በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አራት

“እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ”

“እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ”

እኔ ነኝ

1-3. ኢየሱስ ምን አደጋ ተጋርጦበት ነበር? በዚህ ጊዜ ምን አደረገ?

 ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ወደ ኢየሱስ እየመጡ ነው። እነዚህ ሰዎች ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ሲሆን ወታደሮችም አብረዋቸው አሉ። የወጠኑትን የተንኮል ሴራ ለማስፈጸም ግንባር የፈጠሩት እነዚህ ሰዎች፣ በጨለማ የኢየሩሳሌምን ጎዳናዎች አቋርጠውና የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ አቀኑ። ጨረቃዋ ሙሉ ብትሆንም ሰዎቹ ችቦና መብራት ይዘዋል። መብራት ያስፈለጋቸው ደመና የጨረቃዋን ብርሃን ስለጋረደው ይሆን? ወይስ የሚፈልጉት ሰው ጨለም ያለ ቦታ ይሸሸጋል ብለው አስበው ነው? አንድ ነገር ግልጽ ነው፦ ኢየሱስ ፈርቶ ይሸሸጋል ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ኢየሱስን ፈጽሞ አያውቀውም ማለት ነው።

2 ኢየሱስ ምን ዓይነት አደጋ ከፊቱ እንደተጋረጠበት አሳምሮ ያውቃል። ያም ሆኖ ካለበት ቦታ ንቅንቅ ሳይል ይጠባበቅ ነበር። በአንድ ወቅት ታማኝ ወዳጁ በነበረው በይሁዳ የሚመሩት ሰዎች ኢየሱስ ወዳለበት ቦታ እየቀረቡ ነው። ከዚያም ይሁዳ፣ ለቀድሞ ጌታው የይስሙላ ሰላምታ በመስጠትና እሱን በመሳም ኢየሱስን እንዲለዩት አደረገ፤ በዚህ መንገድ ኢየሱስን ያለምንም ኀፍረት አሳልፎ ሰጠው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ምንም የመረበሽ ምልክት አልታየበትም። ከዚያም ወደፊት ወጣ ብሎ “ማንን ነው የምትፈልጉት?” ሲል የተሰበሰቡትን ሰዎች ጠየቃቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ሲሉ መለሱለት።

3 አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ያሉ የታጠቁ ሰዎች ቢያጋጥሟቸው በፍርሃት መራዳቸው አይቀርም። ምናልባትም ሊይዙት የመጡት ሰዎች፣ ኢየሱስ እንደሚሸበር ጠብቀው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ግን አልተሸበረም፣ አልሸሸም ወይም በፍርሃት ተውጦ የሆነ ያልሆነውን አልዘላበደም። ከዚህ ይልቅ በቀጥታ “እኔ ነኝ” አላቸው። ኢየሱስ ፍጹም መረጋጋትና ድፍረት ይታይበት ስለነበር ሰዎቹ ተደናገጡ። ከዚያም ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።​—⁠ዮሐንስ 18:1-6፤ ማቴዎስ 26:​45-50፤ ማርቆስ 14:​41-46

4-6. (ሀ) የአምላክ ልጅ ከምን ጋር ተመሳስሏል? ለምንስ? (ለ) ኢየሱስ ድፍረት ያሳየባቸው ሦስት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

4 ኢየሱስ እንዲህ ባለው በጣም የሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትና ስሜቱን መቆጣጠር የቻለው እንዴት ነው? በአጭሩ ደፋር ስለሆነ ነው። አንድ መሪ ሊኖሩት ከሚገቡ በጣም አስፈላጊና የሚደነቁ ባሕርያት አንዱ ድፍረት ነው፤ ይህን ባሕርይ ከኢየሱስ በላቀ መንገድ ሊያሳይ ቀርቶ ሊወዳደረው እንኳ የቻለ ሰው ኖሮ አያውቅም። ባለፈው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ምን ያህል ትሑትና ገር እንደነበር ተምረናል። በመሆኑም “በግ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (ዮሐንስ 1:​29) ይሁንና ኢየሱስ ደፋር በመሆኑ ከዚህም በተለየ መንገድ ተገልጿል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ልጅ “እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” በማለት ይገልጸዋል።​—⁠ራእይ 5:5

