በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ መደምደሚያና የጊዜ አመዳደብ

ትክክለኛ መደምደሚያና የጊዜ አመዳደብ

ጥናት 36

ትክክለኛ መደምደሚያና የጊዜ አመዳደብ

1–3. መደምደሚያውን ከንግግርህ መልእክት ጋር ለማያያዝ የምትችለው እንዴት ነው?

1 ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ የሚታወሰው በመጨረሻ የተነገረው ቃል ነው። ስለሆነም የንግግርህ መደምደሚያ በጥንቃቄ መዘጋጀት ያስፈልገዋል። አድማጮችህ እንዲያስታውሷቸው የምትፈልጋቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ሰብሰብ አድርጎ የሚያስጨብጥ፤ የንግግሩን መልእክት አእምሮ ላይ ለዘለቄታው የሚያስቀምጥ መሆን ይኖርበታል። ከንግግሩ አቀነባበርና አሰጣጥ የተነሳ መደምደሚያው አድማጮችን ለሥራ መቀስቀስ መቻል ይኖርበታል። በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ “ግቡን የሚመታ ትክክለኛ መደምደሚያ” ወደሚለው ነጥብ ስትደርስ ትኩረት እንድትሰጠው አጥብቀን የምናሳስብህ ለዚህ ጉዳይ ነው።

2 ከንግግሩ መልዕክት ጋር በቀጥታ የተያያዘ መደምደሚያ። መደምደሚያውን ከንግግሩ መልእክት ጋር እንዴት ማያያዝ እንደምትችል አንዳንድ ሐሳቦችን ለማግኘት ጥናት ቁጥር 27 ላይ የቀረበውን ትምህርት እንደገና እንድትከልስ ሐሳብ እናቀርባለን። ምንም እንኳን አንዳንድ ተማሪዎች፣ በተለይም አዲስ ተማሪዎች የንግግሩን መልዕክት በቀጥታ መናገሩን የሚረዳ ሆኖ ቢያገኙትም መደምደሚያህ የግድ በዚህ መልክ መቅረብ አያስፈልገውም። ሆኖም የንግግሩን መልእክት የሚያስታውስ መሆን ይኖርበታል። ከዚያም በዚያ መልእክት መሠረት አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሳይ።

3 መደምደሚያው ከመልእክቱ ጋር በቀጥታ ካልተያያዘ ትምህርቱ የተሟላ አይሆንም፤ ነጥቦቹም በደንብ አይቋጩም። ሌላው ቀርቶ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች እንደገና አንድ በአንድ በመዘርዘር የትምህርቱን ይዘት አጠር ባለ መልኩ በቀጥታ ብታቀርብም በመጨረሻው ላይ የንግግሩን መልእክት ለመግለጽ አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር ለማከል እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም።

4–9. መደምደሚያህ አድማጮችህ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሊያሳያቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

4 መደምደሚያው አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያሳያል። ንግግር የምትሰጥበት ዓላማ አድማጮችህ አንድ ዓይነት ርምጃ እንዲወስዱ ለመቀስቀስ ወይም አንድ ዓይነት አመለካከት እንዲቀበሉ ለማሳመን ስለሆነ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ የሚቀርቡት ሐሳቦች እነዚያን ነጥቦች ማስጨበጥ አለባቸው። እንግዲያው የመደምደሚያው ዋነኛ ዓላማ አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማሳየትና ያንን እንዲያደርጉ ማበረታታት ነው።

5 በዚህ ምክንያት መደምደሚያው የንግግርህን ዓላማ በግልጽ ከማስቀመጡም በተጨማሪ ለአድማጮችህ ያለህን አሳቢነት፣ በውስጥህ ያለውን ጽኑ እምነትና ለተግባር የሚያበቃ ኃይለኛ ቅስቀሳ ያካተተ መሆን ይኖርበታል። ብዙ ጊዜ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች ለመደምደሚያው ኃይል የሚሰጡ ሆነው ታገኛቸዋለህ። የዓረፍተ ነገሮችህ አዘገጃጀት ምንም ዓይነት ይሁን ለእርምጃ የሚያበቁ ጠንካራ ምክንያቶች መቅረብ አለባቸው። ይህን ዓይነት እርምጃ መውሰዱ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ጭምር መጠቀስ ይኖርባቸዋል።

