በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለሕዝብ ለማንበብ መትጋት’

‘ለሕዝብ ለማንበብ መትጋት’

ጥናት 6

‘ለሕዝብ ለማንበብ መትጋት’

1, 2. በሕዝብ ፊት የምናነብባቸው እንዴት ያሉ አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ?

1 ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለሕዝብ ለማንበብ . . . ትጋ” በማለት መክሮት ነበር። በተጨማሪም የማንበብ ችሎታንም ሆነ ሌሎቹን ለአገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎች ለሌሎች ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲያስተምር ጳውሎስ መመሪያ ሰጥቶታል። (1 ጢሞ. 4:13 አዓት) ይህ በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት የተጻፈ ምክር በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮችም በጣም አስፈላጊ ነው። እኛም ይህን ምክር ሰምተን ብንፈጽመው በጣም እንጠቀማለን።

2 በቲኦክራሲያዊው አመራር ሥር ያለው አገልጋይ ለሕዝብ እንዲያነብ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። በመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ ጥቅሶችና አንቀጾች ይነበባሉ። በአገልግሎት ስብሰባና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንደዚሁም በመስክ አገልግሎት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይነበባሉ። ስለዚህ እያንዳንዱ አገልጋይ ጥሩ የሕዝብ አንባቢ ቢሆን ራሱም ሆነ የሚሰሙት ሰዎች ይጠቀማሉ።

3. ዝግጅት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ለሕዝብ ማንበብ ማለት ሌሎች ለመስማት እንዲችሉ ጮክ ብሎ ማንበብ ማለት ነው። ይሁን እንጂ አንባቢው በእያንዳንዱ ቃል ላይ ቢደናቀፍ ወይም ሐረጎቹን እንደሚገባ ሳይከፋፍል ወይም አለቦታው እያጠበቀ በማንበቡ ትርጉሙ ቢሰወር አድማጮቹ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉን? ምንም ዓይነት ግለት ሳይኖረው በአንድ ዓይነት የድምፅ ቃና ቢያነብ በትኩረት ሊያዳምጡት ይችላሉን? በርከት ባሉ ሰዎች ፊት ጥሩ አድርጎ ለማንበብ ዝግጅት ያስፈልጋል። ማንኛውም ዓይነት የንባብ ክፍል ሲሰጠን፣ በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ ማንበብ እንኳ ቢሆን ጽሑፉን በቅድሚያ ሳያነቡ ለማከናወን መነሣት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። አድማጮች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ከመቅረታቸውም በላይ ከአንባቢው የተሳሳተ አነባበብ ወይም የቃላት አጠራር ሊማሩ ይችላሉ። አዎን፣ ማንኛውም አገልጋይ ለሕዝብ ለማንበብ መትጋት ያስፈልገዋል። — ዕን. 2:2

4, 5. ሕዝባዊ ንባብ አድማጮችን የሚቀሰቅስና በቀላሉ የሚገባ እንዲሆን ምን ዓይነት ባሕርያት አስፈላጊ ይሆናሉ?

4 አስፈላጊዎቹ ባሕርያት። በምታነብበት ጊዜ የጋለ ስሜት ይኑርህ። ሞቅ ባለ መንፈስ በመናገር ቃላቱ የሚያስተላልፉትን ስሜት አንጸባርቅ። ይህን ካደረግህ ንግግሩ ቀዝቃዛና ሕይወት የሌለው አይሆንም። ድምፅህ አድማጮች አንዳንድ ቃላትን መስማት እስኪሳናቸው ድረስ ዝቅ እንዳይል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። የድምፅህ መጠን በክፍሉ ወይም በአዳራሹ በሙሉ ሊሰማ የሚችል መሆን ይገባዋል። የምታነበውን አንዱን ቃል እንኳን ለመስማት የሚቸገር ሰው መኖር የለበትም።

