በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ዘጠኝ

“ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

አንድ ገበሬ አዝመራው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ብቻውን ሊሰበስበው ካልቻለ ምን ያደርጋል?

1-3. (ሀ) አንድ ገበሬ አዝመራው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ብቻውን ሊሰበስበው ካልቻለ ምን ያደርጋል? (ለ) ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት ምን ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? እንዴትስ ተወጣው?

 አንድ ገበሬ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል። የተወሰኑ ወራት ቀደም ብሎ መሬቱን አርሶ ዘር ዘርቷል። ከዚያም ገና ቡቃያው ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ማሳውን በትኩረት ሲከታተል ቆይቷል፤ አዝመራው መድረሱን በማየቱም በጣም ተደስቷል። አሁን አዝመራው የሚሰበሰብበት ጊዜ ስለደረሰ የድካሙን ዋጋ ሊያገኝ ነው። ሆኖም አንድ ያሳሰበው ነገር አለ፦ አዝመራው በጣም ብዙ ስለሆነ ብቻውን ሊሰበስበው አይችልም። ስለዚህ የተወሰኑ ሠራተኞችን ቀጥሮ ወደ እርሻው ለመላክ ወሰነ። ደግሞም የሚሳሳለትን አዝመራ ለመሰብሰብ ያለው ጊዜ አጭር ነው።

2 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የእውነትን ዘር ዘርቷል። አሁን አዝመራው የሚሰበሰብበት ጊዜ ደርሷል፤ ሰብሉ ደግሞ በጣም ብዙ ነው። መልእክቱን የተቀበሉ በርካታ ሰዎች የእሱ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መሰብሰብ አለባቸው። (ዮሐንስ 4:​35-38) ታዲያ ኢየሱስ ይህን ፈታኝ ሁኔታ የተወጣው እንዴት ነው? ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ በገሊላ ባለ ተራራ ላይ ደቀ መዛሙርቱን ሰበሰበና ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲፈልጉ ተልእኮ ሰጣቸው፤ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዘዛቸው።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

3 እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ቁልፉ ያለው እዚህ ተልእኮ ላይ ነው። እስቲ ሦስት ጥያቄዎችን እንመርምር። ኢየሱስ ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲፈልጉ ለደቀ መዛሙርቱ ተልእኮ የሰጣቸው ለምንድን ነው? ተጨማሪ ሠራተኞች ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተስ ያሠለጠናቸው እንዴት ነው? ይህ ተልእኮ እኛንም የሚመለከተው እንዴት ነው?

ተጨማሪ ሠራተኞች ያስፈለጉት ለምንድን ነው?

4, 5. ኢየሱስ የጀመረውን ሥራ ሊጨርሰው የማይችለው ለምንድን ነው? እሱ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ሥራውን በቀጣይነት የሚያከናውኑት እነማን ናቸው?

4 ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. አገልግሎቱን ሲጀምር ይህን ሥራ እሱ ራሱ ሊጨርሰው እንደማይችል ያውቅ ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ ምድርን ለቅቆ ይሄዳል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሊሸፍን የሚችለው ክልልም ሆነ የመንግሥቱን መልእክት ሊነግራቸው የሚችላቸው ሰዎች ብዛት ውስን ነው። በእርግጥ ኢየሱስ በዋነኝነት ይሰብክ የነበረው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ይኸውም ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ሰዎች ነው። (ማቴዎስ 15:​24) ይሁንና እነዚህ ‘የጠፉ በጎች’ የሚኖሩት በመላው የእስራኤል ግዛት ነው፤ ይህም ብዙ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ ምሥራቹ፣ በእርሻ በተመሰለው በመላው ዓለም መዳረስ ነበረበት።​—⁠ማቴዎስ 13:​38፤ 24:​14

5 ኢየሱስ እሱ ከሞተም በኋላ መሠራት ያለበት ብዙ ሥራ እንደሚቀር ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም 11ዱን ታማኝ ሐዋርያቱን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።” (ዮሐንስ 14:​12) ኢየሱስ ተመልሶ ወደ ሰማይ ስለሚሄድ ተከታዮቹ (ሐዋርያቱ ብቻ ሳይሆኑ የወደፊት ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ) የመስበኩንና የማስተማሩን ሥራ መቀጠል ነበረባቸው። (ዮሐንስ 17:​20) ኢየሱስ እነሱ የሚሠሩት ሥራ እሱ ከሚያከናውነው ‘የበለጠ’ እንደሚሆን በትሕትና አምኖ ተቀብሏል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በሦስት መንገዶች ነው።

