ትምህርት ቤቱን የመስክ አገልግሎትህን ለማሻሻል ተጠቀምበት
ጥናት 19
ትምህርት ቤቱን የመስክ አገልግሎትህን ለማሻሻል ተጠቀምበት
1. የተማሪ ንግግሮቻችንን በምንዘጋጅበት ጊዜ የትኛውን የትምህርት ቤቱን ዓላማ ማስታወስ ይኖርብናል?
1 ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማዎች አንዱ እኛን በመስክ አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን መርዳት ነው። የተሰጠህን ክፍል በምትዘጋጅበት ጊዜ ሁሉ ይህን ማስታወስ ይገባሃል። እውቀትን ለመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በመስክ አገልግሎት ላይ በምታከናውነው የስብከትና የማስተማር ሥራ ያንን እውቀት እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ለማወቅ መፈለግ ይኖርብሃል።
2. የተማሪ ንግግሮችን ምሥክርነት ለመስጠት በሚያስችል መንገድ እንዴት መለማመድ ይቻላል?
2 አንዳንዶች ክፍላቸውን በወዳጆቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸው፣ በአስተማሪዎቻቸው፣ በማያምኑ የቤተሰባቸው አባሎችና ሊያዳምጧቸው ፈቃደኞች በሆኑ በሌሎች ፊት በመለማመድ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይጠቀሙበታል። ይህን ማድረግ አንዳንድ ጥቅም አለው። ተማሪው የሚያዳምጡትን ሰዎች ስሜት ለመከታተል ስለሚችል ንግግሩን ለማሻሻል አንዳንድ ለውጥ ለማድረግ ይችላል። በተጨማሪም የሚያዳምጠው ሰው የሚቀርበውን ጠቃሚ ትምህርት በመመልከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው ፍላጎት ሊቀሰቀስ ይችላል። በአገልግሎት ትምህርት ቤት እንዲገኝ ለመጋበዝ የሚያስችል አጋጣሚም ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ወደ መንግሥት አዳራሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊመጡ የቻሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። በጃፓን የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር በአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም የተሰጣትን ክፍል ልዩ ጉብኝት ከምታደርግላት የቤተ ክርስቲያን አባል ፊት ተለማመደች። የንግግሯ መልእክት “የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን እንዲወጡ ታዘዋል” የሚል ነበር። ሴትዮዋ ፍላጎት አደረባትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማች።
3. በትምህርት ቤት የምንሰማውን በመስክ አገልግሎት እንድንጠቀም የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
3 ከመስክ አገልግሎት አንፃር ተመልከተው። ከአገልግሎት ትምህርት ቤቱ በጣም ብዙ ትምህርት ታገኛለህ። አብዛኛውን ትምህርት በቀጥታ በመስክ አገልግሎት ልትጠቀምበት ትችላለህ። በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለምናምንበት ምክንያት፣ መሠረተ ትምህርቶችን በሚመለከቱ ጥያቄዎች ላይ ስለተሰጡ መልሶች፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ፣ ለተወሰኑ ጥቅሶች ስለተሰጡ ማብራሪያዎች እና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ኑሮአችን ተግባራዊ ሊሆኑ ስለሚችሉባቸው መንገዶች ውይይት ይደረጋል። እነዚህን ትምህርቶች በመስክ አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችልህን አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት አድርግ። ስለ እነዚህ ጉዳዮች ሌላ ሰው እስኪጠይቅህ ድረስ መጠበቅ አያስፈልግህም። ለሁኔታው የሚስማማ ከሆነ አንተ ራስህ ጉዳዩን ለማንሣት ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ትምህርቱ
በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጽ ከማስቻሉም በላይ በአገልግሎትህ ከሚያጋጥምህ የተለያየ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም መልእክት ለማቅረብ እንድትችል ይረዳሃል።4. ትምህርት ቤቱ በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ረገድ እንዴት ሊረዳን ይችላል?