6 መደምደሚያው በንግግሩ ውስጥ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ መምጣት አለበት። ይህም በመሆኑ በመደምደሚያው ላይ የምትናገራቸው ነገሮች ሁሉ በንግግሩ ሐተታ ላይ ቀደም ሲል የተገለጹትን ጉዳዮች አድማጮችህ እንዲሠሩባቸው ለመቀስቀስ የታቀዱ መሆን አለባቸው። መደምደሚያህ አድማጮችህ በንግግሩ በተሸፈኑት ቁም ነገሮች መሠረት እርምጃ ለመውሰድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ ማድረግና ማሳሰቢያውን በድጋሚ ማጠናከር አለበት። ይህን ለማድረግ የሚገፋፉት በተለይ መደምደሚያህ ኃይል ካለው ነው።

7 ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ላይ የሚቀርቡት መደምደሚያዎች ብዙ ጊዜ ደከም ያሉ ናቸው። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ባለቤቱ ምን እንዲያደርግ እንደምንጠብቅበት ቁርጥ ባለ መንገድ ሳናሳየው ስንቀር ነው። ለምሳሌ ጽሑፎቻችንን እንዲወስድ፣ ተመልሰን መምጣታችንን እንዲቀበል ወይም ተመሳሳይ ነገሮችን እንዲያደርግ በግልጽ ካላሳየነው መደምደሚያችን ደካማ ይሆናል።

8 በትምህርት ቤቱ ላይ የሚቀርቡት መደምደሚያዎችም ነጥቦቹን በድጋሚ በመዘርዘር ብቻ በማጠቃለያ መልክ የሚቀርቡና አድማጮችን ለአንድ ዓይነት እርምጃ የሚያነሳሱ ከሆነ ደካማ መደምደሚያዎች ናቸው። በትምህርቱ መሠረት አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ወይም ትምህርቱ በሆነ መንገድ ለአድማጮች የሚሰጠው ጥቅም መገለጽ ይኖርበታል።

9 አንዳንድ ተናጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት በሚያስተላልፍ አንድ ንግግር ላይ የቀረቡትን ቁልፍ ጥቅሶችና የንግግሩን መልእክት መሠረት በማድረግ ንግግሩን መደምደሙ በጣም የሚረዳ ሆኖ አግኝተውታል። ልክ ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ እንደምታደርገው በንግግሩ ውስጥ በተሠራባቸው ጥቂት ጥቅሶች ተጠቅመህ ንግግሩን በዚህ መንገድ ጠቅለል ባለ መልኩ ለአድማጮች ስታቀርብ የንግግሩን ፍሬ ሐሳብ ግልጽ ከማድረግህም ሌላ አድማጮች የንግግሩን ጎላ ያሉ ገጽታዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚወያዩበት ጊዜ ሊጠቅሷቸው የሚችሉትን ነጥቦች ትሰጣቸዋለህ። የመደምደሚያው ዋና ዓላማ ይኸው ነው። ይህ ዘዴ ትክክለኛ ከመሆኑም ሌላ ያንን ዓላማ በማሳካት በኩል ግቡን የሚመታ ነው።

**********

10–14. የመደምደሚያው ርዝማኔ እንዴት መሆን እንዳለበት ያሉህን ሐሳቦች ግለጽ።

10 ልከኛ መደምደሚያ። የመደምደሚያህ ርዝመት በሰዓት መለካት የለበትም። እርግጥ ብዙ ጊዜ እንደዚያ ሲደረግ ይታያል። አንድ መደምደሚያ ግቡን የሚመታ ወይም የታቀደለትን ዓላማ የሚያሳካ ከሆነ መጠኑ ልከኛ ነው። ስለዚህ ርዝመቱ ትክክለኛ መሆን አለመሆኑ የሚወሰነው በውጤቶቹ ነው። በንግግር ምክር መስጫ ቅጽ ላይ ያለውን “ልከኛ መደምደሚያ” የሚለውን የንግግር ባሕርይ ለማሻሻል በምትጥርበት ጊዜ ምክር ሰጪህ የሚከታተለው ይህንን ይሆናል።

