በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ሦስት

“እኔ . . . በልቤ ትሑት ነኝ”

“እኔ . . . በልቤ ትሑት ነኝ”

“እነሆ፣ ንጉሥሽ ወደ አንቺ ይመጣል”

1-3. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? በዚያ ከነበሩት ተመልካቾች አንዳንዶቹ ሊገረሙ የሚችሉት ለምንድን ነው?

 ኢየሩሳሌም አንድ አስደሳች ክንውን በጉጉት እየተጠባበቀች ነው። አንድ ታላቅ ሰው እየመጣ ነው! ከከተማዋ ውጭ፣ ሰዎች በመንገዱ ዳር ተሰብስበዋል። ሰዎቹ የሚጠብቁትን ግለሰብ ለመቀበል በጣም ጓጉተዋል፤ ምክንያቱም አንዳንዶች ይህ ሰው የንጉሥ ዳዊት ወራሽና የእስራኤል ሕጋዊ ገዢ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ብዙዎቹ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ወጥተዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ መንገዱን ለማሳመር መደረቢያቸውንና የዛፍ ቅርንጫፎችን በመንገዱ ላይ ያነጥፋሉ። (ማቴዎስ 21:7, 8፤ ዮሐንስ 12:​12, 13) ‘ይህ ሰው ወደ ከተማዋ የሚገባው በምን ዓይነት ሁኔታ ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ ወደ አእምሯቸው ሳይመጣ አልቀረም።

2 አንዳንዶች በብዙ አጀብ ይመጣል ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ክብር ወደ ከተማዋ የገቡ ታላላቅ ሰዎችን እንደሚያውቁ ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ የንጉሥ ዳዊት ልጅ አቢሴሎም፣ ንጉሥ መሆኑን አዋጅ ባስነገረበት ወቅት ከሠረገላው ፊት ፊት የሚሮጡ 50 ሰዎችን አዘጋጅቶ ነበር። (2 ሳሙኤል 15:1, 10) የሮሙ ገዢ ጁሊየስ ቄሳር እንዲደረግለት ያዘዘው ዝግጅት ደግሞ ከዚህም የበለጠ ድምቀት ያለው ነው፤ ይህ ገዢ የድል ሰልፈኞችን እየመራ ወደ ሮም የፖለቲካ ማዕከል የተጓዘው፣ መብራት በተሸከሙ 40 ዝሆኖች ታጅቦ ነበር! የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እየተጠባበቁት ያሉት ሰው ግን ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጥ ነው። የተሰበሰበው ሕዝብ ተረዳውም አልተረዳው ይህ ሰው ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ አዎ፣ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ነው። ይሁንና ወደፊት ንጉሥ የሚሆነው ይህ ሰው ብቅ ሲል አንዳንዶቹ ሳይገረሙ አይቀሩም።

3 ሰውየው ሲመጣ ሠረገላም ሆነ ከሠረገላ ፊት ፊት የሚሮጡ ሰዎች፣ ፈረሶች ወይም ዝሆኖች አልነበሩም። ኢየሱስ የመጣው ዝቅ ተደርጋ በምትታየው የጭነት እንስሳ ይኸውም በአህያ a ላይ ተቀምጦ ነው። እሱም ሆነ የተቀመጠባት አህያ በተለያዩ ጌጣ ጌጦች አላሸበረቁም። በአህያዋ ጀርባ ላይ ያለው የተንቆጠቆጠ ኮርቻ ሳይሆን የኢየሱስ ተከታዮች ልብስ ነው። ከኢየሱስ በጣም ያነሰ ክብር ያላቸው ሰዎች ትልቅ ዝግጅትና ድምቀት ያለው ሥርዓት እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ እሱ ግን እንዲህ ባለ ያልተጋነነ ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት የመረጠው ለምንድን ነው?

4. መጽሐፍ ቅዱስ መሲሐዊው ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባበትን ሁኔታ የሚገልጽ ምን ትንቢት ይዟል?

