በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ አንድ

“ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም”

“ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም”

1, 2. (ሀ) ኢየሱስን እንዲይዙ የተላኩት ጠባቂዎች ባዶ እጃቸውን የተመለሱት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የተዋጣለት አስተማሪ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?

 ፈሪሳውያን እጅግ ተቆጥተዋል። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስለ አባቱ እያስተማረ ነው። ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ለሁለት ተከፍለዋል፤ ብዙዎቹ በኢየሱስ አምነዋል፤ አንዳንዶቹ ግን እንዲታሰር ፈልገዋል። ቁጣቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን እንዲይዙት የቤተ መቅደሱን ጠባቂዎች ላኳቸው። ጠባቂዎቹ ግን ባዶ እጃቸውን ተመለሱ። የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያኑ “ለምን ይዛችሁት አልመጣችሁም?” በማለት አፋጠጧቸው። ጠባቂዎቹም “ማንም እንደዚህ ሰው ተናግሮ አያውቅም” ብለው መለሱ። ጠባቂዎቹ በኢየሱስ ትምህርት እጅግ ከመደነቃቸው የተነሳ እሱን ለማሰር አልደፈሩም። a​—⁠ዮሐንስ 7:​45, 46

2 በኢየሱስ ትምህርት የተደነቁት እነዚህ ጠባቂዎች ብቻ አልነበሩም። እሱ ሲያስተምር ለመስማት በጣም ብዙ ሰው ይሰበሰብ ነበር። (ማርቆስ 3:7, 9፤ 4:1፤ ሉቃስ 5:1-3) ኢየሱስ እንዲህ የተዋጣለት አስተማሪ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? ምዕራፍ 8 ላይ እንደተመለከትነው የሚያስተምረውን እውነትና የሚያስተምራቸውን ሰዎች ይወድ ነበር። በተጨማሪም የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ረገድ የተካነ ነበር። እስቲ ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን ሦስት ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎች እንዲሁም እነዚህን ዘዴዎች እንዴት መኮረጅ እንደምንችል እንመልከት።

በቀላሉ የሚገባ

3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ሲያስተምር ለመረዳት የማይከብዱ አገላለጾችን የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ለ) የተራራው ስብከት ኢየሱስ ቀለል ባለ መንገድ ያስተምር እንደነበር የሚያሳየው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ካለው እውቀት አንጻር ምን ያህል ከባድ ቃላትን ሊጠቀም እንደሚችል መገመት ትችላለህ? ያም ሆኖ ያስተማረው አድማጮቹ በቀላሉ ሊረዱ በሚችሉበት መንገድ ነው፤ ከአድማጮቹ ብዙዎቹ “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” መሆናቸውን ግምት ውስጥ አስገብቷል። (የሐዋርያት ሥራ 4:​13) ለአድማጮቹ ያስብላቸው ነበር፤ የመረዳት ችሎታቸውን ስለሚያስተውል የመረጃ ናዳ አላወረደባቸውም። (ዮሐንስ 16:​12) የመልእክቱን ክብደት ሳይቀንስ ቀላል ቃላትን ይጠቀም ነበር።

4 በማቴዎስ 5:3 እስከ 7:​27 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የተራራውን ስብከት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ በዚህ የተራራ ስብከት ላይ ጥልቀት ያላቸው ነገሮችን ተናግሯል። ሆኖም የተወሳሰቡ ሐሳቦችን ወይም አገላለጾችን አልተጠቀመም። የተናገራቸው ነገሮች ትንሽ ልጅ እንኳ በቀላሉ ሊረዳቸው የሚችሉ ናቸው! በእርግጥም ኢየሱስ ንግግሩን ሲጨርስ ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች (አብዛኞቹ ገበሬዎች፣ እረኞችና ዓሣ አጥማጆች ሳይሆኑ አይቀሩም) “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [መደነቃቸው]” ምንም አያስገርምም።​—⁠ማቴዎስ 7:​28

5. ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው ቀላል ሆኖም ጥልቅ ትርጉም ያላቸው አገላለጾች መካከል አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

