በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምክር ይገነባል

ምክር ይገነባል

ጥናት 20

ምክር ይገነባል

1, 2. ምክር ለማግኘት የምንፈልገው ለምንድን ነው? ይህንንስ ምክር በምን መንገድ ልናገኘው እንችላለን?

1 እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሁሉ በአካሄዳቸው የእርሱን መመሪያ ለማግኘት ከመጣር ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም። ከመጽሐፍ ቅዱስ የመዝሙር ጸሐፊዎች አንዱ “በአንተ ምክር መራኸኝ” በማለት በልበ ሙሉነት ተናግሯል። (መዝ. 73:24) ኤርምያስም ልባዊ ጸሎቱን በሚቀጥሉት ቃላት አቅርቧል:- “ከአንተም የሚያቅት ነገር የለም። . . . ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነው። በምክር ታላቅ፤ በሥራም ብርቱ ነህ።” — ኤር. 32:17–19

2 ዛሬ ይሖዋ ለክርስቲያን አምላኪዎቹ ምክሩን የሚሰጣቸው በተጻፈው ቃሉና እውነተኛ አገልጋዮቹን ባሰባሰበው ድርጅቱ አማካኝነት ነው። ይህም በመሆኑ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚመዘገቡ ተማሪዎች ሁሉ የሚሰጣቸው ምክርና ምክሩ የሚሰጥበት መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመረኮዙ መሆናቸውን ለመገንዘብ ጊዜ አይፈጅባቸውም።

3–5. የንግግር ምክር መስጫው ቅጽና ከጥናት 21 እስከ 37 ድረስ ያሉት ሐሳቦች በቅንጅት እንድንጠቀምባቸው ታስበው የተዘጋጁ ስለመሆናቸው አብራራ።

3 ደረጃ በደረጃ የሚያሻሽል ምክር። ተማሪዎችንም ሆነ የትምህርት ቤቱን የበላይ ተመልካች ለመርዳት ታስቦ የንግግር ምክር መስጫ ቅጽ ተዘጋጅቷል። ቅጹ ተማሪዎቹ እውነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የሚያበቃቸውን ችሎታ እንዲያዳብሩ የሚረዷቸውን ሠላሳ ስድስት ነጥቦች ይዘረዝራል። በዚህ መጽሐፍ ላይ ከጥናት ቁጥር 21 ጀምሮ እስከ 37 ድረስ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ አጠር ያለ ጠቃሚ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን በንግግር ምክር መስጫ ቅጹ ላይ ከነጥቡ ጐን የጥናት ቁጥሩ ተጠቅሷል። እነዚህ ጥናቶች ከምክር መስጫው ቅጽ ጋር በማያያዝ እንድትጠቀምባቸው ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። በጣም የሚቀራረቡ ሁለት ወይም ሦስት የንግግር ባሕርያት አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ጥናት ሥር ተጠቃለዋል። ይህም የተደረገው እነዚህን ነጥቦች አንድ ላይ አቀናጅቶ መውሰዱ ጥሩ ይሆናል በሚል እምነት ነው።

4 የትምህርት ቤቱ አዲስ ተመዝጋቢዎች በንግግር ምክር መስጫ ቅጹ ላይ የሰፈሩትን ነጥቦች በአእምሮአቸው በመያዝ በደንብ መዘጋጀታቸው ጠቃሚ ነው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር ሲሰጡ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች (ወይም የተመዘገቡት ተማሪዎች ብዛት ያላቸው በመሆኑ ምክር እንዲሰጥ የተመደበ ሌላ ወንድም ካለ) ተማሪው በደንብ የሠራባቸውን ነጥቦች ብቻ እየጠቀሰ ያመሰግነዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ግን ምክር ሰጪው የተማሪውን የንግግር አሰጣጥ ለማሻሻል ትኩረት ሊደረግባቸው በሚያስፈልጉት ነጥቦች ላይ ደረጃ በደረጃ ምክር ይሰጠዋል። ይህንንም በተመለከተ ተማሪው በሚቀጥለው ንግግሩ ላይ የትኛውን ነጥብ ለማሻሻል ተዘጋጅቶ መምጣት እንዳለበት የበላይ ተመልካቹ ለይቶ ይገልጽለታል። ተማሪው በምክር መስጫው ቅጽ ላይ ከሰፈሩት ነጥቦች ወደ ሌላው ለማለፍ የሚችል መሆኑን ምክር ሰጪው ያሳውቀዋል።

