በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍርድ ቀንና ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ

የፍርድ ቀንና ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ

ምዕራፍ 21

የፍርድ ቀንና ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ

1. ስለ ፍርድ ቀን ሰዎች ያላቸው የተለመደ አስተያየት ምንድን ነው?

የፍርድ ቀን ሲባል በአእምሮህ ምን ይታይሃል? አንዳንዶች ከፊት ለፊቱ ከሞት የተነሡ ብዙ ሰዎች በሰልፍ የቆሙበት አንድ ታላቅ ዙፋን ይታያቸዋል። እያንዳንዱ ሰው በዙፋኑ ፊት በሚያልፍበት ጊዜ በቀድሞ ሥራዎቹ መሠረት ይፈረድበታል። ሰውየው ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በዳኛው መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ሲሆን በዚያ መሠረት ወደ ሰማይ ወይም ወደ እሳታማ ሲኦል ይላካል ተብሎ ይታሰባል።

2. (ሀ) የፍርድን ቀን ያዘጋጀው ማን ነው? (ለ) ዳኛ እንዲሆንለት የሾመውስ ማንን ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ ፍርድ ቀን ከዚህ በጣም የተለየ መግለጫ ይሰጣል። የፍርድ ቀን የሚያስርድ ወይም የሚያስፈራ ቀን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን እንደሚል ተመልከት:- “ቀን ቀጥሯልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው።” (ሥራ 17:31) ይህ በአምላክ የተሾመ ዳኛ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ የተረጋገጠ ነው።

3. (ሀ) ክርስቶስ አግባብ ያለው ፍርድ እንደሚሰጥ እርግጠኛ ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሰዎች የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ይሆናል?

3 ክርስቶስ አግባብ ባለው መንገድና በፍትሕ እንደሚፈርድ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። በኢሳይያስ 11:3, 4 ላይ ስለ እርሱ የተነገረ ትንቢት ይህንን ያረጋግጥልናል። ስለዚህ ነገሩ አብዛኛው ሰው ከሚያስበው ተቃራኒ ነው። ክርስቶስ ሰዎች በፊት በሠሯቸው ኃጢአቶች መሠረት አይፈርድባቸውም። ሰዎቹ ብዙዎቹን ድርጊቶች የፈፀሙት ባለማወቅ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ሲሞት ከሠራው ኃጢአት ሁሉ ነፃ እንደሚሆን ወይም እንደሚላቀቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። “የሞተ ከኃጢአት ኩነኔ ነፃ ሆኗል።” (ሮሜ 6:7 አዓት) ይህም ሲባል አንድ ሰው ከሞት ሲነሣ ፍርድ የሚሰጠው በፍርድ ቀን ውስጥ በሚሠራው ሥራ መሠረት እንጂ ከመሞቱ በፊት ባደረገው ነገር አይደለም ማለት ነው።

4. (ሀ) የፍርድ ቀን ምን ያህል ርዝመት ይኖረዋል? (ለ) ከክርስቶስ ጋር ዳኞች የሚሆኑት እነማን ናቸው?

4 ስለዚህ የፍርድ ቀን ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝመት ያለው ቀን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የፍርድ ሥራ በመሥራት ስለሚካፈሉት በሚናገርበት ጊዜ ይህንን ግልጽ ያደርገዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:1-3) አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ዙፋኖችንም አየሁ፣ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው” ብሏል። እነዚህ ዳኞች “ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የገለጻቸው የክርስቶስ ታማኝ ቅቡዓን ተከታዮች ናቸው። ስለዚህ የፍርድ ቀን የ1, 000 ዓመታት ርዝመት ይኖረዋል። ክርስቶስና 144, 000 ታማኝ ተከታዮቹ ‘በአዲስ ምድር’ ላይ እንደ “አዲስ ሰማያት” ሆነው የሚገዙበት የ1, 000 ዓመት ጊዜ ይህ ነው። — ራእይ 20:4, 6፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

5, 6. (ሀ) አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ የፍርድን ቀን እንዴት አድርጎ ገለጸው? (ለ) በፍርድ ቀን በምድር ላይ የሚኖረው ሕይወት ምን ዓይነት ይሆናል?

