በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ሦስት

‘እኔ አብን እወደዋለሁ’

‘እኔ አብን እወደዋለሁ’

1, 2. ሐዋርያው ዮሐንስ ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ስላሳለፉት የመጨረሻ ምሽት ምን አሳውቆናል?

 አረጋዊው ሰው ብዕሩን ቀለም ውስጥ እየነከረ ይጽፋል፤ በአእምሮው ውስጥ ብዙ ትውስታዎች አሉት። ይህ ሰው ዮሐንስ ይባላል፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል በሕይወት ያለው እሱ ብቻ ነው። አሁን 100 ዓመት ገደማ የሚሆነው ዮሐንስ ወደ ሰባ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ወዳሳለፈው አንድ የማይረሳ ምሽት በሐሳብ ሄዷል፤ ይህ ምሽት እሱና ሌሎቹ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ያሳለፉት የመጨረሻ ምሽት ነበር። ዮሐንስ በአምላክ መንፈስ መሪነት ስለሚጽፍ በወቅቱ የነበሩትን ነገሮች በዝርዝር ማስታወስ አልተቸገረም።

2 በዚያን ምሽት ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚገደል በግልጽ ተናገረ። ኢየሱስ እንደዚያ ባለ አሰቃቂ ሁኔታ ለመገደል ፈቃደኛ የሆነበትን ምክንያት የገለጸው ዮሐንስ ብቻ ነው፤ ኢየሱስ ምን እንዳለ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው። ተነሱ ከዚህ እንሂድ።”​—⁠ዮሐንስ 14:​31

3. ኢየሱስ አባቱን እንደሚወደው ያሳየው እንዴት ነው?

3 ‘እኔ አብን እወደዋለሁ።’ ኢየሱስ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አልነበረም። እንዲህ ሲባል ግን ይህን አባባል ደጋግሞ ይናገር ነበር ማለት አይደለም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ ኢየሱስ አባቱን እንደሚወደው በቀጥታ የተናገረው በዮሐንስ 14:​31 ላይ ብቻ ነው። ይሁንና ኢየሱስ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን በአኗኗሩ አሳይቷል። ለይሖዋ ያለው ፍቅር በየዕለቱ በግልጽ ይታይ ነበር። ድፍረቱ፣ ታዛዥነቱና ጽናቱ ሁሉ ለአምላክ ያለው ፍቅር መገለጫ ናቸው። መላው አገልግሎቱ ከዚህ ፍቅር የመነጨ ነው።

4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የሚናገረው ስለ ምን ዓይነት ፍቅር ነው? ኢየሱስ ለይሖዋ ስላለው ፍቅርስ ምን ማለት ይቻላል?

4 ዛሬ አንዳንዶች፣ አፍቃሪ የሆኑ ሰዎች ቅልስልስ እንደሆኑ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ስለ ፍቅር ሲነሳ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው የፍቅር ግጥምና የፍቅር ዘፈን ምናልባትም ከተቃራኒ ፆታ ፍቅር ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሚያነሆልል ስሜት ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዛሬ ዓለም ፍቅርን በሚገልጽበት ተራ መንገድ ባይሆንም ክብሩን በጠበቀ አነጋገር ስለ ተቃራኒ ፆታ ፍቅር ይገልጻል። (ምሳሌ 5:​15-21) ያም ሆኖ የአምላክ ቃል ይበልጥ የሚያወሳው ስለ ሌላ ዓይነት ፍቅር ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር ስሜታዊነት የሚገንንበት የወረት ፍቅር አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስሜት አልባና በአእምሮ ስሌት ብቻ የሚመራ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከልብም ሆነ ከአእምሮ ጋር የሚያያዝ ባሕርይ ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር የሚመነጨው ከውስጥ ነው፤ በላቁ መሥፈርቶች የሚመራ ሲሆን ጠቃሚ የሆኑ ተግባሮችን በማከናወን ይገለጻል። ይህ ዓይነቱ ፍቅር ወረትም አልባሌም አይደለም። የአምላክ ቃል “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይናገራል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:8

5 በምድር ላይ ከኖሩ ሰዎች መካከል የኢየሱስን ያህል ለይሖዋ ፍቅር ያለው የለም። አምላክ ከሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” የሚለው ትእዛዝ እንደሆነ የተናገረው ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ በማክበር ረገድ የሚተካከለው ማንም የለም። (ማርቆስ 12:​30) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ሊያዳብር የቻለው እንዴት ነው? በምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሁሉ ለአምላክ ያለውን ፍቅር ጠብቆ እንዲኖር ያስቻለው ምንድን ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ረጅም ዘመን ያስቆጠረና ጠንካራ የሆነ የፍቅር ትስስር

6, 7. ምሳሌ 8:​22-31 ስለ ጥበብ ሳይሆን ስለ አምላክ ልጅ እንደሚገልጽ እንዴት እናውቃለን?

