በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሥላሴ ትምህርት እንዴት ዳበረ?

የሥላሴ ትምህርት እንዴት ዳበረ?

የሥላሴ ትምህርት እንዴት ዳበረ?

እዚህ ላይ እንዲህ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል:- ‘ሥላሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ካልሆነ እንዴት የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርት ሊሆን ቻለ?’ ብዙዎች በ325 እዘአ በተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ላይ የተደነገገ ነው ብለው ያስባሉ።

ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም። እርግጥ የኒቂያ ጉባኤ ክርስቶስና እግዚአብሔር አንድ አካል ያላቸው መሆኑን አረጋግጦ ነበር። ይህም በኋላ ለመጣው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት መሠረት ጥሎ ነበር። የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ግን አልመሠረተም። በዚያ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሦስትነት በአንድነት ያለው እግዚአብሔር ሦስተኛ አካል ስለመሆኑ የተጠቀሰ ነገር አልነበረም።

ቆስጠንጢኖስ በኒቂያ ጉባኤ የነበረው ሚና

ለብዙ ዓመታት ቀስ በቀስ እየተስፋፋ በመጣው ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው በሚለው አስተሳሰብ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ብዙ ተቃውሞ ይደርስ ነበር። የሮማ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ቆስጠንጢኖስ ለዚህ ክርክር እልባት ለመስጠት ሁሉንም ጳጳሳት ወደ ኒቂያ ጠራ። በዚያ ጊዜ ከነበሩት ጳጳሳት ከፊሎቹ ብቻ ማለትም 300 ጳጳሳት ብቻ ስብሰባው ላይ ተገኙ።

ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን አልነበረም። በሕይወቱ መጨረሻ ገደማ የክርስትናን እምነት እንደተቀበለ ቢነገርለትም የተጠመቀው ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ ነበር። ሔንሪ ቻድዊክ ዘ ኧርሊ ቸርች (የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ ቆስጠንጢኖስ እንዲህ ብለዋል:- “ቆስጠንጢኖስ እንደ አባቱ ድል ያልተነሳውን ፀሐይ ያመልክ ነበር፤ . . . የክርስትናን እምነት መቀበሉ ክርስትናን ሙሉ በሙሉ በጸጋ እንደተቀበለ ተደርጎ ሊተረጐም አይገባም . . . ይህ ወታደራዊ እርምጃ ነበር። ስለ ክርስትና መሠረተ ትምህርት ምን ዓይነት ማስተዋል እንደነበረው በግልጽ አይታወቅም። ይሁን እንጂ በጦር ሜዳ ድል የሚገኘው ከክርስቲያኖች አምላክ እንደነበር እርግጠኛ ነበር።”

ይህ ያልተጠመቀ ንጉሠ ነገሥት በኒቂያ ጉባኤ ላይ ምን ሚና ነበረው? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት ይተርካል “ቆስጠንጢኖስ ራሱ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት መርቷል። በውይይቱም በንቃት ተካፍሏል።  . . . ጉባኤው ያስተላለፈውንና ክርስቶስና እግዚአብሔር አንድ አካል መሆናቸውን የገለጸውን ድንጋጌ ጉባኤው እንዲያጸድቀው ያቀረበው እርሱ ራሱ ነው።  . . . ከሁለት ጳጳሳት በስተቀር ጳጳሳቱ በሙሉ ንጉሡን በመፍራት አለፍላጎታቸው ድንጋጌውን በፊርማቸው አረጋገጡ።”

ስለዚህ ቆስጠንጢኖስ በጉባኤው ላይ ቁልፍ ሚና ነበረው። ከሁለት ወራት የተካረረ ሃይማኖታዊ ክርክር በኋላ ይህ አረማዊ የፖለቲካ መሪ ጣልቃ በመግባት ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው የሚሉትን ጳጳሳት የሚደግፍ ውሳኔ አስተላለፈ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ውሳኔ ያስተላለፈው ለምን ነበር? በነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ምክንያት እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው። ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያን ዶክትሪን (የክርስትና መሠረተ ትምህርት አጭር ታሪክ) የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ቆስጠንጢኖስ በግሪክ የሃይማኖት ትምህርቶች ላይ ስለሚነሱት ጥያቄዎች ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።” እሱ የሚያውቀው የሃይማኖት መከፋፈል ለግዛቱ አደገኛ መሆኑን ብቻ ነበር። ግዛቱን ለማጠናከር ብርቱ ፍላጎት ነበረው።

