በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግርና ድንገተኛ የሆነ ንግግር
ጥናት 12
በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግርና ድንገተኛ የሆነ ንግግር
1, 2. ይሖዋ እንድንናገር የሚረዳን እንዴት ነው?
1 “የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፣ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።” (ማቴ. 10:19, 20) እነዚህ ቃላት የጥንቶቹን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአስደናቂ ሁኔታ ሳያደፋፍሩ አይቀሩም። ዛሬም ቢሆን ምሥራቹን የሚሰብኩ የአምላክ አገልጋዮች በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ፊት ቀርበው ምሥክርነት እንዲሰጡ በሚጠየቁባቸው ጊዜያት ድፍረት ይሰጡአቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ለአንዳንዶቹ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ምሥክሮች ይሰጥ የነበረውን የመሰለ “የእውቀት” ወይም “የጥበብ” ንግግር በተአምር ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም። (1 ቆሮ. 12:8) ቢሆንም በጣም ግሩም የሆነ ቲኦክራሲያዊ ትምህርትና ሥልጠና የምናገኝበት አጋጣሚ አለን። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም አምላክ ቃል እንደገባልን መንፈሱ መልሶችን እንድናስታውስ ያደርገናል።
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፣ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች በምታገኘው ሥልጠና አማካኝነት በዛ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ለማከማቸት ትችላለህ። መሠረታዊ የሆኑ የጽድቅ ሥርዓቶችንና እነዚህንም ሥርዓቶች በራስህ ሕይወትና በተለያዩ ሁኔታዎች እንዴት ሥራ ላይ ለማዋል እንደምትችል ትማራለህ። በመስክ አገልግሎት በመሳተፍም የተማርከውን ለሌሎች ሰዎች በማካፈልና ሌሎችን በማነጋገር ረገድ ተሞክሮ ታገኛለህ። ይህን የመሰለውን ንግግር የምትሰጠው አስተዋጽኦ ይዘህ በራስህ አገላለጽ ወይም ያለ አስተዋጽኦ ድንገተኛ የሆነ ንግግር በመስጠት ነው።
3. በራስ አገላለጽ በሚቀርብ ንግግር እና ሳይታሰብ በድንገት በሚሰጥ ንግግር መካከል ያለውን ልዩነት አስረዳ።
3 እነዚህ ሁለት የንግግር ዓይነቶች የቅርብ ዝምድና ያላቸው ቢሆኑም አንድ ዓይነት አይደሉም። የሁለቱን የንግግር ዓይነቶች ልዩነት በምሳሌ ለማስረዳት ይቻላል። አንድ ሰው እቤቱ ሄደህ እያነጋገርከው ነው እንበል። የምትናገርበት ሁሉ ቀደም ብለህ የተዘጋጀህበት ስለሆነ የንግግርህ ቅደም ተከተልና አስተዋጽኦ በአእምሮህ ውስጥ በሚገባ ተቀርጾአል። ከዚህ አስተዋጽኦ በስተቀር ትምህርቱን የምታብራራባቸውን ቃላት በቃል አላጠናህም። እንደዚህ ባለው ሁኔታ የምትሰጠው ንግግር በራስ አገላለጽ የሚሰጥ ንግግር ነው። በዚሁ ጊዜ ሰውዬው ቀደም ሲል ያላሰብህበትና ያልተዘጋጀህበት ጥያቄ ይጠይቅሃል። ይሁን እንጂ በመንግሥት አዳራሹ በቂ ሥልጠና ያገኘህ ስለሆንህ ቀደም ብለህ ካከማቸኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት መልስና ማብራሪያ ለመስጠት ትችላለህ። በዚህ ጊዜ ንግግርህ በዚያ ቅጽበት ተቀናብሮ የተነገረ ስለሆነ ድንገተኛ ንግግር ይሆናል።
4. በራስ አገላለጽ ጥሩ ንግግር ለመስጠት ምን ዓይነት ዝግጅት ያስፈልጋል?