6 ከአንድ ጓደኛህ ጋር አብራችሁ አንድ ሥራ ሠርታችሁ ታውቃላችሁ? ከሆነ፣ በዚህ አጋጣሚ ይበልጥ እንደተቀራረባችሁና ወዳጅነታችሁ እንደተጠናከረ አስተውለህ ይሆናል። ይህ ተሞክሮ በይሖዋና በአንድያ ልጁ መካከል ያለውን ፍቅር በተሻለ ሁኔታ እንድትረዳው ያደርግሃል። ምሳሌ 8:​30 ብዙ ጊዜ የምንጠቅሰው ጥቅስ ቢሆንም እስቲ አሁን በዙሪያው ካለው ሐሳብ አንጻር በስፋት እንመርምረው። ከ22 እስከ 31 ባሉት ቁጥሮች ላይ ጥበብ በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸበትን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ እናገኛለን። እነዚህ ቃላት የአምላክን ልጅ እንደሚያመለክቱ እንዴት እናውቃለን?

7 በቁጥር 22 ላይ ጥበብ “ይሖዋ የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፤ ከብዙ ዘመን በፊት ካከናወናቸው ሥራዎች ቀዳሚው አደረገኝ” በማለት ትናገራለች። ጥበብ በሆነ ወቅት ላይ ‘የተፈጠረ’ ባሕርይ ስላልሆነ እዚህ ላይ ያለው አገላለጽ ከጥበብ ያለፈ ነገርን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖረው ይሖዋ ጥበበኛ ያልነበረበት ጊዜ የለም፤ በመሆኑም ጥበብ ከሆነ ወቅት ጀምሮ ሕልውና እንዳገኘ ተደርጎ ሊገለጽ አይችልም። (መዝሙር 90:2) የአምላክ ልጅ ግን “የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው።” ተፈጥሯል ወይም ወደ ሕልውና እንዲመጣ ተደርጓል፤ ከይሖዋ ሥራዎች ሁሉ ቀዳሚው እሱ ነው። (ቆላስይስ 1:​15) በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው የአምላክ ልጅ ምድርና ሰማያት ከመፈጠራቸው በፊት በሕይወት ነበረ። ኢየሱስ ቃል ማለትም የአምላክ ቃል አቀባይ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ ጥበብ ፍጹም መገለጫ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 1:1

8. የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምን ይሠራ ነበር? የፍጥረት ሥራዎችን አይተን ስንደነቅ ምን ነገር ወደ አእምሯችን ሊመጣ ይችላል?

8 የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በነበረው ረጅም ጊዜ ውስጥ ምን ይሠራ ነበር? ቁጥር 30 “የተዋጣለት ሠራተኛ” በመሆን ከአምላክ ጎን ሲሠራ እንደነበር ይነግረናል። ይህ ምን ማለት ነው? ቆላስይስ 1:​16 እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ . . . የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው። ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ በኩልና ለእሱ ነው።” በመሆኑም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ሌሎች ፍጥረታትን ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው የተዋጣለት ሠራተኛ በሆነው በልጁ በኩል ነው፤ ይህም በሰማይ ያሉትን መንፈሳዊ ፍጥረታት፣ ግዙፍ የሆነውን ግዑዝ ጽንፈ ዓለም እንዲሁም ምድርንና በላይዋ ያሉትን የተለያዩ አስደናቂ ዕፀዋትና እንስሳት ብሎም የምድር ፍጥረታት ቁንጮ የሆነውን የሰውን ልጅ ያካትታል። በአብና በወልድ መካከል ያለው ይህ ትብብር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንድ ንድፍ አውጪና በአንድ ግንበኛ ወይም ሕንፃ ተቋራጭ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የግንበኛው ሚና፣ ንድፍ አውጪው ያወጣው አስደናቂ ንድፍ እውን እንዲሆን ማድረግ ነው። አንድን የፍጥረት ሥራ አይተን ስንደነቅ ለታላቁ ንድፍ አውጪ እውቅና እየሰጠን እንደሆነ የታወቀ ነው። (መዝሙር 19:1) ሆኖም በፈጣሪና “የተዋጣለት ሠራተኛ” በተባለው ልጁ መካከል ስላለው ለረጅም ዘመን የዘለቀ አስደሳች ትብብር ማሰባችንም አይቀርም።

