መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተኮርበት ማድረግ
ጥናት 24
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተኮርበት ማድረግ
1, 2. ሰሚዎቻችንን መጽሐፍ ቅዱስ ወደሚለው መውሰድ ያለብን ለምንድን ነው?
1 ወደ አገልግሎት ስንሰማራ የእያንዳንዱን ሰው ትኩረት ወደ አምላክ ቃል ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዞር እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ እኛ የምንሰብከውን መልዕክት ይዟል። የምንናገረው ነገር ከራሳችን ያመነጨነው ሳይሆን ከአምላክ የመጣ መሆኑን ሰዎች እንዲያውቁ እንፈልጋለን። አምላክን
የሚያፈቅሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል መሆኑን ይተማመኑበታል። መጽሐፉ ሲነበብላቸው ያዳምጣሉ፤ ምክሩንም በልባቸው ውስጥ ያኖራሉ። ነገር ግን የራሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው ጥቅሱን ራሳቸው ሲያነቡት ነጥቡ በአእምሮአቸው ውስጥ በበለጠ ጥልቀት ይቀረጻል። ስለዚህ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ የቤቱ ባለቤት የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያመጣና ጥቅሶችን እያወጣ አብሮ እንዲከታተል ማበረታታቱ ጥበብ ነው። በተመሳሳይም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱሳቸው እንዲጠቀሙ ከተበረታቱ አዲስ ሰዎች የእምነታችን ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ወዲያው ለመገንዘብ ይችላሉ፤ እንዲሁም በማየት ጭምር አድማጮች ሐሳቡ በይበልጥ በአእምሮአቸው ውስጥ ይቀረጻል።2 ስለዚህ በሚቻልበት ቦታ ሁሉ አድማጮችህ የራሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው ጥቅሶችን ስታነብ ቢከታተሉህ የንግግርህን ዓላማ ለማሳካት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ምንም አያጠራጥርም። ይህን ማድረግ አለማድረጋቸው በአብዛኛው የተመካው ግን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው እንዲከታተሉህ ተገቢ ማበረታቻ በመስጠትህ ላይ ነው። በምክር መስጫ ቅጽህ ላይ “አድማጮች በመ/ቅ እንዲጠቀሙ ማበረታታት” ተብሎ የተጠቀሰው ይህ ነው።
3, 4. ይህንንስ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 በመጋበዝ። በጣም ግሩም ከሆኑት መንገዶች አንዱ አድማጮችህ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አውጥተው እንዲከታተሉ በቀጥታ መጠየቅ ነው። ይህ ዘዴ በተደጋጋሚ ይሠራበታል። አንዳንድ ጊዜም ከማንበብህ በፊት ጥቅሱን መናገርህ ብቻ ይህንን ውጤት ሊያመጣ ይችላል። ምናልባት እንደሚከተለው ለማለት ትችላለህ:- “አሁን 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5ን በምናነብበት ጊዜ ሩቅ ሳትሄዱ በዚህ አካባቢ ስላለው ሁኔታ አስቡ።” ከዚያም ራስህ ጥቅሱን እያወጣህ አድማጮች ግብዣውን ተቀብለውት እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት ግራና ቀኝ ለመመልከት ትችላለህ። አብዛኛውን ጊዜ እነርሱም ጥቅሱን ማውጣት ይጀምራሉ።
4 ተናጋሪው እንዲጐሉ የሚፈልጋቸውን ጥቅሶች በመምረጥ አድማጮች እነርሱን አውጥተው እንዲመለከቷቸው ለማድረግ ይችላል። ከዚያም አድማጮችህን ተመልከት። እየተከታተሉህ እንዳሉ የማወቅ ፍላጎት ይኑርህ። በሆነ ምክንያት በንባብ የሚቀርብ ንግግር በምትሰጥበትም ጊዜ ቁልፍ የሆኑ ጥቅሶችን አድማጮች እንዲከታተሉህ በሚያስችል መንገድ ልታነባቸው ትችላለህ።
5, 6. ልናነብ ያቀድነውን ጥቅስ አድማጮች እንዲያገኙት ጊዜ መስጠቱ ለምን ጠቃሚ እንደሆነ ግለጽ።
5 ጥቅሱን እንዲያወጡ ጊዜ በመስጠት። የአንድን ጥቅስ ምዕራፍና ቁጥር መናገሩ ብቻ አይበቃም። አድማጮች ጥቅሱን ለማውጣት ዕድል ሳያገኙ ብታነበውና ወደ ሌላው ብታልፍ ትንሽ ሲቆዩ ተስፋ ይቆርጡና ጥቅስ ማውጣቱን ጨርሶ ሊተዉት ይችላሉ። አድማጮችህን ተከታተል። አብዛኞቹ ጥቅሱን ካወጡ ልታነበው ትችላለህ።