5 የምታነበውን ቃል ሁሉ ሳትቆራርጥና ሳታድበሰብስ በተጣራና ሊደመጥ በሚችል መንገድ ማንበብህ አስፈላጊ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ በጥራት ላይ በማተኮር ዋናው መልእክት በግልጽ እንዳይተላለፍ ማድረግ ጥሩ አይደለም። ንባቡ በጥሩ ሁኔታ የቀረበ ከሆነ አድማጩ የተነበበውን ቃል በሙሉ በማያሻማ ሁኔታ ያዳምጣል። አብዛኛውን ጊዜ ንባቡ ግልጽ ሆኖ የማይሰማው የአንባቢው ድምፅ በቀጥታ ወደ አድማጮች ስለማይተላለፍ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በምታነብበት ጊዜ ራስህን ቀና አድርገህ የማንበብ ልማድ ይኑርህ። ከአፍህ የሚወጣው ድምፅ ምንም ነገር ሳያግደው ወደ አድማጮች ለመድረስ እንዲችል አፍህን በተገቢ ሁኔታ ከፈት አድርገህ አንብብ።

6. የትኞቹ ቃላትና ሐረጎች መጉላት እንዳለባቸው የሚወሰነው እንዴት ነው? ቆም ማለት ቁልፍ ሐሳቦችን ጎላ ለማድረግ የሚጠቅመው በምን መንገድ ነው?

6 በተገቢ ቦታ ላይ ጠበቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው። እንዲያውም የምታነበውን ነገር ለመረዳት ቁልፉ ጠበቅ ማድረግ ነው። በማይገባ ቦታ ላይ ጠበቅ ማድረግ ያልተፈለገ ትርጉም ወደ አድማጮች ሊያስተላልፍ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በልዩ ሁኔታ ጠበቅ መደረግ የሚገባው አንድ ቃል ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ግን ሙሉ ሐረግ ነው። መጥበቅ የሚኖርበት ሐረግ ወይም ቃል የሚወሰነው ማስተላለፍ በተፈለገው ሐሳብ እንጂ በቀረው የአረፍተ ነገር ክፍል አይደለም። በተገቢ ቦታዎች ላይ ቆም ማለት ሐሳቦችን ጠበቅ ለማድረግ ያስችላል። ለአጭር ጊዜ ቆም ማለት አንድ ዓይነት ሐሳብ የሚያስተላልፉ ቃላትን አንድ ላይ ለማሰባሰብና ቁልፍ ሐሳቦች ተለይተው እንዲወጡ ሲያስችል ረዘም ላለ ጊዜ ቆም ማለት ደግሞ የነጥቡ አንድ ዋነኛ ክፍል መደምደሚያ ላይ መድረሱን ያመለክታል።

7. ንባብ ከሰው ጋር የሚደረግ ውይይት እንዲመስል የሚያስችለው ምንድን ነው?

7 በተጨማሪም በጥሩ ሁኔታ ለማንበብ ጥረት በምታደርግበት ጊዜ የድምፅህን ቃናና የአነባበብህን ፍጥነት ስለመለዋወጥ ማሰብ ይኖርብሃል፤ አለዚያ ንባቡ አሰልቺና የማይማርክ ይሆናል። ድምፅህን በተገቢ ሁኔታ ከለዋወጥክ ግን ንባብህ ከወትሮው ንግግርህ ጋር የሚመሳሰልና በውይይት መልክ የቀረበ ይመስላል።

8. በንባብ ንግግር መስጠት አስፈላጊ የሚሆነው እንዴት ባሉ ጊዜያት ነው?

