በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር የኢየሱስ የበላይ ነበርን?

ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር የኢየሱስ የበላይ ነበርን?

ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር የኢየሱስ የበላይ ነበርን?

ኢየሱስ እግዚአብሔር ነኝ ያለበት ጊዜ የለም። ስለ ራሱ የተናገራቸው ቃላት ሁሉ በማንኛውም መንገድ፣ በኃይልም ሆነ በእውቀት ወይም በዕድሜ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንዳላደረገ የሚያመለክቱ ናቸው።

ንግግሩም ሆነ ምግባሩ በሕይወት በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ በሰማያትም ሆነ በምድር ላይ፣ የእግዚአብሔር ተገዥና የበታች መሆኑን ያመለክታል። ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር የበላይ ኢየሱስ የበታች ነው።

ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተለየ ነበር

ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከእግዚአብሔር የተለየ ፍጡር መሆኑን፣ ከበላዩ የሚያመልከውና “አባት” ብሎ የሚጠራው አምላክ ያለው መሆኑን ገልጿል። ወደ እግዚአብሔር ማለትም ወደ አብ በጸለየበት ጊዜም አባቱን “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንክ” ብሎታል። (ዮሐንስ 17:3) ዮሐንስ 20:17 ላይ ለመግደላዊት ማርያም እንዲህ ብሏታል:- “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ።” ሐዋርያው ጳውሎስም 2 ቆሮንቶስ 1:3 ላይ ይህንን የሁለቱን ዝምድና “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” በማለት ያረጋግጣል። ኢየሱስ አባቱ የሆነ አምላክ ስለነበረው ራሱ ተመልሶ ያንን አምላክ ሊሆን አይችልም ነበር።

ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስና እግዚአብሔር የተለያዩ መሆናቸውን ሲገልጽ ምንም ዓይነት ቅሬታ አልተሰማውም ነበር። “ለእኛስ . . . አንድ አምላክ አብ አለን . . . አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” (1 ቆሮንቶስ 8:6) ሐዋርያው እግዚአብሔርና ኢየሱስ የተለያዩ መሆናቸውን ሲገልጽ “በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:21) ጳውሎስ ኢየሱስና መላእክት የተለያዩ መሆናቸውን እንደገለጸ ሁሉ ኢየሱስና እግዚአብሔርም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው።

በዮሐንስ 8:17, 18 የሚገኙት የኢየሱስ ቃላትም ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። እንዲህ ይላል:- “የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደሆነ በሕጋችሁ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፣ የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” እዚህ ላይ ኢየሱስ እሱና እግዚአብሔር ወይም ሁሉን የሚችለው አምላክ ሁለት የተለያዩ አካላት መሆናቸውን አመልክቷል። ባይሆን ኖሮ እንዴት ሁለት ምስክሮች ሊኖሩ ይችሉ ነበር?

በተጨማሪም ኢየሱስ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም” በማለት ከእግዚአብሔር የተለየ መሆኑን አሳይቷል። (ማርቆስ 10:18) ስለዚህ ማንም ቢሆን፣ ኢየሱስም ጭምር የእግዚአብሔርን ያህል ቸር እንዳልሆነ ኢየሱስ መናገሩ ነበር። እግዚአብሔር ከኢየሱስ በሚለየው ሁኔታ ቸር ነው።

ለእግዚአብሔር የሚገዛ አገልጋይ

ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት እንደሚከተሉት ያሉትን ቃላት ተናግሯል:- “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ አይችልም።” (ዮሐንስ 5:19) “እኔ ከሰማይ የወረድሁት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም።” (ዮሐንስ 6:38 የ1980 ትርጉም ) “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም።” (ዮሐንስ 7:16) ላኪ ከመልእክተኛ ይበልጥ የለምን?