5 ኢየሱስ ጥልቅ ትርጉም ያላቸውን ሐሳቦች ቀላልና አጫጭር አገላለጾች በመጠቀም ያስተምር ነበር። በዚያ ዘመን አድማጮቹ የተናገረውን ነገር መልሰው ሊያነብቡት ስለማይችሉ ትምህርቱ በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ በማይፋቅ ሁኔታ እንዲታተም አድርጓል። እስቲ አንዳንዶቹን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ።” “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።” “መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ።” “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” b (ማቴዎስ 7:1፤ 9:​12፤ 26:​41፤ ማርቆስ 12:​17፤ የሐዋርያት ሥራ 20:​35) የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ የተነገሩት እነዚህ አባባሎች ዛሬም ትልቅ ትርጉም አላቸው።

6, 7. (ሀ) ሰዎች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ ቃላትን መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ለምናስጠናው ሰው በአንድ ጊዜ ብዙ መረጃዎችን ከመስጠት መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

6 እኛስ በቀላሉ በሚገባ መንገድ ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ ቁልፍ፣ ብዙ ሰዎች በቀላሉ የሚረዱት ውስብስብ ያልሆነ አነጋገር መጠቀም ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ እውነቶች ውስብስብ አይደሉም። ይሖዋ ዓላማውን የገለጸው ቅን ለሆኑና ትሑት ልብ ላላቸው ሰዎች ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:​26-28) የአምላክን ቃል ቀላል በሆነ መንገድ እንዴት እንደምናስረዳ ካሰብንበት ለመረዳት በማይከብድ መንገድ መልእክቱን ማስተላለፍ እንችላለን።

በቀላሉ በሚገባ መንገድ አስተምር

7 በቀላሉ በሚገባ መንገድ ለማስተማር፣ ለጥናታችን በአንድ ጊዜ ብዙ መረጃ ከመስጠት መቆጠብ ይኖርብናል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ማብራራት የለብንም፤ ብዙ ትምህርት ለመጨረስ መጣደፍም ተገቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥናቱን የምንመራበትን ፍጥነት የሚወስነው ተማሪው የሚያስፈልገው ነገርና ችሎታው ሊሆን ይገባል። ግባችን ተማሪው የክርስቶስ ተከታይና የይሖዋ አምላኪ እንዲሆን መርዳት ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ተማሪው የሚማረውን ነገር መረዳት እንዲችል በቂ ጊዜ መስጠት ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልቡን ሊነካውና ለተግባር ሊያንቀሳቅሰው የሚችለው ይህን ስናደርግ ብቻ ነው።​—⁠ሮም 12:2

ጥያቄዎችን ጥሩ አድርጎ መጠቀም

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ጥያቄዎችን ይጠይቅ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) የቤተ መቅደሱን ግብር መክፈልን በተመለከተ ጴጥሮስ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ለመርዳት ኢየሱስ በጥያቄዎች የተጠቀመው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በጥያቄዎች ግሩም በሆነ መንገድ ይጠቀም ነበር። ሊናገር የፈለገውን ቁም ነገር ለአድማጩ በቀጥታ መናገሩ ጊዜ ሊቆጥብለት የሚችል ቢሆንም በጥያቄ የሚጠቀመው ለምን ነበር? አንዳንድ ጊዜ የተቃዋሚዎቹን ውስጣዊ ዝንባሌ ለማጋለጥ ጥያቄ ይጠይቅ ነበር፤ በዚህ መንገድ ተቃዋሚዎቹን አፋቸውን አስይዟቸዋል። (ማቴዎስ 21:​23-27፤ 22:​41-46) ብዙውን ጊዜ ግን ጥያቄ የሚጠይቀው ደቀ መዛሙርቱ የሚያስቡትን ነገር በግልጽ እንዲናገሩ ለማነሳሳት እንዲሁም ስለ አንድ ጉዳይ በጥልቀት እንዲያስቡ ለማድረግ ነበር። ስለሆነም “ምን ይመስላችኋል?” እና “ይህን ታምኛለሽ?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቋቸዋል። (ማቴዎስ 18:​12፤ ዮሐንስ 11:​26) ኢየሱስ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የደቀ መዛሙርቱን ልብ መንካት ችሏል። እስቲ አንድ ምሳሌ ተመልከት።