8 በንባብ የሚቀርብ ንግግር። ሕዝባዊ ንባብ አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ሁኔታዎች አንዱ ጽሑፍ በማንበብ ንግግር መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ነው። ይህ ዓይነቱ አቀራረብ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል ማኅበሩ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የአምላክ ሕዝብ ጉባኤዎች በሙሉ በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት መልእክት እንዲሰሙ ዝግጅት የሚያደርግበት ጊዜ ይኖራል። በተጨማሪም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡ አንዳንድ ንግግሮች በዜና ማሠራጫዎች በቀጥታ የሚጠቀሱበት ሁኔታ ሲኖርና ከበድ ያለ የተወሳሰበ ትምህርት በትክክል እንዲቀርብ ሲፈለግ ንግግሩ በንባብ መልክ ይሰጣል።

9, 10. በንባብ ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ የሚያጋጥመው ከባዱ ችግር ምንድን ነው? ችግሩንስ እንዴት መወጣት ይቻላል?

9 ከተዘጋጀ ጽሑፍ በማንበብ ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ የሚያጋጥመው ዋነኛ ችግር ቃሎቹንና ሐረጎቹን በተራ ውይይት እንደሚነገሩ አስመስሎ ማቅረብ ነው። ይሁን እንጂ የድምፁ መጠን ከፍ ማለት ይኖርበታል። አብዛኛውን ጊዜም የጽሑፉ አቀራረብ አንተ በተለምዶ ከምትጠቀምበት አነጋገር የተለየ ይሆናል። አረፍተ ነገሮቹ ረዣዥሞችና የተወሳሰቡ ይሆናሉ። ከተለምዶ አነጋገርህ የተለዩ ምርጥ ሐረጎችና አነጋገሮች ሊኖሩት ይችላል። ትምህርቱን በራስህ ቃልና አነጋገር ብታቀርበው የሚሻል መስሎ ሊታይህ ይችላል። ይሁን እንጂ በቂ ልምምድ ባደረግህና በቂ ተሞክሮ ባገኘህ መጠን በንባብ ንግግር የመስጠት ችሎታህ ይሻሻላል።

10 የተሳካ ውጤት ለማግኘት ቁልፉ በቅድሚያ ዝግጅት ማድረግ ነው። በቂ ጊዜ ወስዶ ከጽሑፉ ጋር በሚገባ መተዋወቅ አስፈላጊ ነው። ዋና ዋናዎቹ ሐሳቦች በአእምሮህ ውስጥ በደንብ እንዲቀረጹ ትምህርቱን ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልግሃል። እንግዳ የሆኑ ቃላት ካጋጠሙህ በጥሩ መዝገበ ቃላት ላይ የቃላቱን ትርጉምና አነባበብ ተመልከት። በጽሑፉም ላይ ምልክት አድርግ። ከዚያም ከጽሑፉ አዘጋጅ አቀራረብ ጋር ለመተዋወቅ እንድትችል ጮክ ብለህ እያነበብህ ተለማመድ። አንዳንድ አንባቢዎች መስተዋት እያዩ መለማመድ ከአድማጮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዳሻሻለላቸው ተገንዝበዋል። ከአድማጮች ጋር ጥሩ ግንኙነት መኖሩ በተለይ ንግግሩ የሚሰጠው በአነስተኛ አዳራሽ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ በጣም አስፈላጊ ነው።

11. በጽሑፉ ላይ እንዴት ያሉ ምልክቶችን ማድረግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል?

