ምዕራፍ አሥራ አምስት
“በጣም አዘነላቸው”
1-3. (ሀ) ኢየሱስ ሁለት ዓይነ ስውራን ለማኞች እንዲረዳቸው በተማጸኑት ጊዜ ምን አደረገ? (ለ) “በጣም አዘነላቸው” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
ሁለት ዓይነ ስውራን ከኢያሪኮ ከተማ ውጭ መንገድ ዳር ተቀምጠዋል። በየቀኑ ወደዚህ ስፍራ በመምጣት ብዙ ሰው የሚተላለፍበት ቦታ ላይ ተቀምጠው ይለምናሉ። ይሁን እንጂ በዚህ ዕለት ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚለውጥ ነገር ሊያጋጥማቸው ነው።
2 ለማኞቹ ድንገት ጫጫታ ሰሙ። እየተከናወነ ያለውን ነገር ማየት ስለማይችሉ ከመካከላቸው አንዱ ሕዝቡ እንዲህ የሚንጫጫው ለምን እንደሆነ ጠየቀ፤ በዚያ የነበሩት ሰዎች “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው!” ብለው ነገሩት። ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ነው። ሆኖም ብቻውን አልነበረም፤ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከትሎታል። እነዚያ ለማኞች በዚያ እያለፈ ያለው ማን እንደሆነ ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ መጮኽ ጀመሩ። ሰዎቹ በዚህ ተበሳጭተው ለማኞቹን ዝም እንዲሉ ነገሯቸው፤ እነሱ ግን ይህ አጋጣሚ እንዲያመልጣቸው አልፈለጉም። ፈጽሞ ዝም ሊሉ አልቻሉም።
3 ኢየሱስ ከሕዝቡ ጫጫታ መሃል የለማኞቹን ጩኸት ሰማ። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? በዚህ ወቅት ብዙ የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው ነገር አለ። ምድራዊ ሕይወቱ የሚጠናቀቅበት የመጨረሻ ሳምንት እየቀረበ ነው። ኢየሩሳሌም ከደረሰ በኋላ እንደሚሠቃይና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እንደሚገደል ያውቃል። ያም ሆኖ የለማኞቹን ውትወታ ቸል ብሎ አላለፈም። ቆም አለና እየጮኹ ያሉትን ሰዎች ወደ እሱ እንዲያመጧቸው ጠየቀ። እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ዓይናችንን አብራልን” በማለት ለመኑት። ኢየሱስ “በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ”፤ እነሱም ማየት ቻሉ። a ወዲያውኑም ኢየሱስን ይከተሉት ጀመር።—ሉቃስ 18:35-43፤ ማቴዎስ 20:29-34
4. ኢየሱስ “ለችግረኛው . . . ያዝናል” ተብሎ ስለ እሱ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ርኅራኄ ያሳየው በዚህ ጊዜ ብቻ አልነበረም። ኢየሱስ በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሰዎች ከልብ የመነጨ ርኅራኄ አሳይቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትንቢት ኢየሱስ ‘ለችግረኛው እንደሚያዝን’ ይናገራል። (መዝሙር 72:13) ልክ በትንቢት በተነገረው መሠረት ኢየሱስ የሌሎች ሥቃይ የሚሰማው ሰው ነበር። በራሱ ተነሳስቶ ሰዎችን ለመርዳት እርምጃ ይወስድ ነበር። ለሌሎች እንዲሰብክ ያነሳሳውም ርኅራኄው ነው። የወንጌል ዘገባዎች ከኢየሱስ ንግግርና ድርጊት በስተ ጀርባ ያለውን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት፤ እንዲሁም እንዲህ ዓይነት የርኅራኄ ስሜት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