ይሁን እንጂ በኒቂያ ጉባኤ ከተገኙት ጳጳሳት መካከል አንዱም ቢሆን የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አላስፋፉም። ስለ ኢየሱስ ምንነት ብቻ እንጂ መንፈስ ቅዱስ ስላለው የሥራ ድርሻ የወሰኑት ነገር አልነበረም። ሥላሴ ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቢሆን ኖሮ በዚህ ጉባኤ ላይ አይቀርብም ነበርን?

ተጨማሪ እድገት

ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሳው ክርክር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ቀጠለ። እንዲያውም ኢየሱስ እግዚአብሔር አይደለም ይሉ የነበሩት ለጥቂት ጊዜ ጥሩ ተደማጭነት አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቴዎዳስያስ እነሱን የሚቃወም ውሳኔ አስተላለፈባቸው። በኒቂያ ጉባኤ ላይ የተቀናበረው ድንጋጌ በግዛቱ ሁሉ የጸና እንዲሆን አደረገ። ድንጋጌውንም ለማብራራት በ381 እዘአ የቁስጥንጥንያን ጉባኤ ሰበሰበ።

ይህ ጉባኤ መንፈስ ቅዱስን ከእግዚአብሔርና ከክርስቶስ ጋር በእኩልነት ደረጃ ለማስቀመጥ ተስማማ። ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ሥላሴ በግልጽ መታየት ጀመረ።

ቢሆንም ከቁስጥንጥንያ ጉባኤ በኋላ እንኳን ሥላሴ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ድንጋጌ አልሆነም። ብዙዎች ተቃወሙት። በመቃወማቸውም ምክንያት አስከፊ ስደት በራሳቸው ላይ አመጡ። ሥላሴ በሚገባ ተቀናብሮ መደበኛ የእምነት ድንጋጌ የሆነው በኋለኛዎቹ መቶ ዘመናት ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “የሥላሴ እምነት ተሟልቶ የዳበረው በምዕራብ ሲሆን፣ ይህም የሆነው በመካከለኛው ዘመን በነበሩት ምሁራን አማካኝነት እምነቱን በፍልስፍናና በሥነ ልቦና ቃላት ለማብራራት በተሞከረበት ጊዜ ነበር።”

የአትናቴዎስ የእምነት ድንጋጌ

ሥላሴ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ የተገለጸው በአትናቴዎስ የእምነት ድንጋጌ ነው። አትናቴዎስ በኒቂያ ጉባኤ ላይ ቆስጠንጢኖስን ደግፎ የቆመ ካህን ነበር። በስሙ የሚጠራው የሃይማኖት ድንጋጌ እንዲህ ይላል:- “ሥላሴ የሆነውን አንድ እግዚአብሔር እናመልካለን . . . አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው፣ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ነው፤ ቢሆንም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።”

ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ የጠለቀ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይህንን ድንጋጌ ያቀናበረው አትናቴዎስ እንዳልነበረ ይስማማሉ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- “ይህ ድንጋጌ እስከ 12ኛው መቶ ዘመን ድረስ በምሥራቃዊው ቤተ ክርስቲያን አይታወቅም ነበር። ከ17ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የተነሱ ምሁራን የአትናቴዎስ ድንጋጌ የተጻፈው (በ373 በሞተው) በአትናቴዎስ ሳይሆን ምናልባት በደቡባዊ ፈረንሳይ በ5ኛው መቶ ዘመን እንደተዘጋጀ በአጠቃላይ ይስማማሉ . . . በ6ኛውና በ7ኛው መቶ ዘመናት ድንጋጌው ይታመን የነበረው በደቡባዊ ፈረንሳይና በስፔይን ብቻ ይመስላል። በ9ኛው መቶ ዘመን በጀርመን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ከዚያም ትንሽ ቆየት ብሎ በሮም ውስጥ ይጠቀሙበት ነበር።”

