በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መቅድም

መቅድም

ውድ አንባቢ፦

“ተከታዬ ሁን።” (ማርቆስ 10:​21) ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንድንከተለው ያቀረበልን ግብዣ ነው። አንተስ ኢየሱስ ላቀረበው ግብዣ ምላሽ እየሰጠህ ነው? እንዲህ ማድረግህ በሕይወትህ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህን የምንለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ፣ አንድያ ልጁን ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ ወደ ምድር ልኮታል። (ዮሐንስ 3:​16) ይህ ልጅ ለእኛ ሲል ከመሞቱም በላይ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን አሳይቶናል። ኢየሱስ ባደረገው በማንኛውም ነገር ንጹሕ አቋሙን የጠበቀ ሲሆን በዚህም የአባቱን ልብ ደስ አሰኝቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ አባቱን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ አሳይቶናል። ኢየሱስ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች፣ አባቱ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድና የአባቱን ፈቃድ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል።​—⁠ዮሐንስ 14:9

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ “የእሱን ፈለግ በጥብቅ [እንድንከተል] አርዓያ” እንደተወልን ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 2:​21) ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ፣ በአሁኑ ጊዜ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራትና ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ሳንወጣ መኖር ከፈለግን የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ይኖርብናል።

የኢየሱስን ፈለግ መከተል የሚፈልግ ሰው መጀመሪያ ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት በሚገባ ማወቅ ይኖርበታል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን የኢየሱስን ታሪክ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል። ኢየሱስ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን እንዲሁም በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን እሱን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ መመርመራችን ኢየሱስን እንዴት መከተል እንዳለብን በግልጽ ለመረዳት ያስችለናል።

ይህ መጽሐፍ ለኢየሱስና ለይሖዋ ያለህን ፍቅር እንደሚያሳድግልህ ተስፋ እናደርጋለን። እንዲህ ያለው ፍቅር የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል እንዲያነሳሳህ ምኞታችን ነው፤ ይህም አሁንም ሆነ ለዘላለም የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት ያስችልሃል።

አዘጋጆቹ