በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሥላሴ የሚሰጠው ማብራሪያ ምን ዓይነት ነው?

ለሥላሴ የሚሰጠው ማብራሪያ ምን ዓይነት ነው?

ለሥላሴ የሚሰጠው ማብራሪያ ምን ዓይነት ነው?

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትላለች:- “ሥላሴ የክርስቲያን ሃይማኖትን ዋነኛ መሠረተ ትምህርት ለማመልከት የሚያገለግል ቃል ነው . . . ስለዚህ በአትናቴዎስ እምነት መሠረት ‘አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው፣ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ነው። ቢሆንም ግን ሦስት እግዚአብሔሮች የሉም አንድ እግዚአብሔር እንጂ።’ በሥላሴ ውስጥ . . . ሦስቱም አካላት ዘላለማዊና እኩል ናቸው። ሁሉም ያልተፈጠሩና ሁሉን ማድረግ የሚችሉ ናቸው።”—ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ

በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ለማለት ይቻላል፣ በዚህ ይስማማሉ። ለምሳሌ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥላሴን “መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት” ነው ትላለች። እንዲያውም “ክርስቲያኖች የሚባሉት ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን የሚቀበሉ ናቸው” ትላለች። ይህችው ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊው የክርስትና እምነታችን በተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብላለች:- “እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው . . . አብ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነው። ወልድ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነው። መንፈስ ቅዱስም ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነው።”

ስለዚህ ሥላሴ “ሦስት አካላት ያሉት አንድ እግዚአብሔር” እንደሆነ ይታሰባል። እያንዳንዱ አካል ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖርና መጀመሪያ የሌለው እንደሆነ ይነገራል። እያንዳንዱ አካል ሁሉን የሚችል እንደሆነና አንዱም ከሌሎቹ እንደማይበልጥና እንደማያንስ ይነገራል።

እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ለመረዳት ያስቸግራልን? ብዙ ቅን ልብ ያላቸው አማኞች ግራ የሚያጋባ፣ ከተለመደው የሰው ልጅ አስተሳሰብና ተሞክሮ የሚቃረን ሆኖ አግኝተውታል። አብ እግዚአብሔር ከሆነ፣ ወልድ እግዚአብሔር ከሆነና መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ከሆነ ሦስት እግዚአብሔሮች ሳይሆኑ አንድ እግዚአብሔር ብቻ የኖረው ለምንድን ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ።

“የሰው ሐሳብ ሊደርስበት ከሚችለው በላይ የሆነ”

ይህ ግራ መጋባት በጣም የተስፋፋ ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና የሥላሴ መሠረተ ትምህርት “የሰው ሐሳብ ሊደርስበት ከሚችለው በላይ የሆነ” ትምህርት ነው ተብሎ እንደሚታሰብ አመልክቷል።

የሥላሴን ትምህርት ከሚቀበሉት ሰዎች አብዛኞቹ ይህን የመሰለ አመለካከት አላቸው። ሞንሲኞር ኢዩጂን ክላርክ እንዲህ ይላሉ:- “እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው። በመላው ፍጥረት ውስጥ እንደዚህ ያለ ነገር ስለሌለ እንዲሁ እንቀበለዋለን እንጂ ልንረዳው አንችልም።” ካርዲናል ጆን ኦኮነር “ገና ያልተረዳነው በጣም ጥልቅ የሆነ ምሥጢር እንደሆነ እናውቃለን” ብለዋል። እንዲሁም ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ተመርምሮ ሊደረስበት የማይችለው የእግዚአብሔር ሥላሴነት ምሥጢር” ብለዋል።

ስለዚህ የሃይማኖታዊ እውቀት መዝገበ ቃላት (ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ሪሊጅየስ ኖውሌጅ ) የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በእርግጥ ስለ ትምህርቱ ምንነትም ሆነ ትምህርቱን እንዴት ማብራራት እንደሚቻል የሥላሴ አማኞች እርስ በርሳቸው አይስማሙም።”

በዚህም ምክንያት ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ለምን እንደሚከተለው እንዳለ ለመረዳት እንችላለን። “‘ታዲያ የሥላሴን እምነት እንዴት መስበክ ይቻላል?’ በሚል ጥያቄ ያልተፋጠጡ የሮማ ካቶሊክ የቀሳውስት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶችና (ሴሚናሪዎች) የሥላሴያዊ ሃይማኖት መምህራን ቢኖሩ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ጥያቄው የተማሪዎቹን ግራ መጋባት የሚያመለክት ቢሆንም መምህራኑም ቢሆኑ ከተማሪዎቹ ያላነሰ ግራ የተጋቡ መሆናቸውን ያመለክታል።”

የዚህን አባባል ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄዶ የሥላሴን እምነት የሚደግፉ መጻሕፍትን መመርመር ይቻላል። ስለ ሥላሴ ለማስረዳት ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ ገጾች ተጽፈዋል። ቢሆንም ተመራማሪዎች ግራ ከሚያጋቡ ሃይማኖታዊ ቃላትና ገለጻዎች ጋር ሲታገሉ ቆይተው ምንም የሚያረካ እውቀት ሳያገኙ ይመለሳሉ።

