መንፈስ ቅዱስ—የእግዚአብሔር አንቀሳቃሽ ኃይል
መንፈስ ቅዱስ—የእግዚአብሔር አንቀሳቃሽ ኃይል
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንደሚለው ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል የሆነ አንድነት በሦስትነት ያለው አንድ አምላክ ሦስተኛ ክፍል ነው። አወር ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ፌዝ (ኦርቶዶክሳዊው የክርስትና እምነታችን) የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነው።”
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ “መንፈስ” ለማለት የሚያገለግለው ቃል ሩዋሕ ነው። የዚህም ቃል ትርጉሙ “ትንፋሽ፣ ነፋስ፣ መንፈስ” ማለት ነው። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ደግሞ ከዚህ የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቃል ፕኒውማ ነው። ታዲያ እነዚህ ቃላት መንፈስ ቅዱስ አንደኛው የሥላሴ ክፍል መሆኑን ያመለክታሉን?
አንቀሳቃሽ ኃይል
ይሖዋ የተለያዩ ዓላማዎችን ለመፈጸም የሚጠቀምበት ቁጥጥር የተደረገበት ኃይል “መንፈስ ቅዱስ” መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ቃል ከሚጠቀምበት ሁኔታ ለመረዳት እንችላለን። በመጠኑም ቢሆን የተለያዩ ተግባራትን ለመፈጸም በሚያስችል ሁኔታ ሊስተካከል ከሚችለው ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሊመሳሰል ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1:2 ላይ “የእግዚአብሔርም መንፈስ [አንቀሳቃሽ ኃይል አዓት (በዕብራይስጥ ሩዋሕ)] በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር” ይላል። እዚህ ላይ የእግዚአብሔር አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነው መንፈሱ ምድርን በማዘጋጀት ላይ ነበር።
እግዚአብሔር ለሚያገለግሉት ሰዎች ተጨማሪ ዕውቀት ለመስጠት መንፈሱን ይጠቀማል። ዳዊት “አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም [ሩዋሕ] [ቸር ነው አዓት]፤ በጽድቅ ምድር ይምራኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 143:10) ብቃት ያላቸው 70 ሰዎች ሙሴን እንዲረዱት በተሾሙ ጊዜ አምላክ እንዲህ ብሎት ነበር:- “በአንተ ካለው መንፈስ [ሩዋሕ] ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ።”—ዘኁልቁ 11:17
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጻፉት የአምላክ ሰዎች “በመንፈስ ቅዱስ [ፕኒውማ] ተነድተው” ነው። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት” ነው። “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቴኦፕኔዎስቶስ ሲሆን ትርጉሙም “አምላክ የተነፈሰው” ማለት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎች ራእይ ወይም ትንቢታዊ ሕልሞችን እንዲያዩ አስችሏቸዋል።—2 ሳሙኤል 23:2፤ ኢዩኤል 2:28, 29፤ ሉቃስ 1:67፤ ሥራ 1:16፤ 2:32, 33
መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ገፋፍቶታል። (ማርቆስ 1:12) መንፈሱ በእግዚአብሔር አገልጋዮች ውስጥ እንደ እሳት በመንደድ ልዩ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላቸው ነበር። በተጨማሪም አላንዳች ፍርሃትና በድፍረት እንዲናገሩ አስችሏቸዋል።—ሚክያስ 3:8፤ ሥራ 7:55–60፤ 18:25፤ ሮሜ 12:11፤ 1 ተሰሎንቄ 5:19
እግዚአብሔር ፍርዱን በሰዎችና በመንግሥታት ላይ የሚያስፈጽመው በመንፈሱ ነው። (ኢሳይያስ 30:27, 28፤ 59:18, 19) ከዚህም በላይ የአምላክ መንፈስ የትም ቦታ ሊደርስና በሰዎች ላይ የሚጠቅማቸውም ሆነ የሚጎዳቸው ነገር ሊፈጽም ይችላል።—መዝሙር 139:7–12
‘ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይል’
