በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ሥላሴ “ያስረዳሉ” የሚባሉት “ጥቅሶችስ”?

ስለ ሥላሴ “ያስረዳሉ” የሚባሉት “ጥቅሶችስ”?

ስለ ሥላሴ “ያስረዳሉ” የሚባሉት “ጥቅሶችስ”?

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሥላሴ መኖሩን ያረጋግጣሉ ይባላል። ይሁን እንጂ እነዚህን ጥቅሶች በምናነብበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ሆነ ታሪካዊ ማስረጃዎች የሥላሴን እምነት እንደማይደግፉ ልብ ማለት ይገባናል።

ማንኛውም ለማስረጃነት የሚቀርብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እርስ በርሱ ከማይጋጨው የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ትምህርት ጋር ተገናዝቦ መታየት ይኖርበታል። አብዛኛውን ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን ጥቅሶች ትክክለኛ ትርጉም ከጥቅሱ በፊትና በኋላ ከተገለጹት ሐሳቦች ጋር በማገናዘብ መረዳት ይቻላል።

አንድነት በሦስትነት

ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ለሥላሴ ማረጋገጫ ይሆናሉ የሚላቸውን ሦስት ጥቅሶች ቢሰጥም የሚከተለውን አምኗል። “የቅዱስ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ነው የሚባለው ማስረጃ የሚገኘው በጳውሎስ መልእክቶች በተለይ በ​2 ቆሮ 13:13 [በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች በቁጥር 14] እና በ​1 ቆሮ 12:4–6 ላይ ነው። በወንጌሎች ውስጥ ደግሞ የሥላሴ ማስረጃ የምናገኘው በማቴ 28:19 ስለ ጥምቀት በተሰጠው መግለጫ ላይ ነው።”

በእነዚህ ሦስት ጥቅሶች ላይ ሦስቱ አካላት እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 13:13 (14) በሚከተለው ሁኔታ ሦስቱን አንድ ላይ አስቀምጧቸዋል። “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን።” አንደኛ ቆሮንቶስ 12:4–6 “የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፣ መንፈስ ግን አንድ ነው። አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፣ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።” ማቴዎስ 28:19 ደግሞ እንዲህ ይነበባል:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”

ታዲያ እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር፣ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ ሆነው አንድ ሥላሴያዊ አምላክ እንደሆኑ ወይም ሦስቱም በሕልውና፣ በኃይልና በዘላለማዊነት እኩል እንደሆኑ ያመለክታሉን? በፍጹም አያመለክቱም። በቀለ፣ አበበና ከበደ አንድ ላይ መጠቀሳቸው ሦስቱ ሰዎች አንድ መሆናቸውን እንደማያመለክት ሁሉ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ መጠቀሳቸውም ሦስቱ አንድ መሆናቸውን ሊያመለክት አይችልም።

የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል ቴዎሎጂካል ኤንድ ኤክሊዚያስቲካል ሊትሬቸር እንዳመነበት “ሦስቱ አንድ ላይ መዘርዘራቸው የሚያረጋግጠው እነዚህ ሦስት ክፍሎች መኖራቸውን ብቻ ነው። ብቻውን እነዚህ ሦስቱ የመለኮት ክፍል መሆናቸውንና ሦስቱም እኩል የሆነ መለኮታዊ ክብር ያላቸው መሆኑን አያረጋግጥም።”

ይህ መጽሐፍ የሥላሴ እምነት ደጋፊ ቢሆንም ስለ 2 ቆሮንቶስ 13:13 (14) ሲናገር:- “ከዚህ ጥቅስ እኩል ሥልጣን ወይም አንድ ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው ልንደመድም አንችልም” ብሏል። ስለ ማቴዎስ 28:18–20 ደግሞ እንዲህ ይላል:- “ይህ ጥቅስ ብቻውን የተጠቀሱት ሦስት አካላት ስብዕና እንዳላቸውም ሆነ እኩልነት ወይም መለኮታዊነት እንዳላቸው ሊያረጋግጥ አይችልም።”

ኢየሱስ በተጠመቀበትም ጊዜ እግዚአብሔር፣ ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሰዋል። ኢየሱስ “የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ” አይቷል። (ማቴዎስ 3:16) ይሁን እንጂ ሦስቱ አንድ መሆናቸውን አይናገርም። አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ብዙ ጊዜ አንድ ላይ ተጠርተዋል። ይሁን እንጂ አንድ ላይ መጠራታቸው አንድ አያደርጋቸውም። ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ አንድ ላይ ቢጠሩም አንድ ላይ መጠራታቸው አንድ መሆናቸውን አላመለከተም። ከዚህም በላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኢየሱስ ላይ የወረደው በተጠመቀበት ጊዜ ነው። ይህም ኢየሱስ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በመንፈስ እንዳልተቀባ ያመለክታል። ታዲያ እንዲህ ከሆነ እንዴት የሥላሴ ክፍል ሊሆንና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ሆኖ የኖረ ሊሆን ይችላል?