4 በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር። ንግግሩ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት የሚቀርብ ንግግርም ሆነ ከመድረክ የሚሰጥ በራስ አገላለጽ ንግግር ለማቅረብ ቁልፉ መዘጋጀት ነው። በራስህ አገላለጽ ንግግር የምትሰጥ ከሆነ በርካታ የሚብራሩ ዋና ዋና ነጥቦች ያሉት ጥሩ አስተዋጽኦ አዘጋጅ። በእያንዳንዱ ዋና ነጥብ ግርጌ ድጋፍ ሰጪ ሐሳቦችን፣ ማስረጃዎችን፣ ጥቅሶችንና ምሳሌዎችን ልታሰፍር ትችላለህ። ይህም ዕውቀት ሰጪ የሆነ ንግግር ለመስጠት ያስችልሃል። ከምትናገረው ቃላት በስተቀር ሌላውን ነገር ሁሉ በቅድሚያ አዘጋጅ።
5–7. በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር ያሉትን ጥቅሞች ዘርዝር።
5 በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር ብዙ ጥቅሞች አሉት። አንደኛው ጥቅም የአቀራረብ ለውጥ ለማድረግ ማስቻሉ ነው። ከተዘጋጀ ጽሑፍ እንደሚነበብ ወይም በቃል ተሸምድዶ እንደሚሰጥ ንግግር እንደሁኔታው ሊለወጥ የማይችል አይደለም። ንግግሩ ሊሰጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ ሲቀረው
በንግግሩ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ የሚያስገድድ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። መድረኩ ላይ ልትወጣ ስትል አብዛኞቹ አድማጮች አዲስ የመጡ እንግዶች እንደሆኑ ትገነዘብ ይሆናል። ንግግርህ በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር ከሆነ ማብራሪያዎቹንና መረጃዎቹን እንዲረዱ የሚያስችል ለውጥ ለማድረግ ትችላለህ። ወይም ከአድማጮቹ ብዙዎቹ በትምህርት ቤት የሚገኙ ወጣቶች እንደሆኑ ልትገነዘብ ትችል ይሆናል። ትምህርቱ ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚነካ እንዲያስተውሉ ለመርዳት የምትሰጠውን ምሳሌዎችና የትምህርቱን ተግባራዊ ጥቅም ለእነርሱ በሚጠቅም መንገድ ለማስተካከል ትችላለህ።6 በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር ያለው ሁለተኛ ጥቅም ደግሞ አእምሮህን ለማሠራት መቻሉ ነው። አዳዲስ ሐሳቦችን ለማመንጨት የሚያስችል ነፃነት ይሰጥሃል። በአድናቆትና በጥሞና የሚያዳምጡ አድማጮች ሲያጋጥሙህ ሞቅ ስለሚልህ አዳዲስ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ ይጎርፋሉ። እነዚህንም ሐሳቦች በራስ አገላለጽ በሚቀርበው ንግግርህ ውስጥ ለማስገባት ትችላለህ።
7 ይህ ዓይነቱ ንግግር የሚሰጠው ሦስተኛ ጥቅም ደግሞ ዓይንህ በአድማጮችህ ላይ እንዲያተኩር ማስቻሉ ነው። ይህም ከእነርሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ያሻሽልልሃል። ይህ ደግሞ የምትናገረውን በጥሞና እንዲያዳምጡ ያደርጋቸዋል። አንድን ጽሑፍ ሁልጊዜ አቀርቅረህ ስለማትመለከት አድማጮችህ የምትናገርበትን ርዕሰ ጉዳይ አሳምረህ እንደምታውቅ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም የአድማጮችን ስሜት ለመከታተል ያስችልሃል። የአድማጮች ፍላጎት እየተዳከመ እንዳለ ከተመለከትህ ይህን ችግር ለማስወገድ የሚያስችልህን እርምጃ ትወስዳለህ። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ የንግግር አቀራረብ ሞቅ ያለ፣ የውይይት መልክ ያለውና ልብ ለልብ የሚያገናኝ ንግግር ለማቅረብ ያስችላል።
8–10. በራስ አገላለጽ በሚቀርብ ንግግር ረገድ የሚፈጠሩትን አደጋዎች እንዴት ማስቀረት ይቻላል?