በተጨማሪም የእግዚአብሔር መንፈስ ለአገልጋዮቹ “ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይል” ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት) ይህም የእምነት ፈተናዎችን በትዕግሥት እንዲቋቋሙና በራሳቸው ኃይል ሊፈጽሟቸው የማይችሏቸውን ነገሮች እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል።
ለምሳሌ መሳፍንት 14:6 ስለ ሳምሶን እንዲህ ሲል ይተርካል:- “የያህዌህ መንፈስ ያዘው፣ ምንም ዓይነት መሣሪያ በእጁ ባይኖርም አንበሳውን ቆራረጠው።” (ጀሩሳሌም ባይብል) ሳምሶን ያን ያደረገውን ድርጊት እንዲፈጽም አንድ መለኮታዊ አካል ይዞት ነበርን? አልነበረም። “በድንገትም የእግዚአብሔር ኃይል ሳምሶንን አበረታው።”—የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የሰው መልክ ይዞ ሳይሆን በእርግብ አምሳል እንደወረደበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማርቆስ 1:10) ኢየሱስ በሽተኞችን እንዲፈውስና ሙታንን እንዲያስነሳ ያስቻለው ይህ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ነበር። ሉቃስ 5:17 እንደሚለው “ኢየሱስ በሽተኞችን የሚፈውስበት የእግዚአብሔር ኃይል ነበረው።”—የ1980 ትርጉም
በተጨማሪም የእግዚአብሔር መንፈስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተዓምራታዊ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ኃይል ሰጥቷቸው ነበር። ሥራ 2:1–4 በዓለ ኀምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበው እንዳሉ “ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፣ . . . በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር” ይላል።
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለኢየሱስና ለሌሎችም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ተራ ሰዎች ሊያደርጉ የማይችሏቸውን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ሰጥቷቸው ነበር።
ስብዕና ያለው አካል አይደለም
ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ ስብዕና እንዳለው አድርገው የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ አይደለምን? አዎን፣ አሉ። ይሁን እንጂ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሁር የሆኑት ኤድመንድ ፎርትማን ትርዩን ጎድ (አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ) መጽሐፋቸው ላይ ስለዚህ ጉዳይ የጻፉትን ልብ እንበል። “ይህ መንፈስ ብዙ ጊዜ የራሱ የሆነ ስብዕና እንዳለው በሚያመለክቱ ቃላት ቢገለጽም [የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች] ጸሐፊዎች ይህ መንፈስ የራሱ የሆነና የተለየ ስብዕና እንዳለው አምነው ወይም ገልጸው አያውቁም።”
ለአንድ ነገር ስብዕና መስጠት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያልተለመደ ነገር አይደለም። ጥበብ ልጆች እንዳሏት ተነግሯል። (ሉቃስ 7:35) ኃጢአትና ሞት እንደነገሡ ተገልጿል። (ሮሜ 5:14, 21) ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል (አዲሱ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ) በዘፍጥረት 4:7 ላይ “ኃጢአት በደጅ የሚያደባ አጋንንት ነው” በማለት ኃጢአት በቃየል ደጅ የሚያደባ ክፉ መንፈስ እንደሆነ በመግለጽ ኃጢአት መንፈሳዊ አካል እንደሆነ አድርጎ ገልጿል። ኃጢአት ግን መንፈሳዊ አካል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስም አካል እንደሆነ ወይም ስብዕና እንዳለው ሆኖ መገለጹ መንፈሳዊ አካል እንደሆነ አያመለክትም።
