ምዕራፍ አንድ
“ተከታዬ ሁን”—ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?
1, 2. አንድ ሰው ሊቀርቡለት ከሚችሉት ግብዣዎች ሁሉ የላቀው የትኛው ነው? ራሳችንን ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን?
እስከ ዛሬ ከቀረቡልህ ግብዣዎች ሁሉ እጅግ የተደሰትክበት የትኛው ነው? በአንድ ልዩ ዝግጅት ላይ ምናልባትም በጣም በምትወዳቸው ሁለት ሰዎች ሠርግ ላይ እንድትገኝ የተጋበዝክበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። ወይም ደግሞ ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ እንድትሠራ የተጠየቅክበት ቀን ትዝ ይልህ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ግብዣዎች ቀርበውልህ ከነበረ ይህን አጋጣሚ በማግኘትህ በጣም እንደተደሰትክ አልፎ ተርፎም ክብር እንደተሰማህ ጥርጥር የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከእነዚህ ሁሉ የላቀ አንድ ግብዣ ቀርቦልሃል። ይህ ግብዣ የቀረበው ለእያንዳንዳችን ነው። ለዚህ ግብዣ የምንሰጠው ምላሽ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ከምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ነው።
2 ለመሆኑ ይህ ግብዣ ምንድን ነው? ይህን ግብዣ ያቀረበው የሁሉን ቻዩ አምላክ የይሖዋ አንድያ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ግብዣው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በማርቆስ 10:21 ላይ ኢየሱስ “ተከታዬ ሁን” የሚል ግብዣ አቅርቧል። ኢየሱስ ይህን ግብዣ ያቀረበው ለሁላችንም ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ‘ለዚህ ግብዣ ምን ምላሽ እሰጣለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ‘ይሄማ መልሱ ግልጽ ነው’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ደግሞስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ግብዣ ማን አልቀበልም ሊል ይችላል? የሚያስገርመው ግን አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም። ለምን?
3, 4. (ሀ) ኢየሱስን ስለ ዘላለም ሕይወት የጠየቀው ግለሰብ ብዙዎች በጣም የሚጓጉላቸው ምን ነገሮች ነበሩት? (ለ) ኢየሱስ ሀብታም የሆነው ወጣት አለቃ ምን ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት አስተውሎ ሊሆን ይችላል?
3 ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት ይህ ግብዣ በግለሰብ ደረጃ የቀረበለትን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ግለሰብ በጣም የተከበረ ሰው ነበር። ሰዎች ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸው አልፎ ተርፎም በጣም የሚጓጉላቸው ቢያንስ ሦስት ነገሮች ማለትም ወጣትነት፣ ሀብትና ሥልጣን ነበሩት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ዘገባ ይህ ሰው ‘ወጣት፣’ “ሀብታም” እና ‘ከአይሁዳውያን አለቆች አንዱ’ እንደነበር ይገልጻል። (ማቴዎስ 19:20፤ ሉቃስ 18:18, 23) ይሁን እንጂ ይህ ወጣት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ አንድ ሌላም ነገር ነበረው። ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ የሚናገረውን ያዳመጠ ሲሆን በሰማውም ነገር ተደስቶ ነበር።
4 በዘመኑ የነበሩት አብዛኞቹ አለቆች ለኢየሱስ የሚገባውን አክብሮት አላሳዩትም። (ዮሐንስ 7:48፤ 12:42) ይሁንና ይህ አለቃ ከዚህ የተለየ ነገር አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ] ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ ‘ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ሲል ጠየቀው።” (ማርቆስ 10:17) ይህ ሰው ከኢየሱስ ጋር ለመነጋገር ምን ያህል ጓጉቶ እንደነበር ልብ በል፤ ድሆችና ችግረኞች ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ እሱም በአደባባይ ወደ ኢየሱስ እየሮጠ ሄዷል። በተጨማሪም አክብሮቱን ለመግለጽ በክርስቶስ ፊት ተንበርክኳል። በመሆኑም ይህ ሰው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ትሑትና መንፈሳዊ ፍላጎቱን የሚያውቅ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ላሉት ባሕርያት ከፍ ያለ ግምት ይሰጣል። (ማቴዎስ 5:3፤ 18:4) ከዚህ አንጻር “ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው” መባሉ ምንም አያስገርምም። (ማርቆስ 10:21) ኢየሱስ ወጣቱ ላቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጠው እንዴት ነበር?