4 ኢየሱስ የሚከተለው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ እያደረገ ነው፦ “እጅግ ሐሴት አድርጊ። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ በድል አድራጊነት ጩኺ። እነሆ፣ ንጉሥሽ ወደ አንቺ ይመጣል። እሱ ጻድቅ ነው፤ መዳንንም ያመጣል፤ ትሑት ነው፤ ደግሞም በአህያ . . . ላይ ይቀመጣል።” (ዘካርያስ 9:9) ይህ ትንቢት በአምላክ የተቀባው መሲሕ፣ መለኮታዊ ሹመት ያገኘ ንጉሥ መሆኑን ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንደሚገልጥ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ በልቡ ውስጥ ያለውን አንድ ግሩም ባሕርይ ማለትም ትሕትናውን ያሳያል።

5. በኢየሱስ ትሕትና ላይ ስናሰላስል ልባችን የሚነካው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስን ለመምሰል መጣራችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ካሉት እጅግ ማራኪ ባሕርያት አንዱ በሆነው በትሕትናው ላይ ስናሰላስል ልባችን ይነካል። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” የሆነው ኢየሱስ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 14:6) መቼም በዚህች ምድር ላይ ከኖሩት በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የአምላክን ልጅ ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ማንም እንደሌለ ግልጽ ነው። ይሁንና ኢየሱስ ፍጽምና የጎደላቸው ብዙ ሰዎች የሚቸገሩባቸው እንደ ኩራት፣ ትዕቢት ወይም እብሪት ያሉት ባሕርያት ፈጽሞ አይታዩበትም። እኛም የክርስቶስ ተከታዮች መሆን ከፈለግን የኩራትን መንፈስ መዋጋት አለብን። (ያዕቆብ 4:6) ይሖዋ ትዕቢትን እንደሚጠላ አስታውስ። በመሆኑም የኢየሱስ ዓይነት ትሕትና ለማዳበር መጣራችን በጣም አስፈላጊ ነው።

ከጥንት ጀምሮ ትሕትና አሳይቷል

6. ትሕትና ምንድን ነው? ይሖዋ መሲሑ ትሑት እንደሚሆን ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው?

6 ትሕትና፣ ራስን ዝቅ ማድረግን ማለትም ትዕቢተኛ ወይም ኩራተኛ አለመሆንን ያመለክታል። ይህ ባሕርይ ከልብ የሚመነጭ ሲሆን በአንድ ሰው አነጋገርና ተግባር እንዲሁም ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ይንጸባረቃል። ይሖዋ፣ መሲሑ ትሑት እንደሚሆን ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? ልጁ ትሕትና በማሳየት ረገድ እሱ የተወለትን ፍጹም ምሳሌ እንደተከተለ ያውቃል። (ዮሐንስ 10:​15) ደግሞም ልጁ ትሑት መሆኑን በተግባር ሲያሳይ ተመልክቷል። እንዴት?

7-9. (ሀ) ሚካኤል ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ትሕትና በማሳየት ረገድ የሚካኤልን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

7 የይሁዳ መጽሐፍ ይህን የሚያሳይ አንድ ግሩም ምሳሌ ይዟል፦ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃል በመናገር ሊፈርድበት አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ይሖዋ ይገሥጽህ’ አለው።” (ይሁዳ 9) ሚካኤል፣ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትና ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ የሚጠራበት ስም ነው፤ ይህ መጠሪያ የተሠራበት የመላእክት አለቃ ወይም በሰማይ የሚገኘው የይሖዋ መላእክት ሠራዊት አለቃ ሆኖ ከሚያከናውነው ሥራ ጋር በተያያዘ ነው። b (1 ተሰሎንቄ 4:​16) ይሁንና ሚካኤል ከሰይጣን ጋር በተከራከረበት ወቅት ምን እንዳደረገ ተመልከት።

8 የይሁዳ ዘገባ ሰይጣን የሙሴን አካል በተመለከተ ምን ለማድረግ እንዳሰበ አይናገርም፤ ሆኖም ዲያብሎስ ለአንድ መጥፎ ዓላማ ሊያውለው እንደፈለገ ግልጽ ነው። ምናልባት የዚህን ታማኝ ሰው አስከሬን ሰዎች ለሐሰት አምልኮ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ አቅዶ ሊሆን ይችላል። ሚካኤል የሰይጣንን የተንኮል ዓላማ ከመቃወሙም ሌላ አስደናቂ የሆነ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። በእርግጥ ሰይጣን ሊገሠጽ ይገባው ነበር፤ ያም ቢሆን ሚካኤል ከሰይጣን ጋር እየተከራከረ በነበረበት ወቅት ‘የመፍረድ ሥልጣን ሁሉ’ ገና አልተሰጠውም፤ በመሆኑም ይህን ፍርድ ማስተላለፍ ያለበት ይሖዋ አምላክ ብቻ እንደሆነ ተሰምቶታል። (ዮሐንስ 5:​22) ሚካኤል የመላእክት አለቃ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ያም ሆኖ ከተሰጠው ሥልጣን አልፎ ለመሄድ ከመሞከር ይልቅ ትሑት በመሆን ጉዳዩን ለይሖዋ ለመተው መርጧል። ኢየሱስ ትሑት ከመሆኑም ሌላ ልኩን ወይም ቦታውን የሚያውቅ መሆኑን አሳይቷል።