1 ዮሐንስ 5:6-8 ላይ “መንፈስ” ብቻ ሳይሆን “ውኃውና ደሙም” “ምሥክሮች” እንደሆኑ ተጽፏል። ውኃና ደም ግን የራሳቸው የሆነ ስብዕና ወይም አካል ያላቸው እንዳልሆኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም የራሱ የሆነ ስብዕና ወይም አካል የለውም።
በተመሳሳይምመጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ጋር በመስማማት “መንፈስ ቅዱስ” የሚለውን ቃል ከውኃና ከእሳት ጋር በማመሳሰል ስብዕና የሌለውን ነገር ለመግለጽ ይጠቀምበታል። (ማቴዎስ 3:11፤ ማርቆስ 1:8) ሰዎች ከወይን ጠጅ ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞሉ ተመክረዋል። (ኤፌሶን 5:18) እንደ ጥበብ፣ እምነትና ደስታ ባሉት ባሕርያት በተሞሉበት ዓይነት ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስም እንደተሞሉ ተነግሯል። (ሥራ 6:3፤ 11:24፤ 13:52) በ2 ቆሮንቶስ 6:6 ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች ባሕርያት አንዱ እንደሆነ ተደርጎ ተጠቅሷል። መንፈስ ቅዱስ ስብዕና ያለው አካል ቢሆን ኖሮ እንደነዚህ ያሉት አነጋገሮች በብዛት አይገኙም ነበር።
ከዚህም በላይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መንፈስ እንደሚናገር ቢገልጹም ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ መንፈስ የተናገረው በሰዎች ወይም በመላእክት አማካኝነት እንደሆነ ያመለክታሉ። (ማቴዎስ 10:19, 20፤ ሥራ 4:24, 25፤ 28:25፤ ዕብራውያን 2:2) በእነዚህ ጊዜያት የመንፈስ ሥራ ከአንድ ሰው ሩቅ ወደሚገኝ ሌላ ሰው መልዕክት የሚያስተላልፈው የሬዲዮ ሞገድ ከሚያከናውነው ሥራ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ማቴዎስ 28:19 ላይ “በመንፈስ ቅዱስ ስም” የሚል አነጋገር ይገኛል። ይሁን እንጂ ስም የሚለው ቃል በግሪክኛም ይሁን በአማርኛ ሁልጊዜ አንድን የተፀውኦ ስም አያመለክትም። “በሕግ ስም” ስንል አንድን የተፀውኦ ስም ያለው አካል ማመልከታችን አይደለም። ሕጉ የቆመለትን ዓላማና ሥልጣን ማመልከታችን ነው። የሮበርትሰን ወርድ ፒክቸር ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት (በአዲስ ኪዳን የሚገኝ ሥዕላዊ የቃላት አቀራረብ) እንዲህ ይላል:- “እዚህ ላይ ስም (ኦኖማ) የሚለው ቃል የተሠራበት አጠቃቀም ኃይልንና ሥልጣንን የሚያመለክትና በሴፕቱዋጀንትና በፓፒረስ ጽሑፎች ተዘውትሮ የሚሠራበት አጠቃቀም ነው።” ስለዚህ ‘በመንፈስ ቅዱስ ስም’ መጠመቅ ማለት የመንፈስን ሥልጣን ማወቅና መቀበል እንዲሁም ከእግዚአብሔር የመጣና በመለኮታዊ ፈቃድ የሚንቀሳቀስ መሆኑን መገንዘብ ማለት ነው።
“አጽናኝ” የሆነው
ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ “አጽናኝ” [ረዳት አዓት] እንደሆነና እንደሚያስተምር፣ እንደሚመራና እንደሚናገር ገልጿል። (ዮሐንስ 14:16, 26፤ 16:13) አጽናኝ [ረዳት አዓት] ለማለት የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ጰራቅሊጦስ በተባዕታይ ጾታ የተነገረ ቃል ነው። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ መንፈሱ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች በተናገረ ጊዜ በተባዕታይ ተውላጠ ስሞች ተጠቅሟል። (ዮሐንስ 16:7, 8) በሌላ ጊዜ ደግሞ መንፈስ (ፕኒውማ ) በግዑዝ ጾታ በሚነገርበት ጊዜ ተባዕታይም አነስታይም ባልሆነ ተውላጠ ስም ተጠርቷል።
አብዛኞቹ በሥላሴ የሚያምኑ ተርጓሚዎች ይህንን ሐቅ ይደብቃሉ። ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል (አዲሱ የአሜሪካ መጽሐፍ ቅዱስ) ይህንን በማመን ስለ ዮሐንስ 14:17 እንዲህ ይላል:- “‘መንፈስ’ የሚለው የግሪክኛ ቃል በግዑዝ ጾታ የተነገረ ነው። እኛ በእንግሊዝኛ ‘እርሱ፣ የእርሱ’ የሚሉትን ተውላጠ ስሞች እየሰጠን ብንተረጉመውም አብዛኞቹ የግሪክኛ በኩረ ጽሑፎች (ማኑስክሪፕትስ) ተባዕትም እንስትም መሆኑን በማያመለክቱ ግዑዝ ጾታ ባላቸው ተውላጠ ስሞች ይጠቀሙ ነበር።”
