በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተረጋግቶ መናገር፤ ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ

ተረጋግቶ መናገር፤ ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ

ጥናት 37

ተረጋግቶ መናገር፤ ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ

1–9. ተማምኖና ተረጋግቶ መናገር ምን ማለት እንደሆነ ግለጽ። ወደዚህ ደረጃ እንዴት መድረስ እንደሚቻልም ተናገር።

1 የተረጋጋ ተናጋሪ ዘና ብሎ ይናገራል። ሁኔታዎችን በቁጥጥሩ ሥር ስለሚያደርግ ሚዛኑን ጠብቆ ያለ ምንም የስሜት መረበሽ ንግግሩን ይጨርሳል። በሌላው በኩል ግን ተረጋግቶ ካልተናገረ በተናጋሪነቱ እንደማይተማመን ያሳያል። ሁለቱም አንድ ላይ ይሄዳሉ። በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ “ተማምኖና ተረጋግቶ መናገር” የሚለው እንደ አንድ ነጥብ ሆኖ የሰፈረው በዚህ ምክንያት ነው።

2 ተማምኖና ተረጋግቶ መናገር ጥሩ ቢሆንም ከልክ በላይ የመተማመን መንፈስ ማንፀባረቅ ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ከመጠን በላይ ተዝናንቶ በመቆም፣ በመንጎራደድ፣ በመጀነን፣ ወንበር ላይ እየተንፈላሰሱ በመናገር ወይም ከቤት ወደ ቤት በሚሰበክበት ጊዜ በሩ ላይ በግዴለሽነት ተደግፎ በመቆም ሊንጸባረቅ ይችላል። ንግግሩን ስታቀርብ የትምክህተኝነትን መንፈስ የሚያመለክት ነገር ካሳየህ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በግል ምክር እንደሚሰጥህ ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም የአገልግሎትህን ውጤታማነት የሚቀንስ ምንም ነገር እንዳይታይብህ ሊረዳህ ይፈልጋል።

3 አዲስ ተናጋሪ ከሆንክ ግን ወደ መድረክ ስትወጣ ከዚህ ችግር ይልቅ ፍርሃት ፍርሃት የማለትና ዓይነ አፋርነት ሊሰማህ ይችላል። ከመጠን በላይ ስለተረበሽክና ስለደነገጥክ ዛሬ ጥሩ ንግግር አላቀርብም ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ነገር ግን ሁኔታው አንተ እንደምታስበው ላይሆን ይችላል። በትጋት ከጣርክና ችግሩ ለምን እንደሚነሳ ካወቅህ ልበ ሙሉነትንና መረጋጋትን በውስጥህ ልታሳድር ትችላለህ።

4 አንዳንድ ተናጋሪዎች መተማመን የሚጎድላቸው ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ወይም በሁለት ምክንያቶች የተነሣ ነው። አንደኛው ምክንያት የዝግጅት ጉድለት ወይም ለትምህርቱ ትክክለኛ አመለካከት አለመያዝ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ስለ ንግግር ችሎታቸው አፍራሽ አስተሳሰብ ስላላቸው ነው።

5 ታዲያ የመተማመን ስሜት የሚሰጥህ ምንድን ነው? ዓላማህን በሚገባ መፈጸም እንደምትችል ማወቅህ ወይም ማመንህ ነው። ማንኛውም ነገር በእጅህ ውስጥ እንደሆነና ልትቆጣጠረው እንደምትችል እርግጠኛ መሆንህ ነው። መድረክ ላይ ይህን የመሰለ ስሜት ለማግኘት ልምድ ይጠይቃል። በርካታ ንግግሮችን ከዚህ በፊት ስለሰጠህ የአሁኑ ንግግር እንደሚሳካልህ በመጠኑ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ይሁን እንጂ ብዙም ያልቆየህ ተናጋሪም ብትሆን ቀደም ሲል የሰጠሃቸው ንግግሮች ሊያደፋፍሩህ ይገባል። በዚህም ምክንያት ብዙም ሳትቆይ ይህን የንግግር ባሕርይ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ለማሳየት መቻል ይኖርብሃል።

