በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ሰባት

‘ከዚህ የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም’

‘ከዚህ የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም’

1-4. (ሀ) ጲላጦስ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ በተሰበሰበው በቁጣ የገነፈለ ሕዝብ ፊት ኢየሱስን ባቀረበው ጊዜ ምን ተከሰተ? (ለ) ኢየሱስ ውርደትና ሥቃይ ሲደርስበት ምን ምላሽ ሰጠ? ይህስ የትኞቹ ወሳኝ ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋል?

 “እነሆ፣ ሰውየው!” ሮማዊው አገረ ገዢ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ይህን ያለው ከቤተ መንግሥቱ ውጭ በተሰበሰበው በቁጣ የገነፈለ ሕዝብ ፊት ኢየሱስን ባቀረበው ወቅት ነው፤ ጊዜው 33 ዓ.ም. የፋሲካ ዕለት ጠዋት ላይ ነው። (ዮሐንስ 19:5) ከጥቂት ቀናት በፊት ኢየሱስ በአምላክ እንደተሾመ ድል አድራጊ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕዝቡ አወድሶት ነበር። በዚህ ዕለት ግን በቁጣ የተሞላው ሕዝብ በኢየሱስ ላይ ተነስቶበታል።

2 ኢየሱስ ነገሥታት የሚለብሱት ዓይነት ሐምራዊ ልብስ ለብሷል፤ በራሱም ላይ አክሊል ደፍቷል። ይሁንና በግርፋት በተተለተለው ሰውነቱ ላይ የደረቡለት ልብስም ሆነ ከእሾህ ጉንጉን የተሠራውና ጭንቅላቱን እያደማው ያለው አክሊል ዓላማ በንግሥናው ማፌዝ ነው። የካህናት አለቆቹ፣ ሕዝቡ በድብደባ ቆሳስሎ ፊታቸው በቆመው ሰው ላይ እንዲነሳ ቀሰቀሱ። “ይሰቀል! ይሰቀል!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስ ሲገደል ለማየት የቋመጠው ሕዝብም “መሞት አለበት” በማለት ጮኸ።​—⁠ዮሐንስ 19:1-7

3 ኢየሱስ የደረሰበትን ውርደትና ሥቃይ በእርጋታና በድፍረት አሜን ብሎ ተቀበለ። a ለመሞት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነው። በዚያ የፋሲካ ዕለት በመከራ እንጨት ላይ ተሠቃይቶ ለመሞት ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ።​—⁠ዮሐንስ 19:​17, 18, 30

4 ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ለተከታዮቹ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን አስመሥክሯል። “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:​13) ይህም የሚከተሉት ወሳኝ ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋል፦ በእርግጥ ኢየሱስ ይህን ያህል መሠቃየትና መሞት ያስፈልገው ነበር? ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነውስ ለምንድን ነው? ‘ወዳጆቹ’ እና ተከታዮቹ እንደመሆናችን መጠን እሱ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ መሠቃየትና መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

5. ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን መከራ በዝርዝር ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እንደመሆኑ መጠን ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው ያውቃል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መሲሑ እንደሚሠቃይና እንደሚሞት በዝርዝር የሚገልጹትን በርካታ ትንቢቶች ጠንቅቆ ያውቃል። (ኢሳይያስ 53:3-7, 12፤ ዳንኤል 9:​26) ከፊቱ ስለሚጠብቀው መከራ ለደቀ መዛሙርቱ ደጋግሞ በመንገር አእምሯቸውን እንዲያዘጋጁ አድርጓል። (ማርቆስ 8:​31፤ 9:31) የፋሲካን በዓል ለመጨረሻ ጊዜ ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ሳለ ለሐዋርያቱ እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ነግሯቸዋል፦ “የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል።” (ማርቆስ 10:​33, 34) ኢየሱስ ይህን ሲል እያጋነነ አልነበረም። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በእርግጥ ተፊዞበታል፣ ተተፍቶበታል፣ ተገርፏል በመጨረሻም ተገድሏል።

