በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ አራት

‘እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ እሱ መጡ’

‘እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ እሱ መጡ’

“ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ”

1-3. ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ባመጡበት ጊዜ ምን ተከሰተ? ይህ ሁኔታስ ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

 ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱ የሚያበቃበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ መሆኑን ያውቃል። የቀሩት ጥቂት ሳምንታት ቢሆኑም ገና ብዙ የሚሠራው ሥራ አለ! ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በፔሪያ ክልል ከሐዋርያቱ ጋር እየሰበከ ነው። በስተ ደቡብ አቅጣጫ በመጓዝ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም በማቅናት ላይ ናቸው፤ ይህ ለኢየሱስ የመጨረሻው የፋሲካ በዓል ነው።

2 ኢየሱስ ከአንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ከበድ ባሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ መጨረሱ ነው፤ በኋላ ላይ የሆነ ግርግር ተፈጠረ። ሰዎች ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ማምጣት ጀመሩ። ልጆቹ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም ማርቆስ እነሱን ለማመልከት የተጠቀመው፣ ቀደም ሲል የ12 ዓመቷን ልጅ ለመግለጽ የተጠቀመበትን ቃል ሲሆን ሉቃስ ደግሞ የተጠቀመው “ሕፃናት” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል ነው። (ሉቃስ 18:​15፤ ማርቆስ 5:​41, 42፤ 10:​13) መቼም ልጆች ባሉበት ጫጫታና ግርግር አይጠፋም። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ሥራ ስለሚበዛበት ለልጆች የሚሆን ጊዜ አይኖረውም ብለው በማሰብ ሳይሆን አይቀርም የልጆቹን ወላጆች ገሠጿቸው። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ?

3 ኢየሱስ የተፈጠረውን ነገር ሲያይ ተቆጣ። ለመሆኑ የተቆጣው ማንን ነው? ልጆቹን ነው ወይስ ወላጆቹን? እነሱን አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተቆጣው ደቀ መዛሙርቱን ነው! እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና። እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።” ከዚያም ልጆቹን “አቀፋቸው” እንዲሁም ባረካቸው። (ማርቆስ 10:​13-16) ማርቆስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት አገላለጽ ኢየሱስ ለልጆች ያለውን ፍቅር የሚገልጽ ነው፤ ምናልባትም አንድ ተርጓሚ እንዳሉት ኢየሱስ አንዳንድ ሕፃናትን “በክንዱ እቅፍ አድርጓቸዋል” ወይም ጉያው አስገብቷቸዋል። ኢየሱስ ልጆችን ይወድ እንደነበር ግልጽ ነው። ሆኖም ይህ ሁኔታ ስለ እሱ ሌላም የሚያስተምረን ነገር አለ፦ ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ነበር።

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው እንደነበር በምን እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

4 ኢየሱስ ፊቱ የማይፈታ፣ ሰው የማያቀርብ ወይም ኩሩ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ልጆች ወደ እሱ እንደማይቀርቡ የታወቀ ነው፤ ወላጆቻቸውም ቢሆኑ በነፃነት ወደ እሱ አይመጡም ነበር። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፤ ይህ ደግ ሰው ልጆቻቸውን በፍቅር ሲያቀርባቸውና ሲባርካቸው ወላጆቹ ምንኛ ተደስተው ይሆን? ልጆች በአምላክ ፊት ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ሲገልጽ ሲሰሙ ፊታቸው በደስታ ፈክቶ መሆን አለበት። አዎ፣ ኢየሱስ ከምንም ነገር በላይ የሚያስጨንቅ ከባድ ኃላፊነት ተሸክሞ ባለበት በዚህ ወቅትም በቀላሉ የሚቀረብ ሰው መሆኑን አሳይቷል።

5 ይሁንና እነማን ጭምር ኢየሱስን መቅረብ አልከበዳቸውም? እንዲህ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? እኛስ በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመርምር።

እነማን ኢየሱስን መቅረብ አልከበዳቸውም?

