በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኢየሱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኢየሱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኢየሱስ ምን ይላል?

ሰዎች ስለ ሥላሴ በቅድሚያ የሚያውቁት ነገር ሳይኖር መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ቢያነቡት ካነበቡት ነገር የሥላሴን ጽንሰ ሐሳብ ሊያገኙ ይችላሉን? በፍጹም አይችሉም።

ገለልተኛ ሆኖ የሚያነብ አንድ ሰው በጣም ግልጽ በሆነ ሁኔታ ሊረዳ የሚችለው እግዚአብሔር ሁሉን የሚችል፣ የሁሉ ፈጣሪና ከማንም ሌላ አካል የተለየ መሆኑንና ኢየሱስ ደግሞ ሰው ከመሆኑ በፊት እንኳን ከእግዚአብሔር የተለየ፣ የተፈጠረና የእግዚአብሔር የበታች መሆኑን ነው።

እግዚአብሔር አንድ እንጂ ሦስት አይደለም

እግዚአብሔር አንድ ነው የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሞኖቴይዝም ወይም አምላክ አንድ ነው የሚል እምነት ይባላል። የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤል ኤል ፔይን ያልተበረዘው የሞኖቴይዝም እምነት ከሥላሴ እምነት ጋር ፈጽሞ እንደማይስማማ ሲያመለክቱ እንዲህ ብለዋል:- “ብሉይ ኪዳን የአንድን አምላክ እምነት የሚያስተምር ወይም ሞኖቴይስቲክ ነው። እግዚአብሔር አንድ ነጠላ ሕልውና ያለው አምላክ ነው። በእግዚአብሔር ውስጥ ሥላሴ አለ የሚለው አስተሳሰብ . . . ፈጽሞ መሠረተ ቢስ ነው።”

ኢየሱስ ወደ መሬት ከመጣስ በኋላ አምላክ አንድ ነው በሚለው እምነት ላይ ወይም በሞኖቴይዝም ላይ ለውጥ ተደርጓልን? ፔይን እንዲህ ሲሉ መልስ ይሰጣሉ:- “በዚህ ጉዳይ ላይ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን መካከል ምንም ዓይነት ግጭት የለም። የሞኖቴይዝም ወይም አምላክ አንድ ነው የሚለው ትምህርት አልተሻረም። ኢየሱስ ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ጽሑፎች አይሁዳውያን በነበሩ ወላጆች የሠለጠነ አይሁዳዊ ነበር። ትምህርቱ ሙሉ በሙሉ አይሁዳዊ ነበር። በእርግጥ እርሱ የሰበከው አዲስ ወንጌል እንጂ አዲስ ሃይማኖት አልነበረም። . . . ‘እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ አምላክ ነው’ የሚለውን ታላቁን የአይሁድ አምላክ አንድ ነው የሚለውን እምነት ወይም የሞኖቴይዝም ጥቅስ እንደ ራሱ እምነት አድርጎ ተቀብሎ ነበር።”

እነዚህ ቃላት ዘዳግም 6:4 ላይ ይገኛሉ። የካቶሊኩ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል እንዲህ ይነበባል:- “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ አምላካችን ያህዌህ አንዱና ብቸኛው ያህዌህ ነው።” * በዚህ ጥቅስ ሰዋስዋዊ አገባብ መሠረት “አንዱ” የሚለው ቃል ከአንድ ነጠላ አካል የተለየ ሌላ ነገር ሊያመለክት እንደሚችል የሚያሳይ የብዙ ቁጥር አመልካች የለውም።

ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ እንኳ የእግዚአብሔር ምንነት መለወጡን አላመለከተም። “እግዚአብሔር ግን አንድ ነው” ሲል ጽፏል።—ገላትያ 3:20፤ በተጨማሪ 1 ቆሮንቶስ 8:4–6 ተመልከት።

በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት እግዚአብሔር አንድ ብቻ መሆኑ ተነግሯል። በሚናገርበትም ጊዜ እንደ አንድ ያልተከፋፈለ ግለኛ አካል ሆኖ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ የበለጠ ግልጽ ሊሆን አይችልም። አምላክ ራሱ እንደተናገረው:- “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው፣ የራሴንም ክብር ለማንም አልሰጥም።” (ኢሳይያስ 42:8 አዓት) “እኔ አምላክህ ያህዌህ ነኝ። . . . ከእኔ በስተቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።” (በአይታሊክ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን)—ዘጸአት 20:2, 3 የኢየሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

አምላክ ሦስት አካላት ያሉት ቢሆን ኖሮ በአምላክ መንፈስ ተነድተው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ጸሐፊዎች በሙሉ አምላክ አንድ እንደሆነ ለምን ይጽፉ ነበር? እንዲህ ብለው መጻፋቸውስ ሰዎችን ግራ ከማጋባት ሌላ ምን የሚፈይደው ነገር ይኖራል? በእርግጥ አምላክ የሦስት አካላት ጥምረት ቢሆን ኖሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት አጠራጣሪ ሁኔታ እንዳይኖር በማሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ደጋግመው በመጻፍ ግልጽ እንዲያደርጉት ያደርግ እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። ሌላው ቢቀር ከአምላክ ልጅ ጋር በግል ተገናኝተው የነበሩት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ግልጽ አድርገው ይጽፉ ነበር። ይሁን እንጂ ምንም የጻፉት ነገር የለም።

ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በግልጽ የጻፉት አምላክ አቻ የሌለው፣ የማይከፈል፣ ልዩ፣ ብቸኛና አንድ መሆኑን ነው። “እኔ ይሖዋ ነኝ፣ ሌላም የለም። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም” ብሏል። (ኢሳይያስ 45:5 አዓት ) “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ ብቻ በምድር ሁሉ ላይ የበላይ ነህ።”—መዝሙር 83:18 አዓት

ከአንድ የበለጠ ቁጥር ያለው አምላክ አይደለም

ኢየሱስ እግዚአብሔርን “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 17:3) ከአንድ የበለጡ አካላት ያሉት አምላክ እንደሆነ በሚያሳይ አጠራር ጠርቶት አያውቅም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማንኛውም ቦታ ላይ ከይሖዋ በስተቀር ሁሉን ቻይ ተብሎ የተጠራ ሌላ ማንም ያልኖረው በዚህ ምክንያት ነው። እንዲህ ባይሆን ኖር “ሁሉን ቻይ” የሚለው ቃል ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር። ከሁሉ በላይ የሆነው ይሖዋ ብቻ ስለሆነ ኢየሱስም ሆነ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ቻይ ተብለው ተጠርተው አያውቁም። ይሖዋ በዘፍጥረት 17:1 ላይ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ” ብሏል። በዘጸአት 18:11 ላይ ደግሞ “ይሖዋ ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጣል” ይላል።—አዓት

በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ኤሎህአህ (አምላክ) የተባለው ቃል ሁለት ዓይነት የብዙ ቁጥር አጠራሮች አሉት። እነርሱም ኤሎሂም (አምላኮች) እና ኤሎሄህ (የ . . . አምላኮች) ናቸው። እነዚህ ሁለት ቃላት በአጠቃላይ ይሖዋን የሚያመለክቱ ሲሆኑ እግዚአብሔር ወይም God (ጎድ) በሚለው ነጠላ ቁጥር ባለው ቃል ይተረጎማሉ። እነዚህ በብዙ ቁጥር የሚነገሩት ቃላት ሥላሴ መኖሩን ያመለክታሉን? በፍጹም አያመለክቱም። ዊልያም ስሚዝ ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ) በተባለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “[ኤሎሂም ] በአንድ አምላክ ውስጥ የሚገኙ ሥላሴያዊ አካላት መኖራቸውን ያመለክታል የሚለው የቅዠት አስተሳሰብ የምሁራንን ድጋፍ አላገኘም። የሰዋስው ሊቃውንት ግርማዊነትን የሚያመለክት ነው የሚሉት ወይም የመለኮታዊ ኃይልን ሙሉነትና አምላክ የሚያሳያቸውን ኃይሎች ጠቅላላ ድምር የሚያመለክት የብዙ ቁጥር ነው።”