9 በአንድ ወቅት ግብር ሰብሳቢዎች ጴጥሮስን፣ ኢየሱስ የቤተ መቅደሱን ግብር ይከፍል እንደሆነ ጠየቁት። c ጴጥሮስም “ይከፍላል” ሲል ወዲያውኑ መለሰላቸው። በኋላ ላይ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ስምዖን ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች?” ጴጥሮስም “ከሌሎች” ብሎ መለሰ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እንግዲያው ልጆቹ ግብር ከመክፈል ነፃ ናቸው” አለው። (ማቴዎስ 17:​24-27) የነገሥታት ቤተሰቦች ከግብር ነፃ መሆናቸው ይታወቅ ስለነበር ጴጥሮስ ጥያቄዎቹ የያዙትን ቁም ነገር እንደተገነዘበ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚመለከው ሰማያዊ ንጉሥ አንድያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ግብር የመክፈል ግዴታ አልነበረበትም። ኢየሱስ ጥያቄዎችን እንዴት በዘዴ እንደተጠቀመ ልብ አልክ? ለጴጥሮስ መልሱን በቀጥታ ከመንገር ይልቅ ጴጥሮስ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ረድቶታል፤ ምናልባትም ለወደፊቱ መልስ ከመስጠቱ በፊት ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበትም አስገንዝቦታል።

የቤቱን ባለቤት ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎችን ጠይቅ

10. ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

10 በአገልግሎታችን ላይ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ የቤቱን ባለቤት ፍላጎት ለመቀስቀስ ጥያቄዎችን መጠቀም እንችላለን፤ ይህም ምሥራቹን ለመናገር አጋጣሚ ሊከፍትልን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በሩን የከፈቱልን ሰው አረጋዊ ከሆኑ “በእርስዎ የሕይወት ዘመን በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ምን ያህል ተለውጧል?” ብለን በአክብሮት ልንጠይቃቸው እንችላለን። ሐሳባቸውን ካዳመጥን በኋላ “ይህ ዓለም የተሻለ እንዲሆን ምን መደረግ የሚችል ይመስልዎታል?” የሚል ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:9, 10) በሩን የከፈተችልን፣ ሕፃናት ልጆች ያሏት እናት ከሆነች “ልጆችሽ ሲያድጉ ይህ ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል አስበሽ ታውቂያለሽ?” ብለን ልንጠይቃት እንችላለን። (መዝሙር 37:​10, 11) አንድን ቤት ስናንኳኳ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ የምናስተውል ከሆነ የቤቱን ባለቤት ፍላጎት ያገናዘበ ጥያቄ ማንሳት እንችላለን።

11. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ጥያቄዎችን ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራስ ጥያቄዎችን ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? በጥንቃቄ የተመረጡ ጥያቄዎች በተማሪው ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ቀድቶ ለማውጣት ያስችሉናል። (ምሳሌ 20:5) ለምሳሌ ያህል፣ ለዘላለም በደስታ ኑር!  d ከተባለው መጽሐፍ ላይ “ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?” የሚለውን ምዕራፍ 43⁠ን እያስጠናን ነው እንበል። ይህ ምዕራፍ ከልክ በላይ ስለ መጠጣትና ስለ ስካር አምላክ ምን አመለካከት እንዳለው ያብራራል። ተማሪው የሚሰጠው ምላሽ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር እንደተገነዘበ ሊጠቁም ይችላል፤ ሆኖም ጥናታችን የተማረውን ነገር ያምንበታል? ይህን ለማወቅ “አምላክ ለእነዚህ ነገሮች ያለው አመለካከት ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማሃል?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። በተጨማሪም “ይህን ትምህርት አንተ በሕይወትህ ልትሠራበት የምትችለው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ ልናቀርብለት እንችላለን። ይሁንና ጥያቄዎቹን የምናነሳው ደግነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሊሆን ይገባል። የሚያሸማቅቁት ጥያቄዎች መጠየቅ የለብንም።​—⁠ምሳሌ 12:​18

አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት

12-14. (ሀ) ኢየሱስ አሳማኝ በሆነ መንገድ የማስረዳት ችሎታውን የተጠቀመው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) ፈሪሳውያን ኢየሱስ ኃይሉን ያገኘው ከሰይጣን እንደሆነ በተናገሩበት ጊዜ ኢየሱስ ምን ኃይለኛ ነጥብ አንስቷል?