6 ብዙ ልምድ ቢኖርህም ባይኖርህም የመተማመን መንፈስ እንዲኖርህ ወሳኝ የሆነው ሌላው ነገር ትምህርቱን በደንብ ማወቅህና ይህ ትምህርት ለአድማጮች ያስፈልጋቸዋል የሚል ጽኑ እምነት በውስጥህ ማሳደርህ ነው። ይህም አስቀድመህ ርዕሱን በደንብ መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን እንዴት ንግግሩን እንደምታቀርበው ጭምር በጥንቃቄ መዘጋጀት አለብህ ማለት ነው። ለቲኦክራሲያዊ ዕድገትህና በስብሰባው የሚገኙት ወንድሞች እንዲታነጹ በማሰብ ይህን የምታደርግ ከሆነ ወደ መድረክ የምትወጣው በጸሎተኛነት መንፈስ ይሆናል። በትምህርቱ ትመሰጣለህ፤ ስለሆነም ራስህንና ፍርሃትህን ጨርሶ ትረሳለህ። ሰውን ሳይሆን አምላክን እንዴት እንደምታስደስት ታስባለህ። — ገላ. 1:10፤ ዘጸ. 4:10–12፤ ኤር. 1:8

7 ይህ ማለት የምትናገረው እያንዳንዱ ነገር ትክክል ስለመሆኑ በውስጥህ የእርግጠኝነት ስሜት ማደር አለበት ማለት ነው። በምትዘጋጅበት ጊዜ ይህ ስሜት ያለህ መሆኑን አረጋግጥ። ስሜትን የሚስብና የሚያነቃቃ ንግግር ለማዘጋጀት አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ካደረግህ በኋላ አሁንም ንግግርህ እንደማይደምቅ ከዚህ ይልቅ የሞተ እንደሚሆን ከተሰማህ በንቃት የሚከታተሉ አድማጮች ንግግርህን ሊያሟሙቁት እንደሚችሉ አስታውስ። ስለዚህ በንግግሩ አቀራረብ የአድማጮችህን ስሜት አነቃቃ። እነርሱ በምላሹ የሚያሳዩት ስሜትም በምታቀርብላቸው ትምህርት እንድትተማመን ያደርግሃል።

8 አንድ ሐኪም በሰውነት ላይ ምን የሕመም ምልክቶች እንዳሉ ለማወቅ እንደሚፈልግ ሁሉ ምክር ሰጪህም እንደተረበሽክ በማያሻማ ሁኔታ የሚያሳዩ ምልክቶችን ለማግኘት ይከታተላል። አንድ ጥሩ ሐኪም ምልክቶቹን ለማስታገስ ሳይሆን የሕመሙን መንስኤ ለማጥፋት እንደሚጥር ሁሉ ምክር ሰጪህም ተማምነህና ተረጋግተህ እንዳትናገር ከፊትህ የተጋረጡብህን ችግሮች ለማስወገድ ሊረዳህ ይጥራል። ሆኖም እነዚያን የፍርሃት ምልክቶች እንዴት ልትቆጣጠራቸው እንደምትችል ማወቅህ ከምልክቶቹ በስተጀርባ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድ ይረዳሃል። ታዲያ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

9 አብዛኛውን ጊዜ የታመቀ ስሜት ወይም የውስጥ መረበሽ የሚወጣባቸው ሁለት ቀዳዳዎች አሉ። እነርሱም አካላዊ ምልክቶችና የድምፅ ሁኔታዎች በመባል በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። እነዚህ ምልክቶች በየትኛውም መጠን ከታዩ ሰውዬው የመረጋጋት መንፈስ ይጎድለዋል እንላለን።

10, 11. የአካላችን ሁኔታ በውስጣችን ያለመተማመን ስሜት እንዳለ ሊያጋልጥብን የሚችለው እንዴት ነው?