ስለዚህ ሥላሴ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ከክርስቶስ ዘመን በኋላ ብዙ መቶ ዘመናት ቆይቶ ነው። በእነዚህ ውሳኔዎች በሙሉ እንደ መመሪያ ሆኖ ያገለገለው ምን ነበር? የእግዚአብሔር ቃል ነበር፣ ወይስ ቤተ ክህነታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች? ኢ ደብልዩ ሆፕኪንስ ኦሪጅን ኤንድ ኤቮሉሽን ኦቭ ሪሊጅን (የሃይማኖት ምንጭና እድገት) በተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣሉ:- “በመጨረሻ የሥላሴ ትርጉም ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው በአብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ውጤት ነው።”

ክህደት እንደሚመጣ ተተንብዮ ነበር

ይህ ሊነቀፍ የሚገባው የሥላሴ ታሪክ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከእነሱ ዘመን በኋላ ይመጣል ብለው ከተናገሩት ትንቢት ጋር ይስማማል። እነርሱም ሰዎች ከእውነተኛው አምልኮ እንደሚርቁ፣ እንደሚወድቁና እንደሚክዱ ተናግረዋል። ይህም ክህደት የሚቆየው ክርስቶስ እስከሚመለስበትና ይህ ሥርዓት ከመጥፋቱ ቀደም ብሎ ንፁሑ አምልኮ እስከሚቋቋምበት ጊዜ ነው።

ስለዚያ “ቀን” ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፣ አይደርስምና።” (2 ተሰሎንቄ 2:3, 7) ከዚያም ቆየት ብሎ እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።” (ሥራ 20:29, 30) ሌሎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ስለዚህ ክህደትና ‘ዓመፀኛ’ ስለሆነው የቀሳውስት ክፍል ጽፈዋል።—ለምሳሌ 2 ጴጥሮስ 2:1፤ 1 ዮሐንስ 4:1–3፤ ይሁዳ 3, 4 ተመልከት።

በተጨማሪም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፎአል:- “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፣ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

ኢየሱስ ራሱ ሰዎች ከእውነተኛው አምልኰ የሚርቁበት ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። እርሱ መልካም ዘር እንደዘራና ጠላት የሆነው ሰይጣን በእርሻው ላይ አረም እንደሚዘራበት ተናግሯል። ስለዚህ ስንዴው በበቀለ ጊዜ አረሙም አብሮ መታየት ጀመረ። ስለዚህ የመከሩ ጊዜ ደርሶ ክርስቶስ ነገሮችን እስከሚያስተካክላቸው ድረስ ሰዎች ንጹሕ ከሆነው ክርስትና ፈቀቅ ማለታቸው የሚጠበቅ ነገር ነበር። (ማቴዎስ 13:24–43) ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- “የአራተኛው መቶ ዘመን የሥላሴ ትምህርት የጥንቱ የክርስቲያን ሃይማኖት ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የሰጠውን ትምህርት በትክክል አላንጸባረቀም። እንዲያውም ከዚህ ትምህርት የራቀና የተለየ ነበር።” ታዲያ ይህ ክህደት የመነጨው ከየት ነበር?—1 ጢሞቴዎስ 1:6

የሥላሴ እምነት የተገኘው ከየት ነው?