12 ኢየሱስ ፍጹም አእምሮ ያለው እንደመሆኑ መጠን አሳማኝ ነጥቦችን በማቅረብ ረገድ የተዋጣለት ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ ተቃዋሚዎቹ የሚሰነዝሩበት ክስ ሐሰት መሆኑን አሳማኝ በሆነ መንገድ ያሳይ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ለተከታዮቹ ጠቃሚ ቁም ነገር ለማስጨበጥ አሳማኝ ማብራሪያዎችን ተጠቅሟል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

13 ኢየሱስ ጋኔን ያደረበትን ዓይነ ስውርና ዲዳ ሰው ከፈወሰ በኋላ ፈሪሳውያኑ “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል [በሰይጣን] ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” የሚል ክስ ሰንዝረውበት ነበር። ፈሪሳውያን አጋንንትን ለማስወጣት ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንደሚያስፈልግ አምነዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ኃይል ያገኘው ከሰይጣን እንደሆነ አድርገው ተናገሩ። ይህ ክስ ውሸት ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊም አልነበረም። ኢየሱስ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ መሆኑን ለማጋለጥ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጠ፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም። በተመሳሳይም ሰይጣን ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ታዲያ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል?” (ማቴዎስ 12:​22-26) ኢየሱስ “እናንተ እንደምትሉት እኔ የሰይጣንን ሥራ የማፈርስ የሰይጣን ወኪል ከሆንኩ ሰይጣን የራሱን ዓላማ የሚቃረን ነገር እያደረገ ነው ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ብዙም ሳይቆይ ለውድቀት ይዳረጋል” ያለ ያህል ነበር። ታዲያ እንዲህ ያለውን ምክንያታዊ ሐሳብ በምን ሊያስተባብሉት ይችላሉ?

14 ኢየሱስ በዚህ አላበቃም። ከራሳቸው ከፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ አጋንንት እንደሚያስወጡ ያውቅ ስለነበር “እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ [ወይም ደቀ መዝሙሮቻችሁ] የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው?” በማለት ቀላል ሆኖም ኃይለኛ መልእክት ያዘለ ጥያቄ አቀረበላቸው። (ማቴዎስ 12:​27) ኢየሱስ “እኔ አጋንንትን የማስወጣው በሰይጣን ኃይል ከሆነ የእናንተም ደቀ መዛሙርት የሚጠቀሙት ይህንኑ ኃይል ነው” ያላቸው ያህል ነበር። ፈሪሳውያን ለዚህ ምን ምላሽ መስጠት ይችላሉ? መቼም ፈሪሳውያኑ፣ ደቀ መዝሙሮቻቸው ይህን የሚያደርጉት በሰይጣን ኃይል መሆኑን አምነው እንደማይቀበሉ ግልጽ ነው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ያቀረቡት የመከራከሪያ ሐሳብ የተሳሳተ መሆኑን ግልጽ አደረገ። ኢየሱስ ለእነሱ መልስ ለመስጠት ስለተጠቀመበት ዘዴ ማንበቡ ብቻ እንኳ አያስደስትም? ኢየሱስ ይህን ሲናገር በቦታው የተገኙት ሰዎች ደግሞ ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል ገምት፤ የተናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን ያስረዳበት መንገድም ለመልእክቱ ይበልጥ ክብደት እንደሚሰጠው እሙን ነው።

15-17. ኢየሱስ ስለ አባቱ ልብ የሚነኩ እውነቶችን ለማስተማር “እንዴት አብልጦ” የሚለውን አባባል እንዴት እንደተጠቀመ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

15 ኢየሱስ ስለ አባቱ የሚገልጹ የሚያጽናኑና ማራኪ እውነቶችን ለማስተማር ምክንያታዊ የሆኑ አሳማኝ ነጥቦችን ተጠቅሟል። ብዙውን ጊዜ ይህን የሚያደርገው “እንዴት አብልጦ” የሚለውን አባባል በመጠቀም ነበር፤ ይህም አድማጮቹ እውነታውን ከመቀበል አልፈው በዚያ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት አስችሎታል። e በንጽጽር የሚቀርበው እንዲህ ያለው ትምህርት በአእምሮ ውስጥ ተቀርጾ ይቀራል። እስቲ አንድ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