9, 10. (ሀ) በይሖዋና በልጁ መካከል ያለው ትስስር ይበልጥ እንዲጠነክር ያደረገው ምንድን ነው? (ለ) በሰማይ ካለው አባትህ ጋር ያለህን ዝምድና ሊያጠናክርልህ የሚችለው ምንድን ነው?

9 ፍጽምና የጎደላቸው ሁለት ሰዎች አብረው ሲሠሩ አንዳንድ ጊዜ በመካከላቸው አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። በይሖዋና በልጁ መካከል ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው! ወልድ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ከአባቱ ጋር ሲሠራ የቆየ ቢሆንም “በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር” ብሏል። (ምሳሌ 8:​30) በእርግጥም ወልድ ከአባቱ ጋር አብሮ መሥራት ያስደስተው ነበር፤ አባቱም እንዲሁ ይሰማው ነበር። ወልድ የአባቱን ባሕርያት በመኮረጅ ይበልጥ እሱን እየመሰለ መሄዱ የሚጠበቅ ነው። በአብና በወልድ መካከል ያለው ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጠነከረ መምጣቱ ምንም አያስገርምም! በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ያህል ረጅም ዘመን ያስቆጠረና ጠንካራ የሆነ የፍቅር ትስስር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

10 ታዲያ ይህ ምን ያስገነዝበናል? ከይሖዋ ጋር እንዲህ ዓይነት የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። ማናችንም ብንሆን የወልድን ያህል ከፍ ያለ ቦታ ሊኖረን እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እኛም ግሩም አጋጣሚ አለን። ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ይበልጥ ሊቀራረብ የቻለው አብሮ በመሥራቱ እንደሆነ አስታውስ። ይሖዋ እኛም ከእሱ ጋር ‘አብረን እንድንሠራ’ በፍቅር ተነሳስቶ ግብዣ አቅርቦልናል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል አገልግሎታችንን ስናከናውን ከአምላክ ጋር አብረን እየሠራን እንደሆነ ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። በዚህ ሥራ ስንካፈል፣ ከይሖዋ ጋር ያስተሳሰረን ፍቅር ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል። ታዲያ ከዚህ የላቀ ምን መብት ሊኖር ይችላል?

ኢየሱስ ለይሖዋ ያለውን የጠለቀ ፍቅር ጠብቆ መቆየት የቻለው እንዴት ነው?

11-13. (ሀ) ፍቅርን ሕይወት እንዳለው ነገር አድርገን መመልከታችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ወቅት ለይሖዋ ያለው ፍቅር ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ሰው ሆኖ ምድር ላይ በኖረበት ወቅት ከይሖዋ ለመማር ጉጉት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?

11 ነገሩን ለመረዳት እንዲያግዘን፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ፍቅር ሕይወት እንዳለው ነገር አድርገን መመልከታችን ጠቃሚ ነው። አንድ ተክል እንዲያድግና እንዲያብብ ከተፈለገ እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል፤ ፍቅርም እንደዛው። ቸል ከተባለና እንክብካቤ ካልተደረገለት ግን እየከሰመ ሊሄድና ሊሞት ይችላል። ኢየሱስ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር እንደ ነገሩ ችላ አላለውም። በምድር ላይ ባሳለፈው ጊዜ ሁሉ ለአባቱ ያለው ፍቅር እንደጠነከረና እንዳበበ እንዲቀጥል አድርጓል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

