ምዕራፍ ስድስት
“መታዘዝን ተማረ”
1, 2. አንድ አፍቃሪ አባት ልጁ ሲታዘዘው ሲያይ ደስ የሚለው ለምንድን ነው? የዚህ አባት ስሜት የይሖዋን ስሜት ያንጸባርቃል የምንለውስ ለምንድን ነው?
አንድ አባት፣ ትንሽ ልጁ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት በመስኮት እየተመለከተ ነው። በጨዋታው መሃል ኳሳቸው ከግቢው ነጥሮ ወጣና ወደ አስፋልቱ ተንከባለለ። የልጁም ዓይን ኳሷን ተከትሎ ሄደ። ከጓደኞቹ አንዱ ይህን ልጅ ወደ አስፋልቱ ሄዶ ኳሷን እንዲያመጣት ገፋፋው፤ ልጁ ግን በእምቢታ ጭንቅላቱን በመነቅነቅ “ከግቢ እንዳትወጣ ተብያለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ አባትየው በደስታ ፈገግ ሲል ይታይህ።
2 አባትየው እንዲህ የተደሰተው ለምንድን ነው? ልጁን ብቻውን ወደ ውጭ እንዳይወጣ አዞት ስለነበር ነው። ልጁ አባቱ እያየው መሆኑን ባያውቅም እንኳ ታዛዥ ነበር፤ አባትየው ይህን ሲያይ፣ ልጁ ታዛዥነትን እየተማረ መሆኑንና ይህም ጥበቃ እንደሚሆንለት ይገነዘባል። ይህ አባት የተሰማው ስሜት በሰማይ ያለው አባታችን ይሖዋ የሚሰማውን ስሜት ያንጸባርቃል። በታማኝነት መጽናትና ወደፊት የተዘጋጀልንን አስደናቂ ተስፋ መውረስ ከፈለግን በእሱ መታመንና እሱን መታዘዝን መማር እንዳለብን አምላክ ያውቃል። (ምሳሌ 3:5, 6) ለዚህም ሲል ማንም ሰው ሊተካከለው የማይችል አስተማሪ ልኮልናል።
3, 4. ኢየሱስ ‘መታዘዝን የተማረው’ እና ‘ፍጹም የሆነው’ እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
3 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በተመለከተ የሚከተለውን የሚያስገርም ሐሳብ ይዟል፦ “ልጅ ቢሆንም እንኳ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ። በዚህም ፍጹም ከሆነ በኋላ የሚታዘዙት ሁሉ ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት ሆነላቸው።” (ዕብራውያን 5:8, 9) ይህ ልጅ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት በሰማይ ኖሯል። ሰይጣንና የእሱ ግብረ አበሮች የሆኑት መላእክት ሲያምፁ ተመልክቷል፤ የአምላክ የበኩር ልጅ ግን ፈጽሞ ከእነሱ ጋር አልተባበረም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈ አንድ ትንቢት ስለ እሱ ሲናገር “እኔም ዓመፀኛ አልነበርኩም” ይላል። (ኢሳይያስ 50:5) ታዲያ ፍጹም ታዛዥ የሆነው ይህ ልጅ “መታዘዝን ተማረ” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ቀድሞውንም ፍጹም የሆነውን ኢየሱስን በተመለከተ “ፍጹም ከሆነ በኋላ” የተባለው ከምን አንጻር ነው?