8 ነገር ግን በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር አንዳንድ አደጋዎች አሉት። ይሁን እንጂ እነዚህን አደጋዎች ማስወገድ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ተናጋሪው ከመጠን በላይ ብዙ ተጨማሪ ሐሳቦችን ያስገባና ንግግሩ ከተወሰነለት ጊዜ ሊያልፍ ይችላል። በተጨማሪም በቅጽበት የሚከሰቱለትን ነጥቦች የመጨመር ነፃነት ስለሚኖረው በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ካቀደው የሚበልጥ ብዙ ጊዜ ሊያሳልፍ ይችላል። ለእያንዳንዱ የንግግሩ ክፍል የተፈቀደው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ በአስተዋጽኦህ ላይ ምልክት በማድረግ እንዲህ ያለውን ችግር ለማስወገድ ትችላለህ። ይህንንም የወሰንከውን የጊዜ ክፍፍል ጠብቅ።
9 በተጨማሪም አንዳንድ ነጥቦችን የመዝለል፣ ወይም ትክክል ያልሆኑ ወይም ያልተሟሉ ሐሳቦችን የማቅረብ ወይም በቂ መረጃ ወይም ድጋፍ ያልቀረበባቸው ሐሳቦችን የመስጠት አደጋ ያጋጥማል። ሳትጣደፍ በየጊዜው ማስታወሻህን መለስ እያልክ ብትመለከት ከትምህርትህ ላለመውጣት
ስለምትችል አንዳንድ ነጥቦችን ከመዝለልና ትክክል ያልሆኑ ሐሳቦችን ከመስጠት ትድናለህ። ድጋፍ በሚሰጡ ማስረጃዎችና ጥቅሶች መብራራት የሚኖርባቸው የተለያዩ ዋና ነጥቦች ያሉበት ጥሩ አስተዋጽኦ በማዘጋጀት በቂ ማስረጃ ያልቀረበበት መግለጫ ከመስጠት ልትድን ትችላለህ።10 በራስ አገላለጽ በሚቀርብ ንግግር ላይ የምትናገረውን እያንዳንዱን ቃል መሸምደድ ባይኖርብህም አንዳንድ አነጋገሮችን በቅድሚያ መለማመድ ትችላለህ። የሐሳቦቹን ቅደም ተከተልና አካሄድ በአእምሮ ውስጥ በሚገባ መያዝም ጠቃሚ ነው። ይህን በማድረግ ተራ የሆኑ አነጋገሮችንና ቃላትን ለማስወገድ ትችላለህ። በየዕለቱ ከሰዎች ጋር ጥሩ አነጋገር ለመጠቀም የምትሞክር ከሆንክ ደግሞ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ቀላል ይሆንልሃል። እርግጥ፣ ይህም ቢሆን ከጽሑፍ በንባብ የሚሰጠውን የመሰለ ምርጥ አነጋገርና የተስተካከለ ሰዋስዋዊ አገባብ ላይኖርህ ይችላል። ቢሆንም ይህን ጉድለት ንግግርህን በውይይት መልክ በማቅረብ ልታካክስ ትችላለህ። በተጨማሪም ንግግር ከመስጠትህ በፊት ደጋግመህ ከልሰው። አንዳንዶች ጸጥ ብለው በአእምሮአቸው ብቻ መከለስ በቂ ሆኖ ያገኙታል። አንዳንዶች ግን ጮክ ብሎ መለማመድ በተለይ በጊዜ አጠባበቅ ረገድ በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።
11, 12. አንድ ተናጋሪ አስተዋጽኦ መያዙ ከአደጋ የሚጠብቀው ለምንድን ነው?
