ምዕራፍ አሥራ ስምንት
“እኔን መከተልህን ቀጥል”
1-3. (ሀ) ኢየሱስ ሐዋርያቱን የተሰናበታቸው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? ይህ አሳዛኝ የመጨረሻ ስንብት አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ስላለው ሕይወት ማወቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
አሥራ አንድ ሰዎች በአንድ ተራራ ላይ ሰብሰብ ብለው ቆመዋል። ሌላ አሥራ ሁለተኛ ሰውም አብሯቸው አለ፤ በፍቅርና በአድናቆት ትኩር ብለው እየተመለከቱት ነው። በመሠረቱ ይህ ሰው፣ በሰው አምሳል ይታይ እንጂ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ነው፤ አሁን እንደ ቀድሞው ኃያል መልአክ ሆኗል፤ ከይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች ሁሉ የላቀ ኃያል መልአክ። ኢየሱስ ሐዋርያቱን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ሰብስቧቸዋል።
2 ከኢየሩሳሌም ማዶ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ የደብረ ዘይት ተራራ ይገኛል። መቼም ይህ ተራራ ለኢየሱስ ብዙ ትዝታዎችን ጭሮበት መሆን አለበት። አልዓዛርን ከሞት ያስነሳው በዚህ ተራራ ተረተር ላይ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ በመሆን ወደ ኢየሩሳሌም የገባውም በአቅራቢያው ከምትገኘው ከቤተፋጌ ተነስቶ ነው። ከመያዙ በፊት የነበሩትን አስጨናቂ ሰዓታት ያሳለፈበት የጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራም የሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሳይሆን አይቀርም። አሁን ደግሞ በዚሁ ተራራ ላይ የቅርብ ወዳጆቹንና ተከታዮቹን ተሰናብቶ ሊሄድ ነው። ደግነት የሚንጸባረቅባቸው የመሰናበቻ ቃላት ከተናገረ በኋላ ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ ማለት ጀመረ! ሐዋርያቱም የሚወዱት ጌታቸው ወደ ሰማይ ሲያርግ ትኩር ብለው እያዩ እዚያው ባሉበት ፈዘው ቀሩ። በመጨረሻም ደመና ከዓይናቸው ሰወረው።—የሐዋርያት ሥራ 1:6-12
3 ይህ ክንውን ሐዘንና ደስታ የተቀላቀለበት ስሜት የሚፈጥር አሳዛኝ ስንብት እንደሆነ ይሰማሃል? እውነታው ግን ይህ አይደለም። ሁለት መላእክት ለሐዋርያቱ እንደነገሯቸው የኢየሱስ ታሪክ በዚህ አያበቃም። (የሐዋርያት ሥራ 1:10, 11) እንዲያውም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ታሪኩ ገና እየጀመረ ነው ሊባል ይችላል። የአምላክ ቃል፣ ኢየሱስ ከዚያ በኋላ ምን እንዳደረገ በግልጽ ይነግረናል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ስላለው ሕይወት ማወቃችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ኢየሱስ ጴጥሮስን “እኔን መከተልህን ቀጥል” ብሎት እንደነበር አስታውስ። (ዮሐንስ 21:19, 22) ሁላችንም ይህን ትእዛዝ ማክበር አለብን፤ እንዲህ የምናደርገው ግን ለጊዜው ብቻ ሳይሆን በመላ ሕይወታችን ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ምን እያከናወነ እንዳለና በሰማይ ምን ኃላፊነት እንደተሰጠው ማወቅ ያስፈልገናል።
የኢየሱስ ሕይወት ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ
4. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ስለሚከናወነው ነገር አስቀድሞ የጠቆመው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ወደ ሰማይ በተመለሰበት ጊዜ ምን ዓይነት አቀባበል እንደተደረገለትና ከአባቱ ጋር ሲገናኝ ስለነበረው አስደሳች ሁኔታ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚገልጹት ነገር የለም። ይሁንና ኢየሱስ እንደተመለሰ በሰማይ ስለሚከናወነው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ፍንጭ ሰጥቶናል። ታስታውስ እንደሆነ፣ አይሁዳውያን ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት ሲያከብሩ የኖሩት አንድ ቅዱስ ሥርዓት ነበር። ሊቀ ካህናቱ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ በዚያም በስርየት ቀን መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትን እንስሳት ደም በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይረጨዋል። በዚያ ቀን ሊቀ ካህናቱ የሚያደርገው ነገር ለመሲሑ ጥላ ሆኖ ያገለግላል። ይህ ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት ዓላማ ለኃጢአት ስርየት ማስገኘት ነበር፤ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲመለስ ይህን ዓላማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሳክቷል። በሰማይ ይሖዋ ወደሚገኝበት ክብራማ ቦታ ይኸውም በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ እጅግ ቅዱስ ወደሆነው ስፍራ ገባ፤ ከዚያም የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ ለአባቱ አቀረበ። (ዕብራውያን 9:11, 12, 24) ታዲያ ይሖዋ ተቀብሎት ይሆን?