9 ይሁዳ ይህን ሁኔታ በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው ያለምክንያት አይደለም። የሚያሳዝነው በይሁዳ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ትሑት አልነበሩም። እነዚህ ክርስቲያኖች በትዕቢት ተነሳስተው “ስለማያውቁት ነገር ሁሉ ትችት” ይሰነዝሩ ነበር። (ይሁዳ 10) እኛም ፍጹማን ባለመሆናችን ኩራት በቀላሉ ሊቆጣጠረን ይችላል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተከናወነ አንድ ነገር ለምሳሌ የሽማግሌዎች አካል ያደረገው ውሳኔ ባይገባን ምን እናደርጋለን? ለውሳኔው ምክንያት ስለሆኑት ነገሮች የተሟላ መረጃ ሳይኖረን ውሳኔውን ብንነቅፍና ብንተች ትሕትና እንደሌለን የሚያሳይ አይሆንም? እንግዲያው አምላክ የመፍረድ ሥልጣን ባልሰጠን ጉዳዮች ውስጥ ያለቦታችን ገብተን ከመፍረድ በመቆጠብ የሚካኤልን ማለትም የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል።

10, 11. (ሀ) የአምላክ ልጅ ወደ ምድር እንዲመጣ የተሰጠውን ተልእኮ በፈቃደኝነት መቀበሉ አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስን የትሕትና ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

10 በተጨማሪም የአምላክ ልጅ፣ ወደ ምድር እንዲመጣ የተሰጠውን ተልእኮ በመቀበል ትሑት መሆኑን አሳይቷል። ወደ ምድር ሲመጣ የትኞቹን ነገሮች እንደተወ እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ነበር። በተጨማሪም “ቃል” ማለትም የይሖዋ ቃል አቀባይ ነበር። (ዮሐንስ 1:1-3) እንዲሁም የሚኖረው ‘ከፍ ባለው የይሖዋ የቅድስናና የክብር መኖሪያ’ ይኸውም በሰማይ ነበር። (ኢሳይያስ 63:​15) ያም ሆኖ ወልድ “ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ።” (ፊልጵስዩስ 2:7) በምድር ላይ የተሰጠው ተልእኮ ምን ነገሮችን እንደሚጨምርም አስብ! የኢየሱስ ሕይወት ወደ አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ማህፀን የተዛወረ ሲሆን ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሰው ሆኖ ተወለደ። ኢየሱስ የተወለደው በአንድ ድሃ አናጺ ቤተሰብ ውስጥ ነው። በራሱ ምንም ማድረግ የማይችል ጨቅላ ሕፃን እያለ፣ ድክ ድክ ማለት ሲጀምርና እያደገ ሲሄድ ከዚያም ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲደርስ ይታይህ። ኢየሱስ ፍጹም የነበረ ቢሆንም ፍጹማን ላልሆኑት ሰብዓዊ ወላጆቹ በወጣትነቱ ዘመን ሁሉ ይታዘዝ ነበር። (ሉቃስ 2:​40, 51, 52) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ትሕትና ነው!

11 እኛስ ዝቅ ተደርገው ሊታዩ የሚችሉ ሥራዎችን በፈቃደኝነት በመፈጸም ኢየሱስ የተወውን የትሕትና ምሳሌ መከተል እንችላለን? ለምሳሌ ግድየለሽ፣ ፌዘኛ ወይም ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ሥራችን የተናቀ ሊመስል ይችላል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ሆኖም ይህን ሥራ በጽናት የምናከናውን ከሆነ የሰዎችን ሕይወት ልናድን እንችላለን። ይህ ባይሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችን ትሕትናን በተሻለ ሁኔታ እንድናዳብር ይረዳናል፤ ብሎም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ እንድንከተል ያስችለናል።