ይህን ዝምድና ኢየሱስ ስለ ወይን አትክልት ቦታ ከሰጠው ምሳሌ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። አባቱን እግዚአብሔርን የወይን እርሻውን ለአይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች ምሳሌ ለሆኑ አትክልተኞች አደራ ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር በሄደ ሰው መስሏል። የእርሻው ባለቤት ከወይኑ አትክልት የተገኘውን ፍሬ እንዲያመጣለት ባሪያውን በላከ ጊዜ አትክልተኞቹ ባሪያውን ደብድበው ባዶ እጁን ላኩት። ከዚህ በኋላም የእርሻው ባለቤት መጀመሪያ ሁለተኛ ባሪያውን በኋላም ሦስተኛ ባሪያውን ላከ። በሁሉም ላይ እንደ መጀመሪያው ባሪያ አደረጉባቸው። በመጨረሻም ባለቤቱ “ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን [ኢየሱስን] እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ።” ይሁን እንጂ ምግባረ ብልሹ የነበሩት አትክልተኞች “ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ። ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት።” (ሉቃስ 20:9–16) ስለዚህ ኢየሱስ በአባቱ ዘንድ ያለውን ደረጃ ሰብዓዊ አባት እንደፈቀደ በሚልከው ታዛዥ ልጅ መስሏል። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የተላከ መሆኑንም አመልክቷል።

የኢየሱስ ተከታዮች ኢየሱስን ይመለከቱ የነበሩት ለአምላክ ታዛዥ እንደሆነ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው እንጂ የእግዚአብሔር እኩያ እንደሆነ አድርገው አልነበረም። ወደ አምላክ በሚጸልዩበትም ጊዜ “በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ . . . በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ” ብለዋል።—ሥራ 4:23, 27, 30

ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር የበላይ ነበር

ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ፣ ከተጠመቀበት ውኃ ሲወጣ የአምላክ ድምፅ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ተሰምቶ ነበር። (ማቴዎስ 3:16, 17) ታዲያ ይህን ሲናገር ራሱ የራሱ ልጅ እንደሆነ ወይም ራሱ ራሱን እንደሚወድ ወይም ራሱ ራሱን እንደላከ መናገሩ ነበርን? በፍጹም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፈጣሪ አምላክ የበላይ እንደመሆኑ መጠን ከእርሱ የሚያንሰው ልጁ ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ሥራ እንዲያከናውን የፈቀደ መሆኑን መግለጹ ነበር።

ኢየሱስ “የጌታ [የይሖዋ አዓት] መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና” ማለቱ አባቱ ከእርሱ የሚበልጥ መሆኑን ያመለክታል። (ሉቃስ 4:18) መቀባት ማለት ከአንድ የበላይ ባለ ሥልጣን አንድ ዓይነት ሥራ ወይም ሥልጣን መቀበል ማለት ነው። አምላክ ኢየሱስ ከዚህ በፊት ያልነበረውን ሥልጣን ሰጥቶ ስለቀባው የኢየሱስ የበላይ እንደሆነ ግልፅ ነው።

በተጨማሪም የሁለት ደቀ መዛሙርቱ እናት ወደ እርሱ ቀርባ ኢየሱስ በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ አንዳቸው በቀኙ አንዳቸው ደግሞ በግራው እንዲቀመጡ እንዲያደርግላት በጠየቀችው ጊዜ “በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም” በማለት ኢየሱስ አባቱ ከእርሱ የሚበልጥ መሆኑን ግልጽ አድርጓል። (ማቴዎስ 20:23) ኢየሱስ ሁሉን የሚችል አምላክ ቢሆን ኖሮ ይህን ቦታ የመስጠት ሥልጣን ይኖረው ነበር። ኢየሱስ እግዚአብሔር ስላልነበረ በቀኝና በግራው እንዲቀመጡ ለማድረግ አይችልም። ይህን ለማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ኢየሱስ የጸለያቸው ጸሎቶችም የበታችነት ቦታ ያለው መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” ብሎ በመጸለይ የበታች መሆኑን አመልክቷል። (ሉቃስ 22:42) የሚጸልየው ወደ ማን ነበር? የራሱ ክፍል ለሆነ አምላክ ነበርን? አልነበረም። ሙሉ በሙሉ ከእርሱ ለተለየ፣ ከእርሱ የበለጠና ከእርሱ ሊለይ የሚችል ፈቃድ ላለው፣ “ይህን ጽዋ ከእርሱ የመውሰድ” ችሎታ ላለው አባቱ መጸለዩ ነበር።