6. ኢየሱስ መሠቃየትና መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

6 ይሁን እንጂ ኢየሱስ መሠቃየትና መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ቁልፍ የሆኑ ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ ኢየሱስ በታማኝነት መጽናቱ ንጹሕ አቋም ጠባቂነቱን ያስመሠክራል፤ የይሖዋንም ስም ያስቀድሳል። ሰይጣን ‘ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው’ የሚል የሐሰት ክስ መሰንዘሩን አስታውስ። (ኢዮብ 2:1-5) ኢየሱስ “በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ” ታማኝ በመሆን ሰይጣን ለሰነዘረው መሠረተ ቢስ ክስ የማያዳግም ምላሽ ሰጥቷል። (ፊልጵስዩስ 2:8፤ ምሳሌ 27:​11) በሁለተኛ ደረጃ የመሲሑ መሠቃየትና መሞት የኃጢአት ስርየት ያስገኛል። (ኢሳይያስ 53:5, 10፤ ዳንኤል 9:​24) ኢየሱስ “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ [በመስጠት]” ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት የምንችልበት አጋጣሚ ከፍቶልናል። (ማቴዎስ 20:​28) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ የደረሰበትን ሥቃይና መከራ ሁሉ ችሎ በማለፍ “እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ” መሆን ችሏል። በመሆኑም “በድካማችን ሊራራልን” የሚችል ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሆኗል።​—⁠ዕብራውያን 2:​17, 18፤ 4:​15

ኢየሱስ ሕይወቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነው ለምንድን ነው?

7. ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ ምን መሥዋዕትነት ከፍሏል?

7 ኢየሱስ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደውን ነገር በሚገባ ለመረዳት እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እናስብ፦ አንድ ሰው ቤተሰቡንና አገሩን ትቶ ወደ ባዕድ አገር ለመሄድ ተነሳ እንበል፤ ሆኖም በሚሄድበት አገር አብዛኞቹ ሰዎች እንደሚጠሉት፣ ውርደትና ሥቃይ እንደሚደርስበት ይባስ ብሎም እንደሚገደል ቢያውቅ ለመሄድ ፈቃደኛ ይሆናል? እስቲ አሁን ደግሞ ኢየሱስ ያደረገውን ነገር አስብ። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከአባቱ ጋር ሲኖር ልዩ ክብር ነበረው። ሆኖም በሰማይ ያለውን መኖሪያውን በመተው ሰው ሆኖ ወደ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ሆኗል። ይህን ሁሉ ያደረገው አብዛኞቹ ሰዎች እንደማይቀበሉት፣ ለከፍተኛ ውርደት እንደሚዳረግ፣ ከባድ ሥቃይ እንደሚደርስበትና በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል እያወቀ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:5-7) ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ያለ መሥዋዕት እንዲከፍል የገፋፋው ምንድን ነው?

8, 9. ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ የገፋፋው ምንድን ነው?

8 ከሁሉም በላይ ኢየሱስ ይህን እንዲያደርግ የገፋፋው ለአባቱ ያለው ጥልቅ ፍቅር ነው። የደረሰበትን መከራ በጽናት መቋቋሙ ለይሖዋ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። ይህ ፍቅር ለአባቱ ስም እንዲቆረቆር አድርጎታል። (ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:1-6, 26) ኢየሱስ ከምንም ነገር በላይ በአባቱ ስም ላይ የተከመረው ነቀፋ ተወግዶ ማየት ይፈልግ ነበር። ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ መልካምና ውብ የሆነው የአባቱ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያውቃል፤ በመሆኑም ለጽድቅ ሲል መከራ መቀበሉን እንደ ትልቅ ክብርና መብት ቆጥሮታል።​—⁠1 ዜና መዋዕል 29:​13

9 ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ የገፋፋው ሌላው ምክንያት ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ነው። ገና ከሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ለሰው ልጆች ፍቅር ነበረው። ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ዘመን በፊት “በሰው ልጆች እጅግ [ይደሰት]” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ምሳሌ 8:​30, 31) ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይህ ፍቅሩ በግልጽ ታይቷል። ቀደም ባሉት ሦስት ምዕራፎች ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ በጥቅሉ ለሰዎች በተለይ ደግሞ ለተከታዮቹ ያለውን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ደግሞ ለእኛ ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሰጥቷል። (ዮሐንስ 10:​11) አዎ፣ ለእኛ ያለውን ፍቅር ሊያሳይ የሚችልበት ከዚህ የበለጠ መንገድ የለም። እኛስ በዚህ ረገድ የእሱን ምሳሌ መከተል ይጠበቅብናል? እንዴታ! እንዲያውም ይህን እንድናደርግ ታዘናል።

“እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ”