ወደር የማይገኝለት ግብዣ
5. ኢየሱስ ሀብታም ለሆነው ወጣት ምን ምላሽ ሰጠው? ይህ ሰው “አንድ ነገር” ጎድሎታል ሲል ድሃ መሆን አለበት ማለቱ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
5 ኢየሱስ እንደገለጸው የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ለሚነሳው ወሳኝ ጥያቄ፣ አባቱ ቀደም ብሎም ቢሆን አጥጋቢ መረጃ ሰጥቷል። ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጠቀሰ ሲሆን ወጣቱም የሙሴን ሕግ በሚገባ እንደሚጠብቅ አስረግጦ ተናግሯል። ሆኖም ኢየሱስ ልዩ የማስተዋል ችሎታ ስላለው በሰውየው ልብ ውስጥ ያለውን ነገር መገንዘብ ችሏል። (ዮሐንስ 2:25) ይህ አለቃ፣ አንድ ከባድ የሆነ መንፈሳዊ ችግር እንዳለበት ተረድቶ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “አንድ ነገር ይጎድልሃል” አለው። ይህ ሰው የጎደለው “አንድ ነገር” ምን ነበር? ኢየሱስ “ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ” አለው። (ማርቆስ 10:21) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ‘አንድ ሰው አምላክን ማገልገል ከፈለገ ቤሳ ቤስቲን የሌለው ድሃ መሆን አለበት’ ማለቱ ነበር? በፍጹም። a ክርስቶስ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ግልጽ እንዲሆን ማድረጉ ነበር።
6. ኢየሱስ ምን ግብዣ አቀረበ? ሀብታም የሆነው ወጣት አለቃ የሰጠው ምላሽ ስለ ልቡ ሁኔታ ምን ያሳያል?
6 ኢየሱስ ይህ ሰው የሚጎድለው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ እንዲሆንለት ሲል “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት ግሩም ግብዣ አቀረበለት። እስቲ አስበው፣ የልዑሉ አምላክ ልጅ ይህ ሰው እሱን እንዲከተለው ፊት ለፊት ግብዣ አቀረበለት! በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ሊገምተው ከሚችለው በላይ በረከት እንደሚያገኝ ቃል ገባለት። “በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ” አለው። ይህ ሀብታም አለቃ ይህን አጋጣሚ፣ ይህን ድንቅ ግብዣ ሳያቅማማ ተቀብሎ ይሆን? ዘገባው “ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ አዘነ፤ ብዙ ንብረት ስለነበረውም እያዘነ ሄደ” ይላል። (ማርቆስ 10:21, 22) በመሆኑም ኢየሱስ ያቀረበው ያልተጠበቀ ሐሳብ በዚህ ሰው ልብ ውስጥ ያለው አንድ ችግር ይፋ እንዲወጣ አድርጓል። የሰውየው ሕይወት ከቁሳዊ ንብረቱ እንዲሁም ቁሳዊ ንብረቱ ከሚያስገኝለት ሥልጣንና ክብር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነበር። የሚያሳዝነው ይህ ሰው ለእነዚህ ነገሮች ያለው ፍቅር ለክርስቶስ ካለው ፍቅር በለጠበት። ስለዚህ ሰውየው የጎደለው “አንድ ነገር” ለኢየሱስና ለይሖዋ ከልብ የመነጨና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ነው። ይህ ወጣት እንዲህ ዓይነት ፍቅር ስላልነበረው የቀረበለትን ወደር የሌለው ግብዣ ሳይቀበል ቀርቷል። ይሁንና ይህ ጉዳይ አንተንም የሚመለከተው እንዴት ነው?