5, 6. (ሀ) ይሖዋ የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት እንደተቀበለው የሚያሳየው ማስረጃ ምንድን ነው? (ለ) ከቤዛው ጥቅም የሚያገኙት እነማን ናቸው? እንዴትስ?
5 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተከሰተውን ነገር መመርመራችን መልሱን ይሰጠናል። አንድ መቶ ሃያ ገደማ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም በአንድ ቤት ደርብ ላይ ተሰብስበው ሳለ በድንገት እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ቤቱን ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉ ነገሮች በተሰበሰቡት ሰዎች ራስ ላይ ታዩ፤ እነሱም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) ይህ ክንውን የአንድን አዲስ ብሔር ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤልን መወለድ የሚያበስር ነበር፤ አዲሱ ብሔር በምድር ላይ መለኮታዊውን ፈቃድ እንዲያስፈጽም በአምላክ “የተመረጠ ዘር” እንዲሁም “ንጉሣዊ ካህናት” ቡድን ነው። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይሖዋ አምላክ የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት እንደተቀበለው ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ቤዛው ካስገኛቸው የመጀመሪያ በረከቶች አንዱ ነው።
6 ከዚያ ጊዜ አንስቶ የክርስቶስ ቤዛ በመላው ዓለም ለሚገኙ ተከታዮቹ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝቷል። ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዛው በመንፈስ የተቀባ “ትንሽ መንጋ” አባላትም ሆንን በእሱ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የሚኖሩት “ሌሎች በጎች” ሁላችንም ከኢየሱስ መሥዋዕት ጥቅም እናገኛለን። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16) የወደፊት ተስፋችንም ሆነ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘታችን የተመካው በቤዛው ላይ ነው። ኢየሱስን በየዕለቱ በመከተል በቤዛው ‘እስካመንን’ ድረስ ንጹሕ ሕሊናና ብሩህ የሆነ የወደፊት ተስፋ ይኖረናል።—ዮሐንስ 3:16
7. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ምን ሥልጣን ተሰጠው? አንተስ የእሱን ሥልጣን እንደተቀበልክ ልታሳይ የምትችለው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰበት ጊዜ አንስቶ በዚያ ምን እያከናወነ ነው? ኢየሱስ ከፍተኛ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:18) ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ላይ እንዲገዛ ሾሞታል፤ እሱም ይህን ኃላፊነቱን በፍቅርና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሲወጣ ቆይቷል። (ቆላስይስ 1:13) አስቀድሞ እንደተነገረው ኢየሱስ መንጋውን የሚንከባከቡ ወንዶች ሾሟል። (ኤፌሶን 4:8) ለምሳሌ ጳውሎስን ‘ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ’ እንዲሆን የመረጠው ሲሆን ምሥራቹን በስፋት የማዳረስ ተልእኮ ሰጥቶታል። (ሮም 11:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:7) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ገደማ ኢየሱስ የሮም ግዛት በሆነችው በእስያ ላሉ ሰባት ጉባኤዎች ምስጋና፣ ምክርና እርማት የያዘ መልእክት ልኳል። (ራእይ ምዕራፍ 2 እና 3) አንተስ ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ መሆኑን አምነህ ተቀብለሃል? (ኤፌሶን 5:23) እሱን መከተልህን መቀጠል ከፈለግህ በጉባኤህ ውስጥ ታዛዥና ተባባሪ ሆነህ መገኘት አለብህ።
8, 9. ኢየሱስ በ1914 ምን ሥልጣን ተሰጥቶታል? ይህስ በምናደርገው ውሳኔ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?