10, 11. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው አዲስ ትእዛዝ የትኛው ነው? ይህስ ምን ማድረግን ይጠይቃል? አዲሱን ትእዛዝ ማክበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለቅርብ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:​34, 35) ‘እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ የሚለው ትእዛዝ “አዲስ ትእዛዝ” የሆነው ለምንድን ነው? የሙሴ ሕግ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ትእዛዝ ነበረው። (ዘሌዋውያን 19:​18) አዲሱ ትእዛዝ ግን ከዚያ የላቀ ፍቅር እንድናሳይ ይጠይቅብናል፤ ሕይወታችንን ለሌሎች አሳልፈን እንድንሰጥ የሚያነሳሳ ፍቅር እንድናሳይ ታዝዘናል። ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው ብሎ በመናገር ይህን በግልጽ አስቀምጦታል፦ “ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።” (ዮሐንስ 15:​12, 13) በሌላ አነጋገር አዲሱ ትእዛዝ “ሌሎችን እንደ ራስህ ብቻ ሳይሆን ከራስህ አስበልጠህ ውደድ” የሚል ነው። ኢየሱስ በሕይወቱም ሆነ በሞቱ ይህ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል።

11 አዲሱን ትእዛዝ መታዘዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ “ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ [የራስን ጥቅም መሥዋዕት በሚያደርግ ፍቅር] ያውቃሉ” እንዳለ አስታውስ። አዎ፣ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ማሳየታችን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ያሳውቃል። ይህ ፍቅር የአንድን ሰው ማንነት ከሚገልጽ የባጅ ካርድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ በሚያደርጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ ሲገኙ ባጅ ያደርጋሉ። ይህ ካርድ የግለሰቡን ስምና ጉባኤ ስለሚገልጽ ማንነቱን ለይቶ ያሳውቃል። በተመሳሳይም አንዳችን ለሌላው የምናሳየው የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የባጅ ካርድ ነው ሊባል ይችላል። በሌላ አነጋገር እርስ በርስ ያለን ፍቅር በግልጽ የሚታይ ከመሆኑ የተነሳ እንደ ባጅ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን ለይቶ ማሳወቅ ይኖርበታል። በመሆኑም እያንዳንዳችን ‘አኗኗሬ ይህን “ባጅ” እንዳደረግኩ ማለትም የራሱን ጥቅም የሚሠዋ ፍቅር እንዳለኝ በግልጽ ያሳያል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው።

የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ምንን ይጨምራል?

12, 13. (ሀ) አንዳችን ለሌላው ፍቅር ለማሳየት እስከ ምን ድረስ መሥዋዕት መክፈል ይጠበቅብናል? (ለ) የራስን ጥቅም መሠዋት ሲባል ምን ማለት ነው?

12 የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን እሱ እንደወደደን እኛም እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን። ይህም ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስንል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች መሆንን የሚጠይቅ ነው። ይሁንና ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን ያለብን እስከ ምን ድረስ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እሱ ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ ስለሰጠ በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ሕይወታችንን ለወንድሞቻችን አሳልፈን የመስጠት ግዴታ አለብን።” (1 ዮሐንስ 3:​16) አስፈላጊ ከሆነ እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ አንዳችን ለሌላው ለመሞት ፈቃደኞች መሆን አለብን። በስደት ወቅት ክርስቲያን ወንድሞቻችንን አሳልፈን በመስጠት ሕይወታቸውን ለአደጋ ከማጋለጥ ይልቅ የገዛ ሕይወታችንን መሥዋዕት ማድረግ እንመርጣለን። የዘር ወይም የጎሳ ግጭት በሚነሳበት ጊዜ ሕይወታችንን ለአደጋ አጋልጠንም እንኳ የወንድሞቻችንን ሕይወት ለመታደግ ጥረት እናደርጋለን፤ ወንድሞቻችን ከየትኛው ዘር ወይም ጎሳ መሆናቸው ለውጥ አያመጣም። በተጨማሪም በአገራት መካከል ጦርነት በሚነሳበት ጊዜ በእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆነ በማንኛውም ሰው ላይ የጦር መሣሪያ አናነሳም፤ በዚህ የተነሳ ለእስር ይባስ ብሎም ለሞት ብንዳረግም እንኳ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች አንሆንም።​—⁠ዮሐንስ 17:​14, 16፤ 1 ዮሐንስ 3:​10-12