16 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን’ በማለት ላቀረቡለት ጥያቄ እንዴት ምላሽ እንደሰጠ እንመልከት፤ ፍጹማን ያልሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው “መልካም ስጦታ መስጠት” እንደሚፈልጉ ከተናገረ በኋላ እንዲህ በማለት ደመደመ፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ሉቃስ 11:1-13) ኢየሱስ ነጥቡን ያስረዳው በንጽጽር ነው። ኃጢአተኛ የሆኑ ሰብዓዊ ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት የሚያሟሉ ከሆነ ፍጹምና በሁሉም ረገድ ጻድቅ የሆነው የሰማዩ አባታችን በትሕትና ወደ እሱ ለሚጸልዩት ታማኝ አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!

17 ኢየሱስ ጭንቀትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ጥበብ ያዘለ ምክር ሲሰጥ ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። እንዲህ አለ፦ “ቁራዎች . . . አይዘሩም፣ አያጭዱም እንዲሁም የእህል ማከማቻ ወይም ጎተራ የላቸውም፤ ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ የላቀ ዋጋ የላችሁም? እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፦ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ . . . አምላክ ዛሬ ያለውንና ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን በሜዳ ያለ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ!” (ሉቃስ 12:​24, 27, 28) ይሖዋ ወፎችንና አበቦችን እንኳ እንዲህ የሚንከባከብ ከሆነ እሱን የሚወዱትንና የሚያመልኩትን ሰዎችማ ምን ያህል ይንከባከባቸው! ኢየሱስ እንዲህ ያለ አሳማኝ የሆነ ሐሳብ በማቅረብ የአድማጮቹን ልብ መንካት እንደቻለ ጥርጥር የለውም።

18, 19. አንድ ሰው ‘በማላየው አምላክ አላምንም’ ቢለን በምን መንገድ መልስ ልንሰጠው እንችላለን?

18 እኛም በአገልግሎታችን የሐሰት ትምህርቶችን ውድቅ ለማድረግ ምክንያታዊ የሆኑ ሐሳቦችን ማቅረብ እንፈልጋለን። በተጨማሪም ይሖዋ አፍቃሪና ስለ እነሱ የሚያስብ አምላክ መሆኑን ለሰዎች ስናስተምር አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንፈልጋለን። (የሐዋርያት ሥራ 19:8፤ 28:​23, 24) ታዲያ እንዲህ ሲባል የተራቀቀ ማብራሪያ ማቅረብ ይጠበቅብናል ማለት ነው? በፍጹም! ብዙውን ጊዜ ቀለል ባለ መንገድ የሚቀርቡ አሳማኝ ነጥቦች ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኙ ከኢየሱስ እንማራለን።

19 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ‘በማላየው አምላክ አላምንም’ ቢለን በምን መንገድ መልስ ልንሰጠው እንችላለን? የምክንያትንና የውጤትን ተፈጥሯዊ ሕግ ተጠቅመን ልናስረዳው እንችላለን። አንድን ውጤት ስንመለከት ለዚያ ነገር መገኘት ምክንያት የሆነ ነገር እንዳለ አምነን እንቀበላለን። እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ “ሰው በሌለበት ራቅ ያለ አካባቢ፣ በሚያምር መንገድ የተሠራና በውስጡ የተትረፈረፈ ምግብ የተቀመጠበት ቤት (ውጤት) ብታገኝ ይህን ቤት የሠራና ምግቡን ያስቀመጠ ሰው (ምክንያት) እንዳለ ማመንህ ይቀራል? በተመሳሳይም በአካባቢያችን የሚገኙ ነገሮች የተሠሩበትን ንድፍና በምድር ‘ጓዳ’ ውስጥ የሚገኘውን ምግብ (ውጤት) ስንመለከት እነዚህን ነገሮች የሠራ አንድ አካል (ምክንያት) እንዳለ ማመናችን ተገቢ አይሆንም? መጽሐፍ ቅዱስም ‘እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው’ ይላል።” (ዕብራውያን 3:4) በእርግጥ የምናቀርበው ማስረጃ የቱንም ያህል አሳማኝ ቢሆን ሁሉም ሰው ይቀበለዋል ማለት አይደለም።​—⁠2 ተሰሎንቄ 3:2

