በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርቱን ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብ

ትምህርቱን ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብ

ጥናት 35

ትምህርቱን ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብ

1–3. ትምህርታችንን ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብን መማራችን በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

1 ዛሬ ክርስቲያን አገልጋዮች በመሆን የምናከናውነው ሥራ በአብዛኛው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ያህል እውቀት ለሌላቸው ሰዎች የአምላክን ቃል መስበክንና ማስተማርን የሚመለከት ነው። አንዳንዶቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በፍጹም እጃቸው ውስጥ ገብቶ አያውቅም። ሌሎቹ ደግሞ መደርደሪያቸው ላይ እንዲሁ የተቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይኖራቸው ይሆናል። እንግዲህ ይህ ማለት እኛ ከምንነግራቸው ቃል ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ ከተፈለገ ትምህርታችንን ከሁኔታቸው ጋር አስማምተን ማቅረብ ይኖርብናል ማለት ነው። መልዕክቱን እንለውጠዋለን ማለት ሳይሆን እነርሱ ሊገባቸው በሚችል አነጋገር ለማቅረብ ልዩ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ማለት ነው። ትምህርቱን በዚህ መንገድ ለሰዎቹ እንደሚስማማ አድርገን ለማቅረብ የምናደርገው ሙከራ እኛ ራሳችን ትምህርቱ ምን ያህል እንደገባን የሚያሳይ ነው።

2 ለሁኔታው እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብ ሲባል አዲስ የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ለማስተናገድ ቅርጹን መለወጥ ማለት ነው። ነገሩን ከራሳችን ወይም ከሌላው ሰው ሁኔታ ጋር እንደሚጣጣም አድርጎ ማዘጋጀት ማለት ነው። ትምህርቱን ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርጎ ስለ ማቅረብ እዚህ ላይ የምናደርገው ውይይት በመስክ አገልግሎት የምናቀርበውን ይሁን ማንኛውንም ሌላ ንግግር ለተወሰኑ አድማጮች በተለይም በመስክ አገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ፍላጎት ያሳዩ አዲስ ሰዎች ቀላልና የሚገባ ማድረግ እንደሚያስፈልገን ጎላ ሊያደርግልን ይገባል። ስለዚህ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በዚህ ነጥብ ላይ በምትታረምበት ጊዜ አድማጮችህን ልክ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ምሥክርነት እንደምታገኛቸው ሰዎች አድርገህ መመልከት ይኖርብሃል።

3 እንዲህም ሲባል በዚህ ነጥብ ላይ በምትሠራበት ጊዜ የአቀራረብህ ሁኔታ ከበር ወደ በር የሚደረግ አገልግሎት መሆን አለበት ማለት አይደለም። ሁሉም ንግግሮች ለትምህርት ቤቱ በወጣው ወቅታዊ መመሪያ መሠረት ይቀርባሉ። ትምህርቱን በምንም መንገድ ብታቀርበው የምታብራራቸው ነጥቦችና የምትጠቀምበት አነጋገር በመስክ አገልግሎት ላይ ለምታገኘው ሰው የምትጠቀምበት ዓይነት መሆን አለበት ማለታችን ነው። አብዛኛውን ጊዜ ንግግር የምናቀርበው በመስክ አገልግሎት ላይ ስለሆነ ከዚህ የምናገኘው ልምድ በቀላል አነጋገር የመጠቀምን፤ ማለትም በመስክ አገልግሎት የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ባላቸው የመረዳት ደረጃ የመናገርን አስፈላጊነት ሊያስገነዝብህ ይገባል። ቀደም ሲል የተወሰደው ጥናት ቁጥር 21 ለዚህ የንግግር ባሕርይ አዘጋጅቶሃል። ሆኖም በዚህ ረገድ የጎላ ድክመት ስለሚታይና ነገሩ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ አሁን ነጥቡ ራሱን ችሎ ቀርቧል።

4, 5. ሌሎች ሰዎች በሚገቧቸው ቃላት ለምን መጠቀም እንዳለብን ግለጽ።

4 የአንዳንድ ቃላትን ፍቺ ግልጽ ማድረግ። አንዳንድ ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲያገለግሉ ወይም አዳዲስ ጥናቶችን ሲመሩ የሚጠቀሙባቸው ቃላት የዚህን የንግግር ባሕርይ አስፈላጊነት በጉልህ ያሳያሉ። ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያገኘነው ግንዛቤ ብዙ ሰዎች የማያውቋቸውን መነጋገሪያ ቃላት አሳውቆናል። እንደ “ቀሪዎች”፣ “ሌሎች በጎች” እና የመሳሰሉትን ቃላት እንጠቀማለን። እንደነዚህ በመሳሰሉት ቃላት እየተጠቀምን ብንናገር በመስክ አገልግሎት ለምናገኛቸው ሰዎች የሚያስተላልፉት ምንም ዓይነት ትርጉም የለም። እነዚህ ቃላት ለሰሚው ግልጽ እንዲሆኑ ከፈለግን ተመሳሳያቸውን ሌላ ቃል በመጠቀም ወይም እነርሱን በማብራራት ትርጉማቸውን ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። ሌላው ቀርቶ እንደ “አርማጌዶን” ወይም “የመንግሥቱ መቋቋም” የመሳሰሉትን መግለጫዎች ጠቅሰን መናገራችን ግልጽ ማብራሪያ ካልታከለባቸው የሚያስተላልፉት ምንም ትርጉም አይኖርም።