ሦስቱ በአንድ ቦታ የሚነገሩበት ሌላ ጥቅስ በአንዳንድ የቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች 1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት ብዙ ጊዜ ካለፈ በኋላ የተጨመሩ እንጂ በጥንቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ መሆናቸውን ብዙ ምሁራን ያምናሉ። አብዛኛዎቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን አላግባብ የተጨመረ ቃል አስወጥተዋል።

ሌሎቹ ለሥላሴ ትምህርት እንደ ማስረጃ ሆነው የሚጠቀሱ ጥቅሶች በሁለቱ መካከል ማለትም በአብና በኢየሱስ መካከል ስላለው ዝምድና የሚናገሩ ናቸው። አንዳንዶቹን እንመልከታቸው።

“እኔና አብ አንድ ነን”

ይህ በዮሐንስ 10:30 ላይ የሚገኝ ጥቅስ ስለ ሦስተኛ አካል የማይናገር ቢሆንም ለሥላሴ እምነት እንደ ማስረጃ ሆኖ ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ ከአባቱ ጋር አንድ የሆነው በምን መንገድ እንደሆነ አመልክቷል። በዮሐንስ 17:21, 22 ላይ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፣ . . . አንተ፣ አባት ሆይ፣ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸልዮአል። ታዲያ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ አንድ ሰው እንዲሆኑ መጸለዩ ነበርን? አልነበረም። ኢየሱስ እርሱና እግዚአብሔር በአስተሳሰብና በዓላማ አንድ እንደሆኑ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱም በአስተሳሰባቸውና በዓላማቸው አንድ እንዲሆኑ መጸለዩ ነበር።—በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 1:10ን ተመልከት።

ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 3:6, 8 ላይ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ . . . የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው” ብሏል። ጳውሎስ እሱና አጵሎስ በአንድ አካል ውስጥ ያሉ ሁለት ሰዎች እንደነበሩ መናገሩ አልነበረም። በዓላማቸው አንድ መሆናቸውን መግለጹ ነበር። እዚህ ላይ ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል (ሄን) በግዑዝ ጾታ የተነገረ ሲሆን ቃል በቃል ትርጉሙ “አንድ (ነገር) ” ማለት ነው። ስለዚህ የመተባበር አንድነትን የሚያመለክት ቃል ነው። ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ያለውን ዝምድና ለመግለጽ ዮሐንስ 10:30 ላይ የተጠቀመውም በዚሁ ቃል ነው። ዮሐንስ 17:21, 22 ላይም ኢየሱስ የተጠቀመው በዚሁ ቃል ነው። ስለዚህ በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ “አንድ” (ሄን) የሚለውን ቃል የተጠቀመው የሐሳብና የዓላማ አንድነትን ለመግለጽ ነው።

ራሳቸው የሥላሴ እምነት ተከታይ የነበሩት ጆን ካልቪን ስለ ዮሐንስ 10:30 ኮሜንቴሪ ኦን ዘ ጐስፕል አኰርዲንግ ቱ ጆን (የዮሐንስ ወንጌል ማብራሪያ) በተባለው መጽሐፍ “የጥንቶቹ አባቶች ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ ባሕርይና አንድ አካል እንዳለው ማስረጃ ይሆናል በማለት ይህን ጥቅስ በስህተት ተጠቅመውበታል። ክርስቶስ የተናገረው ስለ አካል ወይም ስለ ሕልውና አንድነት ሳይሆን ከአባቱ ጋር ስላለው ስምምነት ነው።”

ኢየሱስ በዮሐንስ 10:30 ከተገለጸው ርዕሰ ጉዳይ ሳይወጣ ወዲያው እግዚአብሔር ነኝ አለማለቱን ጠንከር ባለ ሁኔታ ገልጿል። ይህን የመሰለ የተሳሳተ ግንዛቤ ያሳደሩትንና ሊወግሩት የፈለጉትን አይሁዳውያን “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልኩ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን:- ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” በማለት ጠይቋቸዋል። (ዮሐንስ 10:31–36) ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ አለ እንጂ እኔ እግዚአብሔር ወልድ ነኝ ብሎ አያውቅም።

“ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ”?

ሥላሴን ለመደገፍ የሚጠቀሰው ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅስ ዮሐንስ 5:18 ነው። አይሁድ (በዮሐንስ 10:31–36 ላይ እንዳደረጉት) “ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ:- እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ” ኢየሱስን ሊገድሉት ፈለጉ ይላል።

ነገር ግን ኢየሱስ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏል ያለው ማን ነበር? ኢየሱስ አልነበረም። ኢየሱስ ከዚህ በሚቀጥለው ጥቅስ (ቁጥር 19) ላይ ከዚህ ሐሰተኛ ክስ ራሱን ነፃ አድርጓል። “ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው:- . . . አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም።”

ኢየሱስ በዚህ አነጋገሩ እሱ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አለመሆኑንና አንዳች ነገር በራሱ ተነሣስቶ እንደማያደርግ ለአይሁዳውያን አመልክቷል። ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር እኩል ቢሆን ኖሮ “ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም” ይል ነበርን? (ከዳንኤል 4:34, 35 ጋር አወዳድር።) በዮሐንስ 5:18 እና 10:30 አካባቢ ያሉት ምንባቦች እንደሚያሳዩት አይሁዳውያን እንደ ሥላሴ አማኞች የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰው የሰነዘሩበት ክስ ሐሰት መሆኑን ገልጿል።

“ከእግዚአብሔር ጋር መተካከል”?