4 የሥራችን አንዱ ዐቢይ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ መጠቀም ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ አስፋፊዎች የፈለጓቸውን ጥቅሶች ፈጠን ብለው ማውጣት ይቸግራቸዋል። አንተስ? የሚቸግርህ ከሆነ ትምህርት ቤቱ በዚህ ረገድ ተጨባጭ መሻሻል እንድታሳይ ሊረዳህ ይችላል። እንዴት? እያንዳንዱ ተናጋሪ የሚጠቅሳቸውን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስህ እያወጣህ ተከታተል። ተናጋሪው ጥቅስ በሚያነብበት ጊዜ ሁሉ ጥቅሱን በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተህ አብረህ አንብብ። ጥቅሶችን ደጋግመህ ስታወጣ ጥቅሶቹን በደንብ ታውቃለህ፤ እንዲሁም ጥቅስ ማውጣት ትለምዳለህ። የሚያስፈልገው ልምምድ ነው። ልምምዱን ደግሞ በመስክ አገልግሎት በምትሰማራበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየሳምንቱ በሚደረገው የትምህርት ቤት ፕሮግራም በምትገኝበት ጊዜ ለማድረግ ትችላለህ። በተጨማሪም ተናጋሪዎች ክፍላቸውን ሲዘጋጁ ካደረጉት ጥናት ብዙ ጥቅም ለማግኘት ትችላለህ። ተናጋሪዎቹ የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች የተሰጧቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ጥሩ አድርገው የሚያብራሩ ናቸው። ተናጋሪዎቹን በምትከታተልበት ጊዜ በመስክ አገልግሎትህ ሊጠቅምህ እንደሚችል የምታስበውን ጥቅስ ዋነኛ ክፍል ልታሰምር ትችላለህ። በተጨማሪም ጥቅሶቹንና የንግግሩን ርዕስ ከመጽሐፍ ቅዱስህ ሽፋን ላይ ልትጽፍ ትችላለህ። በዚህ መንገድ በትምህርት ቤቱ የምትማረውን በመስክ አገልግሎትህ ለመጠቀም ቀላል ይሆንልሃል።
5, 6. ለንግግራችን ሊያጋጥም የሚችል ትዕይንት መጠቀም እንዴት ሊረዳን ይችላል?
5 ንግግርህን በምትዘጋጅበት ጊዜ ትዕይንትህን በጥንቃቄ ብትመርጥ ትምህርት ቤቱ ለመስክ አገልግሎትህ የሚሰጠውን ጥቅም ለማግኘት ትችላለህ። የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ በአገልግሎትህ በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ተጠቀም። ንግግርህ ከቤት ወደ ቤት ለሚደረግ አገልግሎት ወይም መደበኛ ላልሆነ ምሥክርነት የሚያመች ሊሆን ይችላል። አለበለዚያም በተመላልሶ መጠየቅ ጊዜ በሚደረግ ውይይት መልክ ቢቀርብ የተሻለ ሊሆን ይችላል። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚደረግበት ጊዜ በሚነሣ ነጥብ ላይ ያተኮረ ቢሆን የሚመረጥበት ጊዜም ይኖራል። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ትዕይንትህ ሊያጋጥም በሚችል ሁኔታ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ ጣር። አንዳንድ ጊዜ የቤቱ ባለቤት የምትናገረውን እንዲቃወም በማድረግ ትዕይንቱ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ሁኔታዎች ጋር በይበልጥ የሚመሳሰል እንዲሆን ለማድረግ ትችላለህ። ከዚያ በኋላ እንዲህ ያለውን የተቃውሞ ጥያቄ እንዴት መመለስ እንደሚቻል ልታሳይ ትችላለህ። ለመስክ አገልግሎት የሚያመቹ ንግግሮች ሁልጊዜ የግድ የተሳካ ውጤት በማስገኘት መደምደም አይኖርባቸውም። ሰዎች ፍላጎት ሳያሳዩ ሲቀሩ ምን ለማድረግ እንደሚቻል
