥታት በእርግጥ የዲያብሎስ ናቸውን? አዎን፤ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ልስጥህ ብሎ ለኢየሱስ እንዴት ሊያቀርብለት ይችል ነበር? የሰይጣን መሆናቸውን ኢየሱስ አልካደም። እንደዚያ ባይሆኑ ኖሮ ኢየሱስ የአንተ አይደሉም ይለው ነበር። የሁሉም የዓለም ብሔራት የማይታይ 1 ዮሐንስ 5:19) እንዲያውም የአምላክ ቃል ሰይጣንን “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎ ይጠራዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:4
ገዥ በእርግጥ ሰይጣን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ይላል። (6. (ሀ)ስለ ሰይጣን አገዛዝ ያገኘነው ይህ እውቀት ምንን እንድናስተውል ይረዳናል? (ለ) ሰይጣን ምን ሊያደርግብን ይፈልጋል? ስለዚህ ምን ማድረግ አለብን?
6 ይህ እውቀት ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሎ የተናገረበት ምክንያት እንዲገባን ይረዳናል። (ዮሐንስ 18:36) ከዚህም በተጨማሪ ጤነኛ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ፍላጎታቸው በሰላም መኖር ሆኖ ሳለ አንዱ ብሔር ሌላውን የሚጠላበትንና ለማጥፋት የሚፈልግበትን ምክንያት ለማስተዋል ይረዳናል። አዎን ’ሰይጣን መላዋን ምድር እያሳተ ነው።’ (ራዕይ 12:9) እኛንም ጭምር ለማሳሳት ይፈልጋል። የአምላክን የዘላለም ሕይወት ስጦታ እንድናገኝ አይፈልግም። ስለዚህ በእርሱ ግፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ከማድረግ ለመራቅ ልንታገለው ያስፈልገናል። (ኤፌሶን 6:12) ሰይጣን እኛን ለማሳሳት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለመቋቋም ስለ እርሱና ስለ ዘዴዎቹ ማወቅ ያስፈልገናል።
ዲያብሎስ ማን ነው?
7. ዲያብሎስን ለምን ልናየው አንችልም?
7 ‘ሰይጣን ዲያብሎስ በእርግጥ በሕይወት የሚኖር አንድ አካላዊ ፍጡር ነው። አንዳንድ ሰዎች እንደሚያምኑት ሰይጣን በሁሉም የሰው ልጆች ላይ የሚያድር ክፋት ማለት አይደለም። እርግጥ ሰዎች አምላክን ማየት የማይችሉበት ምክንያት እንዳለ ሁሉ ዲያብሎስንም በዚያው ምክንያት ሊያዩት አይችሉም። አምላክም ሆነ ዲያብሎስ ሰው ካለው ዓይነት ሕይወት በጣም የላቀ ሕይወት አላቸው። በዓይናችን ሊታዩ የማይችሉ መንፈሳዊ አካላት ናቸው።—ዮሐንስ 4:24
8. ብዙ ሰዎች አምላክ ዲያብሎስን ዲያብሎስ አድርጎ ፈጠረው ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው?
8 አንድ ሰው ‘አምላክ ፍቅር ከሆነ ታዲያ ለምን ዲያብሎስን ፈጠረው?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። (1 ዮሐንስ 4:8) እንደ እውነቱ ከሆነ ዲያብሎስን አምላክ ዲያብሎስ አድርጎ አልፈጠረውም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘ሁሉንም ሰው የፈጠረው አምላክ ከሆነ ዲያብሎስንም የፈጠረው እርሱ መሆን አለበት። ሌላ ማን ሊፈጥረው ይችላል? ዲያብሎስ ከየት መጣ?’ ብሎ ይናገር ይሆናል።
9. (ሀ) መላእክት ምን ዓይነት ፍጡሮች ናቸው? (ለ) “ዲያብሎስ“ እና “ሰይጣን“ የሚሉት ቃላት ምን ማለት ናቸው?
