ተስማሚ ምሳሌዎች
ጥናት 34
ተስማሚ ምሳሌዎች
1, 2. ምሳሌዎች ለአንድ ንግግር ምን ጥቅም እንዳላቸው በአጭሩ አስረዳ።
1 አንድ ተናጋሪ ምሳሌዎችን ሲያመጣ በአድማጮቹ አእምሮ ውስጥ ትርጉም ያላቸውን ሥዕሎች ደመቅ አድርጎ መሳሉ ነው። ምሳሌዎች ስሜትን ይቀሰቅሳሉ፣ ዐበይት ሐሳቦችንም ያጎላሉ። አእምሮን በማመራመር አዳዲስ ሐሳቦችን በቀላሉ ለመጨበጥ ያስችላሉ። በደንብ ታስቦባቸው የተመረጡ ምሳሌዎች አእምሮን ያሳምናሉ፤ ስሜትንም ይነካሉ። ይህም በመሆኑ መልዕክቱ በበለጠ ኃይል ወደ አእምሮ ይተላለፋል። ነገሩን በቀጥታ መግለጹ የዚህን ያህል ኃይል አይኖረውም። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ምሳሌዎቹ ተስማሚ ከሆኑ ብቻ ነው። ለትምህርቱ የሚስማሙ መሆን ይኖርባቸዋል።
2 አንዳንድ ጊዜ ምሳሌዎችን ዕንቅፋት የሚሆኑ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለማስተካከል ልንጠቀምባቸው እንችላለን። አወዛጋቢ በሆነ መሠረተ ትምህርት ላይ ውይይት ከመጀመራችን በፊት ሰዎቹ ሊያቀርቧቸው የሚችሉ የተቃውሞ መልሶችን ለመዝጋት ሊያገለግሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል “እጁን እሳት ውስጥ በመጨመር ልጁን የሚቀጣ አባት የለም” ለማለት ትችላለህ። “ሲኦል ማሠቃያ ነው” ስለሚለው መሠረተ ትምህርት መወያየት ከመጀመርህ በፊት እንደዚህ ያለ ምሳሌ በመናገር የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት “የሲኦል” ትምህርት ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ ለማሳየት ትችላለህ። በዚህ መንገድ በቀላሉ ለመፍረስ የተመቻቸ ይሆናል።
3–6. ምሳሌዎችን ከምን ምንጮች መውሰድ ይቻላል?
3 ምሳሌዎች በተለያየ መልክ ሊቀርቡ ይችላሉ። ሁለት ነገሮችን በማያያዝ፣ በማወዳደር፣ በማነጻጸር፣ በማዛመድ ወይም በማመሳሰል፤ አለዚያም የግል ተሞክሮዎችን በማምጣትና አንድን ሰው ወይም ሁኔታ እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ ምሳሌ መናገር ይቻላል። ምሳሌዎቹን ከብዙ ምንጮች መውሰድ ይቻላል። ሕይወት ያላቸውን ወይም የሌላቸውን ነገሮች መጥቀስ ይቻላል። በአድማጮች ዕለታዊ ተግባር፣ በሰብአዊ ጠባዮች፣ በቤት ቁሳቁስ፤ ወይም እንደ ቤት፣ መርከብና ወዘተ . . . ባሉት የሰው እጅ ሥራዎች ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ። የትኛውም ዓይነት ምሳሌ ቢቀርብ ለወቅቱ ወይም ለትምህርቱ የሚስማማ በመሆኑ እንጂ ተናጋሪው ያን ምሳሌ ስለሚወደው ብቻ የተመረጠ መሆን የለበትም።
4 ግን ጥንቃቄ አድርግ። ንግግርህ ከመጠን በላይ የምሳሌዎች ቅመም አይብዛበት። ምሳሌዎችን ተጠቀም፤ ግን አይብዙ።
5 ምሳሌዎችን በአግባቡ መጠቀም ልዩ ጥበብ ነው። ጥሩ ችሎታንና ልምድን ይጠይቃል። የምሳሌዎች ውጤታማነት ግን የማያጠያይቅ ነው። በምሳሌዎች መጠቀምን ለመማር ከፈለግህ ነገሮችን ከምሳሌ አንፃር ማየትን መለማመድ ይኖርብሃል። ጽሑፍ በምታነብበት ጊዜ በዚያ ውስጥ የገቡትን ምሳሌዎች ልብ በላቸው። ልዩ ልዩ ነገሮችን ስታይ ከክርስቲያናዊ አኗኗርና አገልግሎት ጋር ለማያያዝ ሞክር። ለምሳሌ ያህል በትንሽ ዕቃ ላይ የተተከለን አበባ ብታይና ደርቆ ብትመለከት “ጓደኝነትም እንደ ተክል ነው። ተክሉ ለማደግ ውኃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጓደኝነትም እንዲዳብር እንክብካቤ