5 አንዳንዶቹ ተማሪ ተናጋሪዎች ፈጣን እርምጃ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሌሎቹ ግን እንዲያውም በአንዱ ጥናት ውስጥ የተጠቃለሉትን ነጥቦች በሙሉ በአንድ ጊዜ ለመሸፈን ከመሞከር ይልቅ አንድ በአንድ ለማሻሻል መጣር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። አንዳንድ ተማሪዎችም ወደ ሌላው የንግግር ባሕርይ ከማለፋቸው በፊት አንዱን ባሕርይ ጠንቅቀው እስኪያውቁት ድረስ የተቸገሩበትን ነጥብ ሦስትና አራት ጊዜ ንግግር እንዲሰጡበት መምከሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል።

6, 7. የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በምን ነጥቦች ላይ ምክር ይሰጣል?

6 ከእያንዳንዱ የተማሪ ንግግር በኋላ የሚሰጠው ምክር ተማሪው የንግግር ችሎታውን እያሻሻለ እንዲሄድ ለመርዳት ታቅዶ በደግነት የቀረበ መሆን ይኖርበታል። የመምሪያ ንግግር ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች የሚያቀርበው ወንድም ምክር የሚያስፈልገው ከሆነ ይህ ምክር የሚሰጠው ትምህርት ቤቱ ካበቃ በኋላ በግል ነው። በተለይ ተናጋሪው ከተወሰነለት ጊዜ ካለፈ ምክር ሊሰጠው ይገባል። መምሪያ ንግግር የሚያቀርበው ተናጋሪ በሁሉም አቅጣጫ ናሙና የሚሆን ንግግር ለመስጠት መጣር ይኖርበታል። ይህንንም ካደረገ ምክር ላያስፈልገው ይችላል።

7 አብዛኛውን ጊዜ ምክር የሚሰጠው ተማሪው ቀደም ሲል እንዲያሻሽል በተመከረባቸው ነጥቦች ላይ ነው። እርግጥ ንግግሩ ጥሩ ሆኖ የቀረበበት ሌላ ሁኔታ ካለ ምክር ሰጪው በሚያቀርበው ምስጋና ውስጥ ይህንንም ሊጨምር ይችላል። ይሁን እንጂ ያንን ነጥብ በምክር መስጫው ቅጽ ላይ ምልክት አይሰጥበትም። የሚሠራባቸው ምልክቶች ቀጥሎ ያሉት ናቸው:- በአንዱ የንግግር ባሕርይ ላይ እንደገና መሥራቱ እንደሚጠቅም ከታመነበት “አ” (አሻሽል) የሚል ምልክት ይሰጣል። ተማሪው ከዚያ በፊት ቢያንስ አንድ ጊዜ ለማሻሻል የሞከረበት ነጥብ ቢኖርና አሁን ቢያሻሽለው፤ ነገር ግን አሁንም እንደገና ቢሠራበት ተማሪው የሚጠቀም ከሆነ “ተ” (ተሻሽሏል) የሚል ምልክት ይሰጠዋል። የተዘጋጀበትን የንግግር ባሕርይ ጥሩ አድርጎ በማሳየቱ በትምህርት ቤቱ ወደፊት ክፍል ለማቅረብ ሲዘጋጅ ሌላ የንግግር ባሕርይ ወደሚያብራራ ጥናት መሸጋገር ይችላል ተብሎ ከታመነ “ጥ” (ጥሩ) የሚል ምልክት ይሰጠዋል። የተማሪው ክፍል ንባብ ከሆነ ምክር ሰጪው ለዚህ ዓይነቱ ክፍል በጣም ተስማሚ በሆኑ ነጥቦች ላይ ምክር ይሰጣል።

8–10. የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ተማሪው ዕድገት ማድረጉን እንዲገፋበት ለማበረታታት በምክር መስጫው ቅጽ ላይ ምልክት ሲሰጥ በአእምሮው ምን ማስቀመጥ ይገባዋል?