የግለሰቡን ልብ ለመንካት አሳማኝ በሆነ መንገድ አስተምር

20, 21. (ሀ) “እንዴት አብልጦ” የሚለውን አባባል ተጠቅመን አሳማኝ በሆነ መንገድ የይሖዋን ባሕርያት ጎላ አድርገን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?

20 በመስክ አገልግሎትም ሆነ በጉባኤ ስናስተምር የይሖዋን ባሕርያትና ሥራዎች ጎላ አድርገን ለመግለጽ “እንዴት አብልጦ” የሚለውን አባባል በመጠቀም አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በገሃነመ እሳት ለዘላለም ስለ መሠቃየት የሚገልጸው ሃይማኖታዊ ትምህርት ይሖዋን የማያስከብር መሆኑን ለማሳየት እንዲህ ልንል እንችላለን፦ “ለመሆኑ የልጁን እጅ በእሳት እየለበለበ ልጁን የሚቀጣ አፍቃሪ አባት ይኖራል? ታዲያ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ማቃጠል የሚለው ሐሳብ በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን እንዴት ይበልጥ አይዘገንነው!” (ኤርምያስ 7:​31) በመንፈስ ጭንቀት የተዋጠ የእምነት ባልንጀራችንን ይሖዋ እንደሚወደው ለማሳመን እንዲህ ልንል እንችላለን፦ “አንዲት ትንሽ ድንቢጥ እንኳ በይሖዋ ፊት ትልቅ ዋጋ ካላት ይሖዋ አንተን ጨምሮ በምድር ላይ ላለ ለእያንዳንዱ ታማኝ አገልጋዩ እንዴት አብልጦ አያስብለት! እንዴትስ አብልጦ አይወደው!” (ማቴዎስ 10:​29-31) እንዲህ ያለው አሳማኝ የማስተማሪያ መንገድ የሌሎችን ልብ ለመንካት ያስችለናል።

21 ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል እስካሁን የተመለከትነው ሦስቱን ብቻ ነው፤ ይህም እንኳ ኢየሱስን ሳይዙት የተመለሱት ጠባቂዎች “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ እንዳላጋነኑ ለመገንዘብ አስችሎናል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ደግሞ ኢየሱስ ይበልጥ ስለሚታወቅበት የማስተማሪያ ዘዴ ይኸውም ምሳሌዎችን ስለመጠቀም እንመረምራለን።

a የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ በሊቀ ካህናቱ ሥልጣን ሥር ሆነው ለሳንሄድሪን የሚሠሩ ሳይሆኑ አይቀሩም።

b መጨረሻ ላይ የተጠቀሰውን በሐዋርያት ሥራ 20:​35 ላይ የሚገኘውን አባባል ያሰፈረው ሐዋርያው ጳውሎስ ብቻ ነው። ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው በቃል ተነግሮት (ማለትም ኢየሱስ ይህን ሲናገር የሰማ ሰው ወይም ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ራሱ ነግሮት) አሊያም በመለኮታዊ ራእይ ተገልጦለት ሊሆን ይችላል።

c አይሁዳውያን በየዓመቱ ሁለት ድራክማ (የሁለት ቀን ደሞዝ ይሆናል) ለቤተ መቅደስ ግብር እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸው ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ግብር በዋነኝነት የሚውለው በየዕለቱ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕትና በሕዝቡ ስም የሚቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕቶች ወጪ ለመሸፈን ነው።”

d በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

e እንዲህ ዓይነቱ የማስረዳት ዘዴ “ኤ ፎርሽዮሪ” በመባል የሚጠራ ሲሆን ከላቲን የተወሰደ ነው፤ “ይበልጥ ጠንካራ ምክንያት፣ የበለጠ የተረጋገጠ” የሚል ትርጉም አለው።