13 የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ማሳየት የምንችለው ለወንድሞቻችን ሕይወታችንን አሳልፈን በመስጠት ብቻ አይደለም። እንዲያውም ብዙዎቻችን እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ሁኔታ አያጋጥመንም። ሆኖም ሕይወታችንን አሳልፈን እስከ መስጠት ድረስ ወንድሞቻችንን የምንወዳቸው ከሆነ እነሱን ለመርዳት ስንል ያን ያህል ከባድ ያልሆኑ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን አይገባንም? የራስን ጥቅም መሠዋት ሲባል ለሌሎች ስንል የግል ጥቅማችንን ወይም ምቾታችንን መሥዋዕት ማድረግ ማለት ነው። አመቺ በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ከራሳችን ይልቅ እነሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገርና ደህንነታቸውን እናስቀድማለን። (1 ቆሮንቶስ 10:​24) ታዲያ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

በጉባኤና በቤተሰብ ውስጥ

14. (ሀ) ሽማግሌዎች ምን መሥዋዕት መክፈል ይጠበቅባቸዋል? (ለ) በጉባኤህ ስላሉት በትጋት የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ምን ይሰማሃል?

14 የጉባኤ ሽማግሌዎች “የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች [ለመንከባከብ]” ሲሉ ብዙ መሥዋዕት ይከፍላሉ። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ቤተሰባቸውን ከመንከባከብ በተጨማሪ ምሽት ላይ ወይም ቅዳሜና እሁድ የተለያዩ የጉባኤ ኃላፊነቶችን መወጣት ይኖርባቸዋል፤ ለምሳሌ በስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ ክፍሎችን መዘጋጀት፣ እረኝነት ማድረግ ወይም የፍርድ ጉዳዮችን መመልከት። ተጨማሪ መሥዋዕት የሚከፍሉ ብዙ ሽማግሌዎችም አሉ፤ ለምሳሌ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን በትጋት ያከናውናሉ እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ወይም በሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ውስጥ ያገለግላሉ። ሌሎቹ ደግሞ የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ያገለግላሉ። እናንት ሽማግሌዎች ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁንና ጥሪታችሁን መንጋውን ለመንከባከብ ስታውሉ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር እያሳያችሁ መሆኑን አትዘንጉ። (2 ቆሮንቶስ 12:​15) ራሳችሁን ሳትቆጥቡ የምታከናውኑትን ሥራ ይሖዋ ብቻ ሳይሆን እንደ እረኛ ሆናችሁ የምታገለግሉት ጉባኤም ያደንቀዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​29፤ ዕብራውያን 6:​10

15. (ሀ) የሽማግሌዎች ሚስቶች የሚከፍሏቸው አንዳንድ መሥዋዕቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ባሎቻቸው ጉባኤውን እንዲያገለግሉ ስለሚደግፉ ሚስቶች ምን ይሰማሃል?

15 ስለ ሽማግሌ ሚስቶችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሴቶች ባሎቻቸው መንጋውን ሲንከባከቡ እነሱን ለመደገፍ ብዙ መሥዋዕት ይከፍላሉ። አንድ ባል ከቤተሰቡ ጋር ሊያሳልፍ ይችል የነበረውን ጊዜ የጉባኤ ጉዳዮችን ለማከናወን ሲጠቀምበት ሚስቱ በእርግጥም መሥዋዕት እየከፈለች ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሚስቶችም ምን ያህል መሥዋዕት እንደሚከፍሉ አስብ፤ ከባሎቻቸው ጋር በመሆን ከጉባኤ ወደ ጉባኤና ከወረዳ ወደ ወረዳ ይሄዳሉ። የራሴ የሚሉት ቤት የላቸውም፤ ምናልባትም በየሳምንቱ የተለያየ አልጋ ላይ መተኛት ይጠበቅባቸዋል። ከራሳቸው ይልቅ የጉባኤውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ ሚስቶች፣ ለሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:3, 4

16. ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ሲሉ ምን መሥዋዕት ይከፍላሉ?

