በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አምስት

“የጥበብ . . . ውድ ሀብት ሁሉ”

“የጥበብ . . . ውድ ሀብት ሁሉ”

1-3. ኢየሱስ በ31 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት በተራራው ላይ በሰበከበት ጊዜ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል? አድማጮቹ በአድናቆት የተዋጡትስ ለምን ነበር?

 ጊዜው 31 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በቅፍርናሆም አካባቢ ነው፤ ቅፍርናሆም በገሊላ ባሕር ሰሜን ምዕራብ ዳርቻ ላይ የምትገኝ ሞቅ ያለች ከተማ ናት። ኢየሱስ በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ተራራ ብቻውን ወጥቶ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል። በነጋ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ ከመካከላቸው 12ቱን መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጣም ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ወዳለበት ወደዚህ ስፍራ በመምጣት በተራራው ላይ ባለ አንድ ደልዳላ ቦታ ተሰበሰቡ፤ አንዳንዶቹ የመጡት ራቅ ካሉ አካባቢዎች ነው። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የሚናገረውን ለመስማትና ከሕመማቸው ለመፈወስ ጓጉተዋል። ኢየሱስም ፍላጎታቸውን አሟላላቸው።​—⁠ሉቃስ 6:​12-19

2 ኢየሱስ ወደ ሕዝቡ ቀርቦ የታመሙትን ሁሉ ፈወሳቸው። አሁን በከባድ ሕመም የተነሳ ሥቃዩን የሚያዳምጥ አንድም ሰው በመካከላቸው የለም፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ተቀምጦ ማስተማር ጀመረ። a በዚያ ቀን ያስተማረው ትምህርት አድማጮቹን ሳያስገርማቸው አይቀርም። ደግሞም ማንም ሰው እንዲህ ሲያስተምር ሰምተው አያውቁም። ኢየሱስ ለትምህርቱ ክብደት ለመስጠት ሲል በቃል ሲተላለፉ የቆዩ ወጎችን አልጠቀሰም፤ እንዲሁም ታዋቂ ከሆኑ የአይሁድ ረቢዎች ሐሳብ አልተዋሰም። ከዚህ ይልቅ ደጋግሞ የጠቀሰው በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ነው። መልእክቱ ቀጥተኛ፣ የተጠቀመባቸው ቃላት ቀላል እንዲሁም የሚያብራራበት መንገድ ግልጽ ነበር። ኢየሱስ አስተምሮ ሲጨርስ ሕዝቡ እጅግ ተደነቁ። ደግሞስ ይህ ምን ያስገርማል? በፊታቸው ተቀምጦ ያስተማራቸው ሰው፣ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ በጥበቡ ወደር የሌለው ነው!​—⁠ማቴዎስ 7:​28, 29

“ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ”

3 የተራራውን ስብከት ጨምሮ ኢየሱስ ያስተማራቸውና ያከናወናቸው ሌሎች በርካታ ነገሮች በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። በመንፈስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ ዘገባዎች ስለ እሱ ምን እንደሚሉ በጥልቀት መመርመራችን ይጠቅመናል፤ ምክንያቱም “የጥበብ . . . ውድ ሀብት ሁሉ” የሚገኘው በኢየሱስ ውስጥ ነው። (ቆላስይስ 2:3) ለመሆኑ ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ጥበብ ማለትም እውቀትንና ማስተዋልን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመጠቀም ችሎታን ያገኘው ከየት ነው? ጥበብ ያሳየው በምን መንገድ ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

“ይህ ሰው ይህን ጥበብ . . . ከየት አገኘ?”

4. ኢየሱስ በናዝሬት ከተማ ሲያስተምር ያዳመጡት ሰዎች ምን ጥያቄ አነሱ? ለምንስ?

