ምዕራፍ አሥራ ስድስት
“ኢየሱስ . . . እስከ መጨረሻው ወደዳቸው”
1, 2. ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የነበረውን የመጨረሻ ምሽት ያሳለፈው እንዴት ነው? እነዚህ ሰዓታት ለእሱ በጣም ውድ የሆኑት ለምንድን ነው?
ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ደርብ ላይ ከሐዋርያቱ ጋር ተሰብስቧል፤ ይህ ከእነሱ ጋር የሚያሳልፈው የመጨረሻ ምሽት እንደሆነ ያውቃል። ወደ አባቱ የሚመለስበት ጊዜ እየቀረበ ነው። ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ኢየሱስ በቁጥጥር ሥር ይውላል፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ገጥሞት የማያውቅ ከባድ የእምነት ፈተና ይደቀንበታል። ሆኖም ከፊት ለፊቱ የተጋረጠው ሞት እንኳ ሐዋርያቱ ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ትኩረት ከመስጠት አላገደውም።
2 ኢየሱስ ተለይቷቸው እንደሚሄድ ለሐዋርያቱ በመንገር አእምሯቸውን እንዲያዘጋጁ አድርጓል፤ ሆኖም ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር ለማበርታት ገና ብዙ የሚነግራቸው ነገር አለ። በመሆኑም በቀረው ውድ ጊዜ፣ በታማኝነት እንዲጸኑ የሚረዷቸውን አስፈላጊ ነገሮች አስተማራቸው። በዚህ ጊዜ የተናገረው ነገር ለእነሱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ይበልጥ የሚገልጽ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ከራሱ ይልቅ ለሐዋርያቱ ይበልጥ የተጨነቀው ለምንድን ነው? ከእነሱ ጋር የሚያሳልፋቸው እነዚህ የመጨረሻ ሰዓታት ለእሱ በጣም ውድ የሆኑት ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ሐዋርያቱን ስለሚወዳቸው ነው። ለእነሱ ያለው ፍቅር እጅግ ጥልቅ ነው።
3. ኢየሱስ ተከታዮቹን እንደሚወዳቸው የገለጸው በመጨረሻው ምሽት ብቻ አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?
3 ሐዋርያው ዮሐንስ በዚያ ምሽት ስለተከናወኑት ነገሮች ከአሥርተ ዓመታት በኋላ በመንፈስ መሪነት ሲጽፍ ዘገባውን የጀመረው እንደሚከተለው በማለት ነው፦ “የፋሲካ በዓል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደደረሰ ስላወቀ በዓለም የነበሩትንና የወደዳቸውን ተከታዮቹን [“የራሱ የሆኑትን፣” ግርጌ] እስከ መጨረሻው ወደዳቸው።” (ዮሐንስ 13:1) ኢየሱስ “የራሱ የሆኑትን” እንደሚወዳቸው የገለጸው በዚህ ምሽት ብቻ አልነበረም። አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ገልጿል። ኢየሱስ ፍቅሩን የገለጸባቸውን አንዳንድ መንገዶች መመርመራችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ መሆናችንን የምናስመሠክረው በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ በመከተል ነው።
በትዕግሥት ይዟቸዋል
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ትዕግሥት ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሦስቱ ሐዋርያቱ ነቅተው መጠበቅ እንዳቃታቸው ባየ ጊዜ ምን አላቸው?