4 የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ አንድ ወታደር ከብረት የተሠራ ሰይፍ አለው እንበል። ሰይፉ በጦር ሜዳ ተፈትኖ ባያውቅም ምንም ዓይነት ጉድለት የለበትም፤ በጥሩ ሁኔታ የተሠራና የሚያምር ነው። ይሁንና ወታደሩ ይህን ሰይፍ፣ ይበልጥ ጠንካራ ከሆነ ብረት በተሠራ ሌላ ሰይፍ ቀየረው። ይህ ሰይፍ በጦርነት ላይ በሚገባ ያገለገለም ነው። ታዲያ ወታደሩ ሰይፉን መቀየሩ ብልህነት አይደለም? በተመሳሳይም ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ያሳየው ታዛዥነት ምንም እንከን የማይወጣለት ነው። ምድር ላይ ከኖረ በኋላ ያሳየው ታዛዥነት ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ኢየሱስ በሰማይ ቢሆን ኖሮ ጨርሶ ሊያጋጥመው በማይችል ፈተና ውስጥ ስላለፈ ታዛዥነቱ ልክ እንደ ሰይፉ የተፈተነና ይበልጥ የጠነከረ ሆኗል።
5. ኢየሱስ ታዛዥ መሆኑ ወሳኝ የነበረው ለምንድን ነው? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
5 ታዛዥነት ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ተልእኮ ዳር ለማድረስ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” እንደመሆኑ መጠን የመጀመሪያው ወላጃችን ማድረግ ሳይችል የቀረውን ነገር ማድረግ ነበረበት፤ ይህም በፈተና ውስጥም ቢሆን ለይሖዋ ታዛዥ መሆን ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ኢየሱስ ታዛዥነት ያሳየው ግን እንዲሁ ስለሚጠበቅበት ብቻ አልነበረም። በሙሉ አእምሮው፣ በሙሉ ልቡና በሙሉ ነፍሱ ታዝዟል። ይህን ያደረገውም በደስታ ነው። የአባቱን ፈቃድ ማድረግ ከምግብ እንኳ ይበልጥበት ነበር! (ዮሐንስ 4:34) ታዲያ እኛስ ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት ታዛዥነት እንድናሳይ ምን ይረዳናል? እስቲ በመጀመሪያ ኢየሱስን ታዛዥ እንዲሆን የገፋፋው ምን እንደሆነ እንመልከት። እኛም በተመሳሳይ ውስጣዊ ግፊት ተነሳስተን መታዘዛችን ፈተናዎችን እንድንቋቋምና የአምላክን ፈቃድ እንድንፈጽም ይረዳናል። ከዚያም የክርስቶስ ዓይነት ታዛዥነት ማሳየታችን ከሚያስገኛቸው በረከቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመለከታለን።
ኢየሱስን ታዛዥ እንዲሆን የገፋፋው ምንድን ነው?
6, 7. ኢየሱስን ታዛዥ እንዲሆን ከገፋፉት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
6 ኢየሱስን ታዛዥ እንዲሆን የገፋፋው በልቡ ውስጥ የነበረው ነገር ነው። ምዕራፍ 3 ላይ እንደተመለከትነው ክርስቶስ በልቡ ትሑት ነው። ኩራት ሰዎች ታዛዥነትን እንዲጠሉ ያደርጋል፤ ትሕትና ግን ይሖዋን በፈቃደኝነት እንድንታዘዝ ይረዳናል። (ዘፀአት 5:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 5:5, 6) በተጨማሪም ኢየሱስን ታዛዥ እንዲሆን ያነሳሳው የሚወደውና የሚጠላው ነገር ነበር።
7 ከሁሉ በላይ ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን ይሖዋን ይወድ ነበር። ኢየሱስ ለአባቱ ስላለው ፍቅር ምዕራፍ 13 ላይ በስፋት እንመለከታለን። እንዲህ ያለው ፍቅር ኢየሱስ አምላካዊ ፍርሃት እንዲኖረው አድርጓል። ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅርና አክብሮታዊ ፍርሃት ስለነበረው አባቱን ላለማሳዘን በጣም ይጠነቀቅ ነበር። ኢየሱስ ጸሎቱ እንዲሰማለት ያደረገው አንዱ ምክንያት አምላካዊ ፍርሃት የነበረው መሆኑ ነው። (ዕብራውያን 5:7) በተጨማሪም ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ የሚያሳየው አንዱ ጉልህ ባሕርይ ይሖዋን መፍራት ነው።—ኢሳይያስ 11:3
8, 9. በትንቢት በተነገረው መሠረት ኢየሱስ ለጽድቅና ለክፋት ምን ስሜት ነበረው? ስሜቱን የገለጸውስ እንዴት ነው?