10 በአካላዊ ሁኔታ መረጋጋትን ማሳየት። እንግዲያው የመጀመሪያው የመረጋጋት ምልክት የሚከሰተው በአካላዊ ሁኔታ ነው። በውስጥህ የመተማመን ስሜት ከሌለ ያንን የሚያሳዩብህ አንዳንድ ነገሮች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል። በመጀመሪያ እጆችህን እንውሰድ። እጅን ወደኋላ አድርጎ መቆም፤ እጆችን ወደታች ዘርግቶ በተጠንቀቅ መቆም፤ አትራኖሱን ሙጭጭ አድርጎ መያዝ፤ ደጋግሞ እጅን ኪስ ውስጥ ገባ ወጣ ማድረግ፣ የኮትን ቁልፍ መፍታትና መቆለፍ፤ ያለ ዓላማ ጉንጭን፣ አፍንጫንና መነጽርን መነካካት፤ ያልተሟላ የእጅ እንቅስቃሴ፤ በሰዓት፣ በእርሳስ፣ በቀለበትና በማስታወሻ ወረቀት መጫወት። በተጨማሪም እግር ያረፈበትን ቦታ መቀያየር፣ ሰውነትን ወዲያና ወዲህ ማወዛወዝ፣ ወገብን እንደ እንጨት ድርቅ ማድረግ፣ የጉልበት መብረክረክ፣ ከንፈርን ደጋግሞ በምራቅ ማራስ፣ ቶሎ ቶሎ ምራቅ መዋጥ እና ትንፋሽን ቁርጥ ቁርጥ ማድረግ የዚሁ ክፍል ናቸው።

11 ተግቶ በመጣር እነዚህን ሁሉ የፍርሃት ምልክቶች መቆጣጠር ወይም መቀነስ ይቻላል። ይህንን ጥረት ካደረግህ የሰውነትህ አቋም ለተመልካች የመረጋጋትን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። ስለዚህ እንደ ወትሮህ በተወሰነ መንገድ ተንፍስ፤ ራስህንም ዘና ለማድረግ ጥረት አድርግ። ንግግር ከመጀመርህ በፊት ቆም በል። አድማጮችህም በአጸፋው ጥሩ ስሜት ያሳዩሃል። ይህም ያንን የምትፈልገውን ነገር ማለትም በንግግርህ መተማመንን ለማግኘት ይረዳሃል። ስለ አድማጮችህ በመጨነቅ ወይም ስለ ራስህ በማሰብ ፋንታ በትምህርቱ ላይ ትኩረት አድርግ።

12–14. ድምፃችን በውስጣችን ያለመተማመን ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ ቢሆን ተረጋግተን ለመናገር ምን ማድረግ እንችላለን?

12 ድምፅን በመቆጣጠር መረጋጋትን ማሳየት። ፍርሃትን የሚያሳዩ የድምፅ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው። ከወትሮው ከፍ ያለ ቃና፣ የድምፅ መርገብገብ፣ ጉሮሮን ደጋግሞ ማጥራት፣ በድምፅ ማውጫ አካሎች ላይ በደረሰው ውጥረት ምክንያት የተፈጠረ በጣም ቀጭን ድምፅ። እነዚህ ችግሮችና ልማዶችም ተግቶ በሚደረግ ጥረት ሊወገዱ ይችላሉ።

13 ወደ መድረኩ በምትወጣበት ጊዜ ወይም ማስታወሻህን በቦታው ላይ ስታስቀምጥ አትጣደፍ። ያዘጋጀሃቸውን ትምህርቶች ለአድማጮች ለማካፈል አጋጣሚ በማግኘትህ ተዝናና ደስተኛም ሁን። መናገር ስትጀምር የድንጋጤ ሁኔታ እንዳለብህ ከተሰማህ በመግቢያህ ላይ ከወትሮህ በተለየ መንገድ ዝግ ብለህ ለመናገር ልዩ ጥረት አድርግ። በተጨማሪም ቃናህን የተለመደ ነው ብለህ ከምትገምተው ባነሰ መንገድ ረገብ አድርገው። ይህም የተሰማህን ፍርሃት ለመቆጣጠር ይረዳሃል። የሰውነት እንቅስቃሴዎችና ቆም እያሉ መናገርም ዘና ለማለት የሚረዱ ሆነው ታገኛቸዋለህ።