4 ኢየሱስ ለመስበክ በሚጓዝበት ወቅት ወዳደገባት ከተማ ወደ ናዝሬት ሄደ፤ በዚያ በሚገኘው ምኩራብ ውስጥም ማስተማር ጀመረ። ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ተደነቁ፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብ . . . ከየት አገኘ?” የሚል ጥያቄም አነሱ። ሰዎቹ ቤተሰቦቹን ማለትም ወላጆቹን እንዲሁም እህቶቹንና ወንድሞቹን ያውቋቸዋል፤ በተጨማሪም ኢየሱስ ያደገው ዝቅተኛ ኑሮ ባለው ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ ያውቃሉ። (ማቴዎስ 13:​54-56፤ ማርቆስ 6:1-3) ይህ አንደበተ ርቱዕ አናጺ፣ ታዋቂ በሆኑት የረቢዎች ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዳልተማረም ማወቃቸው አይቀርም። (ዮሐንስ 7:​15) በመሆኑም ያቀረቡት ጥያቄ ምክንያታዊ ይመስላል።

5. ኢየሱስ ጥበብ ያገኘው ከየት እንደሆነ ገልጿል?

5 ኢየሱስ ያሳየው ጥበብ ፍጹም ከሆነው አእምሮው የመነጨ ብቻ አልነበረም። በኋላ ላይ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በይፋ ባስተማረበት ጊዜ ኢየሱስ ይህን ጥበብ ያገኘው ከሁሉ ከሚበልጥ አካል መሆኑን ገልጿል። “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 7:​16) አዎ፣ ኢየሱስ ጥበብ ያገኘው ከላከው ከአብ ነው። (ዮሐንስ 12:​49) ይሁንና ኢየሱስ ከይሖዋ ጥበብ ያገኘው እንዴት ነው?

6, 7. ኢየሱስ ከአባቱ ጥበብ ያገኘው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

6 የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በኢየሱስ ልብና አእምሮ ውስጥ ይሠራ ነበር። ኢሳይያስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በእሱም ላይ የይሖዋ መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና ይሖዋን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” (ኢሳይያስ 11:2) ኢየሱስ የይሖዋ መንፈስ ያረፈበት ከመሆኑም ሌላ ይህ መንፈስ በአስተሳሰቡም ሆነ በውሳኔው ላይ በጎ ተጽዕኖ ያደርጋል፤ ከዚህ አንጻር የሚናገራቸው ቃላትም ሆኑ የሚያደርጋቸው ነገሮች የላቀ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ቢሆኑ ያስገርማል?

7 ኢየሱስ በሌላም ወሳኝ መንገድ ከአባቱ ጥበብ አግኝቷል። ምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ከአባቱ ጋር ኖሯል፤ ይህም የአባቱን አስተሳሰብ ለመማር አጋጣሚ ሰጥቶታል። ወልድ፣ ሌሎች ነገሮች በሙሉ ይኸውም ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ሲፈጠሩ ከአብ ጋር ነበር፤ “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ ከአባቱ ጋር ሲሠራ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ጥልቅ የሆነ ጥበብ አካብቷል። ወልድ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በጥበብ ተመስሎ መገለጹ በእርግጥም የተገባ ነው። (ምሳሌ 8:​22-31፤ ቆላስይስ 1:​15, 16) ኢየሱስ በሰማይ ከአባቱ ጋር በነበረበት ወቅት ያካበተውን ጥበብ በምድር ላይ ባገለገለበት ጊዜ ሁሉ ተጠቅሞበታል። b (ዮሐንስ 8:​26, 28, 38) በመሆኑም ኢየሱስ የተናገራቸው ሐሳቦች ጥልቅ እውቀት፣ ያከናወናቸው ነገሮች ሁሉ ደግሞ ታላቅ ማስተዋል የሚንጸባረቅባቸው መሆናቸው ሊያስደንቀን አይገባም።

8. የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

8 እኛም የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጥበብ ለማግኘት የጥበብ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ዘወር ልንል ይገባል። (ምሳሌ 2:6) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥበብ አይሰጠንም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልገንን ጥበብ እንዲሰጠን የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት ይሰማል። (ያዕቆብ 1:5) እኛም በበኩላችን ይህን ጥበብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ጥበብን ልክ “እንደተሸሸገ ሀብት” አጥብቀን መፈለግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-6) አዎ፣ አምላክ ጥበቡን የገለጠበትን ቃሉን በጥልቀት መቆፈራችንን መቀጠል አለብን፤ ከዚያም ከተማርነው ነገር ጋር ተስማምተን መኖር ይገባናል። በተለይም የይሖዋ ልጅ የተወልን ምሳሌ፣ ጥበብን ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርግልናል። እስቲ ኢየሱስ ጥበብ ያሳየባቸውን የተለያዩ መንገዶች እንመርምር፤ ከዚያም የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ጥበብ ያዘሉ ቃላት