የሌሎችን ስሜት መረዳት
5, 6. ኢየሱስ ራሱን በሌሎች ቦታ የሚያስቀምጥ ሰው እንደነበር የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
5 ኢየሱስ ራሱን በሌሎች ቦታ የሚያስቀምጥ ሰው ነበር። እየተሠቃዩ ያሉ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ይረዳ እንዲሁም ስሜታቸውን ይጋራ ነበር። እነሱ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ደርሶበታል ማለት ባይሆንም ሥቃያቸው በጥልቅ ይሰማው ነበር። (ዕብራውያን 4:15) ለ12 ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት በፈወሳት ጊዜ ‘ከሚያሠቃይ ሕመምሽ ተፈወሽ’ ብሏታል፤ ይህን ማለቱ በሽታው ያስከተለባትን ከባድ ጭንቀትና ሥቃይ እንደተረዳላት ያሳያል። (ማርቆስ 5:25-34) በአልዓዛር ሞት ምክንያት ማርያምና አብረዋት የነበሩት ሰዎች ሲያለቅሱ ሲያይ ሐዘናቸው ስሜቱን በጥልቅ ስለነካው ውስጡ ተረብሿል። አልዓዛርን ከሞት ሊያስነሳው እንደሆነ ቢያውቅም እንባውን አፍስሷል።—ዮሐንስ 11:33, 35
6 በሌላ ወቅት ደግሞ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ሲል ተማጸነው። ታሞ የማያውቀውና ፍጹም የሆነው ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? በሥጋ ደዌ የተያዘውን ሰው ስሜት ተረዳለት። አዎ፣ ለዚህ ሰው “በጣም አዘነለት።” (ማርቆስ 1:40-42) ከዚያም አስደናቂ የሆነ ነገር አደረገለት። በሙሴ ሕግ መሠረት በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች ርኩስ ተደርገው እንደሚቆጠሩና ወደ ሰዎች መቅረብ እንደማይፈቀድላቸው በሚገባ ያውቃል። (ዘሌዋውያን 13:45, 46) ደግሞም ኢየሱስ ይህን ሰው መንካት ሳያስፈልገው ሊፈውሰው ይችላል። (ማቴዎስ 8:5-13) ሆኖም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው። በእርግጥም ኢየሱስ ታላቅ ርኅራኄ አሳይቷል!
7. ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥን ለመማር ምን ሊረዳን ይችላል? ይህ ባሕርይ በምን ይገለጻል?
7 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን በሌሎች ቦታ በማስቀመጥ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ” የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል። b (1 ጴጥሮስ 3:8) ከባድ በሽታ ወይም የመንፈስ ጭንቀት የሚያሠቃየውን ሰው ስሜት ሙሉ በሙሉ መረዳት ቀላል ላይሆንልን ይችላል፤ በተለይ እንደ እነሱ ያለ ሕመም አጋጥሞን የማያውቅ ከሆነ። ይሁንና ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ የግድ በዚያ ሁኔታ ማለፍን እንደማይጠይቅ አስታውስ። ኢየሱስ ታሞ ባያውቅም የታማሚው ሰው ሥቃይ ይሰማው ነበር። እኛስ እንዲህ ያለ ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? መከራ የደረሰባቸው ሰዎች የልባቸውን ግልጥልጥ አድርገው ሲነግሩንና ስሜታቸውን ሲገልጹልን በትዕግሥት በማዳመጥ ነው። ‘እኔ በእሱ ወይም በእሷ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን ይሰማኝ ነበር?’ እያልን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 12:26) የሌሎች ስሜት በጥልቅ የሚሰማን ዓይነት ሰዎች ለመሆን ጥረት ካደረግን “የተጨነቁትን” በተሻለ ሁኔታ ‘ማጽናናት’ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:14) አንዳንድ ጊዜ የሌሎችን ስሜት መረዳታችን የሚገለጸው በቃል ብቻ ሳይሆን በእንባም ሊሆን ይችላል። ሮም 12:15 “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” ይላል።
