ልታምንበት ይገባሃልን?
ልታምንበት ይገባሃልን?
በሥላሴ ታምናለህን? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች አብዛኛዎቹ በሥላሴ ያምናሉ። ሥላሴ ለብዙ መቶ ዘመናት የአብያተ ክርስቲያናት ዋነኛ መሠረታዊ ትምህርት ሆኖ ቆይቷል።
ከዚህ በመነሳት ስለ ሥላሴ ምንም ዓይነት አጠያያቂ ሁኔታ ሊኖር አይችልም ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አጠያያቂ የሆኑ ነገሮች አሉ። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የሥላሴ እምነት ደጋፊዎች የነበሩ ሰዎች በዚህ እምነት ላይ የሚነሳውን ክርክር አፋፍመዋል።
እንዲህ ያለውን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ላዩን ብቻ ተመልክተን ማለፍ የማይገባን ለምንድን ነው? ኢየሱስ ራሱ “የዘላለም ሕይወትም፣ ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” ስላለ ነው። ስለዚህ ጠቅላላው የወደፊት ሕይወታችን የተመካው ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ባሕርይ በማወቅ ላይ ነው። ይህንንም ለማወቅ ስለ ሥላሴ የሚነሳውን ክርክር ከሥረ መሠረቱ መመርመር ይኖርብናል። አንተስ ይህን ጉዳይ ለምን አትመረምርም? — ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም
የተለያዩ የሥላሴ ጽንሰ ሐሳቦች አሉ። በአጠቃላይ ግን የሥላሴ ትምህርት በአንድ እግዚአብሔር የተጠቃለሉ ሦስት አካሎች ማለትም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንዳሉና ነገር ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት እንደሌሉ ይገልጻል። ይህ መሠረተ ትምህርት ሦስቱም እኩል ናቸው፣ ሁሉን ይችላሉ፣ ሁሉም ያልተፈጠሩና አንድ እግዚአብሔር ሆነው ከዘላለም እስከ ዘላለም ኗሪ ናቸው ይላል።
ይሁን እንጂ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የሥላሴ ትምህርት ሐሰት ነው፤ ሁሉን የሚችለው አምላክ የራሱ የተለየ ሕልውና ያለው፣ ዘላለማዊና አንዳች ነገር የማይሳነው አካል ነው ይላሉ። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት እንደ መላእክት በአምላክ የተፈጠረ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይኖር ስለነበረ መጀመሪያ ያለው መሆን ይኖርበታል ይላሉ። ኢየሱስ በምንም ዓይነት መንገድ ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር እኩል ሆኖ አያውቅም፤ ምንጊዜም ቢሆን የእግዚአብሔር ተገዢ ነበረ፤ አሁንም ነው በማለት ያስተምራሉ። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ አካል ሳይሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ማለትም የእግዚአብሔር አንቀሳቃሽ ኃይል ነው ብለው ያምናሉ።
የሥላሴ ትምህርት ደጋፊዎች ትምህርቱ በሃይማኖታዊ ወግ ላይ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስም ላይ የተመሠረተ ነው ይላሉ። ትምህርቱን የሚተቹ ሰዎች ግን ሥላሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም ይላሉ። እንዲያውም አንድ የታሪክ መጽሐፍ “[የሥላሴ] እምነት የመጣው ሙሉ በሙሉ ከአረማውያን ነው” ይላል። — ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቲያኒቲ (የክርስትናችን አረማዊነት )
ሥላሴ እውነት ከሆነ ኢየሱስ የአንድ አምላክ ሦስተኛ ክፍል አይደለም ወይም ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አልነበረም ማለት ኢየሱስን ማዋረድ ይሆናል። የሥላሴ ትምህርት ሐሰት ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር እኩያ አለው ማለት፣ ከዚያም አልፎ ማርያምን “የእግዚአብሔር እናት” ናት ማለት ሁሉን የሚችለውን አምላክ ማዋረድ ይሆናል። የሥላሴ ትምህርት ሐሰት ከሆነ ካቶሊክነት በተባለው መጽሐፍ እንደተገለጸው “[ሕዝቦች] ይህንን እምነት ሙሉ በሙሉና ሳያረክሱ ካልያዙ ያለ ጥርጥር ለዘላለም ይጠፋሉ። የካቶሊክም እምነት ይህ ነው:- አንድነት በሦስትነት ያለውን ሥላሴ የሆነ አንድ አምላክ እናመልካለን” ማለት ደግሞ እግዚአብሔርን ማዋረድ ይሆናል።
ስለዚህ ስለ ሥላሴ ትምህርት እውነቱን ለማወቅ የምትፈልግበት ጥሩ ምክንያቶች አሉ። ነገር ግን ትምህርቱ ከየት እንደተገኘና እውነተኛ ትምህርት መሆኑንና አለመሆኑን ከመመርመራችን በፊት የመሠረተ ትምህርቱን ፍቺ በግልጽ ማብራራት ጠቃሚ ይሆናል። ሥላሴ ምንድን ነው? የሥላሴ ደጋፊዎችስ ስለ ትምህርቱ ምን ማብራሪያ ይሰጣሉ?
ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በቀር ጥቅሶቹ ሁሉ በ1954 ከታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ናቸው
[በገጽ 2 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በስተግራ:- (ከዘአበ) በሁለተኛው መቶ ዘመን የተሠራ የግብፃውያን ቅርጽ። አሞን–ራ፣ ዳግማዊ ራምሰስና ሙት የተባሉ ሦስት ጣምራ አማልክት። በስተቀኝ:- (እዘአ) በአሥራ አራተኛው መቶ ዘመን የተቀረጸ የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ምስል። ሦስት አካላት ሆነው አራት እግር ብቻ ያላቸው መሆኑን አስተውል።