የካቶሊክ ድዌይ መጽሐፍ ቅዱስ የ1609 ትርጉም በፊልጵስዩስ 2:6 ላይ “በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆንን እንደ ቅሚያ አልቆጠረም” ይላል። በ1611 የተዘጋጀው የኪንግ ጀምስ ትርጉምም ከዚህ አተረጓጎም እምብዛም የተለየ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነበር ለሚለው ሐሳብ ድጋፍ ለማግኘት እንደነዚህ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ እንዴት ብለው እንደተረጎሙት ልብ በሉ።

1869:- “እሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊወሰድ እንደሚገባ ነገር አድርጎ አልተመለከተውም።” ዘ ኒው ቴስታመንት በጄ አር ኖይስ

1965:– “እሱ በእውነት መለኰታዊ ባሕርይ ያለው ሲሆን በራሱ በመተማመን ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አላደረገም።” ዳስ ኖየ፣ ቴስታመንት በፍሬድሪክ ፋፍሊን የተዘጋጀ።

1968:– “በእግዚአብሔር መልክ የኖረ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆንን በስግብግብነት ለራሱ ሊያደርገው እንደሚገባ ነገር አልቆጠረም።” ላ ቢቢያ ኮንኮርዳታ

1976:– “እሱ ምንጊዜም የእግዚአብሔር ባሕርይ ነበረው፣ ነገር ግን በኃይል ተጠቅሞ የእግዚአብሔር እኩያ ሊሆን እንደሚገባው አላሰበም።” ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን

1984:– “እሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር የነበረ ቢሆንም፣ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆን እንደሚገባው ቆጥሮ ለመቀማት አላሰበም።” ኒው ወርልድ ትራንስሌሸን ኦቭ ዘ ሆሊ እስክሪፕቸር (የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም)

1985:– “በእግዚአብሔር መልክ ቢኖርም፣ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆንን የሚነጠቅ ነገር እንደሆነ አድርጎ አልቆጠረውም።” ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል

1954:- “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከእነዚህ ይበልጥ ትክክል የሆኑት አተረጓጎሞች እንኳ (1) ኢየሱስ ምንጊዜም እኩልነት እንደነበረውና ነገር ግን ይህን እኩልነቱን እንደያዘ ለመኖር እንዳልፈለገ ወይም (2) ቀድሞውንም ቢሆን እኩል ስለነበረ እኩልነትን መቀማት እንዳላስፈለገው ያሳያሉ ይላሉ።

በዚህ ረገድ ራልፍ ማርቲን ዘ ኤፒስትል ኦቭ ፓል ቱ ዘ ፊሊፒያንስ (የጳውሎስ መልእክት ወደ ፊልጵስዩስ) በተባለው መጽሐፍ ስለ ጥንቱ ግሪክኛ እንዲህ ይላሉ:- “የግሡ ትርጉም ‘መቀማት’፣ ‘መያዝ’ ‘በኃይል መንጠቅ’ ከሚለው ትክክለኛ ትርጉሙ የተለየ ትርጉም ሊኖረው መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው።” በተጨማሪም ዘ ኤክስፖዝተርስ ግሪክ ቴስታመንት “ሃርፓዞ የተባለው ይህ ቃል ወይም በዚህ ቃል እርባታ የተገኙ ሌሎች ቃላት ‘የራስ አድርጎ ማቆየት’ ወይም ‘አጽንቶ መያዝ’ የሚል ትርጉም ያስተላለፈባቸው አንድም ጊዜ የለም። ‘መቀማት’ ወይም ‘በኃይል መውሰድ’ ከማለት የተለየ ትርጉም ኖሮት አያውቅም። ስለዚህ ‘መውሰድ’ ከሚለው ትክክለኛ ትርጉሙ ርቆ ‘እንደያዘ መኖር’ የሚል የተለየ ትርጉም መስጠት ፈጽሞ የማይፈቀድ ነው” ይላል።

ከላይ በተገለጸው መሠረት፣ እንደ ዱዌይ እና ኪንግ ጀምስ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የተረጐሙ ተርጓሚዎች ሥላሴን ለመደገፍ ሲሉ የሰዋስው ሕግጋትን እንዳጣመሙ ግልጽ ነው። በፊልጵስዩስ 2:6 ላይ የሚገኘው የግሪክኛ አነጋገር በቀና መንፈስ ሲነበብ የሚያመለክተው ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንደነበረ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መፈለግ ተገቢ እንደሆነ ነገር አድርጎ አለማሰቡን ነው።

የቁጥር 6ን ትክክለኛ ትርጉም በቁጥር 3–5, 7, 8 ላይ ከተገለጹት ሐሳቦች ለመረዳት እንችላለን። የፊልጵስዩስ ሰዎች “እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ ቀጥሎ ጳውሎስ በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም አርዓያ የሚሆናቸው ኢየሱስ መሆኑን ሲገልጽላቸው እንዲህ አላቸው:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።” ይህ “አሳብ” ምን ነበር? ‘ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን እንደ ቅሚያ አለመቁጠሩ’ ነውን? ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ሊያስገነዝብ የፈለገውን ነጥብ በቀጥታ የሚቃረን ሐሳብ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ‘እግዚአብሔር ከእርሱ እንደሚበልጥ ይቆጥር’ የነበረው ኢየሱስ ‘ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ለመቀማት ከመፈለግ’ ይልቅ እስከ ሞት ድረስ “ራሱን አዋረደ።”