8, 9. ኢየሱስ ለሌሎች ስሜት እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ ደግና አሳቢ ነበር፤ ሰዎችን ሲረዳ ለስሜታቸው ይጠነቀቅ ነበር። ሰዎች፣ መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት ሰው ወደ ኢየሱስ ባመጡበት ጊዜ የተከናወነውን ሁኔታ አስታውስ። ኢየሱስ ይህ ሰው እንደጨነቀው የሚጠቁም ነገር ሳያስተውል አልቀረም፤ በመሆኑም ሌሎች ሰዎችን ሲፈውስ ከሚያደርገው ወጣ ያለ አንድ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ሰውየውን “ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደው።” አዎ፣ ከሰው ዓይን ዘወር እንዲል ካደረገ በኋላ ፈወሰው።—ማርቆስ 7:31-35
9 በሌላ ወቅትም ሰዎች ዓይነ ስውር ሰው አምጥተው እንዲፈውሰው ሲጠይቁት ኢየሱስ ተመሳሳይ አሳቢነት አሳይቷል። “ዓይነ ስውሩን፣ እጁን ይዞ ከመንደሩ ውጭ ወሰደው።” ከዚያም ደረጃ በደረጃ ፈወሰው። ይህም የሰውየው ዓይን ከሚያጥበረብረው ብርሃን ጋር እንዲላመድ፣ አእምሮውም በዙሪያው ያሉትን ብዙ ነገሮች ቀስ በቀስ ማስተዋል እንዲችል ሳይረዳው አይቀርም። (ማርቆስ 8:22-26) በእርግጥም ኢየሱስ ለሌሎች ስሜት ከልብ ያስብ ነበር!
10. ለሌሎች ስሜት እንደምናስብ በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?
10 የኢየሱስ ተከታዮች መሆን ለሌሎች ስሜት ማሰብን ይጠይቃል። በመሆኑም በአንደበት አጠቃቀማችን ረገድ ጠንቃቆች እንሆናለን፤ ሳናመዛዝን የምንናገረው ነገር የሌሎችን ስሜት ሊጎዳ እንደሚችል እናውቃለን። (ምሳሌ 12:18፤ 18:21) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለሌሎች ስሜት እንጠነቀቃለን፤ ሻካራ ቃላት፣ የሚያንቋሽሽ አነጋገርና የሽሙጥ ንግግር በእኛ ዘንድ ቦታ የላቸውም። (ኤፌሶን 4:31) እናንት ሽማግሌዎች ለሌሎች ስሜት እንደምታስቡ ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? ምክር በምትሰጡበት ጊዜ አነጋገራችሁ በደግነት የለዘበ ይሁን፤ በዚህ መንገድ የግለሰቡን ክብር ትጠብቁለታላችሁ። (ገላትያ 6:1) ወላጆችስ ለልጆቻችሁ ስሜት እንደምትጠነቀቁ ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁ እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ በሚያደርግ መንገድ ተግሣጽ ከመስጠት በመቆጠብ ነው።—ቆላስይስ 3:21
በራስ ተነሳሽነት መርዳት
11, 12. ኢየሱስ ለሌሎች ርኅራኄ ለማሳየት ሁልጊዜ እስኪጠየቅ ይጠብቅ እንዳልነበር የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ጥቀስ።