የአምላክ ጥበብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጧል

9. ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ታላቅ ጥበቡን የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

9 በርካታ ሰዎች ኢየሱስ የሚናገረውን ለመስማት ወደ እሱ ይጎርፉ ነበር። (ማርቆስ 6:​31-34፤ ሉቃስ 5:1-3) ኢየሱስ ለማስተማር አፉን በሚከፍትበት ጊዜ ሁሉ ወደር የሌለው ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ይናገር ነበር! ትምህርቶቹ ስለ አምላክ ቃል ያለውን ጥልቅ እውቀትና ስለ ሰው ልጆች ተፈጥሮ ያለውን ወደር የለሽ ማስተዋል ያሳያሉ። በተጨማሪም ትምህርቶቹ በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎችን ቀልብ የሚስቡና ጊዜ የማይሽራቸው ናቸው። “ድንቅ መካሪ” እንደሆነ ትንቢት የተነገረለት ኢየሱስ ካስተማራቸው ጥበብ ያዘሉ ትምህርቶች ውስጥ እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።​—⁠ኢሳይያስ 9:6

10. ኢየሱስ የትኞቹን ጥሩ ባሕርያት እንድናዳብር አበረታቶናል? ለምንስ?

10 በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው የተራራው ስብከት፣ የኢየሱስ ትምህርት ምንም ዓይነት ትረካም ሆነ የሌሎች ሰዎች ሐሳብ መሃል ላይ ሳይገባበት ወጥ ሆኖ ከሰፈረባቸው ዘገባዎች ሁሉ ረጅሙ ነው። በተራራው ስብከት ላይ ኢየሱስ የመከረን አነጋገራችንና ድርጊታችን ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ብቻ አይደለም። ምክሩ ከዚህም ጠለቅ ብሎ ይሄዳል። ኢየሱስ አስተሳሰባችንና ስሜታችን በንግግራችንና በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም በአእምሯችንና በልባችን ሊያድሩ የሚገቡ መልካም ባሕርያትን ጠቅሷል፤ ለምሳሌ የገርነት መንፈስ እንዲኖረን፣ ጽድቅን እንድንራብ፣ የምሕረትና የሰላም ፈጣሪነት ዝንባሌ እንዲኖረን እንዲሁም ፍቅር እንዲያድርብን አበረታቶናል። (ማቴዎስ 5:5-9, 43-48) ልባችን በእነዚህ ባሕርያት እንዲሞላ ለማድረግ የምንጥር ከሆነ አነጋገራችንና ምግባራችንም ጥሩ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ይሖዋን የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል።​—⁠ማቴዎስ 5:​16

11. ኢየሱስ የኃጢአት ድርጊትን በተመለከተ ምክር ሲሰጥ ከሥረ መሠረቱ የተነሳው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ የኃጢአት ድርጊትን አስመልክቶ ምክር ሲሰጥ ለድርጊቱ ዋና መንስኤ የሚሆነውን ነገር ገልጿል። ለምሳሌ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንድንቆጠብ በመናገር ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ቁጣን በልባችን አምቀን እንዳንይዝ አስጠንቅቆናል። (ማቴዎስ 5:​21, 22፤ 1 ዮሐንስ 3:​15) በተጨማሪም ኢየሱስ የመከረን ከምንዝር እንድንርቅ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን ክህደት ወደ መፈጸም የሚመራው የፍትወት ስሜት በልባችን ውስጥ እንዳይፀነስ አስጠንቅቆናል። የተሳሳተ ምኞትና የፆታ ስሜት በውስጣችን እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ ነገሮችን ከማየት እንድንቆጠብ መክሮናል። (ማቴዎስ 5:​27-30) ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው በድርጊቱ ላይ ሳይሆን በመንስኤው ላይ ነው። ኃጢአት ወደ መፈጸም የሚመሩትን ዝንባሌዎችና ምኞቶች ለይቶ ጠቅሷል።​—⁠መዝሙር 7:​14

12. የኢየሱስ ተከታዮች እሱ ለሰጠው ምክር ምን አመለካከት አላቸው? ለምንስ?