6-8. ብዙውን ጊዜ ከኢየሱስ አጠገብ እነማን አይጠፉም ነበር? ለእነሱ የነበረው አመለካከትስ የሃይማኖት መሪዎቹ ከነበራቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

6 የወንጌል ዘገባዎችን በምታነብበት ጊዜ በጣም ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መቅረብ እንዳልከበዳቸው ማወቅህ ያስገርምህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከእሱ ጋር በተያያዘ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በተደጋጋሚ ጊዜ የተጠቀሱባቸውን እንደሚከተሉት ያሉ ዘገባዎች እናገኛለን፦ “ከገሊላ . . . የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።” “እጅግ ብዙ [ሰዎች] ወደ እሱ መጥተው ተሰበሰቡ።” “እጅግ ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዘ” ነበር። (ማቴዎስ 4:​25፤ 13:2፤ 15:​30፤ ሉቃስ 14:​25) አዎ፣ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ በሕዝብ እንደተከበበ ነው።

7 በጥቅሉ ሲታይ፣ እነዚህ ሰዎች የሃይማኖት መሪዎቹ “የምድሪቱ ሰዎች” በማለት በንቀት የሚጠሯቸው ሰዎች ነበሩ። ፈሪሳውያኑና ካህናቱ “ሕጉን የማያውቀው ይህ ሕዝብ . . . የተረገመ ነው” በማለት በግልጽ ይናገሩ ነበር። (ዮሐንስ 7:​49) ቆየት ብሎ ረቢዎች የጻፏቸው ጽሑፎችም ፈሪሳውያንና ካህናት እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው አረጋግጠዋል። ብዙ የሃይማኖት መሪዎች እነዚህን ሰዎች በንቀት ይመለከቷቸው ነበር፤ ከእነሱ ጋር መብላትም ሆነ ከእነሱ ላይ ሸቀጦችን መግዛት አሊያም አብረው ጊዜ ማሳለፍ አይፈልጉም ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ የቃል ሕጉን የማያውቁ ሰዎች ትንሣኤ እንደማያገኙ አጥብቀው ይናገሩ ነበር! ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ብዙ ሰዎች ከሃይማኖት መሪዎቹ እርዳታ ወይም መመሪያ ከመጠየቅ ይልቅ ከእነሱ ይሸሹ ነበር። ኢየሱስ ግን ከእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የተለየ ነው።

8 ኢየሱስ ከሕዝቡ ጋር በነፃነት ይቀራረብ ነበር። አብሯቸው ይበላ፣ ይፈውሳቸው፣ ያስተምራቸው እንዲሁም ተስፋ የሚሰጥ ነገር ይነግራቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እውነታውን አምኖ የሚቀበል ሰው ነበር፤ አብዛኞቹ ሰዎች የተዘረጋላቸውን ይሖዋን የማገልገል አጋጣሚ እንደማይጠቀሙበት ያውቃል። (ማቴዎስ 7:​13, 14) ሆኖም ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ በብዙዎች ልብ ውስጥ ትክክለኛውን ነገር የማድረግ ቅንነት እንዳለ ተመልክቷል። ኢየሱስ ርኅራኄ ከሌላቸው ካህናትና ፈሪሳውያን ምንኛ የተለየ ነው! የሚያስገርመው ግን፣ ካህናትና ፈሪሳውያንም እንኳ ኢየሱስን ይቀርቡት ነበር፤ ከመካከላቸው የተወሰኑት ደግሞ አካሄዳቸውን አስተካክለው እሱን መከተል ጀምረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 6:7፤ 15:5) አንዳንድ ሀብታምና ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሰዎችም ኢየሱስን መቅረብ አልከበዳቸውም።​—⁠ማርቆስ 10:​17, 22

9. ሴቶች ኢየሱስን መቅረብ ያልከበዳቸው ለምንድን ነው?