ከዚያም በኋላ ለመሞት በተቃረበ ጊዜ “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ብሎ ጮኸ። (ማርቆስ 15:34) ኢየሱስ ይጮህ የነበረው ወደ ማን ነበር? ወደ ራሱ ወይም የራሱ ክፍል ወደ ሆነ አምላክ ነበርን? ይህ “አምላኬ” የሚለው ጩኸት ራሱን እንደ እግዚአብሔር አድርጎ ከሚቆጥር የወጣ ጩኸት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ ኢየሱስ የተተወው በማን ነበር? ራሱ ራሱን ተወ ማለት ነውን? እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም። በተጨማሪም ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ነፍሴን [መንፈሴን አዓት] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ብሏል። (ሉቃስ 23:46) ኢየሱስ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ መንፈሱን ለአባቱ አደራ የሚሰጠው በምን ምክንያት ነው?

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ለሦስት ቀናት ያህል በመቃብር ውስጥ ቆይቷል። እሱ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ ዕንባቆም 1:12 “አቤቱ፣ የተቀደስክ አምላኬ ሆይ፣ አንተ አትሞትም” [አዓት] ያለው ትክክል አይደለም ማለት ነው። ኢየሱስ እንደሞተና በመቃብር ውስጥ በድን ሆኖ እንደቆየ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ታዲያ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው ማን ነው? ሞቶ ከነበረ ራሱን ሊያስነሣ አይችልም። ሙሉ በሙሉ አልሞተ ከነበረ ደግሞ አሟሟቱ የይስሙላ ሞት ስለሆነ ለአዳም ኃጢአት የሚያስፈልገውን ቤዛ ሊከፍል አይችልም። ይሁን እንጂ በትክክለኛ ሁኔታ በመሞት ቤዛውን ከፍሏል። ስለዚህ “እግዚአብሔር የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው።” (ሥራ 2:24) ከሁሉ የበላይ የሆነው ሁሉን የሚችል አምላክ ከራሱ የሚያንሰውንና አገልጋዩን ኢየሱስን ከሞት አስነሣው።

ኢየሱስ ሙታንን እንደ ማስነሣት የመሰሉትን ተአምራት ለማድረግ መቻሉ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ያመለክታልን? ሐዋርያት፣ ኤልያስና ኤልሳዕም ይህን ዓይነት ተአምር የማድረግ ችሎታ ነበራቸው። ይህን ችሎታ ማግኘታቸው ግን ከሰዎች በላይ አላደረጋቸውም። ለነቢያት፣ ለኢየሱስም ሆነ ለሐዋርያት ተአምራት ለማድረግ ያስቻላቸውን ኃይል የሰጣቸው እግዚአብሔር ነው። ይህንንም ኃይል የሰጣቸው የእርሱ ድጋፍ ያላቸው መሆኑን ለማሳየት ነው። ይሁን እንጂ ይህን ኃይል ማግኘታቸው አንዳቸውንም ቢሆን የአንዱ አምላክ ክፍል አላደረጋቸውም።

ኢየሱስ የነበረው እውቀት የተወሰነ ነበር

ኢየሱስ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚገልጸውን ትንቢት በተናገረ ጊዜ “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም” ብሏል። (ማርቆስ 13:32) ኢየሱስ እኩል ማዕረግና ደረጃ ያለው የአንዱ አምላክ ክፍል ቢሆን ኖሮ አብ የሚያውቀውን ሁሉ ማወቅ ነበረበት። ኢየሱስ ግን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ስላልሆነ አባቱ የሚያውቀውን ሁሉ ሊያውቅ አልቻለም።