በዚህ በኩል ኢየሱሳዊው ጀስዊት ጆሴፍ ብራከን ዋት አር ዜይ ሴይንግ አባውት ትሪኒቲ? በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ የተገነዘቡትን አስፍረዋል:- “በብዙ ጥረት . . . በሃይማኖት ትምህርት ቤቶቻቸው ስለ ሥላሴ የተማሩ ቀሳውስት የሥላሴ በዓል በሚከበርበት ቀን እንኳን ለሕዝባቸው ስለ ሥላሴ ለማስተማር ያመነታሉ። ሊረዱ የማይችሉትን ነገር ለማስረዳት በመሞከር ለምን ሰዎችን ያስቸግሯቸዋል?” በተጨማሪም “ሥላሴ በተለምዶ ብቻ የሚታመን እምነት ነው። በዕለታዊው የክርስትና ሕይወትና አምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ በጣም አነስተኛ ነው” ብለዋል። ቢሆንም ሥላሴ የአብያተ ክርስቲያናት “መሠረታዊ ትምህርት” ነው!

የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት ሊቅ የሆኑት ሐንስ ኩንግ ክርስቲያኒቲ ኤንድ ዘ ወርልድ ሪሊጅንስ (ክርስትና እና የዓለም ሃይማኖቶች ) በተባለው መጽሐፋቸው አብያተ ክርስቲያናት ክርስቲያን ባልሆኑ ሕዝቦች ዘንድ ሃይማኖታቸውን ለማሰራጨት ያልቻሉበት አንዱ ምክንያት ሥላሴ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንዲህ ሲሉም አትተዋል:- “እስከ አሁን ድረስ አይሁዶች ሊጨብጡት አልቻሉም። ብዙ ጥናት ያደረጉ እስላሞችም እንኳን የሥላሴ አሳብ ሊገባቸው አልቻለም። . . . የሥላሴ ትምህርት በአንድ እግዚአብሔርና በሦስት ሕያው አካሎች [ሃይፖስቴሲስ] መካከል የሚያደርገውን ልዩነት ለመግለጽ ሲባል ከሲሪያክ፣ ከግሪክና ከላቲን ቋንቋዎች በተወረሱ ቃላት የሚቀርበው ሃይማኖታዊ ማብራሪያ ከማብራራት ይልቅ ግራ የሚያጋባ ነው። ለእስላሞች ተራ የቃላት ጨዋታ ይሆንባቸዋል። . . . እግዚአብሔር ልዩ፣ አቻ የሌለውና አንድ መሆኑን የሚበርዝ ወይም የሚያዳክም ትምህርት ለመጨመር ለምን ተፈለገ?”

“የሁከት አምላክ አይደለም”

እንዲህ ያለው የሚያበጣብጥ ትምህርት እንዴት ሊገኝ ቻለ? ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “እንዲህ ያለው ምሥጢራዊ የሆነ ሃይማኖታዊ ቀኖና መለኮት ራሱ የገለጠው መሆን ይኖርበታል።” የካቶሊክ ሃይማኖት ምሁራን የሆኑት ካርል ራህነርና ኸርበርት ቮርግሪምለር ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ (የሃይማኖት ትምህርት መዝገበ ቃላት ) በተባለው መጽሐፋቸው:- “ሥላሴ መለኮታዊ መግለጫ ካልተገኘ በስተቀር ሊታወቅ የማይችል . . . መለኮታዊ መግለጫ ከተገኘ በኋላ እንኳ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የማይቻል ፍጹም ምሥጢር ነው . . .” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የሥላሴ ትምህርት ይህን ያህል ግራ የሚያጋባ ትምህርት ስለሆነ አምላክ ራሱ ለሰዎች የገለጠው ትምህርት መሆን ይኖርበታል ብሎ ማሰብ ሌላ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። ለምን? ምክንያቱም አምላክ ራሱ የሰጠው ሌላ መግለጫ ስለ አምላክ ማንነት እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን አይፈቅድልንም። “እግዚአብሔር . . . የሁከት አምላክ አይደለም።”—1 ቆሮንቶስ 14:33

በዚህ አባባል መሠረት እግዚአብሔር የዕብራይስጥ፣ የግሪክና የላቲን ምሁራን እንኳ ሊያብራሩ የማይችሉትን የሚያበጣብጥ መሠረተ ትምህርት ሊያመነጭ ይችላልን?

ከዚህም በላይ ሰዎች ‘እውነተኛ አምላክ የሆነውንና የላከውን ኢየሱስን ለማወቅ እንዲችሉ’ የሃይማኖት ሊቃውንት መሆን ይኖርባቸዋልን? (ዮሐንስ 17:3) የሚኖርባቸው ከሆነስ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያወቁት የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ ምሁራን በጣም ጥቂት ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው? ከኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት መካከል ብዙዎቹ ዝቅተኛ ገበሬዎች፣ ዓሣ አጥማጆች፣ ቀራጮችና የቤት እመቤቶች ነበሩ። እነዚህ ተራ ሰዎች ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር ስላስተማራቸው ነገሮች እርግጠኞች ስለነበሩ ለሌሎች ሰዎች ለማስተማርና ለእምነታቸው ሲሉ ለመሞት እንኳን ፈቃደኞች ሆነው ነበር።—ማቴዎስ 15:1–9፤ 21:23–32, 43፤ 23:13–36፤ ዮሐንስ 7:45–49፤ ሥራ 4:13

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተራ ሰዎች ነበሩ እንጂ የሃይማኖት መሪዎች አልነበሩም