5 እነዚህን ገጾች ተመልከት። የፍርድ ቀን ለሰው ዘሮች ምን ያህል አስደሳች ጊዜ እንደሚሆን በትንሹ ያስረዳሉ። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ ስለዚያ ታላቅ ጊዜ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “በረሃ በእርሷም ያለ ሁሉ ሐሴትን ያድርጉ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ [በይሖዋ (አዓት)] ፊት ደስ ይላቸዋል፤ ይመጣልና፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፤ እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል።” — መዝሙር 96:12, 13

6 ከአርማጌዶን የሚተርፉት ሰዎች በፍርድ ቀን ምድርን ገነት ለማድረግ ይሠራሉ። ወደዚች ገነት ሙታን ተመልሰው ይመጣሉ፤ በደስታም እንቀበላቸዋለን። (ሉቃስ 23:43) ለብዙ ጊዜ በሞት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች እንደገና ሲገናኙ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል! አዎን፣ በሰላም መኖር፣ ጥሩ ጤንነት ማግኘትና ስለ አምላክ ዓላማዎች መማር ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! መጽሐፍ ቅዱስ “ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ” ይላል። (ኢሳይያስ 26:9) በፍርድ ቀን የምድር ሕዝቦች በሙሉ ስለ ይሖዋ ይማራሉ፤ እርሱን ለመታዘዝና ለማገልገልም ማንኛውም አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።

7. በፍርድ ቀን አምላክን ለማገልገል የሚመርጡትና እንደዚያ ለማድረግ እምቢ የሚሉት ምን ይሆናሉ?

7 ኢየሱስ ክርስቶስና 144, 000 ተባባሪ ነገሥታቱ ለሰው ዘር ፍርድ የሚሰጡት እንደነዚህ ባሉ ገነታዊ ሁኔታዎች ስር ነው። ይሖዋን ለማገልገል የሚመርጡ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ሁኔታዎቹ እንደዚህ ሆነው በተሻሻሉበት ጊዜ ላይም ቢሆን አንዳንዶች አምላክን ለማገልገል እምቢ ይላሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚናገሩት “ለኃጢአተኛ ሞገስ ቢደረግለት ጽድቅን አይማርም በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል።” (ኢሳይያስ 26:10) ስለዚህ እነዚህ ኃጢአተኞች መንገዳቸውን እንዲለውጡና ጽድቅን እንዲማሩ ሙሉ ዕድል ከተሰጣቸው በኋላ ይደመሰሳሉ። አንዳንዶቹም የፍርድ ቀን ከማለቁ በፊት ይገደላሉ። (ኢሳይያስ 65:20) በሕይወት ኖረው ገነቲቱን ምድር እንዲበጠብጡ ወይም እንዲያበላሹ አይፈቀድላቸውም።

8. የሰዶም ሰዎች ሥነ ምግባራዊ ሁኔታቸው እንዴት ነበር?

8 በታላቁ የይሖዋ የፍርድ ቀን ውስጥ በምድር ላይ ትንሣኤ ማግኘቱ በእውነቱ ታላቅ መብት ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው በዚህ መብት እንደማይጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል በጥንቷ የሰዶም ከተማ የነበሩትን ሰዎች እንውሰድ። የሶዶም ወንዶች ወደ ሎጥ በእንግድነት ከመጡት ወንዶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለማድረግ ጥረው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በተአምር እንዲታወሩ ቢደረግም የብልግና ጠባያቸው በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሳ በሎጥ እንግዶች ላይ የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም “ደጃፉን ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።”— ዘፍጥረት 19:4-11

9, 10. ክፉዎቹ የሰዶም ሰዎች ትንሣኤ ለማግኘት ስላላቸው ዕድል ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ያመለክታሉ?