በእርግጥ ሁሉን ስለሚችለው አምላክ የሚናገር ጥቅስ ሊሆን አይችልም። ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም ጳውሎስ እዚህ ላይ ለማስገንዘብ ለፈለገው የበላያችንና ፈጣሪያችን ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ስለ መታዘዝ አስፈላጊነት በጣም ጥሩ ምሳሌ ሆኗል።

“እኔ ነኝ”

አንዳንድ ዘ ጀሩሳሌም ባይብልን የመሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዮሐንስ 8:58ን ኢየሱስ:- “አብርሃም ከመኖሩ በፊት እኔ ነኝ” እንዳለ አድርገው ተርጉመውታል። እዚህ ላይ የሥላሴ አማኞች እንደሚሉት ኢየሱስ “እኔ ነኝ” በሚለው ማዕረግ ስም ይታወቅ እንደነበር መግለጹ ነውን?

ዘጸአት 3:14 ላይ የኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “እግዚአብሔር ለሙሴ አለው:- እኔ፣ እኔ ነኝ” ስለሚል እነሱ እንደሚሉት ኢየሱስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጸው ይሖዋ እንደሆነ መናገሩ ነበርን?

ዘጸአት 3:14 ላይ (ኪንግ ጀምስ ትርጉም) “እኔ ነኝ” የሚለው ሐረግ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዳለና ቃል የገባበትን ነገር ለማድረግ እንደሚችል የሚገልጽ የማዕረግ ስም ሆኖ አገልግሏል። በዶክተር ጄ ኤች ሄርትዝ የተዘጋጀው ዘ ፔንታቱች ኤንድ ሃፍቶራሕስ ስለዚህ ሐረግ እንዲህ ይላል:- “በባርነት ለነበሩት እስራኤላውያን ሐረጉ ‘እስከ አሁን ድረስ ኃይሉን ያልገለጸላችሁ ቢሆንም አሁን ይገልጽላችኋል። እርሱ ዘላለማዊ በመሆኑ ይቤዣችኋል’ የሚል ትርጉም የሚያስተላልፍ ነበር። አብዛኞቹ ዘመናዊ ተርጓሚዎች ራሺን [ፈረንሣዊ የመጽሐፍ ቅዱስና የታልሙድ ተንታኝ ነው] በመከተል [ዘጸአት 3:14ን] ‘የምሆነውን እሆናለሁ’ እያሉ ተርጉመዋል።”

ዮሐንስ 8:58 ላይ የሚገኘው አነጋገር በዘጸአት 3:14 ላይ ካለው ፈጽሞ የተለየ ነው። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረውን ሕይወቱን ለመግለጽ እንጂ እንደ ስም ወይም እንደ ማዕረግ ስም አድርጐ አልተጠቀመበትም። በዚህም ምክንያት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዮሐንስ 8:58ን እንዴት እንደተረጎሙት እንመልከት:-

1869:– “አብርሃም ከመኖሩ በፊት እኔ ነበርኩ።” ዘ ኒው ቴስታመንት፣ በጂ አር ኖይስ

1935:– “አብርሃም ከመወለዱ በፊት ነበርኩ!” ዘ ባይብል አን አሜሪካን ትራንስሌሽን፣ በጄ ኤም ፒ ስሚዝ እና ኢ ጂ ጉድስፒድ

1965:– “አብርሃም ከመወለዱ በፊት የሆንኩትን ሆኜ ነበር።” ዳስ ኖየ ቴስታመንት በዮርግ ሲንክ (አዲስ ኪዳን)

1980:- “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ።”—የ19 80 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

1981:– “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ በሕይወት ነበርኩ።” ዘ ሲምፕል ኢንግሊሽ ባይብል

1984:– “አብርሃም ከመኖሩ በፊት እኔ ነበርኩ” ኒው ወርልድ ትራንስሌሽን ኦፍ ዘ ሆሊ እስክሪፕቸርስ (የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም)

ስለዚህ እዚህ ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል የሚያስተላልፈው ሐሳብ የእግዚአብሔር በኩር ፍጥረት የሆነው ኢየሱስ አብርሃም ከመኖሩ ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሮ ይኖር እንደነበረ ነው።—ቆላስይስ 1:15፤ ምሳሌ 8:22, 23, 30፤ ራእይ 3:14

ይህ አስተሳሰብ ትክክል መሆኑን አሁንም በጥቅሱ ዙሪያ ከሚገኙት ሐሳቦች መረዳት ይቻላል። በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን ሊወግሩት የፈለጉት ገና ሃምሳ ዓመት እንኳን ያልሞላው ሲሆን ‘አብርሃምን አይቶ እንደነበረ’ በመናገሩ ነው። (ቁጥር 57) ኢየሱስ ትክክለኛ ዕድሜውን እንዲናገር የሚያስገድደው ሁኔታ ነበር። በዚህም ምክንያት “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።”

“ቃልም እግዚአብሔር ነበር”

የ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በዮሐንስ 1:1 ላይ “ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ” ይላል። የሥላሴ አማኞች ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ወደ ምድር የመጣው “ቃል” (ግሪክኛ ሆ ሎጎስ) ሁሉን የሚችለው አምላክ ነበር ማለት ነው ይላሉ።