8 ይሖዋን መውደድ፣ እሱ የሚጠላቸውን ነገሮች መጥላትንም ይጨምራል። ለምሳሌ ስለ መሲሐዊው ንጉሥ የተነገረውን የሚከተለውን ትንቢት ተመልከት፦ “ጽድቅን ወደድክ፤ ክፋትን ጠላህ። ስለዚህ አምላክ ይኸውም አምላክህ ከባልንጀሮችህ ይበልጥ በደስታ ዘይት ቀባህ።” (መዝሙር 45:7) የኢየሱስ “ባልንጀሮች” የተባሉት የንጉሥ ዳዊት ዘር የሆኑት ሌሎቹ ነገሥታት ናቸው። ኢየሱስ በመቀባቱ የተሰማው ደስታ ከሌሎቹ ነገሥታት ይበልጣል። ለምን? ከእነሱ የበለጠ ሽልማት ስላገኘ እንዲሁም ንግሥናው ዘላቂና የላቀ ጥቅም ስለሚያመጣ ነው። ኢየሱስ የላቀ ሽልማት ያገኘው ለጽድቅ ባለው ፍቅርና ለክፋት ባለው ጥላቻ ተነሳስቶ በሁሉም ነገር አምላክን ስለታዘዘ ነው።
9 ኢየሱስ ለጽድቅና ለክፋት ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው? ለምሳሌ ተከታዮቹ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የሰጣቸውን መመሪያ በታዘዙና በዚህም ምክንያት ጥሩ ውጤት ባገኙ ጊዜ ምን ተሰማው? ሐሴት አድርጎ ነበር። (ሉቃስ 10:1, 17, 21) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስቶ እነሱን ለመርዳት ያደረገውን ጥረት ሳይቀበሉ በመቅረት በተደጋጋሚ የዓመፀኝነት መንፈስ ባሳዩ ጊዜስ ምን ተሰማው? ይህች ከተማ የዓመፅ ጎዳና በመከተሏ አለቀሰላት። (ሉቃስ 19:41, 42) ኢየሱስ ጥሩም ሆነ መጥፎ ምግባር ስሜቱን በጥልቅ ይነካዋል።
10. የጽድቅ ሥራዎችንና መጥፎ ተግባሮችን በተመለከተ ምን ዓይነት ስሜት ማዳበር ይኖርብናል? ይህን ለማድረግስ ምን ይረዳናል?
10 ኢየሱስ ለጽድቅና ለክፋት ባለው ስሜት ላይ ማሰላሰላችን እኛም አምላክን እንድንታዘዝ የሚገፋፋንን ውስጣዊ ስሜት እንድንመረምር ያነሳሳናል። ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንኳ ለመልካም ምግባር ከልብ የመነጨ ፍቅር፣ ለመጥፎ ምግባር ደግሞ ከፍተኛ ጥላቻ ማዳበር እንችላለን። ይሖዋ፣ እሱም ሆነ ልጁ ያላቸው ዓይነት ስሜት ማዳበር እንድንችል እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። (መዝሙር 51:10) ከዚህ ጎን ለጎን፣ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ሊያጠፉብን ከሚችሉ መጥፎ ተጽዕኖዎች መራቅ ያስፈልገናል። በመዝናኛና በጓደኛ ምርጫችን ረገድ ጠንቃቃ መሆናችን አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 13:20፤ ፊልጵስዩስ 4:8) ክርስቶስ የነበረው ዓይነት ውስጣዊ ግፊት ካዳበርን የምንታዘዘው እንዲሁ ስለሚጠበቅብን ብቻ አይሆንም። ትክክል የሆነውን ነገር የምናደርገው ያንን ማድረግ ስለሚያስደስተን ነው። በአንጻሩ ደግሞ መጥፎ ነገር ከመፈጸም የምንቆጠበው እንጋለጣለን ብለን ስለምንፈራ ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ስለምንጠላው ነው።
“እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም”
11, 12. (ሀ) ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ ምን አጋጥሞት ነበር? (ለ) ሰይጣን መጀመሪያ ላይ ኢየሱስን የፈተነው ምን ብሎ ነው? ምን ዓይነት መሠሪ ዘዴዎችንስ ተጠቅሟል?
