በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መደጋገምና የሰውነት እንቅስቃሴዎች

መደጋገምና የሰውነት እንቅስቃሴዎች

ጥናት 26

መደጋገምና የሰውነት እንቅስቃሴዎች

1–3. መደጋገም በጣም አስፈላጊ የሆነ የማስተማሪያ ዘዴ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

1 ንግግር ስትሰጥ ዓላማህ አድማጮችህ የሚያስታውሱትንና ሊጠቀሙበት የሚችሉትን እውቀት ማስጨበጥ መሆን አለበት። ትምህርቱን ከረሱት ጥቅሙ ቀረባቸው ማለት ነው። የምትናገረውን በአእምሮአቸው ውስጥ ለመትከል ከምትችልባቸው ዋና ዋና ዘዴዎች አንዱ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ነጥቦች መደጋገም ነው። መደጋገም የአእምሮ ማኅተም ነው። ወሳኝ ከሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች አንዱ መደጋገም ነው። ጥቅሶችን ከማንበብ ጋር በተያያዘ የመደጋገምን አስፈላጊነት ቀደም ሲል ተመልክተሃል። ሆኖም “ለማጉላት ሲባል መደጋገም” የሚለው ነጥብ ለሌሎቹ የንግግር ክፍሎችም ጭምር ስለሚሠራ በንግግር ምክር መስጫ ቅጽህ ውስጥ ለብቻው ተቀምጧል።

2 ለማጉላት ሲባል በመደጋገም ረገድ ጥሩ ችሎታ እንዲኖርህ ጉዳዩን ከሁለት አቅጣጫዎች እንመለከተዋለን። እያንዳንዱ አቅጣጫ የተለያየ የመደጋገም ዘዴ መጠቀምን ይጠይቃል። እያንዳንዱም የተለያየ ዓላማ አለው። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች መደጋገም እነዚያን ነጥቦች በአእምሮ የማስታወሻ ማኅደር ውስጥ ለመክተት ይረዳል። ግልጽ ያልሆኑ ነጥቦችን መደጋገም ደግሞ አድማጮች እነዚያ ነጥቦች እንዲገቧቸው ይረዳቸዋል።

3 ይህንን የንግግር ባሕርይ በተመለከተ ሊታሰብበት የሚገባው የንግግሩ አሰጣጥ ብቻ ሳይሆን ዝግጅቱም ጭምር ነው። የትኞቹን ሐሳቦች መደጋገም እንደሚያስፈልግና የት ላይ እነርሱን መድገም ጥሩ እንደሆነ በቅድሚያ መወሰን ያስፈልግሃል።

4–6. “በየደረጃው” የሚሰጠውን ማጠቃለያና “በመደምደሚያው” ላይ የሚቀርበውን ማጠቃለያ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለመድገም እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ግለጽ።

4 ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች መድገም። ብዙውን ጊዜ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች የምንደጋግመው በማጠቃለያ መልክ በማቅረብ ነው። ጎላ ብለው የሚታዩ ሁለት የማጠቃለያ ዓይነቶችን እንመለከታለን። እነርሱንም “በየደረጃው የሚቀርብ” ማጠቃለያና “የመደምደሚያ” ማጠቃለያ ብለን እንጠራቸዋለን።

5 በየደረጃው የሚቀርብ ማጠቃለያ እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ሲያልቅ ፍሬ ነገሮቹን መልሶ በመዘርዘር የሚከናወን ሲሆን ከዚያ በፊት ከነበሩት ዋና ዋና ነጥቦች ጋር እያያያዙ መሄድ ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ ንግግሩ እንደ ሰንሰለት እርስ በርሱ እየተሳሰረ በመሄድ አንድ ወጥ ይሆናል።