9 እንደነዚህ ያሉ እጅግ በጣም ክፉ የሆኑ ሰዎች በፍርድ ቀን ትንሣኤ ያገኛሉን? እንደማይነሱ ግልጽ ማስረጃዎች መኖራቸውን ቅዱሳን ጽሑፎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ያህል በመንፈስ ተገፋፍተው ከጻፉት የኢየሱስ ደቀመዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ ከሰዎች ሴት ልጆች ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ሰማያዊ ቦታቸውን ትትው ስለመጡ መላእክት በመጀመሪያ ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እንዲሁም እንደነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።” (ይሁዳ 6, 7፤ ዘፍጥረት 6:1, 2) አዎን፤ የሰዶምና በዙሪያዋ የነበሩ ከተሞች ሰዎች እጅግ የበዛ የፆታ ብልግና በመፈፀማቸው ጠፉ፤ ሁኔታው እንደሚያሳየውም ትንሣኤ እንደማያገኙ መረዳት ይቻላል።— 2 ጴጥሮስ 2:4-6, 9, 10

10 ኢየሱስም የሰዶም ሰዎች ላይነሱ እንደሚችሉ አመልክቷል። ተአምራት ከፈጸመባቸው ከተሞች አንዷ ቅፍርናሆም ነበረች። ስለ እርሷ ሲናገር እንዲህ አለ:- “በአንቺ [በቅፍርናሆም] የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል።” (ማቴዎስ 11:22-24) ኢየሱስ እዚህ ላይ የቅፍርናሆምን ሰዎች ተነቃፊነት ለማጉላት ያዳምጡት በነበሩት እሥራኤላውያን አስተሳሰብ በፍርድ ቀን ፈጽሞ ትንሣኤ የማይገባቸው የጥንቶቹ የሰዶም ሰዎች ሁኔታ እንደሚቀል መናገሩ ነበር።

11. በፍርድ ቀን ከማንኛውም “ዓመፀኛ” ይልቅ ለ“ጻድቁ” የሚቀልለው ለምንድን ነው?

11 እንግዲያው ትንሣኤ የሚገባቸው ዓይነት ሰዎች ሆነን ለመገኘት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ‘የሙታን ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል ጽድቅን መማሩና ማድረጉ ከአንዳንዶቹ ይልቅ ለሌሎቹ ይከብድ ይሆንን?’ ብሎ መጠየቅ ይቻላል። እስቲ ነገሩን ከዚህ አንፃር ተመልከተው:- እንደ አብርሐም፣ ይስሐቅ፣ ኢዮብ፣ ዲቦራ፣ ሩትና ዳንኤል የመሳሰሉ “ጻድቅ” የሆኑ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት የመሲሑን መምጣት በተስፋ ሲጠባበቁ ነበር። በፍርድ ቀን ስለ እርሱ ሲማሩና በዚያን ጊዜ በሰማይ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ሲያውቁ እንዴት ይደሰቱ ይሆን! ስለዚህ በዚያን ጊዜ ጽድቅን ማድረጉ ከሞት ከሚነሱት “ዓመፀኞች” ይልቅ እንደነዚህ ላሉት “ጻድቃን” የቀለለ ይሆናል።— ሥራ 24:15

‘የሕይወት’ እና ‘የፍርድ’ ትንሣኤ

12. በዮሐንስ 5:28-30 መሠረት “የሕይወት ትንሣኤ” እና “የፍርድ ትንሣኤ” የሚያገኙት እነማን ናቸው?

12 ኢየሱስ በፍርድ ቀን የሚኖረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና . . . እንደሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።” (ዮሐንስ 5:28-30) ይህ “የሕይወት ትንሣኤ” እና “የፍርድ ትንሣኤ ” ምንድን ነው? እነዚህን ትንሣኤዎች የሚያገኙትስ እነማን ናቸው?

13. አንድ ሰው “የሕይወት ትንሣኤ” ያገኛል ሲባል ምን ማለት ነው?