14 ይሁን እንጂ እነዚህን ነገሮች ለመለማመድ መድረክ ላይ እስክትወጣ ድረስ አትጠብቅ። በየዕለቱ ተማምኖና ሚዛንን ጠብቆ መናገርን ተማር። ይህን ማድረግህ በመድረክና ርጋታ የግድ አስፈላጊ በሆነበት በመስክ አገልግሎት ላይ ተማምነህ ለመናገር ያስችልሃል። ሳትረበሽ ንግግሩን ማቅረብህ አድማጮችህን ስለሚያዝናናቸው ትኩረታቸውን በትምህርቱ ላይ ያደርጋሉ። በስብሰባዎች ጊዜ አዘውትረህ ሐሳብ መስጠትህ በሰው ፊት መናገርን እንድትለምድ ይረዳሃል።

**********

15. በሰው ፊት ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 በአድማጮች ፊት ንጹሕና ሥርዓታማ ሆነህ መቅረብህም የመረጋጋት መንፈስ እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አቀራረብ አስፈላጊ የሆነባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ይህ ጉዳይ በቂ ትኩረት ካልተሰጠው የአንድ ክርስቲያን አገልጋይ የልብስና የሰውነት ሁኔታ ለአድማጮች ደስ የማይል ሊሆን ስለሚችል የሚናገረውን በጥሞና ላይከታተሉ ይችላሉ። ከመልእክቱ ይልቅ ወደ ራሱ ትኩረት ይስባል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህን ለማድረግ አይፈልግም። በሰው ፊት እንዴት ሆኖ መቅረብ እንዳለበት እጅግ በጣም ግድ የለሽ ከሆነ እርሱ አባል የሆነበትን ድርጅት በሌሎች ፊት ሊያስንቅና የሚያቀርብላቸውን መልእክት ለመቀበል ዕንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። ይህ መሆን የለበትም። ምንም እንኳን “ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ” የሚለው ነጥብ በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ ከተዘረዘሩት የመጨረሻው ቢሆንም በአስፈላጊነቱ የመጨረሻ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም።

16–21. ተገቢ ስለሆነ አለባበስና የጸጉር አያያዝ ምን ምክር ተሰጥቶአል?

16 ተገቢ ልብስና የጸጉር አያያዝ። ቅጥ ያጣ ልብስ መወገድ ይኖርበታል። ክርስቲያኑ አገልጋይ ትኩረትን ወደ ራስ የሚስቡትን የዓለም ፋሽኖች አይከተልም። በልዩ ልብስ ተንቆጥቁጦ ለመሄድ ወይም እዩኝ እዩኝ የሚል የሚያብለጨልጭ ልብስ ለመልበስ አይፈልግም። በሌላው በኩል ደግሞ በአለባበሱ ዝርክርክ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያደርጋል። ጥሩ ልብስ መልበስ ሲባል አዲስ ሙሉ ልብስ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ንጹሕና በሥርዓት የተያዘ ልብስ ሊኖረው ይችላል። ሱሪው መተኮስ ክራቫቱም መስተካከል ይኖርበታል። እነዚህ ማንኛውም ሰው ማድረግ የሚችላቸው ነገሮች ናቸው።

17 በ1 ጢሞቴዎስ 2:9 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ ልብስን አስመልክቶ የሰጠው ምክር ዛሬ ላሉት ክርስቲያን ሴቶችም ተስማሚ ነው። ለወንድሞች የተሰጠው ምክር ለእነርሱም ይሠራል። ወደ ራሳቸው ትኩረትን የሚስብ ልብስ መልበስ አይገባቸውም። ልከኝነት እንደጎደላቸው የሚያሳይ ቅጥ የሌለውን የዓለም ፋሽን መከተል የለባቸውም።