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ 16:7, 8 ላይ ጰራቅሊጦስ ለሚለው ቃል ስብዕና እንዳለው የሚያስመስል ተባዕታይ ጾታ የተጠቀመው ከሰዋስው ደንቦች ጋር ለመስማማት ነው እንጂ አንድን ዓይነት መሠረተ ትምህርት ለመግለጽ አልነበረም።
የሥላሴ ክፍል አይደለም
መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ሦስተኛ ክፍል ነው የሚለውን አስተሳሰብ እንደማይደግፍ ብዙ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ ያህል:-
ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሦስተኛ አካል እንዳለ በግልጽ የሚያመለክት ማስረጃ በየትኛውም ሥፍራ አናገኝም” ይላል።
የካቶሊክ የሃይማኖት ትምህርት ምሁር የሆኑት ፎርትማን:- “አይሁዳውያን መንፈስ አካል ወይም ስብዕና እንዳለው አምነው አያውቁም። ማንኛውም የብሉይ ኪዳን ጸሐፊ እንዲህ ያለ እምነት እንደነበረው የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት የተጨበጠ ማስረጃ አይገኝም። . . . መንፈስ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ በወንጌሎችና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ መለኮታዊ ኃይል እንደሆነ ተገልጿል።”
ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን መንፈስ ስብዕና እንዳለው አድርጎ እንደማይመለከት ግልጽ ነው። . . . በቀላል አነጋገር የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔር ኃይል ነው። አንዳንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተለየ እንደሆነ ተደርጎ ቢገለጽም ይህ የሆነው የያህዌህ እስትንፋስ በውጭ ሆኖ የሚሠራ ስለሆነ ነው።” በተጨማሪም እንዲህ ይላል:- “አብዛኛዎቹ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች የእግዚአብሔርን መንፈስ እንደ አንድ ነገር እንጂ እንደ አንድ ሕያው አካል አድርገው አይገልጹም። ይህንንም መንፈስና የእግዚአብሔር ኃይል ተመሳሳይ እንደሆኑ ከሚያመለክቱት መግለጫዎች በግልጽ ለመረዳት ይቻላል።”—በአይታሊክ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን።
ኤ ካቶሊክ ዲክሺነሪ (የካቶሊክ መዝገበ ቃላት):- “በአጠቃላይ አዲስ ኪዳንም እንደ ብሉይ ኪዳን መንፈስ መለኮታዊ ኃይል ወይም ጉልበት እንደሆነ አድርጎ ይናገራል።”
ስለዚህ አይሁዳውያንም ሆኑ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ አንደኛው የሥላሴ ክፍል እንደሆነ አያምኑም ነበር። ይህ ትምህርት የመጣው ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ
ነው። ኤ ካቶሊክ ዲክሺነሪ (የካቶሊክ መዝገበ ቃላት) እንዲህ ይላል:- “ሦስተኛ አካል እንዳለ የተነገረው በ362 በእስክንድርያ በተደረገው ጉባኤና . . . በመጨረሻ ደግሞ በ381 በቁስጥንጥንያ ተደርጎ በነበረው ጉባኤ ነበር።” ደቀ መዛሙርት በጰንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉ ከሦስት ተኩል መቶ ዘመናት በኋላ መሆኑ ነው።መንፈስ ቅዱስ ስብዕና ያለው አካል ስላልሆነ የሥላሴም ክፍል ሊሆን አይችልም። መንፈስ ቅዱስ አምላክ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀምበት አንቀሳቃሽ ኃይሉ ነው። እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ለማገልገል ዝግጁ ሆኖ የሚጠባበቅ ኃይል እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሆነ አካል አይደለም።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በአጠቃላይ አዲስ ኪዳንም እንደ ብሉይ ኪዳን መንፈስ መለኮታዊ ኃይል ወይም ጉልበት መሆኑን ያመለክታል።” —ኤ ካቶሊክ ዲክሽነሪ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንድ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል ታይቷል። በሌላ ጊዜ ደግሞ የእሳት ልሳን መስሎ ታይቷል። የሰው መልክ ይዞ የታየበት ጊዜ ግን ፈጽሞ የለም