8 ኢየሱስ በ1914 ተጨማሪ ሥልጣን ተሰጥቶታል። የይሖዋ መሲሐዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የተሾመው በዚያ ዓመት ነው። ኢየሱስ መግዛት ሲጀምር ‘በሰማይ ጦርነት ተነሳ።’ ውጤቱስ ምን ሆነ? ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር ተወረወሩ፤ ይህም ወዮታ የሞላበት ዘመን እንዲጀምር አድርጓል። በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆችን እያሠቃዩ ያሉት እንደ ጦርነት፣ ወንጀል፣ ሽብርተኝነት፣ በሽታ፣ የምድር መናወጥና ረሃብ ያሉ ችግሮች ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ እየገዛ መሆኑን ያስገነዝቡናል። ሰይጣን ‘ለጥቂት ጊዜ’ ቢሆንም “የዚህ ዓለም ገዢ” ሆኖ ይቀጥላል። (ራእይ 12:7-12፤ ዮሐንስ 12:31፤ ማቴዎስ 24:3-7፤ ሉቃስ 21:11) ያም ሆኖ ኢየሱስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች የእሱን አገዛዝ እንዲቀበሉ አጋጣሚውን እየሰጣቸው ነው።
9 እኛም ከመሲሐዊው ንጉሥ ጎን መቆማችን እጅግ አስፈላጊ ነው። በየዕለቱ የምናደርገው ማንኛውም ውሳኔ ይህን ብልሹ ዓለም ሳይሆን ኢየሱስን የሚያስደስት እንዲሆን እንፈልጋለን። ይህ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” የሰው ልጆችን በሚመረምርበት ጊዜ ጽድቅ ወዳድ የሆነውን ልቡን የሚያስቆጣም ሆነ የሚያስደስት ነገር እንደሚያገኝ የታወቀ ነው። (ራእይ 19:16) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
መሲሐዊውን ንጉሥ የሚያስቆጣውና የሚያስደስተው ነገር
10. ኢየሱስ በዋነኝነት ባሕርይው ምንድን ነው? ሆኖም የጽድቅ ቁጣ እንዲቆጣ የሚያደርገው ምንድን ነው?
10 ጌታችን ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ በባሕርይው ደስተኛ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በቀላሉ የማይደሰት ወይም መተቸት የሚቀናው ሰው አልነበረም። ይሁንና በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ የጽድቅ ቁጣ እንዲቆጣ የሚያደርገው ብዙ ነገር በምድር ላይ እየተፈጸመ ነው። ክርስቲያን ነን በሚሉት የሐሰት ሃይማኖቶች እንደሚበሳጭ ጥርጥር የለውም። ለነገሩ እሱ ራሱ አስቀድሞ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው። በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ . . . ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23
11-13. ኢየሱስ በስሙ “ብዙ ተአምራት” የሚያደርጉትን ሰዎች መቆጣቱ አንዳንዶችን ግራ የሚያጋባቸው ለምንድን ነው? ሆኖም ኢየሱስን ያስቆጣው ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
11 በዛሬው ጊዜ፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች ይህ የኢየሱስ አነጋገር ግራ ሊያጋባቸው ይችላል። ኢየሱስ በስሙ “ብዙ ተአምራት” ያደረጉትን ሰዎች የተቆጣቸው ለምንድን ነው? የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ይደግፋሉ፣ ድሆችን ይረዳሉ፣ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን ይገነባሉ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሥራዎች ያከናውናሉ። ታዲያ ኢየሱስ በእነሱ ላይ የተቆጣው ለምንድን ነው? ይህን ለመረዳት እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
12 አንድ ባልና ሚስት ራቅ ወዳለ ቦታ ለመጓዝ አስበዋል። ልጆቻቸውን ይዘው መሄድ ስለማይችሉ ሞግዚት ይቀጥራሉ። ለሞግዚቷ የሰጧት መመሪያ ምንም የማያሻማ ነው፦ “ልጆቻችንን ተንከባከቢልን። በደንብ መግቢያቸው፣ አጣጥቢያቸው እንዲሁም ከጉዳት ጠብቂያቸው።” እነዚህ ወላጆች ከሄዱበት ሲመለሱ የጠበቃቸው ነገር ግን የሚያስደነግጥ ነበር። ልጆቻቸው ተርበዋል፣ በጣም ቆሽሸዋል፣ ታመዋል እንዲሁም ተጎሳቁለዋል። ልጆቹ እያለቀሱ ቢሆንም ሞግዚቷ ዞር ብላ እንኳ አላየቻቸውም። ለምን? መሰላል ላይ ወጥታ መስታወት እያጸዳች ነው። በንዴት የበገኑት ወላጆች ለምን እንዲህ እንዳደረገች ሲጠይቋት እንዲህ ስትል መለሰችላቸው፦ “ስንት ሥራ እንደሠራሁ አታዩም? እስቲ መስታወቱ እንዴት እንደጸዳ እዩ! ቤቱንም ስጠግን ነበር፤ ይህን ሁሉ ያደረግኩት እኮ ለእናንተ ብዬ ነው!” እነዚህ ወላጆች በሥራዋ የሚደሰቱ ይመስልሃል? በፍጹም! እነዚህን ሥራዎች እንድትሠራ ጨርሶ አላዘዟትም፤ የጠየቋት ልጆቻቸውን በደንብ እንድትንከባከብላቸው ነበር። የታዘዘችውን ነገር ሳትፈጽም መቅረቷ በጣም እንደሚያበሳጫቸው የታወቀ ነው።