8 የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በሚሰጠው ምክር አማካኝነት የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲችል በጣም አስተዋይ መሆን ይኖርበታል። ተማሪው በጣም አዲስ ከሆነ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገው ማበረታቻ ነው። በትምህርት ቤቱ ተመዝግበው ለረዥም ጊዜ ክፍል ሲሰጡ የቆዩ ሌሎች ተማሪዎችም እንዲያሻሽሏቸው ለተነገሯቸው የንግግር ባሕርያት ትኩረት በመስጠት ንግግራቸውን በትጋት ይዘጋጁበት ይሆናል። ሆኖም አቅማቸው ውስን ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባሉት ጊዜያት አንዱ የንግግር ባሕርይ የታየው ውስን በሆነ ደረጃ ቢሆንም የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በምክር መስጫው ቅጽ ላይ “ጥ” የሚል ምልክት በመስጠት ተማሪው ትኩረት ወደሚያስፈልገው ሌላ የንግግር ባሕርይ እንዲያልፍ ሊፈቅድለት ይችላል።

9 በሌላው በኩል ግን የበለጠ ልምድ ወይም የተፈጥሮ ችሎታ ያለው ሌላ ተናጋሪ ምናልባት በሥራ ጫና ምክንያት የተመደቡለትን የንግግር ባሕርያት በማጥናት በቂ ጊዜ አላጠፋ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ችሎታው የሚፈቅድለትን ያህል አልሠራ ይሆናል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በምክር መስጫው ቅጽ ላይ “ጥ” የሚል ምልክት ቢሰጠውና ወደ ሌላ ነጥብ ማለፍ እንደሚችል ቢነግረው እድገቱን መግታት ሊሆን ይችላል። ንግግሩ የተመደበውን የንግግር ባሕርይ ለማሳየት የሚያስችል ዓይነት ከነበረ ምክር ሰጪው “አ” (አሻሽል) የሚል ምልክት ይሰጠውና ተማሪውን እንዲያሻሽል ለመርዳት በግል ቀርቦ በደግነት አንዳንድ ሐሳቦችን ያካፍለዋል። ይህ ከተደረገ ተማሪዎቹ የተሰጣቸውን ክፍል በማቅረባቸው ብቻ ከመርካት ይልቅ ንግግር የሚሰጡበትን እያንዳንዱን አጋጣሚ የተሻሉ ተናጋሪዎች ለመሆን የሚረዳ መረማመጃ አድርገው እንዲመለከቱት ይበረታታሉ።

10 በዚህ የንግግር ማሠልጠኛ ችሎታን ማሻሻል የሚቻለው ደረጃ በደረጃ መሆኑን አስታውስ። በአንድ ጀንበር የተዋጣለት ተናጋሪ እሆናለሁ ብለህ አትጠብቅ። ወደዚህ ደረጃ መድረስ የሚቻለው ቀስ በቀስ ነው። ሆኖም ትጋት የታከለበት ጥረት ከተደረገ ሂደቱ ሊፋጠን ይችላል። በዚህ የንግግር ማሠልጠኛ ፕሮግራም ውስጥ የሚሰጡትን ማሻሻያ ሐሳቦች ካጤንካቸውና ክፍልህን ጥሩ አድርገህ ከተዘጋጀህበት መሻሻልህ ለተመልካቾች ሁሉ በግልጽ የሚታይ ይሆናል። — 1 ጢሞ. 4:15

11–16. ምክር ሰጪው በምክር አሰጣጡ ገንቢ መሆን እንዲችል የትኞቹን መመሪያዎች ለመከተል ይጥራል?