9 ሴቶች ወደ ኢየሱስ መቅረብ አይፈሩም ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ የሚያሳዩአቸው ከፍተኛ ንቀት ብዙውን ጊዜ ስሜታቸውን ሳይጎዳው አልቀረም። አብዛኞቹ ረቢዎች ሴቶችን ማስተማርን ያወግዙ ነበር። እንዲያውም ሴቶች በፍርድ ሂደቶች ላይ ምሥክር ሆነው እንዲቀርቡ አይፈቀድላቸውም፤ ምክንያቱም እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ተደርገው አይታዩም ነበር። ሌላው ቀርቶ ረቢዎች ሴት ሆነው ባለመፈጠራቸው በጸሎት አምላክን ያመሰግኑ ነበር! ሆኖም ኢየሱስ ለሴቶች እንዲህ ዓይነት ንቀት አልነበረውም። በመሆኑም ብዙ ሴቶች ወደ እሱ መቅረብ አላስፈራቸውም፤ ከእሱ ለመማር ይጓጉ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የአልዓዛር እህት ማርታ ምግብ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ስትል እህቷ ማርያም ኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ የሚያስተምረውን ነገር በጥሞና ታዳምጥ ነበር። ማርያም ለትክክለኛው ነገር ቅድሚያ ስለሰጠች ኢየሱስ አመስግኗታል።​—⁠ሉቃስ 10:​39-42

10. ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን የያዘበት መንገድ ከሃይማኖት መሪዎቹ የሚለየው እንዴት ነው?

10 የሃይማኖት መሪዎች የታመሙ ሰዎችን ያገልሏቸው ነበር፤ ሆኖም ብዙ የታመሙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ይመጡ ነበር። እርግጥ ነው፣ የሙሴ ሕግ ለሌሎች ጤንነት ሲባል በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች ተገልለው እንዲቀመጡ ያዛል፤ ይህ ግን በእነዚህ ሰዎች ላይ ደግነት የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም ሰበብ አይሆንም። (ዘሌዋውያን ምዕራፍ 13) ሆኖም ከጊዜ በኋላ ረቢዎች ያወጧቸው ሕጎች በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች የዓይነ ምድርን ያህል አስጸያፊ እንደሆኑ ይገልጹ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች ወደ እነሱ እንዳይቀርቡ ድንጋይ ይወረውሩባቸው ነበር! እንዲህ ዓይነት በደል የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ማንኛውም አስተማሪ ለመቅረብ ድፍረት ያገኛሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው፤ ይሁንና በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ ድፍረት አላጡም። ከእነዚህ መካከል አንዱ “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ያለውን ከፍተኛ እምነት ገልጿል። (ሉቃስ 5:​12) ኢየሱስ ለዚህ ሰው የሰጠውን ምላሽ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን። ይሁንና ይሄ ራሱ እንኳ ኢየሱስ የሚቀረብ ሰው እንደነበር የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ይሆናል።

11. በበደለኝነት ስሜት የሚሠቃዩ ሰዎች በነፃነት ወደ ኢየሱስ ይቀርቡ እንደነበር የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው? ይህስ ምን ያስተምረናል?

11 በበደለኝነት ስሜት የሚሠቃዩ ሰዎች በነፃነት ወደ ኢየሱስ ይቀርቡ ነበር። ለምሳሌ ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋብዞ በነበረበት ወቅት የተከሰተውን ነገር አስታውስ። በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ አንዲት ሴት ኢየሱስ ወዳለበት ቤት ገባች፤ ከዚያም እግሩ ሥር ተንበርክካ በፈጸመችው በደል የተነሳ ታለቅስ ጀመር። እንባዋ እግሩን ባራሰው ጊዜ በፀጉሯ እግሩን ታደርቅ ነበር። ኢየሱስን የጋበዘው ሰው ይህን ሲያይ ደስ አላለውም፤ ኢየሱስ ይህች ሴት ወደ እሱ እንድትቀርብ በመፍቀዱ በልቡ ክፉኛ ነቀፈው። ኢየሱስ ግን ሴትየዋ ከልብ ንስሐ በመግባቷ ያመሰገናት ሲሆን ይሖዋ ይቅር እንደሚላትም አረጋግጦላታል። (ሉቃስ 7:​36-50) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ በጥፋተኝነት ስሜት የሚሠቃዩ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ከአምላክ ጋር መታረቅ እንዲችሉ የሚያግዟቸው ደግና በቀላሉ የሚቀረቡ ረዳቶች ያስፈልጓቸዋል። ለመሆኑ ኢየሱስ እንዲህ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?