13 ሙታን ከመቃብር ሲነሡ ባለፈው ሥራቸው መሠረት እንደማይፈረድባቸው ቀደም ብለን በግልጽ ተመልክተናል። ከዚያ ይልቅ በፍርድ ቀን በሚያደርጉት መሠረት ፍርድ ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ኢየሱስ “መልካምም ያደረጉ” እና “ክፉም ያደረጉ” ብሎ በጠቀሰ ጊዜ በፍርድ ቀን ውስጥ የሚያደርጓቸውን መልካም ነገሮችና ክፉ ነገሮች ማመልከቱ ነበር። ከሞት የሚነሡ ብዙ ሰዎች በሚያደርጓቸው መልካም ነገሮች ምክንያት ሁኔታቸው በየጊዜው እየተሻሻለ ይሄድና በሺው ዓመት የፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ። ስለዚህ በመጨረሻው ላይ ከኃጢአት ነፃ የሆነ ፍጹም ሕይወት ስለሚያገኙ ከሞት መነሣታቸው “የሕይወት ትንሣኤ” ይሆንላቸዋል።

14. አንድ ሰው “የፍርድ ትንሣኤ” ያገኛል ሲባል ምን ማለት ነው?

14 በሌላው በኩል ግን በፍርድ ቀን ውስጥ ‘ክፉ ወይም መጥፎ’ የሚያደርጉትስ ምን ይሆናሉ? ከሞት መመለሳቸው በመጨረሻው ላይ “የፍርድ ትንሣኤ” ይሆንባቸዋል። ይህስ ምን ማለት ነው? የሞት ፍርድ ወይም ቅጣት ማለት ይሆናል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በፍርድ ቀን ውስጥ ወይም በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ይጠፋሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት መጥፎ ስለሚሠሩ፣ ጽድቅን ለመማርና ለማድረግ እምቢተኞች ስለሚሆኑ ነው።

የፍርድ ቀን ሲጀምር

15. የፍርድ ቀን ከመጀመሩ በፊት ምን ይሆናል?

15 ሐዋርያው ዮሐንስ የፍርድ ቀን ሊጀምር ሲል በመጀመሪያ ምን እንደሚሆን በራዕይ ተመልክቶ ነበር። እንዲህ በማለት ጻፈ:- “ታላቅና ነጭ ዙፋን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ . . . ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ . . . ሙታንም [ተፈረደባቸው።”] (ራእይ 20:11,12) ስለዚህ የፍርድ ቀን ከመጀመሩ በፊት ምሳሌያዊ “ምድርንና ሰማይን” የሚያጠቃልለው የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ያልፋል። ክፉ የሆኑት ሰዎች ሁሉ በአርማጌዶን ሲጠፉ አምላክን የሚያገለግሉት ብቻ ይተርፋሉ። — 1 ዮሐንስ 2:17

16. (ሀ) በፍርድ ቀን ከሙታን ሌላ ፍርድ የሚሰጣቸው እነማን ይሆናሉ? (ለ) በምን መሠረት ፍርድ ይሰጣቸዋል?

16 ስለዚህ በፍርድ ቀን ውስጥ ለፍርድ የሚቀርቡት የተነሡት “ሙታን” ብቻ አይደሉም። ከአርማጌዶን የሚተርፉት “ሕያዋን” እንዲሁም ልጆቻቸው ጭምር ፍርድ ይሰጣቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1) ዮሐንስ በራእዩ ውስጥ እንዴት ፍርድ እንደሚሰጣቸው ተመልክቷል። እርሱም “መጽሐፍም ተከፈተ . . . ሙታንም በመጽሐፍ ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ” ሲል ጻፈ። — ራእይ 20:12, 13

17. “ለሕያዋን” እና “ለሙታን” ፍርድ ለመስጠት የሚያገለግሉት “መጻሕፍት” ምንድን ናቸው?

17 “ሙታንም” ሆኑ “ሕያዋን” ፍርድ የሚያገኙባቸው በዚያን ጊዜ የሚከፈቱት ‘መጻሕፍት’ ምንድን ናቸው? አሁን ባለን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ ሆነው የሚሰጡን መጻሕፍት እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። የይሖዋን ሕጎችና መመሪያዎች የያዙ በመንፈስ የተጻፉ ጽሑፎች ወይም መጻሕፍት ናቸው። በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በሙሉ እነዚህን በማንበብ የአምላክን ፈቃድ ለማወቅ ይችላሉ። በእነዚህ ‘መጻሕፍት’ ውስጥ በተሰጡት ሕጎችና መመሪያዎች መሠረት በምድር የሚኖሩ ሁሉ ፍርድ ይሰጣቸዋል። በእነዚህ ውስጥ የተጻፉትን ነገሮች የሚታዘዙ ሁሉ የክርስቶስን የቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች ይቀበላሉ፤ ቀስ በቀስም ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ።

18. (ሀ) በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ የሚኖረው ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) “ሙታን” በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ በሕይወት ኖሩ የተባለው በምን መንገድ ነው?