9 አምላክ እንደ እርሱ ያሉ እጅግ በጣም ብዙ ሕያዋን መንፈሣዊ አካሎችን እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡሮች መላእክት ተብለው ይጠራሉ። በተጨማሪም “የአምላክ ልጆች” ተብለው ይጠራሉ። (ኢዮብ 38:7፤ መዝሙር 104:4፤ ዕብራውያን 1:7, 13, 14) አምላክ ሁሉንም ፍጹማን አድርጎ ፈጠራቸው። አንዳቸውም ቢሆን ሰይጣን ወይም ዲያብሎስ አልነበረም። “ዲያብሎስ” የሚለው ቃል ስም አጥፊ ማለት ሲሆን “ሰይጣን” የሚለው ቃል ደግሞ ተቃዋሚ ማለት ነው።
10. (ሀ) ሰይጣን ዲያብሎስን እንደዚያ አድርጎ የሠራው ማን ነው? (ለ) አንድ ጥሩ ሰው ራሱን ወንጀለኛ ለማድረግ የሚችለው እንዴት ሊሆን ይችላል?
10 ይሁን እንጂ ከእነዚህ መንፈሳውያን የአምላክ ልጆች አንዱ ራሱን ዲያብሎስ የሚያደርግበት ጊዜ መጣ። ይህም መጠሪያ ለሌላው ጥላቻ ያለውና ስሙን እያክፋፋ የሚናገር ሐሰተኛ ማለት ነው። በተጨማሪም ራሱን ሰይጣን አደረገ። ይህም ስም የአምላክ ተቃዋሚ ማለት ነው። ከጊዜ በኋላ እንደዚያ ሆነ እንጂ በዚያ መንገድ አልተፈጠረም ነበር። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ሌባ የሆነ ሰው ሌባ ሆኖ አልተወለደም። ከጥሩ ቤተሰብ የመጣ ሊሆን ይችላል። እውነተኛ የሆኑ ወላጆችና ሕግ የሚያከብሩ ወንድሞችና እኅቶች ይኖሩት ይሆናል። ነገር ግን በገንዘብ ሊገኙ ለሚችሉ ነገሮች ያለው የራሱ ምኞት ሌባ አድርጎት ይሆናል። ታዲያ ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ ያደረገው እንዴት ነው?
11. (ሀ) አንድ አመጸኛ መልአክ ስለ የትኛው የአምላክ ዓላማ ያውቅ ነበር? (ለ) ይህ መልአክ ምን ምኞት አደረበት? ወደ ምንስ አደረሰው?
11 ራሱን ዲያብሎስ ያደረገው መልአክ አምላክ በመጀመሪያ ምድርን በኋላም የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር በቦታው ተገኝቶ ነበር። (ኢዮብ 38:4, 7) ስለዚህ አምላክ ልጆች ውለዱ ብሎ ሲነግራቸው ሰምቶ መሆን አለበት። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ከጊዜ በኋላ መላዋ ምድር አምላክን በሚያመልኩ ጻድቃን ሰዎች እንደምትሞላ አውቆ ነበር። የአምላክ ዓላማ ይህ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መልአክ ስለራሱ ውበትና የማሰብ ችሎታ ከልክ ያለፈ አሰበና ለአምላክ የሚሰጠውን አምልኮ ለራሱ ለመውሰድ ፈለገ። (ሕዝቅኤል 28:13-15፤ ማቴዎስ 4:10) ይህንን የተሳሳተ ምኞት ከአእምሮው በማውጣት ፈንታ እየመላለሰ አሰበበት። ይህም ሁኔታ የተመኘውን ክብርና ትልቅ ቦታ ለማግኘት እርምጃ ወደ መውሰድ አደረሰው። ያደረገው ምን ነበር?—ያዕቆብ 1:14, 15
12. (ሀ) ይህ መልአክ ሔዋንን እንዴት አናገራት? ምን ብሎስ ነገራት? (ለ) ይህ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነው እንዴት ነው? (ሐ) ስለ ዲያብሎስ መልክ ምን የተሳሳተ አስተሳሰብ አለ?