5 ብዙውን ጊዜ አንበሳ የድፍረት ምሳሌ ተደርጎ ይጠቀሳል። ከአንበሳ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠህ ታውቃለህ? ከሆነ አንበሳውን ያየኸው በታጠረ የአራዊት መጠበቂያ ውስጥ ሆኖ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ለደህንነትህ ባትሰጋም እንኳ እንዲህ ያለው አጋጣሚ በውስጥህ ትንሽም ቢሆን የፍርሃት ስሜት ማሳደሩ አይቀርም። የዚህን ግዙፍና ኃይለኛ እንስሳ ፊት ስትመለከትና እሱም ዓይኖቹን ሲያፈጥብህ ‘እንደው አንበሳ የሚፈራው ነገር ይኖር ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ አንበሳን “ከአራዊት ሁሉ ኃያል የሆነውና ማንንም አይቶ ወደ ኋላ የማይመለሰው” በማለት ይገልጸዋል። (ምሳሌ 30:​30) የክርስቶስም ድፍረት እንዲህ ዓይነት ነው።

6 ኢየሱስ እንደ አንበሳ ዓይነት ድፍረት ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት፤ እነዚህም ለእውነት ጥብቅና መቆም፣ ፍትሕ የሆነውን ማድረግ እና ተቃውሞን መጋፈጥ ናቸው። በተጨማሪም በተፈጥሯችን ደፋሮች ሆንንም አልሆንን ሁላችንም ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል እንደምንችል እንመለከታለን።

በድፍረት ለእውነት ጥብቅና ቆሟል

7-9. (ሀ) ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ምን ነገር ተከሰተ? በዚያ የነበረው ሁኔታ ሊያስፈራ ይችላል እንድትል የሚያደርግህ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከነበሩት መምህራን ጋር በተነጋገረበት ጊዜ ደፋር መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

7 “የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን በሚገዛው ዓለም ውስጥ ለእውነት ጥብቅና መቆም ብዙውን ጊዜ ድፍረት ይጠይቃል። (ዮሐንስ 8:​44፤ 14:​30) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን አቋም ለመያዝ ትልቅ ሰው እስኪሆን ድረስ አልጠበቀም። ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በኢየሩሳሌም ከተከበረው የፋሲካ በዓል ሲመለሱ ከወላጆቹ ጋር ተጠፋፍቶ ነበር። ማርያምና ዮሴፍም በጭንቀት ተውጠው ለሦስት ቀናት ያህል ኢየሱስን ሲያፈላልጉት ቆዩ። በመጨረሻም ቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኙት። ኢየሱስ እዚያ ምን እያደረገ ነበር? “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ሲጠይቃቸው” ነበር። (ሉቃስ 2:​41-50) ይህ ውይይት በተካሄደበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ እስቲ በአእምሯችን ለመሣል እንሞክር።

8 የታሪክ ምሁራን እንደሚናገሩት አንዳንድ የታወቁ የሃይማኖት መሪዎች ከበዓላት በኋላ እዚያው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይቆዩ ነበር፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ሰፋፊ ከሆኑት በረንዳዎች በአንዱ ላይ ሆነው የማስተማር ልማድ ነበራቸው። ሰዎችም ለማዳመጥና ጥያቄ ለመጠየቅ እግራቸው አጠገብ ይቀመጡ ነበር። እነዚህ መምህራን የተማሩ ሰዎች ናቸው። የሙሴን ሕግ እንዲሁም በጊዜ ሂደት እየበዙ የሄዱትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውና ውስብስብ የሆኑ የሰው ሕጎችና ወጎች ጠንቅቀው ያውቃሉ። አንተ እነሱ መሃል ብትቀመጥ ምን ይሰማህ ነበር? የፍርሃት ስሜት ያድርብህ ነበር? እንዲህ ቢሰማህ አያስገርምም። በመካከላቸው የተገኘኸው ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለህ ቢሆንስ? ብዙውን ጊዜ ልጆች ዓይናፋር ናቸው። (ኤርምያስ 1:6) አንዳንድ ልጆች በተቻለ መጠን በትምህርት ቤት አስተማሪዎቻቸው ዓይን ውስጥ ላለመግባት ጥረት ያደርጋሉ፤ ‘የሆነ ነገር እንዳደርግ ወይም እንድናገር ብጠየቅስ? አሊያም ሌሎች ትኩረት ቢያደረጉብኝ፣ የሚያሳፍር ነገር ቢያጋጥመኝ ወይም ቢያሾፉብኝስ?’ የሚል ፍርሃት አላቸው።