6 ንግግሩ ሲያልቅ የመደምደሚያ ማጠቃለያ ይሰጣል። ይህም ከእርሱ በፊት የነበሩት በየደረጃው የቀረቡት ማጠቃለያዎች አካል ሆኖ ወይም ራሱን የቻለ ሆኖ ቢቀርብም ሁሉንም ነገር ጨምቆ ጠቅላላው ንግግር በአጫጭር ጥቂት ሐሳቦች እንዲከለስ ያደርጋል። በክለሳው ላይ ምን ያህል ነጥቦች እንደሚዘረዘሩ አስቀድሞ መናገሩ አልፎ አልፎ ይረዳል። ትምህርቱን በአእምሮ ለመያዝ የሚረዳው ተጨማሪ ዘዴም ይህ ነው።

7–10. ነጥቦችን በማጠቃለያ መልክ መድገሙ አስደሳች በሆነ መንገድ ሊከናወን የሚችለው እንዴት ነው?

7 ማጠቃለያው ነጥቦቹን ወይም ሐሳቦቹን በቀጥታ በመዘርዘር ብቻ የሚቀርብ ድርቅ ያለ ክለሳ መሆን አያስፈልገውም። በልዩ ልዩ መንገድ ሊቀርብ ይችላል። ምሳሌ በመናገር፣ በጥቅስ፣ ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ በማየት፣ ነገሮችን በማወዳደር ወይም በማነጻጸር፣ ከሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች ጋር በማስተያየት፣ ተመሳሳይ ቃላት በመጠቀም ወይም በጥያቄ መልክ ሊቀርብ ይችላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የአንድ የሕዝብ ንግግር ማጠቃለያ አጠር ያለ፣ በአምስት ደቂቃ የሚሸፈን፣ በንግግሩ ውስጥ በተጠቀሱት መሠረታዊ ጥቅሶችና በዋና ዋናዎቹ ነጥቦች አማካኝነት የሚቀርብ ሊሆን ይችላል። ጠቅላላው ንግግር በዚህ መልክ ጠቅለል ተደርጎ ማንኛውም ሰው ይዞት ሊሄድና ሊጠቀምበት እንደሚችል ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

8 የማጠቃለያው ዓይነት መደጋገም በተለይ አንድን ነገር ለማሳመን ምክንያቶች ለተደረደሩበት ወይም በቅደም ተከተል ልዩ ልዩ ነጥቦች ለተዘረዘሩበት ንግግር በጣም ይረዳል። ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ በተሰጠበትና አጭር ክለሳ በተደረገበት መሃል ያለው ጊዜ ነጥቦቹ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ ይበልጥ ጠልቀው እንዲገቡ ይረዳል። ይሁን እንጂ በአንድ ነጥብ ሥር ለተብራሩት ሐሳቦች ማጠቃለያ መስጠቱ ሁልጊዜ አስፈላጊ አይደለም። ባጭሩ በመጥቀስ ቀጥለን ለምናብራራው ሌላ ጉዳይ መነሻ አድርገን ልንጠቀምበት እንችላለን።

9 ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች መደጋገም የሚቻልበት ሌላው መንገድ በንግግሩ መግቢያ ላይ እነዚያን ነጥቦች አንድ በአንድ መዘርዘር በኋላም በንግግሩ ሐተታ ላይ እነዚህን ነጥቦች በስፋት ማብራራት ነው። በዚህ መንገድ ሐሳቦቹ መደጋገማቸው በአድማጮች አእምሮ ላይ በደንብ እንዲታተሙ ይረዳል።

10 ዋና ዋና ነጥቦችን መደጋገም የሚቻልባቸውን እነዚህን የተለያዩ መንገዶች ማወቃችን ማራኪ፣ አስደሳችና በቀላሉ ሊታወስ የሚችል ንግግር ለመስጠት ያስችለናል።

11–14. አድማጮች ያልገቧቸውን ነጥቦች በመድገም በኩል ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ቁልፍ ነገሮች ምንድን ናቸው?