4 ፍቅርና ትዕግሥት የማይነጣጠሉ ባሕርያት ናቸው። አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4 “ፍቅር ታጋሽ . . . ነው” ይላል፤ ትዕግሥት ደግሞ ቻይ መሆንን ይጨምራል። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ትዕግሥት አስፈልጎት ነበር? እንዴታ! ምዕራፍ 3 ላይ እንደተመለከትነው ሐዋርያቱ ትሕትናን ለማዳበር ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል። ‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል ብዙ ጊዜ ተከራክረዋል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን ተሰማው? በድርጊታቸው በመበሳጨት ተቆጣቸው ወይም ተመረረባቸው? በፍጹም! በትዕግሥት ይመክራቸው ነበር፤ ከእነሱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት እንኳ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ “በመካከላቸው የጦፈ ክርክር” ሲነሳ ኢየሱስ በትዕግሥት አስተምሯቸዋል።—ሉቃስ 22:24-30፤ ማቴዎስ 20:20-28፤ ማርቆስ 9:33-37
5 በዚያው ምሽት ኢየሱስ ከ11ዱ ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ በሄደበት ወቅትም በድጋሚ ትዕግሥቱን የሚፈትን ሁኔታ አጋጥሞታል። ኢየሱስ ስምንቱን ሐዋርያት ባሉበት ትቶ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ አትክልቱ ስፍራ ዘልቆ ገባ። ከዚያም “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ። እዚህ ሁኑና ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ከእነሱ ትንሽ ራቅ ብሎም አጥብቆ ይጸልይ ጀመር። ረዘም ላለ ጊዜ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ወደ ሦስቱ ሐዋርያት ተመለሰ። በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ ምን ሲያደርጉ አገኛቸው? በኢየሱስ ላይ ታላቅ ፈተና በተደቀነበት በዚህ ወቅት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዷቸዋል! ታዲያ ነቅተው ባለመጠበቃቸው በቁጣ ገሠጻቸው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ በትዕግሥት መከራቸው። በደግነት የተናገረው ነገር ሐዋርያቱ የነበረባቸውን ውጥረትና ድክመታቸውን እንደተረዳላቸው የሚያሳይ ነው። a “እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው” አላቸው። ኢየሱስ በዚያ ምሽት ከአንዴም ሦስት ጊዜ ተኝተው ቢያገኛቸውም በትዕግሥት ይዟቸዋል!—ማቴዎስ 26:36-46
6. ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ በሐዋርያቱ ተስፋ እንዳልቆረጠባቸው ማወቅ ያበረታታል። ትዕግሥቱም የኋላ ኋላ ፍሬ አፍርቷል፤ ከጊዜ በኋላ እነዚህ ታማኝ ሰዎች ትሑትና ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት ተገንዝበዋል። (1 ጴጥሮስ 3:8፤ 4:7) እኛስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በተለይ ሽማግሌዎች ትዕግሥተኛ መሆን ያስፈልጋቸዋል። አንድ ሽማግሌ ደክሞት ወይም የሚያስጨንቅ ነገር ገጥሞት ባለበት ሰዓት አንድ የእምነት ባልንጀራው ችግሩን ሊያወያየው ወደ እሱ ይመጣ ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ ምክር ሲሰጣቸው ቶሎ ተግባራዊ አያደርጉ ይሆናል። ያም ሆኖ ትዕግሥተኛ የሆኑ ሽማግሌዎች “በገርነት” ለማረምና “መንጋውን በርኅራኄ [ለመያዝ]” ይጥራሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25፤ የሐዋርያት ሥራ 20:28, 29) ወላጆችም ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተላቸው ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ልጆች የሚሰጣቸውን ምክር ወይም እርማት ለመቀበል ዳተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ወላጆች አፍቃሪና ታጋሽ መሆናቸው ልጆቻቸውን ለማሠልጠን በሚያደርጉት ጥረት ተስፋ እንዳይቆርጡ ይረዳቸዋል። እንዲህ ያለው ትዕግሥት ታላቅ ወሮታ ያስገኛል።—መዝሙር 127:3
የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አሟልቶላቸዋል
7. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አካላዊም ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት ትኩረት የሰጠው እንዴት ነው?