9 ኢየሱስ ግን በእነዚህ የተማሩ ሰዎች መሃል ቁጭ ብሎ ያለምንም ፍርሃት ጥያቄዎችን ይጠይቃቸው ነበር፤ ደግሞም የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የሚያመራምሩ ነበሩ። ኢየሱስ ሌላም ነገር አድርጓል። ዘገባው “በዚያ የነበሩት ሰዎችም ሁሉ በመረዳት ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው ያዳምጡት ነበር” በማለት ይነግረናል። (ሉቃስ 2:​47) በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ በዚያ ወቅት ምን እንዳለ አይነግረንም፤ ሆኖም በእነዚያ የሃይማኖት አስተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸውን የሐሰት ትምህርቶች እንደ በቀቀን መልሶ እንዳላስተጋባ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 2:​22) ከዚህ ይልቅ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው እውነት ጥብቅና ቆሟል፤ ያዳምጡት የነበሩትን ሰዎችም ያስደነቃቸው አንድ የ12 ዓመት ልጅ እንዲህ ባለ ማስተዋልና ድፍረት ሐሳቡን መግለጹ ሳይሆን አይቀርም።

ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች በድፍረት ስለ እምነታቸው ለሌሎች ይናገራሉ

10. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወጣት ክርስቲያኖች ድፍረት በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ፈለግ የሚከተሉት እንዴት ነው?

10 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች የኢየሱስን ፈለግ እየተከተሉ ነው። እነዚህ ወጣቶች እንደ ወጣቱ ኢየሱስ ፍጹም እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ኢየሱስ እነሱም ለእውነት ጥብቅና ለመቆም ትልቅ ሰው እስኪሆኑ ድረስ አይጠብቁም። በትምህርት ቤት ወይም በሚኖሩበት አካባቢ ሰዎችን በዘዴ ጥያቄ በመጠየቅና መልሳቸውን በማዳመጥ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ እውነትን ለሌሎች ያካፍላሉ። (1 ጴጥሮስ 3:​15) እንደ እነዚህ ያሉት ወጣቶች የክፍላቸውን ተማሪዎች፣ አስተማሪዎቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ ረድተዋል። ይሖዋ እነዚህ ወጣቶች በሚያሳዩት ድፍረት ምን ያህል ይደሰት! ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ወጣቶችን መንፈስን ከሚያድስ፣ ከሚያስደስትና በብዛት ከሚወርድ ጤዛ ጋር ያመሳስላቸዋል።​—⁠መዝሙር 110:3

11, 12. ኢየሱስ ትልቅ ሰው በነበረበት ጊዜ ለእውነት ጥብቅና በመቆም ደፋር መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ትልቅ ሰው ከሆነም በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜ ለእውነት ጥብቅና በመቆም ደፋር መሆኑን አሳይቷል። እንዲያውም አገልግሎቱን ገና ከመጀመሩ፣ ብዙዎች አስፈሪ እንደሆነ ሊቆጥሩት የሚችሉ ግድድር አጋጥሞት ነበር። ከይሖዋ ጠላቶች ሁሉ ይበልጥ ኃይለኛና አደገኛ የሆነውን ሰይጣንን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነበረበት፤ በወቅቱ ደግሞ ኃያል የመላእክት አለቃ ሳይሆን ሥጋና ደም የለበሰ ሰው ነበር። ኢየሱስ ሰይጣንን የተቃወመው ሲሆን በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ጥቅስ በማጣመም የጠቀሰውን ሐሳብም ውድቅ አድርጎበታል። ኢየሱስ፣ ሰይጣንን “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” በማለት በድፍረት አሰናብቶታል።​—⁠ማቴዎስ 4:2-11