13 ሕዝበ ክርስትናም እያደረገች ያለችው ልክ እንደዚህች ሞግዚት ነው። ኢየሱስ በምድር ላሉት ተወካዮቹ የሰጠው መመሪያ፣ የአምላክን ቃል እውነት በማስተማር ሰዎችን በመንፈሳዊ እንዲመግቡና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ እንዲረዷቸው ነው። (ዮሐንስ 21:15-17) ሕዝበ ክርስትና ግን ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በሚያሳዝን ሁኔታ ቸል ብላለች። ሰዎች ለመንፈሳዊ ረሃብ እንዲዳረጉ፣ በሐሰት ትምህርቶች ግራ እንዲጋቡና መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንዳያውቁ አድርጋለች። (ኢሳይያስ 65:13፤ አሞጽ 8:11) ይህን ዓለም ለማሻሻል የምታደርገው ጥረትም ቢሆን የኢየሱስን ትእዛዝ ላለማክበር ሰበብ ሊሆን አይችልም። በመሠረቱ ይህ ዓለም፣ ‘ይፍረስ’ የሚል ምልክት እንደተደረገበት ቤት ነው! የአምላክ ቃል የሰይጣን ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋ በግልጽ ይናገራል።—1 ዮሐንስ 2:15-17
14. በዛሬው ጊዜ ኢየሱስን የሚያስደስተው ሥራ የትኛው ነው? ለምንስ?
14 በአንጻሩ ደግሞ ኢየሱስ በጣም የሚያስደስተው ሌላ ነገር ያያል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ምድር ላይ እያለ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮ እየፈጸሙ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) መሲሐዊውን ንጉሥ ማስደሰት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንግዲያው ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ድጋፍ መስጠታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ማቴዎስ 24:45) አነስተኛ ቁጥር ያለው ይህ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን፣ ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በተለየ መልኩ የስብከቱን ሥራ በታዛዥነት ሲመራና የክርስቶስን በጎች በታማኝነት ሲመግብ ቆይቷል።
15, 16. (ሀ) ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ፍቅር ምን ያህል እንደጠፋ ሲያይ ምን ይሰማዋል? ይህንንስ እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ኢየሱስ በሕዝበ ክርስትና ላይ መቆጣቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ንጉሣችን በዛሬው ጊዜ ፍቅር ምን ያህል እንደጠፋ ሲመለከት እንደሚቆጣ ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ የታመሙትን በሰንበት ዕለት በመፈወሱ ፈሪሳውያን እንደተቹት ትዝ ይለን ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ልባቸው ምንኛ ጨካኝና ደንዳና ነው፤ የሚያሳስባቸው ነገር ቢኖር የሙሴን ሕግ የሚተረጉሙበት ጠባብ እይታና የቃል ሕጋቸው መከበሩ ብቻ ነው፤ ከዚያ አልፈው ማየት ተስኗቸው ነበር። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ብዙ ጥቅም አስገኝተዋል። እነዚህ ተአምራት ለሰዎች ደስታና እፎይታ ከማምጣታቸውም በላይ እምነታቸውን አጠናክረውላቸዋል፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ለፈሪሳውያኑ ምናቸውም አልነበረም። ታዲያ ኢየሱስ ስለ እነሱ ምን ተሰማው? “በልባቸው ደንዳናነት በጣም አዝኖ . . . በብስጭት” እንደተመለከታቸው ተዘግቧል።—ማርቆስ 3:5
16 በዛሬው ጊዜም ኢየሱስ ‘በጣም እንዲያዝን’ የሚያደርገው እጅግ የከፋ ነገር ያያል። የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጩ ሃይማኖታዊ ወጎቻቸውንና ትምህርታቸውን ሙጭጭ አድርገው ይዘዋል። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት ምሥራች መሰበኩ ያበሳጫቸዋል። በብዙ የዓለም ክፍሎች ቀሳውስት፣ ኢየሱስ ይሰብክ የነበረውን መልእክት በሚሰብኩ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስደት አስነስተዋል። (ዮሐንስ 16:2፤ ራእይ 18:4, 24) ይህ ብቻም አይደለም! እነዚሁ ቀሳውስት፣ ተከታዮቻቸው ወደ ጦርነት እንዲዘምቱና የሌሎችን ሕይወት እንዲቀጥፉ ያበረታታሉ፤ ይህ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ሊያስደስተው ይችላል?
17. የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ልቡን ደስ የሚያሰኙት እንዴት ነው?
17 ከዚህ በተቃራኒ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ለሌሎች ፍቅር ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ልክ እንደ ኢየሱስ ምሥራቹን ‘ለሁሉም ዓይነት ሰዎች’ ይሰብካሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) በተጨማሪም አንዳቸው ለሌላው ከልብ የመነጨ ፍቅር አላቸው፤ ዋነኛ መለያቸውም ይህ ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ፍቅርና አክብሮት በማሳየት በእርግጥ ኢየሱስን እየተከተሉ መሆናቸውን ያስመሠክራሉ፤ ይህ የመሲሐዊውን ንጉሥ ልብ ደስ ያሰኛል!
18. ጌታችን ኢየሱስ እንዲያዝን የሚያደርገው ምንድን ነው? ሆኖም እሱን ማስደሰት የምንችለው በምን መንገድ ነው?
18 በአንጻሩ ደግሞ ጌታችን ተከታዮቹ ጸንተው መቆም ሲያቅታቸው፣ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ሲቀዘቅዝና እሱን ማገልገላቸውን ሲተዉ እንደሚያዝን አንርሳ። (ራእይ 2:4, 5) እስከ መጨረሻው በሚጸኑ ሰዎች ግን በጣም ይደሰታል። (ማቴዎስ 24:13) በመሆኑም ክርስቶስ “እኔን መከተልህን ቀጥል” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። (ዮሐንስ 21:19) መሲሐዊው ንጉሥ እስከ መጨረሻው ለሚጸኑ ሰዎች ከሚሰጣቸው በረከቶች ውስጥ አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
የንጉሡ ታማኝ አገልጋዮች የሚያገኟቸው የተትረፈረፉ በረከቶች
19, 20. (ሀ) ኢየሱስን መከተል በአሁኑ ጊዜም እንኳ ምን በረከቶችን ያስገኛል? (ለ) ክርስቶስን መከተላችን “የዘላለም አባት” የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
19 ኢየሱስን መከተል አሁንም እንኳ አስደሳች ሕይወት ለመምራት ያስችለናል። ክርስቶስን እንደ ጌታችን አድርገን በመቀበል መመሪያውን የምናከብርና ምሳሌውን የምንከተል ከሆነ ብዙዎች ቢደክሙለትም ሊያገኙት ያልቻሉትን ውድ ሀብት እናገኛለን። ሕይወታችን ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግ ሥራ ይኖረናል፤ በእውነተኛ ፍቅር የተሳሰረ አንድነት ያለው የእምነት ቤተሰብ እናገኛለን፤ ንጹሕ ሕሊናና የአእምሮ ሰላም በማግኘትም እንባረካለን። በአጭር አነጋገር ሕይወታችን ደስታና እርካታ የሞላበት ይሆናል። በረከቱ ግን በዚህ አያበቃም።
20 ይሖዋ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ሰዎች ኢየሱስን “የዘላለም አባት” አድርጎ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ፣ ልጆቹን ሁሉ ለችግር የዳረገው ሰብዓዊ አባት ይኸውም የአዳም ምትክ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን በማሳየት ‘የዘላለም አባታችን’ አድርገን ከተቀበልነው አስተማማኝ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይኖረናል። በተጨማሪም እንዲህ ስናደርግ ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንቀርባለን። እስካሁን እንደተመለከትነው የኢየሱስን ምሳሌ በየዕለቱ ለመከተል መጣራችን “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ” የሚለውን መለኮታዊ መመሪያ ተግባራዊ የምናደርግበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው።—ኤፌሶን 5:1