ዘ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሴሚቲክ ላንጉጅስ ኤንድ ሊትረቸር (የአሜሪካ የሴማዊ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች መጽሔት ) ስለ ኤሎሂም እንዲህ ይላል:- “ይህን ቃል የሚከተለው ግሥ ሁልጊዜ ነጠላ ቁጥር ያለው ሲሆን ለዚህ ስም የሚያገለግለውም ገላጭ ቃል ነጠላ ቁጥር ነው።” ይህን አባባል በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ኤሎሂም የሚለው ቃል በፍጥረት ታሪክ ውስጥ ብቻ 35 ጊዜ ሲጠቀስ አምላክ ያደረገውንና የተናገረውን የሚገልጸው ግሥ በነጠላ ቁጥር የተነገረ ነው። (ዘፍጥረት 1:1 እስከ 2:4) በዚህ ምክንያት ይኸው መጽሐፍ ሐሳቡን ሲያጠቃልል “[ኤሎሂም ] ታላቅነትን ወይም ግርማዊነትን የሚያመለክት በብዙ ቁጥር የተነገረ ቃል መሆን ይኖርበታል” ይላል።

‘ኤሎሂም ’ “አማልክት” ማለት ነው እንጂ “አካላት” ማለት አይደለም። ስለዚህ ይህ ቃል ሥላሴ መኖሩን ያመለክታል ብለው የሚከራከሩ ሁሉ ራሳቸውን ከአንድ የበለጡ ብዙ አማልክት አምላኪዎች ያደርጋሉ። ለምን ቢባል በሥላሴ ውስጥ ሦስት አማልክት አሉ ማለት ስለሚሆን ነው። ሆኖም ግን የሥላሴ እምነት ደጋፊዎች በሙሉ በሥላሴ ውስጥ ሦስት የተለያዩ አማልክት አሉ የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉም።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ኤሎሂም” እና “ኤሎሄህ” የሚሉትን ቃላት የተለያዩ የሐሰት ጣዖት አማልክትን ለማመልከት ይጠቀምባቸዋል። (ዘጸአት 12:12፤ 20:23) ይሁን እንጂ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አንድን የሐሰት አምላክ ብቻ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ፍልስጥኤማውያን ‘አምላካችን ዳጎን’ ባሉ ጊዜ የተጠቀሙበት ቃል ኤሎሄህ ነው። (መሳፍንት 16:23, 24) በኣል “አምላክ [ኤሎሂም ]ተብሏል። (1 ነገሥት 18:27) በተጨማሪም ይህ ቃል ሰዎችን ለማመልከት አገልግሏል። (መዝሙር 82:1, 6) ሙሴ ለአሮንና ለፈርኦን እንደ “አምላክ” [ኤሎሂም ] ሆኖ እንዲያገለግል ተነግሮታል።—ዘጸአት 4:16፤ 7:1

ስለዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኤሎሂም እና ኤሎሄህ የሚሉት ቃላት ለሐሰት አማልክትና ለሰዎች ጭምር ማገልገሉ እነዚህ አማልክት ከአንድ የበለጡ መሆናቸውን እንዳላመለከተ ሁሉ ይሖዋ ኤሎሂም ወይም ኤሎሄህ መባሉ፣ በተለይ የቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለዚህ ጉዳይ ከሚሰጠው ምሥክርነት ጋር ስናገናዝብ፣ ከአንድ የበለጠ አካል ያለው መሆኑን ሊያመለክት አይችልም።

ኢየሱስ የተለየ ፍጡር ነው

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ፍጹም ሰው ነበር። ይህም ሊሆን የቻለው የኢየሱስን የሕይወት ኃይል ወደ ማርያም ማህፀን ያስተላለፈው አምላክ ስለሆነ ነው። (ማቴዎስ 1:18–25) ይሁን እንጂ በሕይወት መኖር የጀመረው በምድር ላይ አይደለም። እርሱ ራሱ ‘ከሰማይ እንደወረደ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) ስለዚህ ቆየት ብሎ ለተከታዮቹ “የሰው ልጅ [ኢየሱስ] ወደነበረበት ተመልሶ ሲወጣ ስታዩ ምን ልትሉ ነው?” ማለቱ እንግዳ ነገር አይሆንም።—ዮሐንስ 6:62 የ1980 ትርጉም

ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ በሰማይ ይኖር የነበረው ሦስትነት በአንድነት ያለው ሁሉን የሚችል ዘላለማዊ አምላክ ሦስተኛ ክፍል ሆኖ ነበርን? አልነበረም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ልክ እንደ መላእክት በአምላክ የተፈጠረ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይኖር እንደነበረ በግልጽ ይናገራል። መላእክትም ሆኑ ኢየሱስ ከመፈጠራቸው በፊት ምንም ዓይነት ሕልውና አልነበራቸውም።

ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ‘የፍጥረት ሁሉ በኩር’ ነበር። (ቆላስይስ 1:15) በተጨማሪም “በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ” ነው። (ራእይ 3:14) “መጀመሪያ” [በግሪከኛ አርክሄ] የሚለው ቃል ኢየሱስ የአምላክ ፍጥረታት ጀማሪ እንደነበረ ያመለክታል የሚል ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ዮሐንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሆኑትን መጻሕፍት በሚጽፍበት ጊዜ ከ20 ለሚበልጡ ጊዜያት አርክሄ በተባለው የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። ለዚህ ቃል የተሰጠው ትርጉም “መጀመሪያ” የሚል ነው። አዎን፣ ኢየሱስ የማይታዩት የአምላክ ፍጥረታት መጀመሪያ ሆኖ የተፈጠረ የይሖዋ ፍጡር ነው።

እነዚህ ስለ ኢየሱስ መገኘት የሚገልጹት ጥቅሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ምሳሌያዊ የሆነችው “ጥበብ” ስለ ራስዋ ከምትናገረው ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ልብ በል። “እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፣ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፣ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር።” (ምሳሌ 8:12, 22, 25, 26) “ጥበብ” የሚለው ቃል አምላክ የፈጠረውን አንድ አካል ለማመልከት ቢያገለግልም አብዛኞቹ ምሁራን ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር የነበረበትን ጊዜ የሚያመለክት ፈሊጣዊ አነጋገር እንደሆነ ይስማማሉ።

ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕይወቱ እንደ “ጥበብ” ሆኖ፣ “በእርሱ [በአምላክ] ዘንድ ዋና ሠራተኛ” እንደነበር ይናገራል። (ምሳሌ 8:30) ቆላስይስ 1:16 ኢየሱስ የአምላክ “ዋና ሠራተኛ” በመሆን ስለፈጸመው የሥራ ድርሻ ሲገልጽ “እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው” ይላል።—የ1980 ትርጉም

ስለዚህ ሁሉን የሚችለው አምላክ ሁሉንም ሌሎች ነገሮች የፈጠረው የበታቹ ሆኖ የሥራ ተካፋዩ በነበረው በዚህ ዋና ሠራተኛ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳዩን እንዲህ ሲል በአጭሩ ያጠቃልለዋል:- “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ . . . አንድ አምላክ አብ አለን፤ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ . . . አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።”1 ቆሮንቶስ 8:6 (በአይታሊክ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን።)

እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን . . . እንፍጠር” ያለው ለዚህ ዋና ሠራተኛ እንደነበረ አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 1:26) አንዳንዶች እግዚአብሔር “በመልካችን” እና “እንፍጠር” ማለቱ እርሱ ሥላሴ እንደሆነ ያመለክታል ይላሉ። ነገር ግን አንተ ‘አንድ ነገር እንሥራ’ ብትል ይህን አነጋገርህን በውስጥህ ብዙ ሰዎች ተዋህደው ይገኛሉ ብሎ የሚረዳ ሰው አይኖርም። ሁለት ወይም ከሁለት የበለጡ ሰዎች አብረውህ እንዲሠሩ መጠየቅህን ብቻ ያመለክታል። ስለዚህ አምላክ ‘በመልካችን እንፍጠር’ ባለ ጊዜ የመጀመሪያ መንፈሣዊ ፍጡርና ዋና ሠራተኛ የነበረውን ኢየሱስን ማነጋገሩ ነበር።

እግዚአብሔር ሊፈተን ይችላልን?