18 እርግጥ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ልብስ እንደማይለብስ መታወስ ይኖርበታል። ደግሞም ሰዎች እንደዚህ እንዲያደርጉ ሊጠበቅባቸው አይገባም። ለአንዱ ደስ ያለው ልብስ ሌላውን ደስ ላያሰኘው ይችላል። ይህ ስህተት የለበትም። ተገቢ አለባበስ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ መልስ ይሰጠዋል። ሆኖም ለአድማጮች አእምሮ መጥፎ መልዕክት የሚያስተላልፍ ልብስ ከመልበስ መራቅና ወደ ስብሰባዎቻችን የሚመጡትን ሰዎች እንዳናሰናክል መጠንቀቅ ይኖርብናል።

19 በትምህርት ቤቱ ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ንግግር የሚሰጡ ወንድሞች ሊኖራቸው የሚገባ ተገቢ አለባበስ ምንድን ነው? ቢባል የሕዝብ ንግግር አቅራቢዎች በአጠቃላይ የሚለብሱት ዓይነት ልብስ መልበስ ተገቢ ነው ለማለት ይቻላል። የሕዝብ ንግግር የሚሰጡ ሰዎች ክራቫት ማድረጋቸውና ሙሉ ልብስ መልበሳቸው በአካባቢያችሁ የተለመደ ከሆነ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም ለሕዝብ ተናጋሪነት እየሠለጠንህ ስለሆነ በዚሁ መንገድ መልበስህ ተገቢ ነው።

20 ተገቢ የጸጉር አያያዝም ትኩረት ማግኘት አለበት። ያልተበጠረ ጸጉር በሰዎች አእምሮ ላይ መጥፎ ስሜት ሊያሳድር ይችላል። በዚህ በኩል ንጹሕ ሆነን እንድንታይ ምክንያታዊ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንዶች በስብሰባ ላይ ክፍል ሲሰጣቸው ጺማቸው በሚገባ የተላጨ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው።

21 ተገቢ ልብስና የጸጉር አያያዝን በተመለከተ ተማሪው የሚያስመሰግን አቋም ካሳየ ከመድረክ ምስጋና መስጠቱ ምን ጊዜም ተገቢ ነው። እንዲያውም ለአለባበሳቸውና ለጸጉራቸው አያያዝ ተገቢ ትኩረት ለሚሰጡት ወንድሞች ምስጋና መስጠቱ ሌሎችም ጥሩ ምሳሌያቸውን እንዲከተሉ ሊያበረታታቸው ይችላል። ነገር ግን በአለባበስና በጸጉር አያያዝ በኩል መሻሻል የሚያስፈልገው ሁኔታ ካለ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ተማሪውን ከመድረኩ ከመምከር ይልቅ በግል ቀርቦ በደግነት አንዳንድ ሐሳቦችን ቢሰጠው የተሻለ ይሆናል።

22–28. አቋቋማችን ሰዎች ለእኛ ያላቸውን አመለካከት እንዴት ሊነካ እንደሚችል አብራራ።

22 ትክክለኛ አቋቋም። ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ ትክክለኛ አቋቋምንም ይጨምራል። አሁንም ቢሆን ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አቋቋም የለውም። ድርቅ ያለ ሥርዓት አውጥቶ ሁሉም ወንድሞች ይህን መከተል አለባቸው የሚል ደንብ ለማውጣት ምንም ዓይነት ሙከራ መደረግ የለበትም። ይሁን እንጂ ደስ የማይሉና ወደ መልእክቱ ሳይሆን ወደ ግለሰቡ ትኩረት የሚስቡ ከልክ ያለፉ የአቋቋም ሁኔታዎች መታረምና መወገድ እንዲችሉ ትኩረት ማግኘት አለባቸው።