11 ኢየሱስ ለኃጢአት ያለው ጥላቻ የተፈተነው ገና አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ ነበር። ከተጠመቀ በኋላ ምግብ ሳይቀምስ 40 ቀንና ሌሊት በምድረ በዳ ቆየ። በመጨረሻም ሰይጣን ሊፈትነው መጣ። ዲያብሎስ ምን ያህል መሠሪ እንደሆነ ልብ በል።—ማቴዎስ 4:1-11
12 በመጀመሪያ ሰይጣን “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። (ማቴዎስ 4:3) ኢየሱስ ለብዙ ቀናት ከጾመ በኋላ ምን ተሰምቶት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ተራበ” በማለት በግልጽ ይነግረናል። (ማቴዎስ 4:2) ሰይጣን ሆን ብሎ ኢየሱስ የተዳከመበትን ጊዜ በመጠበቅ ተፈጥሯዊ በሆነው የመመገብ ፍላጎት ሊያጠምደው አስቦ ነበር። ሰይጣን “የአምላክ ልጅ ከሆንክ” በማለት ሊገዳደረው እንደሞከረም ልብ በል። ሰይጣን፣ ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” መሆኑን ያውቅ ነበር። (ቆላስይስ 1:15) ያም ሆኖ ኢየሱስ በሰይጣን ግድድር እልኽ ይዞት የአምላክን ትእዛዝ አልጣሰም። ኢየሱስ የተሰጠውን ኃይል የግል ፍላጎቱን ለማሟላት እንዲጠቀምበት የአምላክ ፈቃድ እንዳልሆነ ያውቃል። በመሆኑም ሰይጣን የጠየቀውን ለመፈጸም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፤ የሚያስፈልገውን ምግብና መመሪያ ለማግኘት የይሖዋን እጅ እንደሚጠብቅ በትሕትና ገልጿል።—ማቴዎስ 4:4
13-15. (ሀ) ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት ሁለተኛና ሦስተኛ ፈተናዎች የትኞቹ ናቸው? ኢየሱስ የሰጠውስ ምላሽ ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ምንጊዜም ቢሆን የሰይጣንን ፈተናዎች ለመቋቋም ዝግጁ መሆን እንደነበረበት እንዴት እናውቃለን?
13 ሰይጣን ኢየሱስን ለሁለተኛ ጊዜ ሲፈትነው በቤተ መቅደሱ አናት ላይ ወደሚገኝ ከፍ ያለ ቦታ ወሰደው። ከዚያም መላእክት እንደሚያድኑት የሚናገረውን የአምላክን ቃል በተንኮል አጣሞ በመጥቀስ ከዚያ ከፍታ ላይ ራሱን ወደ ታች እንዲወረውር ጠየቀው፤ ይህን ያለው፣ ኢየሱስ የጀብደኝነት ድርጊት እንዲፈጽም ሊፈትነው ብሎ ነው። በቤተ መቅደሱ የሚሰበሰበው ብዙ ሕዝብ ይህን ተአምር ካየ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ ሊያነሳ የሚደፍር ይኖራል? እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ትዕይንት በማሳየቱ ሰዎች እንደ መሲሕ አድርገው ከተቀበሉት ደግሞ ኢየሱስ ከስንት ልፋትና ችግር ይድን አልነበር? ምናልባት። ኢየሱስ ግን የይሖዋ ፈቃድ፣ መሲሑ ሥራውን በትሕትና እንዲያከናውን እንጂ አስደናቂ ትዕይንቶችን በማሳየት ሰዎች በእሱ እንዲያምኑ ማድረግ አለመሆኑን ያውቃል። (ኢሳይያስ 42:1, 2) በመሆኑም ኢየሱስ በይሖዋ ላይ ለማመፅ ፈቃደኛ አልሆነም። ዝነኛ የመሆን ፍላጎት ኢየሱስን አላታለለውም።
14 ሥልጣን የማግኘት ፍላጎትስ አባብሎት ይሆን? ሰይጣን በሦስተኛው ሙከራው ደግሞ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ተደፍቶ ቢያመልከው የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። ኢየሱስ፣ ሰይጣን ስላቀረበለት ግብዣ ቆም ብሎ ለማሰብ ሞክሮ ይሆን? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” ሲል መለሰለት። በመቀጠልም “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው። (ማቴዎስ 4:10) ኢየሱስ ሌላ አምላክ እንዲያመልክ ምንም ነገር ሊያባብለው አይችልም። በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም ዓይነት ሥልጣንም ሆነ ክብር ቢቀርብለት የአምላክን ትእዛዝ ለመጣስ አይፈተንም።
15 ታዲያ ሰይጣን በዚህ ተስፋ ቆርጦ ይሆን? በእርግጥ ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ትቶት ሄዷል። ይሁን እንጂ የሉቃስ ወንጌል “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ” በማለት ይናገራል። (ሉቃስ 4:13) ደግሞም ሰይጣን እስከ መጨረሻው ድረስ ኢየሱስን የሚፈትንባቸው ሌሎች አጋጣሚዎች መፈለጉ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “በሁሉም ረገድ የተፈተነ” እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 4:15) ስለሆነም ኢየሱስ መቼም ቢሆን ተዘናግቶ አያውቅም፤ እኛም እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል።
16. ሰይጣን በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች የሚፈትነው እንዴት ነው? የሚያደርገውን ጥረት ማክሸፍ የምንችለውስ እንዴት ነው?