12 ኢየሱስ የአባቱን ቃል ለማጣመም ወይም በተሳሳተ መንገድ ለመጥቀስ የተደረገውን ሙከራ በድፍረት በመቃወም፣ አገልግሎቱ ምን መልክ እንደሚኖረው ገና ከጅምሩ በግልጽ አሳይቷል። እንደ ዛሬው ሁሉ በዚያም ዘመን ሃይማኖታዊ ውሸት የተለመደ ነበር። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “ለሌሎች በምታስተላልፉት ወግ የአምላክን ቃል ትሽራላችሁ” ብሏቸዋል። (ማርቆስ 7:​13) እነዚህ ሰዎች በብዙኃኑ ዘንድ በጣም ይፈሩ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ‘ዕውር መሪዎችና ግብዞች’ ሲል በድፍረት አውግዟቸዋል። a (ማቴዎስ 23:​13, 16) ኢየሱስ በዚህ ረገድ ያሳየውን የድፍረት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13. የኢየሱስን ምሳሌ ስለመከተል ስናስብ ምን ነገር መዘንጋት የለብንም? ሆኖም ምን መብት አለን?

13 እርግጥ ነው፣ እኛ እንደ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ የማንበብ ችሎታም ሆነ በሌሎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን እንደሌለን አንዘነጋም። ሆኖም በድፍረት ለእውነት ጥብቅና በመቆም ረገድ የእሱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ይኸውም ስለ አምላክ፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ቃሉ የሚነገሩ የሐሰት ትምህርቶችን እናጋልጣለን፤ በዚህ መንገድ በሰይጣን ፕሮፓጋንዳ የተነሳ ጨለማ በዋጠው ዓለም ውስጥ ብርሃን እንፈነጥቃለን። (ማቴዎስ 5:​14፤ ራእይ 12:9, 10) ሰዎች ጤናማ ባልሆነ ፍርሃት እንዲሞሉና ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲበላሽ ከሚያደርጉ የሐሰት ትምህርቶች ባርነት ነፃ እንዲወጡ እንረዳለን። ኢየሱስ “እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” በማለት የገባው ቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ ማየት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!​—⁠ዮሐንስ 8:​32

ፍትሕ የሆነውን በማድረግ ድፍረት አሳይቷል

14, 15. (ሀ) ኢየሱስ “ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ” በግልጽ ያሳየበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ሳምራዊቷን ሴት ጋር ማነጋገሩ የትኛውን አመለካከት ተጽዕኖ እንዳላሳደረበት ያሳያል?

14 መሲሑ “ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ” ለብሔራት እንደሚያሳውቅ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:​18፤ ኢሳይያስ 42:1) ኢየሱስ ይህን ማድረግ የጀመረው እዚህ ምድር ላይ እያለ ነበር። ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ምንጊዜም ፍትሐዊና የማያዳላ በመሆን ታላቅ ድፍረት አሳይቷል። ለምሳሌ በዙሪያው ባለው ዓለም በጣም ተስፋፍቶ የነበረውና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዲሁም ጠባብ አስተሳሰብ ፈጽሞ ተጽዕኖ አላሳደረበትም።

15 ኢየሱስ በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ሲነጋገር ደቀ መዛሙርቱ በጣም ተገርመው ነበር። ለምን? በዚያ ዘመን አይሁዳውያን ሳምራውያንን ይጠሏቸው ነበር፤ እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ ነበር። (ዕዝራ 4:4) በተጨማሪም አንዳንድ ረቢዎች ለሴቶች ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው። በኋላ በጽሑፍ የሰፈረው የረቢዎች ሕግ፣ ወንድ ከሴት ጋር መነጋገሩን ያወግዝ ነበር፤ እንዲያውም ሴቶች የአምላክን ሕግ ለመማር ብቁ እንዳልሆኑ ይገልጻል። በተለይ ደግሞ ሳምራውያን ሴቶች እንደ ርኩስ ይታዩ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ያለው ኢፍትሐዊነት የሚንጸባረቅበት መሠረተ ቢስ ጥላቻ ተጽዕኖ ሳያሳድርበት ሳምራዊቷን ሴት በግልጽ አስተምሯታል፤ ሴትየዋ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር እንደነበራት ቢያውቅም ለዚህች ሴት መሲሕ መሆኑን ገልጾላታል።​—⁠ዮሐንስ 4:5-27

16. ክርስቲያኖች መሠረተ ቢስ ጥላቻን ከሚያንጸባርቁ ሰዎች የተለየ አቋም መያዝ ድፍረት የሚጠይቅባቸው ለምንድን ነው?

