በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት

በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት

በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት

ቤተሰቦች ደስተኛ መሆን ይችላሉን?

ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

በዚህ ትራክት ላይ የሚታየውን ቤተሰብ የመሰለ አንድነትና ደስታ ያላቸው ቤተሰቦች ያውቃሉን? በየትኛውም ቦታ ቤተሰቦች እየፈራረሱ ነው። ፍቺ፣ የሥራ ዋስትና አለመኖር፣ ነጠላ ወላጆችን የሚያጋጥሙ ከባድ ችግሮችና ብስጭት ለደረሰው ቀውስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በቤተሰብ ኑሮ ጥናት ኤክስፐርት የሆኑ አንድ ሰው “ውሎ አድሮ ቤተሰብ የሚባል ነገር አይኖርም የሚለውን ትንበያ ባሁኑ ጊዜ ማንም ያውቀዋል” በማለት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

በጊዜያችን ቤተሰቦች እነዚህን በመሰሉ ከባድ ችግሮች የማያቋርጥ ጥቃት እየደረሰባቸው ያለው ለምንድን ነው? በቤተሰብ ኑሮ መደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

ቤተሰብ በመጀመሪያ የተመሠረተው እንዴት ነው?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የጋብቻንና የቤተሰብን ምንጭ ማወቅ አለብን። እነዚህ ነገሮች መሥራችና ፈጣሪ ካላቸው በቤተሰብ ኑሮ እንዴት ሙሉ በሙሉ መደሰት እንደምንችል ከማንም በላይ ሊያውቅ የሚችለው እርሱ ነው። ስለዚህ የቤተሰብ አባሎች መመሪያ ለማግኘት ፊታቸውን ወደ እርሱ ማዞር አለባቸው።

የሚገርመው ነገር የቤተሰብ ዝግጅት አንድም መሥራች የለውም ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ዚ ኢንሳይክሎፔዲያ አሜሪካና “አንዳንድ ምሁራን ከሰው በታች የሆኑት እንስሳት ጥንድ ጥንድ በመሆን የሚኖሩበትን ሁኔታ ተከትሎ የመጣ ነው ወደ ማለት አዘንብለዋል” ይላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ስለ ወንድና ሴት መፈጠር ተናግሯል። የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ እንደ ማስረጃ በመጥቀስ “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” ብሏል።—ማቴዎስ 19:4-6

ኢየሱስ ክርስቶስ አልተሳሳተም። የማሰብ ችሎታ ያለው አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ፈጠረና ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ አዘጋጀላቸው። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በጋብቻ አጣመራቸውና ሰው “በሚስቱ ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” አለ። (ዘፍጥረት 2:22-24) እንግዲያው በጊዜያችን ያሉት የቤተሰብ ችግሮች የተከሰቱት ሰዎች ፈጣሪ ያወጣቸውን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙትን መመሪያዎች የሚጻረር የአኗኗር ዘይቤ በመከተላቸው ይሆን?

ስኬታማነትን የሚያስገኘው መንገድ የትኛው ነው?

እርስዎም እንደሚያውቁት ዘመናዊው ዓለም የራስን ጥቅምና የራስን ደስታ ብቻ የማሳደድን መንፈስ የሚያራምድ ነው። “ስግብግብነት ጤናማ አካሄድ ነው” በማለት አንድ የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑ ሰው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከአንድ ኮሌጅ ለሚመረቁ ተማሪዎች ተናግረዋል። “ስግብግብ ሆናችሁ ስለ ራሳችሁ ጥሩ ግምት ሊኖራችሁ ይችላል” በማለት ባለሞያው አክለው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ንብረቶችን ማሳደድ ወደ ስኬታማ ኑሮ አይመራም። እንዲያውም ፍቅረ ነዋይ የቤተሰብን ኑሮ ለአደጋ ከሚያጋልጡት ዋና ዋና ነገሮች መካከል አንዱ ነው፤ ምክንያቱም በሰው ልጆች ዝምድና መካከል ሳንካ ይፈጥራል፤ የሰዎችን ጊዜና ገንዘብም ያሟጥጣል። በአንጻሩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ብቻ ደስታን ለማግኘት አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ መገንዘብ እንድንችል እንዴት እንደሚጠቁሙን ይመልከቱ።

“የጎመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።”

“ጥልና ክርክር በበዛበት ቤት በታላቅ ግብዣ ላይ ከመገኘት ይልቅ፣ ሰላም ባለበት ቤት ደረቅ የዳቦ ፍርፋሪ መመገብ ይሻላል።”