ኢየሱስን በቀላሉ የሚቀረብ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው?

12. ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ መሆኑ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?

12 ኢየሱስ በሰማይ ያለው የሚወደው አባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን አስታውስ። (ዮሐንስ 14:9) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” እንዳልሆነ ይገልጽልናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:​27) “ጸሎት ሰሚ” የሆነው ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹም ሆኑ እሱን ማወቅና ማገልገል የሚፈልጉ ሌሎች ቅን ሰዎች በማንኛውም ጊዜ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። (መዝሙር 65:2) እስቲ አስበው፣ በጽንፈ ዓለም ውስጥ በኃይሉም ሆነ በሥልጣኑ አቻ የሌለው አምላክ ከማንም በላይ የሚቀረብም ነው! እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ሰዎችን ይወዳል። በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ እንደምንመለከተው ኢየሱስ ሰዎችን ከልቡ ይወድ ነበር። ይሁንና በቀላሉ እንዲቀረብ ያደረገው ትልቁ ነገር ሰዎችም ይህን ፍቅሩን በቀላሉ ማስተዋላቸው ነው። ኢየሱስ ፍቅሩን ያሳየባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

13. ወላጆች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ሰዎች ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ከልብ እንደሚያስብላቸው በቀላሉ ማስተዋል ይችሉ ነበር። ኢየሱስ ውጥረት ውስጥ በነበረበት ጊዜም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን አሳቢነት ከማሳየት ወደኋላ ብሎ አያውቅም። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው እነዚያ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ እሱ ይዘው የመጡት ሥራ በዝቶበትና ከባድ ኃላፊነቶች ተጭነውበት በነበረበት ወቅት ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ ልጆቹን በደስታ በመቀበል በቀላሉ የሚቀረብ ሰው መሆኑን አሳይቷል። ኢየሱስ ለወላጆች ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል! በዛሬው ጊዜ ልጆችን ማሳደግ በጣም ፈታኝ ነው። ይሁንና ወላጆች፣ ልጆቻቸው እነሱን መቅረብ ቀላል እንዲሆንላቸው ማድረግ አለባቸው። መቼም ወላጅ ከሆንክ አንዳንድ ጊዜ በሥራ ከመወጠርህ የተነሳ ልጅህ የሚፈልገውን ትኩረት መስጠት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን ታውቅ ይሆናል። ይሁንና ወዲያው ሥራህን እንደጨረስክ እንደምታነጋግረው ልታረጋግጥለት ትችላለህ? ቃልህን ካከበርክ ደግሞ ልጅህ በትዕግሥት መጠበቅ ጥሩ ውጤት እንዳለው ይማራል። በተጨማሪም ምንም ዓይነት ችግር ወይም ጉዳይ ቢያጋጥመው ምንጊዜም ወደ አንተ መምጣት እንደሚችል ይገነዘባል።

14-16. (ሀ) ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተአምር እንዲፈጽም ያነሳሱት ሁኔታዎች ምን ነበሩ? ይህን ተአምር አስደናቂ ያደረገውስ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በቃና የፈጸመው ተአምር ስለ እሱ ምን ይገልጻል? ለወላጆችስ ምን ትምህርት ይዟል?