ያስፈልገዋል” ብለህ ለማሰብ ትችላለህ። ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ጨረቃን የሚመለከቷት ከጠፈር ጉዞ አንፃር ብቻ ነው። ለክርስቲያኖች ግን ጨረቃ የአምላክ የእጁ ሥራ፣ መሬትን የምትዞር፣ ለዘላለም ጸንታ የምትኖር ግዑዝ አካል፣ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን የምትነካ፣ የባሕርን ማዕበል የምታበርድና የምትቀሰቅስ ነገር ናት።6 ንግግር በምትዘጋጅበት ጊዜ ቀላል ምሳሌዎች ቶሎ የማይመጡልህ ከሆነ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ ተመሳሳይ ትምህርት የተብራራበትን ጽሑፍ ለማየት ሞክር። በዚያ ጽሑፍ ላይ ምሳሌዎች ገብተው እንደሆነ ተመልከት። የንግግሩን ቁልፍ ቃላትና እነዚህ ቃላት ለአእምሮህ የሚያስተላልፉትን ሥዕል በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ይህን የሚታይህን ሥዕል አስፋፋው። ይሁን እንጂ ተስማሚ ያልሆነ ምሳሌ ከማምጣት ምንም ምሳሌ አለመናገሩ እንደሚሻል አስታውስ። በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ዝርዝር ውስጥ የገባውን “ለትምህርቱ የሚስማሙ ምሳሌዎች” የሚለውን ነጥብ ስትመለከት ልታስብባቸው የሚያስፈልጉህ ጥቂት የጉዳዩ ዘርፎች አሉ።
7–9. ቀላል ምሳሌዎች በጣም ውጤታማ የሆኑት ለምንድን ነው?
7 ቀላል ምሳሌዎች። ያልተወሳሰበ ምሳሌ ለማስታወስ ቀላል ነው። እየተብራራ ያለውን ነጥብ ይበልጥ ያዳብራል እንጂ የተወሳሰበ በመሆኑ የባሰውን የሚያደነጋግር አይሆንም። ብዙ ጊዜ የኢየሱስ ምሳሌዎች ከጥቂት ቃላት የሚበልጡ አልነበሩም። (ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 13:31–33፤ 24:32, 33ን ተመልከት።) ምሳሌው ቀላል እንዲሆን ሰሚዎች ሊገባቸው በሚችል ቃል መጠቀም ያስፈልጋል። አንድ ምሳሌ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ከሆነ ትርፍ ጓዝ ነው። ተወው፤ አለዚያም ቀለል አድርገው።
8 ኢየሱስ ትልልቅ ነገሮችን ለመግለጽ በትንንሽ ነገሮች፣ ጠጠር ያሉ ነገሮችንም ለማስረዳት በቀላል ነገሮች ይጠቀም ነበር። አንድ ምሳሌ በዓይነ ሕሊና በቀላሉ ሊታይ የሚችል እጥር ምጥን ያለ መሆን አለበት። ስሜትን የሚነካና በቀላሉ የሚጨበጥ መሆን ይኖርበታል። እንደነዚህ ያሉ ምሳሌዎችን አድማጮች አሳስተው አይረዱም።
9 አንድ ምሳሌ ከጉዳዩ ጋር በሁሉም ዘርፎች የሚመሳሰል ከሆነ በጣም የተሻለ ነው። የምሳሌው አንዳንድ ገጽታዎች የማይገጥሙ ከሆኑ ምሳሌውን ጨርሶ አለመጠቀሙ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ከአድማጮች መካከል አንዳንዶቹ ከጉዳዩ ጋር በማይገጥሙት ክፍሎች ላይ ያተኩሩና ምሳሌው ውጤት አልባ ሊሆን ይችላል።
10, 11. በምሳሌው ለማስረዳት የተፈለገው ነጥብ ለምን ግልጽ መሆን እንዳለበት አስረዳ።
10 የምሳሌውን ቁም ነገር ግልጽ ማድረግ። ምሳሌው ምን ሊያስረዳ እንደታቀደ ግልጽ ካልተደረገ አንዳንዶች ቁም ነገሩ ሊገባቸው ቢችልም ብዙዎች ግን አይገባቸውም። ተናጋሪው ምሳሌው በአእምሮው ውስጥ ግልጽ ሆኖ እንዲታየውና ዓላማውንም እንዲያውቅ ያስፈልጋል። ምሳሌው እንዴት እንደሚሠራ በቀላል አነጋገር መግለጽ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 12:10–12ን ተመልከት።)
11 ምሳሌዎችን በተለያዩ መንገዶች መጠቀም ይቻላል። ከምሳሌው በፊት ወይም በኋላ በቀላል አነጋገር የቀረበውን አንድ መሠረታዊ ሥርዓት
ለማጠናከር ልንጠቀምበት እንችላለን። ምሳሌ የቀረበለት ጉዳይ የሚያስከትለውን ነገር ለማጠናከር መጠቀም ይቻላል። ወይም ደግሞ ምሳሌውና ጉዳዩ የሚመሳሰሉባቸውን ሁኔታዎች በመግለጽ ቁም ነገሩን ማስያዝ ይቻላል።12–14. አንድ ምሳሌ ተስማሚ መሆኑን ለመወሰን ምን ይረዳናል?