11 ኢየሱስ ለሌሎች ርኅራኄ ለማሳየት ሁልጊዜ እስኪጠየቅ አይጠብቅም ነበር። ደግሞም ርኅራኄ ግድ የሚል ባሕርይ ነው፣ ችግር ላይ ለወደቀ ሰው የሆነ ነገር ለማድረግ ይገፋፋል። ኢየሱስም ከአንጀቱ የሚራራ ሰው ስለነበር ሳይጠየቅ ሌሎችን የረዳባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት እጅግ ብዙ ሰዎች ከእሱ ጋር ለሦስት ቀን ቆይተው ነበር፤ የሚበሉት ነገር አልነበራቸውም። ኢየሱስ፣ ሕዝቡ እንደተራበ የሚነግረው ወይም የሆነ ነገር እንዲያደርግ የሚጠይቀው ሰው አላስፈለገውም። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ ‘እነዚህ ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ከእኔ ጋር ስለቆዩና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ። እንዲሁ ጦማቸውን ልሰዳቸው አልፈልግም፤ መንገድ ላይ ዝለው ሊወድቁ ይችላሉ’ አላቸው።” ከዚያም ያለማንም ገፋፊነት ሕዝቡን በተአምር መገበ።—ማቴዎስ 15:32-38
12 እስቲ ሌላም ዘገባ እንመልከት። በ31 ዓ.ም. ኢየሱስ ናይን ወደምትባለው ከተማ ሲቃረብ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ተመለከተ። አስከሬን የተሸከሙ ለቀስተኞች ከከተማዋ ሲወጡ አገኘ፤ ምናልባትም በከተማዋ አቅራቢያ ባለ ኮረብታ ላይ ወደሚገኝ የመቃብር ቦታ እየተጓዙ ሳይሆን አይቀርም፤ ሟቹ የአንዲት ‘መበለት አንድያ ልጅ’ ነበር። ይህች እናት ምን ያህል ልቧ በሐዘን ተሰብሮ እንደነበር መገመት ትችላለህ? አንድ ልጇን ለመቅበር እየሄደች ሲሆን ሐዘኗን የሚጋራ ባል የላትም። ኢየሱስ ልጇን በሞት የተነጠቀችውን መበለት ከለቀስተኞቹ ግርግር መሃል ‘አያት።’ ያየው ነገር ስሜቱን ነካው፤ አዎ፣ “በጣም አዘነላት።” ኢየሱስ የሆነ ነገር እንዲያደርግ የለመነው ሰው አልነበረም። በውስጡ የነበረው ርኅራኄ በራሱ ተነሳሽነት እርምጃ እንዲወስድ ገፋፋው። በመሆኑም “ቀረብ ብሎ ቃሬዛውን ነካ”፤ በመቀጠልም ይህ ወጣት ዳግም ሕያው እንዲሆን አደረገ። ከዚያስ ምን ነገር ተከናወነ? ኢየሱስ፣ ወጣቱን ከእሱ ጋር ከሚጓዙት ብዙ ሰዎች ጋር እንዲከተለው አልጠየቀውም። ከዚህ ይልቅ መበለቷ ዳግመኛ አብሯት የሚኖርና የሚጦራት ሰው እንድታገኝ በማሰብ ልጁን “ለእናቱ ሰጣት።”—ሉቃስ 7:11-15
13. በራሳችን ተነሳሽነት የተቸገሩትን በመርዳት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ ሌሎችን በተአምር መመገብ ወይም የሞተ ሰው ማስነሳት አንችልም። ይሁንና በራሳችን ተነሳሽነት የተቸገሩትን በመርዳት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። አንድ የእምነት ባልንጀራችን ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ወድቆ ወይም ከሥራ ተፈናቅሎ ሊሆን ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:17) የአንዲት መበለት ቤት አፋጣኝ ጥገና ያስፈልገው ይሆናል። (ያዕቆብ 1:27) ማጽናኛ ወይም ተግባራዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሐዘን የደረሰበት ቤተሰብ እናውቅ ይሆናል። (1 ተሰሎንቄ 5:11) ችግር ላይ የወደቀ ሰው ስናይ እርዳታ ለመስጠት እስክንጠየቅ መጠበቅ የለብንም። (ምሳሌ 3:27) ርኅራኄ በራሳችን ተነሳስተን አቅማችን በፈቀደው መጠን ሌሎችን እንድንረዳ ይገፋፋናል። ትንሽ የሚመስል የደግነት ተግባር ወይም ከልብ የመነጩ ጥቂት የማጽናኛ ቃላት እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የርኅራኄ መግለጫዎች እንደሆኑ ፈጽሞ አትዘንጋ።—ቆላስይስ 3:12
ርኅራኄ እንዲሰብክ አነሳስቶታል
14. ኢየሱስ ምሥራቹን ለመስበኩ ሥራ ቅድሚያ የሰጠው ለምንድን ነው?