ይሁን እንጂ እዚህም ላይ ቢሆን ጥቅሱን በትክክል እንድንረዳ የሚያስችለን በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ነው። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” እንደሚል አስተውሉ። (በአይታሊክ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን።) በአንድ ሰው ዘንድ የነበረ ሰው ተመልሶ ያንን ሰው ለመሆን አይችልም። በጀስዊት ጆሴፍ ኤ ፊትዝማየር የሚዘጋጀው ጆርናል ኦቭ ቢብሊካል ሊትረቸር (የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ጽሑፍ መጽሔት) ከዚህ አስተሳሰብ ጋር በመስማማት የኋለኛው የዮሐንስ 1:1 ክፍል “እግዚአብሔር” ተብሎ ከተተረጎመ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ “የሚለውን ቀደም ያለ ሐረግ የሚቃረን ይሆናል” ይላል።

በተጨማሪም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን የጥቅሱን ክፍል እንዴት እንደተረጎሙት አስተውል:-

1808:– “ቃልም አምላክ ነበረ።” ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን አን ኢምፕሩቭድ ቨርሽን አፖን ዘ ቤስስ ኦቭ አርክቢሾፕ ኒውካምስ ኒው ትራንስሌሽን ዊዝ ኤ ኰሬክትድ ቴክስት

1864:– “እና ቃል አምላክ ነበር።” ዘ ኢምፋቲክ ዳይግሎት፣ በቤንጃሚን ዊልሰን

1928:– “ቃልም መለኰታዊ የሆነ አካል ነበር።” ላ ቢብል ዱ ሴንቴኔር፣ ሌ ኢቫንዥል ሴሎ ዢን፣ በሞሪስ ጎገል

1935:– “ቃልም መለኰታዊ ነበር።” ዘ ባይብል አን አሜሪካን ትራንስሌሽን፣ በጄ ኤም ፒ ስሚዝ እና ኢ ጄ ጉድስፒድ

1946:- “ቃል መለኰታዊ ዓይነት ነበረ።” ዳስ ኖየ ቴስታመንት (አዲስ ኪዳን)፣ በሉድቪግ ቲሜ

1950:- “ቃልም አምላክ (a god) ነበር።” ኒው ወርልድ ትራንስሌሽን ኦፍ ዘ ክርስቲያን ግሪክ እስክሪፕቸርስ (የአዲሱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም)

1958:- “ቃልም አምላክ (a God) ነበር።” ዘ ኒው ቴስታመንት (አዲስ ኪዳን)በጄምስ ኤል ቶማኔክ

1975:– “ቃል አምላክ (ወይም መለኰታዊ ባሕርይ ያለው) ነበረ።” ዳስ ኢቫንጀሊየም ናኽ ዮሐነስ በዚግፍሪድ ሹልዝ

1978:– “ቃል አምላክን የሚመስል ዓይነት ነበር።” ዳስ ኢቫንጀሊየም ናኽ ዮሐነስ፣ በዮሐነስ ሽናይደር

ዮሐንስ 1:1 ላይ ቴኦስ (አምላክ) የሚለው የግሪክኛ ቃል ሁለት ጊዜ ተጠቅሷል። የመጀመሪያው የሚያመለክተው ሁሉን የሚችለውን አምላክ ነው። (ቃልም [ሎጎስ] ከዚህ ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ነበር።) ከመጀመሪያው ቴኦስ በፊት ቶን የሚል የግሪክኛ ቃል ይገኛል። ይህ ቃል አንድን በግልጽ የታወቀና የተለየ አካል ለይቶ የሚያመለክት ጠቃሽ አመልካች ቃል ነው። እዚህ ላይ የሚያመለክተው ሁሉን የሚችለውን አምላክ ነው። (“ቃልም ከአምላክ ጋር [with the God] ነበር።”)

በሌላ በኩል ግን ዮሐንስ 1:1 ላይ ከሁለተኛው ቴኦስ በፊት አመልካች የሆነ ቃል አይገኝም። ስለዚህ ቃል በቃል ቢተረጐም “ቃሉም አምላክ (god) ነበረ” ተብሎ ይነበባል። ቢሆንም ብዙ ትርጉሞች ይህንን ሁለተኛውን ቴኦስ (በተሳቢነት የገባ ስም) “መለኰታዊ” “አምላክ መሰል” ወይም “አምላክ (a god)” ብለው እንደተረጐሙት ተመልክተናል። ይህን ያደረጉት ምን ምክንያት ቢኖራቸው ነው?

የኰይነ ግሪክኛ “ዘ” (“the”) ከተባለው አመልካች መስተኣምር ጋር የሚመሳሰል ቃል ሲኖረው “ኤ” ወይም “አን” (a, an) ከተባሉት ያልተወሰኑ አመልካች መስተኣምሮች ጋር የሚመሳሰል ቃል የለውም። ስለዚህ በተሳቢነት በተጠቀሰ ስም ፊት አመልካች ቃል ካልኖረ ቃሉ አንድን የተወሰነ አካል ወይም ነገር የማያመለክት ነው ማለት ነው።