11 በቂ ጊዜና ልምምድ ካገኘህ በኋላ እያንዳንዱን ዋና ነጥብ አሳጥረህ በጥቂት ቃላት ብቻ በመግለጽ አስተዋጽኦህን ለማሳጠር መቻል ይኖርብሃል። እነዚህ ዋና ዋና ነጥቦችና የምትጠቀምባቸው ጥቅሶች በቀላሉ ሊታዩ በሚችሉ ካርዶች ወይም ወረቀቶች ላይ ሊሰፍሩ ይችላሉ። በአገልግሎት ትምህርት ቤት እንደሚሰጡት የተማሪ ንግግሮች ያሉትን አጠር ያሉ ንግግሮች በቃል ለመያዝ የሚመርጡ ቢኖሩም ሐሳብህን የሚከፍል ወይም የሚያስረሳ ሁኔታ ቢያጋጥም ለማየት የምትችልበት አስተዋጽኦ መያዝ ምንም ክፋት የለውም። እንደ ሕዝብ ንግግር ያሉትን ረዘም ያሉ ንግግሮች በምታቀርብበት ጊዜ ለማየት እንድትችል ዘርዘር ብሎ የተዘጋጀው አስተዋጽኦ አጠገብህ እንዲኖር ማድረግ ጥበብ ነው።
12 በራስ አገላለጽ የሚቀርበው ንግግር ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በጣም ጠቃሚ ነው። የቤቱ ባለቤት ጥያቄ ሲያነሣ ወይም በአንድ መንገድ ንግግሩን ሲያቋርጥ ለአጭር ጊዜ ከርዕሰ ጉዳዩ ወጣ ብሎ ለጥያቄው መልስ ለመስጠትና እንደገና ዝግጅት ወደተደረገበት ርዕሰ ጉዳይ ለመመለስ ያስችላል። እያንዳንዱ የምትናገረው ቃል በቃል የተሸመደደ ቢሆን እንደዚህ ከመሰለው የንግግር መቋረጥ በኋላ ወደ ዋናው ንግግር ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆናል።
13–15. ያልታሰበ ድንገተኛ ንግግር የምንሰጠው እንዴት ባሉ አጋጣሚዎች ነው? እዚህም ላይ ቢሆን የዝግጅት ጉዳይ የሚገባው እንዴት ነው?
13 ድንገተኛ ንግግር። “ኢምፕሮምቱ” ለተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “አለዝግጅት፣ ወዲያው፣ እዚያው በዚያው ተዘጋጅቶ የሚሰጥ ንግግር” የሚል ፍቺ ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ወይም በነጥቡ ላይ ምንም ዓይነት ዝግጅት አልተደረገበትም ማለት ኢሳ. 50:4
ነውን? አይደለም፣ ምክንያቱም ለማንኛውም ትምህርት ዝግጅት የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በአንድ የተወሰነ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ንግግር እንደምትሰጥ በቅድሚያ የማይነገርህ ጊዜ ሊኖር ይችላል። በዚህም ምክንያት በዚያ ጉዳይ ላይ ለመናገር ዝግጅት አላደረግህም ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚያጋጥመው ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ያገኘኸው ሰው አንድ ጥያቄ ሲያነሣ ሊሆን ይችላል። ወይም ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ወይም መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በምትሰጥበት ወይም በፍርድ ቤት ወይም በሸንጎ ፊት በምትጠየቅበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ባሉት አጋጣሚዎች የንግግርህ ቅንብርና የቃላት አመራረጥህ ያልታሰበበትና ድንገተኛ ቢሆንም የምትናገረው ነገር ከቲኦክራሲያዊ ጥናቶች ባገኘኸው እውቀት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ስለዚህ ድንገተኛ ንግግር የምንለው የንግግር ዓይነትም ቢሆን ለዚያ አጋጣሚ ተብሎ የተደረገ ዝግጅት የሌለው ቢሆንም ከጊዜው በፊት በተደረገ ዝግጅት ላይ የተመሠረተ ነው። —14 አንድ ነገር እንድትናገር እንደምትጠየቅ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እንኳ ካወቅህ ለንግግሩ ለመዘጋጀት የምታደርጋቸው ጠቃሚ እርምጃዎች አሉ። መጀመሪያ የምትገልጻቸውን አንድ ወይም ሁለት ነጥቦች ምረጥ። ለእነዚህ ነጥቦች ድጋፍ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችንና ጥቂት ጥቅሶችን ምረጥ። ከዚያ በኋላ ለንግግርህ መግቢያ ስለምትጠቀምበት አጠር ያለ ሐሳብ አስብ። ከዚህ በኋላ ከተጠየቅህ ንግግርህን ለመጀመር ዝግጁ ሆነሃል ማለት ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሳይመጣ በቀረው ተማሪ ምትክ ሆኖ ንግግር የሚሰጥ ፈቃደኛ እንደሚጠየቅበት ባሉት ሁኔታዎች ሊያጋጥም ይችላል።