23 ለምሳሌ ያህል ሁሉም ሰው በአንድ ዓይነት መንገድ አይቆምም። በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ ሰውዬው ቀጥ ብሎ እስከቆመ ድረስ የአቋቋሙ ሁኔታ ይህን ያህል ለውጥ አያመጣም። ነገር ግን አንድ ተናጋሪ እግሮቹን አንፈራጦ ቢቆምና ለአድማጮች ፈረስ ላይ እንደወጣ መስሎ ቢታይ ይህ ሁኔታ በትኩረት መስማትን የሚያደናቅፍ ነው።

24 በተመሳሳይም አንድ ተናጋሪ ቀጥ በማለት ፋንታ ሸብረክ ብሎ ቢቆም አድማጮች ታሞ ይሆናል በማለት ያዝኑለት ይሆናል። ይህም ትኩረታቸውን ከንግግሩ ያርቃል። ሐሳባቸው ያረፈው እርሱ በሚናገረው ቃል ላይ ሳይሆን በራሱ ላይ ነው።

25 እግርን አጠላልፎ በአንድ እግር መቆም የመረበሽ ምልክት ነው። እጅን ኪስ ውስጥ ከቶ መቆምም እንደዚሁ ነው። እነዚህ ነገሮች መወገድ አለባቸው።

26 በተመሳሳይም በመስክ አገልግሎት ላይ አንድ አስፋፊ የበሩን መቃን ተደግፎ ቢቆም ስሕተት እንደሆነ ሁሉ አንድ ተናጋሪም አለፍ እያለ እጆቹን አትራኖስ ላይ ማሳረፉ ስህተት ባይሆንም አትራኖሱን ተደግፎ መቆም የለበትም። ይህ ለተመልካች ደስ አይልም።

27 ይሁን እንጂ ግለሰቦች የተለያዩ የመሆናቸው ጉዳይ አሁንም ሊተኮርበት ይገባል። ሁሉም ሰው በአንድ መልክ አይቆምም። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡት የአድማጮችን ሐሳብ ከንግግሩ የሚያርቁ ቅጥ የለሽ ሁኔታዎች ብቻ ናቸው።

28 አቋቋምን ማስተካከል የዝግጅት ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ማሻሻል የሚያስፈልግህ ከሆነ ነገሩን ቀደም ብለህ ልታስብበትና መድረክ ላይ ስትወጣ ንግግር ከመጀመርህ በፊት በትክክለኛ መንገድ መቆም እንዳለብህ ማወቅ ያስፈልግሃል። ይህም ችግር ቢሆን በየቀኑ በትክክለኛ መንገድ መቆምን በመለማመድ ሊስተካከል የሚችል ነው።

29–31. የምንጠቀምበት የአገልግሎት መሣሪያ ንጹሕ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

29 ንጹሕ የአገልግሎት መሣሪያዎች። በር ላይ ቆመን ከሰዎች ጋር ስንወያይ ወይም ከመድረክ ንግግር እየሰጠን እያለን ከመጽሐፍ ቅዱሳችን አንዳንድ ወረቀቶች መውደቅ ቢጀምሩ ሁኔታው አእምሮን የሚረብሽና ለተመልካች ደስ የማይል ነው። ይህም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ምንም ነገር ማስቀመጥ የለብንም ማለት አይደለም። ንግግሩን የሚያውኩ ችግሮች ከተፈጠሩ ግን ሁኔታዎች ጥሩ መልክ እንዲይዙ ለነገሩ ትኩረት መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን ይጠቁማሉ። የመጽሐፍ ቅዱስህንም መልክ ወይም ሁኔታ መመርመሩ ጥሩ ነው። ብዙ ጊዜ ከመሥራቱ የተነሳ የቆሸሸ ወይም ያረጀ ወይም የተዝረከረከ መልክ ሊኖረው ይችላል። እንግዲያው በመድረክ ላይ ወይም በመስክ አገልግሎት ላይ የምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ልንረዳው የፈለግነውን ሰው ቅር የሚያሰኝ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ማመዛዘን አለብን።