7. ኢየሱስ ያቀረበው ግብዣ በዛሬው ጊዜ የምንገኘውን እኛንም እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ግብዣውን ያቀረበው ለዚህ ሰው ብቻ ወይም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ አልነበረም። ኢየሱስ ‘ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ያለማቋረጥ ይከተለኝ’ ብሏል። (ሉቃስ 9:23) “ማንም” ሰው ከልቡ “የሚፈልግ” ከሆነ የክርስቶስ ተከታይ መሆን እንደሚችል ልብ በል። አምላክ እንዲህ ያሉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ልጁ ይስባቸዋል። (ዮሐንስ 6:44) የኢየሱስ ግብዣ ለሀብታሞች፣ ለድሆች፣ የተወሰነ ዘር ወይም ብሔር ላላቸው ሰዎች አሊያም በዚያ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ሁሉ የቀረበ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት ያቀረበው ግብዣ አንተንም ይመለከታል። ክርስቶስን ለመከተል መምረጥህ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል?
የክርስቶስ ተከታይ መሆን ያለብህ ለምንድን ነው?
8. ሰዎች ሁሉ ምን ያስፈልጋቸዋል? ለምንስ?
8 አምነን ልንቀበለው የሚገባን አንድ ሐቅ አለ፦ እኛ ሰዎች ጥሩ አመራር የሚሰጠን መሪ የግድ ያስፈልገናል። ሐቁ ይህ ቢሆንም ይህን የሚቀበሉት ግን ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የይሖዋ ነቢይ ኤርምያስ በመንፈስ ተመርቶ የሚከተለውን ጊዜ የማይሽረው እውነት ተናግሯል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።” (ኤርምያስ 10:23) ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ችሎታም ሆነ መብት የላቸውም። ደግሞም የሰው ልጅ ታሪክ ብልሹ በሆነ አስተዳደር የተሞላ ነው። (መክብብ 8:9) በኢየሱስ ዘመን መሪዎቹ ሕዝቡን ይጨቁኑ፣ ያጎሳቁሉና ወደ ተሳሳተ ጎዳና ይመሩ ነበር። ኢየሱስ ተራው ሕዝብ ‘እረኛ እንደሌለው በግ’ እንደሆነ በሚገባ አስተውሎ ነበር። (ማርቆስ 6:34) በዛሬው ጊዜ የሚገኘው የሰው ዘር ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የምንተማመንበትና የምናከብረው መሪ ያስፈልገናል። ታዲያ ኢየሱስ ይህን ፍላጎታችንን ሊያሟላልን ይችላል? ለዚህ ጥያቄ ‘አዎ’ ብለን መልስ እንድንሰጥ የሚያደርጉንን በርካታ ምክንያቶች ተመልከት።
9. ኢየሱስን ከሌሎች መሪዎች ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
9 በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ የተመረጠው በይሖዋ አምላክ ነው። አብዛኞቹ ሰብዓዊ መሪዎች የሚመረጡት እንደነሱ ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች ነው፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ በቀላሉ ሊታለሉና የተሳሳተ ግምት ሊኖራቸው ይችላል። ኢየሱስ ግን የተለየ መሪ ነው። የተሰጠው የማዕረግ ስም ራሱ ይህን ይጠቁመናል። “መሲሕ” እንደሚለው ቃል ሁሉ “ክርስቶስ” የሚለውም ቃል “የተቀባ” የሚል ትርጉም አለው። አዎ፣ ኢየሱስ የተቀባው ወይም ቅዱስ ለሆነ ኃላፊነት የተሾመው በሌላ በማንም ሳይሆን በአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ በይሖዋ ነው። ይሖዋ አምላክ ልጁን አስመልክቶ “እነሆ፣ የምወደውና ደስ የምሰኝበት የመረጥኩት አገልጋዬ! መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:18) ከፈጣሪያችን ይበልጥ ምን ዓይነት መሪ እንደሚያስፈልገን የሚያውቅ የለም። የይሖዋ ጥበብ ወሰን ስለሌለው በእሱ ምርጫ ላይ የምንተማመንበት በቂ ምክንያት አለን።—ምሳሌ 3:5, 6