ማቴዎስ 4:1 ኢየሱስ ‘በዲያብሎስ እንደተፈተነ’ ይናገራል። ሰይጣን “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም” ለኢየሱስ ካሳየ በኋላ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። (ማቴዎስ 4:8, 9) ሰይጣን ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ለማጓደል መሞከሩ ነበር።

ኢየሱስ እግዚአብሔር ከነበረ ግን ይህ የቀረበለት ፈተና ምን ዓይነት የታማኝነት ፈተና ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔር በራሱ ላይ ሊያምጽ ይችላልን? አይችልም። በእግዚአብሔር ላይ ሊያምፁ የሚችሉት መላእክትና ሰዎች ናቸው። ያመፁበትም ጊዜ ነበር። ለኢየሱስ የቀረበው ፈተና ትርጉም ሊኖረው የሚችለው፣ እሱ እግዚአብሔር ቢሆን ሳይሆን የራሱ ነፃ ፈቃድ ያለው፣ ቢፈልግ ታማኝነቱን ሊያጎድል የሚችል የተለየ ግለሰብ ወይም መልአክ ቢሆን ነው።

በሌላም በኩል እግዚአብሔር ኃጢአት ሊሠራና ራሱ ራሱን ሊክድ ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። እርሱ “ሥራው ፍጹም ነው . . . የታመነ አምላክ . . . እርሱ ጻድቅና ቅን ነው።” (ዘዳግም 32:4 አዓት ) ስለዚህ ኢየሱስ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ ሊፈተን አይችልም ነበር።—ያዕቆብ 1:13

ኢየሱስ እግዚአብሔር ስላልነበረ ታማኝነቱን ሊያጐድል ይችል ነበር። እርሱ ግን “ሂድ፣ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ [ለይሖዋ አዓት] ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት ታማኝነቱን ጠብቋል።—ማቴዎስ 4:10

የቤዛው ዋጋ ምን ያህል ነበር?

የሱስ ወደ መሬት ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ የሥላሴን ትምህርት በቀጥታ የሚቃረን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ [ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ አዓት] ሰጠ።”—1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6

ኢየሱስ ከፍጹም ሰው የማይበልጥም የማያንስም ፍጡር በመሆኑ አዳም ያጣውን ፍጹም ሰብዓዊ ምድራዊ ሕይወት በትክክል የሚተካ ቤዛ ሆኗል። ስለዚህ ኢየሱስ በሐዋርያው ጳውሎስ “የኋለኛው (የመጨረሻው አዓት) አዳም” ተብሎ ሊጠራ ችሏል። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚሁ ጉዳይ ሲጽፍ “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:22, 45) ፍጹም የሆነው የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት መለኰታዊ ፍትሕ የሚጠይቀውን “[ተመጣጣኝ] ቤዛ” ሳይበዛም ሳያንስም በትክክል የሚያሟላ ነበር። የሰው ልጆች የፍትሕ ሥርዓት እንኳን የሚከፈለው ዋጋ ከተሠራው ጥፋት ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ይጠይቃል።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንደኛ ክፍል ቢሆን ኖሮ ግን የተከፈለው ቤዛ የአምላክ ሕግ ከሚጠይቀው እጅግ በጣም የበለጠ ይሆናል። (ዘጸአት 21:23–25፤ ዘሌዋውያን 24:19–21) በኤደን ውስጥ ኃጢአት የሠራው ፍጹም የነበረው ሰው አዳም እንጂ እግዚአብሔር አልነበረም። ስለዚህ የሚከፈለው ቤዛ ከእግዚአብሔር የፍትሕ ሥርዓት ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከአዳም ሕይወት ጋር የሚተካከል መሆን አለበት። ፍጹም የሆነ ሰው ማለትም “የኋለኛው አዳም” ሕይወት መከፈል ይኖርበታል። በዚህ መሠረት አምላክ ኢየሱስን ቤዛ እንዲሆን ወደ ምድር በላከው ጊዜ ትክክለኛ ፍትሕ በሚጠይቀው መሠረት ‘ከመላእክት ያነሰ’ ፍጹም ሰው አደረገው እንጂ ሥጋ የለበሰ አምላክ ወይም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው አላደረገውም። (ዕብራውያን 2:9፤ ከመዝሙር 8:5, 6 ጋር አወዳድር።) አንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ክፍል የሆነ አብ፣ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ እንዴት ከመላእክት ያነሰ ሊሆን ይችላል?