11 አድማጮች ያልገቧቸውን ነጥቦች መደጋገም። አድማጮች እንዲገባቸው በማሰብ አንድን ነጥብ መድገሙ ሙሉ በሙሉ በአድማጮች ሁኔታ ላይ የተመካ ነው ለማለት ይቻላል። ነጥቡ በጣም አስፈላጊ ቢሆንና አድማጮች ከአንድ ጊዜ በላይ ያ ነጥብ ካልተደጋገመላቸው ግልጽ የማይሆንላቸው ከሆነ በአንድ ዓይነት ዘዴ ደግመህ መግለጽ ይኖርብሃል፤ አለበለዚያ አድማጮችህን መንገድ ላይ ጥለህ ወደ ንግግሩ መደምደሚያ ትደርሳለህ። በሌላው በኩል ግን ለማጉላት ታስቦ ያልተደረገ አላስፈላጊ ድግግሞሽ ንግግሩን የተንዛዛና አሰልቺ ያደርገዋል።

12 ንግግሩን በምትዘጋጅበት ጊዜ አድማጮችህን በአሳብህ ከፊትህ አስቀምጥ። እንደዚያ ማድረግህ አድማጮችህ ምናልባት ለመረዳት የሚቸገሩበት ነገር ከወዲሁ ይታይህና ለዚያ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ ትችላለህ። እንደነዚህ ያሉትን ሐሳቦች አድማጮችህ ከተለያየ አቅጣጫ ለማየት እንዲችሉ ነጥቦቹን ለመደጋገም ተዘጋጅ።

13 የምትናገረውን ሐሳብ አድማጮች እንዳልገባቸው እንዴት ለማወቅ ትችላለህ? አድማጮችህን ተመልከት። የፊታቸውን ስሜት አስተውል። አለዚያም የምትናገረው ለአንድ ወይም ለሁለት ሰው ከሆነ ጥያቄ ጠይቅ።

14 ሆኖም አንድ ነገር አስታውስ። እነዚያኑ ቃላት ደግሞ መናገሩ ሁልጊዜ የፈለግከውን ዓላማ ለማከናወን አያስችልህም። በደንብ ለማስተማር ከዚያ የበለጠ ነገር ማድረግ ያስፈልግሃል። አድማጮችህ በመጀመሪያው ገለጻ ነጥቡ ካልገባቸው እነዚያኑ ቃላት እንደገና መድገምህ በይበልጥ እንዲገባቸው ለማድረግ በቂ ላይሆን ይችላል። ታዲያ ምን ለማድረግ ትችላለህ? እንደ ሁኔታው ዘዴህን የምትለዋውጥ ሁን። በንግግርህ ላይ አዲስ ሐሳብ አፍልቀህ መጨመር ሊያስፈልግህ ይችላል። አድማጮችህ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ገምግመህ ያንን ችግር እንዴት እንደምትቋቋም መማርህ በአስተማሪነትህ ውጤታማ ያደርግሃል።

**********

15–18. አንድ ተናጋሪ ገላጭ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን እንዴት ለመማር ይችላል?

15 የሰውነት እንቅስቃሴዎች የምትናገረውን ቃል ያጠናክራሉ። እነዚያ ሐሳቦች በእንቅስቃሴዎቹ ይደረጃሉ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ኃይል ያገኛሉ። የሰውነት እንቅስቃሴዎች ሳይጨምር የሚናገር ሰው የለም ለማለት ይቻላል። ስለዚህ መድረክ ላይ ስትወጣ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ካላሳየህ አድማጮችህ እንዳልተዝናናህ ያውቃሉ። ነገር ግን በተፈጥሮ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን እያሳየህ ብትናገር አድማጮችህ ስለ አንተ ምንም አያስቡም። የሚያስቡት ስለምትናገረው ቃል ይሆናል። የሰውነት እንቅስቃሴዎች ያነቃቁሃል። ስሜትህን ስለሚቀሰቅሱት ንግግርህ ሕያው ይሆናል። የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ከመጽሐፍ መውሰድ የለብህም። ፈገግታን፣ ሳቅን ወይም ቁጣን ከሌላ ሰው አልተማርክም። ስለዚህ የሌላውን የሰውነት እንቅስቃሴ መቅዳት አስፈላጊ አይደለም። የሰውነት እንቅስቃሴ ምንም ሳትዘጋጅበት በተፈጥሮ ቢመጣ የተሻለ ነው። ፊት ላይ የምትገልጸው ስሜት ከሰውነት እንቅስቃሴህ ጋር ተዳምሮ የምትናገረውን ቃል ስሜት የሚሰጥ ያደርገዋል።

