በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነውን?

በእርግጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነውን?

በእርግጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነውን?

ሥላሴ እውነት ቢሆን ኖሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ መገለጽ ነበረበት። ለምን? ምክንያቱም ሐዋርያት እንዳረጋገጡት መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች የገለጸበት መጽሐፍ ስለሆነ ነው። እግዚአብሔርን ተቀባይነት ባለው ሁኔታ እንድናመልከው ከተፈለገ እርሱን በትክክል ማወቅ ስለሚኖርብን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ማንነት በግልጽ ሊነግረን ይገባል።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን አማኞች ቅዱሳን ጽሑፎች ትክክለኛ የእግዚአብሔር መግለጫ መሆናቸውን ተቀብለዋል። የእምነታቸው መሠረትና የመጨረሻ ማረጋገጫ ያደረጉት ቅዱሳን ጽሑፎችን ነበር። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በቤሪያ ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች በሰበከላቸው ጊዜ “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ቅዱሳን ጽሑፎችን ዕለት ዕለት እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።”—ሥራ 17:10, 11 አዓት

በዚያን ጊዜ የነበሩ የታወቁ የአምላክ ሰዎች እንደ ዋነኛ ማስረጃ አድርገው የተጠቀሙት በምን ነበር? ሥራ 17:2, 3 እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ጳውሎስም እንደ ልማዱ . . . ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ ምክንያቱን ያስረዳና ማስረጃ እያቀረበ ያብራራ ነበር።” አዓት 

ኢየሱስም ቅዱሳን ጽሑፎችን የትምህርቱ መሠረት አድርጎ በመጠቀም ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። በተደጋጋሚ “ተጽፏል” ይል ነበር። “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።”—ማቴዎስ 4:4, 7፤ ሉቃስ 24:27

ስለዚህ ኢየሱስ፣ ጳውሎስና የመጀመሪያው መቶ ዘመን አማኞች የእምነታቸው መሠረት ያደረጉት ቅዱሳን ጽሑፎችን ነበር። እነርሱ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጐ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ” የሚጠቅም መሆኑን ያምኑ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 4:6፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21 ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ነገሮችን መስመር ለማስያዝ’ [አዓት] ስለሚችል መሠረታዊ ትምህርት ነው ስለተባለው ስለ ሥላሴም አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥ በእርግጥ ይጠበቅበታል። ይሁን እንጂ የሃይማኖት ሊቃውንትና የታሪክ ምሁራን ሥላሴ በእርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው ይላሉን?

“ሥላሴ” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛልን?

ንድ የፕሮቴስታንት ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም . . . እስከ 4ኛው መቶ ዘመን ድረስ በቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት ውስጥ መደበኛ ቦታ አልተሰጠውም ነበር። (ዘ ኢላስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ ) (ሥዕላዊው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ) እንዲሁም አንድ የካቶሊክ ባለ ሥልጣን ሥላሴ “ግልጽና ቀጥተኛ የእግዚአብሔር ቃል . . . አይደለም” ብለዋል። — ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ

በተጨማሪም ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሦስቱን መለኰታዊ አካላት አጠቃልሎ የሚያመለክት አንድ ቃል እስከ አሁን ድረስ አልተገኘም። ትራያስ የሚለው የግሪክኛ ቃል (በላቲን ትሪኒታስ ተብሎ የተተረጐመው) ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ኢየሱስ ከሞተ ከ180 ዓመት በኋላ በአንፆኪያው ቴዎፍሎስ ጽሑፍ ውስጥ ነው።  . . . ከዚያም ትንሽ ቆይቶ ወደ ላቲን የተተረጎመው ትሪኒታስ በተርቱሊያን ጽሑፍ ውስጥ ሰፍሮ ተገኝቷል።”

ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን ተርቱሊያን ስለ ሥላሴ አስተምሮ እንደነበረ አያረጋግጥም። ለምሳሌ ትሪኒታስ — የቅዱስ ሥላሴ ሃይማኖታዊ ኢንሳይክሎፒድያ (ትሪኒታስ — ኤ ቲኦሎጂካል ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ዘ ሆሊ ትሪኒቲ ) የተባለው የካቶሊክ ጽሑፍ አንዳንድ ሰዎች የተርቱሊያንን ቃላት ስለ ሥላሴ ለማብራራት እንደተጠቀሙባቸው አመልክቷል። ቀጥሎም እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “ሆኖም ግን በቃላት አጠቃቀም ብቻ በመመራት የችኰላ ውሳኔ ማድረግ አይቻልም። ምክንያቱም እነዚህን ቃላት የተጠቀመው የሥላሴን እምነት ለማብራራት አይደለም።”

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡት ምስክርነት

“ሥላሴየሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ቢሆንም ስለ ሥላሴ ሐሳብ የሚገልጽ ነገር ይኖር ይሆንን? ለምሳሌ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (“ብሉይ ኪዳን”) ምን ይገልጻሉ?

ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ሲል ያምናል:- “በአሁኑ ጊዜ የሃይማኖት ሊቃውንት የሥላሴ ትምህርት በዕብራውያን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ይስማማሉ።” እንዲሁም ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ብሉይ ኪዳን የቅዱስ ሥላሴን ትምህርት አላስተማረም።”

ኢየሱሳዊው [ጀስዊት] ኤድመንድ ፎርትማንም በተመሳሳይ ዘ ትሪዩን ጐድ (አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ ) በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ አምነዋል:- “ብሉይ ኪዳን . . . አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ስለሚገኙበት አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ በግልጽም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚነግረን ምንም ነገር የለም። . . . እንዲያውም ማንኛውም ቅዱስ ጸሐፊ በአንድ እግዚአብሔር ውስጥ [ሥላሴ ] ይኖራል ብሎ መጠርጠሩን እንኳ የሚያመለክት ማስረጃ የለም። . . . [“በብሉይ ኪዳን”] ውስጥ ሥላሴነት ያላቸው አካላት መኖራቸውን የሚጠቁሙ ሐሳቦች ወይም ‘የተሸፈኑ ምልክቶች’ አሉ ማለት እንኳ ቅዱሳን ጸሐፊዎች ከጻፏቸው ቃላትና ከዓላማቸው አልፎ መሄድ ይሆናል።”—በአይታሊክ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን።

የዕብራይስጥን ቅዱሳን ጽሑፎች ብንመረምር ይህ አባባል ትክክል መሆኑን ለመረዳት እንችላለን። ስለዚህ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በመጀመሪያዎቹ 39 የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ሥላሴ የሚያስተምር ግልጽ ሐሳብ አይገኝም።

የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡት ምስክርነት

የግሪክኛ ክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችስ (“አዲስ ኪዳን”) ስለ ሥላሴ በግልጽ ይናገሩ ይሆንን?

ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ይላል:- “የሃይማኖት ሊቃውንት ግልጽ የሆነ የሥላሴ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥም እንደማይገኝ ይስማማሉ።”

ኢየሱሳዊው [ጀስዊት] ፎርትማን እንዲህ ብለዋል:- “የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች . . . በአንድ እግዚአብሔር ሦስት እኩል የሆኑ መለኰታዊ አካላት እንዳሉ የሚያመለክት የተደራጀና የተረጋገጠ ግልጽ የሥላሴ ትምህርት አላስተላለፉልንም። . . . በአንድ እግዚአብሔር ውስጥ ሦስት መለኮታዊ ሕይወትና ተግባር ያላቸው የተለያዩ አካላት መኖራቸውን የሚገልጽ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት የትም ቦታ አናገኝም።”

ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ሥላሴ የሚል ቃልም ይሁን ግልጽ የሆነ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም።”

ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያን ዶክተሪን (የክርስትና መሠረተ ትምህርቶች አጭር ታሪክ ) በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ በርናርድ ሎህሰ “ማንም ሰው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ግልጽ የሆነ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አያገኝም” ብለዋል።

ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ በተመሳሳይ እንዲህ ይላል:- “የዳበረው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ካርል ባርት ‘መጽሐፍ ቅዱስ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ናቸው የሚል ግልጽ መግለጫ የለውም’ ብለዋል።”