14 ኢየሱስ ሰዎችን የሚያሳስቧቸው ነገሮች እሱንም እንደሚያሳስቡት በግልጽ አሳይቷል። ኢየሱስ የፈጸመውን የመጀመሪያውን ተአምር እንደ ምሳሌ ተመልከት። ኢየሱስ በገሊላ በምትገኘው በቃና በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ ተገኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ጋባዦቹን ለኀፍረት የሚዳርግ ሁኔታ ተከሰተ፤ የወይን ጠጁ አለቀ! የኢየሱስ እናት ማርያም የተከሰተውን ነገር ለልጇ ነገረችው። ታዲያ ኢየሱስ ምን ያደርግ ይሆን? አገልጋዮቹ ስድስት ትላልቅ የድንጋይ ጋኖችን ውኃ እንዲሞሉ አደረገ። ከዚያም ለድግሱ አሳዳሪ ቀድተው እንዲያቀምሱት ነገራቸው፤ አሳዳሪው ሲቀምሰው የወይን ጠጁ በጣም ግሩም ከመሆኑ የተነሳ ተገረመ! ይህ አስማት የሚሠሩ ሰዎች እንደሚያደርጉት ያለ የማስመሰል ድርጊት ነበር? በፍጹም፣ ውኃው በእርግጥ ‘ወደ ወይን ጠጅ ተለውጦ’ ነበር። (ዮሐንስ 2:1-11) አንድን ነገር ወደ ሌላ ነገር መለወጥ ሰዎች ለዘመናት ሲመኙት የኖሩት ነገር ነው። አንዳንድ የጥንት ሰዎች (አልኬሚስቶች) እርሳስን (ሌድ) ወደ ወርቅ ለመቀየር ለብዙ መቶ ዘመናት ሲሞክሩ ቆይተዋል። እርሳስና ወርቅ የሚያስገርም ተመሳሳይነት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ቢሆኑም ይህ ሙከራቸው ሳይሳካ ቀርቷል። a ውኃንና የወይን ጠጅን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ውኃ ከሁለት መሠረታዊ ንጥረ ነገሮች የተሠራ ቀላል ኬሚካላዊ ይዘት ያለው ፈሳሽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የወይን ጠጅ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ውህዶችን የያዘ ነው፤ ከእነዚህ ውህዶች መካከል ብዙዎቹ የተወሳሰበ ኬሚካላዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። ታዲያ ኢየሱስ በዚህ የሠርግ ድግስ ላይ እንዲህ ያለውን አስደናቂ ተአምር የፈጸመው ለምንድን ነው? በሠርግ ድግስ ላይ የወይን ጠጅ እጥረት መከሰቱ ያን ያህል ከባድ ችግር ሆኖ ነው?

15 ይህ ችግር ለሙሽራውና ለሙሽሪት እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አልነበረም። በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ለእንግዶች ጥሩ መስተንግዶ ማድረግ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነበር። በሠርግ ድግስ ላይ የወይን ጠጅ ማለቁ ሙሽራውንና ሙሽሪትን ለከፍተኛ ኀፍረት የሚዳርግ ነው፤ የሠርጋቸውን ቀን የሚያበላሽባቸው ከመሆኑም በላይ መጥፎ ትዝታ ጥሎባቸው ያልፋል። ጉዳዩ ለእነሱ አሳሳቢ ነበር፤ ኢየሱስም አቅልሎ አልተመለከተውም። በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት እርምጃ ወስዷል። ታዲያ ሰዎች አሳሳቢ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው ወደ ኢየሱስ የሚቀርቡት ለምን እንደሆነ አሁን አስተዋልክ?

ልጆቻችሁ በቀላሉ የምትቀረቡ እንደሆናችሁና ከልብ እንደምታስቡላቸው እንዲያውቁ አድርጉ

16 ወላጆች ከዚህ ሁኔታም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ልጅህ በጣም ያሳሰበውን አንድ ጉዳይ ይዞ ወደ አንተ ቢመጣ ምን ታደርጋለህ? ጉዳዩን ወዲያውኑ ቀለል ማድረግ ሊቀናህ ይችላል። አልፎ ተርፎም ለመሳቅ ትፈተን ይሆናል። አንተን ከሚያስጨንቁህ ጉዳዮች አንጻር ልጁ ያጋጠመው ችግር እዚህ ግባ የማይባል ሊመስል ይችላል። ሆኖም ለልጁ ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ አትዘንጋ! ታዲያ በጣም የምትወደውን ሰው ያሳሰበው ጉዳይ አንተንም ሊያሳስብህ አይገባም? ልጅህን ያስጨነቀው ጉዳይ አንተንም እንደሚያሳስብህ መግለጽህ በቀላሉ የምትቀረብ ወላጅ እንድትሆን ያደርግሃል።

17. ገርነትን በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቶልናል? ይህን ባሕርይ ማሳየት ጥንካሬ ይጠይቃል የምንለውስ ለምንድን ነው?