7 ፍቅር ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ተግባር ይገለጻል። (1 ዮሐንስ 3:17, 18) ፍቅር “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።” (1 ቆሮንቶስ 13:5) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አካላዊም ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጥ ያነሳሳው ፍቅር ነው። ብዙውን ጊዜ እነሱ ሳይጠይቁት በራሱ ተነሳስቶ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያደርግላቸው ነበር። እንደደከማቸው ባየ ጊዜ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” ብሏቸዋል። (ማርቆስ 6:31) እንደራባቸው ባስተዋለ ጊዜ ደግሞ እነሱንም ሆነ እሱ ሲያስተምር ለማዳመጥ የመጡትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መግቧቸዋል።—ማቴዎስ 14:19, 20፤ 15:35-37
8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ነገር አስተውሎ ፍላጎታቸውን እንዳሟላላቸው የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሳለ ስለ እናቱ ደህንነት ያስብ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በመንፈሳዊ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ ነበር፤ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታም አድርጎላቸዋል። (ማቴዎስ 4:4፤ 5:3) በሚያስተምርበት ጊዜ በአብዛኛው ልዩ ትኩረት ይሰጣቸው ነበር። የተራራውን ስብከት ያቀረበው በተለይ ደቀ መዛሙርቱን ለመጥቀም ሲል ነው። (ማቴዎስ 5:1, 2, 13-16) በምሳሌዎች ካስተማረ ደግሞ “ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ . . . ለደቀ መዛሙርቱ ሁሉንም ነገር ያብራራላቸው ነበር።” (ማርቆስ 4:34) ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ተከታዮቹ መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ እንዲያገኙ ሲል “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚሾምላቸው አስቀድሞ ተናግሯል። ይህ ታማኝ ባሪያ፣ በምድር ላይ ያሉ ጥቂት ቅቡዓን የኢየሱስ ወንድሞችን ያቀፈ ቡድን ሲሆን ከ1919 ዓ.ም. ጀምሮ “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ምግብ ሲያቀርብ ቆይቷል።—ማቴዎስ 24:45
9 ኢየሱስ በሞተበት ዕለት እንኳ ለሚወዳቸው ሰዎች መንፈሳዊ ደህንነት እንደሚጨነቅ አሳይቷል። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በጣም እየተሠቃየ ነው። አየር ለመሳብ ሲሞክር በእግሩ ተጠቅሞ ሰውነቱን ወደ ላይ መግፋት ይኖርበታል። ይህን ሲያደርግ፣ የሰውነቱ ክብደት እግሩ በምስማር የተበሳበት ቦታ ላይ ስለሚያርፍ ምስማሩ እግሩን ይበልጥ እየቀደደው ይገባል፤ በግርፋት የተተለተለው ጀርባው ደግሞ ከተሰቀለበት እንጨት ጋር ይፋተጋል፤ ይህ ለከባድ ሥቃይ እንደሚዳርገው ጥርጥር የለውም። መናገር ትንፋሽን መቆጣጠር ይጠይቃል፤ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መናገር ምን ያህል እንደሚከብድና እንደሚያሠቃይ መገመት ያዳግታል። ያም ሆኖ ኢየሱስ ሊሞት በማጣጣር ላይ ሳለ እናቱን ማርያምን ከልብ እንደሚወዳት የሚያሳይ ነገር ተናግሯል። ማርያምንና ሐዋርያው ዮሐንስን በአቅራቢያው ቆመው ሲያያቸው እንደምንም ኃይሉን አሰባስቦ ድምፁን በማሰማት እናቱን “አንቺ ሴት፣ ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። ከዚያም ዮሐንስን “እናትህ ይህችውልህ!” አለው። (ዮሐንስ 19:26, 27) ኢየሱስ፣ ይህ ታማኝ ሐዋርያ የማርያምን አካላዊና ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎቷንም እንደሚያሟላላት ያውቅ ነበር። b
10. ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
10 አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላቸው ጠቃሚ ነው። ቤተሰቡን ከልብ የሚወድ አባት ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ይጥራል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሚዛናዊ የሆነ የቤተሰብ ራስ፣ አልፎ አልፎ ቤተሰቡ እረፍት የሚያደርግበትንና የሚዝናናበትን ዝግጅት ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ክርስቲያን ወላጆች የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ያደርጋሉ። እንዴት? ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም እንዲኖራቸው እንዲሁም ጥናቱ ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ የሚገነባና አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ይጥራሉ። (ዘዳግም 6:6, 7) ወላጆች የስብከቱ ሥራ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁም ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መዘጋጀትና በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የመንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ክፍል መሆኑን በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው ልጆቻቸውን ያስተምሯቸዋል።—ዕብራውያን 10:24, 25
ይቅር ብሏቸዋል
11. ኢየሱስ ይቅር ባይነትን በተመለከተ ለተከታዮቹ ምን አስተምሯቸዋል?