16 ለሌሎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ ባላቸው ሰዎች መሃል ተገኝተህ ታውቃለህ? ምናልባትም እነዚህ ሰዎች የሌላውን ዘር ወይም ብሔር የሚያቃልል ቀልድ ይናገሩ፣ ወንዶችን ወይም ሴቶችን የሚያናንቅ ሐሳብ ይሰነዝሩ አሊያም በኑሮ ደረጃቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ ሌሎችን ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ይሆናል። የክርስቶስ ተከታዮች እንዲህ ያለውን የጥላቻ መንፈስ አያስተናግዱም፤ ከዚህ ይልቅ በልባቸው ውስጥ ምንም ዓይነት የጭፍን ጥላቻ ርዝራዥ እንዳይኖር ለማድረግ ይጥራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 10:​34) እያንዳንዳችን በዚህ ረገድ ፍትሕን ለማንጸባረቅ የሚያስችል ድፍረት እንዲኖረን ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።

17. ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ምን እርምጃ ወሰደ? ለምንስ?

17 በተጨማሪም ኢየሱስ ደፋር መሆኑ የአምላክ ሕዝቦች ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁና የሚያቀርቡት አምልኮ ንጹሕ እንዲሆን ለማድረግ እርምጃ እንዲወስድ አነሳስቶታል። አገልግሎቱን እንደጀመረ አካባቢ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ሲመጣ ነጋዴዎችና ገንዘብ ለዋጮች በዚያ ንግዳቸውን ሲያጧጡፉ በማየቱ በጣም ተቆጣ። ኢየሱስ በጽድቅ ቁጣ ተሞልቶ እነዚያን ስግብግብ ሰዎች አባረራቸው፤ ዕቃዎቻቸውንም ገለባበጠ። (ዮሐንስ 2:​13-17) በአገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል። (ማርቆስ 11:​15-18) ኢየሱስ እንዲህ ማድረጉ ኃይለኛ ጠላቶች እንዲነሱበት እንደሚያደርግ ቢያውቅም እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አላለም። ለምን? ከልጅነቱ ጀምሮ ያ ቤተ መቅደስ የአባቱ ቤት እንደሆነ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ይህን ያለው ከልቡ ነበር። (ሉቃስ 2:​49) በዚያ የሚካሄደውን ንጹሕ አምልኮ መበከል ፈጽሞ ሊታገሠው የማይችል ኢፍትሐዊ ድርጊት ነው። ኢየሱስ የነበረው ቅንዓት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ድፍረት ሰጥቶታል።

18. ከጉባኤው ንጽሕና ጋር በተያያዘ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ድፍረት ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?

18 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የክርስቶስ ተከታዮችም ምግባራቸውም ሆነ ለአምላክ የሚያቀርቡት አምልኮ ንጹሕ መሆኑ ከልብ ያሳስባቸዋል። አንድ ክርስቲያን ባልንጀራቸው ከባድ ኃጢአት ሲሠራ ቢመለከቱ አይተው እንዳላዩ ሆነው አያልፉም። እንዲህ ያደረገውን ግለሰብ በድፍረት ያነጋግሩታል ወይም ጉዳዩን ለጉባኤ ሽማግሌዎች ይናገራሉ። (1 ቆሮንቶስ 1:​11) ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የታመሙትን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም የይሖዋ ጉባኤ ንጽሕና ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳሉ።​—⁠ያዕቆብ 5:​14, 15

19, 20. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን ምን ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ተስፋፍተው ነበር? ኢየሱስ ምን ጫና ተደርጎበት ነበር? (ለ) የክርስቶስ ተከታዮች በፖለቲካና በዓመፅ ድርጊቶች የማይሳተፉት ለምንድን ነው? ይህ አቋማቸው ያስገኘላቸው አንዱ ወሮታስ ምንድን ነው?