11 ከትምህርቱ ሐተታ ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ መደምደሚያዎችን ለማስተያየት በመክብብ 12:13, 14 ላይ የሚገኘውን የጠቅላላውን የመክብብ መጽሐፍ መደምደሚያ በማቴዎስ 7:24–27 ላይ ከሚገኘው የኢየሱስ የተራራ ስብከት መደምደሚያ ጋር አወዳድር። ሁለቱም መደምደሚያዎች በዓይነትም በርዝመትም ይለያያሉ። ቢሆንም ሁለቱም ግባቸውን የሚመቱ ናቸው።

12 መደምደሚያው ለአድማጮች ድንገተኛ ነገር መሆን የለበትም። የምትናገራቸው ቃላት ብቻ ሳይሆኑ አነጋገርህም ራሱ ወደ ንግግሩ ፍጻሜ መዳረስህን በግልጽ የሚጠቁም መሆን አለበት። የምትናገረውና የአነጋገርህ አወራረድ ንግግሩ ማለቁን ማመልከት ይኖርበታል። ንግግሩ ሳያስፈልግ መጓተት አይኖርበትም። ወደ መደምደሚያው ከገባህ በኋላ ንግግርህን ሰብሰብ አድርገህ ለማሰር ሳትችል ከቀረህና የአድማጮችን ስሜት ገና እንደያዝክ ከቆየህ ይህንን የንግግር ባሕርይ ለማሻሻል እንደገና ጥረት ማድረግ አለብህ፤ ምክንያቱም መደምደሚያው አሁንም ረጅም ነው።

13 ጀማሪ ተናጋሪ ከሆንክ ብዙውን ጊዜ መደምደሚያውን አንተ ከሚሰማህ በላይ አጠር ብታደርገው ጥሩ ነው። ቀላል፣ ቀጥተኛና አዎንታዊ አድርገው። መደምደሚያህ እልባት የሌለው አይሁን።

14 በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ርዕስ ቢኖርና ከንግግሮቹ አንዱን የምታቀርብ ብትሆን ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ቢኖርህ መደምደሚያህ ከሚቀጥለው ንግግር መግቢያ ጋር መያያዝ አለበት። ስለዚህ በይበልጥ አጠር ሊል ይችላል። ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ክፍል የንግግሩን ዓላማ የሚያሳካ መደምደሚያ ሊኖረው ይገባል። ይህ ከሆነ መደምደሚያው ልከኛ ነው ማለት ነው።

**********

15–18. የጊዜ አመዳደቡ በጥንቃቄ ካልታሰበበት ውጤቱ ምን ይሆናል?

15 የጊዜ አመዳደብ። የመደምደሚያው መጠን ልከኛ መሆኑ አስፈላጊ ከመሆኑም ሌላ ለእያንዳንዱ የንግግሩ ክፍል የሚደረገው የጊዜ አመዳደብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ምክንያት በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ “የጊዜ አመዳደብ” የሚል ራሱን የቻለ አርዕስት ገብቷል።

16 ትክክለኛ የጊዜ አመዳደብ አስፈላጊነቱ ዝቅ ተደርጎ መታየት የለበትም። ንግግሩ በሚገባ ተዘጋጅቶ ከሆነ የጊዜ አመዳደቡ ጉዳይም ታስቦበት መሆን አለበት። ነገር ግን ተናጋሪው በተጣበበው ጊዜ ውስጥ ብዙ ሐሳብ አጭቆ ለማቅረብ ሲሞክር ሰዓቱን ቢያሳልፍ ያሰበው ግብ ሳይሳካ ይቀራል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት አድማጮቹ መቁነጥነጥና ሰዓታቸውን ማየት ስለሚጀምሩና የሚናገረውን መከታተል ስለሚያቆሙ ነው። ትምህርቱ እንዴት ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል የሚገልጸውና አድማጮች አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ የሚቀሰቅሰው መደምደሚያ ሳይ ቀርብ ስለሚቀር የንግግሩ ዓላማ ሊኮላሽ ይችላል። መደምደሚያው ቢቀርብም እንኳን ተናጋሪው ሰዓቱን ስላሳለፈ ብዙዎች አድማጮች ምንም ጥቅም አያገኙበትም።