17 ምዕራፍ 3 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ገርና ትሑት ነው። (ማቴዎስ 11:​29) ገርነት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ትሕትና ጥሩ አድርጎ የሚያሳይ ግሩም ባሕርይ ነው። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንድ ገጽታ ሲሆን ከአምላካዊ ጥበብ ጋር ተዛማጅነት አለው። (ገላትያ 5:​22, 23፤ ያዕቆብ 3:​13) ኢየሱስ በጣም የሚያበሳጭ ሁኔታ በገጠመው ጊዜም እንኳ ራሱን መግዛት ችሏል። ኢየሱስ ገር መሆኑ ደካማ መሆኑን የሚያሳይ አልነበረም። አንድ ምሁር ይህን ባሕርይ አስመልክተው ሲናገሩ “ከገርነት በስተ ጀርባ የብረት ያህል ጥንካሬ አለ” ብለዋል። በእርግጥም ንዴታችንን ተቆጣጥረን ሌሎችን በገርነት መያዝ ብዙውን ጊዜ ጥንካሬ ይጠይቃል። ሆኖም ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት ስለሚባርክልን ገር በመሆን ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን፤ ይህ ደግሞ በቀላሉ የምንቀረብ እንድንሆን ያስችለናል።

18. ኢየሱስ ምክንያታዊ እንደነበር የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው? ይህ ባሕርይ አንድን ሰው በቀላሉ የሚቀረብ ያደርገዋል የምትለው ለምንድን ነው?

18 ኢየሱስ ምክንያታዊ ነበር። ኢየሱስ በጢሮስ ሳለ አንዲት ሴት ወደ እሱ መጣች፤ ‘ጋኔን ይዟት ክፉኛ እየተሠቃየች’ ያለች ልጇን እንዲፈውስላትም ጠየቀችው። ኢየሱስ እሷ የጠየቀችውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በሦስት የተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። በመጀመሪያ ምንም ምላሽ ሳይሰጣት ዝም አላት፤ በሁለተኛ ደረጃ የጠየቀችውን ነገር የማያደርግበትን ምክንያት አስረዳት፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ነጥቡን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ ምሳሌ ነገራት። ይሁንና ይህን ያደረገው በማመናጨቅ ነው? ‘አንዴ ብያለሁ’ የሚል የግትርነት መንፈስ አሳይቷል? ደግሞስ እንደ እሱ ያለ ታላቅ ሰው ያቀረበውን ሐሳብ ባለመቀበሏ አጉል እንደተዳፈረች የሚጠቁም አነጋገር ተጠቅሞ ይሆን? በፍጹም፣ ይህች ሴት ኢየሱስን ማነጋገር አላስፈራትም። እንዲረዳት መጠየቅ ብቻ ሳይሆን እሷን ለመርዳት ፈቃደኛ አለመሆኑን እያየችም መወትወቷን አላቆመችም። ኢየሱስም በጽናት መለመኗን እንድትቀጥል ያደረጋትን አስደናቂ እምነት ስለተመለከተ ልጇን ፈውሶላታል። (ማቴዎስ 15:​22-28) በእርግጥም ኢየሱስ ምክንያታዊ መሆኑ እንዲሁም የሌሎችን ሐሳብ ለማዳመጥና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአቋም ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑ በቀላሉ የሚቀረብ እንዲሆን አስችሎታል!

አንተስ በቀላሉ የምትቀረብ ነህ?

19. በእርግጥ በቀላሉ የምንቀረብ መሆን አለመሆናችንን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

19 ብዙ ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን በቀላሉ የሚቀረቡ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥልጣን ያላቸው አንዳንድ ሰዎች በራቸው ለማንም ክፍት እንደሆነ መናገር ይወዳሉ፤ በእነሱ ሥር ያሉ ሰዎች ምንጊዜም በነፃነት ሊቀርቧቸው እንደሚችሉ ሲገልጹም ይሰማሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ታማኝ ፍቅር ያወራሉ፤ ይሁንና ታማኝ የሆነን ሰው ማን ሊያገኘው ይችላል?” ይላል። (ምሳሌ 20:6) በቀላሉ የምንቀረብ እንደሆንን መናገር ቀላል ነው፤ ሆኖም በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በእርግጥ እየተከተልን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ያለው እኛ ለራሳችን ባለን አመለካከት ላይ ሳይሆን ሌሎች ለእኛ ባላቸው አመለካከት ላይ ነው። ጳውሎስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:5) በመሆኑም እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ሰዎች ለእኔ ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? በሌሎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም አትርፌያለሁ?’