12 ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት እንዴት ያለ ድንቅ ጥበብ ያዘለ ነው! “ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ” መባሉ አያስገርምም። (ማቴዎስ 7:​28) እኛም የእሱ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን እሱ በሰጠው ጥበብ ያዘለ ምክር ሕይወታችንን ለመምራት እንጥራለን። ኢየሱስ እንድናሳይ ያበረታታንን ጥሩ ባሕርያት ለማዳበር ለምሳሌ መሐሪና ሰላማዊ ለመሆን እንዲሁም ፍቅር ለማሳየት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፤ እነዚህ ባሕርያት አምላክን ለሚያስደስት ምግባር መሠረት እንደሆኑ እናውቃለን። በተጨማሪም መራራ ቁጣንና የብልግና ምኞትን ጨምሮ ኢየሱስ ያስጠነቀቀንን መጥፎ ስሜቶችና ምኞቶች ከልባችን ነቅለን ለመጣል ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፤ ይህን ማድረጋችን ከኃጢአት ድርጊት እንድንርቅ ይረዳናል።​—⁠ያዕቆብ 1:​14, 15

ጥበብ የሚንጸባረቅበት አኗኗር

13, 14. ኢየሱስ የመረጠው የሕይወት ጎዳና ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታ እንዳለው ያሳያል የምንለው ለምንድን ነው?

13 ኢየሱስ፣ ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ተግባሩም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነበር። መላው አኗኗሩ ማለትም ያደረጋቸው ውሳኔዎች፣ ለራሱ የነበረው አመለካከትና ከሌሎች ጋር የነበረው ግንኙነት የጥበብን ልዩ ልዩ ማራኪ ገጽታዎች የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ኢየሱስ በአኗኗሩ ሁሉ ‘በጥበብና በማመዛዘን ችሎታ’ እንደሚመራ የሚጠቁሙ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።​—⁠ምሳሌ 3:​21

14 ጥበብ፣ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታንም ይጨምራል። ኢየሱስ ከመረጠው የሕይወት ጎዳና ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ አድርጓል። ኢየሱስ ምን ዓይነት ሕይወት መኖር ይችል እንደነበር መገመት ትችላለህ? ዕጹብ ድንቅ የሆነ ቤት መሥራት፣ በአንድ ሙያ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ወይም በዓለም ላይ ዝነኛ መሆን ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት “ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ” እንደሆነ ያውቅ ነበር። (መክብብ 4:4፤ 5:​10) እንዲህ ያለው አካሄድ የጥበብ ተቃራኒ የሆነውን ባሕርይ ይኸውም ሞኝነትን የሚያንጸባርቅ ነው። ኢየሱስ አኗኗሩን ቀላል ለማድረግ መርጧል። ገንዘብ የመሰብሰብ ወይም ቁሳዊ ሀብት የማካበት ፍላጎት አልነበረውም። (ማቴዎስ 8:​20) ኢየሱስ ልክ ባስተማረው መሠረት ዓይኑ በአንድ ዓላማ ላይ ይኸውም የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ያተኮረ ነበር። (ማቴዎስ 6:​22) ከቁሳዊ ነገሮች ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትንና ብዙ በረከት የሚያስገኙትን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለመፈጸም ጊዜውንና ጉልበቱን በጥበብ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 6:​19-21) በዚህ መንገድ ልንከተለው የሚገባን ምሳሌ ትቶልናል።

15. የኢየሱስ ተከታዮች ዓይናቸው በአምላክ መንግሥት ላይ ያተኮረ መሆኑን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?