17 ተናጋሪው ሰዓቱን ሲያሳልፍ አድማጮች ብቻ ሳይሆኑ ራሱ ተናጋሪው ጭምር መንፈሱ ይረበሻል። ጊዜው እያለቀ እንዳለ ነገር ግን ብዙ ነጥቦች እንደቀሩት ሲመለከት በተጣበበው ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ነገር አግበስብሶ ይሰጥና ትምህርቱ ውጤት አልባ ይሆናል። ይህም የመንፈስ አለመረጋጋትን ያስከትላል። በሌላው በኩል ደግሞ ተናጋሪው ከተመደበው ሰዓት በፊት ንግግሩን በአብዛኛው ቢያገባድድና ለቀሪው ጊዜ በቂ ሐሳብ እንደሌለው ቢመለከት ነጥቦቹን እንደ ላስቲክ እየለጠጠ ለማራዘም ሲሞክር ትምህርቱ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ይሆናል። ብዙ ጊዜ ከመስመሩ ይወጣና የንግግሩ አንድ ወጥነት ይዛባል።

18 እውነት ነው፤ ሰዓቱ ሲያልቅ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ለተማሪው ምልክት ይሰጠዋል። ቢሆንም ንግግሩ አለማለቁ ለተማሪውም ይሁን ለአድማጮች ወሽመጥ የሚቆርጥ ነው። ተማሪው ያዘጋጀውን ትምህርት በሙሉ ለማቅረብ በቂ ፍላጎት እንዲኖረው ያስፈልጋል። አድማጮች መደምደሚያውን ሳይሰሙ ከቀሩ ልባቸውን ሰቅሎ እንደተዋቸው ሊሰማቸው ይችላል። ደጋግሞ በሰዓቱ የማይጨርስ ተማሪ ስለ ሌሎች ግድ እንደሌለው ወይም ዝግጅት እንደሚጎድለው ያሳያል።

19, 20. የጊዜ አመዳደብ በተለይም በአገልግሎት ስብሰባና በወረዳ ስብሰባ ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

19 በአንድ ፕሮግራም ውስጥ በርካታ ተናጋሪዎች ካሉ በተመደበው ሰዓት መጨረሱ በይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል በአገልግሎት ስብሰባ ላይ አምስት ክፍሎች ይኖሩ ይሆናል። እያንዳንዱ ተናጋሪ አንድ አንድ ደቂቃ ብቻ ቢያሳልፍ ጠቅላላው ስብሰባ ከተመደበለት ሰዓት አምስት ደቂቃ ያልፋል ማለት ነው። ግን እያንዳንዱ ተናጋሪ ያሳለፈው ጊዜ በጣም ትንሽ ነበር። በዚህ የተነሣ አንዳንዶች ወደ ቤታቸው ለመመለስ አውቶቡስ እንዳያመልጣቸው ሲሉ ስብሰባውን አቋርጠው ለመውጣት ይገደዳሉ። ወይም ከስብሰባው ወደ ቤት ሊወስዳቸው የመጣው የማያምን የትዳር ጓደኛም ብዙ ስላስጠበቁት መበሳጨት ሊጀምር ይችላል። በአጠቃላይ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም።

20 በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ርዕስ ቢኖርና አንዱ ተናጋሪ ሰዓቱ ከመድረሱ በፊት ንግግሩን ቢጨርስ አንዳንድ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በወረዳ ስብሰባ ላይ የግማሽ ሰዓት ንግግር የተሰጠው ወንድም ንግግሩን በሃያ ደቂቃ ሰጥቶ ቢቀመጥ ተከታዩ ተናጋሪ ወደ መድረኩ ለመውጣት ዝግጁ ሆኖ ካልቆየ ፕሮግራሙ ለትንሽ ጊዜ ሊቋረጥ ይችላል።