19 ይሁንና ኢየሱስ በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚታየውን ማንኛውንም ኢፍትሐዊ ድርጊት ለማስወገድ ይታገል ነበር ማለት ነው? ብዙ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ሲፈጽሙ እንደተመለከተ ምንም ጥርጥር የለውም። የትውልድ አገሩ በባዕድ አገር ገዢዎች እጅ ወድቃ ነበር። ሮማውያን አይሁዳውያንን በወታደራዊ ኃይላቸው ጨቁነዋቸውና ከፍተኛ ግብር ጥለውባቸው ነበር፤ ሌላው ቀርቶ በሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውም ውስጥ ጣልቃ ይገቡ ነበር። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በወቅቱ በነበሩት የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ መፈለጋቸው አያስገርምም። (ዮሐንስ 6:​14, 15) ኢየሱስ በዚህ ጊዜም ድፍረት ማሳየት ነበረበት።

20 ኢየሱስ መንግሥቱ የዓለም ክፍል እንዳልሆነ ተናግሯል። ተከታዮቹም በወቅቱ በነበሩት የፖለቲካ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምሳሌ ሆኖላቸዋል። (ዮሐንስ 17:​16፤ 18:​36) በርከት ያሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሊያውሉት በመጡ ጊዜ ገለልተኝነትን በተመለከተ የማይረሳ ትምህርት አስተምሯል። ጴጥሮስ በፍጥነት ሰይፉን መዞ ከሰዎቹ አንዱን አቆሰለው። ጴጥሮስ የወሰደው እርምጃ ተገቢ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ‘ንጹሕ በሆነው የአምላክ ልጅ ላይ ጥቃት ሲፈጸም እሱን ለማስጣል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ የበለጠ ሰይፍ የሚያስመዝዝ ሌላ ምን ምክንያት ይኖራል?’ ተብሎ ሊታሰብ ይችላል! ሆኖም ኢየሱስ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” አለ፤ ይህ በምድር ላይ ላሉ ተከታዮቹ እስከ ዛሬም ድረስ የሚሠራ መሠረታዊ ሥርዓት ነው። (ማቴዎስ 26:​51-54) በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሰላማዊ ሆኖ መገኘት በዚያን ጊዜ ለነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች ድፍረት እንደጠየቀባቸው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ድፍረት ይጠይቃል። በአሁኑ ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን ስለሚጠብቁ በዘመናችን በተካሄዱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጦርነቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ ብጥብጦችና ሌሎች የዓመፅ ድርጊቶች ውስጥ እጃቸውን አላስገቡም፤ በመሆኑም በእነዚህ ነገሮች ስማቸው አይነሳም። እንዲህ ያለ መልካም ስም ማትረፋቸው በራሱ፣ ድፍረት ማሳየታቸው ያስገኘላቸው አንዱ ወሮታ ነው።

የደረሰበትን ተቃውሞ በድፍረት ተጋፍጧል

21, 22. (ሀ) ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠሙት መከራዎች ሁሉ የከፋውን ፈተና ከመጋፈጡ በፊት ምን እርዳታ አግኝቶ ነበር? (ለ) ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ድረስ ደፋር መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው?

21 የይሖዋ ልጅ እዚህ ምድር ላይ በሚቆይበት ጊዜ ከባድ ተቃውሞ እንደሚገጥመው አስቀድሞ ያውቅ ነበር። (ኢሳይያስ 50:4-7) በተደጋጋሚ ጊዜ የግድያ ዛቻ የተሰነዘረበት ሲሆን በመጨረሻም በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ተከሰተ። ኢየሱስ ለሕይወቱ የሚያሰጉ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን በድፍረት ሊቋቋም የቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሰዎቹ ሊይዙት ከመምጣታቸው በፊት ምን እያደረገ ነበር? ወደ ይሖዋ አጥብቆ እየጸለየ ነበር። ይሖዋስ ምን አደረገለት? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ያቀረበው ልመና ‘እንደተሰማለት’ ይነግረናል። (ዕብራውያን 5:7) ይሖዋ ደፋር የሆነውን ልጁን እንዲያበረታታው ከሰማይ አንድ መልአክ ላከለት።​—⁠ሉቃስ 22:​42, 43