15 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ድንገት ተጠይቀው ለእውነት ምሥክርነት የሰጡ የአምላክ አገልጋዮች አሉ። ከእነዚህም አንዱ በሐሰት ምሥክሮች ከተከሰሰ በኋላ በአይሁዳውያን ሸንጎ ፊት ተገድዶ የቀረበው እስጢፋኖስ ነው። እርሱ የሰጠውን ቀስቃሽ የሆነ ድንገተኛ ንግግር በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 7 ላይ ማንበብ ይቻላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና ሰዎች ተይዞ ወደ አርዮስፋጎስ ከተወሰደ በኋላ ስለ እምነቱ ተጠይቆ ነበር። እርሱ የሰጠው ድንገተኛ ንግግር በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ላይ ይገኛል።
16–18. ተማሪዎች በንባብ መልክ ንግግር ከመስጠት ወይም ንግግራቸውን በቃል ከመሸምደድ ይልቅ በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግር መለማመድ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
16 ከሁሉ የተሻለው ዘዴ። አንዳንድ ጊዜ ጀማሪ ተናጋሪዎች የተማሪ ንግግራቸውን በንባብ መልክ ለማቅረብ ይፈልጋሉ። ይህ ዘዴ በአጠቃላይ ተመራጩ ዘዴ አይደለም። ከአድማጮች ጋር ለመገናኘትና የውይይት መልክ ያለው ንግግር ለማቅረብ ስለማያስችል ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከተዘጋጀ ጽሑፍ በማንበብ ንግግር የሚሰጥባቸው ጊዜያት አሉ። እንደነዚህ ላሉት ንግግሮች ልምምድ የምታደርገው የንባብ ክፍል በሚሰጥህ ጊዜ ነው። በሌሎቹ ንግግሮች
ግን ማስታወሻህን ብቻ በመጠቀም በቃልህ ተናገር።17 አንዳንድ ተማሪዎች ከማንኛውም ዓይነት ማስታወሻ ነፃ ለመሆን ሲሉ ንግግራቸውን በሙሉ በቃል ለመሸምደድ ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ በቃል የተሸመደዱ ንግግሮች ጉዳት አላቸው። እንደ ሁኔታው ሊስተካከሉ አይችሉም። ተናጋሪው የተፈጥሮ ባሕርይ እንዲጎድለው ስለሚያደርጉ አስፈላጊ ነጥቦች የሚረሱበት አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። በመግቢያ ወይም በመደምደሚያ ላይ የሚነገሩ ቁልፍ የሆኑ ዐረፍተ ነገሮችን በቃል መያዝ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሙሉውን ንግግር በቃል መሸምደድ ግን ተገቢ አይደለም።
18 ከሁሉ የሚሻለው በራስ አገላለጽ የሚቀርበው ንግግር ነው። ራሳችንን ችለን እንድንቆም በምንሰለጥንበት በመስክ አገልግሎት የምንጠቀመው በዚህ የንግግር ዓይነት ነው። በጉባኤ ስብሰባዎችም ቢሆን መልእክታችንን ቀጥተኛና ልባዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብና ጥሩ ውጤት ለማስገኘት የሚችለው የንግግር ዓይነት ይህ ስለሆነ አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀመው በራስ አገላለጽ በሚቀርበው ንግግር ነው። ስለዚህ ይህን የንግግር አቀራረብ ዘወትር ተለማመድ። ሳንዘጋጅ በድንገት ንግግር እንድንሰጥ የምንጠየቅባቸው ጊዜያት ቢኖሩም አስተዋጽኦ ይዞ በራስ አገላለጽ ለሚቀርብ ንግግርም ሆነ በድንገት ለሚሰጥ ንግግር ይሖዋ ብቃት እንዲኖረን ስለሚያደርግ ዝግጁዎች እንሆናለን። ሁለቱም የንግግር አቀራረብ ዓይነቶች በአገልግሎታችን ውስጥ የየራሳቸው ቦታ አላቸው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]