11 ጠበቅ ለማድረግ በምትፈልጋቸው ቃላት ላይ ማስመር ወይም የተለየ ምልክት ማድረግ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ አንባቢዎች በጽሑፉ ውስጥ ያሉትን ሐረጎች በትናንሽ ቋሚ መስመሮች መከፋፈል ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በተጨማሪም አንድ ላይ ተያይዘው መነበብ የሚኖርባቸው ቃላት ሲኖሩ ሐረጉን ከመጨረስህ በፊት ቆም እንዳትል ቃሎቹን ጎበጥ ባሉ መሥመሮች ማገናኘት ትችላለህ። ይህም ትርጉሙ ግልጽ ያልሆነ ቃል ከመናገር ወይም ከተለምዶ አነጋገርህ በተለየ ሁኔታ ከመናገር ሊያድንህ ይችላል። በተጨማሪም ረዘም ላለ ጊዜ ቆም ማለት አስፈላጊ የሚሆንባቸውን ቦታዎች የሚያመለክቱ ምልክቶችን ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በንግግር መሃል ቆም ማለት የጉጉት መንፈስ ይፈጥራል፣ ቁልፍ ሐሳቦችን ጎላ ለማድረግ ይረዳል፣ ትምህርቱን ለማዋሃድ የሚያስችል በቂ ጊዜ ያስገኛል። ከዚህም ሌላ በንግግሩ ውስጥ ማሳረጊያ ወይም መቋጫ የሚደረግባቸውን ቦታዎች መለየት በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህን ቦታዎች ምልክት ልታደርግባቸው ትችላለህ። ምልክቶቹ ላይ ስትደርስ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ታሳርጋለህ፤ ከዚያም ፍጥነትህን ለመቀየር ትችላለህ።

12–15. በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብበት ጊዜ በቅድሚያ መዘጋጀት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

12 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ። ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ችሎታ በዕድሜ ለገፉም ሆነ ለወጣቶች በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ጮክ ብሎ ማንበብ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል ይሰጣል። ሁላችንም በመስክ አገልግሎታችን ሰዎችን ስናነጋግር ጥቅሶችን እናነባለን። ይሁን እንጂ ጥቅሶቹን በደንብ እናነባለንን? በየቃላቱ ላይ እንዳንደናቀፍ ወይም ከተናገርነው ነጥብ ጋር የሚስማማውን ሐሳብ ጎላ ለማድረግ እንድንችል ወይም ንባባችን ከዘወትሩ አነጋገራችን ጋር እንዲመሳሰል ተገቢ ዝግጅት አድርገናልን?

13 መጽሐፍ ቅዱስ ከማንበባችን በፊት በቂ ዝግጅት ማድረግ በእርግጥ አስፈላጊ ነው። የምታነበው በጣም ልዩ የሆነ ውበትና ስሜት የሚገለጽበትንና ትክክለኛና ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚቀርብበትን የአምላክ ቃል እንደሆነ ልብ ማለት ይኖርብሃል። አድማጮችን በሙሉ ሊጠቅም በሚችል መንገድ ለማቅረብ መፈለግ ይገባናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናነብበት አጋጣሚ እንደሚኖር በቅድሚያ ካወቅን እንግዳ የሆኑ ቃላት ወይም ሐረጎች ሲያጋጥሙን ግራ እንዳንጋባ በጥንቃቄ መዘጋጀት ይኖርብናል።

14 ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን በኢየሩሳሌም የውኃ በር ፊት በነበረው አደባባይ ተሰብስበው የአምላካቸውን ቃል በጥሞና በሚያዳምጡበት ጊዜ የነበረውን አስደሳች አጋጣሚ አስብ። እንዲያነቡ የተመደቡት ሌዋውያን በሚገባ ያልተዘጋጁና መልእክቱን አድበስብሰው የሚያቀርቡ ነበሩን? ታሪኩ መልሱን ይሰጠናል:- “የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፣ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።” (ነህ. 8:8) እነዚህ አንባቢዎች ቃሉን ለአምልኮ ባልንጀሮቻቸው ለሚያስተላልፉለት ልዑል አምላክ የጠለቀ አክብሮት ነበራቸው።

15 ለራሳችን ብቻ የምናነብም ሆንን ለቤተሰባችን ወይም በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ወይም ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ ላገኘነው ሰው ጮክ ብለን የምናነብ ብንሆን የምናነበውን ጽሑፍ እምነት የመገንባት ኃይልና ስሜት በታማኝነትና በተሟላ ሁኔታ እናስተላልፍ። ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፈልን በሚከተለው ቃል ጎላ ብሎ የተገለጸው ይህ ለሕዝብ ማንበቡ ያለው ቀስቃሽ ኃይል ነው። “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” — ራእይ 1:3

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]