6, 7. (ሀ) የኢየሱስ ተከታዮች የሚያከናውኑት ሥራ ከእሱ የሚበልጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ እምነት መጣሉ ተገቢ እንደነበር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

6 በመጀመሪያ ደረጃ የኢየሱስ ተከታዮች ከእሱ የበለጠ ክልል ይሸፍናሉ። በዛሬው ጊዜ የስብከት ሥራቸው ኢየሱስ ይሰብክበት ከነበረው ክልል አልፎ እስከ ምድር ዳር ድረስ ተዳርሷል። በሁለተኛ ደረጃ ከኢየሱስ የበለጠ ለብዙ ሰዎች ይሰብካሉ። ኢየሱስ ትቷቸው የሄደው ጥቂት ደቀ መዛሙርት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዝተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሆነዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:​41፤ 4:4) በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሆነዋል፤ በየዓመቱም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዲሶች ይጠመቃሉ። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ይሰብካሉ፤ ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነው ለሦስት ዓመት ተኩል ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ ግን ከ2,000 ዓመት ገደማ በኋላም በመስበክ ላይ ናቸው።

7 ኢየሱስ ተከታዮቹ “ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች” እንደሚሠሩ ሲናገር በእነሱ ላይ እምነት እንዳለው መግለጹ ነበር። እሱ ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሰጠውን ሥራ ይኸውም “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” የመስበኩንና የማስተማሩን ሥራ በአደራ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 4:​43) የሰጣቸውን ሥራ በታማኝነት ዳር እንደሚያደርሱት እርግጠኛ ነበር። ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? አገልግሎታችንን በቅንዓትና በሙሉ ልብ ስናከናውን ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ እምነት መጣሉ ተገቢ እንደነበር እናሳያለን። ታዲያ ይህ ትልቅ መብት አይደለም?​—⁠ሉቃስ 13:​24

ለስብከቱ ሥራ አሠልጥኗቸዋል

ፍቅር ሰዎች በሚገኙበት በማንኛውም ቦታ እንድንሰብክ ያነሳሳናል

8, 9. ኢየሱስ ከአገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ምን ምሳሌ ትቷል? እኛስ የእሱን አርዓያ ተከትለን አገልግሎታችንን ማከናወን የምንችለው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ግሩም የስብከት ሥልጠና ሰጥቷቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ግሩም ምሳሌ ሆኗቸዋል። (ሉቃስ 6:​40) ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ ለአገልግሎቱ ምን አመለካከት እንደነበረው ተመልክተናል። እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብለን ኢየሱስ ለስብከት ባደረገው ጉዞ አብረውት ስለነበሩት ደቀ መዛሙርት እናስብ። ኢየሱስ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ይኸውም በሐይቅ ዳርቻ፣ ተራራ ላይ፣ በየከተማው፣ በየገበያ ስፍራውና በየቤቱ ሲሰብክ ተመልክተዋል። (ማቴዎስ 5:1, 2፤ ሉቃስ 5:1-3፤ 8:1፤ 19:5, 6) በማለዳ ተነስቶ እስከ ማታ ድረስ በትጋት የሚሠራ ታታሪ ሠራተኛ መሆኑንም አይተዋል። አገልግሎቱ ለእሱ እንዲሁ ጊዜ ማሳለፊያ አልነበረም! (ሉቃስ 21:​37, 38፤ ዮሐንስ 5:​17) ኢየሱስ አገልግሎቱን እንዲያከናውን ያነሳሳው ለሰዎች ያለው ጥልቅ ፍቅር መሆኑን ደቀ መዛሙርቱ ማስተዋላቸው አይቀርም። ምናልባትም በልቡ ያለውን የርኅራኄ ስሜት ፊቱ ላይ አንብበው ሊሆን ይችላል። (ማርቆስ 6:​34) የኢየሱስ አርዓያ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳደረ ይመስልሃል? አንተ በእነሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ተጽዕኖ ያሳድርብህ ነበር?