“አንድያ ልጅ” ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር “አንድያ ልጅ” እንደሆነ ይናገራል። (ዮሐንስ 1:14፤ 3:16, 18፤ 1 ዮሐንስ 4:9) የሥላሴ እምነት ተከታዮች እግዚአብሔር ዘላለማዊ ስለሆነ የእግዚአብሔር ልጅም ዘላለማዊ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ እንዴት ከአባቱ ጋር በዕድሜ እኩል ሊሆን ይችላል?

የሥላሴ እምነት ተከታዮች “አንድያ ልጅ” የሚለው ቃል “መውለድን ወይም በአባትነት መፍጠርን” አያመለክትም ይላሉ። (ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ ) ኢየሱስን በሚመለከት “አንድያ ልጅ” መሆን ማለት “ወደ ሕልውና የማምጣትን ዝምድና የማያመለክት” መወለድ የሌለበት ልዩ የሆነ የአባትና የልጅ ዝምድና ነው ይላሉ። (ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታሜንት ወርድስ ) ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አባባል ምክንያታዊ ነውን? አንድ ሰው ላልወለደው ልጁ አባት ሊሆን ይችላልን?

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይስሐቅ ከአብርሃም ጋር የነበረውን ዝምድና ሲገልጽ “አንድያ ልጅ” የሚለውን የግሪክኛ ቃል የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ቫይንም ምንም ማብራሪያ ሳይሰጥ ይህን አምኗል።) ዕብራውያን 11:17 ይስሐቅ የአብርሃም ‘አንድያ ልጅ’ እንደነበረ ይናገራል። ይስሐቅ በተለመደው መንገድ የተወለደና በዕድሜውም ሆነ በማዕረጉ ከአባቱ ጋር እኩል ያልሆነ አንድያ ልጅ እንደነበረ አያጠራጥርም።

ኢየሱስና ይስሐቅ “አንድያ ልጅ” መሆናቸውን የሚገልጸው የግሪክኛ ቃል ሞኖጄኔስ ነው። ይህም ቃል “አንድያ፣ ብቸኛ” የሚል ትርጉም ያለውን ሞኖስ የተባለ ቃልና “ወደ ሕልውና ማምጣት፣ ማብቀል፣ ማስገኘት” የሚል ትርጉም ያለውን ጂኖማይ የተባለ ቃል በማጣመር የተገኘ ቃል ነው። ስለዚህ ሞኖጄኔስ “ብቻውን የተወለደ፣ አንድያ ልጅ (አንድ ብቻውን እንደተወለደ ልጅ)” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል።—ኤ ግሪክ ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክስኮን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (የአዲስ ኪዳን የግሪክኛና የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ) በኢ ሮቢንሰን የተጻፈ

በጌርሃርድ ኪተል የተዘጋጀው ቴዎሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (የአዲስ ኪዳን ሃይማኖታዊ መዝገበ ቃላት ) እንዲህ ይላል:- “[ሞኖጄኔስ] ወንድሞችና እህቶች ሳይኖሩ ‘ብቸኛ ልጅ’ ሆኖ መወለድ ማለት ነው።” በተጨማሪም ይህ መጽሐፍ ዮሐንስ 1:18፤ 3:16, 18፤ እና 1 ዮሐንስ 4:9 ላይ “የተገለጸው የኢየሱስ ዝምድና አንድያ ልጅ ከአባቱ ጋር ያለው ዝምድና ብቻ ሳይሆን አንድ ብቻውን የተወለደ ልጅ ከአባቱ ጋር ያለው ዝምድና ነው” በማለት ይገልጻል።