12 ኢየሱስ ልጅ ሳለ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የተፈጠረውን ነገር አሁንም መልሰን እናንሳ። በጭንቀት ተውጠው የነበሩትን ወላጆቹን ምን እንዳላቸው ታስታውሳለህ? “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 2:​49) በዚህ ወቅት ኢየሱስ ልጅ ስለነበር ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ያሳለፈውን ሕይወት ገና የሚያስታውሰው አይመስልም። ያም ሆኖ ለአባቱ ጥልቅ ፍቅር ነበረው። ይህ ፍቅር የሚገለጸው ደግሞ በአምልኮ መሆኑን ያውቅ ነበር። በመሆኑም ንጹሕ አምልኮ ከሚከናወንበት ከአባቱ ቤት በላይ የሚያስደስተው ሌላ ቦታ በምድር ላይ የለም። እዚያ ለመገኘት ይጓጓ የነበረ ሲሆን ከዚያ መውጣትም አይፈልግም። በተጨማሪም በዚያ የሚገኘው እንዲሁ እንደ ተመልካች ሆኖ ብቻ አልነበረም። ስለ ይሖዋ ለመማርም ሆነ የሚያውቀውን ነገር ለሌሎች ለመናገር ይጓጓ ነበር። ኢየሱስ ገና 12 ዓመት ሳይሆነው በፊትም እንዲህ ዓይነት ስሜት ነበረው፤ ከዚያ በኋላም ቢሆን ይህ ስሜቱ አልጠፋም።

13 ወልድ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በጉጉት ከአባቱ ትምህርት ሲቀስም ቆይቷል። በኢሳይያስ 50:4-6 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት እንደሚጠቁመው ይሖዋ ለልጁ መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ትምህርት ሰጥቶታል። ይህ ትምህርት ይሖዋ በቀባው ላይ ስለሚደርሱት መከራዎች መማርን የሚጨምር ቢሆንም ወልድ ትምህርቱን በጉጉት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣና ትልቅ ሰው ከሆነም በኋላ ሁልጊዜ ወደ አባቱ ቤት ለመሄድ ይጓጓ ነበር፤ ይሖዋ በዚያ እንዲቀርብ በሚፈልገው አምልኮና ትምህርት መሳተፍ ያስደስተው ነበር። ኢየሱስ አዘውትሮ ወደ ቤተ መቅደሱና ወደ ምኩራብ ይሄድ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሉቃስ 4:​16፤ 19:​47) እኛም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሕያው ሆኖ እንዲቀጥልና እንዲያብብ የምንፈልግ ከሆነ አዘውትረን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አለብን፤ ስብሰባዎች ይሖዋን ለማምለክ እንዲሁም ስለ እሱ ያለንን እውቀትና አድናቆት ለማሳደግ አጋጣሚ ይሰጡናል።

“ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ”

14, 15. (ሀ) ኢየሱስ ብቻውን መሆን ይፈልግ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ጸሎቶች አባቱን እንደሚቀርበውና እንደሚያከብረው የሚያሳዩት እንዴት ነው?

14 በተጨማሪም ኢየሱስ ዘወትር በመጸለይ ለይሖዋ ያለው ፍቅር ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጓል። የሚገርመው፣ ኢየሱስ ተግባቢና ከሌሎች ጋር መሆን የሚያስደስተው ሰው ቢሆንም ብቻውን መሆን የሚመርጥበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ሉቃስ 5:​16 “ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ጭር ወዳሉ ስፍራዎች በመሄድ ይጸልይ ነበር” ይላል። በተመሳሳይም ማቴዎስ 14:​23 እንደሚከተለው ይላል፦ “ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ በዚያ ብቻውን ነበር።” ኢየሱስ በእነዚህም ሆነ በሌሎች ጊዜያት ብቻውን መሆን የፈለገው ብቸኝነት ስለሚወድ ወይም ከሌሎች ጋር መሆን ስለሚጨንቀው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ብቻውን ሆኖ በጸሎት አማካኝነት ከአባቱ ከይሖዋ ጋር በነፃነት መነጋገር ስለፈለገ ነው።

15 ኢየሱስ በሚጸልይበት ጊዜ አንዳንዴ “አባ፣ አባት ሆይ” የሚለውን መግለጫ ይጠቀም ነበር። (ማርቆስ 14:​36) በኢየሱስ ዘመን “አባ” በቤተሰብ ውስጥ ‘አባትን’ ለመጥራት የሚያገለግል ቅርበትን የሚያሳይ ቃል ነው። ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ ልጆች መጀመሪያ አፋቸውን ከሚፈቱባቸው ቃላት አንዱ ነበር። ሆኖም ይህ ቃል አክብሮትንም የሚገልጽ ነው። ወልድ የሚወደውን አባቱን በዚህ ቃል መጥራቱ በመካከላቸው ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ የአባትነት ሥልጣን ያለውን ጥልቅ አክብሮትም ይገልጻል። በጽሑፍ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ጸሎቶች በሙሉ ኢየሱስ አባቱን ምን ያህል እንደሚቀርበውና እንደሚያከብረው ያሳያሉ። ለምሳሌ ዮሐንስ ምዕራፍ 17 ኢየሱስ በመጨረሻው ምሽት ያቀረበውን ረጅምና ከልብ የመነጨ ጸሎት ይዟል። ይህን ጸሎት መመርመራችን ስሜታችን በጥልቅ እንዲነካ ያደርጋል፤ ይህን ጸሎት ለመኮረጅ መጣራችን ደግሞ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲባል ግን ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት እንደግማለን ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባታችንን አዘውትረን እንዲሁም ከልብ በመነጨ ስሜት ለማነጋገር እንጥራለን ማለት ነው። እንዲህ ማድረጋችን ለእሱ ያለን ፍቅር ሕያውና ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳናል።