ከባቢሎን ጀምሮ በመላው ጥንታዊ ዓለም ውስጥ በሦስት በሦስት የተደራጁ ወይም በሦስትነት የተጣመሩ የአረማውያን አማልክት አምልኰ በጣም የተለመደ ነበር። በክርስቶስ ዘመንም ሆነ ከዚያ በፊትና በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት የዚህ አምልኮ ተጽዕኖ በግብፅ፣ በግሪክና በሮም የተስፋፋ ነበር። ከሐዋርያት ሞት በኋላ እንደነዚህ ያሉት የአረማውያን እምነቶች የክርስትናን ሃይማኖት መውረር ጀመሩ።

የታሪክ ምሁር የሆኑት ዊል ዱራንት እንደሚከተለው ብለዋል:- “ክርስትና አረማዊነትን አላጠፋም፣ አሻሽሎና እንደሚመቸው አድርጎ ተቀበለው እንጂ። . . . የመለኰታዊ ሥላሴ ሐሳብ የመጣው ከግብፅ ነው።” እንዲሁም ዚግፍሪድ ሞሬንዝ ኢጂፕሽያን ሪሊጅን (የግብፃውያን ሃይማኖት) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “ግብፃውያን የሃይማኖት ሊቃውንት ለሥላሴ ከፍተኛ ቦታ ይሰጡ ነበር . . . ሦስት አማልክት በአንድ ላይ ተጣምረው እንደ አንድ ነጠላ አምላክ ይቆጠሩ ነበር። የሚጠሩትም በነጠላ ቁጥር ነበር። በዚህ መንገድ የግብፅ ሃይማኖት መንፈሳዊ ኃይል ከክርስትና ሃይማኖታዊ ትምህርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ይታያል።”

በዚህ ምክንያት በሦስተኛው መቶ ዘመን መጨረሻና በአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በግብፅ አገር በእስክንድሪያ ይኖሩ የነበሩ እንደ አትናቴዎስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ወደ ሥላሴ እምነት የመራቸውን ሐሳብ በሚያቀናብሩበት ጊዜ የዚህ የግብፃውያን እምነት ተጽዕኖ እንደነበረባቸው በግልጽ ታይቷል። የእነዚህ ሰዎች ተጽዕኖ በመስፋፋቱ ምክንያት ሞሬንዝ “የእስክንድሪያ ሃይማኖታዊ ትምህርት ከግብፃውያን ሃይማኖታዊ ቅርስና በክርስትና ሃይማኖት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል” ብለዋል።

ኤድዋርድ ጊቦን በጻፉት ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ (የክርስትና ታሪክ) በተባለው መጽሐፍ መቅድም ላይ የሚከተለውን እናነባለን:- “አረማዊነት በክርስትና ድል ቢነሳም ክርስትናም በዚያው መጠን በአረማዊነት ተበክሏል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ንፁሕ መለኮታዊ አምልኮ . . . በሮም ቤተ ክርስቲያን ለመረዳት አስቸጋሪ በሆነው የሥላሴ ቀኖናዊ እምነት ተለወጠ። ብዙዎቹ በግብፃውያን የተፈለሰፉና ፕላቶ እንደ ፍጹም እውነታዎች እንዲታዩ ያደረጋቸው አረማዊ መሠረተ ትምህርቶች ሊታመንባቸው የሚገቡ ናቸው ተብለው ተቀባይነት አግኝተው ነበር።”

ኤ ድክሽነሪ ኦቭ ሪሊጅየስ ኖውሌጅ (የሃይማኖታዊ እውቀት መዝገበ ቃላት) የተባለው መጽሐፍ ብዙ ሰዎች ሥላሴ “ከአረማውያን ሃይማኖቶች ተቀድቶ በክርስትና ሃይማኖት ላይ የተለጠፈ ብልሽት ነው” ይላሉ ብሏል። እንዲሁም ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቲያኒቲ (የክርስትናችን አረማዊነት) እንዲህ ይላል:- “[የሥላሴ] እምነት የመነጨው ሙሉ በሙሉ ከአረማውያን ነው።”