11 ምክር ሰጪው። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በየሳምንቱ እንዲወሰዱ የተመደቡትን ትምህርቶች በጥንቃቄ ማጥናት ይኖርበታል። ይህን ካደረገ የተመደበው ትምህርት በደንብ መሸፈኑን ለመከታተልና የተሳሳቱ ሐሳቦች ከቀረቡም ለማረም ይችላል። ይሁን እንጂ ንግግሮቹን በመስማት የሚገኘው ደስታ እስኪያመልጠው ድረስ የትምህርቱን አሰጣጥ ከመጠን በላይ በነቀፌታ ዓይን መከታተል የለበትም። እርሱም ጭምር ከሚቀርቡት ግሩም እውነቶች ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል።

12 ምክር ሲሰጥ አብዛኛውን ጊዜ ተማሪው ስላደረገው ጥረት በማመስገን ይጀምራል። ከዚያም ተናጋሪው ለማሻሻል በተዘጋጀባቸው በምክር መስጫው ቅጽ ባሉት ነጥቦች ላይ ሐሳብ ይሰጣል። አንዱ ነጥብ ቀጣይ ትኩረት የሚያስፈልገው ከሆነ ምክር ሰጪው ማጉላት ያለበት የተናጋሪውን ድክመት ሳይሆን እንዴት ማሻሻል እንደሚችል መሆን ይኖርበታል። ይህ ከሆነ ምክሩ ተናጋሪውንም ሆነ አድማጮችን የሚገነባ ይሆናል።

13 አንድን ተናጋሪ ጥሩ ሠርተህበታል ወይም በአንደኛው የንግግር ባሕርይ ላይ እንደገና መሥራት ያስፈልግሃል ብሎ ማለፉ በቂ አይሆንም። ምክር ሰጪው አቀራረቡ ለምን ጥሩ እንደነበረ ወይም ለምን መሻሻል እንደሚያስፈልገውና እንዴት መሻሻል እንደሚችል ሐሳብ ቢያክል በስብሰባው የተገኙትን ሁሉ ሊረዳ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ የንግግር ባሕርይ ለመስክ አገልግሎት ወይም ለጉባኤ ስብሰባዎች ለምን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ማጉላቱ ይጠቅማል። እንደዚህ ማድረጉ ጠቅላላው ጉባኤ ለዚያ ነጥብ ክብደት እንዲሰጥ ያደርጋል፤ ተማሪውም ለዚሁ ነጥብ ትኩረት መስጠቱን እንዲቀጥል ያበረታታዋል።

**********

14 ተማሪው የሰጠውን ንግግር እንደገና መከለሱ የምክር ሰጪው ሥራ አይደለም። ሐሳቡ አጠር ያለ፤ ምክሩም ነጥቡን ለይቶ የሚያስጨብጥ መሆን ይኖርበታል። በእያንዳንዱ የተማሪ ንግግር ላይ ከሁለት ደቂቃ የበለጠ ጊዜ እንዳያጠፋ መጠንቀቅ ይኖርበታል። ይህን ጥንቃቄ ካደረገ እርሱ የሚሰጠው ምክርና ተጨማሪ ሐሳብ በቃላት ብዛት አይድበሰበስም። በተጨማሪም ሐሳብ ስለተሰጠበት ጉዳይ ተማሪው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የትኞቹን ገጾች መመልከት እንደሚችል ሊጠቀስለት ይገባል።