14 በዚህ መጽሐፍ ክፍል 2 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) ለዚህ ሥራ ቅድሚያ የሰጠው ለምንድን ነው? በዋነኝነት ለአምላክ ፍቅር ስለነበረው ነው። ሆኖም ኢየሱስ ሌላም የገፋፋው ምክንያት ነበር፤ ከልብ የመነጨ ርኅራኄ፣ ለሌሎች መንፈሳዊ ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጥ ገፋፍቶታል። ኢየሱስ ርኅራኄውን ካሳየባቸው መንገዶች ሁሉ የላቀው የሰዎችን መንፈሳዊ ጥማት ማርካቱ ነው። ኢየሱስ ይሰብክላቸው ለነበሩት ሰዎች ምን አመለካከት እንደነበረው የሚያሳዩ ሁለት ክስተቶችን እስቲ እንመልከት። ይህን ማድረጋችን በአገልግሎት እንድንካፈል የሚያነሳሳንን ውስጣዊ ግፊት ለማጤን ይረዳናል።
15, 16. ኢየሱስ ይሰብክላቸው ለነበሩት ሰዎች ምን አመለካከት እንደነበረው የሚያሳዩ ሁለት ክስተቶች ጥቀስ።
15 ጊዜው 31 ዓ.ም. ነው፤ ኢየሱስ ለሁለት ዓመት ያህል በቅንዓት ሲያገለግል ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ በገሊላ በሚገኙት ‘ከተሞችና መንደሮች እየዞረ’ ይሰብክ ጀመር። በዚያ ያየው ነገር ልቡን በጥልቅ ነካው። ሐዋርያው ማቴዎስ “ሕዝቡንም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው” በማለት ዘግቧል። (ማቴዎስ 9:35, 36) ኢየሱስ የሕዝቡ ነገር አንጀቱን በልቶታል። ያሉበትን አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ በሚገባ ተረድቶ ነበር። እንደ እረኛ እነሱን የመጠበቅ ኃላፊነት የነበረባቸው የሃይማኖት መሪዎች በደል እንደሚፈጽሙባቸውና ጨርሶ ቸል እንዳሏቸው ተገንዝቧል። ኢየሱስ ጥልቅ ርኅራኄ ስለገፋፋው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ተስፋ ያዘለውን መልእክት ለሰዎች ሰብኳል። ደግሞም ከአምላክ መንግሥት ምሥራች ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር አልነበረም።
16 ከተወሰኑ ወራት በኋላም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቶ ነበር፤ ጊዜው 32 ዓ.ም. ሲሆን የፋሲካ በዓል ተቃርቧል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ የሚያርፉበት ጸጥ ያለ ስፍራ ስለፈለጉ ጀልባ ተሳፍረው የገሊላን ባሕር አቋርጠው ሄዱ። ሆኖም ሕዝቡ የባሕሩን ዳርቻ ተከትሎ በመሮጥ ከጀልባዋ ቀድሞ ወደ ባሕሩ ማዶ ደረሰ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን ተሰማው? “ከጀልባዋ ሲወርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው። ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 6:31-34) በዚህ ጊዜም ኢየሱስ ሰዎቹ ምን ያህል በመንፈሳዊ እንደተራቡ ሲመለከት “በጣም አዘነላቸው።” “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” በመንፈሳዊ ተርበው ነበር፤ የሚንከባከባቸውም አልነበረም። ኢየሱስ ለሌሎች ለመስበክ የተነሳሳው ግዴታው እንደሆነ ስለተሰማው ብቻ ሳይሆን ሩኅሩኅ ስለነበረም ነው።
17, 18. (ሀ) በአገልግሎት እንድንካፈል የሚገፋፋን ምንድን ነው? (ለ) ለሌሎች ርኅራኄ ማሳየትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
17 የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን በአገልግሎት እንድንካፈል የሚገፋፋን ምንድን ነው? በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ እንደተመለከትነው ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮና ኃላፊነት ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16) ሆኖም በዚህ ሥራ የምንካፈለው ግዴታችን እንደሆነ ስለሚሰማን ብቻ መሆን የለበትም። የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነው። እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች ያለን ርኅራኄም እንድንሰብክ ይገፋፋናል። (ማርቆስ 12:28-31) ታዲያ ለሌሎች ርኅራኄ ማሳየትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