11 ይቅር ባይነት የፍቅር አንዱ ገጽታ ነው። (ቆላስይስ 3:13, 14) አንደኛ ቆሮንቶስ 13:5 “ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም” ይላል። ኢየሱስ ይቅር ባይነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ለተከታዮቹ አስተምሯቸዋል። “እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ” ሳይሆን “እስከ 77 ጊዜ” ይቅር ማለት እንዳለባቸው ማለትም ይቅር ባይነታቸው ገደብ ሊኖረው እንደማይገባ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 18:21, 22) የበደላቸው ሰው ተግሣጽ ሲሰጠው ከተጸጸተ ይቅር ሊሉት እንደሚገባ አስተምሯቸዋል። (ሉቃስ 17:3, 4) ሆኖም ኢየሱስ፣ የሚያስተምሩትን ተግባራዊ እንደማያደርጉት ግብዝ ፈሪሳውያን አልነበረም፤ እሱ ራሱ በዚህ ረገድ ምሳሌ ሆኖላቸዋል። (ማቴዎስ 23:2-4) ኢየሱስ፣ የሚያምነው ወዳጁ በከዳው ጊዜ እንኳ ይቅር ባይ መሆኑን እንዴት እንዳሳየ እስቲ እንመልከት።
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ጴጥሮስ እንደሚጠበቀው ሳይሆን የቀረው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያደረጋቸው ነገሮች ይቅር ባይነትን በማስተማር ብቻ እንዳልተወሰነ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው፤ ይህ ሐዋርያ አንዳንድ ጊዜ ችኩልነት ቢታይበትም አፍቃሪ ሰው ነው። ኢየሱስ የጴጥሮስን ጥሩ ባሕርያት ስላስተዋለ ለየት ያሉ መብቶች ሰጥቶታል። እንደ ያዕቆብና ዮሐንስ ሁሉ ጴጥሮስም ሌሎቹ ሐዋርያት ያላዩአቸውን አንዳንድ ተአምራት አይቷል። (ማቴዎስ 17:1, 2፤ ሉቃስ 8:49-55) ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ከእሱ ጋር ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ዘልቀው ከገቡት ሐዋርያት አንዱ ጴጥሮስ ነበር። ሆኖም በዚያው ምሽት ኢየሱስ አልፎ ሲሰጥና ሲያዝ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ጥለውት ሸሹ። በኋላ ላይ ኢየሱስ አላግባብ ለፍርድ በቀረበበት ጊዜ ጴጥሮስ ራሱን አደፋፍሮ እዚያው ግቢው ድረስ ሄዶ ነበር። ሆኖም ስለፈራ ከባድ ስህተት ፈጸመ፤ ኢየሱስን ጭራሽ እንደማያውቀው በመናገር ሦስት ጊዜ ካደው! (ማቴዎስ 26:69-75) ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? አንተ አንድ የቅርብ ጓደኛህ እንዲህ ዓይነት ነገር ቢፈጽምብህ ምን ታደርግ ነበር?
13 ኢየሱስ ጴጥሮስን ይቅር ሊለው ፈልጓል። ጴጥሮስ በፈጸመው በደል ስሜቱ እንደተደቆሰ ጌታው አውቋል። በድርጊቱ የተጸጸተው ሐዋርያ “እጅግ አዝኖ [አልቅሷል]።” (ማርቆስ 14:72) ኢየሱስ ከሞት በተነሳበት ዕለት ለጴጥሮስ ተገለጠለት፤ ይህን ያደረገው እሱን ለማጽናናትና እንዳልተቀየመው ሊያረጋግጥለት ፈልጎ ይመስላል። (ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮንቶስ 15:5) ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ጴጥሮስን በሌላ መንገድ አከበረው፤ በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ለተሰበሰቡት ሰዎች በተሰጠው ምሥክርነት ግንባር ቀደም እንዲሆን ፈቅዶለታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:14-40) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ሌሎቹ ሐዋርያትም ጥለውት በመሸሻቸው ቂም እንዳልያዘባቸው ማስታወስ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ከሞት ከተነሳ በኋላ “ወንድሞቼ” ሲል ጠርቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:10) ኢየሱስ ስለ ይቅር ባይነት ከማስተማር ባለፈ በዚህ ረገድ ምሳሌ እንደነበረ ከዚህ በግልጽ ማየት አይቻልም?