16 ዛሬም ቢሆን ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች መፈተኑን ቀጥሏል። የሚያሳዝነው ደግሞ ያለብን አለፍጽምና ለሰይጣን ዒላማ በቀላሉ እንድንጋለጥ ያደርገናል። ሰይጣን የራስ ወዳድነት፣ የኩራትና ሥልጣን የመፈለግ ዝንባሌ እንዳለን ያውቃል። ቁሳዊ ነገር ያለውን የማታለል ኃይል በመጠቀም ደግሞ በእነዚህ በሦስቱም አቅጣጫዎች ወጥመድ ውስጥ ሊያስገባን ይሞክራል! አንዳንድ ጊዜ ቆም ብለን ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። በ1 ዮሐንስ 2:15-17 ላይ በሚገኘው ሐሳብ ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ ‘ይህ ዓለም የሚያሳድረው የሥጋ ምኞት፣ የቁሳዊ ነገሮች አምሮትና የሌሎችን አድናቆት የማትረፍ ፍላጎት በሰማይ ላለው አባቴ ያለኝን ፍቅር በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሸርሽረውት ይሆን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ይህ ዓለም እንደ ገዢው እንደ ሰይጣን ሁሉ በቅርቡ ተጠራርጎ እንደሚጠፋ ማስታወስ ያስፈልገናል። ሰይጣን የተንኮል ዘዴዎቹን በመጠቀም እኛን አባብሎ ኃጢአት ውስጥ ለመክተት የሚያደርገውን ጥረት ማክሸፍ አለብን! “ምንም ኃጢአት አልሠራም” የተባለለት ጌታችን የተወውን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ጴጥሮስ 2:22
‘ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’
17. ኢየሱስ አባቱን ስለ መታዘዝ ምን ይሰማው ነበር? ያም ሆኖ አንዳንዶች ምን ብለው ሊከራከሩ ይችላሉ?
17 ታዛዥነት ከኃጢአት ከመራቅ ያለፈ ነገርን ይጨምራል፤ ክርስቶስ እያንዳንዱን የአባቱን ትእዛዝ ዘወትር ይፈጽም ነበር። “ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:29) ይህ ታዛዥነቱ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶለታል። እርግጥ ነው፣ ታዛዥ መሆን ለኢየሱስ ያን ያህል አስቸጋሪ እንዳልሆነ የሚያስቡ ይኖራሉ። ‘ኢየሱስ ታዛዥ መሆን የሚጠበቅበት ፍጹም ለሆነው ለይሖዋ ብቻ ነው፤ እኛ ግን በአብዛኛው መታዘዝ የሚጠበቅብን በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎችን ነው’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኢየሱስ በኃላፊነት ላይ ያሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎችንም ይታዘዝ ነበር።
18. ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ጊዜ ታዛዥነትን በተመለከተ ምን አርዓያ ትቷል?