ማሳየትም ጠቃሚ ነው።6 ረዳት ወይም ባለቤት እንድትሆን በምትመደብበት ጊዜም ለመስክ አገልግሎትህ የሚጠቅም ነገር ለማግኘት ትችላለህ። በዚህ አጋጣሚ የባለቤቶችን አስተሳሰብና ለምን የተቃውሞ አስተያየት እንደሰጡ ለመረዳት ሞክር። ባለቤቱን በትክክል ለመምሰል ጥረት ስታደርግና ተናጋሪ የሆነው ተማሪ የተነሣበትን ችግር እንዴት እንደሚወጣ ስትመለከት በአገልግሎትህ ወጤታማ እንድትሆን የሚያስችልህን ማሠልጠኛ ታገኛለህ።
7. የማያቋርጥ ዕድገት ለማሳየት እንድንችል በየሳምንቱ በአገልግሎታችን በምን ነጥቦች ላይ ለመሻሻል ጥረት ለማድረግ እንችላለን?
7 በየሳምንቱ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ንግግር ሲሰጥ ትምህርቱ ከቤት ወደ ቤትም ሆነ በሌሎቹ የአገልግሎት ዘርፎች ለማሻሻል እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል መርምረው። በዚያ ሳምንት በተብራራው ነጥብ ላይ አገልግሎትህን ለማሻሻል ትኩረት ብታደርግ ጥሩ አይደለምን? ለምሳሌ ያህል ለስብከታችን የተወሰነ መልእክት እንዲኖረን የሚያሳስብ ንግግር ተሰጥቶ ከነበረ በመስክ አገልግሎትህ ያቀረብከው ስብከት በእርግጥ የተወሰነ መልእክት የነበረው ስለመሆኑና ስላለመሆኑ አስብ። ከነበረውስ ይህን መልእክት በባለቤቱ አእምሮ ውስጥ ሊቀረጽ እስኪችል ድረስ ግልጽ አድርገህለታልን? ካላደረግህ በዚህ ሳምንት አስፈላጊውን መሻሻል ለማድረግ በዚህ ነጥብ ላይ አተኩር። በተጨማሪም ጥቅሶችን ስለማንበብና ከነጥቡ ጋር ስለማገናዘብ የሚገልጽ ትምህርት ትሰማለህ። ይህንን ንግግር በምታዳምጥበት ጊዜ ስለራስህ የጥቅስ አጠቃቀም መርምር። ለባለቤቱ ጥቅሱን ብቻ አንብበህ ሳታብራራለት ትቀራለህን? ጥቅሶቹን ከንግግሩ መልእክት ጋር የምታዛምደው እንዴት ነው? ከባለቤቱ ሁኔታ ጋር የምታያይዘውስ እንዴት ነው? እንዲህ ያለው ምርምር ጥቅሶችን የማንበብና ከነጥቡ ጋር የማገናዘብ ችሎታህን ያሻሽልልሃል። ንግግሩ የተሰጠው በምሳሌዎች አጠቃቀም ላይ ነውን? በምሳሌዎች አጠቃቀም ረገድ እንዴት ልትሻሻል ትችላለህ? ወይም ንግግሩ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ስለማስተማር የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። ይህን እንዴት ሥራ ላይ ለማዋል እንደምትችል ለመረዳት የራስህን የማስተማር ዘዴ መርምርና ትምህርቱን በዚያው ሳምንት ሥራ ላይ አውል። በዚህ መንገድ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምታገኘውን እውቀት በመስክ አገልግሎትህ ትጠቀምበታለህ።
8. በመስክ አገልግሎት በምንሰማራበት ጊዜ ራሳችን ለራሳችን እንዴት ምክር ለመስጠትና ለመጠቀም እንችላለን?