ኢየሱስ ሰው በነበረበት ጊዜ ያሳየው ትሕትና

12-14. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎች ባወደሱት ጊዜ ትሑት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ሌሎችን የያዘበት መንገድ ትሑት መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሐ) ኢየሱስ ትሑት የሆነው ለታይታ ወይም ለደንቡ ያህል አለመሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

12 ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ትሕትናው በግልጽ ታይቷል። ውዳሴና ክብር በሙሉ የሚገባው አባቱ እንደሆነ በመግለጽ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ኢየሱስን ስለተናገራቸው ጥበብ ያዘሉ ቃላት፣ ስለፈጸማቸው ታላላቅ ተአምራት ሌላው ቀርቶ ስለሚያሳየው ግሩም ባሕርይ ያወድሱት ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ኢየሱስ ክብሩ ለእሱ ሳይሆን ለይሖዋ እንዲሰጥ አድርጓል።​—⁠ማርቆስ 10:​17, 18፤ ዮሐንስ 7:​15, 16

13 ኢየሱስ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ትሑት መሆኑን አሳይቷል። እንዲያውም ወደ ምድር የመጣው እንዲገለገል ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:​28) ሰዎችን በገርነትና በምክንያታዊነት በመያዝ ትሕትና አሳይቷል። ተከታዮቹ እንደጠበቀው ባልሆኑበት ጊዜ በኃይለ ቃል አልተናገራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ልባቸውን ለመንካት በተደጋጋሚ ይጥር ነበር። (ማቴዎስ 26:​39-41) ኢየሱስ ለማረፍ ሲል ወደ አንድ ጸጥ ያለና ገለልተኛ የሆነ ስፍራ በሄደበት ወቅት ሰዎቹ ተከትለውት እዛው ድረስ ሲመጡ ከአጠገቡ እንዲሄዱለት አላደረገም፤ ይልቁንም የራሱን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው “ብዙ ነገር” አስተምሯቸዋል። (ማርቆስ 6:​30-34) አንዲት እስራኤላዊት ያልሆነች ሴት ልጇን እንዲፈውስላት ደጋግማ በለመነችው ጊዜ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ማድረግ እንደማይፈልግ ጠቁሟት ነበር። ሆኖም የጠየቀችውን እንደማያደርግ የገለጸው በቁጣ አይደለም፤ ደግሞም ወደፊት በምዕራፍ 14 ላይ እንደምንመለከተው የሴትየዋን አስደናቂ እምነት በመመልከት ሐሳቡን ቀይሮ ያለችውን ለመፈጸም ፈቃደኛ ሆኗል።​—⁠ማቴዎስ 15:​22-28

14 ኢየሱስ “እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ” በማለት ስለ ራሱ የተናገረውን ሐሳብ በብዙ መንገዶች ተግባራዊ አድርጓል። (ማቴዎስ 11:​29) ትሑት የሆነው እንዲሁ ለታይታ፣ ለይስሙላ ወይም ለደንቡ ያህል አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ትሕትናው ከልብ የመነጨ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹ ትሑት እንዲሆኑ አበክሮ ማስተማሩ አያስገርምም!

ተከታዮቹ ትሑት እንዲሆኑ አስተምሯል

15, 16. ኢየሱስ የዚህ ዓለም ገዢዎች ባላቸው ዝንባሌና ተከታዮቹ ሊያዳብሩት በሚገባው ዝንባሌ መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ገልጿል?

15 የኢየሱስ ሐዋርያት ትሕትናን ለማዳበር ብዙ ጊዜ ወስዶባቸዋል። ኢየሱስ እነሱን ትሕትና ለማስተማር ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ አስፈልጎታል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከፍ ያለ ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ቃል እንዲገባላቸው በእናታቸው አማካኝነት ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። ኢየሱስ ግን “በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ . . . አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” በማለት በትሕትና መለሰላቸው። ሌሎቹ አሥር ሐዋርያት በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ “ተቆጡ።” (ማቴዎስ 20:​20-24) ታዲያ ኢየሱስ ይህን አለመግባባት የፈታው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ሁሉንም በደግነት መከራቸው፦ “የዚህ ዓለም ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባል።” (ማቴዎስ 20:​25-27) ሐዋርያቱ “የዚህ ዓለም ገዢዎች” ምን ያህል ኩሩዎች፣ ለራሳቸው ክብር የሚፈልጉና ራስ ወዳዶች እንደሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሳይመለከቱ አይቀሩም። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የሥልጣን ጥመኞች ከሆኑት ጨቋኝ ገዢዎች የተለዩ መሆን እንዳለባቸው በግልጽ ተናግሯል። በእርግጥም ትሑት መሆን ይጠበቅባቸው ነበር። ታዲያ ሐዋርያቱ ኢየሱስ ምን ሊያስተምራቸው እንደፈለገ ገብቷቸው ይሆን?