በተመሳሳይም ዕብራውያን 5:8 ላይ ኢየሱስ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን” እንደተማረ እናነባለን። እግዚአብሔር የሚማረው ነገር ይኖራል ብለን ለማሰብ እንችላለንን? በፍጹም አንችልም። ኢየሱስ ግን እግዚአብሔር የሚያውቀውን ሁሉ ስለማያውቅ ትምህርት ማግኘት አስፈልጎት ነበር። ይህን ኢየሱስ መማር የነበረበት የታዛዥነት እውቀት ደግሞ ለእግዚአብሔር የሚያስፈልገው እውቀት አልነበረም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለማንም መታዘዝ አያስፈልገውም።

ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም ቢሆን በእግዚአብሔርና በኢየሱስ እውቀት መካከል ልዩነት መኖሩ አልቀረም። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የመክፈቻ ቃላት ምን እንደሚሉ ልብ በሉ። “እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው።” (ራእይ 1:1) ኢየሱስ ራሱ አንደኛው የእግዚአብሔር ክፍል ቢሆን ኖሮ በሌላው የእግዚአብሔር ክፍል የሚሰጠው እውቀት ወይም መግለጫ ሊኖር ይችላልን? እግዚአብሔር የሚያውቀውን ሁሉ እርሱም ማወቅ ነበረበት። ኢየሱስ ግን እግዚአብሔር ስላልነበረ አላወቀም።

ኢየሱስ የበታች መሆኑ አልቀረም

ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊትም ሆነ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአባቱ የበታች ነበር። ከሙታን ከተነሣ በኋላም ቢሆን የበታችነቱና ከአባቱ ሁለተኛ ደረጃ ያለው መሆኑ አልቀረም።

ጴጥሮስና ከእሱ ጋር የነበሩት ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ለአይሁድ ሸንጎ ሲናገሩ “ይህን እግዚአብሔር፣ . . . በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው” ብለዋል። (ሥራ 5:31) ጳውሎስም “እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 2:9) ኢየሱስ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀድሞ ከነበረው ደረጃ ከፍ ከፍ ሊደረግ ይችላል? የሥላሴ ክፍል ቢሆን ኖር ቀድሞውንም ቢሆን የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ነበረው ማለት ነው። ከፍ ከፍ ከመደረጉ በፊት የእግዚአብሔር እኩያ ቢሆን ኖሮ ከፍ ከፍ መደረጉ የእግዚአብሔር የበላይ እንዲሆን ያስችለው ነበር።

በተጨማሪም ጳውሎስ ክርስቶስ “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ” ብሏል። (ዕብራውያን 9:24) በአንድ አካል ፊት ከታየህ እንዴት አንተ ያንን አካል ልትሆን ትችላለህ? አትችልም። በፊቱ ከታየኸው አካል የተለየህና የተነጠልክ መሆን ይኖርብሃል።

በተመሳሳይ መንገድ ሰማዕት የሆነው እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ከመሞቱ በፊት “ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ።” (ሥራ 7:55) የተመለከተው ሁለት የተለያዩ አካሎችን እንደነበረ ግልጽ ነው። አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ ወይም መንፈስ ቅዱስን አልተመለከተም።

በራእይ 4:8 እስከ 5:7 በሚገኘው መግለጫ ላይ እግዚአብሔር በሰማያዊ ዙፋን እንደተቀመጠ ተገልጿል። ኢየሱስ ግን በዙፋን ላይ አልተቀመጠም። ከእግዚአብሔር ቀኝ እጅ የመጽሐፍ ጥቅልል ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነበረበት። ይህም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም ቢሆን ከእግዚአብሔር የተለየ ሆኖ እንደኖረ እንጂ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ያመለክታል።

በእንግሊዝ አገር በማንቸስተር ከተማ የሚታተመው ቡለቲን ኦቭ ዘ ጆን ራይላንድስ ላይብረሪ ከላይ ከተመለከትነው ጋር በመስማማት እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በነበረው ሰማያዊ ሕይወቱ ምድራዊ ሰው ሆኖ በምድር ላይ እንደኖረበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ፈጽሞ የተለየና የተነጠለ ሕልውና እንዳለው በግልጽ ተመልክቷል። የአምላክ ልጅ በመሆኑ ልዩ ምድብ የተሰጠውና ከመላእክትም በጣም የሚበልጥ ማዕረግ ያለው ቢሆንም ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጻጸርና ሲወዳደር ግን በእግዚአብሔር ሰማያዊ ሸንጎ ውስጥ የሚገኝ እንደ መላእክት ያለ ሰማያዊ አካል ነው።”—ከፊልጵስዩስ 2:11 ጋር አወዳድር።