ጆርናል ኦቭ ቢብሊካል ሊትሬቸር (የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ጽሑፎች መጽሔት) “ከግሥ በፊት የገባ አመልካች ቃል የሌለው ተሳቢ አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው አንድን ዓይነት ባሕርይ ነው” ይላል። ይህ መጽሔት ቀጥሎ እንደሚናገረው ሎጎስ ከአምላክ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በተጨማሪም ስለ ዮሐንስ 1:1 ሲናገር “በተሳቢነት የገባው ቃል የሚሰጠው የባሕርይ ትርጉም በጣም ጎልቶ የሚታይ ስለሆነ ይህ ስም (ቴኦስ) አንድን የተወሰነ አካል የሚያመለክት ሊሆን አይችልም።”

ስለዚህ ዮሐንስ 1:1 አጉልቶ የሚያሳየው የቃልን ባሕርይ ማለትም “መለኮት”፣ “አምላክ መሰል”፣ “አምላክ (a god)” መሆኑን እንጂ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን አይደለም። ይህም እዚህ ላይ “ቃል” ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ የአምላክ ቃል አቀባይ በመሆኑ የበላዩ በሆነው ሁሉን የሚችል አምላክ ወደ ምድር በታዛዥነት የተላከ መሆኑን ከሚያመለክቱት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚስማማ ነው።

ሁሉም ተርጓሚዎች ተመሳሳይ የሰዋስው አገባብ ያላቸውን የግሪክኛ ዓረፍተ ነገሮች ሲተረጉሙ “a” (ኤ) ወይም “an” (አን) የተባሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት እያስገቡ የተረጎሙባቸው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል በማርቆስ 6:49 ላይ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በውኃ ላይ ሲሄድ በተመለከቱ ጊዜ ኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚለው “መንፈስ [a spirit]” መስሏቸው ነበር። በኮይነ ግሪክኛ ውስጥ “መንፈስ” ከሚለው ቃል በፊት ከእንግሊዝኛው “a” ጋር የሚመሳሰል ቃል አልገባም። ይሁን እንጂ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች አተረጓጎሙን ከቃሉ አገባብ ጋር ለማስማማት ሲሉ “a” ጨምረውበታል። ዮሐንስ 1:1ም በተመሳሳይ ሁኔታ ቃልም ከእግዚአብሔር (God) ጋር እንደነበረ ከተናገረ እግዚአብሔር (God) ራሱን ሊሆን ስለማይችል “a god” ወይም “መለኮት” መሆን ይኖርበታል ማለት ነው።

የሃይማኖት ትምህርት ምሁር የሆኑትና በአሜሪካን ስታንደርድ ቨርዥን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ተካፋይ የነበሩት ጆሴፍ ሄንሪ ታዬር በቀላሉ እንዲህ ብለዋል:- “ሎጐስ መለኮታዊ ነበር እንጂ ዋናው መለኮት አልነበረም።” ጀስዊት ጆን ኤል ማኬንዚም ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት) በተባለው መጽሐፍ ላይ “ዮሐንስ 1:1 ‘ቃል መለኮታዊ ነበር’ ተብሎ መተርጎም ይኖርበታል” ብለዋል።

የሰዋስውን ሕግ የሚጻረር ነውን?

ቢሆንም አንዳንዶች እንደዚህ ያለው አተረጓጎም በ1933 የግሪክኛ ምሁር የሆኑት ኢ ሲ ኮልዌል ያሳተሙትን የኮይነ ግሪክኛ የሰዋስው ሕግ የሚጻረር ነው ይላሉ። እኚህ ምሁር በግሪክኛ ቋንቋ “አንድ ስም የዓረፍተ ነገሩ ተሳቢ ሆኖና ከግሥ ተከትሎ የገባ ከሆነ በእንግሊዝኛ ዘ (the) የተባለው አመልካች ቃል ይገባለታል። ከግሥ በፊት የገባ ከሆነ ግን the የተባለው ቃል አይገባለትም” ብለዋል። በዚህ አባባላቸው በተሳቢነት የገባ ስም ከግሥ በፊት ከሆነ ከፊቱ (“the”) እንዳለው ተደርጎ መቆጠር አለበት ማለታቸው ነው። ስለዚህ በዮሐንስ 1:1 ላይ የዓረፍተ ነገሩ ተሳቢ ሆኖ የገባው ሁለተኛው ቴኦስ ከግሥ በፊት የሚገኝ ስለሆነ ዮሐንስ 1:1 “እግዚአብሔርም [the God] ቃል ነበር” ተብሎ መነበብ ይኖርበታል ይላሉ።

ነገር ግን ዮሐንስ 8:44 ላይ የሚገኙትን ሁለት ምሳሌዎች ብቻ እንመልከት:- በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ዲያብሎስን “እርሱ ነፍሰ ገዳይ (a manslayer) . . . ሐሰተኛ (a liar)” ነው ብሏል። እነዚህ በተሳቢነት የገቡት ስሞች በግሪክኛ (ነፍሰ ገዳይና ሐሰተኛ) እንደ ዮሐንስ 1:1 (“ነበር” እና “ነው”) ከሚሉት ግሦች በፊት የሚገኙ ናቸው። በኮይነ ግሪክኛ “a” ወይም “an” ከተባሉት የእንግሊዝኛ ቃላት ጋር የሚመሳሰል ቃል ስላልነበረ ከሁለቱም ስሞች በፊት የ “a” ተመሳሳይ የሆነ ቃል አልነበረም። ይሁን እንጂ ብዙ ተርጓሚዎች የሰዋስው ሕግጋትና የቃላቱ አገባብ ስላስገደዷቸው “a” የተባለውን ቃል ጨምረውባቸዋል።—በተጨማሪ ማርቆስ 11:32፤ ዮሐንስ 4:19፤ 6:70፤ 9:17፤ 10:1፤ 12:6 ተመልከት።