ሽማግሌዎች በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ይጥራሉ

20. (ሀ) ክርስቲያን ሽማግሌዎች በቀላሉ የሚቀረቡ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በጉባኤ ካሉ ሽማግሌዎች በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

20 በተለይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ይጥራሉ። በኢሳይያስ 32:1, 2 ላይ እንደተጠቀሰው ሆነው ለመገኘት ልባዊ ፍላጎት አላቸው፤ ጥቅሱ እንደሚከተለው ይላል፦ “እያንዳንዱም ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣ ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣ በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።” አንድ ሽማግሌ እንዲህ ያለ መሸሸጊያ እንዲሁም የደስታና የእረፍት ምንጭ መሆን የሚችለው በቀላሉ የሚቀረብ ከሆነ ብቻ ነው። ሽማግሌዎች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ብዙ ከባድ ኃላፊነቶች ስላሉባቸው ይህን ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። ያም ሆኖ ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች ለመንከባከብ ጊዜ የሌላቸው መስለው መታየት የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:2) በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ደግሞ ከእነዚህ ታማኝ ወንዶች በሚጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ለመሆን መጣር ይኖርባቸዋል፤ በዚህ መንገድ ትሑትና ተባባሪ መሆናቸውን ያሳያሉ።​—⁠ዕብራውያን 13:​17

21. ወላጆች፣ ልጆቻቸው በነፃነት እንዲቀርቧቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ ምን ጉዳይ እንመለከታለን?

21 ወላጆች ልጆቻቸው በፈለጓቸው ጊዜ ሁሉ ለእነሱ ትኩረት ለመስጠት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ አክብደው ሊያዩት የሚገባ ጉዳይ ነው! ወላጆች፣ ልጆቻቸው ሚስጥራቸውን በነፃነት ቀርበው የሚነግሯቸው ዓይነት ሰዎች መሆናቸውን ማስመሥከር ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ገርና ምክንያታዊ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ ለምሳሌ ልጃቸው የሠራውን ጥፋት ሲነግራቸው ወይም የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳለው የሚጠቁም ነገር ሲመለከቱ ስሜታቸውን መቆጣጠር ይኖርባቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን በትዕግሥት በሚያሠለጥኑበት ጊዜ ግልጽ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ጥረት ማድረግ አለባቸው። ሁላችንም ልክ እንደ ኢየሱስ በቀላሉ የምንቀረብ መሆን እንፈልጋለን። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስን በቀላሉ እንዲቀረብ ካደረጉት ዋና ዋና ባሕርያት መካከል አንዱን ይኸውም ከልብ የመነጨ ርኅራኄውን እንመለከታለን።

a የኬሚስትሪ ተማሪዎች እርሳስና ወርቅ ፔሬዲክ ቴብል በተባለው ሰንጠረዥ ላይ ተቀራራቢ በሆኑ ቦታዎች ላይ እንደሚገኙ ያውቃሉ። አንድ የእርሳስ አተም ከወርቅ አተም የሚለየው በኒውክለሱ ውስጥ ባሉት ሦስት ተጨማሪ ፕሮቶኖች ብቻ ነው። እንዲያውም በዘመናችን ያሉ የፊዚክስ ሊቃውንት በጣም ትንሽ መጠን ያለውን እርሳስ ወደ ወርቅ መለወጥ ችለዋል፤ ሆኖም ይህን ማድረግ ከፍተኛ ኃይል ስለሚጠይቅ ከወጪ አንጻር ሲታይ የሚያዋጣ ሆኖ አልተገኘም።