22 ኢየሱስ ማበረታቻ ካገኘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሐዋርያቱን “ተነሱ፣ እንሂድ” አላቸው። (ማቴዎስ 26:​46) ይህ አነጋገሩ ምን ያህል ደፋር እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። ኢየሱስ “እንሂድ” ያለው ሊይዙት የሚመጡት አደገኛ ሰዎች ጓደኞቹን እንዲተዉአቸው እንደሚጠይቅ እንዲሁም እነዚሁ ወዳጆቹ ትተውት እንደሚሸሹና በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠሙት መከራዎች ሁሉ የከፋውን ፈተና ብቻውን እንደሚጋፈጥ እያወቀ ነው። ሕገ ወጥና ኢፍትሐዊ ፍርድ ሲፈረድበት፣ ሲፌዝበት፣ በጭካኔ ሲገረፍና ተሠቃይቶ ሲሞት ማንም ከጎኑ አልነበረም። ይህን ሁሉ መከራ የተጋፈጠው በድፍረት ነው።

23. ኢየሱስ ለሕይወቱ አደገኛ የሆነውን ሁኔታና ሞትን ፊት ለፊት የተጋፈጠው በጀብደኝነት አይደለም የምንለው ለምን እንደሆነ አብራራ።

23 ኢየሱስ ይህን ሁሉ ያደረገው እንዲሁ በጀብደኝነት ነው? በፍጹም፤ እውነተኛ ድፍረትና ጀብደኝነት ጨርሶ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እንዲያውም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ጠንቃቆች በመሆንና አደገኛ ከሆኑ ሁኔታዎች በዘዴ በመራቅ የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አስተምሯል። (ማቴዎስ 4:​12፤ 10:​16) በዚህ ወቅት ግን ኢየሱስ ሁኔታውን ማስቀረት የሚችልበት ምንም መንገድ እንደሌለ ያውቅ ነበር። ደግሞም የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን ላለማጉደፍ ቆርጦ ነበር፤ ስለዚህ ማድረግ ያለበት ነገር ፈተናውን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች የደረሰባቸውን ስደት በድፍረት ተጋፍጠዋል

24. ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን በድፍረት እንደምንወጣው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

24 የኢየሱስ ተከታዮች በድፍረት የጌታቸውን ፈለግ እንደሚከተሉ በተደጋጋሚ ጊዜ አሳይተዋል! ብዙዎቹ ቢፌዝባቸውም፣ ቢሰደዱም፣ ቢታሰሩም፣ ወህኒ ቤት ቢጣሉም፣ ሥቃይ ቢደርስባቸውም አልፎ ተርፎም ለሞት ቢዳረጉም እንኳ በአቋማቸው ጸንተዋል። ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች እንዲህ ያለ ድፍረት ያገኙት ከየት ነው? ይህ ከራሳቸው የመጣ ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ ከይሖዋ እርዳታ እንዳገኘ ሁሉ ተከታዮቹም በተመሳሳይ መንገድ እርዳታ አግኝተዋል። (ፊልጵስዩስ 4:​13) አንተም ወደፊት ስለሚያጋጥምህ ሁኔታ በማሰብ መፍራት የለብህም። በአንተ በኩል ንጹሕ አቋምህን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ፤ ይሖዋም የሚያስፈልግህን ድፍረት ይሰጥሃል። “አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ የተናገረው መሪያችን ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ብርታት ማግኘት ትችላለህ።​—⁠ዮሐንስ 16:​33

a በጥንት ዘመን እንደነበሩት የእምነት አባቶችና እንደ ነቢያት መቃብሮች ሁሉ የረቢዎች መቃብሮችም ልዩ ክብር ይሰጣቸው እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።