16 የሰውነት እንቅስቃሴዎች ከባሕርያቸው አንፃር በሁለት ይከፈላሉ። እነርሱም ገላጭና ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ናቸው።

17 ገላጭ የሰውነት እንቅስቃሴዎች። ገላጭ የሰውነት እንቅስቃሴዎች የድርጊትን አኳኋን፣ የአንድን ነገር መጠንና ቦታ ይገልጻሉ። ከሁለቱም ለመማር ቀላል የሆኑት እነዚሁ ገላጭ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ናቸው። ስለዚህ መድረክ ላይ ስትወጣ የሰውነት እንቅስቃሴ በማሳየት በኩል ችግር ካለብህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀላልና ገላጭ የሆኑትን የሰውነት እንቅስቃሴዎች ለማሳየት ሞክር።

18 በትምህርት ቤቱ ውስጥ ይህንን ባሕርይ ለማሻሻል በምትጥርበት ጊዜ አንድ ወይም ሁለት የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ብቻ በማሳየት አትርካ። ንግግሩ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ብዙ ቦታ ላይ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ለማሳየት ሞክር። ለዚህም ይረዳህ ዘንድ አቅጣጫን፣ ርቀትን፣ መጠንን፣ ስፋትን፣ ፍጥነትን፣ ቦታን፣ ልዩነትን፣ ማወዳደርን ወይም ማስተያየትን የሚያመለክቱ ቃላት ፈልግ። አስፈላጊ ከሆነ እነዚህን ቃላት በማስታወሻ ወረቀትህ ላይ በሆነ መንገድ ምልክት አድርግባቸው። እዚያ ነጥብ ላይ ስትደርስ ምልክቱ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለብህ ሊያስታውስህ ይችላል። በዚህ የንግግር ባሕርይ ገና በመጀመሪያው ላይ “ጥ” ብታገኝም መለማመድህን ቀጥልበት። ሦስትና አራት ንግግር ከሰጠህ በኋላ የሰውነት እንቅስቃሴዎች የምታደርግባቸው ቦታዎች ላይ ምልክት ማድረጉ ወይም ቀደም ብሎ አስቦ መምጣቱ የማያስፈልግ ሆኖ ታገኘዋለህ። በደመነፍስ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ትጀምራለህ።

19, 20. ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ለምን ዓላማ ያገለግላሉ?

19 ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች። ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ስለ አንድ ነገር ያለንን ስሜት ወይም ጠንካራ እምነት ያሳያሉ። የሐሳቦች ማሳረጊያ ሆነው ያገለግላሉ፣ ሁኔታዎችን ሕያው አድርገው ይገልጻሉ፣ ነጥቦችን ያጐለብታሉ። ይህም በመሆኑ ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ልማድ ወይም አመል የሚሆኑት እነዚሁ ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ናቸው። ይህ እንዳይሆን ተደጋጋሚ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ከማሳየት ተቆጠብ።

20 ችግርህ በልማድ አንድ ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ ማሳየት ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ገላጭ የሰውነት እንቅስቃሴን ብቻ አሳይ። ገላጭ የሰውነት እን ቅስቃሴን ጠንቅቀህ ካወቅክ በኋላ ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴን መልመዱ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ይሆናል። ልምድ ስታገኝና መድረክ ላይ በይበልጥ መዝናናት ስትጀምር ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎችህ በተፈጥሮ የሚሰማህን ስሜት፣ በአንድ ነገር ላይ ያለህን ጥብቅ እምነትና በቅን ልቦና የምትናገር መሆንህን የሚገልጹ ይሆናሉ። ለንግግርህ ትርጉም ይጨምሩለታል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]