15 በአነጋገር ጥራትና በሰዋስው በኩል የሚታዩት ትንንሽ ስህተቶችን እንደ ትልቅ ችግር ቆጥሮ መከታተል አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ ምክር ሰጪውን ሊያሳስበው የሚገባው ተናጋሪው ያቀረበው ትምህርት በአድማጮች ላይ ያሳደረው አጠቃላይ ውጤት መሆን ይኖርበታል። የቀረበው ትምህርት ጊዜ ሊጠፋለት የሚገባና አዲስ ነገር የሚያሳውቅ ነውን? በደንብ የተቀነባበረና ለመከታተል ቀላል የሆነ ነውን? አቀራረቡ ቅንነትንና ልባዊነትን የሚያንጸባርቅና አሳማኝ ነውን? ፊቱ ላይ የሚነበበው ስሜትና የሰውነት እንቅስቃሴዎቹ የሚናገረውን እንደሚያምንበት፤ በይበልጥ የሚያሳስበው ነገርም ሰዎች ለንግግሩ የሚሰጡት ግምት ሳይሆን ግሩም የሆኑትን እውነቶች ለአድማጮች ማስተላለፍ እንደሆነ ያሳያሉን? እነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች በደንብ ከተሟሉ አድማጮች ጥቂት የፊደላት ግድፈቶችንና የሰዋስው ስህተቶችን ልብ አይሏቸውም።

16 በአገልግሎት ትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ምክር ምን ጊዜም በደግነትና ተማሪውን በመርዳት መንፈስ መቅረብ ይኖርበታል። ተማሪውን ለመርዳት ቅን ፍላጎት መኖር አለበት። ምክር የሚሰጠው ተማሪ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ግምት ውስጥ አስገባ። ቶሎ የሚነካ ሰው ነውን? የትምህርት ደረጃው ዝቅተኛ ነውን? ድክመቶቹን ለማለፍ የሚያበቁ ምክንያቶች ይኖራሉን? ምክሩ ተመካሪውን እንደተረዳ እንጂ እንደተተቸ እንዲሰማው ሊያደርግ አይገባም። ምክሩም ሆነ የምክሩ ምክንያታዊነት እንዲገባው አድርግ።

17–19. አንድ ተማሪ ንግግር ባቀረበ ቁጥር የሚቻለውን ያህል ጥሩ መሻሻል ለማድረግ እያንዳንዱን ንግግር ከመዘጋጀቱ በፊትና ንግግሩን አቅርቦ ከጨረሰ በኋላ ምን ማድረግ አለበት?

17 ከምክር ጥቅም ማግኘት። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ንግግር እንድታቀርብ ክፍል ሲሰጥህ ንግግሩን የምትሰጥበት ምክንያት ለጉባኤው የሚገነባ ትምህርት ለማቅረብ ብቻ ሳይሆን የንግግር ችሎታህን ለማሻሻል ጭምር እንደሆነ ምን ጊዜም አስታውስ። በዚህ ረገድ የተሳካ ውጤት ለማግኘት እንድትዘጋጅባቸው የተነገሩህን ነጥቦች በሚገባ ለመመርመር በቂ ጊዜ ማጥፋት ይኖርብሃል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለውን ለማሻሻል ስለምትጥረው ነጥብ የሚገልጸውን ጥናት በጥንቃቄ አንብብ። ይህን ካደረግህ እንዴት አድርገህ መዘጋጀት እንዳለብህና ንግግሩን በምታቀርብበት ጊዜ ይህንን የንግግር ባሕርይ እንዴት ማሳየት እንደምትችል ለማወቅ ትችላለህ። አንተን ለመርዳት ሲባል የእያንዳንዱ የንግግር ባሕርይ ዋና ዋና ዘርፎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጎላ ባሉ ፊደላት ቀርበዋል። ልታተኩርባቸው የሚገቡ ዋና ነገሮችም እነዚሁ ናቸው።

18 ንግግርህን ሰጥተህ ከጨረስክ በኋላ በቃል የሚቀርብልህን ምክር በጥንቃቄ አዳምጥ። ምክሩን በደስታ ተቀበል። ከዚያም ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች ለማሻሻል ጣር። መሻሻልህን ለማፋጠን ከፈለግህ ሌላ ንግግር እስኪሰጥህ ድረስ አትጠብቅ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አንተ ልታሻሽላቸው ስለሚያስፈልጉህ ነጥቦች የሚያብራራውን ክፍል አጥናው። የሚቀርቡልህንም ሐሳቦች በየዕለቱ ከሰዎች ጋር በምታደርገው ንግግር ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር። በዚህ መንገድ ከጣርክ የሚቀጥለው የተማሪ ንግግርህ ከመድረሱ በፊት ያንን ነጥብ በደንብ አሻሽለህ ልትጠብቅ ትችላለህ።