12 ትልልቅ ነጥቦችን ማጉላት። አንድ ምሳሌ ወደ አእምሮህ ስለመጣልህ ብቻ አትጠቀምበት። ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ንግግሩን አንድ በአንድ መርምር። ከዚያም እነዚያን ነጥቦች ለማጠናከር ምሳሌዎች ምረጥ። አነስተኛ ነጥቦችን ለማጉላት ኃይለኛ ምሳሌዎችን ካመጣህ አድማጮች ከዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ይልቅ ትንንሾቹን ነጥቦች ሊያስታውሱ ይችላሉ። (ማቴዎስ 18:21–35ን፤ 7:24–27ን ተመልከት።)
13 ምሳሌው ነጥቡን ሊጋርደው አይገባም። አድማጮች የሚያስታውሱት ምሳሌውን ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ምሳሌው ትዝ ሲላቸው ቁም ነገሩም አብሮ ትዝ ሊላቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ምሳሌው ከመጠን በላይ ደምቋል ማለት ነው።
14 ንግግር በምትዘጋጅበትና ምሳሌዎችን በምትመርጥበት ጊዜ እንዲጠብቁ ከተፈለጉት ነጥቦች አንጻር ምሳሌው የሚሰጠውን ጥቅም አመዛዝን። እነዚህን ነጥቦች ያጠናክራልን? ጐላ ብለው እንዲታዩ ያደርጋልን? ነጥቦቹ በቀላሉ የሚገቡና የሚታወሱ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋልን? ይህ ካልሆነ ምሳሌው ተስማሚ አይደለም ማለት ነው።
**********
15, 16. ምሳሌዎች ለአድማጮችህ ለምን ተስማሚ መሆን እንዳለባቸው አብራራ።
15 ምሳሌዎች ተስማሚ መሆን ያለባቸው ለትምህርቱ ብቻ አይደለም። ለአድማጮቹም ሁኔታ የሚስማሙ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ ጉዳይ በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ “ለአድማጮች የሚስማሙ ምሳሌዎች” ተብሎ ለብቻው ቀርቧል። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ስለፈጸመው ኃጢአት እንዲያርመው ናታን በተላከ ጊዜ ናታን ስለ አንድ ድሀና ያ ሰው ስለነበረችው አንዲት በግ የሚገልጽ ምሳሌ ለመጠቀም መረጠ። (2 ሳሙ. 12:1–6) ይህ ምሳሌ ስሜትን በማይጎዳ መንገድ የቀረበ ከመሆኑም በላይ ለዳዊት ሁኔታም ተስማሚ ነበር፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል ዳዊት እረኛ ነበር። ዳዊት ነጥቡ ወዲያው ገባው።
16 አብዛኞቹ አድማጮች በዕድሜ ሸምገል ያሉ ከሆኑ ወጣቶችን ብቻ በሚማርኩ ምሳሌዎች መጠቀም የለብህም። የኮሌጅ ተማሪዎችን አንድ ላይ የምታነጋግር ከሆነ ግን እንደነዚህ ያሉ ምሳሌዎች ለእነርሱ ፍጹም ተስማሚ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ምሳሌዎች ከሁለት ተቃራኒ አመለካከቶች አንጻር፤ ለምሳሌ ከሽማግሌዎችና ከወጣቶች ወይም ከወንዶችና ከሴቶች አመለካከት አንጻር ሊዘጋጁ ይችላሉ።
17–19. ምሳሌዎችህ አድማጮችህን የሚማርኩ እንዲሆኑ ከምን ነገሮች የተወሰዱ መሆን ይኖርባቸዋል?