ጄምስ ሃስቲንግ በኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ (የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ኢንሳይክሎፒድያ) የሚከተለውን የጻፉት በዚህ ምክንያት ነው:- “ለምሳሌ በሕንዳውያን ሃይማኖት ውስጥ ብራህማ፣ ሲቫ እና ቪስኑ የተባሉ ሦስት አማልክት ጥምረት በግብፃውያን ሃይማኖት ደግሞ ኦሲሪስ፣ አይሲስ እና ሆረስ የተባሉ የሦስት አማልክት ጥምረት እናገኛለን። . . . አምላክ ሥላሴ እንደሆነ የሚታመነው በታሪክ በታወቁ ሃይማኖቶች ብቻ አይደለም። በተለይ የፕላቶ ፍልስፍና ተከታዮች ከሁሉ በላይ ስለሆነው ወይም የመጨረሻው ሕላዌ ስለሆነው አካል የነበራቸው አመለካከት ሊጠቀስ የሚገባው ነው። የሦስት አካላት ጥምረት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።” ፕላቶ የተባለውን ግሪካዊ ፈላስፋ ከሥላሴ ጋር ምን ያገናኘዋል?

የፕላቶ ፍልስፍና (ፕላቶኒዝም)

ፕላቶ የኖረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ428 እስከ 347 እንደሆነ ይታሰባል። ሥላሴን አሁን በሚታወቅበት መልኩ ባያስተምርም የዚህ ሰው ፍልስፍና ለሥላሴ ትምህርት መንገድ ጠርጓል። ከእርሱ በኋላ ሥላሴያዊ እምነት ያላቸው የፍልስፍና እንቅስቃሴዎች ተነሥተዋል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ፕላቶ ስለ አምላክና ስለ ተፈጥሮ የነበረው አስተሳሰብ ነው።

በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፈው ኑቮ ዲክስዮነር ዩኒቨርሴል (አዲሱ ዩኒቨርሳል መዝገበ ቃላት) ፕላቶ ስላሳደረው ተጽዕኖ እንዲህ ይላል:- “ከመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ጀምሮ የነበሩትን የሥላሴ እምነቶች በማሻሻልና በማቀናጀት የተዘጋጀው የፕላቶ የሥላሴ ፍልስፍና የክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ለሚያስተምሩት የሦስት መለኮታዊ አካላት ወይም ሕላዌዎች እምነት መወለድ ምክንያት የሆነ ይመስላል። . . . ይህ ግሪካዊ ፈላስፋ ስለ ሥላሴ የነበረውን ጽንሰ ሐሳብ . . . በጥንቶቹ [አረማዊ] ሃይማኖቶች በሙሉ ማግኘት ይቻላል።”

ዘ ኒው ሻፍ ሔርዞግ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጀስ ኖውሌጅ ይህ ግሪካዊ ፈላስፋ የነበረውን ተጽዕኖ እንዲህ በማለት ያመለክታል:- “የሎጎስና የሥላሴ መሠረተ ትምህርቶች ቅርጻቸውን ያገኙት ከግሪክ አባቶች ነው። . . . እነዚህ የግሪክ አባቶች ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፕላቶ ፍልስፍና ተጽዕኖ ነበረባቸው። . . . ስህተቶችና ሃይማኖታዊ ብልሽቶች ከዚህ ምንጭ እየሠረጉ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባታቸውን ፈጽሞ መካድ አይቻልም።”

ዘ ቸርች ኦቭ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ (የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን) እንዲህ ይላል:- “የሥላሴ ትምህርት ቀስ በቀስ የመጣና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርብ ጊዜ የተደራጀ ትምህርት ነው። . . . ትምህርቱ የተገኘው ለአይሁዳውያንም ሆነ ለክርስትና ቅዱሳን ጽሑፎች ባዕዳን ከሆኑ ምንጮች ነው። . . . የፕላቶ ፍልስፍና ተከታዮች በሆኑ አባቶች እጅ አድጎ በክርስትና ላይ የተለጠፈ ትምህርት ነው።”

በሦስተኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር መጨረሻ ላይ “ክርስትና” እና የፕላቶ ፍልስፍናዎች አንዳቸው ከሌላው ሊነጠሉ በማይችሉበት ሁኔታ ተጣመሩ። አዶልፍ ሃርናክ አውትላይንስ ኦቭ ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዶግማ (የቀኖናዎች ታሪክ አጭር ማስታወሻ) በተባለው መጽሐፋቸው እንደጻፉት የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርት “ሥሩን በሄሌናውያን የፍልስፍና [የግሪክ አረማውያን ፍልስፍና] አፈር ውስጥ ሰደደ። በዚህም ምክንያት ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ምሥጢር ሆነ።”

ቤተ ክርስቲያን አዲሶቹ መሠረተ ትምህርቶችዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ትላለች። ይሁን እንጂ ሃርናክ እንደሚሉት “እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለሄሌናዊ (ለግሪክ) ግምታዊ አስተሳሰቦችና ለአረማዊ ምሥጢራዊ አምልኮቶችና አጉል እምነቶች ሕጋዊ እውቅና ሰጥታለች።”

አንድሩስ ኖርተን ኤ ስቴትመንት ኦቭ ሪዝንስ (የምክንያቶች መግለጫ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ ሥላሴ እንዲህ ብለዋል:- “የዚህን መሠረተ ትምህርት ታሪካዊ አመጣጥ ስንከታተል ምንጩ ክርስቲያናዊ መግለጫ ሳይሆን የፕላቶ ፍልስፍና እንደሆነ እንገነዘባለን። . . . ሥላሴ የክርስቶስም ሆነ የሐዋርያት መሠረተ ትምህርት አይደለም። በኋላ ዘመን የተነሱት የፕላቶ ፍልስፍና ተከታዮች ልብ ወለድ ትምህርት ነው።”

ስለዚህ ኢየሱስና ሐዋርያት ቀደም ሲል የተነበዩለት ክህደት በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ሙሉ በሙሉ ፈነዳ። የሥላሴ መሠረተ ትምህርት መስፋፋት የዚህ ክህደት አንደኛው ገጽታ ብቻ ነበር። ከሃዲዎቹ አብያተ ክርስቲያናት እንደ እሳታማ ሲኦል፣ እንደ ነፍስ አለመሞትና እንደ ጣዖት አምልኮ የመሰሉትን ሌሎች አረመኔያዊ አስተሳሰቦችም ተቀብለዋል። ሕዝበ ክርስትና ቁጥሩ እያደገ በሄደው “የዓመፅ ሰው” የቀሳውስት ክፍል መገዛት ወደ ጀመረችበት የመንፈሣዊ ጨለማ ዘመን ውስጥ ገባች።—2 ተሰሎንቄ 2:3, 7

የእግዚአብሔር ነቢያት ይህን ትምህርት ያላስተማሩት ለምንድን ነው?

ባለፉት በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በሙሉ ከአምላክ ነቢያት መካከል አንዳቸው እንኳን ሕዝቦቻቸውን ስለ ሥላሴ ያላስተማሩት ለምንድን ነው? ሌላው ቢቀር ኢየሱስ እንኳን ታላቅ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን በነበረው ጥሩ የማስተማር ችሎታ ተጠቅሞ ለተከታዮቹ ስለ ሥላሴ ግልጽ አድርጎ አያስረዳቸውም ነበርን? ሥላሴ የእምነት “ማዕከላዊ መሠረተ ትምህርት” ከሆነ አምላክ በመቶ የሚቆጠሩ ገጾች ያሏቸውን ቅዱሳን ጽሑፎች ሲያስጽፍ ከእነዚህ ጽሑፎች በአንዳቸው እንኳን ስለ ሥላሴ አያስተምርም ነበርን?

ክርስቲያኖች፣ ከክርስቶስ በኋላ ብዙ መቶ ዘመናት ቆይቶና አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ ካስጻፈ በኋላ አገልጋዮቹ በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ያላወቁትን፣ “ሊመረመር የማይቻል ምሥጢር የሆነን”፣ “የሰው አእምሮ መርምሮ ሊደርስበት የማይችለውን”፣ ከአረመኔዎች እንደተገኘ የሚታመነውንና “በአብዛኛው ለቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ ጥቅም ተብሎ የተስፋፋውን” ይህን መሠረተ ትምህርት ይደግፈዋል ብለው ለማመን ይችላሉን?