ምሳሌ 15:17፤ 17:1 የ1980 ትርጉም

ኃይለኛ አነጋገር ነው፤ አይደለም እንዴ? እያንዳንዱ ቤተሰብ ለእነዚህ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ዓለም ምንኛ የተለየች ትሆን እንደነበረ ይገምቱ! መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ አባሎች አንዳቸው ሌላውን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው የሚገልጽ ጠቃሚ መመሪያም ይሰጣል። መጽሐፉ ከሚሰጣቸው መመሪያዎች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ይመልከቱ።

ባሎች:- ‘እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል።’—ኤፌሶን 5:28-30

ቀላል ግን በጣም የሚሠራ መመሪያ ነው! በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ባል ‘ሚስቱን እንዲያከብር’ መመሪያ ይሰጣል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ይህን የሚያደርገው ርኅራኄን፣ አሳቢነትንና ማጽናኛን ጨምሮ ለሚስቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት ነው። በተጨማሪም ለምታቀርባቸው ሐሳቦች ከፍ ያለ ግምት ይሰጣል፤ የምትለውንም ይሰማል። (ከዘፍጥረት 21:12 ጋር አወዳድር።) ባልየው ሚስቱን ለእርሱ እንዲደረግለት በሚፈልገው መንገድ ትኩረት ሰጥቶ የሚይዛት ከሆነ የትኛውም ቤተሰብ ጥቅም ያገኛል ቢባል አይስማሙምን?—ማቴዎስ 7:12

ሚስቶች:- “ለባሎቻችሁ የጠለቀ አክብሮት አሳዩ።”—ኤፌሶን 5:33 NW

አንዲት ሚስት ባሏ ያሉበትን ከባድ ኃላፊነቶች እንዲወጣ በማገዝ ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። አምላክ ሚስትን ሲፈጥር ዓላማው “ረዳትና ማሟያ እንድትሆነው” ስለነበር ከአንዲት ሚስት የሚፈለገው ይህ ነው። (ዘፍጥረት 2:18 NW) አንዲት ሚስት የባልዋን ውሳኔዎች በመደገፍና የቤተሰቡን ግቦች ዳር ለማድረስ ከእርሱ ጋር በመተባበር አክብሮት ስታሳየው በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ የሚኖረውን በረከት መገመት ይችላሉን?

የትዳር ጓደኛሞች:- “ባልና ሚስት ታማኝነትን በማጉደል ጋብቻን አያርክሱ።”—ዕብራውያን 13:4 የ1980 ትርጉም

ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ሲሆኑ የቤተሰቡ ኑሮ እንደሚሻሻል አያጠራጥርም። ብዙውን ጊዜ ምንዝር ቤተሰብን ይበታትናል። (ምሳሌ 6:27-29, 32) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ጥበባዊ ምክር ይሰጣል:- “ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። . . . ስለ ምን ጋለሞታ ሴት ትወድዳለህ?”ምሳሌ 5:18-20

ወላጆች:- “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው።”—ምሳሌ 22:6

ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜና ትኩረት ሲሰጧቸው የቤተሰብ ኑሮ እንደሚሻሻል የታወቀ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ልጆቻቸውን ‘በቤት ሲቀመጡ፣ በመንገድ ሲሄዱ፣ ሲተኙና ሲነሡ’ ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲያስተምሯቸው ምክር ይሰጣል። (ዘዳግም 11:19) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ልጆቻቸውን በመገሠጽ ፍቅራቸውን ሊያሳዩአቸው እንደሚገባ ይናገራል።ኤፌሶን 6:4

ልጆች:- “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ።”—ኤፌሶን 6:1

እውነት ነው፣ በዚህ ሕገ ወጥነት በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ወላጆችህን መታዘዝ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ሆኖም የቤተሰብ መሥራች የሚለውን ማድረጉ ጥበብ ነው ቢባል አትስማማምን? የቤተሰባችንን ኑሮ ይበልጥ ደስታ የሰፈነበት ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ እርሱ ያውቃል። ስለዚህ ወላጆችህን ለመታዘዝ ከፍተኛ ጥረት አድርግ። መጥፎ እንድትሠራ ከሚገፋፉህ ብዙ የዓለም ፈተናዎች ለመሸሽ ቆራጥ አቋም ውሰድ።ምሳሌ 1:10-19

እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ሲያውል ከቤተሰብ ኑሮ ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ምንም አያጠራጥርም። ቤተሰቡ የተሻለ ሕይወት በማግኘት የሚደሰተው አሁን ብቻ አይደለም፤ አምላክ አመጣዋለሁ ብሎ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር አስደሳች የወደፊት ተስፋም ይኖረዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ላይ ማጥናትን የቤተሰባችሁ ልማድ አድርጉት! በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ የቀረበውን ምክር በእውነት ጥቅም የሚሰጥ ሆኖ አግኝተውታል።

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።