10. ሰዎች ሊከተሉት የሚገባው ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ኢየሱስ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
10 በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ ፍጹምና ለተግባር የሚያነሳሳ ምሳሌ ትቶልናል። አንድ ጥሩ መሪ ተገዢዎቹ የሚያደንቋቸውና ሊኮርጇቸው የሚፈልጓቸው ባሕርያት ይኖሩታል። እሱ ራሱም ምሳሌ በመሆን ሌሎች ይበልጥ የተሻሉ ሰዎች ለመሆን እንዲጣጣሩ ያነሳሳቸዋል። አንድ መሪ ከሁሉ ይበልጥ የትኛው ባሕርይ ቢኖረው ደስ ይልሃል? ድፍረት፣ ጥበብ ወይስ ርኅራኄ? አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት የሚቋቋም ቢሆንስ ደስ አይልህም? ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት የሚገልጸውን ዘገባ ስትመረምር እነዚህን ጨምሮ ሌሎች ግሩም ባሕርያትም እንዳሉት ትገነዘባለህ። በሰማይ የሚኖረው አባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የሆነው ኢየሱስ የአምላክን ባሕርያት በተሟላ ሁኔታ ያንጸባርቃል። ኢየሱስ ምንም የማይወጣለት ፍጹም ሰው ነበር። በመሆኑም ካከናወነው ከማንኛውም ነገር፣ ከተናገረው ከየትኛውም ቃልና ውስጣዊ ስሜቱን ከገለጸባቸው የተለያዩ ድርጊቶች ልንኮርጀው የሚገባ ነገር እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ [ትቶላችኋል]” ይላል።—1 ጴጥሮስ 2:21
11. ኢየሱስ “ጥሩ እረኛ” መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው?
11 በሦስተኛ ደረጃ፣ ክርስቶስ “እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ” ብሎ የተናገረውን ቃል ሙሉ በሙሉ ጠብቋል። (ዮሐንስ 10:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የዚህን ምሳሌያዊ አነጋገር ትርጉም በቀላሉ ይረዱታል። እረኞች የሚጠብቋቸውን በጎች ለመንከባከብ ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። “ጥሩ እረኛ” ከራሱ ደህንነት ይልቅ የመንጋውን ደህንነት ያስቀድማል። ለምሳሌ ያህል፣ የኢየሱስ ቅድመ አያት የሆነው ዳዊት በወጣትነቱ እረኛ የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜያት በጎቹን ከኃይለኛ አውሬ ለመከላከል ሲል ሕይወቱን ለአደጋ አጋልጧል። (1 ሳሙኤል 17:34-36) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከዚህ የበለጠ ነገር አድርጓል። ለእነሱ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 10:15) ለመሆኑ እንዲህ ያለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የሚያሳዩት ስንቶቹ መሪዎች ናቸው?