የታሪክ ማስረጃ የሚሰጠው ምሥክርነት በጣም ግልጽ ነው። የሥላሴ ትምህርት ከእውነት የራቀና የክህደት ትምህርት ነው።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘የአራተኛው መቶ ዘመን የሥላሴ ትምህርት ከጥንቱ የክርስትና ትምህርት የራቀ ነበር’—ዘ ኢንሳይክሎፒድያ አሜሪካና

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የታላላቆቹ አማልክት ሥላሴነት”

ከክርስቶስ ዘመን ብዙ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ በጥንቶቹ ባቢሎንና አሦር ውስጥ ብዙ በሦስት የተጣመሩ ወይም ሥላሴዎች የሆኑ አማልክት ነበሩ። የፈረንሳይ “ላሩስ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሚቶሎጂ (የላሩስ የአማልክት ተረት ኢንሳይክሎፒድያ)” በመስጴጦምያ አካባቢ ስለነበረ አንድ የሦስት አማልክት ጥምረት እንዲህ ሲል ይዘግባል:- “ጽንፈ ዓለሙ እያንዳንዱ የአንድ አምላክ ግዛት በሆነ ሦስት ክፍሎች ተከፍሎ ነበር። የአኑ ድርሻ ሰማይ ነበር። መሬት ለኤንሊል ተሰጥታ ነበር። ኢአ የውኃዎች ገዥ ሆነ። እነዚህ አማልክት አንድ ሆነው የታላላቆቹ አማልክት ሥላሴ ሆኑ።”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሂንዱ ሥላሴ

“ዘ ሲምቦሊዝም ኦቭ ሂንዱ ጎድስ ኤንድ ሪችዋልስ” (የሂንዱ አማልክት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችና ምሳሌያዊ መግለጫዎች) የተባለው መጽሐፍ ከክርስቶስ በፊት ብዙ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ ስለነበረ የሂንዱ ሥላሴ እንዲህ ይላል:- “ሲቫ ከሥላሴ አማልክት አንዱ ነው። እሱ የጥፋት አምላክ ነው ይባላል። ሌሎቹ ሁለት አማልክት የፍጥረት አምላክ የሆነው ብራህማ እና የፍጥረት ጠባቂ የሆነው ቪስኑ ናቸው። . . . እነዚህ ሥራዎች አንድና ተመሳሳይ መሆናቸውን ለማመልከት ሦስቱ አማልክት በአንድ አምሳል ተዋህደዋል።”—በኤ ፓርታሳራቲይ የታተመ፣ ቦምቤይ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“በመሠረቱ ቆስጠንጢኖስ በግሪክ የሃይማኖት ትምህርቶች ውስጥ ስለሚነሱት ጥያቄዎች ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።”—ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያን ዶክትሪን

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1. ግብፅ። ሆረስ፣ ኦሲረስና ኦይሲስ የሚገኙበት ሥላሴ፣ 2ኛው ሺህ ዓመት ከዘአበ

2. ባቢሎን። ኢሽታር፣ ሲንና ሻማሽ የሚገኙበት ሥላሴ፣ 2ኛው ሺህ ዓመት ከዘአበ

3. ፓልሚራ። የጨረቃ አምላክ፣ የሰማያት ጌታና የፀሐይ አምላክ የሚገኙበት ሥላሴ፣ 1ኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

4. ህንድ። አንድነት በሦስትነት ያለው የሂንዱ አምላክ፣ 7ኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

5. ካምፑቺያ። አንድነት በሦስትነት ያለው የቡዲሂስት አምላክ፣ 12ኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

6. ኖርዌይ። ሥላሴ (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ)፣ 13ኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

7. ፈረንሣይ። ሥላሴ፣ 14ኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

8. ኢጣልያ። ሥላሴ 15ኛው፣ መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

9. ጀርመን። ሥላሴ፣ 19ኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ

10. ጀርመን። ሥላሴ፣ 20ኛው መቶ ዘመን እዘአ