18 ኢየሱስ ልጅ ሳለ ፍጽምና በጎደላቸው ወላጆቹ ማለትም በዮሴፍና በማርያም ሥልጣን ሥር ነበር። ከሌሎች ልጆች ይበልጥ የወላጆቹን ድክመት ማስተዋል ይችል እንደነበር መገመት ይቻላል። ታዲያ ኢየሱስ ወላጆቹን አልታዘዝም ብሏል? አምላክ ከሰጠው ቦታ አልፎ በመሄድ ቤተሰባቸውን እንዴት ማስተዳደር እንደሚችሉ ለወላጆቹ ምክር ለመስጠት ሞክሯል? ሉቃስ 2:51 ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ እያለ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “እንደ ወትሮውም ይገዛላቸው ነበር” እንደሚል ልብ በል። ኢየሱስ በዚህ መንገድ ያሳየው ታዛዥነት፣ ለወላጆቻቸው ለመታዘዝና ተገቢውን አክብሮት ለማሳየት ለሚጥሩ ክርስቲያን ወጣቶች ግሩም አርዓያ ይሆናቸዋል።—ኤፌሶን 6:1, 2
19, 20. (ሀ) ኢየሱስ ፍጽምና ለሌላቸው ሰዎች በመታዘዝ ረገድ ምን ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች አመራር ለሚሰጧቸው ወንድሞች መታዘዝ ያለባቸው ለምንድን ነው?
19 ፍጽምና የሌላቸውን ሰዎች በመታዘዝ ረገድ ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ፈጽሞ ሊያጋጥሟቸው የማይችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ምን ዓይነት ለየት ያሉ ሁኔታዎች እንደነበሩ ተመልከት። በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስና የክህነት አገልግሎቱን ጨምሮ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለረጅም ዘመናት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፤ ይሁንና የአምላክን ሞገስ ሊያጣና በክርስቲያን ጉባኤ ሊተካ ተቃርቦ ነበር። (ማቴዎስ 23:33-38) በዚህ ወቅት ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ከግሪክ ፍልስፍና የተወሰዱ የሐሰት ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር። ብልሹ ሥነ ምግባር በቤተ መቅደሱ ውስጥ እጅግ ተስፋፍቶ ስለነበር ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን “የዘራፊዎች ዋሻ” ሲል ጠርቶታል። (ማርቆስ 11:17) ታዲያ ኢየሱስ ወደዚህ ቤተ መቅደስና ወደ ምኩራቦቹ ከመሄድ ተቆጥቧል? በፍጹም! ይሖዋ በእነዚያ ዝግጅቶች መጠቀሙን አላቆመም። አምላክ እርምጃ እስኪወስድና በዝግጅቶቹ ላይ ለውጥ እስኪያደርግ ድረስ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ወደሚከበሩት በዓላትና ወደ ምኩራቡ በታዛዥነት ይሄድ ነበር።—ሉቃስ 4:16፤ ዮሐንስ 5:1
20 ኢየሱስ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር ታዛዥ ከነበረ ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችማ ይበልጥ ታዛዥ መሆን አይጠበቅባቸውም? እንዲያውም ዛሬ እኛ የምንኖረው ከኢየሱስ ዘመን ፍጹም ልዩ በሆነ ወቅት ላይ ነው፤ ከረጅም ዘመን በፊት በትንቢት እንደተነገረው አሁን ንጹሑ አምልኮ ተመልሶ ተቋቁሟል። አምላክ፣ ተመልሶ የተቋቋመውን ሕዝቡን ሰይጣን እንዲበክለው ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 2:1, 2፤ 54:17) እርግጥ ነው፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃጢአትና አለፍጽምና እንዳለ እሙን ነው። ይሁን እንጂ የሌሎች አለፍጽምና ይሖዋን ላለመታዘዝ ምናልባትም ከክርስቲያን ጉባኤ ለመራቅ ወይም ሽማግሌዎችን ለመተቸት ሰበብ ሊሆነን ይገባል? በጭራሽ! ከዚህ ይልቅ በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡንን ወንድሞች ከልብ መደገፍ ይኖርብናል። በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም በዚያ የምናገኛቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ ታዛዥ መሆናችንን እናሳያለን።—ዕብራውያን 10:24, 25፤ 13:17
21. ኢየሱስ አምላክን እንዳይታዘዝ ሰዎች ላሳደሩበት ጫና ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ለእኛስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
21 ኢየሱስ ማንም ሰው ሌላው ቀርቶ አሳቢ የሆኑ ወዳጆቹ እንኳ ይሖዋን ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲል እንዲያደርጉት አልፈቀደም። ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ መሠቃየትና መሞት እንደማያስፈልገው ጌታውን ሊያሳምነው ሞክሮ ነበር። ጴጥሮስ በራሱ ላይ እንዳይጨክን ኢየሱስን የመከረው ቅን አስቦ ቢሆንም ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ምክር በመሆኑ ኢየሱስ አጥብቆ ተቃውሞታል። (ማቴዎስ 16:21-23) በዛሬው ጊዜም የኢየሱስ ተከታዮችን አሳቢ የሆኑ ዘመዶቻቸው፣ የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲሉ ይመክሯቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ እኛም “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” የሚል አቋም አለን።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
የክርስቶስ ዓይነት ታዛዥነት የሚያስገኘው ወሮታ
22. ኢየሱስ ለየትኛው ጥያቄ መልስ ሰጥቷል? እንዴትስ?