በተጨማሪም ይኸው ቡለቲን እንዲህ ይላል:- “ይሁን እንጂ ክርስቶስ በሰማይ ስላለው ሕይወትና ኑሮ የተነገሩት ነገሮች ሁሉ በመለኮትነቱ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንደሆነ ወይም ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አያመለክቱም። ከዚህ ይልቅ አዲስ ኪዳን ስለ ሰማያዊ ሕልውናውና አገልግሎቱ በሚሰጠን ሥዕል ውስጥ የምንመለከተው ከእግዚአብሔር የተለየና ያነሰ መሆኑን ነው።”

ኢየሱስ በሰማይ በሚኖረው ዘላለማዊ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር የተለየና ለእግዚአብሔር የሚገዛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “በኋላም፣ [በሰማይ የሚኖረው ኢየሱስ] መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ . . . ፍጻሜ ይሆናል። . . . በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ፣ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።”—1 ቆሮንቶስ 15:24, 28

ኢየሱስ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አያውቅም

የመጽሐፍ ቅዱስ አቋም ግልጽ ነው። ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ ከኢየሱስ የተለየ አካል ከመሆኑም በላይ ምንም ጊዜ ቢሆን የእርሱ የበላይ ነው። ኢየሱስ ምን ጊዜም ሁሉን ከሚችል አምላክ የተለየ፣ የበታችና ትሁት የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆነ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” እንደሆነ ሁሉ “የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር” ነው የሚለው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ኢየሱስም ራሱ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ያለው በዚህ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 14:28

ኢየሱስ እግዚአብሔር አለመሆኑና ነኝም ብሎ አለመናገሩ የተረጋገጠ ሐቅ ነው። ይህ ሐቅ ቁጥራቸው እየጨመረ በሚሄዱ ብዙ ምሁራን ዘንድ እየታወቀ ሄዷል። የራይላንድ ቡለቲን እንደሚለው “ከሐቁ ልንሸሽ አንችልም። ባለፉት ሠላሳ ወይም አርባ ዓመታት በአዲስ ኪዳን ላይ የተደረጉ ጥናቶች ቁጥራቸው እየበዛ የሚሄድ ብዙ ዕውቅ የሆኑ የአዲስ ኪዳን ምሁራን ኢየሱስ . . . እግዚአብሔር እንደሆነ አምኖ ወይም ተናግሮ አያውቅም ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል።”

በተጨማሪም ይህ ቡለቲን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ክርስቶስ፣ የሰው ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እና ጌታ የሚሉትን የማዕረግ ስሞች [ለኢየሱስ] መስጠታቸው ኢየሱስ እግዚአብሔር ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሥራ የሠራ መሆኑን ማመልከታቸው ነው።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እግዚአብሔር የበላይ ሲሆን ኢየሱስ ግን የበታች አገልጋይ እንደሆነ ነው።

በዚህ ምክንያት አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን እንኳን ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው የሚለው አስተሳሰብ መላውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት የሚቃወም እንደሆነ ያምናሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እግዚአብሔር የበላይ ሲሆን ኢየሱስ ግን የበታች አገልጋይ እንደሆነ ነው።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘በአዲስ ኪዳን ላይ የተደረገው ጥናት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ብዙ ምሁራን ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን በፍጹም አላመነም ወደሚል መደምደሚያ እያደረሳቸው ነው’—ቡለቲን ኦቭ ዘ ጆን ራይላንድ ላይብረሪ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ለአይሁድ እንዲህ ሲል ነገራቸው:- “ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁ።”—ዮሐንስ 6:38

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ሲል የጮኸው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ያምን ስላልነበረ ነው