12 አመጸኛው መልአክ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን ለማነጋገር በአንድ ዝቅተኛ ፍጡር ይኸውም በእባብ ተጠቀመ። ጥሩ ልምድ ያለው ሰው በአቅራቢያው ያለ እንስሳ ወይም አሻንጉሊት እየተናገረ ያለ እንደሚያስመስል ሁሉ ሰይጣንም እንዲሁ አደረገ። ይሁን እንጂ ለሔዋን እየተናገረ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ “የመጀመሪያው እባብ” ብሎ የሚጠራው ይህ አመጸኛ መልአክ ነበር። (ራዕይ 12:9) እርሱም አምላክ እውነቱን አልነገረሽም፣ ሊኖርሽ የሚገባውንም እውቀት ደብቆሻል አላት። (ዘፍጥረት 3:1-5) ይህ በጥላቻ የተነገረ ውሸት ነው። በዚህም ምክንያት ዲያብሎስ ሆነ። በተጨማሪም በዚህ መንገድ የአምላክ ተቃዋሚ ወይም ሰይጣን ሆነ። እዚህ ላይ ማስተዋል እንደምትችለው ዲያብሎስ ከምድር በታች ያለን አንድ ማቃጠያ ሥፍራ በበላይነት የሚቆጣጠር በራሱ ላይ ቀንድ ያለውና ሰዎች የሚያገለባብጥበት መንሽ የያዘ ፍጡር ነው ብሎ ማሰብ ስሕተት ነው። እርሱ በእርግጥ በጣም ኃይለኛ የሆነ ክፉ መልአክ ነው።
የዓለም መከራዎች ምንጭ
13. (ሀ) ሔዋን የዲያብሎስን ውሸት ሰምታ ምን አደረገች? (ለ) ዲያብሎስ ምን ብሎ ተናገረ?
13 ዲያብሎስ ለሔዋን የነገራት ውሸት ልክ እንዳሰበው ግቡን መታ። እርሱ የነገራትን አመነችና አምላክን ሳትታዘዝ ቀረች። ባልዋም እንደ እርስዋ የአምላክን ሕግ እንዲያፈርስ ለማድረግ ቻለች። (ዘፍጥረት 3:6) ዲያብሎስ ሰዎች ያለ አምላክ መኖር ይችላሉ ባይ ነበር። ሰዎች ያለ አምላክ እርዳታ ራሳቸውን በተሳካ ሁኔታ መግዛት ይችላሉ ብሎ ተከራከረ። ከዚህም በላይ ዲያብሎስ የአዳምና የሔዋን ዘሮች የሆኑትን ሁሉ ከአምላክ ዘወር ለማድረግ እችላለሁ አለ።
14.አምላክ ሰይጣንን ለምን ወዲያውኑ አላጠፋውም?
14 እርግጥ አምላክ ሰይጣንን ወዲያውኑ ሊያጠፋው ይችል ነበር። ሆኖም እንደዚያ ማድረጉ ሰይጣን ላስነሳቸው ጥያቄዎች መልስ አይሆንም። ደግሞም እነዚያ ጥያቄዎች ሁኔታዎቹን ይመለከቱ በነበሩት መላእክት አእምሮ ውስጥ እየተጉላሉ
ሊኖሩ ይችሉ ነበር። ስለዚህ ሰይጣን አባባሉን ለማረጋገጥ እንዲሞክር አምላክ ጊዜ ፈቀደለት። ውጤቱስ ምን ሆነ?15, 16. (ሀ) የዘመናት ማለፍ ስለ ሰይጣን አባባል ምን አረጋግጧል? (ለ) ምን ሁኔታ ቀርቧል?