8 የራስህን አቀራረብ መርምር። በትምህርት ቤቱ ምክር ሲሰጥ አዘውትረህ ትሰማለህ። ከምክሮቹም የሚገኘውን ጥቅም ትመለከታለህ። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች አብሮህ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ምክር ላይሰጥህ ይችላል። ቢሆንም ራስህ ለራስህ ምክር የመስጠት ልማድ ለምን አይኖርህም? አንዱን ባለቤት ማነጋገር ጨርሰህ ወደሚቀጥለው በር በምትሄድበት ጊዜ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ምን ለማድረግ
እችል ነበር? ብለህ ራስህን ጠይቅ። አሁን ባገኘሁት እውቀት መሠረት ተመልሼ ይህን ሰው ለማነጋገር ብችል ኖሮ ምን የተለየ ዘዴ እጠቀም ነበር? እንዲህ ያለው ምርምር በዚያውም ቀን ቢሆን ጥሩ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፤ ምክንያቱም ካጋጠመህ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ በሌላ ቤት ሊያጋጥምህ ይችላል። በአገልግሎት ላይ እያለህ የመልእክትህን አቀራረብ የመመርመር ልማድ ቢኖርህ የማያቋርጥ ዕድገት ለማሳየት ትችላለህ። ከሌላ አስፋፊ ጋር በምታገለግልበት ጊዜም ጓደኛህ ሐሳብ እንዲሰጥህ መጠየቅ ትችላለህ።9, 10. እዚህ ላይ የምናገኘውን ትምህርት በመስክ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ቀላል እንዲሆንልን በቤት ውስጥ ምን ልምምድ ማድረግ እንችላለን?
9 የመልእክትህን አቀራረብ እንድታሻሽል የሚያስችልህ በጣም ጥሩ ዘዴ ከሌሎች ጋር አብሮ መለማመድና በአንድነት ሆኖ የአቀራረቡን ሁኔታ መመርመር ነው። ይህንንም ከቤተሰቦችህ አባሎች ወይም ከሌሎች የጉባኤ አባሎች ጋር ለማድረግ ትችላለህ። ባለቤት እንዲሆኑና ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ የተቃውሞ አስተያየቶችን እንዲያቀርቡ አድርግ። ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ መልሱን ካወቅህ መልስ ስጥ። ካላወቅከው ግን ቆም ብለህ አብረውህ የሚለማመዱት ሐሳብ እንዲሰጡህ አድርግ። ከዚያም የሰጡትን ሐሳብ በመጠቀም መልስ ስጥ። ከጨረስክ በኋላ አቀራረብህ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበረ አንድ ላይ ሆናችሁ ተወያዩበት። እንደነዚህ ያሉት በቤት የሚደረጉ ልምምዶች አቀራረብህን ለማሻሻል ከመርዳታቸውም በላይ ወደ መስክ ከመውጣትህ በፊት ስህተትህን እንድታርም ያስችሉሃል። በትምህርት ቤቱ የተማርካቸውን ቁም ነገሮች በመስክ አገልግሎትህ እንድትጠቀምባቸው ይረዱሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጎለመሱ ሰዎች “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቦና” እንዳላቸው ገልጿል። (ዕብ 5:14) ልቦናችንን ወይም የማስተዋል ኃይላችንን ከምናሠለጥንባቸው መንገዶች አንዱ የልምምድ ፕሮግራም ማድረግ ነው።
10 ይሖዋ እኛን ለማሠልጠን በልግስና ከሰጠን ብዙ የማሠልጠኛ ዝግጅቶች አንዱ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ነው። ከዚህ ትምህርት ቤት የምናገኘውን ትምህርት በትጋት ከተከታተልንና ሥራ ላይ ካዋልን ነቢዩ እንደተናገረው እንዲህ ለማለት እንችላለን:- “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፣ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል።” — ኢሳ. 50:4
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]