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ለአባቱ ያለውን ፍቅር በቃላት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የአባቱን ልግስና የገለጸው በምን መንገድ ነው?

16 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ኢየሱስ ‘አብን እወደዋለሁ’ የሚለውን መግለጫ ደጋግሞ አልተጠቀመም። ሆኖም ፍቅሩን በቃላት የገለጸባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? ኢየሱስ ራሱ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ . . . በይፋ አወድስሃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:​25) በዚህ መጽሐፍ ክፍል 2 ላይ እንዳየነው ኢየሱስ ሰዎች ስለ አባቱ እንዲያውቁ በመርዳት እሱን ማወደስ ያስደስተው ነበር። ለአብነት ያህል፣ ስለ ይሖዋ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ ዓመፀኛ የሆነ ልጁን ይቅር ለማለት ከፍተኛ ጉጉት ስላለው አንድ አባት ጠቅሷል፤ ይህ አባት፣ ልጁ ተጸጽቶ የሚመለስበትን ጊዜ ይናፍቅ ስለነበር ገና ከሩቅ ሲያየው ሮጦ ወደ እሱ በመሄድ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው። (ሉቃስ 15:​20) ይህን ታሪክ ሲያነብ ኢየሱስ የይሖዋን ፍቅርና ይቅር ባይነት በገለጸበት መንገድ ልቡ የማይነካ ይኖራል?

17 ኢየሱስ አባቱን ስለ ልግስናው ብዙ ጊዜ አወድሶታል። አባታችን የሚያስፈልገንን መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንደምንችል ለማሳየት ፍጹም ያልሆኑ ወላጆችን ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። (ሉቃስ 11:​13) እንዲሁም ኢየሱስ፣ አባቱ በልግስና ስለሰጣቸው አስደናቂ ተስፋዎች ተናግሯል። ኢየሱስ እሱ ራሱ በናፍቆት የሚጠብቀውን ተስፋ ሲገልጽ ተመልሶ በሰማይ ከአባቱ ጎን ለመሆን እንደሚጓጓ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:​28፤ 17:5) በተጨማሪም ይሖዋ ለክርስቶስ “ትንሽ መንጋ” ስለሰጠው ተስፋ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል፤ በሰማይ እንደሚኖሩና ከመሲሐዊው ንጉሥ ጋር አብረው እንደሚገዙ ገልጾላቸዋል። (ሉቃስ 12:​32፤ ዮሐንስ 14:2) እንዲሁም ሊሞት በማጣጣር ላይ የነበረውን ወንጀለኛ በገነት ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዳለው በመግለጽ አጽናንቶታል። (ሉቃስ 23:​43) ኢየሱስ ስለ አባቱ ታላቅ ልግስና በዚህ መንገድ መናገሩ ለይሖዋ ያለው ፍቅር ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል እንደረዳው ጥርጥር የለውም። ብዙዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች ከራሳቸው ተሞክሮ እንደተገነዘቡት ስለ ይሖዋና እሱን ለሚወዱት ሰዎች ስለሰጣቸው ተስፋዎች ከመናገር የበለጠ ለእሱ ያለንን ፍቅርና በእሱ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክር ነገር የለም።

አንተስ ኢየሱስ ለይሖዋ ያለው ዓይነት ፍቅር ለማዳበር ትጥራለህ?

18. የኢየሱስን ፈለግ ከምንከተልባቸው መንገዶች ሁሉ የላቀው የትኛው ነው? ለምንስ?