19 እያንዳንዱ ተማሪ በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ውስጥ ንግግር በሚሰጥበት በእያንዳንዱ አጋጣሚ ንግግሩን የማሻሻል ግብ እንዲኖረው ያስፈልጋል። እርግጥ ይህ ማለት የማያቋርጥ ጥረት መደረግ አለበት ማለት ነው፤ ይሁን እንጂ የይሖዋን በረከት ያስገኛል። ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ማሠልጠኛ ትልቅ ጥቅም ለሚያገኙት ተማሪዎች በምሳሌ 19:20 ላይ “ምክርን ስማ፣ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ” የሚሉት ቃላት ልዩ ትርጉም አላቸው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 104, 105 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የንግግር ምክር መስጫ

ተናጋሪ..........................................

(ሙሉ ስም)

ምልክቶች:- አ - አሻሽል

ተ - ተሻሽሏል

ጥ - ጥሩ

ቀን የንግግር ቁጥር

አዲስ ነገር የሚያሳውቅ (21)

ግልጽ፣ የሚጨበጥ (21)

ስሜት የሚቀሰቅስ መግቢያ (22)

ለአርዕስቱ የሚስማማ መግቢያ (22)

ልከኛ መግቢያ (22)

የድምፅ መጠን (23)

ቆም እያሉ መናገር (23)

አድማጮች በመ/ቅ እንዲጠቀሙ ማበረታታት (24)

ጥቅሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ (24)

ጥቅስ ሲነበብ ተፈላጊዎቹን ቃላት ማጉላት (25)

ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ (25)

ለማጉላት ሲባል መደጋገም (26)

የሰውነት እንቅስቃሴዎች (26)

አርዕስቱን ማጉላት (27)

ዋና ዋና ነጥቦችን መለያየት (27)

ከአድማጭ ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ የማስታወሻ አጠቃቀም (28)

ከአስተዋጽኦ መናገር (28)

ተጨማሪ ሐሳቦች:– ․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․

በቅንፍ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ቁጥር ለተጠቀሰው የንግግር ባሕርይ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ማብራሪያ የሚገኝበትን የጥናት ቁጥር ያመለክታል።

S-48-AM Printed in Italy የታተመው በኢጣልያ ነው።

ቀን የንግግር ቁጥር

ቅልጥፍና (29)

የውይይት መልክ (29)

ጥራት (29)

በማያያዣዎች ማገጣጠም (30)

የተቀነባበረ፣ አንድ ወጥ የሆነ (30)

አሳማኝ ነጥቦች (31)

ነጥቦቹን እንዲያገናዝቡ መርዳት (31)

ማጥበቅ (32)

ድምፅን መለዋወጥ (32)

ግለት (33)

ፍቅራዊ ስሜት (33)

ለትምህርቱ የሚስማሙ ምሳሌዎች (34)

ለአድማጮች የሚስማሙ ምሳሌዎች (34)

ለመስክ አገልግሎት የሚስማማ አቀራረብ (35)

ግቡን የሚመታ ትክክለኛ መደምደሚያ (36)

ልከኛ መደምደሚያ (36)

የጊዜ አመዳደብ (36)

ተማምኖና ተረጋግቶ መናገር (37)

ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ (37)