22 ኢየሱስ ከሞት ጋር ፊት ለፊት በተፋጠጠበት ወቅት ታዛዥነቱ ከፍተኛ ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። በዚያ የጭንቅ ቀን በተሟላ ሁኔታ ‘መታዘዝን ተምሯል።’ የራሱን ሳይሆን የአባቱን ፈቃድ ፈጽሟል። (ሉቃስ 22:42) በዚህ መንገድ ንጹሕ አቋምን በመጠበቅ ረገድ እንከን የለሽ ታሪክ አስመዝግቧል። (1 ጢሞቴዎስ 3:16) ‘ፍጹም የሆነ ሰው ፈተና ቢደርስበትም እንኳ ለይሖዋ ታዛዥ ሆኖ ይቀጥላል?’ ለሚለው ዘመናት ያስቆጠረ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። አዳምና ሔዋን ይህን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በኋላ ግን ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ በመኖርና በመሞት ይህ በእርግጥ እንደሚቻል አሳይቷል። ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ ታላቅ የሆነው ኢየሱስ ለጥያቄው የማያዳግም ምላሽ ሰጥቷል። መታዘዙ ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍለውም ይህን ከማድረግ ወደኋላ አላለም።
23-25. (ሀ) ታዛዥነት ከንጹሕ አቋም ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
23 ንጹሕ አቋም ወይም በሙሉ ልብ ለይሖዋ ያደሩ መሆን የሚገለጸው በታዛዥነት ነው። ኢየሱስ ታዛዥ በመሆኑ ንጹሕ አቋም ጠባቂ መሆኑን አስመሥክሯል፤ እንዲሁም ለመላው የሰው ዘር ጥቅም አስገኝቷል። (ሮም 5:19) ይሖዋ ኢየሱስን አትረፍርፎ ባርኮታል። እኛም ጌታችንን ክርስቶስን የምንታዘዝ ከሆነ ይሖዋ ወሮታ ይከፍለናል። ክርስቶስን መታዘዛችን “ዘላለማዊ መዳን” ያስገኝልናል!—ዕብራውያን 5:9
24 በሌላ በኩል ደግሞ፣ ንጹሕ አቋም በራሱ ለታዛዥነት የሚሰጥ ወሮታ ነው። ምሳሌ 10:9 “ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ የሚሄድ ያለስጋት ይመላለሳል” ይላል። ንጹሕ አቋም፣ በምርጥ ጡቦች በተሠራ አንድ ትልቅ ቤት ቢመሰል እያንዳንዱ የታዛዥነት ተግባር ከእያንዳንዱ ጡብ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ ጡብ እንዲሁ በተናጠል ሲታይ ብዙም ጥቅም የሌለው ቢመስልም እያንዳንዱ ጡብ የራሱ የሆነ ቦታና የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለው። ብዙ ጡቦች አንድ ላይ ሲነባበሩ ደግሞ የላቀ ዋጋ ያለው ነገር ይገነባሉ። እኛም ከቀን ቀን፣ አልፎም ከዓመት ዓመት በእያንዳንዱ ነገር የምናሳየው ታዛዥነት አንድ ላይ ሲነባበር ውብ በሆነ ቤት ሊመሰል የሚችል ንጹሕ አቋም እንድንገነባ ያስችለናል።
25 ለዓመታት የዘለቀ ታዛዥነት ደግሞ አንድን ሌላ ባሕርይ ያስታውሰናል፤ ይህም ጽናት ነው። ኢየሱስ በዚህ ረገድ የተወው ምሳሌ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።