9 የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን አገልግሎታችንን የምናከናውነው የእሱን አርዓያ ተከትለን ነው። በመሆኑም “በተሟላ ሁኔታ [ለመመሥከር]” ስንል የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። (የሐዋርያት ሥራ 10:​42) ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ከቤት ወደ ቤት እየሄድን እንሰብካለን። (የሐዋርያት ሥራ 5:​42) ሰዎች ቤት ሊገኙ በሚችሉበት ጊዜ ለማገልገል ስንል ፕሮግራማችንን እንደ አስፈላጊነቱ እናስተካክላለን። በተጨማሪም ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ቦታዎች ይኸውም መንገድ ላይ፣ በመናፈሻ ቦታ፣ በገበያ ስፍራና በሥራ ቦታ በጥበብ ለመመሥከር ጥረት እናደርጋለን። ይህን ሥራ በቁም ነገር ስለምንመለከተው “ጠንክረን በመሥራትና ብርቱ ጥረት በማድረግ” አገልግሎታችንን እናከናውናለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:​10) ለሌሎች ያለን ጥልቅ ፍቅር፣ ሰዎች በሚገኙበት በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለመመሥከር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እንድንፈልግ ያነሳሳናል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:8

‘ሰባዎቹ ደስ እያላቸው ተመለሱ’

10-12. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ከመላኩ በፊት ምን አስፈላጊ ቁም ነገሮች አስተምሯቸው ነበር?

10 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያሠለጠነበት ሌላም መንገድ አለ፤ ይህም ዝርዝር መመሪያዎችን መስጠት ነው። በመጀመሪያ 12 ሐዋርያቱን፣ በኋላ ደግሞ 70 ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት የላካቸው ሥልጠና ከሰጣቸው በኋላ ነው። (ማቴዎስ 10:1-15፤ ሉቃስ 10:​1-12) ሉቃስ 10:​17 “70ዎቹ ደስ እያላቸው ተመልሰው” እንደመጡ ስለሚገልጽ ሥልጠናው ጥሩ ውጤት አስገኝቶ ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ሁለት አስፈላጊ ቁም ነገሮች እስቲ እንመልከት፤ ይህን ስናደርግ ኢየሱስ የተናገራቸውን ነገሮች መረዳት ያለብን በዘመኑ ከነበረው የአይሁድ ባሕል አንጻር መሆኑን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።

11 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በይሖዋ እንዲታመኑ አስተምሯቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ወርቅ ወይም ብር አሊያም መዳብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ወይም ለጉዞ የምግብ ከረጢት ወይም ሁለት ልብስ ወይም ትርፍ ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።” (ማቴዎስ 10:9, 10) በዚያ ዘመን አንድ መንገደኛ መቀነቱ ላይ ገንዘብ መያዣ መታጠቁ እንዲሁም ስንቁን የሚይዝበት የምግብ ከረጢትና ትርፍ ጫማ መያዙ የተለመደ ነበር። a ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እነዚህ ነገሮች እንዳይጨነቁ መመሪያ ሰጥቷል፤ ይህን ሲል “ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኑ፤ እሱ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች ያሟላላችኋል” ማለቱ ነበር። ይሖዋ፣ ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎች ደቀ መዛሙርቱን በእንግድነት እንዲቀበሏቸው በማነሳሳት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያሟላላቸዋል፤ በወቅቱ እስራኤላውያን እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበራቸው።​—⁠ሉቃስ 22:​35