18 እኛም ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል፤ ኢየሱስ፣ ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” እንደነበር ተሰምቶታል። ለምሳሌ አንዲት የባዘነች በግ አገኘህ እንበል። ወደ ግጦሽ ቦታ የሚወስዳትም ሆነ ውኃ የሚያጠጣት እረኛ በማጣቷ በረሃብና በጥም ተጎሳቁላለች። ይህች በግ አታሳዝንህም? የምትበላውና የምትጠጣው ነገር ለመስጠትስ የተቻለህን ጥረት አታደርግም? ምሥራቹን ያልሰሙ ብዙ ሰዎች ከዚህች በግ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። መንፈሳዊ እረኞች ነን የሚሉት የሃይማኖት መሪዎቻቸው ችላ ብለዋቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ለመንፈሳዊ ረሃብና ጥማት ከመዳረጋቸውም ሌላ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እውነተኛ ተስፋ የላቸውም። እኛ ግን እነሱ የሚያስፈልጋቸው ነገር አለን፤ ይህም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ገንቢ መንፈሳዊ ምግብና የሚያረካ የእውነት ውኃ ነው። (ኢሳይያስ 55:1, 2) በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ያሉበትን መንፈሳዊ እጦት ስናስብ ከልብ እናዝንላቸዋለን። እንደ ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ የምናዝን ከሆነ ደግሞ የመንግሥቱን ተስፋ ለእነሱ ለማካፈል የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።
19. በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቁ የሆነን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለማበረታታት ምን ልናደርግ እንችላለን?
19 ሌሎች የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቁ የሆነን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለማበረታታት ፈለግን እንበል። ወይም ቀዝቅዞ የነበረን አንድ አስፋፊ በድጋሚ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለመርዳት አሰብን። እንዲህ ያሉ ሰዎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ልባቸውን ለመንካት መጣር ይኖርብናል። ኢየሱስ በመጀመሪያ ለሰዎቹ ‘እንዳዘነላቸው’ ከዚያም እንዳስተማራቸው አስታውስ። (ማርቆስ 6:34) ስለዚህ ጥናቶቻችን ወይም የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ርኅራኄ እንዲያዳብሩ ልንረዳቸው ይገባል፤ ያን ጊዜ እነሱም እንደ ኢየሱስ ልባቸው ምሥራቹን እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል። እንዲህ እያልን ልንጠይቃቸው እንችላለን፦ “የመንግሥቱን መልእክት መቀበልህ በሕይወትህ ውስጥ ምን አዎንታዊ ለውጦችን እንድታደርግ ረድቶሃል? ይህ መልእክት ያልደረሳቸው ሰዎችስ ምሥራቹን መስማት ያለባቸው አይመስልህም? አንተ በበኩልህ እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?” እርግጥ ነው፣ በአገልግሎት እንድንካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅርና እሱን ለማገልገል ያለን ልባዊ ፍላጎት ነው።
20. (ሀ) የኢየሱስ ተከታይ መሆን ምን ማድረግን ይጨምራል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
20 የኢየሱስ ተከታይ መሆን ሲባል የእሱን ንግግርና ተግባር መድገም ማለት ብቻ አይደለም። የእሱን “አስተሳሰብ” ማዳበርንም ይጨምራል። (ፊልጵስዩስ 2:5) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ከኢየሱስ ንግግርና ተግባር በስተ ጀርባ ያለውን አመለካከትና ስሜት ስለሚገልጽልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ባወቅን መጠን ይበልጥ የሌሎች ስሜት የሚገባንና ከልብ ሩኅሩኅ እንሆናለን፤ ይህም ኢየሱስ ሰዎችን በያዘበት መንገድ ሌሎችን እንድንይዝ ያስችለናል። (1 ቆሮንቶስ 2:16) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ በተለይ ለተከታዮቹ ፍቅር ያሳየባቸውን የተለያዩ መንገዶች እንመለከታለን።