ኰልዌልም በተሳቢነት በሚገቡ ስሞች ረገድ ይህ አተረጓጎም ትክክል መሆኑን ተቀብለዋል። “የቃሉ አገባብ በሚያስገድድበት እንደዚህ ባለው ጊዜ ብቻ [“a” ወይም “an”] መጨመር ይቻላል ብለዋል። ስለዚህ እሳቸው እንኳን ለቃሉ አገባብ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተርጓሚዎች እንደነዚህ ባሉት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ በሚገኙ ስሞች ላይ “a” ወይም “an” ሊጨምሩ እንደሚችሉ አምነዋል።

ታዲያ ዮሐንስ 1:1 ላይ የቃሉ አገባብ “a” መጨመርን የሚጠይቅ ነውን? አዎን፣ ምክንያቱም መላው መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሁሉን የሚችል አምላክ አለመሆኑን ይመሰክራል። ስለዚህ እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች አንድ ተርጓሚ መመራት የሚኖርበት አጠያያቂ በሆነው የኮልዌል የሰዋስው ሕግ ሳይሆን በቃሉ አገባብ ነው። ብዙ ምሁራንም ሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ያልተረጋገጠ ሕግ ጋር እንደማይስማሙ በዮሐንስ 1:1 ላይ “a” የተባለውን ቃል እየጨመሩ ከተረጎሙት ብዙ ተርጓሚዎች በግልጽ ለመረዳት እንችላለን።

እርስ በርሱ የሚጋጭ አይደለም

ኢየሱስ ክርስቶስን “አምላክ” (a god) ነው ማለት አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነውን? አይደለም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በአንዳንድ ጊዜያት ይህን ቃል ኃያላን ፍጥረታትን ለማመልከት ይጠቀምበታል። መዝሙር 8:5 “[ሰውን] ከአምላክ መሰሎች [በዕብራይስጥ፣ አሎሂም] በጥቂቱ አሳነስኸው” (አዓት) ይላል። ይህም ከመላእክት አሳነስኸው ማለቱ ነው። ኢየሱስም አይሁዳውያን አምላክ ነኝ ብሏል በማለት ላቀረቡለት ክስ መልስ ሲሰጥ ‘ሕጉ እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ሁሉ አማልክት ብሎ ጠርቷቸዋል’ ብሏል። ሰብዓዊ ዳኞችን ማለቱ ነው። (ዮሐንስ 10:34, 35፤ መዝሙር 82:1–6) እንዲያውም ሰይጣን በ2 ቆሮንቶስ 4:4 ላይ “የዚህ ዓለም አምላክ” ተብሏል።

ኢየሱስ ከመላእክት፣ ፍጽምና ከጐደላቸው ሰዎች ወይም ከሰይጣን እጅግ ከፍ ያለ ማዕረግ አለው። እነዚህ “አማልክት” ወይም ኃያላን ተብለው ከተጠሩ ኢየሱስ “አምላክ” ተብሎ ሊጠራ እንደሚችልና በእርግጥም “አምላክ” እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። በአባቱ ዘንድ ልዩ የሆነ ቦታና ማዕረግ ስላለው “ኃያል አምላክ” ነው።—ዮሐንስ 1:1፤ ኢሳይያስ 9:6

ይሁን እንጂ “ኃያል አምላክ” የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ በትልልቅ ፊደላት በሚጀምሩ ቃላት [“Mighty God”] ተብሎ መጻፉ ኢየሱስ በአንድ ዓይነት መንገድ ከይሖዋ አምላክ ጋር እኩል መሆኑን አያመለክትምን? በፍጹም አያመለክትም። ኢሳይያስ ኢየሱስ ከሚጠራባቸው አራት ስሞች አንዱ “ኃያል አምላክ” እንደሚሆን ትንቢት መናገሩ ነበር። በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ የመጠሪያ ስሞች የሚጻፉት በካፒታል (በትላልቅ) ፊደል ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ “ኃያል” ተብሎ ቢጠራም “ሁሉን የሚችል” ሊባል የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። አማልክት ተብለው የሚጠሩና ከይሖዋ ያነሰ ቦታ ያላቸው ባይኖሩ ኖሮ ይሖዋ አምላክ “ሁሉን የሚችል አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ብዙም ትርጉም አይኖረውም ነበር።

እንግሊዝ አገር የሚታተመው ዘ ቡለቲን ኦቭ ዘ ጆን ራይላንድስ ላይብረሪ ካቶሊኩ የሃይማኖት ትምህርት ምሁር ካርል ራህነር እንደሚሉት ቴኦስ የሚለው ቃል እንደ ዮሐንስ 1:1 ባሉት ጥቅሶች ኢየሱስን ቢያመለክቱም “ከእነዚህ ጥቅሶች በአንዳቸውም ላይ ቢሆን ‘ቴኦስ’ ኢየሱስን ከ‘ሆ ቴኦስ’ ማለትም ከልዑሉ አምላክ ጋር አንድ ለማድረግ አልተሠራበትም።” ይኸው ቡለቲን በመቀጠል “የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የእምነት ሰዎች በሙሉ ኢየሱስ እግዚአብሔር (God) መሆኑን መመስከራቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ቢያምኑ ኖሮ ይህን የመሰለ ግልጽ መግለጫ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ፈጽሞ ያልኖረው ለምንድን ነው?” ይላል።