15 ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ሰዎች ያለ አምላክ እርዳታ ራሳቸውን በተሳካ መንገድ ማስተዳደር እንደማይችሉ ተረጋገጠ። ሙከራዎቻቸው ሁሉ ፈጽመው ከሽፈዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች ከበስተኋላ ሆኖ ዲያብሎስ ይቆጣጠራቸዋል ብለው የሚናገሩላቸው የሰዎች መንግሥታት በሕዝቡ ላይ ብዙ ስቃይና መከራ አምጥተዋል። ከዚህም ሌላ አምላክ ጊዜ መስጠቱ ሰይጣን ሰዎችን ሁሉ አምላክን ከማገልገል ዘወር ለማድረግ እንዳልቻለ በግልጽ አሳይቷል። ለአምላክ አገዛዝ በታማኝነት የቆሙ አንዳንድ ሰዎች ምን ጊዜም ነበሩ። ለምሳሌ ኢዮብ አምላክን ማገልገሉን ለማስቆም ሰይጣን እንደሞከረና እንዳልተሳካለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማንበብ ትችላለህ።—ኢዮብ 1:6-12
16 ዲያብሎስ ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሐሰት እንደሆኑ በዚህ መንገድ ተረጋገጡ። በአምላክ ላይ ክፉ አመጽ በማስጀመሩ በእውነትም ሊጠፋ ይገባዋል። ደስ የሚለው ነገር አምላክ የሰይጣንን አገዛዝ በሚያቆምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የተወሰደውን የመጀመሪያውን እርምጃ ሲገልጽ በሰማይ አንድ ትልቅ ጦርነት መደረጉን ይናገራል። እርግጥ በምድር ያሉ ሰዎች ጦርነቱን ለማየት ወይም ለመስማት አልቻሉም። ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ በጥንቃቄ አንብብ፦
17. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ የተደረገውን ጦርነት እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል? (ለ) ጦርነቱ በሰማይ ላሉት ምን ውጤት አስከተለ? በምድር ባሉትስ ላይ?
17 “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና [ማለትም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስና]መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ራዕይ 12:7-9, 12
ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”—18. (ሀ) በሰማይ ጦርነት የተደረገው መቼ ነው? (ለ) ሰይጣን ወደ ምድር ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ምን ሲካሄድ ቆይቷል?
18 ይህ ጦርነት በሰማይ የተደረገው መቼ ነው? ማስረጃው በ1914 በተጀመረው አንደኛ የዓለም ጦርነት አካባቢ መደረጉን ያሳያል። ራዕዩ በግልጽ እንዳመለከተው በዚያን ጊዜ ሰይጣን ከሰማያት ተባረረ። ይህም ማለት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሰይጣን በቀረው “ጥቂት ዘመን“ ውስጥ እንኖራለን ማለት ነው። እንግዲያው አሁን ያለንባቸው ቀኖች የሰይጣን ዓለም “መጨረሻ ቀኖች“ ናቸው። እየጨመረ የሄደው ዓመጽ፣ ፍርሃት፣ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረት፣ በሽታዎችና በእኛ ላይ የደረሱት ሌሎች አስጨናቂ ሁኔታዎች የዚህ ማረጋገጫ ናቸው።—ማቴዎስ 24:3-12፤ ሉቃስ 21:26፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
19. (ሀ) ሰይጣን አሁን ምን ለማድረግ ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ነው? (ለ) ምን ማድረጋችን አስተዋይነት ነው?
19 ሰይጣን የቀረው “ጥቂት ዘመን“ ሊያከትም እንደሆነ ስለሚያውቅ ሰዎች አምላክን እንዳያገለግሉ ለማደናቀፍ ከመቼውም የበለጠ ይፍጨረጨራል። የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን አብሮ ወደ ጥፋት ሊወስድ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስን አንድን ሰው ለመብላት ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ አድርጎ መግለጹ በጥሩ ምክንያት ነው። (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) በእርሱ መዳፍ ውስጥ እንዳንገባ ከፈለግን እንዴት አድርጎ እንደሚያጠቃና ሰዎችን በምን መንገዶች እንደሚያሳስት ማወቅ ያስፈልገናል።—2 ቆሮንቶስ 2:11
ሰይጣን ሰዎችን እንዴት አድርጎ እንደሚያሳስት
20. (ሀ) የሰይጣን ጥቃት የቱን ያህል የተሳካ ውጤት አስገኝቷል? (ለ) ዘዴዎቹ ብዙ ጊዜ ምንም ተንኰል የሌለባቸው እንዲያውም ጠቃሚ መስለው ይታያሉ ብለን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?