የየል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢ ዋሽበርን ሆፕኪንስ እንዲህ ሲሉ አረጋግጠዋል:- “በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስና ጳውሎስ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ . . . ስለዚህም መሠረተ ትምህርት የተናገሩት ምንም ነገር የለም።” — ኦሪጅን ኤንድ ኢቮሉሽን ኦቭ ሪሊጅን (የሃይማኖት አመጣጥና እድገት )

የታሪክ ምሁር የሆኑት አርተር ዌይጋል እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ:- “ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ስላለ ነገር በፍጹም አላነሳም። ‘ሥላሴ’ የሚለው ቃል ራሱ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በየትም ቦታ አይገኝም። ይህን ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን የተቀበለችው ጌታችን ከሞተ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ነው።”—ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቲያኒቲ (የክርስትናችን አረማዊነት )

ስለዚህ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑት 39 መጻሕፍትም ሆኑ 27ቱ በአምላክ መንፈስ የተጻፉት የግሪክኛ ክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ግልጽ የሆነ የሥላሴ ትምህርት አይሰጡም።

የጥንት ክርስቲያኖች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን?

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሥላሴን አስተምረዋልን? ከዚህ በታች የቀረቡትን የታሪክና የሃይማኖት ሊቃውንት የሰጧቸውን ሐሳቦች ተመልከት:-

“ጥንታዊው የክርስትና ሃይማኖት፣ በኋላ ጊዜ በተደነገጉት የእምነት ቃሎች የተብራራውን የመሰለ ግልጽ የሥላሴ ትምህርት አልነበረውም።”—ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ

“ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመጀመሪያ ላይ [የሥላሴን] ጽንሰ ሐሳብ የራሳቸው እምነት ክፍል ለማድረግ አላሰቡም ነበር። አምልኰታቸውን ለእግዚአብሔር አብና የእግዚአብሔር ልጅ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ያቀርቡ ነበር። የመንፈስ ቅዱስንም . . . ምንነት ያውቁ ነበር። እነዚህ ሦስቱ ግን እኩልና አንድ አምላክ የሆኑ ሥላሴ መሆናቸውን የሚገልጽ ሐሳብ ፈጽሞ አናገኝም።—ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቲያኒቲ (የክርስትናችን አረማዊነት )

“በመጀመሪያ ላይ የክርስትና እምነት የሥላሴ እምነት ተከታይ አልነበረም . . . በአዲስ ኪዳንና በሌሎችም ጥንታዊ የክርስቲያን ጽሑፎች እንደሚታየው በሐዋርያትና ከሐዋርያት በኋላ በነበሩት ዘመናት የሥላሴ እምነት አልነበረም።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ (የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ኢንሳይክሎፒድያ )

“‘በአንድ እግዚአብሔር ሦስት አካላት አሉ’ የሚለው እምነት 4ኛው መቶ ዘመን ከማለቁ በፊት . . . ሙሉ በሙሉ አልተመሠረተም ነበር። ከዚህ ጊዜ በፊት ከክርስትና ሕይወትና እምነት ጋር ፈጽሞ ያልተዋሃደ ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም። ሐዋርያዊ አባቶች የዚህ ዓይነት አመለካከትም ሆነ አስተሳሰብ እንደነበራቸው የሚያመለክት ምንም ዓይነት ፍንጭ አይገኝም።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ

ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበሩት አባቶች ምን አስተማሩ?

ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበሩት አባቶች ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት ግንባር ቀደም የሃይማኖት መምህራን እንደነበሩ ይታወቃል። እነዚህ መምህራን ያስተማሩትን ማወቅ ጠቃሚ ነው።

በ165 እዘአ በሰማዕትነት የሞተው ጀስቲን ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ሁሉን ከፈጠረው እግዚአብሔር የተለየና” የተፈጠረ መልአክ እንደሆነ ገልጿል። በተጨማሪም ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ያነሰ እንደነበረና “ፈጣሪ እንዲናገርና እንዲሠራ ከፈቀደለት ውጭ ምንም ነገር የማያደርግ . . .” እንደነበረ ተናግሯል።

ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ከእግዚአብሔር የተለየና ያነሰ ሕልውና እንደነበረው በ200 እዘአ አካባቢ የሞተው ኢረንየስ ተናግሯል። ኢየሱስ “ከአንዱ እውነተኛና ብቸኛ እግዚአብሔር” ማለትም “የሁሉም የበላይ ከሆነውና ሌላ እኩያ ከሌለው አምላክ” ጋር እኩል እንዳልሆነ አመልክቷል።

በ215 እዘአ አካባቢ የሞተው የእስክንድሪያው ክሊመንት እግዚአብሔርን “ያልተፈጠረ፣ የማይሞትና ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነ” ብሎታል። ወልድ ደግሞ “አንዳች ነገር ከማይሳነው አብ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ያለው” እንጂ ከአብ ጋር እኩል እንዳልሆነ ተናግሯል።

በ230 እዘአ አካባቢ የሞተው ተርቱልያን እግዚአብሔር የሁሉም የበላይ መሆኑን አስተምሯል። እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “አብ ከወልድ የተለየና የበለጠ ነው። ወላጅ ከልጁ፣ ላኪም ከተላኪው የተለየ እንደሆነ የታወቀ ነውና።” በተጨማሪም “ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር . . . ማንኛውም ነገር ከመገኘቱ በፊት እግዚአብሔር ብቻውን ይኖር ነበር።”

በ235 እዘአ አካባቢ የሞተው ሂፖሊተስ ስለ እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል:- “የመጀመሪያውና አቻ የሌለው፣ የሁሉም ሠሪና የሁሉም ጌታ የሆነው፣ የዕድሜ እኩያ የሌለው እግዚአብሔር . . . አንድ ራሱን ሆኖ ብቻውን ሲኖር ፈቃዱ ሆነና ከዚህ በፊት ያልነበሩ ነገሮች ወደ መኖር እንዲመጡ አደረገ።” ከእነዚህም አንዱ ሰው ከመሆኑ በፊት ተፈጥሮ የነበረው ኢየሱስ ነው።

በ250 እዘአ አካባቢ የሞተው ኦሪጀን:- “አብና ወልድ ሁለት የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ናቸው። . . . በአካላዊ ባሕርያቸውም ቢሆን የተለያዩ ናቸው። [ወልድ] ከአብ ጋር ሲነፃፀር በጣም ትንሽ ብርሃን ነው” ብሏል።

አልቫን ላምሶን የታሪክ ጭብጦችን አንድ ላይ በማጠቃለል ዘ ቸርች ኦቭ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ (በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት የነበረው ቤተ ክርስቲያን ) በተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብለዋል:- “በአሁኑ ዘመን በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘው የሥላሴ ትምህርት . . . ከጀስቲን [ከሰማዕቱ] አነጋገር ምንም ዓይነት ድጋፍ አያገኝም። ከኒቂያ ጉባኤ በፊት ስለ ነበሩት አባቶች በሙሉ ማለትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት ሦስት መቶ ዘመናት ስለተነሱት ክርስቲያን ጸሐፊዎች በሙሉ እንዲሁ ሊባል ይችላል። እውነት ነው ስለ አብ፣ ስለ ወልድና . . . ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናግረዋል። ነገር ግን የሥላሴ አማኞች አሁን እንደሚሉት ሦስቱም እኩል፣ አንድነት በሦስትነት ያላቸውና ፍጹም አንድ ስለመሆናቸው የተናገሩት ነገር አልነበረም። እውነቱ የዚህ ተቃራኒ ነው።”

ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስና በታሪክ ምሥክርነት መሠረት ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ዘመናትና ከዚያም በኋላ በነበሩት በርካታ ዘመናት በፍጹም የማይታወቅ እንደነበረ ተረጋግጧል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ማንኛውም ቅዱስ ጸሐፊ በእግዚአብሔር ራስነት ውስጥ [ሥላሴ] ይኖራል ብሎ የተጠራጠረ እንኳ ስለመኖሩ የሚያመለክት ማስረጃ የለም”— ዘ ትሪዩን ጎድ (ሦስትነት ያለው አምላክ)