ማሳሰቢያ:– ተማሪው ንግግር ባቀረበ ቁጥር ምክር ሰጭው በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ምክር ይሰጠዋል። ለዚህም ከላይ ያለውን ቅደም ተከተል የግድ መከተል አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ተማሪው እንዲያሻሽላቸው በሚያስፈልጉት ነጥቦች ላይ ያተኩራል። በቅጹ ላይ ያሉት ክፍት ቦታዎች በዝርዝሩ ውስጥ ባልገቡ ነጥቦች ላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ምክር ለመስጠት ያገለግላሉ። ለምሳሌ:- ትክክለኛ ነገር መናገር፣ የሐሳቦች ቅንብር፣ አቋቋም፣ የቃላት ምርጫ፣ ሰዋስው፣ ለተመልካች ደስ የማይሉ ልማዶች፣ የማያስፈልጉ ነጥቦችን ማበጠር፣ የማስተማር ዘዴዎችና የድምፅ ዓይነት። ተማሪው ምክር የሚሰጥበትን አንዱን ነጥብ ሲጨርስ በሚቀጥለው ጊዜ በየትኛው ላይ ተዘጋጅቶ መምጣት እንዳለበት ለማሳየት ምክር ሰጪው በሚቀጥለው ነጥብ ትይዩ ያለውን “አ” “ተ” ወይም “ጥ” የሚል ምልክት የሚያስቀምጥበትን ሣጥን ዙሪያውን በቀለም ያደምቃል። የዚህ ነጥብ የጥናት ቁጥር ለተማሪው በሚሰጠው የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል መስጫ ቅጽ (S-89-AM) ላይ መጠቀስ አለበት።

[በገጽ 106, 107 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የንግግር ባሕርያት ማጠቃለያ

አዲስ ነገር የሚያሳውቅ (21)

ቁልጭ ያሉ ነጥቦች

ለአድማጮችህ አዲስ ሐሳብ የሚሰጥ

ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው ትምህርት

ትክክለኛ ነገር መናገር

ተጨማሪ ማብራሪያዎች

ግልጽ፣ የሚጨበጥ (21)

በቀላል አገላለጽ የቀረበ

ያልተለመዱ ቃላትን መግለጽ

ሐሳብ አለማብዛት

ስሜት የሚቀሰቅስ መግቢያ (22)

ለአርዕስቱ የሚስማማ መግቢያ (22)

ልከኛ መግቢያ (22)

የድምፅ መጠን (23)

ያለ ችግር እንዲሰሙን በቂ ድምፅ ማሰማት

ሁኔታዎችን ለመቋቋም የምናሰማው የድምፅ መጠን

ለትምህርቱ የሚስማማ የድምፅ መጠን

ቆም እያሉ መናገር (23)

ሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም ማለት

የሐሳብ ለውጥ ለማድረግ ቆም ማለት

ለማጉላት ቆም ማለት

በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቆም ማለት

አድማጮች በመ/ቅ እንዲጠቀሙ ማበረታታት (24)

በመጋበዝ

ጥቅሱን እንዲያወጡ ጊዜ በመስጠት

ጥቅሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ (24)

የአድማጮችን አእምሮ ለጥቅሱ ማዘጋጀት

ጥቅሱ በተጠቀሰበት ምክንያት ላይ ትኩረት ማድረግ

ጥቅስ ሲነበብ ተፈላጊዎቹን ቃላት ማጉላት (25)

ትክክለኛ ቃላትን ማጉላት

ውጤታማ በሆነ የማጉላት ዘዴ መጠቀም

ባለቤቱ የሚያነባቸው ጥቅሶች

ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ (25)

ለማያያዝ የምትጠቀምባቸውን ቃላት ለየት ማድረግ

የጥቅሱን ማስተዋወቂያ ከጥቅሱ ጋር ማገናዘብ

ለማጉላት ሲባል መደጋገም (26)

ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች መድገም

አድማጮች ያልገቧቸውን ነጥቦች መደጋገም

የሰውነት እንቅስቃሴዎች (26)

ገላጭ የሰውነት እንቅስቃሴዎች

ማጠናከሪያ የሰውነት እንቅስቃሴዎች

አርዕስቱን ማጉላት (27)

ተስማሚ የንግግር መልዕክት

የአርዕስቱን ቃላት ወይም ሐሳብ መደጋገም

ዋና ዋና ነጥቦችን መለያየት (27)

ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች አይብዙ

ዋና ዋና ሐሳቦችን ለየብቻ ማስፋፋት

ንዑስ ነጥቦች በዋናዎቹ ሐሳቦች ላይ ያተኩራሉ

ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ የማስታወሻ አጠቃቀም (28)

ከአድማጮች ጋር የእይታ ግንኙነት ማድረግ

በቀጥታ ለአድማጮች በመናገር ግንኙነት ማድረግ

ከአስተዋጽኦ መናገር (28)

ቅልጥፍና (29)

የውይይት መልክ (29)

በመወያያ ቃላት መጠቀም

የውይይት መልክ ያለው አቀራረብ

ጥራት (29)

በማያያዣዎች መገጣጠም (30)

በመሸጋገሪያ ቃላት መጠቀም

የንግግሩ ወጥነት ለአድማጮችህ አቅም በቂ መሆን አለበት

የተቀነባበረ፣ አንድ ወጥ የሆነ (30)

ምክንያታዊ የነጥቦች ቅደም ተከተል

አግባብነት ያላቸውን ነጥቦች ብቻ መጠቀም

ቁልፍ ሐሳቦችን አለማስቀረት

አሳማኝ ነጥቦች (31)

መሠረት መጣል

ጠንካራ ማስረጃ ማቅረብ

ውጤታማ ማጠቃለያ

ነጥቦቹን እንዲያገናዝቡ መርዳት (31)

የጋራ አቋምን አለመልቀቅ

ነጥቦቹን በበቂ መጠን ማብራራት

ለአድማጮች ነጥቡን ከጉዳዩ ጋር አያይዝላቸው

ማጥበቅ (32)

ሐሳቡን የሚያስተላልፉትን የዓረፍተ ነገሩን ቃላት ማጥበቅ

የንግግሩን ዋና ዋና ሐሳቦች ማጥበቅ

ድምፅን መለዋወጥ (32)

የድምፅን ኃይል መለዋወጥ

ፍጥነት መለዋወጥ

ቃናን መለዋወጥ

ለሐሳቡ ወይም ለስሜቱ የሚስማማ ድምፅ

ግለት (33)

ሞቅ ባለ ስሜት በመናገር ግለትን ማሳየት

ለትምህርቱ የሚስማማ ግለት

ፍቅራዊ ስሜት (33)

ፍቅራዊ ስሜት ፊት ላይ ይነበባል

ፍቅራዊ ስሜትን በድምፅ ቃና ማሳየት

ለትምህርቱ የሚስማማ ፍቅራዊ ስሜት

ለትምህርቱ የሚስማሙ ምሳሌዎች (34)

ቀላል ምሳሌዎች

የምሳሌውን ቁም ነገር ግልጽ ማድረግ

ትልልቅ ነጥቦችን ማጉላት

ለአድማጮች የሚስማሙ ምሳሌዎች (34)

ከተለመዱ ሁኔታዎች የተወሰዱ

ለዛ ያለው

ለመስክ አገልግሎት የሚስማማ አቀራረብ (35)

የአንዳንድ ቃላትን ፍቺ ግልጽ ማድረግ

ተስማሚ ነጥቦችን መምረጥ

የትምህርቱን ተግባራዊ ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ ማሳየት

ግቡን የሚመታ ትክክለኛ መደምደሚያ (36)

ከንግግሩ መልዕክት ጋር በቀጥታ የተያያዘ መደምደሚያ

መደምደሚያው አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያሳያል

ልከኛ መደምደሚያ (36)

የጊዜ አመዳደብ (36)

ተማምኖና ተረጋግቶ መናገር (37)

በአካላዊ ሁኔታ መረጋጋትን ማሳየት

ድምፅን በመቆጣጠር መረጋጋትን ማሳየት

ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ (37)

ተገቢ ልብስና የጸጉር አያያዝ

ትክክለኛ አቋቋም

ንጹሕ የአገልግሎት መሣሪያዎች

ፊት ላይ ተገቢ ያልሆነ ስሜት አለማሳየት