20 ሰይጣን ሰዎች እንዲከተሉት ለማድረግ የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ሁልጊዜ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ብለህ አታስብ። ሰዎችን በማሞኘት በኩል የወጣለት ብልሃተኛ ነው። ባለፉት አያሌ ሺህ ዓመታት የተጠቀመባቸው ዘዴዎች በጣም መሠሪ ከመሆናቸው የተነሣ ዛሬ ብዙ ሰዎች ሰይጣን አለ ብለው እንኳን አያምኑም። በእነርሱ አስተሳሰብ ክፋትና ተንኰል ምን ጊዜም የሚኖሩ የተፈጥሮ ሁኔታዎች ናቸው። ሰይጣን የሚሠራው ልክ እንደ ዘመናዊ የወንጀል መሪዎች ነው። እነዚህ ሰዎች ከውጭ የሚከበሩ መስለው ይታዩና ከዚያ ከለላ በስተኋላ በጣም ክፉ 2 ቆሮንቶስ 11:14) እንግዲያው ሰዎችን ለማሳሳት የሚጠቀምባቸው የተንኰል ዘዴዎቹ ከውጭ ሲታዩ ምንም ተንኰል የሌለባቸው እንዲያውም ጠቃሚ እንደሚመስሉ ልንጠብቅ እንችላለን።
ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል” ሲል ይገልጽልናል። (21. ሰይጣን የተጠቀመበት አንዱ የተንኰል ዘዴ ምንድን ነው?
21 ሰይጣን ሔዋንን ወዳጅ መስሎ እንደቀረባት ትዝ ይበልህ። ከዚያም አታልሎ ይጠቅመኛል ብላ ያሰበችውን ነገር እንድትፈጽም አደረጋት። (ዘፍጥረት 3:4-6) ዛሬም የሚጠቀምበት ዘዴ ያው ነው። ለምሳሌ ሰይጣን በሰብዓዊ ተወካዮቹ እየተጠቀመ ሰዎች የሰብዓዊ መንግሥታትን ፍላጎት ከአምላክ አገልግሎት እንዲያስቀድሙ ያበረታታቸዋል። ይህም አስከፊ ጦርነቶችን ያስከተለውን የብሔራዊ ስሜትን መንፈስ እንዲወለድ አድርጓል። ሰዎች ሰላምንና ደህንነትን ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ ሰይጣን በቅርብ ዓመታት ልዩ ልዩ ዘዴዎችን እንዲፈጥሩ ገፋፍቷቸዋል። ከእነዚህ ዘዴዎች አንዱ የተባበሩት መንግሥታት ነው። ታዲያ ይህ ድርጅት ሰላማዊ ዓለም አስገኝቷልን? በፍጹም፤ የዓለም ሁኔታ ከዚያ የራቀ ነው! ከዚህ ይልቅ ድርጅቱ አምላክ ለሰዎች ሰላም ለማምጣት ከሚጠቀምበት ዝግጅት ይኸውም “በሰላሙ መስፍን“ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሚመራው ከመጪው የአምላክ መንግሥት ሐሳባቸውን ዘወር ለማድረግ እንደ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።—ኢሳይያስ 9:6፤ ማቴዎስ 6:9, 10
22. ሰይጣን ምን እውቀት እንድናገኝ አይፈልግም?
22 የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከፈለግን ስለ አምላክ፣ ንጉሥ ሆኖ ስለተሾመው ልጁና ስለ መንግሥቱ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልገናል። (ዮሐንስ 17:3) ሰይጣን ዲያብሎስ ይህንን እውቀት እንድታገኝ እንደማይፈልግና ለዚህ ሲል የተቻለውን ያህል እንደሚጥር እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ሰዎች እንዲያፌዙብህ በማድረግ ባንተ ላይ ተቃውሞ ማስነሳት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ ያደሩ ሆነው ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ ይሰደዳሉ” ብሎ ይነግረናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:12 አዓት
23. (ሀ) ሰይጣን እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ በወዳጆችና በዘመዶችም እንኳን እንዴት አድርጎ ሊጠቀም ይችላል? (ለ) በተቃውሞ ፈጽሞ መሸነፍ የሌለብህ ለምንድን ነው?