17-19. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለሐዋርያቱ በማይረሳ መንገድ ትሕትናን ያስተማራቸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ሰው በነበረበት ጊዜ ትሕትናን ካስተማረባቸው መንገዶች ሁሉ የላቀው የትኛው ነው?

17 ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ ሊያስተምራቸው የፈለገውን ቁም ነገር በቀላሉ አልተረዱትም። ኢየሱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ትምህርት ሲሰጣቸው ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አልነበረም። ከዚህ በፊት ‘ከሁላችን ማን ይበልጣል?’ ብለው በተከራከሩ ጊዜ አንድ ትንሽ ልጅ በመካከላቸው አቁሞ እንደ ልጆች እንዲሆኑ ነግሯቸዋል። ልጆች እንደ አዋቂዎች ኩራት አይንጸባረቅባቸውም፤ እንዲሁም ለራሳቸው ክብር አይፈልጉም፤ ብሎም የሥልጣን ጉዳይ አያሳስባቸውም። (ማቴዎስ 18:1-4) ያም ሆኖ ኢየሱስ፣ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ እንኳ ሐዋርያቱ የኩራት ባሕርይ ይታይባቸው እንደነበር አስተውሏል። በመሆኑም ፈጽሞ የማይረሳ ትምህርት ሰጣቸው። ፎጣ ካሸረጠ በኋላ በዘመኑ አገልጋዮች ለአንድ እንግዳ ያደርጉ የነበረውንና ከሥራዎች ሁሉ ዝቅ ተደርጎ የሚታየውን ሥራ አከናወነ። ኢየሱስ፣ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳን ጨምሮ የእያንዳንዱን ሐዋርያ እግር አጠበ!​—⁠ዮሐንስ 13:1-11

18 ኢየሱስ “አርዓያ ሆኜላችኋለሁ” በማለት ሊያስተምራቸው የፈለገው ቁም ነገር ምን እንደሆነ ነገራቸው። (ዮሐንስ 13:​15) አሁንስ በዚህ ትምህርት ልባቸው ተነክቶ ይሆን? የሚገርመው በዚያኑ ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ ‘ከመካከላችን ታላቅ ሊሆን የሚችለው ማን ነው?’ በሚል እንደገና ተከራከሩ! (ሉቃስ 22:​24-27) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚህ ጊዜም ቢሆን በትዕግሥት የያዛቸው ሲሆን ትሑት በመሆን አስተምሯቸዋል። ከዚያም “ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ” በመሆን ከበፊቱ ይበልጥ ጠንከር ያለ ትምህርት ሰጣቸው። (ፊልጵስዩስ 2:8) ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛና አምላክን እንደተሳደበ ተቆጥሮ የውርደት ሞት ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። በመሆኑም የአምላክ ልጅ የትሕትናን ትርጉም ፍጹም በሆነና በተሟላ መንገድ በማሳየት ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ የተለየ መሆኑን አስመሥክሯል።

19 ምናልባትም ታማኝ ሐዋርያቱ ልባቸው የተነካው ኢየሱስ ሰው እያለ ትሕትናን አስመልክቶ በሰጠው በዚህ የመጨረሻ ትምህርት ሳይሆን አይቀርም፤ ትምህርቱ በማይፋቅ ሁኔታ በአእምሯቸው ውስጥ ታትሟል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐዋርያቱ ይህ ከሆነ ከዓመታት አልፎ ተርፎም ከአሥርተ ዓመታት በኋላም በትሕትና ሲያገለግሉ እንደነበር ይነግረናል። እኛን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

ኢየሱስ የተወውን አርዓያ ትከተላለህ?

20. በልባችን ትሑት መሆን አለመሆናችንን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

20 ጳውሎስ “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር” በማለት እያንዳንዳችንን መክሮናል። (ፊልጵስዩስ 2:5) ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም በልባችን ትሑት መሆን አለብን። በልባችን ውስጥ ትሕትና መኖር አለመኖሩን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (ፊልጵስዩስ 2:3) በመሆኑም ቀደም ብሎ ለተነሳው ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ የተመካው ለሌሎች ባለን አመለካከት ላይ ነው። አዎ፣ ሌሎችን ከእኛ እንደሚበልጡና እንደሚሻሉ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ታዲያ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ታደርጋለህ?