30 ይህ ምክር ጽሑፍ ለምንይዝበት ቦርሳም ይሠራል። ጽሑፎችን በቦርሳችን ውስጥ ሥርዓት ባለው መንገድ ማስቀመጥ የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ነገር ግን ከበር ወደ በር እየሄድን ስናገለግል ቦርሳችንን ከፍተን ጽሑፍ ለማውጣት ስንፈልግ በውስጡ ከታጨቁት ወረቀቶች መካከል በዳበሳ ለይተን ማውጣት ካለብን ወይም መጽሔት መዘን ስናወጣ ብዙ ነገሮች አብረው በመውጣት በሩ ላይ ቢዝረከረኩ አንድ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል ማለት ነው።

31 የተናጋሪው የውጭ ኪሶች በብዕር፣ በእርሳስና በሌላ ዕቃ አብጠው መታየታቸውም የአድማጮችን ትኩረት ያውካል። እነዚህ ነገሮች የት መቀመጥ እንዳለባቸው በተመለከተ ምንም ዓይነት ሕግ ማውጣት አያስፈልግም። ሆኖም የአድማጮችን ትኩረት በመሳብ ንግግሩን እንዳይከተታሉ ዕንቅፋት የሚሆኑ ከሆነ አንድ ነገር መደረግ ይኖርበታል።

32–34. በፊታችን ላይ የሚነበበው ስሜት በሰው ላይ በምናሳድረው አመለካከት ምን ድርሻ አለው?

32 ፊት ላይ ተገቢ ያልሆነ ስሜት አለማሳየት። ንግግሩን በምንዘጋጅበት ጊዜ ትምህርቱ በምን ዓይነት ስሜት ወይም መንፈስ መቅረብ እንዳለበት ብናጤነው ጥሩ ነው። ለምሳሌ ያህል ስለ ሞትና ስለ ጥፋት ንግግር የምንሰጥ ቢሆን ቦግ ያለ ፈገግታ ብናሳይ ትክክል አይሆንም። በተመሳሳይም በአዲሱ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ስለሚኖሩት አስደሳች ሁኔታዎች ስንገልጽ ፊታችንን ጥቁር አድርገን አድማጮችን ብንመለከት ልክ አይሆንም።

33 የፊት ጉዳይ ብዙ ጊዜ ችግር የለውም። እርግጥ አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ፊታቸውን ከበድ ወደማድረግ ያዘነብላሉ። ልናስወግደው የሚገባን ንግግሩን ለመከታተል የሚያውክ ከልክ ያለፈን ሁኔታ ነው። የፊቱ ሁኔታ ከልብ እየተናገረ ስለመሆኑ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ ጥያቄ የሚያስነሳ ከሆነ ይህ ፈጽሞ የማይፈለግ ነገር ነው።

34 እንግዲያው ንግግር ስታዘጋጅ በምን ዓይነት ስሜት ወይም መንፈስ መቅረብ እንዳለበት ብታስብበት ጥሩ ነው። ክብደት ያለው ርዕሰ ጉዳይ ቢሆን፤ ለምሳሌ ክፉዎች ስለሚመጣባቸው ጥፋት የሚገልጽ ንግግር ከሆነ የሁኔታውን አሳሳቢነት በሚያሳይ ሁኔታ መቅረብ አለበት። ሐሳብህ በትምህርቱ ላይ ከሆነና እስከ መጨረሻው ድረስ ከአእምሮህ ካልጠፋ ፊትህ በደመ ነፍስ ያንን ያንጸባርቃል። አድማጮችን ፍልቅልቅ የሚያደርግ አስደሳች ርዕሰ ጉዳይ ከሆነ ትምህርቱ በደስታ መቅረብ አለበት። መድረክ ላይ ስትወጣ ዘና የምትል ከሆነ ፊትህ አብዛኛውን ጊዜ ይህንን የውስጥ ደስታ ያንጸባርቃል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]