5 ምክር ሰጪህ ይህን የንግግር ዘርፍ አስመልክቶ ምክር ለመስጠት በሚያስብበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ምንም ትውውቅ የሌለው ሰው ነጥቡ ወይም ቃሉ ሊገባው ይችላልን? እያለ ራሱን ይጠይቃል። እንደነዚህ ባሉት ቲኦክራሲያዊ አነጋገሮች ፈጽሞ መጠቀምን ይከለክልሃል ማለት አይደለም። የምንነጋገርባቸው ቃላት ክፍል በመሆናቸው ፍላጎት ያሳዩ አዲሶችም ከእነርሱ ጋር እንዲተዋወቁ እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ እንደነዚህ በመሳሰሉት ቃላት ከተጠቀምህ ምክር ሰጪህ አስፈላጊውን ገለጻ ማከልህን ይከታተላል።

6–8. ንግግር በምናዘጋጅበት ጊዜ ተስማሚ ነጥቦችን በጥንቃቄ መምረጥ ያለብን ለምንድን ነው?

6 ተስማሚ ነጥቦችን መምረጥ። የምትጠቀምባቸውን ቃላት እንደ ሁኔታው እንደምትለዋውጥ ሁሉ በመስክ አገልግሎት ላይ ለማቅረብ የምትመርጣቸውንም ሐሳቦች እንዲሁ መለዋወጥ ያስፈልጋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ፍላጎት ካሳየ አዲስ ሰው ጋር ለመወያየት የማትመርጣቸው አንዳንድ ነገሮች ስለሚኖሩ ነው። እንዲህ በመሳሰሉት ጊዜያት የነጥቦቹ ምርጫ ለአንተው የተተወ ነው። በትምህርት ቤቱ ክፍል እንድታቀርብ በምትመደብበት ጊዜ ግን ልትሸፍነው የሚገባህ ትምህርት ቀደም ሲል ተመርጦ ተጠቁሞልሃል። መምረጥ የምትችለው በትምህርቱ ውስጥ ካሉት ሐሳቦች ብቻ ነው። እንግዲህ ምን ማድረግ አለብህ?

7 በመጀመሪያ ልትጠቀምባቸው የምትችል ነጥቦች የተወሰኑ ስለሆኑ ብዙ ተስማሚ ነጥቦችን ለማካተት የሚያስችል ትዕይንት ለንግግርህ መምረጥ አለብህ። ምክር ሰጪህ ምን ምን ነጥቦችን እንደምትመርጥና ከንግግርህ ሁኔታዎች ጋር እንዴት እንዳስማማሃቸው ለማየት ይፈልጋል። ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት በዚህኛው የንግግር ባሕርይ ላይ ስትሠራ በመስክ አገልግሎት የሚያጋጥሙ የተለያዩ ሁኔታዎች የተለያየ ዓይነት ትምህርት ማቅረብን እንደሚጠይቁ በማሳየት ላይ ስለሆንክ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድን ፍላጎት ያሳየ አዲስ ሰው ወደ ስብሰባ ለመጋበዝ የምትሰጠው ንግግርና ከበር ወደ በር በመሄድ ሰዎችን ስታነጋግር የምትጠቀምባቸው ነጥቦች አንድ ዓይነት አይሆኑም። እንግዲያው ክፍልህ ከአንድ የቤት ባለቤት ጋር በመወያየት የሚቀርብም ይሁን ወይም መደበኛ የመድረክ ንግግር፣ በምትናገራቸው ቃላትና ከተመደበው ጽሑፍ ውስጥ በምትመርጣቸው ነጥቦች አማካኝነት ትምህርቱን ለማን እያቀረብህ እንዳለ በውል መታየት ይኖርበታል።

8 ነጥቦቹ ተስማሚ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን ምክር ሰጪህ የንግግሩን ዓላማ ግምት ውስጥ ያስገባል። ከቤት ወደ ቤት በምትሄድበት ጊዜ ዓላማህ ሰዎችን ለማስተማርና ጥናታቸውን እንዲቀጥሉበት በውስጣቸው ፍላጎት ለመቀስቀስ ነው። ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ግብህ ፍላጎታቸውን በይበልጥ ለማቀጣጠልና ከተቻለም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ነው። ጥናቱ ካለቀ በኋላ አጠር ያለ ንግግር የሚደረግ ከሆነ ዓላማው ሰውዬው ወደ ስብሰባ እንዲመጣ፣ የመስክ አገልግሎት እንዲጀምር ወይም የመሳሰሉትን እንዲያደርግ ለማበረታታት ነው።

9, 10. የመረጥናቸው ነጥቦች ተስማሚ መሆናቸውን እንዴት ለማወቅ እንችላለን?