6 ብዙውን ጊዜ ጥቅስ ለማንበብ ስታስብ ጥቂት ቀደም ብለህ ምዕራፍና
ቁጥሩን ተናግረህ ብትቆይ ይመረጣል፤ ምክንያቱም ቆም ማለትን በማብዛት ጠቃሚ ጊዜህን ከማባከንና አድማጮች ጥቅሱን እስኪያወጡ ድረስ ያለውን ክፍተት ‘ለመሙላት’ አላስፈላጊ ሐሳብ ከመጨመር ትድናለህ። ያም ሆኖ ግን እዚህም ላይ በተገቢ ቦታ ቆም ማለት ያስፈልጋል። በሌላው በኩል ግን ገና ጥቅሱን ማስተዋወቅ እንደጀመርክ ምዕራፍና ቁጥሩን ከተናገርክ ከዚያ በኋላ የምትናገራቸውን ነገሮች አድማጮች እንደ ሌላው ጊዜ ልብ ብለው እንደማይሰሙ ማወቅ አለብህ። ስለዚህ ለነጥብህ ድጋፍ የሚሰጡ ዐበይት ሐሳቦችን መናገር ያለብህ ምዕራፍና ቁጥሩን ከመንገርህ በፊት መሆን ይኖርበታል።**********
7–18. ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተዋወቅ በምን በምን ዘዴዎች መጠቀም ይቻላል?
7 በአንድ ንግግር ውስጥ የምንጠቀምባቸው ጥቅሶች ብዙውን ጊዜ የንግግሩ ትኩረት የሚያርፍባቸው ቦታዎች ናቸው። ነጥቦችን ለማስረዳት የሚቀርቡት ማብራሪያዎች በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ያተኩራሉ። እንግዲያው ጥቅሶቹ ለንግግሩ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የሚወስነው የአጠቃቀምህ ሁኔታ ነው። ስለሆነም “ጥቅሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ” የሚለው በንግግር ምክር መስጫ ቅጽህ ላይ የሰፈረው ነጥብ ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ነው።
8 አንድን ጥቅስ ማስተዋወቅ፣ ማንበብና ከነጥቡ ጋር ማያያዝ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ጥቅስ የምንሰጠው የማስተዋወቂያ ሐሳብ ጥቅሱን ወደማንበብ የሚመራ ከመሆኑም ሌላ ጥቅሱን ከነጥቡ ጋር ለማያያዝ ያገለግላል። ስለዚህ ጥቅሱ የሚነበበው ሐሳቡን ለማጠናከር ወይም ለማጥበቅ ብቻ ይሆናል። በሌላው በኩል ግን አንዳንድ ጥቅሶች በጣም ውጤታማ በሆነ መንገድ ያለ ምንም ማስተዋወቂያ ሊነበቡ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ያህል በንግግሩ መክፈቻ ላይ።
9 ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ማስተዋወቅ እንደምትችል ለመማር ብዙ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች የሚያደርጉትን አንድ በአንድ መርምር። ጥቅሶቹን የሚያስተዋውቁባቸውን የተለያዩ መንገዶች ለይተህ ለማወቅ ሞክር። ምን ያህል ውጤታማ እንደነበሩ ገምግም። የራስህን ንግግር በምትዘጋጅበት ጊዜ ጥቅሱ ምን ዓላማ እንዲያከናውን እንደታቀደ ቀደም ብለህ አስብበት። በተለይም ጥቅሱ ለአንድ ዋና ነጥብ ቁልፍ ከሆነ እንደዚያ አድርግ። ጥቅሱ ኃይል እንዲኖረው የጥቅሱን ማስተዋወቂያ በጥንቃቄ አስበህ አዘጋጅ። ለዚህ የሚረዱ ጥቂት ጥቆማዎች ቀጥሎ ቀርበዋል:-
10 ጥያቄ። ጥያቄ መልስ ይፈልጋል። ጥያቄ አእምሮን ያመራምራል። ጥቅሱና በጥቅሱ ላይ የምትሰጠው ማብራሪያ መልሱን እንዲሰጥ አድርግ። ለምሳሌ ያህል ለሕክምና ደም ስለመውሰድ እየተናገርህ ብትሆን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ደም የተከለከለ ነገር እንደነበረ ከገለጽክ በኋላ ሥራ 15:28, 29ን ታስተዋውቅ ይሆናል። እንዲህ ብለህ በመጠየቅ ጥቅሱን ልታስተዋውቅ ትችላለህ:- “ይሁን እንጂ ይህ እገዳ በክርስቲያኖችም ላይ ይሠራልን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካል በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት የሰጠውን ቀጥሎ ያለውን ውሳኔ ይመልከቱ።”