18 በ1, 000 ዓመት የፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ በምድር የሚኖር ማንኛውም ሰው በአዳም ኃጢአት ምክንያት ሟች አይሆንም። በእርግጥም በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ሙሉ በሙሉ ወደ ሕይወት መጥቷል ሊባል ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የቀሩቱ ሙታን ግን [ወደ ሰማይ ከሚሄዱት ከ144, 000ዎቹ ሌላ] ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም” ሲል የጠቀሰው ሐሳብ ይህ ነው። (ራእይ 20:5) እዚህ ላይ “የቀሩቱ ሙታን ግን” ተብሎ መጠቀሱ በ1, 000 ዓመት የፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ሌሎችም ይነሣሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰዎች በመጨረሻ ላይ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ስለሚደርሱ ወደ ሕይወት መጥተዋል ለማለት ስለሚቻል ነው። አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ እንደነበራቸው ዓይነት የፍጽምና ሁኔታ ይኖራቸዋል። ከዚያስ በኋላ ምን ይሆናል?

ከፍርድ ቀን በኋላ

19. በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ክርስቶስ ምን ያደርጋል?

19 ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንዲሠራው የሰጠውን ሥራ ሁሉ ካከናወነ በኋላ ‘መንግሥቱን ለአምላክ ለአባቱ አሳልፎ ይሰጣል።’ ይህም የሚሆነው በ1, 000 ዓመት የፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ነው። በዚያን ጊዜ ጠላቶች ሁሉ ጠፍተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ከአዳም የተወረሰው ሞት የመጨረሻው ይሆናል። እርሱም ይጠፋል! ከዚያ በኋላ መንግሥቱ የይሖዋ አምላክ ንብረት ይሆናል። እርሱም በቀጥታ እንደ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። — 1 ቆሮንቶስ 15:24-28

20. (ሀ) “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ስማቸው የሚጻፈውን ሰዎች ለመወሰን ይሖዋ ምን ያደርጋል? (ለ) በሰው ዘር ላይ የመጨረሻ ፈተና መምጣቱ ለምን ተገቢ ነው?

20 ይሖዋ ስማቸው “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ መጻፍ የሚኖርባቸውን ሰዎች የሚወስነው እንዴት ነው? (ራእይ 20:12, 15) በሰው ዘሮች ላይ በሚመጣ ፈተና አማካኝነት ይሆናል። እንደዚህ በመሰለው ፈተና አዳምና ሔዋን እንዴት እንደወደቁና ኢዮብ በተፈተነ ጊዜ እንዴት ፍጹም አቋሙን እንደጠበቀ አስታውስ። ይሁን እንጂ እስከ 1, 000 ዓመት መጨረሻ ድረስ በሕይወት የሚቆዩት አብዛኞቹ ሰዎች እምነታቸው አልተፈተነም። ከሞት ከመነሣታቸው በፊት የይሖዋ አምላክን ዓላማዎች አያውቁም ነበር። የሰይጣን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ክፍል በመሆን “ዓመፀኞች” ነበሩ። ትንሣኤ ካገኙ በኋላ ግን የዲያብሎስ ተቃውሞ በሌለበት በገነት ውስጥ ስለሚኖሩ ይሖዋን ማገልገሉ ቀላል ሆኖላቸዋል። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ፍጹም የሚሆኑት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰይጣን ይሖዋን ማገልገላቸውን ለማስቆም እንዲሞክር ዕድል ቢሰጠው በዚያው አቋማቸው ይቀጥሉ ይሆን? ሰይጣን ፍጹም የነበሩትን አዳምንና ሔዋንን እንዳስካደ እነርሱንም ሊያስክዳቸው ይችል ይሆን?

21. (ሀ) ይሖዋ የሰው ዘሮች እንዲፈተኑ የሚያደርገው እንዴት ነው? (ለ) ፈተናው ሲያበቃ በፈተናው ውስጥ የገቡት ሁሉ ምን ይሆናሉ?