ታዲያ ሐዋርያው ቶማስ ዮሐንስ 20:28 ላይ ኢየሱስን “ጌታዬ አምላኬም” በእንግሊዝኛ [My Lord and my God] ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ለቶማስ፣ በተለይ ይህን እንዲናገር ባደረገው ተአምራዊ ሁኔታ፣ እንደ “አምላክ” ነበር። አንዳንድ ምሁራን ቶማስ በድንጋጤና በመደነቅ ስለ እግዚአብሔር መናገሩ ሊሆን ይችላል ይላሉ። በሁለቱም ሁኔታዎች ቢሆን ቶማስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ተናግሮ እንደማያውቅና ይሖዋ “ብቻውን እውነተኛ አምላክ” መሆኑን እንዳስተማረ ያውቁ ስለነበረ ኢየሱስ ሁሉን የሚችል አምላክ ነው ብሎ አላሰበም።—ዮሐንስ 17:3

አሁንም ቢሆን በዚህ ጥቅስ አካባቢ ያለው ሐሳብ ትክክለኛውን ትርጉም ለመረዳት ያስችለናል። ከሙታን የተነሳው ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በፊት መግደላዊት ማርያም ለደቀ መዛሙርት:- “እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ” ብላ እንድትነግራቸው ነግሯት ነበር። (ዮሐንስ 20:17) ኢየሱስ ኃያል መንፈስ ሆኖ ከሙታን ከተነሣ በኋላም እንኳ ቢሆን ይሖዋ አምላኩ ነበር። ታላቅ ክብር ከተቀዳጀ በኋላም ቢሆን የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋን አምላኬ እያለ ጠርቶታል።—ራእይ 1:5, 6፤ 3:2, 12

ቶማስ በመደነቅ መጮሁ ከተገለጸበት ሦስት ቁጥር ያህል ወረድ ብሎ በዮሐንስ 20:31 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ . . . ይህ ተጽፎአል” በማለት ስለ ጉዳዩ ግልጽ ማብራሪያ ይሰጠናል። ይህን ሲልም በሥጋዊ አባትና ልጅ መካከል እንዳለው ዝምድና “ልጅ” መሆኑን መግለጹ ነበር እንጂ አንድነት በሦስትነት ያለው አንድ አምላክ ምሥጢራዊ ክፍል እንደሆነ መናገሩ አልነበረም።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማት አለበት

ሥላሴን የሚደግፉ ሌሎች ብዙ ጥቅሶችም አሉ ይባላል። ይሁን እንጂ እነዚህም ጥቅሶች ቢሆኑ በጥንቃቄ ሲመረመሩ ምንም ዓይነት ድጋፍ ስለማይሰጡ ከላይ ከተመለከትናቸው የተለዩ አይደሉም። እነዚህ ሥላሴን ይደግፋሉ የሚባሉትን ጥቅሶች ስንመረምር አተረጓጎሙ ይሖዋ ብቻ ልዑል አምላክ መሆኑን ከሚገልጸው ከመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይስማማልን? ብለን መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው። ከዚህ ትምህርት ጋር የማይስማማ ከሆነ የተሳሳተ አተረጓጎም ነው ማለት ነው።

በተጨማሪም የሥላሴ ማስረጃ ናቸው ከሚባሉት ጥቅሶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እግዚአብሔር፣ ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ አንድ ምሥጢራዊ የሆነ አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ ክፍል መሆናቸውን አይገልጹም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በማንኛውም ሥፍራ ላይ ሦስቱም በባሕርይ፣ በኃይልና በዘላለማዊነት እኩል መሆናቸውን የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የጥንቶቹ አባቶች ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ ባሕርይና አንድ አካል እንዳለው ማስረጃ ይሆናል በማለት [በዮሐንስ 10:30] በስህተት ተጠቅመዋል”—ኮመንተሪ ኦን ዘ ጎስፕል አኮርዲንግ ቱ ጆን፣ በጆን ካልቪን

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከአንድ አካል “ጋር” የነበረ ተመልሶ ያንን አካል ሊሆን አይችልም

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሎጎስ መለኰታዊ ነበር እንጂ ዋነኛው መለኮት አልነበረም” —ጆሴፍ ሄንሪ ታዬር የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢየሱስ እሱና አብ “አንድ እንደሆኑ” ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” ወደ እግዚአብሔር ጸልዮአል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ለአይሁድ ‘አብ ሲያደርግ ያየውን እንጂ እሱ በራሱ ምንም እንደማያደርግ’ በመናገር ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አለመሆኑን ገልጾላቸዋል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን፣ መላእክትንና ሰይጣንን እንኳን “አምላክ” ወይም “ኃያላን” ብሎ የሚጠራቸው ከሆነ ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጠው በሰማይ ያለው ኢየሱስ “አምላክ” ተብሎ ሊጠራ መቻሉ ተገቢ ነው