12 በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትኩረታቸውን የሚከፋፍሉ አላስፈላጊ ነገሮችን እንዲያስወግዱ አስተምሯቸዋል። “በመንገድም ላይ ቆማችሁ ከማንም ጋር ሰላምታ አትለዋወጡ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 10:4) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሰዎችን አይተው እንዳላዩ ሆነው እንዲያልፉ መናገሩ ነበር? በፍጹም። በዘመኑ የነበረው ሰላምታ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ነገር ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “በምሥራቁ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሰላምታ የሚለዋወጡት እኛ እንደምናደርገው በትንሹ አንገት ሰበር በማድረግ ወይም በመጨባበጥ አልነበረም፤ ሰላምታቸው ደጋግሞ መተቃቀፍንና ጎንበስ ቀና ማለትን እንዲሁም መሬት ላይ ተደፍቶ መስገድን ይጨምር ነበር። ይህ ሁሉ ረጅም ጊዜ ይወስዳል።” ታዲያ ኢየሱስ የተለመደውን ዓይነት ሰላምታ እንዳይሰጡ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው ምን ማለቱ ነበር? “የያዛችሁት መልእክት እጅግ አጣዳፊ ስለሆነ ጊዜያችሁን በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባል” ማለቱ ነበር። b

13. ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን መመሪያ በቁም ነገር እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን መመሪያዎች እኛም ልብ ልንላቸው ይገባል። አገልግሎታችንን ስናከናውን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንታመናለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥት እስከፈለግን’ ድረስ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ፈጽሞ እንደማናጣ እርግጠኞች ነን። (ማቴዎስ 6:​33) በምድር ዙሪያ ያሉ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪዎች፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያትም እንኳ የይሖዋ እጅ ፈጽሞ አጭር እንዳልሆነ ሊመሠክሩ ይችላሉ። (መዝሙር 37:​25) በተጨማሪም ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን። ካልተጠነቀቅን ይህ ሥርዓት በቀላሉ ትኩረታችንን ሊሰርቅብን ይችላል። (ሉቃስ 21:​34-36) ይሁንና ያለንበት ጊዜ ትኩረታችን እንዲከፋፈል የምንፈቅድበት አለመሆኑን እናስታውስ። የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ስለሆነ መልእክታችን አጣዳፊ ነው። (ሮም 10:​13-15) ምንጊዜም የጥድፊያ ስሜታችንን የምንጠብቅ ከሆነ ይህ ዓለም የሚያቀርባቸው ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ለአገልግሎቱ ልናውለው የሚገባንን ጊዜና ጉልበት እንዲሻሙብን አንፈቅድም። የቀረን ጊዜ አጭር፣ አዝመራው ደግሞ ብዙ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም።​—⁠ማቴዎስ 9:​37, 38

ለእኛም ጭምር የተሰጠ ተልእኮ

14. በማቴዎስ 28:​18-20 ላይ የሚገኘው ተልእኮ ሁሉንም የክርስቶስ ተከታዮች እንደሚመለከት የሚያሳየው ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

14 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ” በማለት ለተከታዮቹ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይህን የተናገረው በዚያ ቀን በገሊላ ባለ ተራራ ላይ የነበሩትን ደቀ መዛሙርት ብቻ በአእምሮው ይዞ አይደለም። c ኢየሱስ የሰጠው ይህ ሥራ ‘በሁሉም ብሔራት ውስጥ ላሉ ሰዎች’ መስበክ የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” የሚቀጥል ነው። እንግዲያው ይህ ተልእኮ በዛሬው ጊዜ የምንገኘውን እኛን ጨምሮ ሁሉንም የክርስቶስ ተከታዮች እንደሚመለከት ግልጽ ነው። በማቴዎስ 28:​18-20 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ በጥልቀት እንመርምር።

15. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠውን ትእዛዝ መታዘዛችን ብልህነት የሆነው ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ተልእኮውን ከመስጠቱ በፊት “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ብሏል። (ቁጥር 18) በእርግጥ ኢየሱስ ይህን ያህል ከፍተኛ ሥልጣን አለው? እንዴታ! ኢየሱስ እልፍ አእላፋት መላእክትን የሚያዝ የመላእክት አለቃ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:​16፤ ራእይ 12:7) ‘የጉባኤው ራስ’ እንደመሆኑ መጠን በምድር ባሉ ተከታዮቹ ላይ ሥልጣን አለው። (ኤፌሶን 5:​23) ከ1914 አንስቶ በሰማይ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ይገኛል። (ራእይ 11:​15) የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ኃይል ስላለው ሥልጣኑ በመቃብር ባሉትም ላይ ሳይቀር ይሠራል። (ዮሐንስ 5:​26-28) ኢየሱስ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳለው አስቀድሞ የገለጸው ከዚያ ቀጥሎ ለሚናገረው ሐሳብ ክብደት ለመስጠት ነው፤ ትእዛዝ እያስተላለፈ እንጂ እንዲሁ ሐሳብ እያቀረበ አለመሆኑን ይጠቁማል። ይህ ሥልጣን ኢየሱስ በራሱ ያገኘው ሳይሆን ከአምላክ የተቀበለው ስለሆነ እሱን መታዘዛችን ብልህነት ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​27