21–24. የጊዜ አመዳደብን በተመለከተ ስለሚፈጠሩት ችግሮችና ስለ መንስኤዎቻቸው ባጭሩ ግለጽ።

21 እርግጥ ከተመደበው ሰዓት ለማሳለፍ መሠረታዊ ከሆኑት ችግሮች አንዱ ብዙ ሐሳብ አዘጋጅቶ መምጣት ነው። ይህ ችግር ንግግሩ በሚዘጋጅበት ጊዜ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው። በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ የሰፈሩት ቀደም ሲል የተዘረዘሩትን ሌሎቹን የንግግር ማሻሻያ ነጥቦች በደንብ ሠርተህባቸው ከሆነ በሰዓቱ መጨረስ ከባድ አይሆንብህም። የንግግርህን ዋና ዋና ነጥቦች እንዴት እንደምትለይና ጥሩ አስተዋጽኦ እንዴት እንደምታዘጋጅ ቀደም ሲል ተምረህ ከሆነ የሰዓቱ አመዳደብ የሂደቱ ተፈጥሮአዊ ክፍል በመሆን አብሮ ይመጣል። የጊዜ አመዳደብ በምክር መስጫው ቅጽ ላይ የተጠቀሰው ወደ መጨረሻው አካባቢ ነው፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል በተብራሩት ሌሎች የንግግር ባሕርያት ላይ በጣም የተመካ ስለሆነ ነው።

22 በጊዜ አመዳደብ በኩል ብዙውን ጊዜ የሚታየው ችግር ሰዓት ማሳለፍ ነው። በደንብ የተዘጋጀ ተናጋሪ ብዙ ሐሳብ ይኖረዋል፤ ይሁን እንጂ ከተፈቀደለት ጊዜ እንዳያሳልፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

23 አዲስ ወይም ልምድ የሌላቸው ተናጋሪዎች ግን ሰዓቱ ከመድረሱ በፊት መጨረስ ይቀናቸዋል። የተመደበውን ሰዓት እንዴት ሙሉ በሙሉ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ቢያውቁ ጥሩ ነው። በመጀመሪያ ላይ ንግግራቸውን ልክ በተመደበው ሰዓት እንደሚያልቅ አድርጎ መመጠኑ ትንሽ ሊያስቸግራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ወደ ተመደበው ሰዓት የተቻላቸውን ያህል ለመጠጋት መጣር አለባቸው። ያም ሆነ ይህ ተማሪው ንግግሩን በደንብ ከተዘጋጀበትና የተሟላና አጥጋቢ ንግግር ከሰጠ ሰዓቱ ከመድረሱ በፊት ብዙ ቀደም ብሎ እስካላቆመ ድረስ በጊዜ አመዳደብ ረገድ ድክመት እንዳሳየ ተደርጎ አይቆጠርም።

24 ተናጋሪው በሰዓት አመዳደብ በኩል ድክመት እንዳሳየ ወይም እንዳላሳየ ለመወሰን ከሁሉ የተሻለው መንገድ የቀረበው ትምህርት አድማጮችን ምን ያህል እንደነካቸው መመልከት ነው። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ሰዓቱ አልቋል የሚል ምልክት ሲሰጥ ተማሪው የጀመረውን ዓረፍተ ነገር ለመጨረስ ነፃነት ሊሰማው ይገባል። በዚያ ዓረፍተ ነገር አማካኝነት ንግግሩን በጥሩ ሁኔታ ለማጠቃለል ከቻለ፤ ይኸውም አድማጮች የተሟላ ማብራሪያ እንዳገኙ ከተሰማቸው የጊዜ አመዳደቡ ደካማ እንደሆነ ተደርጎ መቆጠር የለበትም።

25–29. አንድ ሰው ንግግሩ ትክክለኛ የጊዜ አመዳደብ የተደረገለት መሆኑን ማረጋገጥ የሚችለው እንዴት ነው?

25 የንግግሩ የጊዜ አመዳደብ ትክክለኛ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? መሠረታዊ የሆነው ነገር ዝግጅት ነው። በንግግሩ ላይ የሚቀርቡትን ነጥቦች ብቻ ሳይሆን አቀራረቡንም ጭምር መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው። ንግግሩ እንዴት መቅረብ እንዳለበት በበቂ ሁኔታ ዝግጅት ከተደረገ የጊዜው አመዳደብ ልክ ይመጣል።