14. ሌሎችን ይቅር ማለትን መማር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
14 የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ሌሎችን ይቅር ማለትን መማር ያስፈልገናል። ለምን? ከኢየሱስ በተለየ ሁኔታ እኛ ፍጹም አይደለንም፤ የሚበድሉን ሰዎችም እንደዛው። ሁላችንም ብዙ ጊዜ በቃልም ሆነ በድርጊት እንሰናከላለን። (ሮም 3:23፤ ያዕቆብ 3:2) ይቅር ለማለት የሚያስችል መሠረት በሚኖርበት ጊዜ ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ አምላክም የእኛን ኃጢአት ይቅር የሚልበት መሠረት ያገኛል። (ማርቆስ 11:25) ታዲያ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ፣ ጥቃቅን በደሎችንና ስህተቶችን ችላ ብለን በማለፍ ነው፤ ፍቅር እንዲህ እንድናደርግ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 4:8) የበደሉን ሰዎች እንደ ጴጥሮስ ከልባቸው ከተጸጸቱ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይቅር ለማለት ፈቃደኞች እንሆናለን። ቂም በመያዝ ጥበብ የጎደለው ነገር አናደርግም፤ ከዚህ ይልቅ ቅሬታችንን ለመተው እንመርጣለን። (ኤፌሶን 4:32) እንዲህ ማድረጋችን ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ለእኛም የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 3:11
እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል
15. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ድክመት ቢኖርባቸውም የተማመነባቸው ለምንድን ነው?
15 ፍቅርና መተማመን የማይነጣጠሉ ባሕርያት ናቸው። ፍቅር “ሁሉን ያምናል።” c (1 ቆሮንቶስ 13:7) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ድክመቶች ቢኖሩባቸውም እንኳ እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል፤ ይህን እንዲያደርግ የገፋፋው ፍቅር ነው። ይሖዋን ከልባቸው እንደሚወዱና ፈቃዱን ለማድረግ እንደሚፈልጉ ሙሉ እምነት ነበረው። ስህተት በሚሠሩበት ጊዜም እንኳ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን ተጠራጥሮ አያውቅም። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ያዕቆብና ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ከእሱ አጠገብ እንዲያስቀምጣቸው በእናታቸው በኩል ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ታማኝነታቸውን አልተጠራጠረም ወይም ከሐዋርያነታቸው አልሻራቸውም።—ማቴዎስ 20:20-28
16, 17. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ኃላፊነቶች ሰጥቷቸዋል?