16. ኢየሱስ “ሂዱ” ሲለን ምን እንድናደርግ እያዘዘን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

16 ቀጥሎም ኢየሱስ ለተከታዮቹ ተልእኮ ሰጣቸው፤ “ሂዱ” አላቸው። (ቁጥር 19) ኢየሱስ ይህን ማለቱ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ለማድረስ እኛ ቅድሚያውን መውሰድ እንዳለብን ያመለክታል። ይህን ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል። ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ቀርበን ለማነጋገር ከሁሉ በላይ ውጤታማ የሆነው ዘዴ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:​20) መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምንመሠክርባቸውን አጋጣሚዎችም እንፈልጋለን፤ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን አመቺ ሆኖ ባገኘነው ጊዜ ሁሉ ጭውውት ለመጀመርና ምሥራቹን በዘዴ ለመንገር ንቁ ነን። ለመስበክ የምንጠቀምበት ዘዴ እንደየአካባቢው ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። ይሁንና አንድ የማይለወጥ ነገር አለ፤ የትም እንኑር የት መልእክቱ የሚገባቸውን ሰዎችን ለመፈለግ ‘እንሄዳለን።’ ​—⁠ማቴዎስ 10:​11

17. ሰዎችን ‘ደቀ መዛሙርት የምናደርገው’ እንዴት ነው?

17 በመቀጠል ኢየሱስ የተልእኮውን ዓላማ ገለጸ፤ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” አለ። (ቁጥር 19) ‘ደቀ መዛሙርት የምናደርገው’ እንዴት ነው? በመሠረቱ ደቀ መዝሙር ማለት ተማሪ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርት ማድረግ ሲባል እውቀት ማካፈል ማለት ብቻ አይደለም። ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና ግባችን የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ መርዳት ነው። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እሱ የተወውን ምሳሌ ጎላ አድርገን እንገልጻለን፤ ዓላማችን፣ የምናስጠናቸው ሰዎች ኢየሱስን አስተማሪያቸውና አርዓያቸው አድርገው እንዲመለከቱት ይኸውም በአኗኗራቸው እንዲመስሉትና እሱ የሠራውን ሥራ እንዲሠሩ መርዳት ነው።​—⁠ዮሐንስ 13:​15

18. ጥምቀት በአንድ ደቀ መዝሙር ሕይወት ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው?

18 “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው” የሚለው ሐሳብ የተልእኮውን አብይ ገጽታ ይገልጻል። (ቁጥር 19) ጥምቀት በአንድ ደቀ መዝሙር ሕይወት ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው እርምጃ ነው፤ ምክንያቱም በሙሉ ልቡ ራሱን ለአምላክ መወሰኑን የሚያሳይ ክንውን ነው። በመሆኑም ጥምቀት ለመዳን እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። (1 ጴጥሮስ 3:​21) አዎ፣ አንድ የተጠመቀ ደቀ መዝሙር ይሖዋን ለማገልገል የተቻለውን ሁሉ እስካደረገ ድረስ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ማለቂያ የሌለው በረከት እንደሚያገኝ መጠበቅ ይችላል። የተጠመቀ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን የረዳኸው ሰው አለ? በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ከዚህ የበለጠ የሚያስደስት ነገር የለም።​—⁠3 ዮሐንስ 4