ስለዚህ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ለሕይወቱ መጀመሪያ ነበረው። ሁሉን የሚችለው አምላክም እንደ እነ አብርሃምና ሌሎች ምድራዊ አባቶች አባት ወይም ወላጅ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። (ዕብራውያን 11:17) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የኢየሱስ አባት እንደሆነ በሚናገርበት ጊዜ ስለ ሁለት የተለያዩ አካላት መናገሩ ነው። እግዚአብሔር የበላይ ሲሆን ኢየሱስ ደግሞ በዘመን፣ በማዕረግ፣ በኃይልና በእውቀት የበታች ነው።

በሰማይ የተፈጠረው የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ኢየሱስ ብቻ አለመሆኑን ስንመለከት ኢየሱስ “አንድያ ልጅ” ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ብዙ መንፈሳዊ ፍጥረቶች ወይም መላእክት የሕይወት ኃይል ያገኙት የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ስለሆነ “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለው ተጠርተዋል። አዳምም የእግዚአብሔር ልጅ ተብሏል። (ኢዮብ 38:7፤ መዝሙር 36:9፤ ሉቃስ 3:38) ይሁን እንጂ እነዚህ ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩት በቀጥታ በአምላክ ለመፈጠር ብቸኛ በሆነው “በአንድያ ልጁ” በኩል ነው።—ቆላስይስ 1:15–17

ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበርን?

ኢየሱስ ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ የተጠራ ቢሆንም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስን እግዚአብሔር ወልድ ነው ብሎ የሚያስብ ሰው አልነበረም። “እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ . . . ያምናሉ” የተባሉት አጋንንት እንኳ በመንፈሳዊው ዓለም ከነበራቸው ተሞክሮ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንዳልነበረ አውቀው ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስን “የእግዚአብሔር ልጅ” ብለው በመጥራት የራሱ የሆነ የተለየ ሕልውና እንዳለው ገልጸዋል። (ያዕቆብ 2:19፤ ማቴዎስ 8:29) ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ባጠገቡ ቆመው የነበሩት አረማውያን የሮማ ወታደሮች እንኳ ከተከታዮቹ እንደሰሙት ኢየሱስ እግዚአብሔር ሳይሆን “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ” ብለው ለመናገር ችለው ነበር።—ማቴዎስ 27:54

ስለዚህ “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው ኢየሱስ የተፈጠረ የተለየ አካል መሆኑን ነው እንጂ የሥላሴ ክፍል መሆኑን አይደለም። የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑም እግዚአብሔርን ሊሆን አይችልም። ዮሐንስ 1:18 “እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም” ይላል።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ኢየሱስ “በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛ” እንደሆነ እንጂ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አያምኑም ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 2:5) መካከለኛ የሆነ ሰው መካከለኛ ወይም አስታራቂ ከሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተለየ መሆን ስለሚኖርበት ኢየሱስ ሊያስታርቅ ከሚፈልጋቸው ሁለት ወገኖች የአንዱ ክፍል ሊሆን አይችልም። እንዲህ ቢሆን ያልሆነውን ለመሆን የፈለገ ያስመስልበታል።

እግዚአብሔር ከኢየሱስ ጋር ስላለው ዝምድና መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መግለጫ ግልጽና እርስ በርሱ የማይጋጭ ነው። ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው። እርሱም ኢየሱስን ሰው ከመሆኑ በፊት ፈጥሮታል። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ መጀመሪያ የነበረው ስለሆነ በኃይልም ሆነ በዘላለማዊነት ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ሊሆን አይችልም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 የአምላክ ስም በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ያህዌህ” ሲባል በሌሎች ትርጉሞች ደግሞ “ይሖዋ” ተብሏል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ በእግዚአብሔር የተፈጠረ በመሆኑ በዘመን፣ በኃይልና በእውቀት ዝቅ ያለና ሁለተኛ ደረጃ ያለው ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ይኖር እንደነበረ ተናግሯል፤ ከማይታዩት የእግዚአብሔር ፍጡሮች የመጀመሪያ ሆኖ በእግዚአብሔር ተፈጥሯል