15 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች ዓይናቸው ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዙ ነገሮች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጋቸው የጥበብ አካሄድ መሆኑን ይገነዘባሉ። በመሆኑም ሳያስፈልግ ዕዳ ውስጥ ከመዘፈቅ ይቆጠባሉ፤ እንዲሁም ብዙ ትኩረት የሚሹና ጉልበት የሚያሟጥጡ አላስፈላጊ ነገሮችን አያሳድዱም። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ብዙዎች ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ ለማዋል አልፎ ተርፎም የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ ሰባኪዎች ለመሆን ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። መንግሥቱን ማስቀደም ከሁሉ የላቀ ደስታና እርካታ ስለሚያስገኝ ከዚህ የተሻለ የጥበብ አካሄድ ሊኖር አይችልም።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ከራሱ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ልኩን የሚያውቅና እውነታውን አምኖ የሚቀበል መሆኑን ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) እኛስ ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ልካችንን የምናውቅና እውነታውን አምነን የምንቀበል መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብና ልክን ማወቅ ተያያዥነት እንዳላቸው ይገልጻል፤ ልክን ማወቅ የአቅም ገደብ እንዳለብን መገንዘብን ይጨምራል። (ምሳሌ 11:2) ኢየሱስ ከራሱ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ልኩን የሚያውቅና እውነታውን አምኖ የሚቀበል ነበር። መልእክቱን ከነገራቸው ሰዎች መካከል ለውጥ የማያደርጉ እንደሚኖሩ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 10:​32-39) በተጨማሪም መልእክቱን እሱ ራሱ ሊነግር የሚችለው ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለተከታዮቹ በአደራ በመስጠት ጥበበኛ መሆኑን አሳይቷል። (ማቴዎስ 28:​18-20) ተከታዮቹ ከሚያናግሯቸው ሰዎች ብዛት፣ ከሚሸፍኑት ክልል ስፋትና ከሚሰብኩበት ጊዜ ርዝመት አንጻር እሱ ካከናወነው “የበለጡ ሥራዎች” እንደሚሠሩ አምኖ በመቀበል ልኩን እንደሚያውቅ አሳይቷል። (ዮሐንስ 14:​12) በተጨማሪም ኢየሱስ የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገው ጊዜ እንዳለ ተገንዝቧል። በምድረ በዳ ሊያገለግሉት ከመጡት መላእክትም ሆነ በጌትሴማኒ እሱን ለማበረታታት ከመጣው መልአክ የተሰጠውን እርዳታ ተቀብሏል። የአምላክ ልጅ እገዛ በፈለገበት ወሳኝ ወቅት ላይ እርዳታ ለማግኘት ከመጮኽ ወደኋላ አላለም።​—⁠ማቴዎስ 4:​11፤ ሉቃስ 22:​43፤ ዕብራውያን 5:7

17 እኛም ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ልካችንን የምናውቅና እውነታውን አምነን የምንቀበል መሆን ይኖርብናል። በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግና በሙሉ ነፍሳችን መካፈል እንፈልጋለን። (ሉቃስ 13:​24፤ ቆላስይስ 3:​23) ይሁንና ይሖዋ አንዳችንን ከሌላው ጋር እንደማያወዳድር ማስታወስ ያስፈልገናል፤ እኛም ብንሆን እንዲህ ማድረግ የለብንም። (ገላትያ 6:4) ጥበብ አቅማችንንና ሁኔታችንን ያገናዘቡ ልንደርስባቸው የምንችላቸው ግቦች እንድናወጣ ይረዳናል። በተጨማሪም ጥበበኛ የሆኑ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞች፣ የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ፤ አንዳንድ ጊዜ የሌሎች እርዳታና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አምነው ይቀበላሉ። እነዚህ ወንድሞች፣ ይሖዋ አንድ የእምነት ባልንጀራቸውን ለእነሱ “የብርታት ምንጭ” አድርጎ ሊጠቀምበት እንደሚችል ይገነዘባሉ፤ በመሆኑም ልክን ማወቅ ሌሎች የሚሰጧቸውን እርዳታ በአመስጋኝነት እንዲቀበሉ ይገፋፋቸዋል።​—⁠ቆላስይስ 4:​11

18, 19. (ሀ) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያታዊና አዎንታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እርስ በርሳችን ባለን ግንኙነት አዎንታዊና ምክንያታዊ ለመሆን የሚያነሳሳ ምን ምክንያት አለን? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