19. አዲሶችን ምን ነገሮች እናስተምራቸዋለን? ከተጠመቁ በኋላም ማስተማራችንን መቀጠላችን አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ የተልእኮውን ቀጣይ ክፍል ሲገልጽ “ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው” ብሏል። (ቁጥር 20) አዳዲስ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ እናስተምራለን፤ የኢየሱስ ትእዛዝ አምላክንና ባልንጀራን መውደድን እንዲሁም ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግን ይጨምራል። (ማቴዎስ 22:​37-39) ከዚህም ሌላ ጥናቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማብራራት እንዲሁም ስለ እምነታቸው መልስ መስጠት እንዲችሉ ደረጃ በደረጃ እናስተምራቸዋለን። በመደበኛ የስብከት እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ሲፈቀድላቸው ደግሞ አብረናቸው እናገለግላለን፤ በዚህ ሥራ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ በቃልም ሆነ ምሳሌ በመሆን እናሠለጥናቸዋለን። አዲስ ደቀ መዛሙርትን የማስተማሩ ሥራ የግድ ከመጠመቃቸው በፊት መጠናቀቅ አለበት ማለት አይደለም። ክርስቶስን ሲከተሉ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንዲችሉ ከተጠመቁ በኋላም ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆናል።​—⁠ሉቃስ 9:​23, 24

“እኔ . . . ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”

20, 21. (ሀ) ኢየሱስ የሰጠንን ተልእኮ በምንወጣበት ጊዜ መፍራት የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) አሁን የጥድፊያ ስሜታችን የሚቀዘቅዝበት ጊዜ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን አለበት?

20 ኢየሱስ የሰጠውን ተልእኮ የደመደመበት ሐሳብ በጣም የሚያበረታታ ነው፦ “እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 28:​20) ኢየሱስ ይህ ሥራ ከባድ መሆኑን ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ይህን ሥራ ስናከናውን አንዳንድ ጊዜ ተቃውሞ ሊያጋጥመን እንደሚችል ያውቃል። (ሉቃስ 21:​12) ይሁንና የምንፈራበት ምክንያት የለም። መሪያችን ይህን ሥራ ያለማንም እርዳታ ወይም ብቻችንን እንድናከናውን አይጠብቅብንም። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው ኢየሱስ ከእኛ ጋር ነው፤ ይህን ተልእኮ ዳር ለማድረስ ስንጥር ከጎናችን ሆኖ እንደሚረዳን ማወቃችን አያጽናናም?

21 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” ከእነሱ ጋር እንደሚሆን ዋስትና ሰጥቷቸዋል። መጨረሻው እስከሚመጣ ድረስ ኢየሱስ የሰጠንን ተልእኮ መወጣታችንን መቀጠል አለብን። አሁን የጥድፊያ ስሜታችን የሚቀዘቅዝበት ጊዜ አይደለም። ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ የመከር ሥራ እየተካሄደ ነው! መልእክቱን የሚቀበሉ በርካታ ሰዎች በመሰብሰብ ላይ ናቸው። እንግዲያው የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን በአደራ የተሰጠንን ከባድ ተልእኮ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። “ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን የክርስቶስ ትእዛዝ ለመፈጸም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እንዲሁም ጥሪታችንን ለመስጠት ቆርጠን እንነሳ።

a በዘመኑ ሰዎች ሳንቲሞቻቸውን በመቀነት ይታጠቁ ነበር። የምግብ ከረጢት የተባለው ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከቆዳ የሚሠራና በትከሻ ላይ የሚነገት ትልቅ ቦርሳ ነው፤ ምግብ ወይም ለስንቅ የሚሆን ሌላ ነገር ለመያዝ ያገለግላል።

b ነቢዩ ኤልሳዕ በአንድ ወቅት ተመሳሳይ መመሪያ ሰጥቷል። አገልጋዩን ግያዝን ልጇ ወደሞተባት ሴት ቤት በላከው ጊዜ “መንገድ ላይ ሰው ብታገኝ ሰላም አትበል” ብሎት ነበር። (2 ነገሥት 4:​29) ተልእኮው አጣዳፊ ስለነበር አላስፈላጊ በሆነ ነገር መዘግየት አልነበረበትም።

c አብዛኞቹ ተከታዮቹ ያሉት በገሊላ ነበር፤ በመሆኑም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች” የታየው በማቴዎስ 28:​16-20 ላይ የተገለጸው ሁኔታ በተከናወነበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮንቶስ 15:6) በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልእኮ በሰጠበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቹ በቦታው ተገኝተው ሊሆን ይችላል።