9 እርግጥ በአንዱ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍም አድማጮችህ የተለያዩ ከመሆናቸው የተነሳ የምትመርጣቸው ነጥቦች ሊለያዩ ይችላሉ። ስለዚህ ይህም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ክፍልህ በተመደበበት ጽሑፍ ውስጥ ላሰብከው ግብ ተስማሚ ያልሆኑ ነጥቦች ካሉ በንግግርህ ውስጥ መግባት የለባቸውም።

10 እንግዲህ ይህን ሁሉ ስትመለከት ንግግርህን ከማዘጋጀትህ በፊት ትዕይንቱን (ሴቲንግ) መምረጥ እንዳለብህ ግልጽ አይሆንልህምን? እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ምን ለማከናወን እፈልጋለሁ? ይህንንስ ግብ ለማከናወን የሚያስፈልጉት ነጥቦች ምንድን ናቸው? እነዚህ ነጥቦች ከንግግሩ ጋር እንዲስማሙ እንዴት ሆነው መስተካከል ይኖርባቸዋል? እነዚህን ጉዳዮች ከወሰንክ በኋላ ተገቢ ነጥቦችን ያለ ችግር ለመምረጥና ትምህርቱንም ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርገህ ለማቅረብ ትችላለህ።

11–13. ያቀረብነው ትምህርት ምን ተግባራዊ ጥቅም እንዳለው ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 የትምህርቱን ተግባራዊ ጠቀሜታ ጐላ አድርጎ ማሳየት። ትምህርቱ የሚሰጠውን ተግባራዊ ጥቅም ማጉላት ማለት ትምህርቱ ባለቤቱን እንደሚመለከት፣ እንደሚያስፈልገውና ሊሠራበት እንደሚችል ግልጽ በሆነና በማያሻማ መንገድ ማሳየት ማለት ነው። ገና ከንግግሩ መጀመሪያ አንሥቶ የቤቱ ባለቤት “ይህ እኔን የሚመለከት ትምህርት ነው” ለማለት መቻል አለበት። አድማጮችህ እንዲከታተሉህ ከተፈለገ ይህን የመሰለ ስሜት እንዲያድርባቸው ያስፈልጋል። ነገር ግን ያንን ትኩረት እስከ መጨረሻው ይዞ ለመቀጠል ትምህርቱ እስኪያልቅ ድረስ ሰውዬው ከራሱ ሁኔታ ጋር እያገናዘበ እንዲመለከተው ማድረግ ያስፈልጋል።

12 ለዚህም ከአድማጮች ጋር ግንኙነት ማድረግና አድማጮች የነጥቦቹን ትክክለኛነት እንዲያገናዝቡ መርዳት ብቻውን አይበቃም። አሁን ከዚያም አልፈህ በመሄድ ትምህርቱን ከባለቤቱ ሁኔታ ጋር ማዛመድ ይኖርብሃል። በመስክ አገልግሎት ስንሰማራ ዓላማችን በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት ለሰዎች ማስተማርና ወደ መዳን የሚያደርሰውን መንገድ እንዲያውቁት መርዳት ነው። ስለዚህ የቤቱ ባለቤት አንተ የምታቀርብለትን ትምህርት ቢያዳምጥና ቢሠራበት የሚያገኛቸውን ተጨባጭ ጥቅሞች በዘዴና በአክብሮት ማሳየት አለብህ።

13 ይኸኛው የንግግር ባሕርይ ወደ መጨረሻው አካባቢ የቀረበው በአስፈላጊነቱ የመጨረሻ ስለሆነ አይደለም። በጣም ወሳኝነት ያለው ነጥብ ነው፤ ስለሆነም ቸል ሊባል አይገባም። ይህንን ባሕርይ ለማዳበር ጣር፤ ምክንያቱም ለመስክ አገልግሎት በጣም አስፈላጊ ነው። የቤቱ ባለቤት አንተ የምትናገረው ነገር በሕይወቱ ውስጥ በሆነ መንገድ ሊጠቅመው እንደሚችል ለማየት ካልቻለ ትኩረቱን ለትንሽ ጊዜም እንኳን ይዞ ማቆየት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]