21, 22. (ሀ) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ትሑት መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ትሕትናን እንደለበስነው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

21 ኢየሱስ ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላም ሐዋርያው ጴጥሮስ የትሕትናን አስፈላጊነት እንዳልዘነጋ አሳይቷል። ጴጥሮስ፣ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በይሖዋ በጎች ላይ ሥልጣናቸውን ከማሳየት ይልቅ ኃላፊነታቸውን በትሕትና እንዲወጡ አስተምሯል። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ኃላፊነት፣ ለመኩራት ሰበብ ሊሆን አይገባም። እንዲያውም ኃላፊነት የተሰጠው ሰው፣ ይበልጥ እውነተኛ ትሕትና እንዲያሳይ ይጠበቅበታል። (ሉቃስ 12:​48) እርግጥ ነው፣ የበላይ ተመልካቾች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች ይህን ባሕርይ እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል።

22 ጴጥሮስ አጥብቆ እየተቃወመውም ኢየሱስ እግሩን ያጠበበትን ያን ምሽት ፈጽሞ እንደማይረሳው የታወቀ ነው። (ዮሐንስ 13:6-10) ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች “እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:5) “ልበሱ” የሚለው አገላለጽ፣ አንድ አገልጋይ ዝቅ ተደርጎ የሚታይን ሥራ ለመሥራት ሽርጥ ማሸረጡን የሚያመለክት ነው። ይህ ቃል ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር ለማጠብ ከመንበርከኩ በፊት ፎጣ ማሸረጡን ያስታውሰን ይሆናል። የኢየሱስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ አምላክ ከሰጠን ሥራዎች ውስጥ ክብራችንን እንደሚነካ አድርገን የምናስበው ሥራ ይኖራል? ከልባችን ትሑት መሆናችን ልክ እንደምንለብሰው ልብስ ለሌሎች በግልጽ መታየት ይኖርበታል።

23, 24. (ሀ) የትዕቢት ዝንባሌ በውስጣችን ጨርሶ እንዳይኖር ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የሚቀጥለው ምዕራፍ ትሕትናን በተመለከተ ሰዎች ያላቸውን የትኛውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል ይረዳል?

23 ትዕቢት ልክ እንደ መርዝ ነው። ለውድቀት ይዳርጋል። እንዲህ ያለው ባሕርይ የላቀ ችሎታ ያለውን ሰው በአምላክ ፊት ዋጋ ቢስ ሊያደርገው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና፣ ዝቅ ተደርጎ የሚታየውን ሰው እንኳ ይሖዋ እንዲጠቀምበት ሊያደርገው ይችላል። የክርስቶስን ፈለግ በመከተል ትሕትናን ለማዳበር በየዕለቱ ጥረት ማድረግ ቢያስፈልገንም ይህን ካደረግን አስደሳች ወሮታ እናገኛለን። ጴጥሮስ “ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:6) ኢየሱስ በሁሉም ነገር ራሱን ዝቅ በማድረጉ ይሖዋ ከፍ ከፍ አድርጎታል። አንተም ትሕትና የምታሳይ ከሆነ አምላካችን ወሮታ ይከፍልሃል።

24 የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች ትሕትናን የድክመት ምልክት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ይህ አስተሳሰብ ስህተት መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል፤ ምክንያቱም ከሁሉ ትሑት የሆነው ይህ ሰው ከማንም ይበልጥ ደፋር ነበር። የሚቀጥለው ምዕራፍ የሚያብራራው ይህን ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል።

a አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ሁኔታ በተመለከተ ባቀረበው ዘገባ ላይ እነዚህ እንስሳት “ዝቅ ተደርገው የሚታዩ” እንደሆኑ ተናግሯል፤ አክሎም “ቀርፋፎች፣ አስቸጋሪዎች፣ ድሃ የሆኑ ሰዎች ለአንዳንድ ተራ ሥራዎች የሚጠቀሙባቸውና ብዙም የማይማርኩ” መሆናቸውን ገልጿል።

b ሚካኤል፣ ኢየሱስ መሆኑን በተመለከተ ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት jw.org በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ዓምድ ሥር የሚገኘውን “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።