18 ያዕቆብ 3:​17 ‘ከሰማይ የሆነው ጥበብ ምክንያታዊ ነው’ ይላል። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያታዊና አዎንታዊ ነበር። ስህተቶቻቸውን አሳምሮ የሚያውቅ ቢሆንም በመልካም ጎናቸው ላይ ያተኩር ነበር። (ዮሐንስ 1:​47) በተያዘበት ምሽት ጥለውት እንደሚሸሹ ቢያውቅም ታማኝነታቸውን አልተጠራጠረም። (ማቴዎስ 26:​31-35፤ ሉቃስ 22:​28-30) ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደማያውቀው በመናገር ሦስት ጊዜ ክዶታል። ያም ሆኖ ኢየሱስ ስለ ጴጥሮስ ምልጃ አቅርቧል፤ ታማኝነቱን እንደሚጠብቅ ያለውን እምነትም ገልጾለታል። (ሉቃስ 22:​31-34) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ለአባቱ ያቀረበው ጸሎት ደቀ መዛሙርቱ በፈጸሙት ስህተት ላይ ያተኮረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “ቃልህን ጠብቀዋል” በማለት እስከዚያ ምሽት ድረስ ስለነበራቸው አቋም አዎንታዊ ነገር ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:6) ደቀ መዛሙርቱ ድክመቶች ቢኖሩባቸውም የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የሰጠው ለእነሱ ነው። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ኢየሱስ እንደሚተማመንባቸው መግለጹ ያዘዛቸውን ሥራ በትጋት እንዲያከናውኑ ብርታት እንደሰጣቸው ጥርጥር የለውም።

19 የኢየሱስ ተከታዮችም በዚህ ረገድ የእሱን ምሳሌ ለመከተል የሚያነሳሳቸው በቂ ምክንያት አላቸው። ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ ፍጽምና የጎደላቸውን ደቀ መዛሙርቱን በትዕግሥት ከያዛቸው፣ ኃጢአተኞች የሆንነው እኛማ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ምክንያታዊ መሆናችን ምንኛ የተገባ ነው! (ፊልጵስዩስ 4:5) በእምነት ባልንጀሮቻችን ድክመቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ መልካም ጎናቸውን ለማየት መጣራችን የተሻለ ነው። ይሖዋ ወደ ራሱ እንደሳባቸው ማስታወሳችን ጥበብ ነው። (ዮሐንስ 6:​44) መቼም ይሖዋ የሆነ መልካም ነገር እንዳየባቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን የሌሎችን ድክመት ወይም ‘በደል እንድናልፍ’ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ለማመስገን የሚያስችሉንን ምክንያቶች እንድንፈልግም ያነሳሳናል። (ምሳሌ 19:​11 ግርጌ) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደምንተማመንባቸው ስንገልጽላቸው ይሖዋን ለማገልገል አቅማቸው የቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉና ከአገልግሎታቸው ደስታ እንዲያገኙ እንረዳቸዋለን።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​11

20. በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ የተከማቸውን ውድ የጥበብ ሀብት እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል? ለምንስ?

20 ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት በሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች ውስጥ በእርግጥም ውድ የሆነ የጥበብ ሀብት ተከማችቷል! ይህን በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል? ኢየሱስ በተራራው ስብከት መደምደሚያ ላይ እንደገለጸው አድማጮቹ የተናገራቸውን ጥበብ ያዘሉ ቃላት መስማት ብቻ ሳይሆን በተግባር ማዋልም አለባቸው። (ማቴዎስ 7:​24-27) ኢየሱስ የተናገራቸው ጥበብ ያዘሉ ቃላትና አኗኗሩ አስተሳሰባችንን፣ ዝንባሌያችንንና ድርጊታችንን እንዲቀርጹት መፍቀዳችን በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል፤ ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው ጎዳና እንዳንወጣም ይረዳናል። (ማቴዎስ 7:​13, 14) በእርግጥም ከዚህ የተሻለ ጥበብ የሚንጸባረቅበት አካሄድ የለም!

a ኢየሱስ በዚያ ቀን የሰጠው ንግግር የተራራው ስብከት በመባል ይታወቃል። ከማቴዎስ 5:3 እስከ 7:​27 ላይ ባሉት 107 ቁጥሮች ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ንግግር 20 ደቂቃ ያህል እንደፈጀ ይታሰባል።

b ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ‘ሰማያት ሲከፈቱ’ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ያሳለፈውን ሕይወት ማስታወስ የቻለ ይመስላል።​—⁠ማቴዎስ 3:​13-17