11 በምታስተዋውቀው ጥቅስ ደጋፊነት የሚረጋገጥ አንድ ዓይነት ሐሳብ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት መናገር። ለምሳሌ ያህል ስለ ዓመፀኝነት ንግግር እየሰጠህ ብትሆን በቀላሉ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:- “የጓደኛ ምርጫችን ትክክልና ስህተት ለሆኑት ነገሮች የሚኖረንን አመለካከት ጭምር ሊነካ ይችላል።” ከዚያም ይህንን አባባል ለመደገፍ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ ያሉትን የጳውሎስ ቃላት ለማንበብ ትችላለህ።
12 መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ መጥቀስ። በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ጥቅሶችን “በዚህ ነጥብ ላይ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል እስቲ ይመልከቱ” በማለት በአጭሩ ለማስተዋወቅ ትችላለህ። ይህም ጥቅሱ የሚለውን በጉጉት እንዲጠባበቁ ለማድረግ በቂ ይሆናል፤ ጥቅሱ የተጠቀሰበትንም ምክንያት ግልጽ ያደርገዋል።
13 አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ መጥቀስ። ስለ “ሲኦል” ንግግር የምትሰጥ ብትሆን እንዲህ ለማለት ትችላለህ:- “አንድ ሰው በዘላለማዊ የእሳት ነበልባል ይሠቃያል ከተባለ ሰውዬው ከሞተ በኋላ ይሰማል ማለት ነው። ይሁን እንጂ መክብብ 9:5, 10 ምን እንደሚል እስቲ ይመልከቱ።”
14 በርካታ ምርጫዎች ማቅረብ። ቀጥተኛ ጥያቄ ወይም አንድ አስቸጋሪ ሐሳብ ማቅረብ ለአድማጮችህ የሚከብዳቸው ከሆነ ሦስት አራት ዓይነት አማራጮችን በማቅረብ ጥቅሱና ስለ ጥቅሱ የምትሰጠው ማብራሪያ መልሱን እንዲሰጥ ለማድረግ ትችላለህ። ካቶሊኮችን ስታነጋግር ጸሎታችን ወደ ማን ቢቀርብ ተገቢ እንደሆነ ለማሳየት ማቴዎስ 6:9ን ለመጠቀም ትፈልግ ይሆናል። ቀጥተኛ ጥያቄ ወይም አንድ ዓይነት አስቸጋሪ ሐሳብ ብታቀርብለት የቤቱን ባለቤት አእምሮ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራው ይችላል። ስለዚህ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:- “ወደ ማን መጸለይ አለብን በሚለው ጥያቄ ላይ ብዙ የተለያዩ አስተያየቶች ይቀርባሉ። አንዳንዶች ጸሎታችን ለማርያም ሌሎች ደግሞ ‘ከቅዱሳን’ ለአንዱ መቅረብ አለበት ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጸሎታችን መቅረብ ያለበት ለአምላክ ብቻ ነው ይላሉ። ኢየሱስ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት።”
15 መሠረት መጣል። ለምሳሌ ያህል ስለ ቤዛው በሚያብራራ ንግግር ላይ ኢየሱስ የገዛ ራሱን ደም በማቅረብ ‘ስለ እኛ የዘላለም መዳንን እንዳስገኘ’ ለመግለጽ ዕብራውያን 9:12ን ብትጠቀም ጥቅሱን ከማንበብህ በፊት ኢየሱስ የገባበትን ስፍራ ያመለክታል ሲል ጳውሎስ የተናገረለት የማደሪያው ድንኳን ክፍል የሆነው “ቅድስት” ምን እንደሆነ አጠር ያለ ማብራሪያ መስጠት ሊያስፈልግህ ይችላል።
16 ከጥቅሱ ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች መጥቀስ። አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ጥቅስ በፊት ወይም በኋላ ያሉት ሐሳቦች ጥቅሱን ለማስተዋወቅ ይረዳሉ። ለምሳሌ ያህል ‘የቄሣርን ለቄሣር መክፈል’ እንደሚያስፈልግ ለማሳየት በሉቃስ 20:25 ብትጠቀም ከጥቅሱ በፊት ያለውን ሐሳብ በመውሰድ ኢየሱስ የቄሣር ጽሑፍ ባለበት ሳንቲም እንዴት እንደተጠቀመ ማብራራቱ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችል ይሆናል።
17 ቅልቅል። እነዚህን ዘዴዎች ቀላቅሎ መጠቀም ይቻላል፤ ብዙ ጊዜም ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።
18 አንድን ጥቅስ ለማስተዋወቅ የምትናገራቸው ቃላት አድማጮች ጥቅሱን እንዲጠብቁ አእምሮአቸውን ለማዘጋጀት በቂ መሆን አለባቸው። ይህ ከሆነ ጥቅሱ ሲነበብ የአድማጮችን ትኩረት ይስባል። ይህ ማስተዋወቂያ ጥቅሱን ልትጠቀምበት በፈለግከው ምክንያት ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል።
19, 20. አድማጮች ጥቅሱ የያዘውን ሐሳብ በጉጉት እንዲጠብቁ አእምሮአቸውን እንዳዘጋጀን እንዴት ለማወቅ እንችላለን?