12, 13. (ሀ) አንድ እረኛ በጎቹን ያውቃቸዋል ሲባል ምን ማለት ነው? እነሱስ የሚያውቁት እንዴት ነው? (ለ) በጣም ጥሩ የሆነው እረኛ መሪህ እንዲሆን የምትፈልገው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ “ጥሩ እረኛ” መሆኑን በሌላም መንገድ አሳይቷል። “በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል” ብሏል። (ዮሐንስ 10:14) ኢየሱስ አድማጮቹ በአእምሯቸው እንዲሥሉት የፈለገውን ሐሳብ እስቲ ቆም ብለህ አስብ። አንድ ሰው የበግ መንጋ ሲመለከት አንድ ላይ ከተሰበሰቡ እንስሳት ባለፈ የሚታየው ነገር ላይኖር ይችላል። ሆኖም እረኛው እያንዳንዱን በግ በተናጠል ያውቀዋል። ልትወልድ የደረሰችውና የእሱ እርዳታ የሚያስፈልጋት የትኛዋ በግ እንደሆነች፣ ትንሽና አቅመ ቢስ በመሆናቸው የተነሳ ረጅም መንገድ መጓዝ ስለማይችሉ እሱ እንዲሸከማቸው የሚፈልጉት ግልገሎች የትኞቹ እንደሆኑ፣ በቅርቡ ታመው ወይም ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት በጎች የትኞቹ እንደሆኑ ያውቃል። በጎቹም እረኛቸውን ያውቁታል። ድምፁን የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ ከሌላ እረኛ ድምፅ ጋር ፈጽሞ አይምታታባቸውም። የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሲያሰማቸው ወዲያውኑ ምላሽ ይሰጣሉ። ወደሚመራቸውም ቦታ ተከትለውት ይሄዳሉ። እሱም ወዴት እንደሚመራቸው ያውቃል። ለምለም ሣር ያለበት መስክና ንጹሕ ውኃ እንዲሁም ያለስጋት ሊሰማሩ የሚችሉበት ቦታ የት እንደሚገኝ ያውቃል። እረኛው በአቅራቢያቸው ሆኖ ሲጠብቃቸው በጎቹ ያለፍርሃት ይሰማራሉ።—መዝሙር 23
13 እንዲህ ዓይነት መሪ ለማግኘት አትጓጓም? ጥሩ የሆነው እረኛ ተከታዮቹን በዚህ መንገድ በመያዝ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን አስመሥክሯል። አሁንም ሆነ ለዘላለም አስደሳችና አርኪ ወደሆነ ሕይወት እንደሚመራህ ቃል ገብቷል! (ዮሐንስ 10:10, 11፤ ራእይ 7:16, 17) እንግዲያው ክርስቶስን መከተል ምን ማድረግን እንደሚጨምር ማወቅ ያስፈልገናል።
የክርስቶስ ተከታይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
14, 15. የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ክርስቲያን ነኝ ብሎ መናገር ወይም ኢየሱስን እወደዋለሁ ማለት ብቻ በቂ ያልሆነው ለምንድን ነው?
14 በዛሬው ጊዜ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የክርስቶስን ግብዣ እንደተቀበሉ ይሰማቸዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ክርስቲያኖች ብለው ይጠራሉ። ምናልባትም በልጅነታቸው ክርስትና የተነሱበት ቤተ ክርስቲያን አባል ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ክርስቶስን በጣም እንደሚወዱትና እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው እንደተቀበሉት ይናገሩ ይሆናል። ሆኖም ይህ የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል? ኢየሱስ ተከታዮቹ እንድንሆን ግብዣ ሲያቀርብልን ይህን ማለቱ ነበር? የክርስቶስ ተከታይ መሆን ከዚህ የላቀ ነገርን ያካትታል።
15 አብዛኞቹ ዜጎቻቸው የሕዝበ ክርስትና አባላት የሆኑባቸውን አገሮች እስቲ እንመልከት፤ እነዚህ ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ ይናገራሉ። ታዲያ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች ተግባራዊ ያደርጋሉ? ወይስ እንደሌላው የዓለም ክፍል ሁሉ በእነዚህ አገሮችም ጥላቻ፣ ጭቆና፣ ዓመፅና ግፍ ተንሰራፍቶ ይታያል?
16, 17. ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምን ይጎድላቸዋል? የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ተለይተው የሚታወቁትስ በምንድን ነው?