16 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ኃላፊነቶችን በመስጠት በእነሱ እንደሚተማመን አሳይቷል። በጥቂት ምግብ ብዙ ሰዎችን በተአምር በመገበባቸው ሁለት ወቅቶች ምግቡን የማከፋፈሉን ኃላፊነት የሰጠው ለደቀ መዛሙርቱ ነበር። (ማቴዎስ 14:19፤ 15:36) ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ የሚያከብረውን የፋሲካ በዓል እንዲያዘጋጁ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ኢየሩሳሌም ልኳቸዋል። እነሱም በጉን፣ የወይን ጠጁን፣ እርሾ ያልገባበትን ቂጣና መራራ ቅጠል እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አዘጋጅተዋል። ለሐዋርያቱ የተሰጣቸው ይህ ሥራ እንደ ቀላል የሚታይ አልነበረም፤ ምክንያቱም የሙሴ ሕግ የፋሲካ በዓል በተገቢው መንገድ እንዲከበር የሚያዝ ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ ይህን ሕግ መፈጸም ይጠበቅበት ነበር። በተጨማሪም በዚያኑ ምሽት ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ሲያቋቁም የወይን ጠጁንና እርሾ ያልገባበትን ቂጣ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል።—ማቴዎስ 26:17-19፤ ሉቃስ 22:8, 13
17 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከዚህ የበለጡ ኃላፊነቶችንም ሰጥቷቸዋል። ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ እንደሰጣቸው አስታውስ። (ማቴዎስ 28:18-20) ቀደም ብሎ እንደተመለከትነው ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡን ከባድ ኃላፊነት በምድር ላይ ለሚገኙ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ተከታዮቹ እንደሚሰጥ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 12:42-44) በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ እየገዛ ቢሆንም በምድር ላይ ያለውን ጉባኤውን የመንከባከቡን ኃላፊነት መንፈሳዊ ብቃት ላላቸው ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ በአደራ ሰጥቷል።—ኤፌሶን 4:8, 11, 12
18-20. (ሀ) የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንደምንተማመንባቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ለሌሎች ኃላፊነትን በመስጠት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) የሚቀጥለው ምዕራፍ ስለ ምን ነገር ያብራራል?
18 እኛስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንደምንተማመንባቸው ማሳየት ፍቅራችን የሚታይበት አንዱ አቅጣጫ ነው። ፍቅር አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ እንዳልሆነ እናስታውስ። ፍቅር ካለን ሌሎች ሲያስቀይሙን (ደግሞም ይህ ብዙ ጊዜ ያጋጥማል) ‘ይህን ያደረጉት በክፋት ተነሳስተው ነው’ ወደሚል መደምደሚያ ለመድረስ አንቸኩልም። (ማቴዎስ 7:1, 2) ምንጊዜም በእምነት ባልንጀሮቻችን መልካም ጎን ላይ የምናተኩር ከሆነ እነሱን የምንይዝበት መንገድ የሚያፈርስ ሳይሆን የሚያንጽ ይሆናል።—1 ተሰሎንቄ 5:11
19 ኢየሱስ ለሌሎች ኃላፊነት በመስጠት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሥራዎችን ለሌሎች ሊሰጡ ይገባል፤ የተሰጣቸውን ሥራ በተገቢው መንገድ እንደሚያከናውኑም ይተማመኑባቸዋል። በዚህ መንገድ፣ ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለመርዳት ‘ለሚጣጣሩ’ ብቃቱን ያሟሉ ወጣት ወንድሞች ጠቃሚ ሥልጠና ሊሰጧቸው ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2) እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ብዙ ሰዎችን ወደ ጉባኤው እየሳበ በመሆኑ ኃላፊነት የሚሸከሙ ብቃት ያላቸው ተጨማሪ ወንዶችን ማሠልጠን ያስፈልጋል።—ኢሳይያስ 60:22
20 ኢየሱስ ፍቅር በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስን መከተል ከምንችልባቸው መንገዶች ሁሉ የላቀው፣ ፍቅር በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ ነው። ከሁሉ የላቀው የፍቅሩ መግለጫ ደግሞ ሕይወቱን ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑ ነው፤ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህን እንመለከታለን።
a ሐዋርያቱ እንቅልፍ የተጫጫናቸው ሰውነታቸው በመድከሙ ብቻ አልነበረም። በሉቃስ 22:45 ላይ የሚገኘው ተመሳሳይ ዘገባ ኢየሱስ “ከሐዘን የተነሳ ደክሟቸው ስለነበር ሲያንቀላፉ” እንዳገኛቸው ይገልጻል።
c እንዲህ ሲባል ግን ፍቅር በቀላሉ ይታለላል ወይም ሞኝ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፍቅር ስህተት አይለቃቅምም ወይም ተጠራጣሪ አይደለም ማለት ነው። ፍቅር የሌሎችን ዝንባሌ በመጥፎ ለመፈረጅ ወይም የሌሎችን ድርጊት በክፉ ለመረዳት አይቸኩልም።