23 ምናልባት የቅርብ ወዳጆችህ ወይም ዘመዶችህ ቅዱሳን ጽሑፎችን መመርመርህን እንዳልወደዱት ይነግሩህ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” ሲል አስጠንቅቆናል። (ማቴዎስ 10:36, 37) ዘመዶችህ ተስፋ ሊያስቆርጡህ ይሞክሩ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አስደናቂ እውነቶች ስለማያውቁ ይህንን በሙሉ ቅንነት ያደርጉት ይሆናል። ነገር ግን ተቃውሞ ሲመጣብህ የአምላክን ቃል ማጥናትህን ብታቆም አምላክ እንዴት ይመለከትሃል? ከዚህም ሌላ አንተ ጥናቱን ካቆምህ እነዚያ ወዳጆችህና የምታፈቅራቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት ማግኘቱ የሕይወትና የሞት ጉዳይ መሆኑን እንዲያስተውሉ እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ? ከአምላክ ቃል በተማርካቸው ነገሮች መጽናትህ ውሎ አድሮ እነርሱንም እውነትን እንዲማሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
24. (ሀ) ሰዎች ሕይወት የሚሰጠውን እውቀት እንዳያገኙ ለማድረግ ሰይጣን በምን ሌሎች መንገዶች ይጠቀማል? (ለ) የአምላክን ቃል ማጥናቱ የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
24 በሌላው በኩል ግን ሰይጣን አምላክን የሚያስከፋ አንድ ዓይነት የጾታ ብልግና ለመፈጸም እንድትፈተን ሊያደርግ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ እንደሌለህ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ነገሩን ስታስብበት ይህን ዓይነቱን እውቀት ከማግኘት የሚበልጥ አንዳች ነገር ሊኖር ይችላልን? በምድር ላይ በገነት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያበቃህን ይህንን እውቀት እንዳታገኝ ምንም ነገር እንዲከለክልህ አትፍቀድለት!
25. ዲያብሎስን መቃወማችንን ከቀጠልንበት ምን ሊያደርገን አይችልም?
25 መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን ተቃወሙት” ሲል አጠንክሮ ያሳስበናል። ይህንን ካደረግህ ከአንተ ይሸሻል። (ያዕቆብ 4:7) ነገር ግን እንደዚህ ሲባል የሰይጣንን ጥቃት ከተቋቋምህ ከዚያ በኋላ እርሱ ይተውሃል ወይም ምንም ችግር አያመጣብህም ማለት ነውን? አይደለም፤ እርሱ የሚፈልገውን እንድታደርግለት ደጋግሞ ይሞክራል። ነገር ግን እርሱን መቃወምህን ከቀጠልክበት አምላክን የሚጻረር አካሄድ እንድትከተል ሊያደርግህ ከቶውንም አይችልም። እንግዲያው ከሁሉ የበለጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማግኘት ትጋ። የምትማረውንም በሥራ ላይ አውለው። ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት በሚጠቀምበት በሌላው ዘዴ ይኸውም በሐሰት ሃይማኖት ከመታለል እንድትጠበቅ ይህን ማድረግህ የግድ አስፈላጊ ነው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እነዚህ ሁሉ የዓለም መንግሥታት የራሱ ባይሆኑ ኖሮ ሰይጣን ለክርስቶስ ልስጥህ ብሎ ያቀርብለት ነበርን?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ ሌባ ሌባ ሆኖ እንዳልተወለደ ሁሉ ዲያብሎስም “ዲያብሎስ“ ሆኖ አልተፈጠረም
[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰማይ የተደረገው ጦርነት ሲፈጸም ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር ተጣሉ። አሁን አንተ የዚያ ውጤት እየነካህና እየተሰማህ ነው
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን እንዳትቀጥል ተቃውሞ ይነሳብህ ይሆናል