16 ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ በዋነኝነት የሚታወቁት፣ በሚናገሩት ነገር ወይም ለራሳቸው በሚሰጡት ስም ሳይሆን በተግባራቸው መሆኑን ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ብሏል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።” (ማቴዎስ 7:21) ታዲያ ኢየሱስ ጌታቸው እንደሆነ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች የአባቱን ፈቃድ የማያደርጉት ለምንድን ነው? ሀብታም የሆነውን ወጣት አለቃ አስታውስ። ክርስቲያን ነኝ የሚሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ‘አንድ ነገር ይጎድላቸዋል’፤ ይህም ኢየሱስንም ሆነ እሱን የላከውን አምላክ በሙሉ ነፍስ መውደድ ነው።
17 እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ክርስቶስን እንደሚወዱት ይገልጹ የለም? በእርግጥ የሚሉት እንደዚያ ነው። ሆኖም ኢየሱስንና ይሖዋን መውደድ ይህን ከማለት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ኢየሱስ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:23) በሌላም ጊዜ ኢየሱስ ራሱን ከእረኛ ጋር በማመሳሰል “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል” ብሏል። (ዮሐንስ 10:27) አዎ፣ ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን የሚያረጋግጠው የምንናገረው ነገር አሊያም ለእሱ ያለን ስሜት ሳይሆን በዋነኝነት ተግባራችን ነው።
18, 19. (ሀ) ስለ ኢየሱስ እውቀት መቅሰማችን ምን ውጤት ያስገኛል? (ለ) የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ምንድን ነው? ይህ መጽሐፍ የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ ሰዎችን ሁሉ የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
18 ተግባራችን ውስጣዊ ማንነታችንን ያሳያል። በመሆኑም በመጀመሪያ መቀረጽ ያለበት ውስጣዊ ማንነታችን ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።” (ዮሐንስ 17:3) ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት ከቀሰምንና ባወቅነው ነገር ላይ ካሰላሰልን ልባችን ይነካል። ለእሱ ያለን ፍቅር እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በየዕለቱ እሱን የመከተል ፍላጎት ያድርብናል።
19 የዚህ መጽሐፍ ዓላማም ይኸው ነው። መጽሐፉ የተዘጋጀው የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት ለመተንተን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እሱን መከተል የሚቻልበትን መንገድ በግልጽ ማስተዋል እንድንችል ለመርዳት ነው። b መጽሐፉ ‘በእርግጥ ኢየሱስን እየተከተልኩ ነው?’ እያልን ራሳችንን በመጠየቅ ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር ራሳችንን እንድንመረምር ያስችለናል። (ያዕቆብ 1:23-25) ምናልባት ስለ ራስህ ስታስብ፣ ጥሩ በሆነው እረኛ የሚመራ በግ እንደሆንክ ይሰማህ ይሆናል። ያም ሆኖ ‘ሁላችንም ብንሆን ምንጊዜም ማስተካከያ ማድረግ የሚጠይቁብን ነገሮች ይኖራሉ’ ቢባል አትስማማም? መጽሐፍ ቅዱስ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ” የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ ) አፍቃሪ በሆነውና ይሖዋ እኛን እንዲመራ በሾመው ጥሩ እረኛ ይኸውም በኢየሱስ በእርግጥ እየተመራን መሆኑን ለማወቅ ብርቱ ጥረት ማድረጋችን የሚያስቆጭ አይሆንም። 13:5
20. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?
20 ይህን መጽሐፍ ማጥናትህ ለኢየሱስና ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ይበልጥ እንዲያጠናክርልህ ምኞታችን ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር ሕይወትህን እንዲመራው ስትፈቅድ በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ወደር የሌለው ሰላምና እርካታ ታገኛለህ፤ ከዚያም ባለፈ እንዲህ ያለ ጥሩ እረኛ የሰጠንን ይሖዋን ለዘላለም ለማወደስ ትበቃለህ። እርግጥ ነው፣ በመጀመሪያ ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት ሊኖረን ይገባል። በመሆኑም ምዕራፍ 2 ላይ ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና መመርመራችን የተገባ ነው።
a ኢየሱስ የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ፣ ያላቸውን ንብረት በሙሉ ለሌሎች እንዲሰጡ አልጠየቃቸውም። ለሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ቢናገርም “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” ብሏል። (ማርቆስ 10:23, 27) ደግሞም ባለጸጋ የሆኑ ጥቂት ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሀብትን በሚመለከት ቀጥተኛ ምክር የተሰጣቸው ቢሆንም ያላቸውን ሀብት ሁሉ ለድሆች እንዲሰጡ አልተጠየቁም።—1 ጢሞቴዎስ 6:17
b የኢየሱስን ሕይወትና ያከናወነውን አገልግሎት በጊዜ ቅደም ተከተል ለመከለስ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።