21. የክርስቶስ ተከታዮች በዚህ በጨለማ በተዋጠ ዓለም ውስጥ ብርሃን የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
21 ኢየሱስንና አባቱን ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ስናደርግ አስደናቂ መብት እናገኛለን። ይህም በዚህ በጨለማ የተዋጠ ዓለም ውስጥ ብርሃን ማንጸባረቅ ነው። በዛሬው ጊዜ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሰይጣን ተታልለው የእሱን ባሕርያት እያንጸባረቁ ነው፤ እኛ የክርስቶስ ተከታዮች ግን ደማቅ የሆነውን የእውነት ብርሃን፣ ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርያት የሚፈነጥቁትን ብርሃን እንዲሁም ከእውነተኛ ደስታ፣ ሰላምና ፍቅር የሚመነጨውን ብርሃን እናንጸባርቃለን። እንዲህ ስናደርግ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን፤ ይህ ደግሞ የማሰብ ችሎታ ያለው ማንኛውም ፍጡር ሊደርስበት የሚመኘው ከሁሉ የላቀ ግብ ነው።
22, 23. (ሀ) ኢየሱስን በታማኝነት መከተላቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ ወደፊት ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
22 ይሖዋ በመሲሐዊው ንጉሡ አማካኝነት ወደፊት ምን እንደሚያደርግልህም አስብ። በቅርቡ ይህ ንጉሥ ክፉ በሆነው የሰይጣን ሥርዓት ላይ የጽድቅ ጦርነት ያውጃል። ኢየሱስ በዚህ ጦርነት ድል እንደሚቀዳጅ ጥርጥር የለውም! (ራእይ 19:11-15) ከዚያ በኋላ ክርስቶስ በምድር ላይ ለሺህ ዓመት መግዛት ይጀምራል። በሰማይ ያለው መንግሥቱ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ በመጨረሻም ወደ ፍጽምና ደረጃ ያደርሳቸዋል። ሙሉ በሙሉ ጤነኛ፣ ወጣትና ጠንካራ ሆነህ አንድነት ካለው ቤተሰብ ጋር ምድርን ገነት በማድረጉ ሥራ በደስታ ስትካፈል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ! በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ መልሶ ያስረክባል። (1 ቆሮንቶስ 15:24) ክርስቶስን በታማኝነት መከተልህን ከቀጠልክ ልትገምተው ከምትችለው በላይ አስደናቂ የሆነ በረከት ማለትም “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ታገኛለህ! (ሮም 8:21) አዎ፣ አዳምና ሔዋን አግኝተው ያጧቸውን በረከቶች ሁሉ እናገኛለን። የይሖዋ ምድራዊ ልጆች እንሆናለን፤ የአዳም ኃጢአት ካስከተለብን የባርነት ቀንበር ለዘላለም ነፃ እንወጣለን። ያን ጊዜ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” የሚለው ተስፋ ይፈጸማል።—ራእይ 21:4
23 ምዕራፍ 1 ላይ የተጠቀሰውን ሀብታም ወጣት አለቃ አስታውስ። ኢየሱስ “ተከታዬ ሁን” በማለት ያቀረበለትን ግብዣ ሳይቀበል ቀርቷል። (ማርቆስ 10:17-22) አንተ ግን ፈጽሞ እንዲህ ዓይነት ስህተት መሥራት የለብህም! ኢየሱስ ያቀረበልህን ግብዣ በደስታና በአድናቆት እንደምትቀበል ተስፋ እናደርጋለን። እንግዲያው ቁርጥ ውሳኔህ እስከ መጨረሻው መጽናት፣ ጥሩውን እረኛ በየዕለቱ መከተልህን መቀጠል እንዲሁም የይሖዋ ዓላማ ክብራማ ፍጻሜውን ሲያገኝ ለማየት መብቃት ይሁን!