21 ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማስገኘት ይሖዋ ሰይጣንንና አጋንንቱን ለ1, 000 ዓመት ታስረው ከነበሩበት ጥልቅ ይለቃቸዋል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? ሰይጣን አንዳንድ ሰዎችን ይሖዋን ከማገልገል ዘወር ለማድረግ እንደሚሞክርና እንደሚሳካለት መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። እነዚህም “እንደ ባሕር አሸዋ” ይሆናሉ፤ ማለትም ቁጥራቸው ያልተወሰነ ነው። ይህ ፈተና ከተፈጸመ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ እንዲሁም ፈተናውን የማያልፉት ሰዎች በምሳሌያዊው “የእሳት ባሕር” ውስጥ ይጣላሉ። ይህም ሁለተኛው (ዘላለማዊው) ሞት ማለት ነው። (ራእይ 20:7-10, 15) ስሞቻቸው “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ተጽፈው የሚገኙት ግን በክብራማዋ ምድራዊት ገነት ላይ ሕያው ሆነው ይቀራሉ። ስሞቻቸው “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ተጽፏል ሲባል ይሖዋ በልብ፣ በአእምሮና በአካል ፍጹም ናችሁ ብሎ ፈርዶላቸዋል፤ ስለዚህ በገነት ምድር ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ብቁ ናቸው ማለት ነው።

በዘመናችን የሚካሄደው የፍርድ ቀን

22. የፍርድን ቀንና የመጨረሻውን የሰው ዘር ፈተና በሕይወት ኖረን ለማየት በአሁኑ ጊዜ ከምን ማለፍ ያስፈልገናል?

22 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1, 000 ዓመታት ቀደም ብሎ ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን ያሳውቀናል። በተጨማሪም ወደፊት ስለሚሆነው ነገር የምንፈራበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ያሳያል። ሆኖም ጥያቄው ይሖዋ አምላክ ያዘጋጃቸውን መልካም ነገሮች አግኝተህ ለመደሰት አንተ በዚያ ትገኛለህን? የሚል ነው። ይህ ነገር የተመካው ከዚያ ቀደም ብሎ ያለውን የፍርድ ቀን ማለትም ‘አምላክን የማያመልኩ ሰዎች የሚጠፉበትን አሁን የሚካሄደውን የፍርድ ቀን’ በሕይወት በማለፍህ ላይ ነው። — 2 ጴጥሮስ 3:7

23. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በምን ሁለት ክፍሎች እየተለዩ ነው? (ለ) እያንዳንዱ ክፍል ምን ይሆናል? ለምንስ?

23 አዎን፣ ክርስቶስ ተመልሶ በሰማያዊ ዙፋን ላይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ዘር በሙሉ በፍርድ ላይ ነው። ይህ የአሁኑ “የፍርድ ቀን” መምጣት ያለበት የ1, 000 ዓመቱ የፍርድ ቀን ከመጀመሩ በፊት ነው። በአሁኑ የፍርድ ወቅት ላይ ሰዎች ፍየል በመሆን ከክርስቶስ በስተግራ በኩል ወይም በጎች በመሆን በቀኙ በኩል በመቆም እርስ በርሳቸው እየተለያዩ ነው። “ፍየሎቹ” የክርስቶስ ቅቡዓን “ወንድሞች” ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት ድጋፍ ስለማይሰጡ ይጠፋሉ። እነዚህ “ፍየሎች” ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች፣ ክፉዎች፣ በዐመፀኝነት ድርጊታቸው የደነደኑ መሆናቸውን ውሎ አድሮ የሚያሳዩ ሰዎች ናቸው። በሌላው በኩል ግን “በጎቹ” በሁሉም መንገድ የክርስቶስን “ወንድሞች” በመደገፋቸው ምክንያት በመንግሥቱ አገዛዝ ስር ሕይወት በማግኘት ይባረካሉ። — ማቴዎስ 25:31-46

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 178 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በፍርድ ቀን ለሰዶም ሰዎች ይቀልላቸዋል ሲል ምን ማለቱ ነበር?