16 በቤተሰብ ውስጥ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ወላጆች ልጆቻችሁ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት እንዲሁም “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ ብዙ መሥዋዕት ትከፍላላችሁ። (ኤፌሶን 6:4) ልጆቻችሁ የዕለት ጉርስ፣ ልብስና መጠለያ እንዲያገኙ ስትሉ ለረጅም ሰዓት አድካሚ ሥራ ትሠሩ ይሆናል። ልጆቻችሁ መሠረታዊ ነገሮችን ከሚያጡ እናንተ ብትቸገሩ ትመርጣላችሁ። በተጨማሪም ከልጆቻችሁ ጋር ለማጥናት፣ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛችኋቸው ለመሄድና አብራችኋቸው ለማገልገል ከፍተኛ ጥረት ታደርጋላችሁ። (ዘዳግም 6:6, 7) የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ማሳየታችሁ የቤተሰብ መሥራች የሆነውን አምላክ ያስደስተዋል፤ ልጆቻችሁ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሊረዳቸውም ይችላል።​—⁠ምሳሌ 22:6፤ ኤፌሶን 3:​14, 15

17. ክርስቲያን ባሎች ኢየሱስ ያሳየውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ሊኮርጁ የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ባሎች፣ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምትችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ራሱን ለጉባኤው አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌሶን 5:​25) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ኢየሱስ ተከታዮቹን በጣም ይወዳቸው ስለነበር ለእነሱ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። አንድ ክርስቲያን ባልም፣ “ራሱን አላስደሰተም” የተባለለት ኢየሱስ ያሳየውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይኮርጃል። (ሮም 15:3) እንዲህ ዓይነት ባል ከራሱ ይልቅ የሚስቱን ፍላጎትና ስሜት ያስቀድማል። ምንጊዜም እኔ ያልኩት ይሁን ብሎ ድርቅ አይልም፤ ከዚህ ይልቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የሚስቱን ሐሳብ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ይሆናል። የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር የሚያሳይ ባል በይሖዋ ፊት ሞገስ ያገኛል፤ በተጨማሪም የሚስቱንና የልጆቹን ፍቅርና አክብሮት ያተርፋል።

ምን ማድረግ ይጠበቅብሃል?

18. እርስ በርስ እንድንዋደድ የተሰጠንን አዲስ ትእዛዝ እንድንፈጽም የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

18 እርስ በርስ እንድንዋደድ የተሰጠንን አዲስ ትእዛዝ መፈጸም ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው፤ ይሁንና እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል፤ . . . በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።” (2 ቆሮንቶስ 5:​14, 15) ኢየሱስ ለእኛ ሲል መሞቱ እኛም ለእሱ እንድንኖር ግድ አይለንም? የኢየሱስ ዓይነት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር በማሳየት ይህን ማድረግ እንችላለን።

19, 20. ይሖዋ ምን ውድ ስጦታ ሰጥቶናል? እኛስ ይህን ስጦታ መቀበላችንን የምናሳየው እንዴት ነው?

19 ኢየሱስ “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ብሎ ሲናገር እያጋነነ አልነበረም። (ዮሐንስ 15:​13) ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ሕይወቱን ለእኛ ሲል አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑ ነው። ይሁንና ከዚህ የበለጠ ፍቅር ያሳየን ሌላም አካል አለ። ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:​16) አምላክ እኛን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የምንወጣበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ኤፌሶን 1:7) ቤዛው ይሖዋ የሰጠን ውድ ስጦታ ነው፤ ሆኖም ይህን ስጦታ እንድንቀበል አያስገድደንም።

20 ይህን የይሖዋ ስጦታ መቀበል አለመቀበል የራሳችን ምርጫ ነው። ስጦታውን መቀበላችንን የምናሳየው እንዴት ነው? በልጁ ‘በማመን’ ነው። ይሁን እንጂ እምነት እንዲያው በቃል ብቻ የሚገለጽ አይደለም። በተግባራችን ማለትም በአኗኗራችን የሚታይ ነገር ነው። (ያዕቆብ 2:​26) በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዳለን የምናስመሠክረው በየዕለቱ የእሱን ፈለግ በመከተል ነው። እንዲህ ማድረጋችን አሁንም ሆነ ወደፊት የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል፤ የዚህ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ይህን ያብራራል።

a ኢየሱስ በዚያን ዕለት ሁለት ጊዜ ተተፍቶበታል፤ በመጀመሪያ በሃይማኖት መሪዎቹ በኋላ ደግሞ በሮማውያን ወታደሮች። (ማቴዎስ 26:​59-68፤ 27:​27-30) ያም ሆኖ ይህን የሚያዋርድ ድርጊት በጸጋ ተቀብሏል፤ “ፊቴን፣ ከሚያዋርዱ ነገሮችና ከትፋት አልሰወርኩም” የሚለው ትንቢት እንዲፈጸምም አድርጓል።​—⁠ኢሳይያስ 50:6