17 ከተለመዱ ሁኔታዎች የተወሰዱ። በአጠገብህ ያሉ ነገሮችን ምሳሌ አድርገህ ብትጠቀምባቸው ለአድማጮችህ እንግዳ አይሆኑም። ኢየሱስ ልክ እንደዚሁ ያደርግ ነበር። በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሴት የራሱን ሕይወት ሰጪ ባሕርያት ከውኃው ጋር አመሳስሎላታል። ብርቅ ወይም ልዩ በሆኑ ነገሮች ሳይሆን በሕይወት ውስጥ ባሉ ትንንሽ ነገሮች ይጠቀም ነበር።
የኢየሱስ ምሳሌዎች በአድማጮቹ አእምሮ ውስጥ በቀላሉ መልዕክት ያስተላልፉ ነበር። ወይም በራሳቸው ሕይወት በግል ያጋጠማቸውን ነገር ወዲያው ያስታውሷቸው ነበር። ኢየሱስ ምሳሌዎችን በደንብ ለማስተማር ተጠቅሞባቸዋል።18 ዛሬም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። የቤት እመቤቶች ስለ ንግዱ ዓለም የሚያውቁት ነገር ይኖር ይሆናል። ቢሆንም በዕለታዊ ኑሮ የሚያጋጥሙ ነገሮችን፣ ልጆቻቸውን፣ የቤት ውስጥ ተግባሮቻቸውንና የሚገለገሉባቸውን እቃዎች የሚመለከቱ ምሳሌዎች ብትጠቀም የተሻለ ነው።
19 ባለህበት አካባቢ ብቻ በሚገኙ ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ምሳሌዎችም በጣም ውጤታማ ናቸው። በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ በደንብ የታወቁ በቅርብ የተፈጸሙ ነገሮች፤ ለምሳሌ በዜና ላይ የተገለጹ ነገሮችም ለዛ ያላቸው እስከሆኑ ድረስ ተስማሚ ናቸው።
20–22. በምሳሌዎች አጠቃቀም በኩል ልናስወግዳቸው የሚገቡን አንዳንድ ስህተቶች ምንድን ናቸው?
20 ለዛ ያለው። የምንጠቀምበት ማንኛውም ምሳሌ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ምሳሌዎች ከሥነ ምግባር አንጻር ሲታዩ “ከመስመር የወጡ” መሆን እንደሌለባቸው ግልጽ ነው። ሰሚዎች በሌላ መንገድ ሊረዷቸው የሚችሉ ከሆነ አሻሚ ትርጉም ያላቸውን ሐሳቦች አትናገር። ልትከተለው የምትችል አንድ ጥሩ መመሪያ እንዲህ ይላል:- ከተጠራጠርከው ተወው።
21 የምትጠቀምባቸው ምሳሌዎች በአድማጮችህ መካከል የሚገኝን ማንኛውንም ሰው በተለይም በቅርብ መሰብሰብ የጀመሩ አዲሶችን ሳያስፈልግ ቅር የሚያሰኙ መሆን የለባቸውም። በዚህ ምክንያት ውይይቱ በመሠረተ ትምህርታዊ ወይም አወዛጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እስካልሆነ ድረስ እነዚህን ነገሮች ማንሳት ጥሩ አይሆንም። ለምሳሌ ያህል የንግግርህ ዋና ነጥብ ደም ስለመውሰድ ወይም ለባንዲራ ሰላምታ ስለመስጠት እስካልሆነ ድረስ እነዚህን ነገሮች እንደ ምሳሌ አድርገህ አትጠቀምባቸውም። በዚህ ሊከፋ ወይም ሊሰናከል የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል። የንግግርህ ዋና ዓላማ ስለነዚህ ነገሮች ማብራራት ከሆነ ሌላ ነገር ነው። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ ምክንያቶችን እያቀረብህ አድማጮችህን ለማወያየትና እነርሱን ለማሳመን ጥሩ አጋጣሚ ይኖርሃል። ነገር ግን በምሳሌዎችህ ምክንያት አድማጮችህ የምታቀርብላቸውን በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶች አስቀድመው እንዲጠሉ በማድረግ የንግግርህ ዓላማ እንዲከሽፍ አትፍቀድ።
22 ስለዚህ ምሳሌዎችን በምትመርጥበት ጊዜ አመዛዛኝ ሁን። ምሳሌዎችህ ትክክል መሆናቸውን አረጋግጥ። ትክክል ሊሆኑ የሚችሉት ለትምህርቱም ይሁን ለአድማጮችህ የሚስማሙ ሲሆኑ ነው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]