18 የኢየሱስን ፈለግ ከምንከተልባቸው መንገዶች ሁሉ የላቀው ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አእምሯችንና ኃይላችን መውደድ ነው። (ሉቃስ 10:​27) ይህ ፍቅር መጠኑ የሚለካው ባለን ጥልቅ ስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባራችንም ጭምር ነው። ኢየሱስ ለአባቱ ያለው ፍቅር እንዲሁ የስሜት ወይም ‘እኔ አብን እወደዋለሁ’ ብሎ የመናገር ጉዳይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 14:​31) ሰይጣን ማንም ሰው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተነሳስቶ ይሖዋን አያገለግልም የሚል ክስ ሰንዝሯል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን በተንኮል ተነሳስቶ ለሰነዘረው ክስ የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት ኢየሱስ አባቱን ምን ያህል እንደሚወደው በድፍረት ለዓለም አሳይቷል። ሕይወቱን አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ ታዛዥ ሆኗል። አንተስ የኢየሱስን ፈለግ ትከተላለህ? ይሖዋ አምላክን ከልብ እንደምትወደው ለዓለም ታሳያለህ?

19, 20. (ሀ) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንድንገኝ የሚያነሳሱን ምን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን? (ለ) ለግል ጥናት፣ ለማሰላሰልና ለጸሎት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

19 በተፈጥሯችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር ለማሳየት የሚያነሳሳ መንፈሳዊ ፍላጎት አለን። በመሆኑም አባታችን ይሖዋ ለእሱ ያለን ፍቅር እያደገና እየጠነከረ እንዲሄድ የሚያደርግ የአምልኮ ዝግጅት አድርጎልናል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝ እዚያ የተገኘኸው አምላክህን ለማምለክ መሆኑን አትዘንጋ። ከልብ የመነጨ ጸሎት ሲቀርብ አብረህ በመጸለይ፣ የውዳሴ መዝሙሮችን አብረህ በመዘመር፣ በጥሞና በማዳመጥና አጋጣሚው ሲገኝ ተሳትፎ በማድረግ አምልኮ ማቅረብ ትችላለህ። በተጨማሪም እነዚህ ስብሰባዎች የእምነት ባልንጀሮችህን ለማበረታታት አጋጣሚ ይፈጥሩልሃል። (ዕብራውያን 10:​24, 25) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ይሖዋን ዘወትር ማምለክህ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ እየጠነከረ እንዲሄድ ይረዳሃል።

20 የግል ጥናት ማድረግ፣ ማሰላሰልና መጸለይም ተመሳሳይ ጥቅም ያስገኙልናል። እነዚህን ዝግጅቶች ብቻህን ከይሖዋ ጋር ለመሆን እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገህ ተመልከታቸው። በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ቃል ስታጠናና በዚያ ላይ ስታሰላስል ይሖዋ ሐሳቡን እየገለጸልህ ነው። በምትጸልይበት ጊዜ ደግሞ የልብህን አውጥተህ እየነገርከው ነው። ጸሎት አምላክ አንድ ነገር እንዲያደርግልን መለመን ማለት ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። ከዚህ ይልቅ ላገኘሃቸው በረከቶች ይሖዋን የምታመሰግንበት እንዲሁም ድንቅ ለሆኑት ሥራዎቹ እሱን የምታወድስበት አጋጣሚም ጭምር ነው። (መዝሙር 146:1) ይሖዋን የምታመሰግንበትና እሱን እንደምትወደው የምታሳይበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በደስታና በቅንዓት ይሖዋን በይፋ ማወደስ ነው።

21. ይሖዋን መውደድ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ ምን እንመረምራለን?

21 ዘላቂ ደስታ ማግኘትህ የተመካው ለአምላክ ባለህ ፍቅር ላይ ነው። አዳምና ሔዋን ይህን ፍቅር አዳብረው ቢሆን ኖሮ ስኬታማ በሆኑ ነበር። አንተም የእምነት ፈተናዎችን በስኬት ማለፍ፣ የኃጢአት ማባበያዎችን ማሸነፍ እንዲሁም የሚደርስብህን ማንኛውንም መከራ በጽናት መወጣት ከፈለግህ ቁልፉ ለአምላክ ያለህ ፍቅር ነው። የኢየሱስ ተከታይ መሆናችንን የምናሳይበት ዋነኛ መንገድም ነው። እርግጥ ነው፣ አምላክን መውደድ ሰዎችን ከመውደድ ጋር ተዛማጅነት አለው። (1 ዮሐንስ 4:​20) በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ ኢየሱስ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በምዕራፍ 14 ላይ፣ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን በቀላሉ ሊቀርቡት የቻሉት ለምን እንደሆነ እንመረምራለን።