26 የንግግሩን አስተዋጽኦ ስታወጣ ዋና ዋና ነጥቦችን ግልጽ በሆነ መንገድ አመልክት። ከእያንዳንዱ ዋና ነጥብ በታች ሦስት አራት ንዑስ ነጥቦች ሊኖሩ ይችላሉ። እርግጥ አንዳንዶቹ ንዑስ ነጥቦች ከሌሎቹ ይበልጥ አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ። የትኞቹ ነጥቦች ለንግግሩ የግድ አስፈላጊ እንደሆኑ የትኞቹ ደግሞ ሊቀሩ እንደሚችሉ እወቃቸው። ከዚያ በኋላ ንግግሩን በምታቀርብበት ጊዜ ሰዓቱ እየደረሰ እንዳለ ከተመለከትክ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነጥቦች አቅርቦ ሁለተኛ ደረጃ ነጥቦችን ማስቀረቱ ቀላል ይሆናል።

27 በመስክ አገልግሎት ላይ ይህን የመሰለ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ያጋጥመናል። ወደ ሰዎች በር ስንሄድ ሰዎቹ ካልተቻኮሉና ሊያዳምጡን ፈቃደኞች ከሆኑ ሦስትና አራት ደቂቃ ያህል እናነጋግራቸዋለን። ይሁን እንጂ ያንኑ ንግግር አጠር አድርገን ለማቅረብም ዝግጁ ነን። አስፈላጊ ከሆነ ምናልባት በአንድ ወይም በሁለት ደቂቃ ንግግሩን ሰጥተን ለመጨረስ እንችላለን። ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቁልፍ ነጥብ ወይም ነጥቦች እና አስፈላጊዎቹ የድጋፍ ሐሳቦች በአእምሮአችን ውስጥ ግልጽ ሆነው መቀመጥ አለባቸው። በተጨማሪም ውይይቱን ማስፋፋት ከተፈለገ ልንጠቀምባቸው የምንችል አስፈላጊነታቸው ሁለተኛ ደረጃ የሆኑ ነጥቦችም አሉን። ሁኔታው በሚያስገድድበት ጊዜ ግን እነዚህን ነጥቦች እንተዋቸዋለን። በመድረክ ላይ ስንወጣ ይህንኑ ዘዴ ልንሠራበት እንችላለን።

28 ተናጋሪው የጠቅላላው ሰዓቱ አጋማሽ ላይ ሲደርስ ከንግግሩ ውስጥ ምን ያህሉን ሸፍኖ መሆን እንዳለበት ለማመልከት በአስተዋጽኦው ኅዳግ ላይ ምልክት ማድረጉ ብዙ ጊዜ ይረዳዋል። ንግግሩ ረዘም ያለ ከሆነም በአራት ሊከፋፍለው ይችላል። ከዚያም ንግግር እየሰጠ በአስተዋጽኦው ላይ ባሉት የጊዜ ማመልከቻዎች ላይ ሲደርስ ሰዓቱን በመመልከት ሁኔታውን ማረጋገጥ አለበት። ሰዓቱ እየተዳረሰ እንዳለ ከተመለከተ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ከመቆየትና መደምደሚያውን በጣም በማጨናነቅ ኃይሉን እንዲያጣ ከማድረግ ይልቅ ሁለተኛ ደረጃ ነጥቦችን ማስቀረት መጀመር አለበት። ነገር ግን ተናጋሪው አሁንም አሁንም ሰዓቱን የሚያይ ከሆነ ወይም ትኩረትን በጣም በሚስብ መንገድ ሰዓቱን ቢመለከት ወይም ለአድማጮች ሰዓቴ ስለ ደረሰ መጣደፍ አለብኝ ብሎ ከተናገረ ሐሳባቸውን ሊረብሸው ይችላል። ይህንን ተፈጥሮአዊ በሆነና አድማጮቹን በማይረብሽ መንገድ ማከናወን ይኖርበታል።

29 ለጠቅላላው ንግግር ትክክለኛ የጊዜ አመዳደብ ተደርጓል ለማለት የሚቻለው መግቢያው ልከኛ ከሆነ፣ እያንዳንዱ ቁልፍ ነጥብ የሚገባውን ያህል ከተብራራና ለመደምደሚያው በቂ ጊዜ ከተተወ ነው። ይህ ጉዳይ ሰዓትህ እያለቀ መሆኑን ስታይ ብቻ የምታስብበት አይደለም። ገና ከጅምሩ የጊዜህን አመዳደብ ከተከታተልክ ንግግሩ ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ይሸፈናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]