19 የአድማጮችን አእምሮ ለጥቅሱ ማዘጋጀት። አድማጮችን ለጥቅሱ እንዳዘጋጀሃቸው እንዴት ለማወቅ ትችላለህ? አንደኛ አድማጮች በሚያሳዩት ስሜት ነው። ሁለተኛ ጥቅሱን እንዴት አድርገህ እንዳስተዋወቅህ በማየት ነው። ጥቅሱን ካስተዋወቅህ በኋላ ሳታነበው ብትቀር የአድማጮች ሐሳብ እንደተንጠለጠለ የሚቀር ቢሆን ወይም በጥቅሱ ማስተዋወቂያ ላይ የቀረበ ጥያቄ ገና መልስ ካላገኘ ጥቅሱን እንዲጠብቁ አእምሮአቸውን እንዳዘጋጀህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። እርግጥ ማስተዋወቂያው ከአርዕስቱም ሆነ ከጥቅሱ ሐሳብ ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት። የጥቅሱ መነበብ ወይም ከዚያ በኋላ የሚቀርበው ማብራሪያ የጥቅሱ ማስተዋወቂያ አንጠልጥሎ የተወውን ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል።
20 የጥቅሱን ማስተዋወቂያ ከአንድ የመንደር ልፈፋ በፊት ከሚሰማው የጥሩንባ ድምፅ ጋር ማመሳሰል ይቻላል። ለፋፊው የመጣው የተሟላ የሙዚቃ ቅንብር ለማሰማት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቀስቃሽ የሆነው የጥሩንባው ድምፅ የሰውን ትኩረት ወደ ማስታወቂያው ይስባል። የመረጥከውን ጥቅስ በዚህ መንገድ ማስተዋወቅህም አድማጮችህ በደስታ እንዲሰሙት ያደርጋል፤ ጥቅምም ያገኙበታል።
21. ጥቅሱን የጠቀስንበት ምክንያት እንዲተኰርበት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
21 ጥቅሱ በተጠቀሰበት ምክንያት ላይ ትኩረት ማድረግ። ምንም እንኳን የአንድ ጥቅስ ማስተዋወቂያ አንድን ጥያቄ አንጠልጥሎ ለመተው ቢችልም ጥቅሱ ለምን ተገቢ እንደሆነና ለምን ሙሉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ቢያንስ ጥቂት ምክንያት የሚያቀርብ መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል ምድር የሰው ዘላለማዊ መኖሪያ መሆንዋን በሚገልጽ ውይይት ላይ ራእይ 21:3, 4ን ለመጠቀም እየተዘጋጀህ ነው እንበል። ስለዚህ ጉዳይ ለማስረዳት በመጀመሪያ ላይ ከሰጠኸው ነጥብ ጋር በማያያዝ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:- “አሁን ቀጥለን በምናየው ጥቅስ ማለትም በራእይ 21:3, 4 ላይ ሥቃይና ሞት በማይኖርበት ዘመን ላይ የአምላክ ድንኳን የት ይሆናል ተብሎ እንደተነገረ እስቲ ልብ ይበሉ።” ጥቅሱ ምን ይል ይሆን የሚል ጉጉት ከመቀስቀስህም በላይ ለነጥብህ ድጋፍ የሚሰጠው የጥቅሱ ክፍል እንዲተኮርበት አድርገሃል። ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ ይህን የጥቅሱን ክፍል ከነጥብህ ጋር በቀላሉ ልታያይዘው ትችላለህ። በዚህ መንገድ አድማጮች ጥቅሱ በያዛቸው ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የአምላክ ቃል አስፈላጊነቱ ጎልቶ እንዲታይ ታደርጋለህ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]